Wednesday, January 8, 2014

በሰዓሊተ ምሕረት ካቴድራል የተንሰራፋው የክህደት፤ የዘረፋ፤ የሕገ ወጥ መሬት ንግድና ኪራይ ሰብሳቢነት እውን መንግሥትና ሕግ ባለበት ሀገር የተፈጸመ ነው?


የደ/ም ሰዓሊተ ምሕረት ቅ/ማርያም ካቴድራል
እኩይ ዓላማውን ይዞ ገለልተኛ ቤተክርስቲያን መፍጠር የሚለውን የመናፍቃን ሐሳብና መንግሥትን በሽምቅ ለመዋጋት የሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል የመቃብር ሥፍራ የተሸሸገገው ቡድን 2 ፓትርያርኮች ፣ 3 ጳጳሳትንና ፣ 3 ሥራ አስኪያጆች ደክመውበት መፍትሔ ሳይሰጡት  በአክሲዮንነት ቤተክርስቲያኗን በመዋጋት  አሁንም ቤተክርስቲያኗን እየበጠበጠ ነው፡፡
ሰንበቴዎቹ በ 70 ሺህ ብር ለኢ አማንየን ፤በ50 ሺ ብር ከውጭ ለሚመጣ አስክሬን፤ በ 35 ሺህ ብር ለሀገር ውስጥ የሚሸጡትን ፉካ ንግድ አላቆሙም።




በመንፈሳዊ ቅብብሎሽ ሲያያዝ የመጣ የቤተክርስቲያን የታሪክ መዝገብ የሚያውቀው ትውፊት ስለሆነ በሀገራችን ተጠብቆና ተከብሮ እስከ አሁን መቆየቱ የሚያስመሰግን ነው፡፡ የሚያኮራም ነው፡፡
ነገር ግን በዚህ መንፈሳዊ ትውፊት ውስጥ የግል ፍላጐትን ለማሳካት ነቀፋን የሚያስከትሉ ጠብ፣ ክርክር ወይም ሌላ ሥጋዊ ፍላጎት ወይም የቤተክርስቲያኗን ዶግማ ቀኖናና ትውፊት ያልጠበቁ ድርጊቶች ሰርገው ገብተው ዛሬ ሰንበቴ ማኅበራት መንግሥት ግብር የማይቀበልበት በአቋራጭ መክበሪያ እና የመናፍቃን መሰብሰቢያ ሆኗል፡፡ በምስራቃዊ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የምትገኘው ደብረ ምጥማቅ ሰአሊተ ምህረት ቅድስት ማርያም ካቴድራል በ1969 ዓ.ም ስትመሰረት በወቅቱ ገጠር ልትባል የምትችል ደብር ነበረች፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንዲሁም በ1997 ዓ.ም ተመርቆ አገልግሎት በመስጠት ላይ በሚገኘው ካቴድራል ግንባታ ቦታው በአዲስ አበባ ከተማ ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት አይን ማረፊያ ለመሆን በቃ፡፡ ከዚህም በላይ በማንኛውም አብያተክርስቲያናት የሌለ 200.000.00 (ሁለት መቶ ሺህ) ካሬ ሜትር ይዞታ ባለቤት መሆነኗ ግን ብዙ ሺህ ጠላቶች በቦው ላይ እንዲነሱ አደረጋቸው በቅድሚያ በቁጥር 11 የሚሆኑ አገልጋዮቿ ከካቴድራሉ ይዞታ 18.000.00 (አሥራ ሰስምንት ሺህ ካሬ ሜትር ) ቦታ በመውሰድ ለግል ጥቅማቸው በማዋላቸው ከ 8 ዓመት በላይ በቆየ የፍርድ ቤት ክርክር ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት እስከ ሰበር ሰሚ ይዞታው ለቤተክርስቲያኗ ተፈረደ ይህን ተከትሎ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባለ አደራ  ካቢኔ ከይዞታዋ ላይ በአውደ ምህረቱ ትክክል 7000 ካሬ ሜትር ለግዮን ጋዝ ኃ.የተ.የግ ማኅበር በሊዝ ሸጠው ይህንን ሁሉ ችግር እያለ በሰንበቴ ሽፋን የገቡ 7 ሰንበቴዎች እያንዳንዳቸው ከ1000 ካሬ ሜትር በላይ ቦታ በመያዝ ከዚያው ከቤተክርስቲያኑ በወጣ የድንጋይ ማእድን ትልልቅ አዳራሾችና የቀብር ፉካ በመገንባት የይዞታ ተቀናቃኝ ሆኑ፡፡ (ይህ ቦታ አሁን ባለው የሊዝ ዋጋ ከ850 ሚሊዮን ብር በላይ ይገመታል ) ለእነዚሁ ሰንበቴዎች ቦታውን ከፋፍሎ በመስጠት ጉልህ ስፍራ የነበረው ወልዴ የሺጥላ የተባለው የህንጻ ኮሚቴ ሊቀ መንበር ሲሆን ኤርትራዊው ፎርማን አቶ ጸሐዬ እራሱን ኢንጂነር ብሎ በመጥራት ልኬቱን አከናውኗል፡፡ አቶ ወልዴ የህንጻ ሊቀ መንበር ሆኖ ቤተክርስቲያኗ ላይ ሲያዝና ሲናዝዝ ኖረ ቀድሞ የቴሌ ጉርድ ሾላ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በቂ የትምህርት ዝግጅት ስለሌለው አለኝ ብሎ ባቀረበው ሰርተፍኬት በሽያጭ ሰራተኝነት ተመድቦ ኮተቤ ቅርንጫፍ የሚሰራ ግለሰብ ነው ይህ ግለሰብ  ለሰንበቴ ቦታ አከፋፍሎ ሲጨርስ ለእሱና ለሚስቱ ማረፊያ የሚሆን ዘመናዊ ሰርቪስ ቤት እና 26 የቀብር ፉካ ለቤተክርስቲያኑ ሕንጻ ማሰሪያ ከመጣው ሲሚንቶና አሸዋ  በመገንባት የፉካ ንግዱን ተቀላቀለ፡፡ 


ዛሬ ወልዴ ቅዳሴ የሚያስቀድሰው በቤተክርስቲያኒቱ  ቤተልሔም ጎን በሰራው ሰርቪስ ሳሎን ሶፋ ላይ ጋደም ብሎ ሲሆን መሸት ሲል ደግሞ አየር ለመቀበል ወደ መኝታ ቤት ይገባል፡፡ ለቤተክርስቲያን መላ ዘመናቸውን የደከሙ የቀድሞ ነገስታት እንኳ ያላደረጉትን ድፍረት በመድፈር በቅድስት ቤተክርስቲያን ውስጥ ለራሱ መኖሪያ የሰራ በ 21 ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከእሱ ሌላ መገኘቱን እጠራጠራለሁ፡፡ ሕንጻው ከተመረቀ ከ 6  ዓመታት በላይ አንዳች የልማት ተግባር ሳያከናውን በሊቀ መንበርነት ሕንጻ ኮሚቴ ብሎ የሰየመውን የቤተክርስቲያኗን ሐብት የሚዘርፍበት ኮሚቴ   ከመሰሎቹ ጋር ቤተክርስቲያኗን በአጽሟ አስክትቀር ድረስ ከዘረፋት በኋላ በዚያ ገንዘብ አያት ግቢ ውስጥ ዘመናዊ ባለ ሁለት ፎቅ መኖሪያውን ገዝቶ የቀድሞ ቤቱን አከራይቶ ሲኖር ንቡረ እድ ኤልያስ አብርሃ በነባሩ ሰበካ ጉባዔ አባላት በቀረበላቸው ጥቆማ ቀደም ሲል ጀምሮ ሲፈርምበት ለነበረው ባንክ እግድ በመጻፍ ቋሚ የዘረፋ ገቢውን እንዲቆም አደረጉ፡፡ በወቅቱ የነበረው ሰበካ ጉባዔም ያላለቀውን ቤተክርስቲያን ለማስፈጸም ጥረት ያደረገ ሲሆን ቀድሞ ኮሚሽን የተቀበለባቸውን የሥዕል ሥራ ለሌላ ባለሙያ በመስጠት እንዲጠናቀቅ ከማድረጉም በላይ አጥር