Saturday, January 18, 2014

የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት በ1994 እና በ1995 ዓ/ም በአንጻራዊነት የተሻለ የአስተዳደር ዘመን ነበረው!



ከመሪጌታ ይኄይስ ተአምኖ፤  ኩቤክ- ካናዳ

እንዲህ እንደዛሬው ሳይሆን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅ ማለት በሀ/ስብከቱ ውስጥ የፈለገውን ማድረግ የሚችል ሹመኛ ማለት ነው። ከ1992 ዓ/ም  ጥቂት ቀደም ብሎ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የሊቀ ካህናት ብርሃኑ ገ/አማኑኤል ሥራ አስኪያጅነትና (ነፍሱን ይማረውና) የዮሐንስ ዋለ ዘመን እንዳበቃ፤ ከቤተ ክህነቱ ሙያ ውጪ የሌላ ሙያ ባለቤት ያልሆኑትና የተለየ ሥራ እንዳላቸው የማናውቅላቸው ነገር ግን በአድዋና በመቀሌ  ትልቅ ኢንቨስትመንት ያላቸው አለቃ መኮነን ገ/መድኅን የሥራ አስኪያጅነቱን ኃላፊነት ከተረከቡ በኋላ ሙስናው ያለማስታወቂያ መደበኛ የስራ መስክ ሆኖ እንደነበር የምናውቅ ሰዎች የምንዘነጋው አይመስለኝም።

  እንደዚያም ሆኖ አለቃ መኮነን ገ/መድኅን ጎበዝ የአስተዳደር ሰው ናቸው። በዚያ ላይም ባመኑበት ጉዳይ ደፋርና ወደኋላ የማያፈገፍጉ ጠንካራ ሰው ስለመሆናቸውም መጥቀሱ ተገቢ ይመስለኛል። በወቅቱ ፀሀፊ የነበረውና አሁን በአሜሪካ በታክሲ ሾፌርነት የሚሰራው ክነፈ ርግብ ሐጎስ ፈጣንና ከዓይን ላይ የሚነጥቅ ቀልጣፋ እንደመሆኑ መጠን የሚበቃውን ገንዘብ መሰብሰብ ችሎ እንደነበር የምናውቅ እናስታውሳለን። እንደዛሬው የጉቦው የጨረታ መነሻ ዋጋው ከፍ ሳይል በፊት ለጉቦው በተሰጠው የሀ/ስብከቱ ምሥጢራዊ መጠሪያ ሥም ማለትም «ሥላሴ ስንት ናቸው? ከተባለ መልሱ «አንድም ሦስትም ናቸው» ማለት ሲተረጎም ክፍያው ከአንድ ሺህ እስከሦስት ሺህ ይደርሳል ማለት ሲሆን «አምስቱ አዕማደ ምሥጢር» ከተባለ ደግሞ «እስከ አምስት ሺህ»፤ ሰባቱ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ከተባለ ደግሞ « እስከ ሰባት ሺህ ብር» ጉቦ ይጠየቃል ወይም ይከፈላል ማለት ነበር። ዛሬን ወደኋላ መለስ ብዬ ሳየው በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሽፋን የጉቦ መቀበያ ተመንን በቁጥር የማስቀመጥ መጥፎ ልምድ መነሻው እምነትን ለገንዘብ የማዋል ምሥጢራዊ ክህደትና ማላገጥ እየተስፋፋ የመምጣቱ ምልክት መሆኑን ያመላከተ እንደነበር ነው። እምነት ከሰዎች ውስጥ እየጠፋ በመጣ ቁጥር እምነቱ ለሥም መጠሪያ ይሆንና በተግባር ግን ወደሸቀጥነት ይለወጣል ማለት ነው። ጌታችንንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በቤተ መቅደሱ ደጃፍ ሲሸጡና ሲለውጡ የነበሩትን በሃይማኖት ስም የመጡ ነገር ግን እምነቱን የመሸቀጫ መድረክ ያደረጉትን ሰዎች የገለጸበት መንገድ ተመሳሳይ ነበር። 

«የአይሁድ ፋሲካም ቀርቦ ነበር፥ ኢየሱስም ወደ ኢየሩሳሌም ወጣ።በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው።ደቀ መዛሙርቱም። የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደ ተጻፈ አሰቡ» ዮሐ2፤13-17 

