Monday, February 13, 2012

የአቡነ ገብርኤል ተልዕኰ!


በሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት በተለይም በሀዋሳ ለአንድ ዓመት ከስምንት ወራት ያህል የቆየው ውዝግብ እስካሁን መቋጫ አለማግኘቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ ለውዝግቡ መባባስ የአቡነ ገብርኤል አንዱን አቅርቦ አንዱን የማራቅ አድሏዊ አመራር ትልቁን ድርሻ ሲወስድ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፣ የመንበረ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤትና ጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ተገቢውን እርምጃ ባለመውሰዳቸው የምዕመናኑ ሰቆቃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ከተለያዩ ምንጮች ለመረዳት ችለናል፡፡

አቡነ ገብርኤል በሁለንተናዊ የስብዕና ቀውስ ውስጥ ያሉ ሰው ናቸው ያሉ ታዛቢዎቻችን እንዳስረዱን፣ ሊቀጳጳሱ የሚናገሯቸውና የሚፈጽሟቸው ድርጊቶች የትላንቱ ከዛሬው፣ የዛሬው ከነገ የማይጣጣሙ ርስ በርሳቸው የሚምታቱ ናቸው ብለዋል፡፡ በተከበረውና በተቀደሰው ዐውደ ምሕረት ላይ አንድ ጊዜ በድያለሁ ይቅርታ ሲሉ፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ በግል መጽሔት ጭምር በአምሳለ ሥላሴ የተፈጠሩትን ምዕመናንንና ምዕመናትን ቀበሮዎች እያሉ የሚሳደቡ መሆናቸው ተገልጿል፡፡  ሰውየው በዚህ ብቻ ሳያበቁ በቅዱስ ሲኖዶስ ፊት ከቤተክርስቲያን የተለየ እና የተከፈለ ሕዝብ የለም ጥቂት ተሃድሶአውያን ናቸው እያሉ የ"ማኅበረ ቅዱሳን"ን የውሸት አሉባልታ ያስተጋባሉ፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ አዎን የተሰደደ ሕዝብ አለ፡፡ ዕድሉ ይሰጠኝና ሁለቱንም አስማማለሁ እያሉ ሲማጸኑ ይታያሉ፡፡

አቡነ ገብርኤል በግል ቀርቦ ለሚያነጋግራቸው አሁን ያለው የቤተክርስቲያን ቀውስ በዋነኛነት በ"ማኅበረ ቅዱሳን" የተንኮልና የጥፋት ዕቅድ እንደሚመራ፣ እንዲሁም አገልጋዮች ያለ ጥፋታቸው እንደሚሰደቡና በግላቸውም አገልጋዮቹን እንደሚያደንቋቸው ሲመሰክሩ፣ በአደባባይ ሲሆን ግን ከማኅበሩ ብሰው ሽንጣቸውን ገትረው ይራገማሉ፡፡ አቡነ ገብርኤል የማስመሰል ድርጊታቸው ከውስጥ ባህርያቸው የሚመነጭ ነው ያሉ እነዚህ ወገኖች፣ እንደማሳያ የሚሆነን በዕድሜ ያረጁ ሆነው ሳለ ወጣት ለመምሰል ጥቁር ሂና (የፀጉር ቀለም) መቀባታቸው ራሳቸውን በወጣትነት ውስጥ ደብቀው ከሁኔታዎች ጋር ለመመሳሰል መሞከራቸው ነው ብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያንንም የሚያጠቁት የዋህና ምንም የማያውቅ ቅን ክርስቲያን በመምሰል ነው ብለዋል፡፡

