Friday, January 3, 2014

አዲዮስ ማኅበረ ቅዱሳን፤ አዲዮስ!!



ስጳኛውያን ደህና ሰንብት፤ ደህና ሁን! ብለው ሲሰናበቱ «አዲዮስ!» ማለት ልምዳቸው ነው። እኛም ይህንን ቃል ተውሰው ሲናገሩ እንደቆዩት አበው ዛሬም ለማኅበረ ቅዱሳን «አዲዮስ» ብለነዋል።
መነሻ ምክንያታችን ሁለት ነው።
1/ ማኅበሩ ራሱ እያደገ ከመጣበት የኢኮኖሚ አቅምና የመዋቅር ስፋት አንጻር በቤተ ክርስቲያኒቱ ስር ተጠልሎ ያለስጋት መዝለቅ እንደማይችል በመረዳቱ  ወደ «ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት» ወይም ሼር ካምፓኒ የመዛወር ፍላጎት እንዳለው ውሰጥ አወቅ ምንጮች በመጠቆማቸው የተነሳ ይህ እውን ከሆነ ለዓላማው ስኬት የምንሰጠው ድጋፍ «ማኅበረ ቅዱሳን አዲዮስ» በማለት ነው። Good bye MK!!
2/ በ23/ 4/2006 ዓ/ም  በጠቅላይ ቤተ ክህነት አዳራሽ ከፓትርያርኩ ጋር ተገናኝተው በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ ሊተገበር በተፈለገው የማኅበረ ቅዱሳን ድርጅታዊ ጥናት ላይ የቀረበው የአስተዳዳሪዎችና የማኅበረ ካህናቱ ተወካዮች የተቃውሞ ሃሳብ ማኅበረ ቅዱሳን ከቤተ ክርስቲያን ታዛ ተገፍትሮ የመውጣቱን የጅማሬ ያመላከተ በመሆኑ «አዲዮስ ማኅበረ ቅዱሳን» ብለነዋል።
3/  በማኅበረ ካህናቱ መካከል ካለን መረጃ አንጻር ከዚህ በፊት «የማኅበረ ቅዱሳን መግነንና ብቀላ መሳ ለመሳ ናቸው፤ እንደጠዋት ጤዛም ቀትር ላይ ይጠፋሉ!» በሚል ርዕስ ባወጣነው ጽሁፍ ላይ እንደዚህ የሚል ቃል ጠቅሰን ነበር።
« ምናልባትም የማኅበረ ቅዱሳን በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ውስጥ የማቡካት የመጋገር ጅማሮ የማኅበሩን ዕድሜ ቀጣይነት ወሳኝ ምዕራፍ ከፋች ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። በሂደት የምናየውም ይሆናል» (የጥቅሱ መጨረሻ)
ይህንን ጽሁፋችንን ወደተግባር ስለመቀየሩ የሚያመላክቱ ክስተቶች በቤተ ክህነቱ ደጃፍ በተግባር እያስተዋልን ነው። ወደፊት ማኅበሩ ራሱን እንዴት ሊከላከል ይችላል? በመናጆ ጳጳሳቱ በኩል እስከየት ይራመዳል? የሚሉ ጥያቄዎቻችን እንዳሉ ሆነው አሁን ያለው የማኅበረ ካህናቱ ድምጽ የማኅበሩን ረጅም ጉዞ በትክክል ባለበት አቁሞታል ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ከዚህ በላይ እንዳይሄድ አስሮታል ማለት ይቻላል።
 አሁን በተያዘው የአስተዳዳሪዎችና የማኅበረ ካህናቱ አጠቃላይ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ያለው ተቃውሞ ቀጣይነት የማኅበሩን እድሜ ቀጣይነት ወሳኝ ምዕራፍ ከፋች መሆኑን አሳይቶናል። ለዚህ የሚጠቀስ በማኅበሩ ላይ በስብከተ ወንጌል አዳራሽ የቀረበው ተቃውሞ በጣም ከፍተኛ ሆኖ መገኘቱ፤ ፓትርያርኩም የካህናቱን ጥያቄ ተፈጻሚ ለማድረግ ቃል መግባታቸው አረጋጋጭ መሆኑ ነው።
