(የጽሁፍ ምንጭ፤ አዲስ አድማስ )
በገዳሙ እንክብካቤ እንጂ ጭቆናና እንግልት የለም /የገዳሙ አስተዳደር/
የምስካየ ህዙናን መድሀኒያለም ገዳም ሰራተኞች በቤተ - ክርስቲያኑ አስተዳደር ከፍተኛ ጭቆናና በደል እንደሚደርስባቸው ተናገሩ፡፡ የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ መላዕከ ገነት አባተክልማርያም አምኜ የገዳሙን ሰራተኛየ ሚያስተዳድሩት እንደመፈንሳዊ አባት ሳይሆን እንደ አምባገነን መሪ ነው ሲሉ ሰራተኞቹ አማረዋል የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ተ/ማርያም አምኜ በበኩላቸው በቤተክርስቲያኒቱ ሁሉም ስርዓትና ደንብን ተከትሎ እንጂ ያለ አግባብ የሚንገላታም የሚጨቆንም የለም ሲሉ መልሰዋል፡፡ “ቤተክርስቲያኑ የሚመራው በፓትሪያርኩ ነው” ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ የደሞዝ ማነስን ተከትሎ እንዲያነጋግሩን አባ ተክለ ማርያምን ለስብሰባ ጠርተን እግረ መንገዳችንን የገዳሙን የመልካም አስተዳደር ችግር፣ እርሳቸው ያለ አግባብ የሚሰሯቸውን ስራዎች፣ እና አጠቃላይ ያለውን ችግር አስረዳናቸው ይላሉ ቅሬታ አቅራቢዎቹ፡፡
ይሁን እንጂ ለምን አካሄደን ተቃወማችሁ በሚል በግል እየጠሩ ማስፈራሪያና ዛቻ ያቀርቡብናል ለአንዳንዶቻችን ያለ አግባብ የማስጠንቀቂያ ደብዳቤ ተፅፎብናል ብዙዎችም ከስራ ተባረዋል ብለዋል የገዳሙ ሰራተኞች፡፡ አስተዳዳሪው ወደ ገዳሙ ተሹመው ከመጠ አንድ አመት ከስድስት ወር ቢሆናቸውም እስከዛሬ በቤተክርስቲያኑ አንድም ልማት እንዳላካሄዱ የገለፁት ቅሬታ አቅቢዎቹ ችግር አለ ይስተካከል በማለት ቅሬታ የሚያርበውን ሁሉ እንደጠላት በማየት ሊመደብ ወደማይገባው ቦታ ይመድባሉ፣ ከደረጃ ዝቅ ያደርጋሉም ብለዋል፡፡ ቤተክርስቲያኒቷ ያለ አግባብ እየተመራች ነው ሰራተኞቹ እየተንገላቱ ነው በሚል ቅሬታ ያቀረበውና የቤ/ክርስቲያኑ ጉዳይ አስፈፃሚ የነበረውን መምህር ሰለሞን ተስፋዬን ከስራው አንስተው ሙያው ወደማይፈቅደው የገዳሙ ክሊኒክ እንደመደቡትና በዚህም ለገዳሙ የቦርድ ሊቀመንበር አመልክቶ ጉዳዩ እየታየ ባለበት ከስራ እንዳባረሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ ተናግረዋል፡፡
የቤተክርስቲያኑ አስተዳዳሪ አባ ተክለማሪያም በጉዳዩ ዙሪያ ተጠይቀው ሲመልሱም ሰራተኞቹ የደሞዝ ጥያቄ ባነሱ ጊዜ ባለፈው ሀምሌ ጨምረናልም ምግብ መጠለያና ሁሉን አሟልተን ይዘናችሁ እንዴት አሁን የጭማሪ ጥያቄ ታነሳላችሁ ብለናቸዋል ይላሉ፡፡ የመምህር ሰለሞንንን ከስራ መባረር በተመለከተም “ወደ ክሊኒኩ ያዛወርነው በእድገትና በሁለት እርከን የደሞዝ ጭማሪ ነው” ያሉት አስተዳዳሪው ጉዳዩን አምኖበት ስራውን ከተረከበ በኋላ ማንም ሳያውቅ ዘግቶ በመጥፋቱ ሊሰናበት ችሏል ብለዋል፡፡ ማስጠንቀቂያውን በተመለከተ ለአንድ ሰራተኛ መስጠቱን አምነው “ቤተክርስቲያኗ ሲኦል ናት” በሚል ለተናገረው ንግግር ማስጠንቀቂያ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡ የገዳሙ ክሊኒክ መካከለኛ ሆኖ ሳለ አልትራ ሳውንድ ይጠቀማሉ፡፡ ይህ ክልክል ነው በሚል ቅሬታ አቅራቢዎቹ የተናገሩ ሲሆን “በፊት እንጠቀም ነበር አሁን ተከልክለን አቁመናል” ብለዋል አባ ተክለማሪያም አምኜ፡፡ “የቤተክርስቲያኗን ስም ለማጥፋት የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች እንዳሉ እናውቃለን” ያሉት አስተዳዳሪው በገዳሙ ያሉ እስረኞች በእንክብካቤ ተያዙ እንጂ በአንዳቸውም ላይ ጭቆናና እንግልት አላደረስንም ብለዋል፡፡