Tuesday, February 14, 2012

የይስሙላ ድርድር እንዳይሆን እንሰጋለን!


የይስሙላ ድርድር እንዳይሆን!
ሰሞኑን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የ20 ዓመት የሁለት ሲኖዶስ ክፍፍል ለማቆም ድርድር እንደተጀመረ ከሚዲያው ሰምተናል። ምንም ይሁን ምንም እርቅና ስምምነት ከልብ ከሆነ መልካም ነው። እነዚህ ሁለት ወገኖች የራሳቸው ጥቅምና መብት የማስከበር ዓላማ እንዳላቸው ሁሉ ለስምምነቱ እልባት አለመድረስም ያንን በማስጠበቅ ላይ የተመሰረተ ስለሆነ የከዚህ በፊቶቹ ድርድሮች ውጤታማ ሳይሆኑ ቀርተዋል። ያሁኑን የተለየ የሚያደርገው ምን እንደሆነ በግልጽ የተነገረ ነገር ባይኖርም እኛ ግን ያለፈው ነገር እንዳይደገም ከመስጋት አንጻር የግላችንን ሃሳብ ከታች በአጭሩ ለማቅረብ ሞክረናል።

ድርድር የእርቅ መነሻ ምእራፍ ነው። ተደራዳሪዎች ግራና ቀኝ ሆነው ይሄንን ማግኘት ወይም ማስጠበቅ አለብኝ ብለው ይዘው የሚቀርቧቸው የድርድር ጭብጦች ይኖራቸዋል። ጭብጡ የሚወሰነው ተደራዳሪው ወገን በሚያመጣው ነጥብ ላይ ነው። የትኛውም ተደራዳሪ ወገን አስቀድሞ እነዚህን አምስት ነጥቦች አስወግዶ ወደ ድርድሩ ጠረጴዛ ካልመጣ ድርድሩ ውጤታማ አይሆንም።
የተደራዳሪዎች ውስጣዊ ሁኔታዎች፥
1/ ለድርድር የሚያቀርባቸው ነጥቦች ከተደራዳሪው ወገን የሚጠብቀው በነባራዊ ሁኔታ ያልተመሰረተ ጥያቄ ከሆነ፣
2/ ከምፈልጋቸው ነጥቦች ምንም አላጎድልም ወይም ሁሉም ይጠበቁልኝ ብሎ ከተዘጋጀ፣
3/ ከሁለቱ ተደራዳሪዎች ውጪ የሚያግባባ የሶስተኛ ወገን አደራዳሪን ሃሳብ ለመቀበል ካልፈቀደ፣
4/ ተደራዳሪው ወገን ለሚያቀርበው ሃሳብ «ምን እያለ ነውብሎ ከማጣጣል «እያለ ያለው ለምንድነውብሎ ለመረዳት ካልፈለገ፣
5/ ነገሮችን በሰከነ መንፈስ ለመገንዘብ ከመሞከር ይልቅ ከተደራዳሪው ወገን ምንም ላይገኝ ብሎ እልህ በመጋባት የሚያከር ከሆነ፣ የሁለት ወገን ተደራዳሪዎች ድርድር ውጤታማ ላይሆን ይችላል።
የተደራዳሪዎች ውጫዊ ሁኔታዎች፣
የትኛውም ተደራዳሪ ወገን ከጎኑ በድጋፍ የቆሙ ወይም በእጅ አዙር የሚደግፉ ወይም ሃሳቡን የሚመሩ ወገኖች ድርድሩን ሊያከሩበት ወይም ተደራዳሪው በማይፈልጋቸው የኃይል ውጫዊ አሰላለፎች ድርድሩን ውጤታማ እንዳይሆን ሊያደርጉት ይችላሉ።
1/ ተደራዳሪውን ከኋላ የሚነዱት ኃይሎች፣ በተደራዳሪያቸው ሳቢያ የሚደርስባቸውን ጉዳት ለመከላከል ድርድሩን ከፍጆታ ባለፈ የማይፈልጉት ሆኖ ሲገኝ፣
2/ ተደራዳሪውን የሚደግፉ አባላት፣ በተደራዳሪያቸው ምክንያት የአባልነት ወይም የደጋፊነት መብታቸው የማይጠበቅ ከሆነ ወይም ካልተከበረ፣ ድርድሩ በውጪያዊ ተጽእኖ ሊስተጓጎል ይችላል።
