Saturday, February 4, 2012

ማኅበሩ አያንቀላፋም!

« ማኅበሩ አያንቀላፋም»

እንቅልፍ ለሰዎች የተሰጠ የሥጋ እረፍት ነው። «ቀን ለሰራዊት፣ሌሊት ለአራዊት»እንዲሉ! ዛሬ ግን ዓለማችን ቀንና ሌሊቱን አቀላቅላው ሰውም አራዊቱም ጉዞአቸው ባንድ ሆኗል። በሌሊት! ከነዚህ ቀኑንም ሌሊቱንም ከማያንቀላፋው ሀገርኛ ድርጅት አንዱ ራሱን በራሱ የቅዱሳን ማኅበር ነኝ የሚለው «ማኅበረ ቅዱሳን» በቁልምጫ ስሙ «ማቅ» የተባለው ድርጅት ነው። በቤተክርስቲያን ውስጥ ስፍራውና ድርሻው ለጊዜው ባይገባንም ረጅምና ስውር እጁ የሌለበት ቦታ የለም በሚባል ደረጃ ያለእረፍት ይንቀሳቀሳል። ለዚህም ነው የጽሁፋችንን ርእስ «ማኅበሩ አያንቀላፋም» ያልነው። አዎ! ማኅበረ ቅዱሳን አያንቀላፋም። የማያንቀላፋው ራሱን የቤተክርስቲያን ተጠሪ በማድረግና ሲኖዶሱ ባልሰጠው ውክልና በቤተክርስቲያኒቱ መዋቅር ውስጥ ስውር እጁን እንደአባጨጓሬ እያርመሰመሰ በመገኘቱ ነው። ማኅበሩ በሲኖዶስ መሃል ቁጭ ብሎ በስውር እጁ ጳጳስ ሆኖ ይወስናል፣ ያስወስናል፣ይከራከራል፣ይሞግታል። ለሲኖዶሱ አጀንዳ ይቀርጻል፣ የማይስማማውን ይጥላል፣ የፓትርያርኩ የራስ ህመም እስኪነሳ ያሳብዳል። ምክንያቱም ማኅበሩ ጳጳስ ስለሆነ አያንቀላፋም። በአምሳለ ጳጳስ «ማኅበረ ቅዱሳን ባይኖር ቤተክርስቲያን ምን ተስፋ አላት» ያሰኛል። በአድባራትና ገዳማትም መካከል ሳያንቀላፋ በአለቃነት ወይም በሀገረ ስብከት ደረጃ በሥራ አስኪያጅነት ወይም በመምሪያ ኃላፊነት ውስጥም ኅቡእ መንፈስ ሆኖ ይንቀሳቀሳል። የሰባኪዎችን፣የሰንበት ት/ቤቶችን ወይም የምእመናንን ማንነት ይቆጣጠራል፣ ይመረምራል፣ ይሰልላል። ማኅበረ ቅዱሳን አያንቀላፋምና እዚህም ቦታ አለ። ንግዱ ውስጥ! ይነግዳል፣ያስነግዳል። ግብርና ታክስ የማይከፍል የንግድ ተቋም ሆኖ በሆቴሎች፣ በሱቆች፣ በንዋያተ ቅድሳት መሸጫዎች፣በኢንኮርፖሬትድ ድርጅቶች፣ በህትመት፣ በሚዲያ ውጤቶች ውስጥ ሁሉ አለ።


