የእግዚአብሔር መንፈስ እንዲያድርባችሁ ሳር ጋጡ የተባሉ ደቡብ አፍሪካውያን ሳር ሲግጡ ዋሉ!!

የፍጻሜው ዘመን የተቃረበ ይመስላል። ጤናማ አእምሮና በማኅበራዊ ኑሮው ሰላማዊ የነበረ ሕዝብ እንደጋማ ከብት ሳር እንዲግጥ ሲታዘዝ  ሲበላ ዋለ ማለት እጅግ ያስገርማል። ነገሩ በእርግጥ ሆኗል። በደቡብ አፍሪካ ፤ ጋራኑካ በተባለች ከተማ ውስጥ  የተቋቋመችውና ከ1000 በላይ ተከታዮች ያሏት ማኅበር መሪ የሆነው ፓስተር ሌሴጎ ዳንኤል የስብከት መርሐ ግብሩን እንደፈጸመ መገለጥ መጥቶልኛልና ከአዳራሽ ወጥታችሁ የሜዳውን ሳር ጋጡና በመንፈሰ እግዚአብሔር ትሞላላችሁ ባላቸው መሰረት ትእዛዙን ተቀብለው ሳር ለመጋጥ መሰማራታቸውን «ክርስቲያን ፖስት» ጋዜጣና «ቺካጎ ዲፌንደር» ዘግበዋል።


   ግማሹ ሳሩን አጎንብሶ እንደከብት እየጋጠ፤ ገሚሱ ደግሞ እንደጭላዳ ዝንጀሮ እየነጨ ሳሩን ሲበላ የዋለ ሲሆን የሰው ጭላዳ ከሆኑት መካከል አንዷ የሆነችው የ21 ዓመቷ የህግ ተማሪ ሮዝመሪ ፔታ ለጋዜጠኞች እንደተናገረችው «ሳሩን በመጋጤ ለአንድ ዓመት ያህል ሲያሰቃየኝ ከነበረው ከጉሮሮ ቁስለት በሽታ ተፈውሻለሁ» በማለት ያገኘችውን አስደናቂ ተአምርና የሳር መጋጡን ጠቃሚነት የገለጸች ሲሆን የ27 ዓመቷ ዶሪን ጋትል የተባለችው ደግሞ እንዲህ ስትል ስለተደረገላት ተአምር ያገኘችውን ጥቅም ገልጻለች። «በነበረኝ የስትሮክ በሽታ እግሮቼን ላለፉት ሁለት ዓመታት ማንቀሳቀስ ተስኖኝ ነበር። ሳር ብትበሉ በመንፈስ ትሞላላችሁ፤ በማለት ስለሳር መብላት አስፈላጊነት ፓስተሬ ባዘዘኝ ጊዜ በመብላቴ ከበሽታዬ በፍጹም ድኜ እነሆ በሁለት እግሬ ለመሄድ በቅቻለሁ» በማለት ስለተደረገላት ተአምር ለሚዲያ ተናግራለች።

  ይሁን እንጂ የሁለቱንም ሴቶች አባባል የሰሙ ታዛቢዎች በአባባላቸው ስቀዋል። ጤንነታቸውንም ተጠራጥረዋል።  ይህ የማይታመን ቀልድና በእግዚአብሔር ስም ማላገጥ ነው። መንፈስ ቅዱስ እንዲያድርብን ሳር አጎንብሳችሁ ጋጡ ተብለናል የሚሉት ጉዳይ የግድ መቆም ያለበትና ለህብረተሰቡ በመጥፎ አርአያነቱ ካልሆነ በመልካምነቱ የሚታይ አይደለም በማለት የተመለከቱ ታዛቢዎች ተቃውሟቸውን ገልጸዋል ። የሰው ልጅ ሲፈጠር እንደእንስሳ ሳር ለመጋጥና ለመፍጨት የተዘጋጀ የሰውነት አወቃቀር ስለሌለው የተደረገው ነገር ሁሉ ከክርስትና ሃይማኖት ጋር የማይገኛኝና መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሰረት የሌለው በመሆኑ ድርጊቱን እንቃወማለን ሲሉ ስለሳር ጋጮቹ ተናግረዋል።

 ከዚሁ ጋር ተያይዞ ስለሳር መጋጡ ውሎ እንደተዘገበው፤ በመስኩ ላይ ተሰማርተው ሳር ሲግጡ ከዋሉት የሰው ጭላዳዎች መካከል አብዛኛዎቹ ሲያስመልሳቸውና ሲሰቃዩ የዋሉ ሲሆን ገሚሶቹ መብላት አቅቷቸው ሲያለቅሱ ታይተዋል። አንዳንዶቹም ሆዳቸውን ታመው ህክምና እስኪደርስላቸው ድረስ መታመማቸውም ታውቋል። ከዚህ በፊትም ፓስተር ሌሴጎ ዳንኤል በአዳራሹ ውስጥ የተገኙ ተከታዮቹን በጥፊ እንዲጠፋጠፉ ባዘዛቸው ጊዜ ትእዛዙን ተቀብለው፤  ጉንጫቸው ድልህ እስኪመስል በጥፊ መጠዛጠዛቸውም ተዘግቧል።

እንደሚታወቀው ሳር በመጋጥ እንደእንስሳ ይሆን ዘንድ ከእግዚአብሔር ትእዛዝ የወጣበትና ልቡ የተሰወረበት ናቡከደነጾር እንደነበረ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል።  ናቡከደነፆርም ለዚህ የበቃው በትምክህቱና በትዕቢቱ እንጂ ለበጎ ተግባሩ የተሰጠው ልዩ ጸጋ አልነበረም። እና ታዲያ የዘመኑ ሰዎች እንደናቡከደነፆር ወደእንስሳነት ወርደው ሳር በመጋጣቸው የናቡከደነፆር ቤተሰቦች የማይሆኑበት ምክንያት ይኖር ይሆን?
«ልዑሉም በሰዎች መንግሥት ላይ እንዲሠለጥን፥ ለሚወድደውም እንዲሰጠው እስክታውቅ ድረስ ከሰዎች ተለይተህ ትሰደዳለህ፥ መኖሪያህም ከምድር አራዊት ጋር ይሆናል እንደ በሬም ሣር ትበላ ዘንድ ትገደዳለህ፥ ሰባት ዘመናትም ያልፉብሃል አለው» ዳን 4፤32
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 2 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
January 13, 2014 at 2:48 AM

አይ የጴንጤ መንፈስ በ"የሱስ'' ስም ያላግጣል:: ደሞ እኮ ማህበር ይባልልኛል አንድን የጴንጤ ድርጅትና ፓስተር::

Anonymous
January 14, 2014 at 11:05 AM

መቼም ቢሆን ከእነርሱ ከዚህ በላይ አይጠበቅም ዋናው የኦርቶዶክስ ልጆች ራስን ባሉበት ሃይማኖት ማጽናት ነው፡፡

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger