ክርስትና በደም ተመስርታ፤ በፈተና ወጀብና ማዕበል እየተገፋች እነሆ ዛሬ ላይ ደርሳለች። ዓለም አንድ መንደር ሆናለች፤
ህግና ህግ ብቻ ዓለምን ይመራታል በተባለበት በ21ኛው ክ/ዘመን ላይም ክርስትና ሞትና የእሳት አደጋ አልተለያትም።
የሚገርመው ደግሞ ክርስትና በእጇ የሚገኘውን መጽሐፍ ቅዱስ ይዛ ከመጓዝ ባሻገር ለእምነቷ መስፋፋት ጦርና ሰይፍ የማትመዝ
ቢሆንም ባላጋራዎቿ እንዳትመጣባቸው ለመከላከል ሲሉ ወይም ከመጣች በኋላ ለማጥፋት ሲሹ በተቃራኒው ሰይፍና ጦር እየመዘዙባት ዘመናትን
ማስቆጠሯ ነው።
ይህንን መከራ ካሳለፉት ጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት
መካከል የሶርያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን( የአንጾኪያ) ወይም ያዕቆባዊት ቤተ ክርስቲያን ግንባር ቀደሟ ቤተ ክርስቲያን ናት። በሐዋርያት ሥራ 11፤26 ላይ እንደተመለከተው «ሐዋርያት በመጀመሪያ ክርስቲያን
ተባሉ» የሚለውን ቃል የክርስትናቸው መነሻ አድርገው የሚቆጥሩት ሶርያውያን ክርስቲያኖች፤ በሮማውያን፤ በፋርሶችና፤ በቱርኮች ወረራ
ብዙ ግፍና መከራ ያሳለፉ ሲሆን ሶርያ ወደእስላማዊ ግዛት በእስላም ወረራ ከተለወጠችበት ጊዜ ጀምሮ ስቃይና ፈተናው ተጠናክሮ እንደቀጠለ
ታሪክ ይነግረናል። ሀገሪቱ በአላዋይት የእስልምና ጎሳ በምትመራበት ዘመን የተሻለ ሰላም የነበራት የሶርያ ቤተ ክርስቲያን ዐረባዊ
ዐመጽ በዐረብ ሀገራት ከተቀጣጠለ ጊዜ አንስቶ ግን ሰላም ርቋት፤ ገዳማቷ ፈርሰው፤ መነኮሳትና መነኮሳይያቷ ተገድለው፤ ክርስቲያኖቿ
ተሰደው፤ አድባራቷ ተቃጥለው ዛሬ ላይ ወደመጥፋት ከተቃረቡት ጥናታዊ አብያተ ክርስቲያናት መካከል አንዷ ወደመሆን ደርሳለች።
በሰሜን ሶሪያ ወናውን የቀረው ገዳም |
እስካሁን በዓለም አቀፍ አኀዛዊ መረጃ መሠረት 400, 000 ክርስቲያኖች የተወለዱበትንና ያደጉበትን ቀዬ ለቀው እግራቸው
ወደመራቸው ተሰደዋል። 60 ትላልቅ ጥናታውያን አድባራትና ገዳማት ተቃጥለዋል። ከዚህ ውስጥ ለአብነት የሚጠቀሰው የጦርነቱ ቀውስ
በክርስቲያኖቹ ላይ ያደረሰው በደል በታህሳስ ወር መጨረሻ ገደማ ላይ 13 መነኮሳይያት ጦርነቱን ሸሽተው ከተሸሸጉበት ገዳም ውስጥ
እጃቸው በጽንፈኞቹ ተይዞ እንደመደራደሪያ መሣሪያ መቆጠራቸው አይዘነጋም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሱኒ/ወሀቢዝም ጽንፈኞች ባሉበት ቦታ
ሁሉ ከሳዑዲ ጋር ከጀርባ የማትጠፋው ኳታር ከሊባኖስ መንግሥት ጋር ባደረገችው ሽምግልና አሸባሪዎቹ በመነኮሳይያቱ ላይ ምን ጉዳት
እንዳያደርሱና እንደመያዣ መጠቀማቸውን አቁመው በነጻ እንዲለቋቸው በማግባባቷ መለቀቃቸውን የሊባኖሱ ዴይሊ ስታር መዘገቡ አይዘነጋም።
ይህንኑ ዘገባ የኳታሩ «አልጀዚራ ሙባሸር» ቴሌቪዥን መነኮሳይያቱን
በምስል በማሳየትም ጭምር የኳታርን ትስስርና የማንነት አቅም መረዳት ችለናል።
በኳታሩ አልጀዚራ ሙባሸር ቲቪ ከቀረቡት የታፈኑ መነኮሳይያት በከፊል |
ይህ በዚህ እንዳለ ብዙ ሶርያውያን ክርስቲያኖች በዚያው ያሉ ሲሆን፤ የሚመጣውን ሞት ለመቀበል የተዘጋጁ መነኮሳይያትና
መነኮሳት ከሶርያ ገዳማት እስካሁን አልወጡም። ከእነዚህ መካከል አንዱ የሆኑት ፋዘር ኢዮአቄም የተባሉት ካህን ለሚዲያ እንደገለጹት
የሚመጣውን ሁሉ እዚሁ ሆኜ ከመቀበል በስተቀር የትም ለመሄድ አልተዘጋጀሁም። አያይዘው እንደተናገሩት «የሶርያ ክርስቲያኖች ስደትና