የሌላትን ቤተክርስቲያን በአጥር እንድትከበር፤ ዶሙ ዝናብ ያስገባ የነበረውን ሕንጻ 4 ዶሞች አሉሚኒየም በማልበስ ዘመናዊ መጠለያ በመስራት ለካቴድራሉ አቋቋምና ዜማ ትምህርት ቤት የተማሪዎች መኖሪያ የአረንጓዴ አጸዶች ሥራ የመጠለያ ግንባታ እና ወደ ካቴድራሉ በ 3 አቅጣጫ የሚያስገቡ ዘመናዊ ኮብል ስቶን መንገዶችና ሌሎችም  ሥራ ሰርቷል፡፡ የቤተክርስትያኑ አስተዳዳሪ እና የሥራ ባልደረቦቻቸው ለረጅም ዘመን በጭቅጭቅ የቆየውን ይህንን ቦታ በካርታ ለማስከበር ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለው 200.000.00 ካሬ ሜትሩን የሚያረጋግጥ ካርታ ተቀብለውበታል፡፡ በቀጣይ ሰንበቴዎቹ ያለ ከልካይ የሚያደርጉትን ሕገ ወጥ ተግባር ሥርዓት ለማስያዝ በወቅቱ ፓትርያርክ አቡነ ጳውሎስን በመውሰድ የሰንበቴዎቹን ይዞታና ሕገ ወጥ ድርጊት አሳይቷቸዋል፡፡ ቅዱስነታቸውም እንባ እየተናነቃቸው በንዴት ከግቢው እንደወጡ ይዞታውን የወሰዱና ተከራክረው በፍርድ ቤት የተረቱ 13 ሰራተኞች ከቦታው እንዲነሱ በማድረግ ሰንበቴዎቹ ላይ ሕግ እንዲወጣ መመሪያ ሰጡ፡፡
-    ሰንበቴ ማኅበራቱ በካቴድራሉ ግቢ ሚገኘውን የድንጋይ ማእድን እንደፈለጉ   አስፈልጠው በመሸጥ ከፍተኛ ገንዘብ በመሰብሰባቸው፡፡
-    ያለ ፈቃድ በገነቧቸው ሰፋፊ አዳራሾች ውስጥ በኪራይ ኗሪዎችን በማፈራቸው
-    ያለ ቁጥጥር በሚሸጡት ፉካ ከፍተኛ ገቢ በማግኘታቸው
-    በአዳራሾቹ ያልተፈቀዱ ፖለቲካ ስብሰባ በማካሄዳቸው
-    ቤተክርስቲያኗን ሥርዓት በመጣስ በቅዳሴ ሰዓት ግቢን በ40 እና 80 ቀን መታሰቢያ ድግሶች ከድርገት በፊት ምግብ እንዲበላ በማድረጋቸው፡፡
-    ባልተፈቀደ የንግድ ተግባር በመሰማራታቸው
-    በሕገ ወጥ መልኩ ቦታ በመውረር ለብዙኃኑ ጥቅም መስጠት የሚገባውን ቦታ ለግል ጥቅም በማዋላቸው
-    ከቀብር የሚያገኙትን ገንዘብ በሕይወት መድን ዋስትና ዓይነት ለአባላት በጥሬ ገንዘብ የሚከፍሉ በመሆናቸው፡
-    ሁሉን እምነት ያቀፍን ነን ለማለት ወደ በጎ አድራጎት ማኅበርነት ለመቀየር በመንቀሳቀሳቸው፡፡
-    ዛሬም ማንነታቸው በውል የማይታወቅ በወንጀል ጭምር የተገደሉ ሰዎች ከተለመደው የጥቁር አንበሳ መዝገበ ሙታን ውጪ ሳይመዘግቡ የሚቀብሩ መሆናቸው፡
-    በጥበቃ ስም ባስገቡዋቸው ግልሰቦች ምክንያት ቤተክርስቲያን ውስጥ ከፍተኛ ወንጀል እንዲፈጸም የሚያደርጉ በመሆናቸው፡፡
ነበር ሕግ ያስፈለጋቸው፡፡
ነገር ግን ይህን ቤተክርስቲያን ዓመታት ብቻ 10 አለቆች ተደብድበው የተባረሩ ሲሆን ሊቀ ጉባዔ ኤርሚያስ ወልደኢየሱስ፣ መላከ ሰላም ዘለዓለም እሰይ እና መልአከ ሣህል አወቀ ተጠቃሽ አስተዳዳሪዎች ናቸው፡፡