ዕለተ ፋሲካ ቀርቦ ሳለ የሃይማኖት ሰዎች ሸቀጥ በመቅደሱ ደጃፍ ከትንሿ እርግብ እስከ ትልቁ በሬ ድረስ ሲሸጥ እንደነበር ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል። ዛሬም እንደ ቃሉ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የነዋይ ፋሲካቸውን የሚያከብሩ ሞልተዋል። ከነጋዴውና ሸቃጩ ማኅበረ ቅዱሳን አንስቶ በሥራ አሥኪያጅነት ዘመናቸው ባርከውና ቀድሰው ጉቦውን ያስፋፉት አባ እስጢፋኖስ፤ ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ ዛሬም ቤተ መቅደሱ ደጃፍ ላይ ተኮልኩለው አዋጭ ያሉትን የጥናትና ስትራቴጂ ገበያ ዘርግተው ለመሸጥ እያስማሙ መገኘታቸው ብዙም ላያስገርም ይችላል። በእምነት ሥም በዐደባባይ መሸጥ፤ መለወጥ ሲያያዝ የመጣ ነውና ብዙም ግር አያሰኝም።  ዛሬም ድረስ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ውስጥ ሸቃጮቹ መልካቸውን እየለዋወጡ መነገዳቸውን አላቆሙም። «የቤትህ ቅናት በላኝ» ለማለት በመጀመሪያ የንግድ ሂሳቡን ዘግቶ ወደኋላ የሚጎትተውን ብዙ ሀብት ትቶ ሊመጣ ይገባል እንጂ ስሜትና አፍን አስተባብሮ ነፍስያን በማባበል ማንንም ማታለል እንደማቻል ግን እንነግራቸዋለን።

«እርሱም በመንገድ ሲወጣ አንድ ሰው ወደ እርሱ ሮጦ ተንበረከከለትና። ቸር መምህር ሆይ፥ የዘላለም ሕይወትን እወርስ ዘንድ ምን ላድርግ? ብሎ ጠየቀው። ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።ትእዛዛትን ታውቃለህ፤ አታመንዝር፥ አትግደል፥ አትስረቅ፥ በሐሰት አትመስክር፥ አታታልል፥ አባትህንና እናትህን አክብር አለው። እርሱም መልሶ፦ መምህር ሆይ፥ ይህን ሁሉ ከሕፃንነቴ ጀምሬ ጠብቄአለሁ አለው። ኢየሱስም ወደ እርሱ ተመልክቶ ወደደውና። አንድ ነገር ጐደለህ፤ ሂድ፥ ያለህን ሁሉ ሽጠህ ለድሆች ስጥ፥ በሰማይም መዝገብ ታገኛለህ፥ መስቀሉንም ተሸክመህ ና፥ ተከተለኝ አለው። ነገር ግን ስለዚህ ነገር ፊቱ ጠቈረ፥ ብዙ ንብረት ነበረውና እያዘነም ሄደ» ማር 10፤17-22