አቡነ ገብርኤል፣ ሀዋሳ ላይ የቅዱስ ገብርኤል፣ የቅድስት ሥላሴ እና የቅዱስ ሩፋኤል ሰንበት ት/ቤቶችንና ሕጋዊ ሰበካ ጉባዔዎችን ከቃለ ዐዋዲ ውጪ በማፍረስና ከቅጥር ግቢ በማባረር፣ መዋቅሩን በ"ማኅበረ ቅዱሳን"ና አሥር በማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎች ቁጥጥር ሥር አውለውታል፡፡ ዛሬ ቤተክርስቲያናቱን በግሉ የሚመራው አንድ ብርሃን የሚባል የ"ዩጎቪያ ዳንስ ምሽት ቤት" ባለቤት ነው ያሉ ታዛቢዎቻችን፣ ሊቀጳጳሱ ያለምንም ሐፍረት ሰውዬው ለሚያደርግላቸው የግል እንክብካቤ ሲሉ የሀገረ ስብከቱን ሥልጣን ጨምሮ ሁሉም ነገር በዳንስ ቤቱ ባለቤት ቁጥጥር ሥር እንዲውል መፍቀዳቸው ተገልጾልናል፡፡ የምሽት ዳንስ ቤቱ ከሀገሪቱ ልዩ ልዩ አካባቢዎች የሚመጡ ለጋ ሴት ልጆች አካላቸውን ለወሲብ የሚሸጡበትና ከወንድ ጋር ለአዳር ሲወጡ ለብርሃን ኮሚሽን እንዲከፍሉ የሚገደዱበት ምድራዊ ሲዖል ቤት ነው፡፡ እንግዲህ "ሊቀጳጳሱ" ይህንን ሰው ይዘው ነው ክርስቲያኖችን የሚያሳድዱት፡፡

ከብርሃን (የአባታቸው ስም ለጊዜው ይቆየን) በተጨማሪ፣ ብንያም፣ ታሪኩ፣ ክብሩ፣ አዳነ፣ ግርማ፣ዓለማየሁ፣ ሰይፉ፣ አንተነህ እና ሌሎችም ጥገኛ ነጋዴዎች ያለ ጨረታ ለቤተክርስቲያኗ ልዩ ልዩ የሕንፃ መሣሪያ ዕቃዎችን በማቅረብ ሀብት የሚያጋብሱ ሲሆን፣ ይህ የወሮበላ ቡድን በመቶ ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ ከቤተክርስቲያን እየወሰደ፣ በአምስት ሺህ የሚቆጠር ገንዘብ መልሶ ሲለግስ እያስጨበጨበ ሕዝቡን ሲያደናግር ኖሯል በማለት ገልጸውልናል፡፡ የዚህ ቡድን አባላት የሀብት መነሻቸው የመንግሥትና ልዩ ልዩ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች የዕቃ ግዥና የአስተዳደር የሥራ መደቦች ሲሆኑ ራሳቸውን ችለው ከወጡ በኋላ የግል የንግድ ድርጅቶቻቸው ሕልውናም በቤተክርስቲያን ሀብት ላይ የተመሠረተ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው ተብሏል፡፡ ምዕመናንንና ቤተክርስቲያንን እንደዚህ የሚያናውጠው ይህ የማፊያ ቡድን በከተማዋ ልዩ ልዩ አጥቢያዎች በተነሱ ብጥብጦች ከአቡነ በርተለሜዎስ ጊዜ አንስቶ የአሥራ አምስትና ሃያ ዓመታት ያህል የረጅም ጊዜ ልምድ ያለው መሆኑን እነዚሁ ምንጮቻችን ገልጸዋል፡፡ ቡድኑ በመንግሥት ልዩ ዕይታ ውስጥ እንዳይገባና እንዳይጠየቅ በመልካም ገጽታ ግንባታ የሚታገልላቸውና የሚከላከልላቸው እንዲሁም ባለው የሕወሀት-ኢህአዴግ አባልነትና ሥልጣን ሽፋን የተሳሳተ መረጃ ለመንግሥት እያቀበለ እንዳሻው እንዲፈነጭ የሚያደርገው ተከስተ የሚባል ግለሰብ መሆኑን ደርሰንበታል፡፡

