Wednesday, February 22, 2012

ልሳን


ልሳን ምንድን ነው

ሀ . ልሳን ምንድን ነው፤ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሰቸው ቦታዎችሰ
1.ልሳን ቋንቋ ማለት ነው።
ልሳን ማለት ቋንቋ ማለት ነው። በአዲስ ልሳን መናገር ማለትም በአዲስ ቋንቋ መናገር ማለት ነው። በአዲስ ቋንቋ መናገር ሲባልም ተወልደው ባላደጉበት፤ ባልተማሩት ቋንቋ በመንፈስ ቅዱስ ገላጭነት መናገር ማለት ነው። የመጀመሪያውና ትክክለኛው ልሳን የተገለጸው በጰራቅሊጦስ እለት ነው። ታሪኩም በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ ሁለት ተገልጿል። ሐዋርያትም ሆነ በዘመኑ የነበሩ ክርስቲያኖች የተናገሩት በሚሰማና ሊተረጎም በሚችል ቋንቋ ነበር። ሐዋ 2፡ 6 ይህም ድምፅ በሆነ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ ተሰበሰቡ፥ እያንዳንዱም በገዛ ቋንቋው ሲናገሩ ይሰማ ስለ ነበር የሚሉትን አጡ። ሐዋርያት በልሳን ሲናገሩ የተሰበሰቡት አይሁድ በራሰቸው ቋንቋ ሲናገሩ ሰምተዋቸዋል። ሐዋርያት የሚያወቁት የራሳቸውን ቋንቋ ብቻ ነበር ነገር ግን እነዚህ ሰዎች የተሰበሰቡት ከዓለም ሁሉ ነበር። ሐዋርያትም የተናገሩት የአለምን ቋንቋ ነበር።ጌታችንም በማር 16፤ 17 በአዲስ ቋንቋ ይናገራሉ ሲል በሚሰማ ቋንቋ ማለቱ ነው።
1ኛቆሮ 14፡ 9-11 እንዲሁ እናንተ ደግሞ የተገለጠውን ቃል በአንደበት ባትናገሩ ሰዎች የምትናገሩትን እንዴት አድርገው ያስተውሉታል ? ለነፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁና። በዓለም ምናልባት ቁጥር የሌለው የቋንቋ ዓይነት ይኖራል ቋንቋም የሌለው ሕዝብ የለም፤ እንግዲህ የቋንቋውን ፍች ባላውቅ ለሚናገረው እንግዳ እሆናለሁ፥ የሚናገረውም ለእኔ እንግዳ ይሆናል።
ብሎ ቋንቋ ሁሉ ሰሚ እንዳለውና እናንተም የምትናገሩት ቋንቋ ሰሚ ባለው ህዝብ መሐከል መሆን አለበት ብሎ ያብራራል።
2.ልሳን መንፈስ ቅዱስ ከሚሰጣቸው ልዩ ልዩና ስፍር ቁጥር ከሌላቸው ጸጋዎች አንዱ ነው።

 
የእግዚአብሔር ጸጋ ብዙና ልዩ ልዩ ነው በዚህ እንደተገለጠው፡ ልሳንም ከነዚህ ውስጥ አንዱ ነው።
1ቆሮ 12፤ 4-11 የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል።ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።
በመሆኑም በልዩ ቋንቋ መናገር ለሁሉም ሰው የሚሰጥ ሳይሆን እንደ ስጦታ ለአንዳንድ ሰዎች የሚሰጥ የጸጋ ስጦታ ነበር። ለዚህም በሐዋርያት ስራ ምዕራፍ ሁለት ፤በምዕራፍ አስራ አንድና ምዕራፍ 18 ላይ ሲገለጽ ሌሎች ተጠማቂዎች ግን በልሳን ተናገሩ የሚል የለም።
ይህንንም የሚያጠነክርልን ሐዋርያው እንዲህ ይላል
1ቆሮ 12፤ 29-30 ሁሉ ሐዋርያት ናቸውን ? ሁሉስ ነቢያት ናቸውን ? ሁሉስ አስተማሪዎች ናቸውን ? ሁሉስ ተአምራትን ይሠራሉን ? ሁሉስ የመፈወስ ስጦታ አላቸውን ? ሁሉስ በልሳኖች ይናገራሉን ? ሁሉስ ይተረጉማሉን ?
ስለዚህ በልሳን መናገር ለሁሉም የሚሰጥ ሳይሆን እንደማስተማር ፤ እንደመምከር ፤ ትንቢት እንደመናገር ሁሉ በጸጋ ለተወሰኑ ሰዎች የሚሰጥ ነው።
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መንፈስ ቅዱስ ሞላባቸው ተብለው በልሳን ያልተናገሩ አሉ ለምሳሌ
ሉቃ 1፤ 15 መጥምቁ ዮሐንስ መንፈስ ይሞላበታል ይላል በልሳን አልተናገረም ሉቃ 1፤ 41 ኤልዛቤጥ መንፈስ ቅዱስ ሞላባት በልሳን አለተናገረችም ሉቃ 1፤ 67 ዘካሪያስ መንፈስ ቅዱስ ሞላበት ግን በልሳን አልተናገረም ሉቃ 3፤ 22፣ 4፤ 1 ጌታችን በመንፈስ ቅዱስ አደገ ይላል ግን በልሳን ሲናገር አላየንም።
እንዲሁም በሐዋ 4፤ 31፡ ሐዋ 7፡ 55 ፤ ሐዋ 8፡ 14 ላይ የተጠቀሱት ክርስቲያኖች መንፈስ ቅዱስ ወረዳላቸው ይላል እንጂ በልሳን ተናገሩ አይልም። በመሆኑም በልሳን መናገር ለሁሉም ሰው የተሰጠ እንዳልነበር እንገነዘባለን።
3.የመንፈስ ቅዱስም ጸጋ የሚሰጠው ለጥቅም ነው
1ቆሮ 12፡ 7 ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። በመሆኑም ልሳን የሚሰጠው ለጥቅም ነው። የማይጠቅም ስጦታ እግዚአብሔር አይሰጥምና።
በሐዋርያት ዘመንም ሆነ በአሁኑ ዘመን ጸጋ የሚሰጠው ለቤተ ክርስቲን እድገት /ለጥቅም / ነው። በተለይም ለሐዋርያት በዓለሙ ሁሉ ስለሚያስተምሩ በቋንቋ እንዳይቸገሩ ሰጥቷቸዋል። በተጨማሪም ልሳን የሚሰጠው አዲስ ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ ሲነገር ሰምተው እግዚአብሔርን እንዲያከብሩ እና በእርሱ እንዲያምኑ ነው እንጂ ላመኑትና ክርስቲያን ለሆኑት አስፈላጊ አለመሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ ይገልጻል።
እንግዲያስ በልሳኖች መናገር ለማያምኑ ምልክት ነው እንጂ ለሚያምኑ አይደለም፥ ትንቢት ግን ለሚያምኑ እንጂ ለማያምኑ አይደለም። 1ቆሮ 14፤ 22 እዚህ ላይ ትንቢት የሚለው ትምህርቱን ስብከቱን ነው።
4.ቅዱስ ጳውሎስ የልሳንን ጥቅም ማጣት ጠቁሟል
ቅዱስ ጳውሎስ በ 1ኛቆሮ 14 ላይ ልሳን ጥቅም እንዳጣና እያገለገለ እንዳልሆነ ሲናገር እናየዋልን። ይህም መልእክቱ ደግሞ ከጌታ የተቀበለው እንደሆነ ይገልጻል።
14፡ 2 በልሳን የሚናገርስ ለእግዚአብሔር እንጂ ለሰው አይናገርም፤ የሚያስተውለው የለምና፥ በመንፈስ ግን ምሥጢርን ይናገራል፤ በልሳን የሚናገር ሰው እስካልተተረጎመ ድረስ ለማህበሩ ምንም የሚጠቅም ነገርን አይናገርም። ለራሱ ግን ያመሰግን ይሆናል። ምንም እየጠቀመው አይደለም ይላል። በዚህም ጥቅሙ ያን ያክል እንደሆነ የገልጻል። እንዲያውም በቁጥር 9 ላይ ለንፋስ የምትናገሩ ትሆናላችሁ ይላል። በቁጥር 18 ላይ ራሱ በብዙ ልሳናት /ቋንቋዎች / እንደሚናገር ከገለጽ በሗላ በልሳን ብዙ ቃል ከመናገር ይልቅ አምስት ቃላትን በሚታወቅ ቋንቋ ብናገር ይሻላል እያለ ያ የእግዚአብሔር ስጦታ የነበረው ልሳን በጊዜው እየጠቀመ እንዳልነበር ይገልጻል። መናገር ግድ ከሆነ ራሱ መተርጎም እንዳለበት አብራርቶ ይገልጻል።
በአጠቃላይ የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲን ሰዎች የሚተረጉም ሳይኖር ልሳን እንናገራለን እያሉ ልሳንን አላግባቡ እየተጠቀሙበት እንደነበር እና ያም አግባብ አለመሆኑን ነው ቅዱስ ጳውሎስ አስረግጦ የነገራቸው። 14፤ 33 እግዚአብሔርስ የሰላም አምላክ ነው እንጂ የሁከት አምላክ አይደለምና፤ በቅዱሳንም አብያተ ክርስቲያናት ሁሉ እንዲህ ነው።
ይህንን የሚመለከቱ የቤተ ክርስቲያን ሙህራን ልሳን ለጥቂት ጊዜ ቢያገለግልም ወዲያውኑ እንደጠፋ ይናገራሉ።
5 በልሳን እንናገራለን የሚሉ ሰዎች 1ኛቆሮ 14 ላይ የሚያሱት ጥያቄ፡
በዚህ ጥቅስ ላይ አንዳንደ ሐረጋትን ብቻ መዞ በመያዝ ፕሮቴስታንቶች ልሳን ሁሉ አይተረጎምም /የሚታወቅ ቋንቋ ላይሆን ይችላል / በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ብቻ ሊያልቅ ይችላል ይላሉ። ሆኖም የጥቅሱን /የምእራፉን / ሙሉ ሐሳብ ስናነብ የሚያሳየው ልሳን የሚባለው ሁሉ እንደሚተረጎም ልሳን ከተነገረ መተርጎም እንዳለበት ነው።
14፤ 6 አሁን ግን፥ ወንድሞች ሆይ፥ ወደ እናንተ መጥቼ በልሳኖች ብናገር፥ በመግለጥ ወይም በእውቀት ወይም በትንቢት ወይም በትምህርት ካልነገርኋችሁ ምን እጠቅማችኋለሁ ? እዚህ ላይ የሚያስተላልፈው በማይተረጎም ልሳን ብነግራችሁ ካልገለጥሁላችሁ ምን ይጠቅማል ነው። ምንም አይጠቅምምና ሆኖም ግን ልሳን በሚነገርበት ጊዜ ሊተረጎም እንደሚገባው ሲናገር ነው።
የሚነገር ልሳን ሁሉ ሊተረጎም እንደሚገባው ከልተተረጎመ ሊነገር እንደማይገባው ይናገራል።
14፡ 27-28 በልሳን የሚናገር ቢኖር ሁለት ወይም ቢበዛ ሦስት ሆነው በተራቸው ይናገሩ አንዱም ይተርጉም፤ የሚተረጉም ባይኖር ግን በማኅበር መካከል ዝም ይበልና ለራሱና ለእግዚአብሔር ይናገር።
የሚተረጉም ባይኖር ግን ሲል ለጊዜው ተርጓሚ ከሌለ ማለቱ ነው እንጂ ትርጉም አይኖረው እያለ አይደለም። ለጊዜው በሚነገርበት ቦታ ተርጓሚ ከሌለ አይነገር ማለቱ ነው እንጂ ልሳን ሁሉ መተርጎም የሚችልና የዚህ ዓለም ውስጥ ካሉት ቋንቋዎች ውስጥ አንዱ ነው።
ተርጓሜን በተመለከተ፡
አንደኛው ዋናው የቋንቋው ባለቤቶች ሰምተው ሊተረጉሙት ይችላሉ። በሌላ መልኩ ደግሞ የመተርጎም ጸጋ የተሰጠው አማኝ አለ። ታዲያ የመተርጎም ጸጋ የተሰጠውም ቢሆን ከሚነገረው አንድ ቋንቋ ሰው ወደሚሰማው ቋንቋ ይተረጉማል እንጅ ከሌለ ቋንቋ አይደለም የሚተረጉመው። ይህንንም ለማብራራት ያክል በልሳን ተናጋሪው በጉራጌኛ ቢናገር ታዳሚዎቹ አማርኛ ብቻ ቢናገሩ ተርጓሚው ከጉራጌኛ ወደ አማርኛ ይተረጉማል እንጂ ከማይታወቀ ጰረረረረረረረረረረረ ከሚል ቋንቋ አይደለም የሚተረጉመው።
ለ . አሁን የሚነገረው ቋንቋ በትክክል ከእግዚአብሔር የተገለጠ ነውን ?
በአሁኑ ጊዜ ፕሮቴስታንቶች የሚናገሩት ቋንቋ በመጽሐፍ ቅዱስ የሚነገረው የተገለጠው ቋንቋ ነውን ? ይህንን ለመመዘን በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው ልሳን ጋር ማነጻጸር ይኖርብናል።
1.ልሳን ከጠፋ ከ 1800 ዓመት በሗላ በ 20ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በተወሰኑ የፕሮቴስታንት ክፍሎች የተጀመረ ነው። የመጀመሪያው በ 1901 የተጀመረ ነው። ታዲያ አሁን በትክክል ምን አዲስ ነገር መጥቶ ነው። ክርስቲያኖች ድሮም ነበሩ። ፕሮቴስታንት እንኳን ራሱ ከተፈጠረ ከሶስት መቶ አመታት በሗላ ነው ልሳን የመጣው።
ስለዚህ መንፈስን ሁሉ አትመኑ ነገር ግን መናፍሰት ከጌታ እንደሆኑ መርምሩ እንዳለው መመርመር አለበት። 1ኛ ዮሐ 4፤ 1
2.በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠው ልሳን ሰው የሚሰማው ቋንቋ ነው አሁን የሚነገረውን ግን ማንም የሚያውቀው ቋንቋ አይደለም።
ሐዋያት 2፤ 7-8 የአይሁድ ሰዎች ሐዋርያት በልሳን ሲናገሩ ሰምተዋቸዋል። “ተገርመውም ተደንቀውም እንዲህ አሉ። እነሆ፥ እነዚህ የሚናገሩት ሁሉ የገሊላ ሰዎች አይደሉምን ? እኛም እያንዳንዳችን የተወለድንበትን የገዛ ቋንቋችንን እንዴት እንሰማለን ? “ በመሆኑም መንፈስ ቅዱስ የሚገልጸው ቋንቋ ሊተረጎም የሚችልና መሰማት የሚችል ነው።
በአሁኑ ጊዜ መጽሐፍ በሐገራችን የሚናገሩ ሰዎች አንዱም ቢሆን በማያውቀው ቋንቋ የሚናገር የለም። ለምሳሌ አንድ አማርኛ ብቻ ተናጋሪና ልሳን እናገራለሁ የሚል ሰው በኦሮሞኛ ወይም በትግሬኛ የተናገረ የለም። አንድም ልሳን ተናጋሪ በሚታወቅ ቋንቋ ተናግሮ የሚያውቅ የለም።
3.አሁን በፕሮቴስታንቶች ልሳን እየተባለ የሚነገረው ነገር በሌሎች ማለትም ክርስቲያን ባልሆኑና በክርስቶስ በማያምኑ ሰዎች ይነገራል። እውነተኛና በመንፈስ ቅዱስ የሚገለጽ ቢሆን ኖሩ ክርስቲያን ያልሆኑ ሰዎች ሊናገሩት አይችሉም ነበር።
ለምሳሌ

4.የአሁኑ ልሳን ምንም ጥቅም የለውም። የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ የሚሰጠው ለጥቅም ነው አሁን የሚደረግ የልሳን ስጦታ ጥቅም የለውም። በመጀመሪያ የማስተማሪያ ቋንቋ እንዳያጥርና ለማስተማር እንዲረዳ ነው እንዳይባል የሚሰማ ቋንቋ አይደለም። ከዚህም በተጨማሪ የእግዚአብሔርን ቃል የሚናገሩ ሰዎች በሁሉም ቋንቋዎች አሉ ስለዚህ በዚህ በኩል ጥቅም የለውም። አዲስ አማኞችን ለማስተማር ነው እንዳይባል ራሳቸው ብቻ ባሉበት ጊዜ ሳይቀር ሲጮሁ ነው የሚውሉት። በመሆኑም የአሁኑ ልሳን ጥቅም የለውም። ጥቅም ከሌለው ደግሞ ከእግዚአብሔር የተገለጠ አለመሆኑን እንረዳልን።