ስለማያንቀላፋ ለቤተክርስቲያኒቱ ጥናት የሚያጠናላት እሱ ነው። ማኅበሩ እንደቀንድ አውጣ ባንቀላፋ ሲኖዶስ መካከል የተገኘ ንቁ በመሆኑ ሰዶ በማሳደድ ፖሊሳዊ ሥራ ውስጥም እጁ አለ። ግለሰቦችን በግለሰቦች በኩል ሙልጭ አድርጎ ያሰድባል።(ዘመድኩንን ልብ ይሏል?) ከኋላ ሆኖ ጠበቃ ያቆማል፣ዜና ይሰራል፣ ሲሞቀው ወሬውን ያራግባል።(በደጀ ሰላም) ይመሰክራል፣ ያስመሰክራል፣ ሲጠላ ይጥላል፣ ሲወድ ደግሞ ይወዳጃል።(ዘሪሁን ሙላቱን የመሰሉ) ኃጢአት ለእርሱ ዋጋ የሚኖረው ተመንዝሮ በሚያስገኘው ውጤት እንጂ ኃጢአትን ከመጸየፍ አንጻር አይደለም። እንደቤተክርስቲያኒቱ ሕግ ነውራሞች እስከተስማሙት ድረስ ለእርሱ ቅዱሳን ናቸው፣ የማይስማሙት ደግሞ ወደሲኦል መወርወር አለባቸው ብሎ ይዋጋቸዋል፣ ያዋጋቸዋል፣ ከፊት ቀድሞ ወጥመድ ያኖርባቸዋል። ከኋላ ሆኖ ጀርባቸው ላይ ጥላት ይቀባቸዋል። (አባ ፋኑኤልን ልብ ይሏል?) ማኅበሩ እጁ የሌለበት ቦታ የለም። መንፈሱ ሁሉ ገብ ነው። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን አያንቀላፋም። ሲኖዶስ በስም ጠቅሶ እነእገሌ ተሐድሶ ስለሆኑ ቢችሉ በንስሃ እንዲመለሱ፣ ፈቃደኛ ካልሆኑ ተወግዘው እንዲለዩ ሳይል ማኅበሩ ራሱ ስም ጠርቶ ያወግዛል፣ያባርራል፣ በር ይዘጋል፣ ደብዳቤ ይጽፋል፣ ያጽፋል። ስለማያንቀላፋ ሁሉ ቦታ መንፈሱ ይሰራል። በየመድረኩ ማስተማርና መስበክ የሚችሉት ፈቃድ የተሰጣቸው ብቻ መሆን እንዳለበት ሲኖዶስ ከተናገረ እሱ ቃሉን መንዝሮና ተርጉሞ እነእገሌ ይከልከሉ፣ እነእገሌም ይሰቀሉ ሲል ኢትዮጵያዊ ኢንተርፖል ሆኖ ይቆጣጠራል፣መግለጫ ይሰጣል፣ ያሰጣል። ኦርቶዶክሳዊነታቸው ባልተገፈፈና ውግዘት ባልተሰጠበት ወገን መታገዝ በራሱ ብቻውን በቂ ባለመሆኑ የማኅበሩ ፈቃድ በየትኛውም ቦታ የግድ መሆኑን ሰውር አዋጅ ያውጃል። ያለበለዚያ ሁሉም ቦታ በሚገኘው በስውር መንፈስ እጁ ያግዳል፣ ያሳግዳል።(የልብ ህሙም የእንዳለ ገብሬን ጉዳይ ልብ ይሏል?) ሌላው ቀርቶ ማኅበሩ ያለፍርድ ቤት ትእዛዝ ወይም ያለሲኖዶስ ሕጋዊ መግለጫ ራሱ መግለጫ ይሰጣል፣ ለፖሊስ፣ለደህንነት ይወነጅላል፣ያስወነጅላል። በግለሰቦች ነጻነት ውስጥ ጣልቃ ይገባል። በደብዳቤ ስም ጠርቶ መብት ይገፋል። ስም ያጠፋል። የመንቀሳቀስን መብት ለማገድ ይደክማል፣ ይወነጅላል። በሕግ ከሚያስጠይቁ የመብት ገፈፋ ተግባራቱ መካከል አንዱ አባ ድሜጥሮስ በተባለ ጳጳስ እጅ ማኅበሩ የጻፈውና ስም እየጠራ ከሀገር ያለመውጣት የውንጀላ ደብዳቤውን ከደጀሰላም ስውር አፉ አግኝተናልና ለእናንተም ሆነ መብታቸው ለተገፈፈ ወገኖች እንዲደርስ አውጥተነዋል።