Wednesday, February 15, 2012

በኤርትራዊው አሸባሪ የተመራው የማኅበረ ቅዱሳን ቡድን!

ለዘማርያን የመዝሙር ግጥምና ዜማ በመቀመር የሚታወቀው ዲ/ን ጋሻዬ መላኩ ጥር 4 ቀን 2004 ዓ.ም ጋብቻውን  በሥርዓተ ተክሊል በአዲስ አበባ ደብረ ጽጌ ቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን ፈጸመ፡፡ (ምናልባት ዲ/ን ጋሻዬን ለማታውቁት በዘማሪት ዘርፌ ከበደ እውነተኛ ታሪክ ዙሪያ በሚያጠነጥነው የ"ፓራሜራ" ፊልም ላይ ከዘማሪ ዲ/ን ሀብታሙ ሽብሩ ጋር ሆኖ ግጥምና ዜማ ሲያስጠናት የሚታየው ነው)፡፡

በዲ/ን ጋሻዬ መላኩ ሥርዓተ ተክሊል ላይ ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ በርካታ የቤተክርስቲያናችን ሰባክያንና ዘማሪያን እንዲሁም ልዩ ልዩ አገልጋዮች የተገኙ ሲሆን እስከ ጥዋቱ 2፡30 የነበረው መርሐ ግብር የተረጋጋ እና የሰከነ እንደነበር ተገልጿል፡፡ ይሁን እንጂ፣ ሥጋ ባየበት እንደሚዞር ጆፌ አሞራ ከአገልጋዮች ሥር የማይጠፋው "ማኅበረ ቅዱሳን" ዝግጅቱን ለማደናቀፍ መሞከሩ አልቀረም፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" ያዘጋጀው ይህ የረባሽ ቡድን ሦስት መታወቂያዎችን ይዞ ሲንቀሳቀስ በካራማራ ወረዳ ፖሊስ የተያዘና ጉዳዩ በፍርድ ቤት በመታየት ላይ ያለ ተስፋዬ በሚባል ኤርትራዊ አሸባሪ ግለሰብ እና ሐጂ እና እንድዬ በሚባሉ ሁለት ረዳቶቹ እንደተመራ ታውቋል፡፡ ቁጥጥር በማይደረግበት በቤተክርስቲያን አንጡራ ሀብት ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" በወር እስከ 3500 (ሦስት ሺህ አምስት መቶ) የሚከፈላቸው እነዚህ ግለሰቦች ጥቅምት 11/2004 ዓ.ም በዲ/ን ዘማሪ ትዝታው ሳሙኤል ላይ ድብደባ የፈጸሙና በዘመድኩን በቀለ የክስ ሂደት ላይም በየችሎቱ እየተገኙ በአገልጋዮች ላይ የዛቻ እና የማስፈራራት ወንጀል የሚፈጽሙ መሆናቸው በተጨማሪ ታውቋል፡፡

እነዚህ ሦስት ግለሰቦች የተመደቡላቸውን ወደ ሰባ የሚሆኑ ወሮበሎች መርተው ወደ ተቀደሰው የቤተክርስቲያን ቅጥር ግቢ ገብተው ሁከት ለማሰነሳት የሞከሩ ሲሆን፣ በቅድሚያ መረጃ የደረሰው የፖሊስ ሠራዊት ደርሶ ሁከቱን በቁጥጥር ሥር ሊያውለው ችሏል፡፡ ይህ የወሮበላ ቡድን አገልጋዮችን በስም እየጠራ እነ እከሌ፣ እነ እከሌ ይውጡልኝ እያለ ላንቃው እስኪላቀቅ ቢጮኽም፣ በቤተክርስቲያን የሚካሄደው የዲ/ን ጋሻዬ መላኩ የጋብቻ ሥነ ሥርዓት መርሐ ግብር በስብከተ ወንጌል አዳራሹ በተሳካ ሁኔታ መካሄዱን በሥፍራው የነበሩ ታዳሚዎች ገልጸውልናል፡፡

በስብከተ ወንጌል አዳራሹ በነበረው አገልግሎት መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ደሳለኝ ተገኝቶ ለዕለቱ የሚገባ መንፈሳዊ መልዕክት ያስተላለፈ ሲሆን፣ መምህር አሰግህድ ሣህሉ፣ መምህር ተረፈ አበራ እና ሌሎችም አገልጋዮች መታደማቸው ተገልጿል፡፡ በዕለቱ መርሐ ግብር መሠረት ከመምህር ተረፈ ቀጥሎ ትምህርቱን ያቀረበው መጋቤ ሀዲስ በጋሻው ሲሆን፣ በዚሁ ትምህርቱ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ወደ ልጇ በማማለድ የእነ ዶኪማስን ጉድለት በማሟላት የአማላጅነቷ ሚስጥር የተገለጠበት እና በጌታ ዘንድም ጋብቻ ክቡር መሆኑ የተመሠከረበት ነው በማለት በመሳጭ ስብከቱ ምዕመናንና ምዕመናትን አገልግሏል፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን"፣  "በሃይማኖት ጉዳይ መፍረድ የአንተ ሥልጣን አይደለም፤ አርፈህ ተቀመጥ" ቢባልም የሚሰማበት ጆሮ ስለሌለው ቤተክርስቲያንንና ሕዝብን የማወክ ተግባሩን ቀጥሎበታል፡፡

"ማኅበረ ቅዱሳን" በቤተክርስቲያንና በፍርድ ቤት ፊት እውነትን መጋፈጥ ሲያቅተው፣  በውድቅት ሌሊት እንደሚልከሰከስ ሰይጣን በየአጥቢያ ቤተክርስቲያናቱ፣ በየጎዳናውና በየቤቱ እየዞረ የሚረብሽ ተናካሽ ውሻ ወደመሆን ደረጃ ወርዷል ሲሉ ታዛቢዎቻችን ገልጸዋል፡፡ በወንጌል ብርሃን ሲፈተሽ እንደ ቅቤ የሚቀልጠው "ማኅበረ ቅዱሳን" በእግዚአብሔር ቤተመቅደስ እንደዚህ ዓይነቱን ርኩሰት እየደጋገመ መፈጸሙ የዘመኑ መጨረሻ ዓይነተኛ ምልክት መታየት መጀመሩን አንባቢ ያስተውል ብለዋል፡፡

የዝግጅት ክፍላችንም እግዚአብሔር ለወንድማችን ለዲ/ን ጋሻዬ መላኩ፣ ጋብቻው የሠመረ የአብርሃምና የሣራ እንዲያደርግለትና ቀሪው የአገልግሎት ዘመኑን እንዲባርክለት፣ እንዲሁም በሚሠራው ሥራና በሚሰጠው አገልግሎት ፀጋውን እንዲያበዛለት  ይመኛል፡፡

የእግዚአብሔር ጥበቃና ቸርነት ከሁላችን ጋር ይሁን!!!
አሜን!!!