Thursday, January 2, 2014

ከፈረሱ ጋሪው የቀደመበት በማኅበረ ቅዱሳን የቀረበው የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አዲሱ ጥናት!



ማኅበረ ቅዱሳን ባልታጠበ እጁ የመቅደሱን አገልግሎት ለመናኘትና የአስተዳደሩን ወንበር ለመጨበጥ ላይ ታች ማለት የጀመረው ገና አቡነ ጳውሎስን ገፍቶ እስከሞት ድረስ ከመታገሉ አስቀድሞ ነው። ተላላኪ ጳጳሳቱን ካሰማራ በኋላ በአዋጅ ባለባቸው ህመም ሳቢያ እንደሞቱ የሚነገርላቸው እና በውስጥ አዋቂዎች ደግሞ ከህመሙ ባሻገር የሰው እጅም አለበት የሚለውን  የስውር አካሄድን ይትበሃል የተመለከተ የአቡነ ጳውሎስ ኅልፈት  ከመድረሱ በፊት ማኅበሩ ራሱን ከሰንበት ት/ቤቶች መምሪያ ነጻ በማውጣት በቀጥታ ተጠሪነቱ ለሲኖዶሱና ለሥራ አስኪያጁ እንዲሆን ነጋሪት አስመታ። ከዚህ አዋጅ በኋላ ማኅበረ ቅዱሳን የማይደፈር፤ የማይነካ የቤተ ክህነቱ አንበሳ ሆነ።  በግንቦቱ የ2004 ዓ/ም  ሲኖዶስ ላይ ይህንን አስወስኖ ድል በድል በሆነበት ዋዜማ ሟቹን ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስ እንዲህ ብለን ነግረናቸው ነበር።
«አመኑንም አላመኑም ፓትርያርክ ጳውሎስ፤አንድ ነገር አስረግጠን እንነግርዎታለን። በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊዎቹ ጳጳሳት ግብዓተ መሬትዎ ሊፈጸም የቀረው ጥቂት ነው» ብለን ነበር። [1]
እንዳልነውም ይህንን ከተናገርን ከሁለት ወራት በኋላ አቡነ ጳውሎስ ወደማያልፈው ዓለም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ሄዱ። ነብይ ስለሆንን ወይም ከሰው የተለየ ራእይ ስለመጣልን አልነበረም። በወቅቱ የነበረው የማኅበሩና በገዛ እጃቸው ጰጵሰው የጥላቻ ፈረስ ያሰገራቸው ጳጳሳት አካሄድ ጤናማ ስላልነበር አንድ ነገር ሊመጣ እንዳለ ይጠቁመን ነበርና ነው። ያልነውም ሆነ። ማኅበሩም ተደላድሎ ቤተ ክህነቱን ያዘ። ከእንግዲህ ምን ቀረው ማለት ነው? ቤተ መንግሥቱ? በዚህ ዙሪያ በሌላ ርእስ እንመለስበታለን።

 አሁን አንድ ነገር እዚህ ላይ አስረግጠን በመናገር ወደርእሰ ጉዳያችን እናምራ።
ጳጳሳቱ አንድም በራስ የመተማመን ጉድለት ባመጣው ፍርሃት ለማኅበሩ አጎብድደዋል፤ በሌላም አንድ ምክንያት ግለ ነውራቸውን አደባባይ እንዳያወጣ የበደል ምርኮኝነታቸውን አስበው ራሳቸውን ለማኅበረ ቅዱሳን አሳልፈው ሰጥተዋል። ይሁን እንጂ፤
«አመናችሁም፤ አላመናችሁም እናንተም የአባ ጳውሎስን የጥላቻ ጽዋ ከማኅበረ ቅዱሳን ዋንጫ በተራችሁና በሰዓቱ ትጎነጫላችሁ። ወደማይቀረውም ሞት ተራ በተራ በጊዜአችሁም፤ አለጊዜአችሁም ትሸኛላችሁ፤ በሕይወት እያለን ይህንን የማኅበረ ቅዱሳንን ሚዛን ስትቀበሉ እናያለን፤ ያኔ ደግሞ እንደዚህ ብለናችሁ ነበር እንላለን» ይህም ደግሞ በቅርቡ ይጀምራል»
