Thursday, February 16, 2012

የምንገዛው ለማነው?


                        
1/ ነፍስ ሁሉ በበላይ ላሉት ባለ ስልጣኖች ይገዛ፡፡ ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ስልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለስልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፡፡
2. ስለዚህ ባለ ስልጣንን የሚቃወም እግዚአብሔርን ሥርዓት ይቃወማል፤የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ፡
3. ገዢዎች ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና፡፡ባለስልጣንን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙንአድርግ ከእርሱም ምስጋና ይሆንልሃል፤
4. ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና፡፡ በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቅምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቁጣውን ለማሳየት ክፉ አድራጊን የሚበቀል የእገዚአብሔር አገገልጋይ ነውና፡፡



5. ስለዚህ ስለቁጣው ብቻ አይደለም ነገር ግን ስለህሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው፡፡እነዚህ ትእዛዛት ምንን እንደሚያመለክቱ እና ምን ለማለት እንደፈለጉ ዘርዘር አድርገን ለዛሬ ብናየው ጠቃሚ ይመስለኛል፡፡አዎ! ጳውሎስ እንደ ፃፈው ወደ ሮሜ ሰዎች ምዕራፍ አስራ ሶስትን ብናይ ጥሩ ነው፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ ለእነማን ነው ወደ ሮም የጻፈው? የሚለውን ጥያቄ ስንጠይቅ በሮሜ 1፡7ላይ ተቀምጧል፡፡ 