በአዳራሹ ውስጥ የተገኙትና በማኅበረ ቅዱሳን የስም ማጥፋት ዘመቻ የተከፈተባቸው፣ እንዲሁም በተገኙበት ቦታ በስውር እንዲገደሉ የተወሰነባቸው ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ እንዲህ ሲሉ ደስታቸውን መግለጽ እስኪሳናቸው ድረስ ለማኅበረ ካህናቱ መናገራቸው ታውቋል።
« ማኅበሩ አሉ ብፁዕነታቸው፤ ማኅበሩ እስከሞት ድረስ እንደሚፈልገኝ አውቃለሁ፤ እንድንስማማ ለማባበል ቢሞክር አለመቀበሌ ቢያበሳጨው ስም ማጥፋትና ልዩ ልዩ ዘመቻ እንደዘመተብኝም ለሁላችሁ የተሰወረ አይደለም። ስላልቻለ እንጂ እንደእቅዱ እስከዛሬ እኔ የለሁም። የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ አሟሟት ራሱ ምስጢር ነው። የብፁዕ አቡነ መርሐ ክርስቶስ አሟሟት ራሱ ስውር ነው። ማንም እግዚአብሔር ካዘጋጀለት የሞት እድሜ ባያልፍም አሟሟት ሁሉ አንድ አይደለም። ስለዚህ ይህ ስውር አሟሟት ከተዘጋጀላቸው ሰዎች አንዱ እኔ ነኝ። ድሮ ብቻዬን የሆንኩ ያህል ይሰማኝ ነበር። ለካስ አጠቃላይ ማኅበረ ካህናቱ በዚህ መሰሪ ማኅበር ላይ ያለው እውቀትና ምሬት እኔ ከምጠብቀው በላይ ነበር። ሳልሞት እንኳን ይሄንን ለማየት በቃሁ እንጂ ከእንግዲህ ለምን ነገ አልሞትም፤ የቤተ ክርስቲያን ትንሣዔ መድረሱን ዛሬ አየሁ! ሲሉ ከፍ ያለ ጭብጨባና እልልታ በአዳራሹ አስተጋባ። አስተዳዳሪዎቹም በመረጃና በማስረጃ ስለማኅበሩ ያለውን አመለካከት የገለጹ ሲሆን ለአብነትም «ማኅበረ ቅዱሳን በሚሊዮኖች ብር እንደሚያንቀሳቅስ እናውቃለን፤ ለቤተ ክርስቲያን ፐርሰንት አይከፍልም፤ ለመንግስት ታክስ፤ ቀረጥ አይከፍልም። ይነግዳል፤ ያስነግዳል። በየዐውደ ምህረቶቻችን ይሸጣል፤ ይለውጣል። የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት የራሱ ምልምል አድርጎ ያደራጃል፤ ይሰልላል። ወንጌል ሰባክያንን ይነቅፋል፤ ይወነጅላል፤ ያስፈራራል። ታዲያ እንዲህ ዓይነቱን በሕጋዊነት ሽፋን የማፊያ ስራ የሚሰራ ማኅበር የምንሸከመው እስከመቼ ነው? ሲሉ ይጠይቃሉ። እኛ ይፍረስ ወይም ይጥፋ አንልም። የቤተ ክርስቲያኒቱ አባል ነኝ ካለ ሀብትና ንብረቱን በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ያስመዝግብ፤ ገቢውን ያሳውቅ። እንደአንድ ማኅበር በሚፈቀድለት ልክ ይኑር። አልፈልግም ካለ ግን ራሱን ችሎ ቢሻው የእርዳታ ድርጅት፤ ቢሻው ኢንቨስተር ሆኖ በመንግስት አስፈቅዶ በሕግ ስር ይኑር። ዐመጻ ከፈለገ ደግሞ መንግስት እንዲያስታግስልን አቤታችንን እንቀጥላለን በማለት ተራ በተራ ለፓትርያርኩ አስረድተዋል።
ጉዞውን ጀመርን እንጂ አልጨረስንም፤ እስከ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮና  የተወካዮች ምክር ቤት ድረስ እንዲህ እንደዛሬው ተሰብስብን ጩኸታችንን እናሰማለን። ማኅበረ ቅዱሳንን እንዲያስታግስልን ሰላማዊ ሰልፍ እንወጣለን» በማለት ምሬታቸውን መግለጻቸውን ለመረዳት ተችሏል።  በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ ስለተጀመረው የስራ ዋስትና የሚያሳጣው የማኅበሩና የጳጳሱን ጥናት በተመለከተም  አስተዳዳሪዎቹና ማኅበረ ካህናቱ በአንድ ድምጽ እንደተናገሩት « ቤተ ክርስቲያናችንን የሚጠቅም፤ የማኅበረ ካህናቱን ችግር የሚፈታ፤ ሙስናን፤ አድልዎን፤ መልካም ያልሆነ አስተዳደርንና በአጠቃላይ ያሉብንን ችግሮች መቅረፍ የሚችል ጥናትና እቅድ በምሁራን ልጆችዋ፤ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በሕግ አዋቂዎቿና ቅዱስ ሲኖዶስ በሚሰጠው መመሪያ የሚወጣ ማንኛውንም የማሻሻያውን ትግበራ የምንደግፍና ለአፈጻጸሙም የበኩላችንን ድርሻ  ለመወጣት ቃል የምንገባ መሆኑን እየገለጽን ማኅበር በተባለ ድርጅትና በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት የፓትርያርኩ ረዳት ሊቀ ጳጳስ በኩል የመጣውን የማንቀበል መሆኑን አበክረን እናስገነዝባለን በማለት ለፓትርያርኩ በግልጽ ተነግሯል። በአዳራሹ ውስጥ የነበረው ተሰብሳቢ በድጋፍ ስሜቱን  ገልጿል።
ፓትርያርኩም በተፈጸመው ነገር ማዘናቸውን፤ ወደፊትም የቤተ ክርስቲያኒቱን አጠቃላይ ችግር በሚፈታ መልኩ ጥናት ሊደረግ እንደሚገባው፤ ካህናቱ ያልተቀበሉትንና ያልደገፉትን በካህናቱ ላይ በግድ መጫን እንደማይቻል፤ ሁላችንም ለቤተ ክርስቲያናችን ሰላምና እድገት የሚጠቅመውን ማዘጋጀት እንደሚገባን አምናለሁ በማለት ለተሰብሳቢዎቹ የተስፋ ቃል በመስጠት የካህናቱን ድምጽ በጥሞና ሰምተው ምላሻቸውን በጉባዔው ላይ አቅርበዋል። ማኅበረ ካህናቱ የአቡነ እስጢፋን ከቦታቸው መነሳት በትኩረት ያነሱት ጉዳይ ሲሆን እሳቸውን በተመለከተ በሲኖዶስ የሚታየውን ነገር በዚያ ጉባዔ ላይ ይህ ይሆናል ብሎ መናገር ለጊዜው እንደማይቻልና ችግሮችን ከግለሰቦች ጋር ማስተሳሰሩ  ወደፊት አያራምድም በማለት ፓትርያርኩ በወዳጃቸውና ለሹመታቸው በተዋደቁላቸው ሊቀ ጳጳስ ላይ ማተኮር እንደማይገባ ለመምከር ሞክረዋል። እሳቸው እንዲህ ይበሉ እንጂ ማኅበሩን በካህናቱ ጫንቃ ላይ ይዘል ዘንድ የፈቀዱት ሊቀ ጳጳሱ መሆናቸው መስተባበል የሌለበት ጉዳይ  እንደሆነ ለመግለጽ እንወዳለን።
ብዙ ሃሳቦች ተሰንዝረውና የማኅበረ ካህናቱም ጥያቄ ተቀባይነት አግኝቶ የውይይቱ ፍጻሜ ሲሆን የማኅበረ ቅዱሳን ጥናት ግን «አዲዮስ» ተብሏል።
ማሳሰቢያ፦ ለአስተዳዳሪዎችና ማኅበረ ካህናት !
አበው  «የነብር ጅራት አይዙም፤ ከያዙም አይለቁም» እንዲሉ ይህንን በነብር የተመሰለ ጥፍራም ማኅበር የበለጠ እንዳይቧጥጠን ጥፍሩን ከተቻለ መከርከም ወይም ተይዞ ሰው በማይጎዳበት ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ እንጂ አንድ እርምጃ በመጓዝ ውጤት ተገኝቷል ብሎ መቀመጥ የበለጠ እንዲደራጅ እድል መስጠት ስለሆነ ማኅበሩ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ጥጉን እንዲይዝ በሚደረገው ርብርብ ውስጥ እንቅስቃሴያችሁ ቀጣይነት ያለው ይሁን ምክራችን ነው። « ማኅበረ ቅዱሳን» በቅዱሳን ስም የተሰየመ ነጋዴ ቡድን፤ አዲዮስ!!!