ሀብትና ንብረታቸውን እያከማቹ «የቤትህ ቅናት በላኝ» ቢሉ ሁሉን ዐዋቂ ፈጣሪን ቀርቶ በዓይን የምናያቸው እኛን ሊታልሉ ከቶ አይችሉም። የገነቡትን የመኖሪያ ቤት ለቤተ ክርስቲያናቸው ይስጡ፤ ከመቅደሱ ደጃፍ የተገተረውንም ህንጻ የተወደደ መስዋዕት እንዲሆንላቸው ለቤተ መቅደስ መባዕ ይስጡና ስለ ቤቱ ቅናቱ   ይንገሩን። ያኔም ምሳሌ የሚሆነውን ሥራቸውን ዐይተን እንደነዚህ ዓይነቶቹን ቤተ ክርስቲያን ትፈልጋቸዋለች ብለን ምስክርነታችንን እንሰጣቸዋለን።
   ከዚያ ባሻገር የወጣቱን ሀብታም ታህል  «አታመንዝር፤ አትስረቅ፤ አታታልል፤ በሀሰት አትመስክር» የሚለውን ትዕዛዛት ከህጻንነታቸው ጀምረው ማክበር ስለመቻላቸው አፋቸውን ሞልተው ለመናገር የማይችሉ «የቤተ መቅደሱ ቅናት በላኝ» ቢሉ ማን ያምናቸዋል? ሌላው ቀርቶ ማኅበረ ቅዱሳን  የቤተ መቅደሱን ደጃፍ ሰናዖር ህንጻውን መባዕ አድርጎ ሊሰጥ ይቅርና ቤተ ክርስቲያን ሂሳብህን ኦዲት ታድርግህ፤ በቤተክህነቱም ሰነድ ገቢህን ሰብስብ፤ ሲባል በሕጋዊ የውጭ ኦዲተር አስመርምሬአለሁና የምሰጣችሁ ወረቀት በቂያችሁ ነው በማለት አቅሙም፤ ሥልጣኑም የላችሁም በማለት ማናናቁ ብቻ የማንነቱ ምሥክር ነውና ወቅታዊውን ችግር ተመልክቶ የራስን አጀንዳ ማስፈጸም አግባብ አይደለም።
  ወደ ርዕሰ ጉዳያችን ስንመለስ በ1994 ዓ/ም  አለቃ መኮነን ገ/መድኅን የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ሥራ አስኪያጅነቱን ጨርሰው ለስድስት ወር ገደማ የወረቀት ራስጌና ግርጌ የማይለዩት፤ የማኅጸንቱ ልጅ ሥራ አስኪያጅነቱ እንደለቀቁ፤ በወቅቱ ከአሜሪካ የተመለሱት አባ ተከስተ ብርሃን ወ/ሳሙኤል / በኋላም አባ ሳሙኤል ሊቀ ጳጳስ/ መረከባቸው ይታወሳል።  ፀሀፊ የነበረው ክነፈ ርግብ ሐጎስም የዞረ ሂሳቡን በአባ ማኅጸንቱ በማስጨረስና የሚሸመጥጠውን ጨራርሶ በአጋጣሚ ያገኛትን ኢትዮጵያዊ አሜሪካዊትን አግብቶ ወደአሜሪካ ኮበለለ።
   አባ ተከስተ ብርሃን የወቅቱ ሥራ አስኪያጅ ሆነው በትኩስና ባልተበረዘ ስሜት በሀ/ስብከቱ ውስጥ ተንሰራፍቶ የነበረውን ሙስናና ቤተሰባዊ ተቋም ለመናድ ጊዜ አልፈጀባቸውም። የካህናት አስተዳደሩን መጋቤ ሃይማኖት ጸገየን፤ የትምህርትና ስብከተ ወንጌል ኃላፊውን ርዕሰ ደብር መሀሪን፤ የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊውን (ነፍሱን ይማረውና) ኃይሉ ማርቆስን፤ ከወረዳ ቤተ ክህነት ወደ ፀሀፊነት የተዛወሩት አፈ መምህር ገ/ዮሐንስን፤ ከብዙ ድካምና ጥረት በኋላ ደ,ግሞ ወ/ሮ ሣራ ገ/ሥላሴን፤ ወ/ሮ ኢትዮጵያ ክፍሌን የመሳሰሉትን የማይገፉ ተራሮች አንድ በአንድ ለመናድ በመቻላቸው ትልቅ ስም ለመገንባትና በበታቾቻቸው ላይም የማይቻሉ ሰው የመሆናቸውን ተፅዕኖ ማሳደር ችለው ነበር።
 ከላይ የተዘረዘሩት ሰዎች በአንድም ሆነ፤ በሌላም ምክንያት ከበላይ ባለሥልጣናት በተለይም (ነፍሳቸውን ይማርና) ከወቅቱ ፓትርያርክ ከአቡነ ጳውሎስ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ስለነበሩ እንደዚህ ዓይነቶቹን ሰዎች ከያዙበት ስኳር ከሆነ ሥልጣን ላይ ማስነሳት የሚታሰብ ባለመሆኑ የአባ ተከስተ ብርሃን ወ/ሳሙኤል ግንባር እድለኛ ስለነበር ይሆናል ወይም በበላይ አካል በኩል ተሰሚነት ያገኙ እንደነበሩ መገመት ይቻላል።  ይህም የስምና የኃይል ግንባታ ብቃት በበታቾቻቸው ላይ ፍርሃት በማንገሱ ትእዛዞቻቸው ሁሉ ተፈጻሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። 
በእርግጥም ቀደም ብሎ ከእነ አባ ኃ/ማርያም ዘመንና ከወዲህም በእነ ሊቀ ካህናት ብርሃኑና ዮሐንስ ዋለ በኋላም በአለቃ መኮንንና ክነፈ ርግብ ሐጎስ አስተዳደር ጊዜያት ውስጥ ሀ/ስብከቱ ተጨመላልቆ ስለነበር የአባ ተከስተ ብርሃን ወ/ሳሙኤል አዲስ የአወቃቀር መንፈስ ተስፋን መፈንጠቁ የሚጠበቅ ነው።  ደግሞም ከእነድክመቶቹ በወቅቱ የአዲሱ ሥራ አስኪያጅ ቀናና ትኩስ መንፈስ ብዙ ድጋፍ ከካህናቱ ወገን አግኝቶም ነበር።
  መረን የለሽ የግል ጋዜጦች የቤተ ክህነቱን ገመና ሳይዙ የሚወጡበት ቀን አለ ለማለት አይቻልም ነበር። ይህም በብዙ መልኩ ቀንሶ የተገኘው በአባ ተከስተ ብርሃን ሥራ አስኪያጅነት ወቅት ለመሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። በተለይም በ1994 እና በ1995 ዓ/ም በይበልጥም አባ ተከስተ ብርሃን የሊቀ ጳጳስነቱን ሥልጣን ከማግኘታቸው በፊት የነበረው የሀ/ስብከቱ አስተዳደር በአንጻራዊነት ሲታይ በሀ/ስብከቱ ታሪክ ከመቼውም ጊዜ የተሻለ እንደነበር አይካድም። የዚህ ጽሁፍ አቅራቢም ይህንኑ ይመሰክራል።