እነዚህ ሰንበቴ ማኅበራት መካከል ዋነኛው የመድኃኔዓለም ሰንበቴ ማኅበር ሊቀ መንበር የደርግ የፖለቲካ ትምህርት ቤት መምህር የመቶ አለቃ አባቡ መሰል የደርግ ዘመን ጓደኞቹን በመጥራት ጥቅማቸውን ለማስቀጠል በቡድን ተደራጁ እዚህ ቡድን ውስጥ የሴት ሰባኪ ሆነችውና ሕጋዊ ባሏንና ሥራዋን ጥላ ከእድሜ አባቶቿ ጋር  በካቴድራሉ ግቢ የቀን ቀን ኑሮዋን የመሰረትችው ቅድስት አሳልፍ ስትገኝበት የቀድሞ የደርግ የምስራቅ ጎጃም አስተዳዳሪውና በቅርቡ ከእስር ተፈታው ስመ ገናናው አንሙት ክንዴ የቀድሞ የደርግ የቀጠና  2 አስተዳዳሪና የአንሙት ክንዴ ዘመድ አስማረ ዋሴ በ1997 ምርጫ የቅንጅት ፓርቲ የወረዳ ኃላፊ ሙሉ በለጠ በቀድሞ መንግሥት ካድሬ አብቡ ታከለው በመሪነት የተሳተፉበት እና ሌሎችም በመንግሥት ላይ ያኮረፉ አብዮታዊ ጡረተኞች ያሉበት ሲሆን በቤተክርስቲያኗ የተዘጋጀውንና ካለ ቤተክርስቲያኗ ፈቃድ ቀብር እንዳይፈጸም፣ በሰንበቴ አዳራሾቹ በካቴድራሉ ግቢ በጥበቃና በጽዳት ስም የሚያኖሩዋቸውን ተዋልደው በካቴድራሉ ውስጥ መንደር የመሠረቱ ግለሰቦችን  በማስወጣት በቤተክርስቲያኗ ሃይማኖታዊ ተቋም ባቻ ሆና እንድትቀጥል፡፡ መናፍቃንን በ70 ሺ ብር መቅበር እንዲቀር፣ የቤተክርስቲያኗን የድንጋይ ማእድን መሸጥ እንዲቆም የሚያዘውን ሕግ እንደማይቀበሉ አስታወቁ፡፡ ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሲያመራ እነዚሁ ቀድሞ መንግሥት መኮንኖችና መናፍቃን ይዦታው የቤተክርስቲያኗ አይደለም በማለት መቃወሚያ አቀረቡ፡፡ ዳኛው እነዚህን ቡድኖች አንድ ጥያቄ ጠየቁ ለመሆኑ ቀብር ትፈጽማላችሁ ሲሉ “አዎ ” አሉ የሰንበቴ ቡድኖች ታድያ ቤ/ክ ግቢ አይደለንም ካላችሁ ቀብር የምትፈጽሙት መንገድ ላይ ነው መልስ አልነበራቸውም ፍርድ ቤቱ ቤተክርስቲያኗ በራሷ ሕግና ሥርዓት አደብ ታስገባቸው ሲል ሥልጣኑን ለቤተክርስቲያኗ ሰጠ፡፡ እስከ ሰበር በደረሰው የፍርድ ሂደት ይኸው ውሳኔ ጸና፡፡ እነ አቶ ወልዴ በዚህ ወቅት አማራጭ ያደረጉት ሟቹን ፓትርያርክ በሚያውቋቸው ሰዎች ማግባባት ነበር፡፡ እናም ፓትርያርኩን የሚያውቁ ግለሰቦችና ባለሥልጣናትን ይዘው ገብተው ፉካ መነገዳቸው ቤተክርስቲያኗን እንደማይጎዳ እና ለማስፋፊያ ቦታ እንዲጨምሩላቸው አነጋገሯቸው ፓትርያርኩም ‹‹የሥራ ተነሳሽነታችሁ መልካም ነው ነገር ግን ይህንን የቢዝነስ ሐሳባችሁን ወደ መንግሥት ውሰዱት በጠቃቅንና አነስተኛ ተደራጅታችሁ ብትሞክሩት ይሻላል እኔ የምላችሁ ይህንን ነው›› በማለት መለሱላቸው ሕጉ ይጎዳናል በማለት ቅሬታቸውን ለወቅቱ ጳጳስ ለአቡነ ቀውስጦስ አቀረቡ አቡኑም እኔ የቤተክርስቲያን ይዞታ ልጠብቅ እንጂ ልሸጥ አልመጣሁም አሏቸው፡፡ ጉዳዩ እልባት ሳያገኝ ፓትርያርኩን አረፍተ ዘመን ገታቸው አቡነ ዳንኤልም የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ሆኑ ሥራ አስኪያጃቸው ሊቀ ኅሩያን ሰርጸ ጋር በመሆን ጉዳዩ ለሀገረ ስብከቱ አስተዳደር ጉባዔ ቀረበ ጉባዔውም በሰንበቴ ስም ተደራጅቶ መነገድ አግባብ አይደለም ቤተክርስቲያኗም በይዞታዋ ተጠቃሚ መሆን አለባት ቀብር መፈጸምም የሰንበቴ ድርሻ ተግባር አይደለም በማለት አስተዳደራዊ ውሳኔ ሰጥቶ ለሰንበቴዎቹ መተዳደሪያ ሕግና መመሪያ አውጥቶ ላከ፡፡ በካቴድራሉ ከሚገኙ 11 ሰንበቴ ማኅበራት 5 የሚሆኑት ሕጉን ተቀብለናል ሲሉ ለሀገረ ስብከቱ አስታወቁ 7 የቀድሞ መንግሥት ወታደሮች የሚመሯቸው  ሰንበቴዎች ግን የሥራ ጊዜውን በጨረሰው የሰበካ ጉባዔ ምትክ ምርጫ እንዲደረግና እነሱ በምርጫው ሊቃነ መናብርቶቻቸውን በማስመረጥ ሕጉ ተግባራዊ እንዳይሆን ለማድረግ ምርጫ ይደረግ ሲሊ ለአዲስ የአቡነ እስጢፋኖስ አስተዳደር አቤት አሉ ፡፡ አቡነ እስጢፋኖስና ሥራ አስኪያጃቸው መጋቤ ሐዲስ ይልማ ቸርነት እንዲሁም የእሳቸው አስተዳደር ጉባዔ ከመከረ በኋላ ቀደም ሲል በአቡነ ዳንኤል የሚመራው ጉባዔ ያሳለፈውን ውሳኔ መልሶ በማጽደቅ ሰንበቴዎቹ በ 70 ሺህ ብር ለኢ አማንየን በ50 ሺ ብር ከውጭ ለሚመጣ አስክሬን በ 35 ሺህ ብር ለሀገር ውስጥ የሚሸጡትን ፉካ ንግድ እንዲያቆሙ ለተለያዩ የፖለቲካ ስብሰባዎች፣ ለሰርጋና ለቅሶ አዳራሽ በማከራየት መነገዳቸው እንዲያቆሙ አዘዘ፡፡
አዲሱ ፓትርያርክ ብፁዕ አቡነ ማትያስ በቦታው ተገኝተው የሰንበቴ ማኅበራቱ (አክሲዮን ማኅበራቱ) ሕንጻ እና ሕገ ወጥ የቀብር ሥፍራ ከተመለከቱ ባኋላ ባስተላለፉት መመሪያ ይህ ቦታ የቤተክርስቲያን ብቻ ነው ማንም አለአግባብ ሊጠቀምበት አይገባም ሲሉ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
ጠቅላይ ቤተክህነት በዋና ስራ አስኪያጁ በብፁዕ አቡነ ማቴዎስ በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ አቡነ ሉቃስ አማካኝነት በሰንበቴ ማኅበራቱ የካቴድራሉን ይዞታ ለመንጠቅ ክስ የመሰረተ ግለሰቦች በተመራጭነት እንዳይሳተፉ መመሪያ አስተላለፉ ፡፡ በዚህ ሁኔታ የአጥቢያው ሰንበት ትምህርት ቤት በሰራው ከፍተኛ ቅስቀሳ ብዙ መራጭ የእነዚህን ነጋዴ ሽማግሌዎች ሐሳብ በመረዳት በተጻራሪነት በምርጫው ስፍራ ተገኘ፡፡ ከሰንበቴዎቹ ጋር በመሆን በእብነበረድ ሽያጭ የተሰማራ እና የደህንነት አባል ነኝ በማለት ጳጳሳቱን ጭምር የሚያስፈራራቸው አለማየሁ ከልል የተባለ ግለሰብም ከደህንነት ተወክያለሁ በማለት ምርጫው ውስጥ የሚሳተፉ ግለሰቦችን ስም ዝርዝር አዘጋጅቶ በስፍራው ተገኘ፡፡ ምርጫው በቤተክህነቱ ቀላል ግምት ስላልተሰጠው መስከረም 8 ቀን ብፁዕ አቡነ ሉቃስ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በስፍራው