ከአቡነ ጳውሎስ ሞት በኋላ ሲኖዶስ ማለት ማኅበረ ቅዱሳን ነው። ቀንደኛ የማኅበሩ መዘውሮች ደግሞ አፍንጫና ጆሮ በመቁረጥ በራሱ የተአምር መጽሐፍ ላይ የተመሰከረለት የዘርዓ ያዕቆብ ደቀመዛሙርት ናቸው። በእርግጥ የማኅበሩን እርጥባን እየተቀበሉ በመናጆነት የሚያገለግሉ የሉም ማለት አይደለም። እነዚህ የዘርዓ ያዕቆብ ጉዶች በረቀቀ ስልት ቤተ ክህነቱን በእጃቸው አድርገዋል። ዋነኛ መፈክራቸው ቤተ ክህነትን « በገንዘባችን፤ በጉልበታችን፤ በእውቀታችን እናገለግላለን» ነው። ገንዘባቸውን  እንደሆነ ቤተ ክህነት በጭራሽ አታውቀውም። ጉልበታቸውንም  ቢሆን እንደአበራ ሞላ በአካባቢ ጽዳት ተሰማርተው ወይም  ጥቃቅንና አነስተኛ አቋቁመው ስራ አጥ ካህናቱን ወደስራ ሲያስገቡ አላየንም። እውቀታቸውን ግን እነሆ ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ባቀረቡት ጥናት ሽፋን የቁጥጥር መረባቸውን ሲዘረጉ አይተናል። ይህም የረጅም ጊዜ ህልማቸውን እውን ያደረጉበት እውቀት በመሆኑ ቤተ ክህነት የጀመረችው የቁልቁለት መንገድ ነው ብሎ መናገር ይቻላል። መጨረሻውም እንደማያምር ጀማሪውን አይቶ መተንበይ አይከብድም። ይህንን እንድንል የሚያደርጉን ምክንያቶች አሉ። በጥቂቱ እንያቸው።
1/ የፕሮጀክት ጥናቱ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮችን የዳሰሰ መሆን ነበረበት። የችግሮቹን መግፍኢ ምክንያቶች፤ ያስከተሉት ውጤትና የመፍትሄ መንገዶችን ያመላከተ ሊሆን ይገባዋል።  የጥናቱ ዝርዝር ሁሉንም አሳታፊ በሆነ ውይይት ዳብሮ ለመፍትሄና አፈጻጸም በሚያመች መልኩ ተዘጋጅቶ አተገባበሩ ግን ለናሙና በተመረጠ አንዱ ሀ/ስብከት መሆን በተገባው ነበር እንላለን። እየሆነ ያለው ግን ማኅበሩ በሚነዳቸው ጳጳስ ፈቃጅነትና ማኅበሩ በሚዘውረው ቋሚ ሲኖዶስ ይሁንታ ከማኅበሩ ቤተ ክህነቷን የመቆጣጠር ምኞት ተፈብርኮ አዲስ አበባ ላይ የመዋቅር ብረዛ ችካል መትከል ተጀመረ።
2/ በአጠቃላይ የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግሮች ላይ ሊደረግ የሚገባው ሁለ ገብ ጥናት የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት፤ ሊቃውንት፤ ምሁራን፤ የሕግ አዋቂዎች፤  ጋዜጠኞች፤ ስልጣን ያላቸው ከፍተኛ ሹማምንት፤ የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ፤ የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪዎች የተካተቱበትና የቤተ ክርስቲያኒቱ እድገትና ልማት የሚመለከታቸው ሁሉ ተቀናጅተው ይህን የማስተባባር ኃላፊነት ቢቻል በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ ራሱን የቻለ ክፍል ተዋቅሮ መካሄድ በተገባው ነበር። ጋኖች አለቁና ማኅበረ ቅዱሳን አርቃቂ ሆኖ ጳጳሳቱ ከየትም ይምጣ እንጂ እንቀበላለን ብለው አረፉ። በማፈሪያዎች ዘመን የሚያሳፍር ነገር የለምና ብዙም አያስገርምም።
3/ ቤተ ክርስቲያኒቱ በሥጋዊ ወመንፈሳዊ አገልግሎቷ የሚጠበቅባትን ያህል እየተራመደች እንዳይደለ እርግጥ ነው። በአብዛኛው ውጫዊ ምክንያቶች እንደሆነ ተደርጎ ቢወሰድም፤ ለድክመቷ በዋናነት መነሳት ያለበት ከውስጧ ባለው ጉድለት መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው። ሲኖዶስና የሲኖዶስ የሕግ አመራር የዘመኑን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ የተመለከተ ስለመሆኑ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ አጠቃላይ የመዋቅር ዝርጋታው፤ አተገባበሩ፤ መመሪያውና ደንቦቿ ሁሉ ችግሮቿን የቃኙ፤ መፍትሄ ማምጣት የሚችሉና የሚያራምዱ አይደሉም። ቃለ ዓዋዲ የተባለው ደንብ በምንም መልኩ የዛሬይቱን ቤተ ክርስቲያን የማስተዳደር አቅም የሌለው ስለመሆኑ በማስረጃ አስደግፎ መናገር ይቻላል። ስለሆነም አጠቃላይ ጥናት ያስፈልጋል ሲባል ይህንን የተመለከተ መሆን ስላለበት ጭምር ነው። አንዱን ጥሎ አንዱን በማንጠልጠል የአዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ችግር ለብቻው ለመፍታት በፍጹም አይቻልም። የጳጳሳቱ ስሜትና የማኅበረ ቅዱሳን መንቀዥቀዥ ችግሩን ከማወሳሰብ በስተቀር የችግሩን ሰንኮፍ በፍጹም አይነቅልም።
4/ እስካሁን ያልተነገረለትና ሊነገርም ያልተወደደው የቤተ ክርስቲያኒቱ ችግር መንፈሳዊ ብልጽግናዋን የተመለከተው ክፍል ነው። በእርግጥ የአፄ ዘርዓያዕቆብ ትራፊዎች የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥንታዊነትና ሐዋርያዊ አስተምህሮዋን የበረዘ የብርሃን ወረደልን ደብረ ብርሃናዊ ዜማ በጭራሽ እንዲነካ አይፈልጉም። የአባ እስጢፋኖስና ደቀ መዛሙርቱ የአፍንጫና ጆሮ መቆረጥን ተገቢነት ዛሬም እንደታመነበት እንዲቀጥል ይፈልጋሉ። ቤተ ክርስቲያኒቱ መከራን የተቀበለችበትን የክርስቶስን ወንጌል ወደጎን ገፍተው አለያም ወንጌሉን ጨብጠናል ለማለት ብቻ መሳ መሳ የሚራመዱት ተረት፤ እንቆቅልሽና አልፎ ተርፎም ክህደት ያለባቸው አስተምህሮዎች በጥናቱ ውስጥ በመካተት እርምት ሊወሰድባቸው የሚገባቸውን በቃለ እግዚአብሔር ሚዛንነት የመለየት ስራ ፈጽሞ ሊታለፍ የማይገባው ነው። ዘመናዊው አስተዳደር ያለመንፈሳዊ ልማት በጭራሽ አይታሰብም።
 የሰይጣን መነኮሰ ክህደትና እርምት ሲነገር ለምን ይሄ ተነክቶ በማለት ጸጉራቸው እንደጃርት እሾክ ከሚቆመው መካከል ማኅበረ ቅዱሳን አንዱ ነው። ይህ የተረት አባት የሆነ ማኅበር ነው እንግዲህ ሕግ አርቃቂ የሆነልን። ስለዚህ በወርቅ የቃለ ወንጌል ወራጅና ቋሚ ዐምድ የተተከለችው ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ውስጥ ማንም ሳይፈቅድላቸው ገብተው የሸረሪት ድራቸውን ያደሩባት የዘመን እራፊዎች ጸድተው መገኘቷ አገልግሎቷን ምሉዕ፤ ክብሯንም በሚጠሏት ላይ ሳይቀር ከፍ ከፍ እንድትል ያደርጋታል። ደርግም፤ ኢህአዴግም ገፉን እያሉ ማልቀስ መነሻው የቀደመ መንፈሳዊ ክብሯ ስለቀነሰ ካልሆነ ሲያቦኩንና ሲጋግሩን አናይም ነበር።
ስለሆነም ከላይ ባየናቸው አራት ዋና ዋና መግፍኢ ምክንያቶች የተነሳ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ የቀረበው የማኅበረ ቅዱሳን ጥናት ተብዬ ከፈረሱ ጋሪው የቀደመበት ነው ማለት ይቻላል። በየግል ጋዜጣው የላኩትን ጽሁፍ መልሶ እንደአዲስ ግኝት በዜና መልክ ማቅረብ ወሬ ማብዛት የሚወድ የወፈፌ ስራ እንጂ የቤተ ክርስቲያን ችግር እንደሰጎን እንቁላል አትኩሮ የተመለከተ የመልካም ዘር ተስፈኛ አስተሳሰብ አይደለም። ስለዚህ ይንን ጋሪው ከፈረሱ የቀደመበትን ጥናት በየትም ይምጣ ቀልደኞችን ጥሎ ጋሪው ፈረሱን የሚጎትትበት አግባብ ቶሎ መፍትሄ ይሰጠው።
------------------------------------------------------