Monday, February 20, 2012

«ብጹእ አቡነ አብሳዲ እኒህ ነበሩ»

 

«ብጹእ አቡነ አብሳዲ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ»

ብጹእ አቡነ አብሳዲ (በቀድሞ ስማቸው አባ ገ/ማርያም) ግንቦት 12 ቀን 1912 /ም በትግራይ ተወለዱ። እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በተወለዱበት ደብር  ከፊደል ቆጠራ ጀምሮ ንባብና እስከ ግብረ ዲቁና ያለውን ከዚያም ወደ ቀድሞው የኤርትራ ክ/ሀገር በአባ አብሳዲ ገዳም ገብተው ቅዳሴና ዜማ ቀጽለዋል። በዚያው በተማሩበት በአባ አብሳዲ ገዳም ማእረገ ምንኩስናን ተቀብለው እስከ 1942 /ም ቆይተው ሲያበቁ የግብጽን ገዳማት ለማየት ባደረባቸው ጉጉት ተነሳስተው የሱዳንን በረሃ በእግራቸው አቋርጠው ወደትልቁ የግብጽ ገዳም ገዳመ አስቄጥስ ሄደዋል። እዚያም የገዳሙ አባቶች በፈቀዱላቸው መሰረት ከገዳሙ አንድነት ገብተው እስከ 1944 /ም ቆይተዋል። እንደገና ኢየሩሳሌምን ተሳልሜ እመጣለሁ በማለት ከአንድ መንፈሳዊ ጓደኛቸው ጋር በመሆን የሲናን በረሃ በእግራቸው በማቋረጥ ወደኢየሩሳሌም አምርተው በዚያ ከሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳም ተቀላቅለዋል። ገዳሙን ያስተዳድሩ የነበሩት አቡነ ፊልጶስ ተቀብለው ከገዳሙ አንድነት ያስገቧቸው ሲሆን ከዚህ ዓለም በሞት እስከተለዩበት የካቲት 11/ 2004 /ም ድረስ ላለፉት 60 ዓመት በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም በተለያዩ ኃላፊነቶች ደከመኝ፣ ሰለቸኝ ሳይሉ ሲያገለግሉ ቆይተዋል። ብጹእ አቡነ አብሳዲ ከውጭ ቋንቋዎች እብራይስጥኛና አረብኛ ቋንቋዎችን በደንብ የሚያውቁ ሲሆን በዚህ የቋንቋ ችሎታቸው የኢትዮጵያ ገዳም ከግብጾች ጋር ባለው የይገባኛል ችግር እንዲያግዙና ማንኛውንም ጉዳይ መፍትሄ እንዲያመጡ ተመርጠው በገዳሙ አስተዳዳሪነት ለ27 ዓመታት አገልግለዋል። ብጹእነታቸው ለሰው አዛኝና ርኅሩህ፣ በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳም ተቆርቋሪና ጠበቃ ነበሩ።
ብጹእ አቡነ አብሳዲ በቀድሞ ስማቸው መጋቢ ገ/ማርያም ለኢትዮጵያ ገዳማት ያበረከቱት መንፈሳዊ ተጋድሎ ከታየ በኋላ በ1985 /ም በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠው በብጹእ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ በኤጲስ ቆጶስነት ማእረግ ተሹመው በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ረዳት ሊቀጳጳስ ተብለው ሲያገለግሉ ቆይተው የካቲት 11/2004 /ም ባደረባቸው ህመም በተወለዱ 92 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።
የብጹእነታቸውን ነፍስ ከቅዱሳን ጋር ያሳርፍልን! አሜን
ከመንፈሳዊ ልጃቸው ኃ/ማርያም- ግሪክ አቴንስ