እንዲህም ይላል ‹‹በእግዚአብሔር የተወደዳችሁ እና ቅዱሳን ልትሆኑ ለተጠራችሁት በሮማ ላላችሁት ሁሉ…››፡፡ ከዚህ መረዳት እንደምንችለው ጳውሎስ መልእክቱን የፃፈው ለአጠቃላዩ የሮማ ሕዝብ ሳይሆን ‹‹ቅዱስ ለመሆን ለተጠሩት›› ብቻ ነው፡፡ ጳውሎስ ስለምድራዊ መንግስት እያወራ ቢሆን ኖሮ መልእክቱ ለአጠቃላዩ የሮም ህዝብ በሙሉ በሆነ ነበር፡፡እርሱ ለምድራዊ ነገስታት እና መንግስታት ተገዙ ቢል ኖሮ ቄሳር ምንኛ በወደደው፡፡ ነገር ግን ቄሳር ሊያስገድለው አልፈለገምን? ለቄሳር ተገዙ ብሎ በሰበከ ሞት ይፈረድበት ነበር? እውንቱ ግን ሌላ ነው፡፡እንደውም ከአስራሁለቱ የክርስቶ ደቀመዛሙርት ጳውሎስን ጨምሮ አስራአንዱ የሞቱት በምድራዊ መንግስታት ተገድለው ነው፡፡ ጳውሎስ ይናገር የነበረው የቄሳርንም ሆነ የምድርን ነገስታት ስለምትቃወመዋ ‹‹እግዚአብሔር መንግስት›› ነው፡፡ ቄሳርም ጳውሎስን ለማስገደል የፈለገው የእግዚአብሔር መንግስት ለስልጣኑ ስለምታሰጋ ነው፡፡ሮሜ 13 የሚናገረው ‹‹ለምድራዊ መንግስታት ተገዙ!›› ብሎ ካልሆነ ታዲያ ስለምንድን ነው የሚያወራው? መጽሐፍ ቅዱስ መሪዎች የሚላቸውስ እነማንን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች ማየቱ አስፈላጊ ነው፡፡ዕብራውያን 13፡7 ‹‹የእግዚአብሔርን ቃል በመጀመሪያ የነገሩዋችሁን መሪዎቻችሁን አትርሱ›› ይላል፡፡ ይህን ሲልም መንፈሳዊ አባቶችን እንደ መሪ አድርጎ በመውሰድ ነው፡፡ ስለዚህም ነው ጳውሎስ መልእክቱን በእግዚአብሔር ላመኑት ብቻ የጻፈው፡፡ ምክንያቱም ስለምድራዊዎቹ ቢሆን ኖሮ በአጠቃላይ በሮም ላለው ሕዝብም ይጽፍ ነበርና ነው፡፡ እንዲያውም በዚሁ ምዕራፍ ሮሜ 13 ቁጥር 4 ‹‹መሪ መልካም የእግዚአብሔር አገልጋይ ነውና….›› ሲል በግልፅ አስቀምጦታል፡፡መችም እነ ጋዳፊ እና ሒትለር ወይም መንግስቱ ኃ/ማርያም አሊያም ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የእግዚአብሔር አገልጋዮች ነበሩ የሚል ይኖራል ብዬ አልጠብቅም፡፡ በታሪክ እስከምናውቀው ድረስ ምድራዊ መንግስታት ሮሜ 13ትን የክርስትያኖች ፀጥ ማሰኛ እና የእምብርክክ መግዣ መሳሪያ አድርገው ተጠቅመውበታል፡፡ አንድ ቡድን ወይም ግለሰብ በምርጫም ሆነ በአብዮት አሊያም በትጥቅ ትግል ስልጣን ስለጨበጠ እግዚአብሔር ሾሞታል ማለት አይደለም፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ በትንቢተ ሆሴዕ ምዕራፍ 8፡4 ላይ ‹‹ለራሳቸው ነገስታትን አነገሱ፥ ከእኔም ዘንድ አይደለም አለቆችንም አደረጉ…›› በማለት ይናገራል፡፡ በሌላ በኩል ሮሜ 13፡1 ደግሞ ‹‹….ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ስልጣን የለምና፤ ያሉትም ባለ ስልጣኖች በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው›› ይላል፡፡ በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች እርስ በእርስ መጣረዝ እንኳን ይህ ምዕራፍ ስለምድራዊ መሪዎች እንደማያወራ መገንዘብ እንችላለን፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ትክክለኛ የአምላክ ቃል ነው በሚለው ከተስማማን ሆሴዕ ላይ ‹‹ከእኔ ውጪ ነገስታትን አነገሱ›› ብሎ ሮሜ ላይ ደግሞ ‹‹ከእኔ ካልተገኘ በቀር ስልጣን