በተደራዳሪዎቹ ውስጣዊ የድርድር አቋምና ዓላማ እንዲሁም ድርድሩ በቀጥታ ባይመለከታቸውም ከድርድሩ የሚጠቀሙ ወይም የሚጎዱ አካላት በድርድሩ ላይ ተጽእኖ በማሳረፍ ውጤታማነት እንዲጎድለው ሊያደርጉ ይችላሉ።
ከነዚህ ነጥቦች ተነስተን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የውጪና የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ መካከል ያለውን የእርቅ ድርድር መገምገም ይቻላል።
በሀገር ውስጥና በውጪው ሲኖዶስ አንጻር፣
1/ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ በግዛቱ ያለውን ሲኖዶስ በራሱ ሕግ ጥላ ሥር እስካለ ድረስ እንደሕጋዊ ሲኖዶስ ስለሚቆጥር በድርድሩ ላይ በውጪ ካለው ሲኖዶስ የሚቀርቡ የድርድር መልኮች ሁሉ የእሱን(የመንግሥትን) ሉዓላዊነት የማይነኩ እንዲሆኑ ይፈልጋል።
2/ በሀገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስ ድርድሩ በስደተኝነት ወይም በሁለተኛ ሀገር የሚኖር ባለመሆኑ ከውጪ ያለውን ሲኖዶስ እንደአቻ ሳይሆን እንደመብት ጠያቂና ተቀባይ ወገን አድርጎ የመመልከት ሁኔታ ሊኖር ይችላል።
3/ በውጪ ያለው ሲኖዶስ በድርድሩ መነሻ እርቁ ፍጻሜ ቢኖረው የሚያጣው ነገር ሊኖር እንደሚችል ከገመተ ወይም ድርድሩ የነበረውን ሁኔታ ቀይሮ ፍጹም ሊያደርገው አይችልም ብሎ ካመነ ድርድሩን ውጤታማ ላያደርገው ይችላል።
ስለሆነም በሁለቱ ሲኖዶስ ወገኖች በኩል ያሉትን ነባራዊ ሁኔታዎች ገምግመውና አስቀድመው ለሲኖዶሱ ድርድር መልካምነት በየራሳቸው መንገድ ጠርገው በዚያ ላይ እየተረማመዱ ወደድርድሩ ጠረጴዛ ካልመጡ በስተቀር ስምምነቱ ፍጻሜ ይደርሳል ማለት አስቸጋሪ ነው።
እስካሁን የተደረጉ ግንኙነቶች ሁሉ ውጤታማ ያልሆኑበት ምክንያት ይህንን መሠረት ያደረጉ ናቸው።
እኛም እነዚህን ነጥቦች ያነሳነው ቤተክርስቲያንን እንደክርስቶስ አካልነቷ ሳይሆን እንደፖለቲካ መሳሪያነቷ እየተጠቀሙ በሚገኙት የውጪና የሀገር ውስጥ ሲኖዶስ አመለካከት ላይ ተንተርሰን እንጂ እንደመንፈሳዊ ተቋም ሰዎች አይተናቸው አይደለም። ሥልጣንንና ኃይልን (Authority & Power) ስለመካፈል እንደፖለቲካው የድርድር መሳሪያነት (Negotiation tools) ከላይ ያየናቸው ነጥቦች ጠቃሚ ናቸው። ከሃዲና ከሃዲ ተባብለው ተወጋግዘው ሲያበቁ አሁን ስለክህደቱ ጉዳይ ጉባዔ ለመጥራት ሳይሆን ስለሥልጣኑ ጉዳይ ሼር ለመነጋገር እንደሆነ ስንመለከት ቀድሞውኑ የተጣሉት ስለክርስቶስ ቤተክርስቲያን እንዳልነበረ ያረግጥልናል። ስለሆነም ፖለቲከኞቹ የሃይማኖት ሰዎች ድርድራችሁን አለዝባችሁ ስምምነት ላይ በድርድር መርህ ለመድረስ ሞክሩ!
ለዚህም የድርድሩ መርህ ይርዳችሁ እንላለን!