 አባ ሳሙኤል ሊቀ ጳጳስ ከሆኑም በኋላ ጥቂት ለማስቀጠል ሞከረው ነበር። ነገር ግን ቀደም ሲል የነበራቸውን የመልካም ስራ መንፈሳቸውን ማን እንደቀማቸው ሳይታወቅ፤ በፓትርያርክ ጳውሎስ ፊት የነበራቸውንም ግርማ ሞገስ እየሸረሸረ የወሰደው ነገር ሳይገለጥ ሀ/ስብከቱን ማስተዳደር ትተዋል በሚባል ደረጃ ወደ መርሳት ደርሰው ነበር። ምናልባትም ሥራ የአስኪያጅነቱን ዘመን የተጠቀሙት ወደሥልጣን የመሸጋገሪያ ስልት አድርገውት ይሆን? የሚል ጥያቄ የሚያስነሳው ሥራ አስኪያጅ ሳሉ ከነበሩበት ዘመን የተሻለ ሥልጣን ሲይዙ የበለጠ መስራት እየቻሉ ለመስራት አለመፈለጋቸው ፍንጭ ሊሰጠን ይችላል። ከዚያም በላይ አብረውአቸው የሚውሉትንና የሚወርዱትን ሰዎች ማንነት ስንመለከት በወቅቱ በትክክለኛ የኅሊናቸው መስመር ላይ እንዳልነበሩ ያረጋገጠ ማረጋገጥ ችለናል።

  ከሀ/ስብከቱ ሽያጭ ክፍል ተነስቶ ወደሥራ አስኪያጅነት ያደገው መሪጌታ መኩሪያ ደሳለኝ ከያዘው በኋላ የሀ/ስብከቱ የአስተዳደር ዘመን ሳይሆን የሞት ዘመኑ ሆኖ ተተክቷል። የተገነባው መልካም አወቃቀርና አስተዳደር እምጥ ይግባ ስምጥ ሳይታወቅ በአፍ ጢሙ ተደፋቷል። በተመሳሳይ መልኩ ሊቀ ጳጳስ ሳሙኤል መተንፈሻ እስኪያጡ ድረስ ከረቫት ባሰሩ አሸርጋጅ ፀሐፊዎች፤ ራሳቸውን ባልሰበኩ ሰባኪዎች፤ በሙዳየ ምጽዋት ገልባጭ አስተዳዳሪዎች ተከበው በውዳሴ ከንቱ መከራቸውን ያዩ ነበር። ሃይማኖት የለሹ ዘሪሁን ሙላቱ (ዛሬም በየመድረኩ ሃይማኖት እንዳለው ሰው ያናፋል) ቀኝ እጃቸው ሆኖ አለሁልዎ ሲላቸው መጨረሻውን ለማየት እንመኝ ነበር። የዛሬው የቦሌ መድኃኔ ዓለም ፀሀፊ ሰሎሞን በቀለ የካዝናውን ቀበኛ አይጥ ይዘው ሲጓዙ ለተመለከተ አጀብ የሚያሰኝ ነበር። የባሌ ጎባው አጭበርባሪ ሰሎሞን ቶልቻ (ቄስ ነኝ ይላል)፤  የቅድስት ማርያሙ ሰንበት ተማሪ ሡራፌል ወንድሙ (እሱም አሁን አሜሪካ ገብቶ ቄስ ነኝ ይላል) የመሳሰሉት ሁሉ እንደበረዶ ናዳ የሚሟሙ ወዳጆችን አፍርተው አይተን የሚቀልጡበትን ቀን ስንጠባበቅ ነበር።

