Sunday, February 12, 2012

ያልገባኝ ነገር አለ!

ጥያቄ፦ እኔ ያልገባኝ ነገር አለ፤ እሱም ጌታ ፍቅር ነው እና ኃጢአት የሚሠራ ሥጋ ነው እና እሱ ራሱ ካልቅደሰኝ እንዴት ራሴ ልቀደስ እችላለሁኝ? ራሴ የምቀደስ ከሆነ ሕግ ይሆንብኛል እና እወድቃለሁ። አታድርግ ከሆነ ሰው በኋላ አይበርታም፡ ሰለዚህም ግራ መጋባት ላይ ነኝ።
 መልስ፦
ጸጋና ኃጢአት

በቅድሚያ አዲስ ኪዳን ስለ ሁለት ኃጢአቶች ይናገራል። አንደኛው ሳናውቅና ሳናስብ አንዳንዴ ስለምናደርገው ኃጢአቶች። እንደዚህ ያሉትን ኃጢአቶች ካደረግን፤ ንስሐ ገብተን ኃጢአታችንን እግዚአብሔር ይቅር እንደሚለን ተጽፎአል።

Quote:
1ኛ የዮሐንስ መልእክት 1
8 ኃጢአት የለብንም ብንል ራሳችንን እናስታለን፥ እውነትም በእኛ ውስጥ የለም።
9 በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።



ሁለተኛው አይነት ኃጢአት ደግሞ በኃጢአት ጸንቶ መኖር (ሮሜ 6፡1) ወይም የኃጢአት ባሪያ መሆን ነው። ማለትም አንድ ጊዜ በስህተት መሴሰን ሳይሆን ሴሰኛ መሆን ማለት ነው። አንድ ጊዜ በስህተት መስከር ሳይሆን ሰካራም መሆን ማለት ነው። አንድ ጊዜ በስህተት መስረቅ ሳይሆን ሌባ መሆን ማለት ነው። እንደዚህ የሚኖሩ የእግዚአብሔርን መንግስት እንደማይወርሱ ከአንዴም ሁለቴ በአዲስ ኪዳን ተጽፎአል (ስለዚህ ጉዳይ እዚህ ያንብቡ)

ከሕግ በታች ሳይሆን ከጸጋ በታች የሆነን እኛን ኃጢአት ባሪያ አድርጎ ሊገዛን እንደማይችል ተጽፎአል። ምክንያቱም ጸጋው ከኃጢአት ባርነት እንድንወጣ የሚያስችል ኃይል ነውና። ከጸጋ በታች የሆኑ የኃጢአት ባሪያ ሊሆኑ እንደማይችሉ በሮሜ ላይ እንዲህ ተጽፎአል፦
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች
6፥14 ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና።

ስለዚህ በጸጋው መኖር ማለት ኃጢአትን በመንፈስ ቅዱስ እርዳታ አሸንፎ የኃጢአት ባሪያ ሳይሆኑ መኖር ማለት ነው። በሕግ ያለ ሰው ከኃጢአት ባርነት ሊላቀቅ አይችልም። በጸጋ ያለ ሰው ደግሞ በተቃራኒው ኃጢአት ባሪያ አድርጎ አይገዛውም። ጸጋው ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት እንድንክድ ያስተምራልና
Quote:
ወደ ቲቶ
2፥12-13 ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤

ስለዚህ በጸጋ መኖር ማለት ኃጢአት ባሪያ እንዳያደርገን በሚያግዝ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መኖር ማለት ነው እንጂ በኃጢአት ውስጥ ጸንቶ መኖር ማለት አይደለም።

የኃጢአት ባሪያ ሆኖ የሚኖር ጸጋ የበዛለት ሳይሆን ከጸጋ የወጣ ሰው ነው። በህግ ወይም በሥጋ እየተመላለሰ ነው እንጂ በጸጋ እየተመላለሰ አይደለም። በጸጋ መመላለስ በመንፈስ ቅዱስ መመላለስ ማለት ነውና።