5.በልሳን እንናገራለን የሚሉ ሰዎች ያመኑትን እነዚህ ምልክቶች ይከተላቸዋል የሚለውን ሲፈጽሙ አይታዩም። በልሳን ብቻ እንናገራልን ይላሉ እንጂ።
በማር 16፤ 17 ላይ እንደተገለጸው ያመኑት /በልሳን የሚናገሩ ከሆነ / ሌሎችንም ሊያደርጉ ይገባል ለምሳሌ
-በስሙ አጋንንትን ማውጣት፡ ይህንን አያደርጉም አንዳንድ የሐሰት ታምራት ይደረጉ እንደሆነ እንጂ በታሪክ እውር ሲበራ አላየንም። ደንቆሮ ሲሰማ አልታየም። አንዳንዶች ግን ወገቤን ታምሜ ነበር ዳንሁ ምናምን ሲሉ ይሰማል። በትክክል ግን ጽኑ በሽታ የያዘው ሰው ፕሮቴስታንቶች ጋር ሄዶ ሲድን አላየሁም።
-ያወጣሉ፤እባቦችን ይይዛሉ፤የሚገድል ነገር ቢጠጡ አይጎዳቸውምና፡ ይህንን ነገር ማንም አይሞክረውም መሞከርስ እግዚአብሔርን አልፈታተንም ብሎ አያድርግ ግን ቢያደርግ እንደሚሞት ነው የሚያምነው። ሆኖም በትክክል በልሳን የተናገሩ /የእግዚአብሔር መንፈስ የነበረባቸው ቅዱሳን / ይህንን አድርገዋል። ለምሳሌ ቅዱስ ጳውሎስ እባብ ነድፎት ምንም ሳይሆን ቀርቷል። ሐዋ 28፡ 3 ቅዱስ ጊዮርጊስ መርዝ ጠጥቶ አልሞተም።
ሐ . ስለ ልሳን ሊኖረን የሚገባው ግንዛቤን በተመለከተ፡
ክርስቲያኖች ስለልሳን ሌላ ትርጉም አንሰጠውም።ልሳን ቋንቋ ነው። ትክክለኛ ልሳን በሐዋርያት ዘመን ተነግሯል። ያም ለጥቅም የመጣ ነበር ማለትም ሐዋርያቱ የቋንቋ እጥረት ኖሮባቸው የእግዚአብሔርን ቃል ከማስተላለፍ እንዳይታገዱ። ሆኖም ይህ ልሳን በቤተ ክርስቲያን ታሪክ እንደምንረዳው ከመጀመረያው መቶ አመት በሗላ ታይቶ አይታወቅም። ለዚህም በጊዜው እግዚአብሔር ለዓለም የነበረውን ዓላማ አሳክቶ ስጦታውን እንደወሰደው አምናለሁ።
ይህንን የምልበት ዋና ምክነያት፡
1.አሁን የሚነገረው ልሳን ከመጽሐፍ ቅዱሱ ልሳን ጋር አንድ አይደለም።
2.በመጽሐፍ ቅዱሱ የተጠቀሰለት ጥቅም በአሁኑ ጊዜ እየተከናወነበት አይደለም
3.ብዙ አሳች መንፈሶች የገቡበት ዘመን በመሆኑ ይህ ልሳን ደግሞ ከአሳቹ መንፈስ የሚለይበት መንገድ ባለመኖሩ
4.በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ከሐዋርያት በሗላ የታየ አለመኖሩ
5.የልሳኑ ተናጋሪዎች ውስጥ አብዛኛዎቹ በዶክትሪናቸው ችግር ያለባቸው ስለሆኑና በክርስቲያናዊ ሞራልም የማይኖሩ ስለሆነ እግዚአብሔር ይህን ልዩ ስጦታ አሁን ሰጥቷል ለማለት ያስቸግራል።
wengelforall.wordpress.com