እንግልት ግን ልቤን ያደማዋል፤ ይህ ሁሉ ለምን ሆነብን? እያልኩ አምላኬን እጠይቃለሁ» በማለት የተሰማቸውን መንፈሳዊ ስብራት ለጋዜጠኞች
ገልጸዋል።
የሶርያ ክርስቲያኖች እየደረሰባቸው ያለው እንግልትና መከራ ትኩረት አግኝቶ ዓለም አቀፍ ክርስቲያኖች ሁሉ ከጎናቸው በመቆም
ለችግራቸው በአፋጣኝ እንዲደርሱ የሚያሳስብ ጉባዔ በአሜሪካ የተደረገ ሲሆን በተለይም ምሥራቃውያን ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት
ፕሮግራሙን በጸሎትና እየጠፉ ላሉት ክርስቲያኖች እንድረስላቸው የሚል ጥሪ በማስተጋባት ማሰማታቸው ታውቋል። ይህንንም ተከትሎ የአሜሪካ
መንግሥት በጎረቤት ሀገሮች ላይ ጫና በማሳደር የበኩላቸውን ሚና እንዲጫወቱ የሚያሳስብ መልዕክት እንድታስተላልፍ ጥሪ የቀረበላት
ሲሆን ሳዑዲና ኳታርም የበሽር አልአሳድን መንግሥት በመጣሉ ዘመቻ ላይ ባላቸው ድርሻ ተዋጊዎቹ በክርስቲያኖች ላይ የሚያደርሱትን
ጥቃት እንዲያቆሙ ጥሪ ቀርቧል።
ወሀቢያዊና ሰላፊያዊ የዐረብ ዐመጽ ከተነሳ ወዲህ በዐረብ
ሀገራት የሚገኙ ክርስቲያኖች መከራ፤ስደትና ሞት ከመቼውም ጊዜ የከፋ ቢሆንም እስካሁን የተደረገው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።
አሸባሪዎች በሶርያ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ |
ከዚህ በፊት የሶርያ፤ አሌፖ ከተማ ሊቀጳጳስ ፖል ይዚጊ በአሸባሪዎቹ
ታፍነው ከተወሰዱ በኋላ በብዙ ድርድር ሲለቀቁ በሶርያ የፍራንሲስካን ቄስ የነበሩት ፍራንሶይስ ሙራድ የተባሉት ደግሞ አቡ ባናት በተባለው የአሸባሪዎቹ አለቃ ሌሎች
ሦስት ሰዎችን ጨምሮ በሰይፍ« አላሁ አክባር» እያለ እንዳረዳቸው መረጃዎች ያሳያሉ። በኢራቅም ከነበሩት ክርስቲያኖች ውስጥ በመቶ
ሺዎች ሀገራቸውን ለቀው ተሰደዋል። በግብጽ፤ በቱኒዚያ ያሉት ክርስቲያኖችም ለመኖር የሚያበቃ መንግስታዊ ጥበቃ ስለሌላቸው እየተሰደዱ
ይገኛሉ።
ከቀኝ ወደግራ በሁለተኛው ረድፍ የሚገኘውና አቡ ባናት (የእስላም ሴቶች አባት) የተባለው የአሸባሪዎቹ አለቃ ቄስ ፍራንሶይስ ሙራድንና ሁለት ዲያቆናትን በሰይፍ ያረደ |
የምሥራቅ ኦርየንታል ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዓለም ላይ መከራና
ሞት ለሚደርስባቸው ክርስቲያኖች በዘወትር ጸሎቷ እንደምታስባቸው ቢታወቅም በኦፊሴል የጸሎትና የዓለም ክርስቲያኖች ኅብረት ለተጎጂዎች
በፍጥነት እንዲደርስ ማሳሰብ ብትችል መልካም ነበር። በተለይም በአሁኑ ሰዓት ገዳማትና አድባራቷ እየወደሙ፤ክርስቲያኖቿ እየተሰደዱ፤
እየታረዱ፤ ለምትገኘው ለሶርያ ያዕቆባዊት ቤተ ክርስቲያን፤ የኢትዮጵያ
ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እንደአኀት ቤተ ክርስቲያንነቷ አጋርነቷን አለማሳየቷ ያሳዝናል።
የክርስትና ምልክት መስቀል አንገታቸው ላይ በመገኘቱ ብቻ ክርስቲያኖች በገፍ እያተረዱ ነው |
ለሶርያ ቤተ ክርስቲያን ሀዘንና
ድምጽን ማሰማት የፖለቲካው ክፍል ፈቃድ የሚያስፈልገው ሳይሆን የክርስቶስን አገልግሎት መፈጸም መሆኑ መታወቅ ይገባዋል። በሶርያ
ቤተ ክርስቲያን ላይ የእጅ አዙር መንግሥታት ሰይፍና ጦር ሲልኩ ያላፈሩ እኛ በጸሎትና በድምጽ ክርስቲያን ወንድሞቻችንን ለማጽናናት
የሚያስፈራን ነገር ሊኖር ባልተገባ ነበር። እዚያ ያለው እሳት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይመጣ ድምጻችን መሰማት ያለበት ዛሬ ነው።