ፈተና (temptation)

ከጸጋ በታች የሆነ ሰው ግን አይፈተንም ማለት አይደለም። ሆኖም ፈተናዎች ሁሉ የሚመጡት በፈተናው እንድንወድቅ ሳይሆን ፈተናዎቹን ድል እንድንነሳቸውና እንድናሸንፋቸው ነው። ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ ተመርቶ 40 ቀን በበረሃ ሲፈተን፤ ፈተናው የመጣው ኢየሱስ ፈተናውን እንዲያሸንፈው ነው እንጂ እንዲወድቅበት እግዚአብሔር አስቦ አይደለም እንዲፈተን የፈቀደው።

ልናሸንፈው የማንችለው ፈተና ወደ እኛ አይመጣም። "ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው" ተብሎ ተጽፎአልና፦

Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
10፥13 ለሰው ሁሉ ከሚሆነው በቀር ምንም ፈተና አልደረሰባችሁም፤ ነገር ግን ከሚቻላችሁ መጠን ይልቅ ትፈተኑ (temptation) ዘንድ የማይፈቅድ እግዚአብሔር የታመነ ነው፥ ትታገሡም ዘንድ እንድትችሉ ከፈተናው ጋር መውጫውን ደግሞ ያደርግላችኋል።

ስለዚህ እግዚአብሔር በሰይጣን እንድንፈተን የሚፈቅደው ፈተናውን ድል እንድናደርግና እንድናሸንፍ ነው እንጂ እንድወድቅበትና የኃጢአት ባሪያ ሆነን እንድንኖር አይደለም። ኃጢአት ባሪያ አድርጎ አይገዛንም ምክንያቱም ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደለንምና።

አትፈታተን

ጸጋው ኃጢአትን ድል እንድናደርግ ይረዳናል ማለት ግን ታዲያ የእኛ ድርሻ የለም ማለት ነው? አይደለም። ወደ ኃጢአት ከሚያመሩ ነገሮች እንድንርቅ መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል። "ከዝሙት ሽሹ" ይላል መጽሐፍ ቅዱስ፤ እኛ ግን ገና ለገና በጸጋ ነን ብለን ራሳችንን ዝሙትን ወደሚገፋፉ ሁኔታዎች የምናስገባ ከሆነ ይህ እግዚአብሔርን መፈታተን ይባላል። ለምሳሌ ዝሙትን የሚያነሳሱ ፊልሞችንና መጽሔቶችን አንድ ሰው እያየ በሕግ አይደለም የምኖረው ጸጋው ካላስቻለኝ እኔ እንዴት እቻላለሁ ማለት አይችልም። ራሳችንን ወደ አደጋ እያስገባን ጸጋው ያውጣኝ ማለት እግዚአብሔርን መፈታተን ነው።

በማቴዎስ ወንጌል ላይ ኢየሱስ እግዚአብሔርን እንዲፈታተን ሰይጣን ፈልጎ ነበር። ገና ለገና እግዚአብሔር ያወጣኝ ብሎ ራሱን ወደታች እንዲወረውር፤ ሆኖም ጌታ ግን ይህ ራስን ወደ አደጋ እየጣሉ እግዚአብሔር ያውጣኝ ማለት እግዚአብሔርን መፈታተን እንደሆነ ነው የተናገረው።
Quote:
የማቴዎስ ወንጌል 4
6 መላእክቱን ስለ አንተ ያዝልሃል እግርህንም በድንጋይ ከቶ እንዳትሰናከል በእጃቸው ያነሡሃል ተብሎ ተጽፎአልና የእግዚአብሔር ልጅስ ከሆንህ፥ ወደ ታች ራስህን ወርውር አለው።
7 ኢየሱስም፦ ጌታን አምላክህን አትፈታተነው ተብሎ ደግሞ ተጽፎአል አለው።

ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ ከዝሙት እንድንሸሽ ይነግረናል። ሆኖም ግን አይ ጸጋው ነው የሚያውጣኝ እያልን በዝሙት ልንወድቅባቸው ወደምችላቸው ሁኔታዎች ውስጥ ራሳችንን ማስገባት እግዚአብሔርን መፈታተን እንጂ ፈጽሞ በጸጋ መኖር ማለት አይደለም።

መፍትሔ፦ በመንፈስ መመላለስ

አዲስ ኪዳን በኃጢአት እንዳንገዛ የሚሰጠን መፍትሔ በመንፈስ መመላለስ የሚባል መፍትሔ ነው።
Quote:
ወደ ገላትያ ሰዎች 5
16 ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ()
17 ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።
18 በመንፈስ ብትመሩ ግን ከሕግ በታች አይደላችሁም።

ከላይ ባለው ገላትያ 5፡16 ላይ ትክክለኛው የግሪኩ ሃሳብ የሚለውና በሁሉም የእንግሊዝኛ ትርጉሞችም እንደተተረጎመው፤ በመንፈስ ብትመላለሱ የሥጋን ምኞት አትፈጽሙ ነው የሚለው። በአማርኛው ትርጉም "ም" ስላልተጨመረች ትዕዛዝ ይመስላል። ትዕዛዝ ሳይሆን መፍትሔ ነው ጳውሎስ እየሰጠን ያለው። የሥጋን ምኞት ላለመፈጸም መፍትሔው በመንፈስ መመላለስ ነው እያለን ነው።
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች 8
12 እንግዲህ፥ ወንድሞች ሆይ፥ ዕዳ አለብን፥ እንደ ሥጋ ፈቃድ ግን እንኖር ዘንድ ለሥጋ አይደለም።
13 እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።

በጸጋ መኖር ማለት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል መኖር ማለት ነው። ስለዚህ የሥጋን ነገር እያሰብን በሥጋ ከመመላለስ የሰማዩንና የመንፈስን ነገር እያሰብንና በመንፈስ ቅዱስ እየተሞላን መመላለስ ማለት ነው።
Quote:
ወደ ሮሜ ሰዎች 8
5 እንደ ሥጋ ፈቃድ የሚኖሩ የሥጋን ነገር ያስባሉና፥ እንደ መንፈስ ፈቃድ የሚኖሩ ግን የመንፈስን ነገር ያስባሉ።
6 ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።
7 ስለ ሥጋ ማሰብ በእግዚአብሔር ዘንድ ጥል ነውና፤ ለእግዚአብሔር ሕግ አይገዛምና፥ መገዛትም ተስኖታል፤
8 በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።
9 እናንተ ግን የእግዚአብሔር መንፈስ በእናንተ ዘንድ ቢኖር፥ በመንፈስ እንጂ በሥጋ አይደላችሁም። የክርስቶስ መንፈስ የሌለው ከሆነ ግን ይኸው የእርሱ ወገን አይደለም።

በጸጋ መኖር በድል መኖር ማለት ነው። በመንፈስ ቅዱስ ኃይልና እርዳታ መኖር ማለት ነው። ኃጢአትን እምቢ እያልንና ድል እያደረግን በዚያ ፈንታ ግን ዕለት ዕለት በመንፈስ ቅዱስ እየተሞላን፣ አዕምሮአችንን በእግዚአብሔር ቃል እየሞላንና እያደስን የሰማዩን መንግስት እያሰብንና ጌታን እያገለገልን መኖር ማለት ነው።

በመንፈስ ብንመላለስ ማለትም እለት እለት በመንፈስ ቅዱስ ብንሞላ፤ አዕምሮአችንም ሁል ጊዜ የቃሉንና የሰማዩን ነገር ቢያስብ በጌታ አገልግሎትም ብንጠመድ፤ ከንቱ በሆነና በማይረባ በሥጋና በምድራው ነገር አዕምሮአችንና ሃሳባችን ባልተያዘ፤ ከጸጋም ወጥተን የኃጢአት ባሪያ ባልሆንን ነበር።
ከኢየሱስ.ኮም ድረ ገጽ