Monday, January 13, 2014

ጦርነቱ በማጣጣር ላይ ባለው የማኅበረ ቅዱሳን አልሞት ባይነትና እጁን ለመስጠት በተዘጋጀው የቤተ ክህነት ባለሥልጣናት መካከል ነው!!!



እንደወትሮው ስለማኅበረ ቅዱሳን የምናትተው ሰፊ ጽሁፍ የለንም። ማኅበሩ እያጣጣረ ነው። ለጊዜው ትንሽ መቆየቱ የእድገት መጨረሻውን አያስቀጥለውም።  ይሁን እንጂ ይህ የብላቴ ትራፊ «አንዲት ጥይት ወይም ሞት» በማለት የጥንት ቃል ኪዳኑን ለማደስ እየተንፈራገጠ ነው።
ለዚህም በመሞትና በመዳን መካከል እየተንፈራገጠ ያለው ማኅበረ ቅዱሳን ራሱን ለማዳን እየታገለ ይገኛል። ለመዳን የሚያደርጋቸውን ትግሎች በአጭር በአጭሩ በነጥብ ሲቀመጡ ይህንን ይመስላሉ።


1/ በሙስናና በአስተዳደር ብልሹነት ሊጠየቁ የሚገባቸው አስተዳዳሪዎችና ፀሐፊዎች አዲሱን ስልቴን እየተቃወሙት ነው በማለት ራሱን ደብቆ ለቤተ ክህነት የለውጥ ማሻሻያ ህግ አያስፈልጋትም የተባለ አስመስሎ ማሳየት ይፈልጋል።

2/ ህጉ ከየትምና ከማንም ይመንጭ ለቤተ ክህነት ስለማስፈለጉ ብቻ እንተማመን በማለት የሕጉን ምንጭ ማንነት እንዳይገለጥ በአስፈላጊነቱ ስር ሸሽጎ ለማስቀጠል ይፈልጋል።

3/ ከአባ አማቴዎስ፤ ከአባ ሉቃስ፤ ከአባ እስጢፋኖስ እና ለጊዜው ስማቸው መጥቀስ ከማንፈልጋቸው ሌሎች ጳጳሳት ጀርባ ተጭኖ የህጉን አስፈላጊነትን በማጦዝ ሲኖዶሳዊ ለማስመሰል በትጋት ይሰራል።

4/ ስለህጉ እጹብ ድንቅነትና ትንግርታዊነት በመረጃ መረብና በስመ ነጻ ሚዲያ ጋዜጦች ላይ በመለፈፍ የምርጫ ዓይነት ቅስቀሳውን በህዝብ ውስጥ በማስረጽና በጳጳሳቱ መካከል የወደፊት በል  ዘመቻውን ለማስቀጠል  ድፍረት የሚሆናቸውን ኃይል በማስታጠቅ ላይ ተጠምዷል።

5/  በካህናት ሽፋን፤  የጥምቀት ተመላሾችንና የተወሰኑ አባላት ምእመናኑን በማሰለፍ በፓትርያርኩ ላይ ጫና በማሳደር የሰማይ ተሰበረ ሽብሩን በመንዛት ላይ ላይ ይገኛል።
እነዚህ ከብዙ በጥቂቱ የተዘረዘሩት እስትንፋሱን የማስቀጠል ዘመቻው ጊዜ ከሚገዛለት በስተቀር በፍጹም ሊታደጉት አይችሉም። ምክንያቶቹ፤
ሀ/ በቤተ ክህነት አጠቃላይ መዋቅራዊ ማሻሻያና የለውጥ እስትራቴጂ ጥናት አስፈላጊነትን የተቃወመና የሚቃወም ማንም የለም። ሊቃወምም አይችልም።

ለ/ የለውጥ ጥናቱ መምጣት ያለበት  ከሲኖዶስ ውስጥ የሚመነጭ ሆኖ በሊቃውንቱ፤ በምሁራኑ፤ በካህናቱ፤ በአዋቂዎቹና በህግ ባለሙያዎች የሚዘጋጅ እንጂ ከማኅበረ ቅዱሳን ጡንቻ ነጻ የመሆን አቅምና ጠባይ በሌላቸው አባ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ የማዘዝ ስልጣንን ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም  ዓላማን የማስፈጸም ግብ ሊሆን አይችልም።