  ጉዳይ የሚፈጸመው በስልክ ወደመሆን ተቀይሯል። በጉድ ሙዳዩ አባ አብርሃም በኩል የሚቀርቡ ተቀጣሪዎች ውጤታማ መሆናቸውም የታየበት ወቅት ነበር። ባለ ጉዳይ፤ ጉዳይ የለሽ ሆኗል። የአድባራትና ገዳማት ምዝበራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ገኗል። ከስራ የሚባረር፤ አላግባብ የሚዛወር፤ ከደረጃው የሚወርድ በርክቷል። ፍርድ ቤቶችን የቤተ ክህነት አቤቱታ አሰልችቶታል። ብዙ ችግሮችና የሥልጣን ሽኩቻዎች ተበራክተው የሀ/ስብከቱ አስተዳደር ግብዓተ መሬቱ ሊፈጸም ሲል ከአባ ጳውሎስ ጋር የጠለቀ ክርክር ሲነሳ ጎራው ይለይ ጀመረ። ዘመቻው ሁሉ ፈልቶ፤ ገንፍሎና ቀዝቅዞ የሆነው ሁሉ ሆነ።  በተለያየ ጊዜ ከሀ/ስብከቱ ያስቀየሯቸው ሰዎች አባ ሳሙኤልን መዋጋት ዛሬ ነው በማለት ጦር ሰበቁ። አየር ላይ የተንሳፈፉት እነአባ ዕዝራ በጀት መደቡ። እነኤልዛቤል እጅጋየሁም እንደጉዲት ተፋለሙ። አባ ሳሙኤልም ብቻቸውን ቀርተው፤ ብቻቸውን ተዋግተው ዘለቁ። ሁሉም ጥጉን ይዞ «ያመኑት ፈረስ በደንደስ» እንዲሉ ያመኗቸው ሁሉ ከዱ። አባ ሳሙኤል ሀ/ስብከታቸውን በአግባቡ የአስተዳደር ማዕከላዊነት ይዘውት ቢሆን ኖሮ አንድ ጊዜ ለዐራት፤ ሌላ ላንድ ሲጠቀለልና ሲፈታ ባልኖረም ነበር። እንደጀመሩት ለመጨረስ አልቻሉም።

  ዛሬስ? ዛሬ ያለፈውን ስህተት ሲደገም ማየት የባሰ ያሳምማል። አባ እስጢፋኖስ ያንን ስህተት እየደገሙት ነው። ማኅበረ ቅዱሳንና ተላላኪዎቹ ከኋላ ሆነው ሀ/ስብከቱን እያስተዳደሩት መገኘታቸው እርግጥ ነው። እኛ የምንለው ራሳችሁን ሁኑ ነው። ሌሎችን ተደግፋችሁ የራሳችሁን ገመና ለአጋልጦ ገላጭ አትስጡ ነው። እውነት መናገር ካስፈለገ ካህናቱ የማንንም አባቶች ገመና አደባባይ ማውጣት አይፈልጉም፤ አይወዱምም። ችግሩ ያለው ከራሳቸው ከባለገመናዎቹ ሲሆን ገመናቸውን እንደድመት ሽፍን አድርገው መያዝ ያቅታቸውና ያለቦታቸው ተገኝተው እንዲገለጥላቸው አርፎ የተኛውን ካህን በግድ ይነካኩታል።  አፄ ቴዎድሮስን እልክ ያጋባቸውና እስከሞት ያደረሳቸው የካህን አድማ ነው። አባ እስጢፋኖስም አዲስ አበባ ሀ/ስብከትን ያለማኅበረ ቅዱሳን ውሻል ማስተዳደር አልቻሉበትም። በእልኽ ቤት አይገነባምና በእልኸኝነት ሁሉን ከግብ አደርሳለሁ ማለቱን ትተው ሀ/ስብከትን ለቀው አንዱን፤ ጅማዎትን ለዚያውም ከቻሉ እስኪ እሱኑ በደንብ ያስተዳድሩ ምክሬ ነው!!