አቡነ ገብርኤል ይህ ለበርካታ ዓመታት ያለማንም ጣልቃ ገብነት የቤተክርስቲያንን ሀብት ሲበጠቡጥ የኖረውን ቡድን ኦዲት አስደርገው ለፍርድ በማቅረብ ፈንታ አገልጋዮችንና ክርስቲያኖችን ማሳደድ ነው የተያያዙት፡፡ የዳንስ ቤት ባለቤቱን ንስሐ እንዲገባ ከመምከር ይልቅ፣ በእርሱ የግል ትዕዛዝ በየአጥቢያዎቹ የሚገኙ ቅን አገልጋይ ካህናትን ከሥራ ማባረርንና የካህናት ማሠልጠኛውን መዝጋት ነው የመረጡት፡፡

በአሁኑ ጊዜ በሀገረ ስብከቱ በተለይም በሀዋሳ ከተማ አጥቢያ ቤተክርስቲያናት ዐውደ ምሕረት ወንጌል እየተሰበከ አይደለም፡፡ ይልቁንም፣ ዐውደ ምሕረቱ የአቡነ ገብርኤልን የመልካም አስተዳደር ብልሹነት የሚቃወሙትን በመራገም ጊዜ እየባከነ መሆኑ ታውቋል፡፡ ካህናቱ የዕለት እንጀራቸውን እንዳያጡ አቡነ ገብርኤልን፣ "ዶክቶር"! ፣ "ዶክቶር"! እያሉ ከማወደስ በስተቀር እውነቱን መመስከር ተስኗቸዋል፡፡

አቡነ ገብርኤል ነባሮቹ የሰንበት ት/ቤት ጽ/ቤት አመራሮች ሕጋዊ ርክክብ ሳይፈጽሙና በሌሉበት እንደሌባ አድብተው ማሕተምና ቲተር ወስደው ጽ/ቤቱን ካሳሸጉ በኋላ፣ መልሰው በራሳቸው ጊዜ ራሳቸው ከፍተውታል፡፡ አሁን ደግሞ መልሰው መላልሰው በተቀደሰው ዐውደ ምሕረት ላይ ነባሮቹ የሰንበት ትምሕርት ቤት ወጣቶቹ ንዋየ ቅዱሳቱን ሠርቀውናል በማለት በአደባባይ እነ ብርሃን የሚነግሯቸውን ስድብ እንደ ድምፅ ማጉያ ያስተላልፋሉ፡፡  አቡነ ገብርኤል ንዋየ ቅዱሳኑ ተሠርቀው ሲወጡ ዘበኞቻቸው የማንን ጎፈሬ ሲያበጥሩ ነበር? ያሉት ታዛቢዎቻችን፣ አቡነ ገብርኤል አላዋጣቸውም፤  አልሆነላቸውም እንጂ የሰንበት ት/ቤቱ አመራሮችና አባላቱ ከያሉበት ታፍሰው ወደ እሥር ቤት እንዲወረወሩም ወትውተው ነበር፡፡ ሆኖም፣ ሕገወጦቹና ሌቦቹ ራሳቸው ሆነው ስለተገኙ ወደፊት መራመድ አልቻሉም፡፡  በርግጥ በርካታ መቋሚያዎች ከቁጥር ጎድለዋል፡፡ መቋሚያዎቹ ከቁጥር የጎደሉት የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ቡችሎች በንጹሐን ላይ ባደረሱት ጭፍጨፋ በመሰባበራቸው መሆኑ የታወቀ ሲሆን፣ የአቡነ ገብርኤል "ተዘርፈናል" ጩኸትም ለጋ ወጣቶችን ከገደለ በኋላ "የጥይት ዋጋ ክፈሉኝ" ከሚለው ከፋሽስቱ ደርግ አቋም ጋር የሚመሳሰል መሆኑ ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡

አቡነ ገብርኤል የተገነጠለው ሕዝብ የተሃድሶና የኑፋቄ አራማጅ እንደሆነ አስመስለው ያለምንም ሐፍረት በአደባባይ ይዋሻሉ፡፡ ሕዝቡ ከቅጥር ግቢው የወጣው የአቡነ ገብርኤል ሕገወጥ እና የመልካም አስተዳደር ብልሹነት አንገሽግሾት ይባስ ብሎም የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ዱላ፣ የኪራይ ሰብሳቢ ፖሊሶች ድብደባ፣ እሥራትና እንግልት አስመርሮት እንጂ፣ እናት ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖቱን ትታደስ ብሎ፣ ክዶ ወይም ለውጦ አይደለም፡፡ "ሊቀጳጳሱ ቀደም ሲል መጽሐፍ በማሳተም ጭምር የጀመሩትን የራሳቸውን ኑፋቄ ድሃ አደጎችን ከቤተክርስቲያን በማባረር እምነቱን የማዳከም ስልታዊ እርምጃቸውን ውስጥ ለውስጥ በማካሄድ፣ ራሳቸው በኑፋቄያቸው ይወድቋታል እንጂ እኛ ከሃይማኖታችን ንቅንቅ የማንል ጽኑ አማንያን ነን" በማለት ግፉአኑ አረጋግጠዋል፡፡

አቡነ ገብርኤል ግፉአኑን ለማጠልሸት ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች አንዱ እንቅስቃሴአቸው የተራ ወመኔና አፍላ ጎረምሶች ድርጊት አስመስሎ ዐውደ ምሕረት ላይ መውረግረግ ነው ያሉት ታዛቢዎቻችን፣ ለማስቀደስ በመጡ ምዕመናን ፊት "ልጆቻችሁን ተቆጣጠሩ!! በወንጌሉ እንደተጻፈው ከጉያችሁ ያወጧቸዋል"፤ እያሉ መደስኮር የተለመደ ተግባራቸው ሆኗል ብለዋል፡፡ "ሊቀጳጳሱና መሰሎቻቸው እንዳሉት እንቅስቃሴው የጎረምሶች ድርጊት ይሁን እሺ፣ ልጆቹን ዐዋቂዎቹ ይቆጧቸው፡፡ ከወጣቶቹ ጋር ያሉ አዛውንቶቹን፣ ቆራቢ አባት እናቶችን፣ አገልጋዮቹን፣ ዐዋቂዎቹን ማን ይቆጣቸው"? ሲሉ የእነ አቡነ ገብርኤል ቅስቀሳ ከከንቱ ፕሮፓጋንዳ ያለፈ ዋጋ የሚሰጠው አይደለም ሲሉ ግፉአኑ ምላሽ ይሰጣሉ፡፡

በአሁኑ ወቅት በሀዋሳ መንበረ ጵጵስና ቅዱስ ገብርኤል ቤተክርስቲያን እንደቀድሞው ከአፍ እስከ ገደፍ የሞላ አገልግሎትና የምዕመናን ብዛት አይታይም፡፡ የወንጌል ጉባዔና የመዝሙር አገልግሎት ተቋርጧል፡፡ አልፎ አልፎ ጉባዔ ቢዘጋጅም ያው የ"ማኅበረ ቅዱሳን" መልካም ገጽታ የሚገነባበትና ኦሪታዊ ትውፊት ብቻ የሚነገርበት ከመሆን የዘለለ አልሆነም፡፡ ከቅዳሴ በኋላ እነ አቡነ ገብርኤል ዐውደ ምሕረት ላይ ወጥተው የስድብ ቃላቶቻቸውን ከመወርወራቸው በፊት ምዕመናን ጥርግ ብለው ይወጣሉ፡፡ ተናጋሪም፣ አድማጭም አቡነ ገብርኤልና ለእንጀራዎቻቸው ያደሩ ጥቂት ካህናት፣ እንዲሁም የ"ማቅ" አባላት ብቻ ሆነው ይቀራሉ፡፡