የለም›› እንደማይልም እንስማማለን ማለት ነው፡፡እነዚህ ሁለት ሓረጎች ደግሞ ሊታረቁ የሚችሉት ከሁለት አንዱ የተለየ ትርጉም ሲኖራቸው ነው፡ማሳረጊያውም ሆሴእ ስለምድራዊ መሪዎች ሮሜ ደግሞ ስለመንፈሳዊ መሪዎች መግለጹ ነው፡፡ሌላው ነገር ጳውሎስ ስለምድራዊ መሪዎች እያወራ ቢሆን ኖሮ በዚሁ ሮም ም.13 ቁ.2 ‹‹ባለ ስልጣንን የሚቃወም የእገዚአብሔርን ስርዓት ይቃወማል፤ የሚቃወሙትም በራሳቸው ላይ ፍርድን ያመጣሉ›› ብሎ እያስተማረ በ2ኛ ቆሮንጦስ 11፡32-33 ላይ ደግሞ ‹‹ደማስቆ… የሆነ የህዝብ ገዥ ሊይዘኝ እየወደደ የደማስቆ ሰዎችን ከተማ ያስጠብቅ ነበር፥ በቅጥሩም በቅርጫት አወረዱኝና ከእጁ አመለጥሁ›› ሲል ባለስልጣንን ባልተቃወመው ነበር፡፡ እናም ጳውሎስ ለምድራዊ መሪዎች ተገገዙ ቢል ኖሮ ከራሱ ህይወት ጋር በተጋጨ ነበር፡፡ ቀድሞ ነገር እርሱ የቄሳር ወዳጅ ነበረ ወይስ ጠላት? የሚለውን ብናቅ መልሱ ግልፅ እና አጭር ነው፡፡ ጳውሎስ የቄሳር ጠላት ነበር፡፡ በአንድ ጊዜ ለሁለት ጌቶች መገዛት እንደማይቻል ሁሉ ጳውሎስም በአንድ ጊዜ ለቄሳርም ለእግዚአብሔርም መገዛት አይችልምና፡፡ማቴዎስ ም.22 ቁ.3 ጀምሮ የአለውን ደግሞ እንመልከተው አንድ የሙሴ ህግ መምህር ክርስቶስን እንዲህ ሲል ጠየቀው ‹‹መምህር ሆይ ከሕግ ማናቸይቱ ትእዛዝ ታላቅ ናት? ኢየሱስም እንዲህ አለው፡- ጌታ አምላክህን በፍፁም ልብህ በፍፁም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ፡፡ ታላቂቱና ፊተኛይቱ ትእዛዝ ይህች ናት›› ሲል መለሰለት፡፡ ነገር ግን የሁሉም ምድራዊ መንግስታት አቋም ይህን የሚጻረር ነው፡፡ምድራዊ መንግስታት የሕጎች ሁሉ የበላይ ወይም Supreme law of the land’ ብለው የሚጠሩት እራሳቸው የጻፉትን ህገ መንግስት ነው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካን ሕገ መንግስት አንቀጽ ሁለት እና የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግስት አንቀፅ ዘጠኝ ንዑስ አንቀጽ አንድ ላይ የሕገ መንግስት የበላይነት በማያሻማ መልኩ ተቀምጧል፡፡ ኤፌ 1፡20-22 ግን ‹‹ክርስቶስንም…ከአለቅነትና ከስልጣንም ከኃይልም ከጌትነትም ሁሉ በላይና በዚህ ዓለም ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ሊመጣ ባለው ዓለም…›› ስልጣንን ሰጠው ይላል፡፡ እናም ማንን መቃወም እና ማንን አለመቃወም እንዳለብን ለይተን ማወቅ ይጠበቅብናል፡፡ የመጽሐፉ ቃል በጊዜያዊነት ለተቀመጥንባት ለአለም እና ለመንግስት አይደለም ተገዙ የሚለው፡፡እስካሁን ባለው ጽሁፍ ትክክለኛ ነው ብዬ የማምንበትን አመለካከት አስቀምጫለሁ፡፡
ምናልባት አሁንም ሃሳቡን የማይቀበሉ ካሉ ሮሜ 13 እነሱ እንደሚሉት ስለምድራዊ መንግስታት የሚናገር ቢሆን ትርጉሙ ምን ሊመስል እንደሚችል በቅርቡ በሊቢያ ካየነው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር አስቀምጨዋለሁ፡፡
1.ነፍስ ሁሉ ለጋዳፊ ይገዛ፡፡ከእግዚአብሔር ካልተገኘ በቀር ስልጣን የለምና፤ጋዳፊም በእግዚአብሔር የተሾሙ ናቸው፡፡
2. ስለዚህ ጋዳፊን የሚቃወም የእግዚአብሔርን ስርዓት ይቃወማል፤የሚቃወሟቸውም በራሳቸው ላይ ፍርድን ይቀበላሉ፡፡
3. ጋዳፊ ለክፉ አድራጊዎች እንጂ መልካም ለሚያደርጉ የሚያስፈሩ አይደሉምና፡፡እርሳቸውን እንዳትፈራ ትወዳለህን? መልካሙን አድርግ ከእርሳቸውም ምስጋና ይሆንልሃል፤
4. ለመልካም ነገር ለአንተ የእግዚአብሔር አገልጋይ ናቸውና፡፡ በከንቱ ግን ሰይፍ አይታጠቁምና ክፉ ብታደርግ ፍራ፤ ቁጣቸውን ለማሳየት ክፉ አድራጊውን የሚበቀሉ የእግዚአብሔር አገልጋይ ናቸውና፡፡
5. ስለዚህ ስለቁጣቸው ብቻ አይደለም :ነገር ግን ስለህሊና ደግሞ መገዛት ግድ ነው፡፡እናሳ! እግዚአብሔር ይህን ሊል ይችላል የሚል ግብዝ አለን በበኩሌ አለ ብዬ አላስብም፡፡ሊቢያውያን ሆ ብለው እንደ ጋዳፊን ያለ ጨካኝ እና አጭበርባሪ መሪን በማውረዳቸው እግዚአብሔር ደስተኛ ነው፡፡ ቢያንስ ህዝቡ የተወሰነ ጊዜ ሰላም እንደሚያገኝ ያውቃልና፡፡እነሆም የመጽሐፉ ቃል እና የምድራዊ መንግስትን ለይተን እናውቅ ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን፡፡ አሜን ይርዳን፡፡

ከፍትህ ጋዜጣ