ሐ/ በመሰረቱ ማኅበረ ቅዱሳን ለቤተ ክርስቲያኒቷ ምኗም አይደለም። ቤተ ክርስቲያን ነጋዴ አይደለችም። እሱ ግን የሚታይ የሚጨበጥ የንግድ ተቋም ያለው ግልጽ ነጋዴና አትራፊ ድርጅት ነው። በዐውደ ምሕረቷ ላይ የሚነግድ ይህ ድርጅት የንግድ ጠረጴዛው መገልበጥ አለበት። በጅራፍም ሊባረር የተገባው ነው። ስለዚህ በምንም ዓይነት መልኩ ወርቅና አልማዝ አቅርቤአለሁ ቢል ተቀባይነት ሊኖረው አይችልም።

መ/ ማኅበረ ቅዱሳንን የሚደግፉ ሊቃነ ጳጳሳት በግልጽ ቋንቋ ስንናገር፤

ሀ/ በቤተ ክርስቲያኗ ሕግና ደንብ መሰረት ለጵጵስና የሚያበቃ ሥነ ምግባር በጭራሽ የሌላቸው ናቸው።

ለ/ በዘር ፖለቲካ የተለከፉና ኢህአዴግ እንደጉም ተኖ፤ እንደጢስ በኖ  ይጠፋ ዘንድና  የራሳቸውን ሥርወ ቤተ ክህነት ለመትከል የሚናፍቁ ናቸው።  ከዚህ የወጣ  ደጋፊ የለውም።
በተለይ አባ እስጢፋኖስ ለማኅበሩ ጥብቅና የመቆማቸው ነገር በፍቅሩ ስለተቃጠሉ አይደለም።  ጵጵስና ስሙና ታሪኩ ክብር ያጣው ጸሊማን አርጋብ በምግባር /ጥቋቁር እርግቦች/ የሆኑ ቦታውን ከወረሩት በኋላ ነው። አባ እስጢፋኖስ ኮተቤ ያሰሩት የሚሊዮን ብሮች ግምት ቤታቸው የተሰራው በደመወዛቸው ነው?  መነኩሴ እናቱም አባቱም ቤተ ክርስቲያን ናት ስለሚባል እስኪ ለቤተ ክርስቲያን የውርስ ኑዛዜ ይስጡ!!
ስለዚህ እስትራቴጂ፤ ጥናት፤ ስብሰባ፤ ተቃውሞ፤ ስነ ምግባር፤ ሙሰኛ ወዘተ በሚሉ የቃላት ማደናገሪያ ቤተ ክህነቱ እጁ ሲጠመዘዝ አሜን ማለት የለበትም። አካፋን አካፋ ማለት የሚገባው ወቅት ቢኖር አሁን ነው። ቤተ ክህነት ችግሮቿን ታውቃለች። ለችግሮቿም መፍትሄ ማመንጨት አይሳናትም። የወላድ መካንም አይደለችም። ስለዚህ በፓትርያርኩ አመራር ከራሷ ልጆች በወጣ ህግ ለችግሮቿ መፍትሄ መስጠት አለባት እንጂ በማመልከቻና በደጋፊ ብዛት መጠምዘዝ አይቻልም። 
የማኅበረ ቅዱሳን ስፍራው መናገር ካስፈለገ ሼር ካምፓኒ/ የአክሲዮን ማኅበር መሆን ብቻ ነው። አዲዮስ ማኅበረ ቅዱሳን ከማለት ውጪ በዚህ ማኅበር ስንታመስ መቆየት ያብቃ!!  በዚህ ማኅበር ዙሪያ ከቤተ መንግሥቱ የተሰማውን መረጃ በሌላ ጽሁፍ ይዘን እንመለሳለን።