Saturday, January 18, 2014

የማኅበረ ቅዱሳን የግል ጋዜጦች ዘመቻና የሐራ ተዋሕዶ ጭቃ ሹምነት የትም አያደርስም!!





ደጀ ሰላም የተባለችው የማኅበረ ቅዱሳን ብሎግ ከተዘጋች በኋላ የጭቃ ሹምነቱን ሥልጣን የተረከበችው «ሐራ ዘተዋሕዶ» ብሎግ አንድም ቀን ተሳስታ ነገረ ወንጌል ሳታስተምር በነገረ ወሬ ጫሪነቷ እነሆ አንድ ዓመቷን አከበረች። የሐራ ዘተዋሕዶ ብሎግ አገልግሎት በወሬ ነጋሪነት ላይ ጊዜዋን የማጥፋቷ ምክንያት በማኅበሩና በዙሪያው ስላሉት የመርሃ ስብከት መልእክት በሙሉ «በማኅበረ ቅዱሳን» ዋናው ድረ ገጽ ስለሚተላለፍ «ሐራ» ስለወንጌልና ስለማኅበሩ አዳዲስ ዜና መዘገብ አይጠበቅባትም። ይህ የሚያሳየው የማኅበሩ  አመራር ቁጭ ብሎ እንዴት መተላለፍ እንዳለበትና ምን መተላለፍ እንደሚገባው በደንብ የመከረበት መሆኑን ያሳያል።
 ሰሞኑን ደግሞ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ ለመቸከል ያዘጋጁትን የአፈና እቅዳቸው መግቢያ መንገድ ይሆን ዘንድ የነደፉት የጥናትና ስትራቴጂ መርሃ ግብር በሐራ ዘተዋሕዶ ላይ  ብቻ እየለቀለቁ ዜና መስራት ስላቃታቸው የግል በተባሉ ጋዜጦች ላይ የጥናት ጩኸታቸውን ማስተጋባት ከጀመሩ ሳምንት አልፏቸዋል። ሐራ ደግሞ በማኅበሩ አባላት በጋዜጦች ላይ የወጡትን ዜና ወዲያው እንደ አዲስ ዜና ተከትላ ትለጥፋች።

ማኅበሩ የጳጳሳት አባላት ብቻ ሳይሆን በህክምና ሆስፒታሎች፤ በፌዴራል ፖሊሶች፤ በፍርድ ቤቶች፤ በትምህርት ሚኒስቴር፤ በመንገድ ትራንስፖርትና በመሳሰሉት መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ በግልጽና በስውር የሚሰሩ ምልምል አባላት እንዳሉት እርግጥ ነው።በግል ጋዜጦች ላይ የሚሰሩ አባላቱም በስም ጭምር የሚታወቁ እንዳሉም የአደባባይ ምስጢር ነው። ስለሆነም በፈለገው ጊዜ የፈለገውን መረጃና ዜና በፈለገው ጋዜጣ ላይ ለማውጣት የሚቸገር ባለመሆኑ የመረጃ መረቡን በቂ ሽፋን መስጠት ያቃታትን «ሐራ ዘተዋሕዶ» ብሎግን ለማስተንፈስ በስመ ነጻ ሚዲያዎች ላይ ያቀረበውን ጥናት ለመተግበር እንዲቻልና  ተፅዕኖ ለማሳረፍ ሲል በስመ አባ እስጢፋኖስ፤ በስመ ሰንበት ተማሪ አለያም ማን እንደዘገበው ስም ሳይገለጽ ጋዜጣ ላይ እንዲለቀለቅ ለማድረግ ውጣ ውረድ የለበትም።


በእርግጥ በስመ ነጻ ሚዲያ የሚታተሙት የኢትዮጵያ ጋዜጦች አብዛኞቹ ይህንን ያህል ትኩስና የአንባቢን ቀልብ በሚስብ መረጃ በቂ ልምድና ብቃት ያላቸው ስላልሆኑ ከጊዜ ማሳለፊያ ዜናነት ባለፈ ለማኅበረ ቅዱሳን ጥረት ውጤታማ ጎን ያስገኛሉ ተብሎ አይጠበቅም። ግማሾቹ የፕሬስ ህጉን ስለሚፈሩ እንደዱሮው በሬ ወለደ ብለው በመጻፍ ጉድ፤ ድንቅ የሚያሰኝ ፈጠራ ላለማቅረብ ራሳቸውን በራሳቸው ሳንሱር በማድረግ የተቸገሩ ናቸው። ገሚሶቹም «አቶ እንትና ተከሰሰ፤ ወ/ሮ ብሪቱ ቲማቲም ሸጠው ትርፋማ ሆኑ፤ ዓለማየሁ አዲስ ሆቴል ከፈተ » በሚል የተለመደ ዜና የሚውተረተሩ ስለሆነ የማኅበረ ቅዱሳንን የጥናት ወረቀት ተቀብለው ዜና ቢሰሩ ለጊዜ ማሳለፊያነት ማንበብ ከሚቻል ውጪ በዚያ ንባብ ስለጥናቱ የድጋፍ ይሁን የተቃውሞ ሰልፍ የሚወጣ እንደሌለ በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ብዙዎቹም /tabloid /ወሬና ጭምጭምታ በመለቃቀም፤ የኮከብ ቆጠራና ታሮት በመተረክ፤ ስሜታዊ ፈጠራ ላይ የሚያተኩሩ ናቸው። society reporting/ ማኅበራዊ ዜና የሚሰሩ፤ ስለምግብ፤ ፋሽን፤ ስለቁንጅና የሚተርኩ ናቸው። comedic 
/ ዋዛና ፈዛዛ፤ ቀልድና ቧልት የሚዘግቡ ሲሆኑ በተወሰነ መልኩ gonzo journalism / የተሻለ ምልከታ አለው። ራሱ የመረጃው ምንጭ ሆኖ በመጀመሪያ ረድፍ የሚዘግብ ሲሆን በያዘው አሳማኝ ጭብጥ ለመረጃው ኃላፊነትን የሚወስድ ነው። አሉ፤ ሰማሁ፤ ሰዎች ነገሩኝ አይልም።  /Investigative journalism/ የምርመራ ጋዜጠኝነትን ባህል የተከተለ ጋዜጣ ኢትዮጵያ ውስጥ የለም ብቻ ሳይሆን አይታሰብም። ታዲያ ከዚህ አንጻር የማኅበሩ ስውር ጋዜጠኞች ጽሁፍ በደረጃ በየትኞቹ ጋዜጦች ላይ የሀ/ስብከቱን የጥናት አስፈላጊነት አከታትለው አወጡ ብለን ብንጠይቅ ግልጽ መልስ አናገኝም።  በቃ ዜና ሆኖ መውጣቱ ብቻ በቂያቸው ነበርና ለማውጣት ማውጣት በቻሉት ጋዜጣ ላይ ሁሉ ዜና ሆኖ እንዲወጣ ደክመዋል። ውጤቱ ድካም ሆኖ መቅረቱ ግን ያሳዝናል።

ምናልባት 50 ሚሊየን ተከታይ አለኝ የምትለዋን ቤተ ክርስቲያን የሚመሩት ሹመኞች «አንድ ለእናቱ» የሆነውና ያውም በየወሩ አንዴ ከሚታተመው «ከዜና ቤተ ክርስቲያን» ውጪ ለጋዜጦች ዜና ባይተዋር ስለሆኑ ዛሬ ምን ተባለ? አዲስ አድማስ ምን ይዞ ወጣ? በማለት እንደአዲስ የመረጃ ምንጭነት የጽሁፉ ስውር ባለቤት የሆነው  ማኅበሩ እንደአዲስ ግኝት ሲነግራቸው በመባነን ተደንቀው ከሚያነቡት በስተቀር ለማኅበሩ የዜና ስራ ድካም አንዳች ትርፍ ለማስገኘት የሚችል ተጨባጭ ነገር እንደሌለው እርግጥ ነው።
«ድከም ያለው ውሃ ይወቅጣል» እንዲሉ ማኅበሩ አንዴ በሐራ ተዋሕዶ፤ አንዳንዴ በግል ጋዜጦች፤ አንዴ በሰንበት ተማሪዎች፤ አንዴ በጥምቀት ተመላሾች፤ ሌላ ጊዜ በጳጳሳት በኩል የሚወጣ፤ የሚወርደው ለአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ተጨንቆ ሳይሆን የራሱን መዋቅር በሀ/ስብከቱ ችግር አስታኮ ለመዘርጋት ከማለም የመነጨ ስለሆነ እንደታወቀበት ስንነግረው ፈጽሞ አይገባውም። 


አሁን ደግሞ የያዘው አዲስ ስልት ፓትርያርኩን በውዳሴ ከንቱ ጠልፎ በአንድ ጀንበር የጥናቱን ተአምር ለማሳየት ተዘጋጅተዋል የምትል ዜና ደጋግሞ ማሰማት ጀምሯል። ወደኋላ ያፈገፍጉብኛል ብሎ ስለሰጋ ብርታት ሰጪ የምስጋና መርፌ እየወጋ መሆኑ ነው። ቤተ ክህነትን በማኅበሩ ያስወረራት የሚያዥጎደጉደው ውዳሴ ከንቱ፤ ጥቅማ ጥቅምና በስለላ የሚሰበስበው የግለሰቦች የነውር ፋይል ናቸው። ስለዚህ ፓትርያርክ ማትያስ ቤተ ክርስቲያኒቷ ያለማንም ጣልቃ ገብነት በራሷ ልጆች፤ በራሷ ሊቃውንት፤ ለራሷ የሚሆን ሕግ ማውጣት ትችላለችና ማኅበሩ በግል ጋዜጦች፤ በወጣቶችና በጳጳሳት በኩል ጫና ለማሳደር የሚያደርገውን ዘመቻ እንዳይፈሩ እናሳስባለን። የማኅበረ ቅዱሳን የጋዜጦች ላይ ዘመቻና የሐራ ዘተዋሕዶ የጭቃ ሹምነት የትም አያደርስም!!