ተገኙ የሀገረ ስብከቱ ሁሉም የመምሪያ ኃለፊዎችም በእለቱ በአውደ ምህረቱ ተሰየሙ በፉካ ንግድ የተሰማሩት ግለሰቦች አመጽና አድማ በመፍራት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላት ስፍራው ላይ በተጠንቀቅ ቆሙ፡፡ ነጋዴዎቹ አበል ከፍለው ያመጡት ሕዝብ በቁጥር አንሶ ለቤተክርስቲያን የቆመው ወጣት ቁጥሩ በልጦ ሲያዩ ምርጫውን መበጥበጣቸው አልቀረም ነገር ግን ጳጳሳቱ እምነታቸው ዘብ ቆመው ዋሉ፡፡ በዚህ ሁናቴ ምርጫው በሰላም መካሄዱን ሲመለከቱ ብዙዎቹ የተቃዋሚ ሰንበቴ አመራሮች ምርጫውን ረግጠው ወጡ፡፡ መናፍቋ ቅድስት አሳልፍ ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስን ‹‹ገዝቼዎታለሁ ›› በማለት ኦፈ ግዝት እርግማን አወረደች፡፡ እሳቸውም ገዘተው አወገዟት፡፡ ምርጫውም በሰላም ተጠናቆ አዲስ አመራር ቤተክርስቲያኗና የእነዚህን ነውጠኛ ቡድኖች መካል ተመረጠ፡፡ ማንኛውም የቤተክርስቲያን አካል እነዚህን ቡድኖች በመፍራት ወደ ሰአሊተ ምህረት ቅ/ማርያም ካቴድራል ለመዛወር ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ከመንግሥት የጸጥታ አካላት በላይ የሚፈሩ ቤተክህነቱን እንደ እንስራ ውሃ ባሻቸው ጊዜ እያንቦጫቦጩት 2 ፓትርያርኮች 3 ሊቃነ ጳጳሳትና 3 ሥራ አስኪያጆችን ሲሻቸው እጠሳደቡና እያስፈራሩ ዛሬ ላይ ደርሰዋል፡፡
አሁንም እነዚህ ቤተክርስቲያን ብር ከልዩ ልዩ የቢራ አምራች አክስዮን ማኅበራት ከፍተኛ አክስዮን በሚገዙ በቤተክርስቲያን ብር ለኃጢአት ተግባር  ገንዘብ ከሚመድቡ እድሜ ያላስተማራቸው ግለሰቦች ቤተክርስቲያኗን እየበጠበጡዋት ይገኛሉ፡፡ ቤተክርስቲያኑንም የሚመራው አካል አንድ ዘላቂ እርምጃ ካልወሰደ በተደጋጋሚ እንደሚዝቱትና በተግባርም እንደሚሞክሩት ገለልተኛ ቤተክርስቲያን በሚል ሕዝበ ክርስቲያኑን መክፈላቸውና ቋመጡለትንና ለዘመናት ያልተሳካላቸውን  የፖለቲካ ሥራ በድብቅ ለማካሄድ በሚፈጥሩት ችግር ቤተክርስቲያኗ የሰላም ስፍራነቷን ማጣት የለባትም፡፡ እነሱም ካለፈው የስህተት ዘመናቸው በመነሳት ይህ ወቅት የንስሀ ሊሆንላቸው ይገባ ነበር፡፡ ዛሬም ቤተክርስቲያን ውስጥ ባሉት አንዳንድ ደላሎች አማካኝነት ወልዴ የምሸጠው 5 ፉካ አለና ሰዎች በሕይወት እያሉ ይጫረቱ በማለት የግለሰቦችን ገንዘብ እየሰበሰበ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የጥቅምቱ ሲኖዶሰ በወሰነው መሠረት የነጋዴ ሰንበቴ ማኅበራት ጉዳይ እልባት ይሰጠው፡፡ መንግሥትም እነዚህን ድብቅ የፖለቲካ ኃይሎች ሕጋዊ እርምጃ በመውሰድ ምነው በእንቁላሉ የሚሉበትን ጊዜ ሊያቀርብ ይገባል፡፡