እግዚአብሔር አቡነ ገብርኤልን በራሱ ጊዜ ከላያቸው ላይ እስኪያነሳላቸው ድረስ የሀዋሳ ምዕመናን ስቃይ በዚሁ መቀጠሉ አይቀሬ ነው፡፡ በአሥር ሺህ የሚቆጠሩ ምዕመናን ራሳቸውን ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር ራሳቸውን ለይተዋል፡፡ እዚህ ላይ ልብ በሉ፤ የተለዩት ከአቡነ ገብርኤል አስተዳደር እንጂ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አይደለም፡፡ አሁን ባሉበት ሁኔታ በቤተክርስቲያን አገልግሎት ረገድ ቀርቶባቸዋል የሚባል ነገር የለም፡፡ በግል ለሠላምና ፀጥታ ወደሚመቻቸው አጥቢያ ቤተክርስቲያን ሄደው ያስቀድሳሉ፤ ክቡር ሥጋውንና ደሙን ይቀበላሉ፡፡ በጋራ ደግሞ ተሰባስበው በአቡነ ገብርኤልና የ"ማኅበረ ቅዱሳን" የተገደበባቸውን  የወንጌል ጉባዔ በራሳቸው ዘርግተው የእግዚአብሔርን ቃል ይካፈላሉ፡፡ በሠርክ መርሐ ግብሮች የቤተክርስቲያኗ ሰንበት ት/ቤት አገልግሎት ክፍሉ መዝሙር ያቀርባል፣ የኪነ ጥበብ ክፍሉም ልዩ ልዩ ሥነጽሑፎችን፣ ጭውውቶችንና ድራማዎችን ያቀርባል፡፡ ጉባዔው በጋራ ፀሎት ይጀመራል፤ ይጠናቀቃል፡፡ የሱባዔና የምህላ ጸሎት መርሐ ግብሮችም እንዳስፈላጊነታቸው ይካሄዳሉ፡፡ ለጉባዔው አገልግሎት የድምፅ ማጉያና ከበሮ ተገዝቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ምዕመናን እና ምዕመናቱ በፅኑና በጠንካራ ክርስቲያናዊ መንፈስ ከውጭ በስደት ሆነው እግዚአብሔርን እያመሰገኑ፣ እየጾሙና እየጸለዩ እርሱ የሚሰጣቸውን መፍትሔ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡

አቡነ ገብርኤል እና ጀሌዎቻቸው ይህንን በስደት ላይ ያለውን ሕዝብ ከገጠር የተሰባሰበ፣ የነዳያን ስብስብ፣  ሃይማኖቱ የማይታወቅ፣ የተሃድሶ አቀንቃኞች፣ መናፍቃን እያለ ተመቸኝ ብሎ በቤተክርስቲያን ድምፅ ማጉያ ዘወትር ቢሳደብም፣ እግዚአብሔር ግን ግፉአኑን እያፀና እና እያበረታ ከእነርሱ ጋር መሆናቸውን እያሳየ ነው፡፡ አሳዳጃቸውና አሳሪያቸው የነበረው የመንግሥት የፀጥታ ኃላፊ በራሱ የሙስና ወጥመድ ተጠልፎ በሕግ ጥላ ሥር ወድቋል፡፡ ሌላም፣ ሌላም የትድግና ታሪክ እየሠራላቸው ነው፡፡ እሥራኤላውያንን ከግብፃውያን፣ ከአማሌቃውያንና መሰል ነገሥታት የጠበቀ አምላክ ዛሬም ግፉአኑን እየጠበቃቸው ነው፡፡

አቡነ ገብርኤል ጥምቀተ ባህር ላይ ለበዓል በተሰበሰበው ሕዝብ ፊት አቡነ ፋኑኤል የቤተክርስቲያኗ ይዞታ የነበረውን ጥምቀተ ባህር ለግል ባለሀብት እንደሸጡ አድርገው ነጭ ውሸት ዋሽተዋል፡፡ በዚህም "ማኅበረ ቅዱሳን" አቡነ ፋኑኤልን ለማጠልሸት ከሚጠቀምበት ማሳሳቻ ስልት አንዱን በመጠቀም ወራዳ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ከንቱ ልፋት ሆኖ ነው እንጂ፣ የአቡነ ገብርኤል ጥሩነት፣ በብፁዕ አቡነ ፋኑኤል መጥፎነት አይለካም፡፡ ሕዝብንም በዚህ ማሳሳት አይቻልም፡፡

ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል የቤተክርስቲያን ይዞታ ያልሆነ መሬት እንዴት ሸጡ ተብለው ሊወቀሱ ይችላሉ? ይህ የአቡነ ገብርኤል ውሸት ሁለት መሠረታዊ ግድፈቶች አሉት፡፡ አንደኛ መሬት አይሸጥም፣ አይለወጥም፡፡ ሁለተኛ ቤተክርስቲያን በይዞታ ካርታ የማታስተዳድረው መሬት እንደ ቤተክርስቲያን ይዞታ ተቆጥሮ ሊታወጅ ወይም ሊለፈፍ አይችልም፡፡ ከዚህ አንፃር አቡነ ገብርኤል ሁለት ኃላፊነቶችን ይወስዳሉ፡፡ አንደኛ በሕዝብ፣ በመንግሥትና በቤተክርስቲያን ፊት በይፋ የተናገሩትን በማስረጃ አስደግፈው ማብራራት፡፡ ሁለተኛ በካርታ የሚታወቅ የቤተክርስቲያን ይዞታ ካለ ሊሸጥ ስለማይቻል በአፋጣኝ እንዲያስመልሱ፡፡ እነዚህን ሁለት ጉዳዮች ካልፈጸሙ ሕዝብን፣ መንግሥትንና ቤተክርስቲያንን ውዥንብር ውስጥ በመክተት ለሚያደርሱት ጉዳት ሙሉ ኃላፊነትንና ተጠያቂነትን ይወስዳሉ፡፡
አቡነ ገብርኤል በቤተክርስቲያን ላይ ሁለንተናዊ ቀውስ በማስከተል ላይ ቢገኙም በውብስብ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሤራ ምክንያት ቅዱስ ሲኖዶስ ለሀዋሳ ምዕመናን ዕምባ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አልቻለም፡፡ በጥምት ወር 2003 ዓ.ም መጀመሪያ ላይ በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የተመራ አጣሪ ቡድን ወደ ሥፍራው የተላከ ቢሆንም ጉዳዩ ተራ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" እና የተስፋ ኪዳነ ምሕረት ማኅበራት ውዝግብ እንደሆነ ተቆጥሮ በቤተክርስቲያን መዋቅር ውስጥ ጣልቃ እንዳይገቡ የሚያሳስብ ውሳኔ ብቻ ተላለፈ፡፡ ብፁዕ አቡነ ፋኑኤል በአጣሪ ኮሚቴው ሪፖርት መሠረት ንጽሕናዬ ተረጋግጦ ማንኛውም ውሳኔ ይወሰን ብለው ቢጠይቁም አካሄዱ መስመሩን ስቶ ችግሩን አደፋፈነው፡፡

መሠረታዊ መፍትሔ ባለመሰጠቱ የተደፋፈነው ችግር ተባብሶ ቤተክርስቲያን በተኩስ ስትናወጥ እነ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል የሚገኙበት በብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የተመራ ሁለተኛ ቡድን እንደገና ወደ ሥፍራው ተላከ፡፡  በቡድኑ ሪፖርት መሠረት የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀሕሩያን ዓለምሸት ገ/ፃድቅ እንዲነሳ ከመወሰኑ በስተቀር በሌሎች ችግሮች ላይ የተቀመጠ ውሳኔ አልነበረም፡፡ አሁንም ችግሩ ተባብሶ በመቀጠሉ በቤተክርስቲያን ዕውቅና ይሁን አይሁን ባይታወቅም፣ ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ፣ ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፣ የቀደሞው የስብከተ ወንጌልና ሐዋርያዊ ተልዕኮ መምሪያ ኃላፊ አባ ኃይለ ማርያም የሚገኙበት በብፁዕ አቡነ ፊሊጶስ የተመራ ቡድን መጥቶ ሁለቱንም ወገኖች አነጋግሮ መጨረሻ ላይ "ሀዋሳ ሠላም ናት" ከማለት ውጪ የተነፈሰው አልነበረም፡፡ የቡድኑ ተልዕኮ ማስታረቅ ይሁን ማጣላት፣ መሰለል ይሁን መጎብኘት፣ መገምገም ይሁን ማጣራት እስከ ዛሬም ድረስ በግልፅ የሚታወቅ ነገር የለም፡፡

በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የሀዋሳ፣ የዲላ እና የአለታ ወንዶ ምዕመናን፣ አቡነ ገብርኤልና "ማኅበረ ቅዱሳን" ግንባር ፈጥረው በሀገረ ስብከቱ ላይ እያደረሱ ስላለው ጥፋት በጥቅምት 2004ቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ ለማመልከት ቢመጡም፣ "ማኅበረ ቅዱሳን" ራሱን የአዲስ አበባ ሰንበት ት/ቤቶች ሕብረት ብሎ የሚጠራ ወሮበላ ቡድን በማሠማራት የጉባዔውን ዋዜማ ሥርዓተ ጸሎት ሲያውክ ውሎ ሲያውክ በማምሸቱ በዕለቱ ሳይቀርብና ሳይደመጥ ቀረ፡፡ ይሁን እንጂ፣ ምዕመናኑ የሀገረ ስብከቱን ሁለንተናዊ ችግር በተሰባሰበ ፊርማ እና በተወካዮቻቸው አማካይነት በሌላ ፕሮግራም ማስረዳት ችለዋል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በአቡነ ገርኤል ላይ የቀረቡትን ማመልከቻዎች መርምሮ ውሳኔ ለመስጠት ቢሞክርም አቡነ ገብርኤል ሆን ብለው ከጉባዔው ለዚያች ቀን በመቅረትና ማንንም ሳያስፈቅዱ ወደ አሜሪካ ሄጃለሁ በማለታቸው፣  "እርሳቸው በሌሉበት ጉዳያቸው አይታይም" የሚል ማረሳሻ ውሳኔ ተወስኖላቸው፣ የሀዋሳ ምዕመናን ጥያቄ አሁንም ዕልባት ሳይሰጠው ቀረ፡፡  ይህ በ"ማኅበረ ቅዱሳን" አንዳንድ ሆድ-አደር ሊቃነጳጳሳት የተስተጓጎለው ውይይት በሌላ አስቸኳይ የምልዐተ ጉባዔ እንዲታይ የተደረገ ቢሆንም እንደእነ አቡነ ሕዝቅኤል ባሉ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ጥገኛ ሊቃነጳጳሳት አማካይነት:-
  1. በአቡነ ገብርኤል ጉዳይ ላይ የሚሰጠው ውሳኔ እስከ ግንቦት 2004ቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባዔ እንዲቆይ፣
  2. ችግሩን የሚያጣራ ኮሚቴ ወደ ሥፍራው እንዲላክ፣
  3. እስከዚያ ድረስ አቡነ ገብርኤል ምዕመናኑን በአባትና በልጅነት መንፈስ አቀራርበው ወደ አንድነት እንዲያመጡ የሚል የተውሸለሸለ ውሳኔ ተላለፈ፡፡
ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በፊት በላካቸው ሦስት ቡድኖች ሪፖርት ላይ ምንም ሳይሠራ ሌላ አራተኛ ቡድን ይላክ ማለቱ አሁንም ችግሩን በሥርዓት ለመፍታትና በ"ማኅበረ ቅዱሳን"ና በአቡነ ገብርኤል ላይ ቆራጥ ውሳኔ ከመወሰን ይልቅ ምዕመናን እንዳለቀሱ፣ ከእናት ቤተክርስቲያን እንደተለዩ ቢቀሩ የተሻለ እንደሚመርጥ ያሳየ ሲሆን፣ምዕመናንና ምዕመናት ሁሉም ከእግዚአብሔር ነው በሚል ዕምነት የእርሱን ማዳን በተስፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ አቡነ ገብርኤል በርቱ ቀጥሉበት የተባሉ ይመስል ተራና የወረደ ስድባቸውንና ዘለፋቸውን በማውረዱ ቀጠሉበት፡፡ በተቀደሰው የጥምቀት ብሔራዊ በዓል ላይ ስለበዓሉ ታላቅነት በማስተማር ፈንታ የዘረፋችሁትን የቤተክርስቲያኗን ንዋየ ቅዱሳት መልሱና፣ . . . ጳጳስ ለመሆን ብትፈልጉም አትችሉም፤ ቄስ ለመሆን ብትመኙም ቄስ መሆን አትችሉም . . . እያሉ በመሳደብ ከአንድነት ይልቅ ልዩነትን፣ ከማቀራረብ ይልቅ ማራራቅን እንደሚፈልጉ አሳይተዋል፡፡ በፖሊስ ታጅበው በፖሊስ መቀደስ መቻላቸውን እንደቁም ነገር በመቁጠር የፖሊስ ያለህ በማለት ከንቱ ውዳሴ በመዝራት የሠለቸ ንግግራቸውን አሁንም፣ አሁንም ይደግሙታል፡፡ ሊቀጳጳሱ ለቤተክርስቲያን ያሏት ዐይኖቿ ናቸው በማለት አሥር የማይሞሉ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎችን ማወደስ የዘወትር ተግባራቸው ከመሆናቸውም በላይ ያልተጻፈ በማንበብ ዋናውንና መሠረታዊውን ችግር በመደበቅ ራሳቸውን ብቻ ጻድቅ ማድረግ ልማዳቸው ሆኗል፡፡

ከዚህ አንፃር ምዕመናን ለሀዋሳና ለሀገረ ስብከቱ የሁለት ዓመት ሁለንተናዊ ቀውስ ሁለት መፍትሔዎችን ያስቀምጣሉ፡፡ አንደኛውና ቀዳሚው፣ አቡነ ገብርኤል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሀገረ ስብከቱን ለቀው እንዲሄዱ እና በምትካቸው ሁሉንም ሰው በእኩልነት የሚያዩ፣ ለቤተክርስቲያን ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጡና እውነትን የሚናገሩ ቅን አባት እንዲመደቡ፡፡ አቡነ ገብርኤል በጠቅላይ ቤተክህነት ውስጥ የአንድ መምሪያ ወይም ክፍል ኃላፊ ከመሆን በስተቀር በማናቸውም ሀገረ ስብከቶች እንዳይመደቡና ተመሳሳይ ችግር እንዳይፈጥሩ መከላከል፡፡ ሁለተኛው የሀዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ለልማት የተከፈተው አካውንት በገለልተኛና ነፃ ኦዲተሮች ኦዲት እንዲደረግ እና አሁን ያሉት አሥር የማይሞሉ በጥባጭ ኪራይ ሰብሳቢ ነጋዴዎችን ንጽሕናቸውን እንዲያረጋግጡ ማድረግ፡፡ ንጹሕ ስለማይሆኑ ወደ ሕግ ፊት በማቅረብ የቤተክርስቲያኗን ሠላምና ፀጥታ ወደነበረበት መመለስ፡፡ ከዚህ ውጪ አቡነ ገብርኤል በምንፍቅናቸው ቤተክርስቲያንን የሚያፈራርስ ተግባር እየፈጸሙና ክርስቲያኖችን እያሳደዱ እንዲሁም የሀገረ ስብከቱ መዋቅር በ"ማኅበረ ቅዱሳን" ፈላጭ ቆራጭነት ሥር ውሎ፣ በናይት ክለብ ባለቤት እየተመራ የተፈለገው ሠላም ሊመጣ አይችልም፡፡

እግዚአብሔር የቤተክርስቲያናችንን ሠላምና አንድነት ይጠብቅልን!!!
 
አሜን!!!
ከደጀ ሰላዓም ብሎግ ስፖት