Wednesday, May 23, 2012

ማኅበረ ቅዱሳን የፓትርያርክነቱን ወንበር ሊጨብጥ የቀረው ትንሽ ነው!


  • በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ማኅበረ ቅዱሳን ከተራ ማኅበርነት ወደ ሀገረ ስብከትነት  አደገ።
  • ሲኖዶሱ ሙሉ በሙሉ በማኅበረ ቅዱሳን እጁን ተጠምዝዞ እንደሚሰራ አስመሰከረ።
  • ማኅበረ ቅዱሳን ከእንግዲህ የቀረው ፓትርያርክነቱና ቤተመንግሥቱ ነው!
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተጠሪነቱ ለቅዱስ ሲኖዶስ ሆኖ  የየሀገረ ስብከቶቹ  ጠቅላይ ጽ/ቤት ሆኖ ያገለግላል። ይህ ጽ/ቤት ደግሞ የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ በየ3 ዓመቱ በሚያደርገው ምርጫ በሚመድበው ሊቀጳጳስ ነው። እንግዲህ ማኅበረ ቅዱሳን ተጠሪነቱ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ዋና አሥኪያጅ ሆነ ማለት ራሱን የቻለ ሀ/ስብከት  ሆነ ማለት ነው። የጠቅላይ ቤተክህነቱ መምሪያዎች ሊያዙት አይችሉም። ከዚያም በላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ ሊያዙት፤ ሊናገሩትና ሊቆጡት አይችሉም ማለት ነው። በቀጥታ በቅዱስ ሲኖዶስ በሚመደበው ሊቀጳጳስ በኩል ግንኙነቱ ከቅዱስ ሲኖዶሱ ጋር ብቻ ይሆናል ማለት ነው። እንዲህ ነው እንጂ ሹመት፤ መሾም ካልቀረ!! አንድ ማኅበር ባንድ ጊዜ እመር ብሎ አናት ላይ ፊጢጥ ብሎ ከመቀመጥ ወዲያ ሹመት ከወደየት ይገኛል? ከእንግዲህ  ከተቀመጠበት ደረጃ አንጻር ማኅበር መባሉ ዝቅ የሚያደርገው ስም ስለሆነ የቅዱሳን መምሪያ ወይም የወጣቶች ሀ/ስብከት እንዲባል ሲኖዶሱ በነካካው እጁ ስሙንም ማሻሻል ይገባዋል። ከዚያም አያይዞ ለዚሁ አዲስ ሀ/ስብከት አንድ ሊቀጳጳስ እንዲመድቡለትም ጥቆማውን እናቀርባለን።
አንድ ነገር ታዘብን። ቤተክርስቲያኒቱ ሲኖዶስ የሚባል አካል እንደሌላት ተረዳን። በአንድ ተራ ማኅበር እየተመሩ የእሱን ጉዳይ ብቻ ሲያነሱና ሲጥሉ ሦስትና አራት ቀናት ስብሰባ መወዘፍን ምን ይሉታል? ስንት ስራ መስራት እየቻሉ ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ማውረድ እስኪያቅታቸው ድረስ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን አጀንዳ ይዞ መከራከርን እውነት ሰዎቹ በመንፈስ ቅዱስ ነው የሚመሩት እንድንል ያደርገናል።
 በመሰረቱ እኰ ማኅበረ ቅዱሳን አሸባሪ አመራር እንደሚነዳው መንግሥት በድብቅ ሳይሆን በግልጽ አውጆ እያለ ስለማኅበሩ አጀንዳ መያዝ ትልቅ ስህተት ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩ ከፈጸሙት ስህተት ሁሉ ይህኛው ይከፋል። መንግስት ያስጠነቀቀውን ማኅበር ጉዳይ ለክርክር ማቅረብ አልነበረባቸውም። ከሽብር ተግባር ነጻና ትክክለኛ ማኅበር ስለመሆኑ በህግ አግባብ ከመንግስት ማረጋገጫ ሊያቀርብ ሲገባው ጭራሹኑ ከማኅበርነት ወደ ሀ/ ስብከትነት ማሳደግ እብደት ካልሆነ ጤንነት አይደለም። ቅዱስ ፓትርያርኩ አሁንም ደግመው ሊያስቡበት ይገባል እንላለን። ከየጎዳናው እየጠሩ ድስት የደፉለት ሁሉ አንድ ላይ አድሞ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር በጥቅም ሲተሳሰር እንዴት አሜን ብለው ሊቀበሉ ቻሉ? ብለን ፓትርያርኩን አጥብቀን እንጠይቃለን።
ይህ ማኅበር እስካሁን እየታዘዘ እንዳልቆየ የተጻፉለት ደብዳቤዎች አረጋጋጮች ናቸው። እሱ ራሱ አልቀበልም ብሎ በደብዳቤ አረጋግጧል። አንዴ ከኢህአዴግ፤ አንዴ ደግሞ ከተቃዋሚ ነኝ እያለ፤ ሌላ ጊዜ ከሀገር ቤቱ ሲኖዶስ፤ ሌላ ጊዜ ደግሞ ገለልተኛ እየመሰለ የተጓዘበትን ሁላችንም እናውቃለን። የወንድሞች ከሳሽና አሳዳጅ ስለመሆኑም ግፉን የቀመሱ ሁሉ ይመሰክራሉ። የተጓዘባቸውን ስልቶች ሁሉ ያጠናው መንግሥት ከሽብር አቀንቃኝ  ከሰለፊያ ጋር በአንድ ረድፍ አንዳስቀመጠው ነግሮናል። ስለሆነም አቡነ ጳውሎስ ይህንን የአድማና በጥቅም የተሳሰረ ውሳኔ አልፈርምም በማለት ውድቅ ሊያደርጉት ይገባል። ማኅበሩ አስቀድሞ ከሰለፊያ ተግባር ነጻ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ማምጣት ይጠበቅበታል። ደጋፊዎቹ ጳጳሳትን በማስረጃና በሰው ምስክር ተጠንተው ብቁ ሆነው ያልተገኙ ካሉ ከማእረጋቸው መሰናበት አለባቸው።  ቄስ የነበሩ፤ ልጆች የወለዱ፤ ቅምጥ ያላቸው እንዳሉ ይወራል፤ የአንዳንዶቹም ይታወቃል። ለዚሁም ማሳያ የሚሆነው አባ ሚካኤል በፍርድ ቤት ባለልጅነታቸው መረጋገጡ ነው። እየተሸፋፈነ መቀመጡ ለቤተክርስቲያን ጠንቅ የሆነ ውሳኔ ለማስወሰን ያልተመለሱ ሰዎች ስብስብን አስገኘ። ስለዚህ አባ ገብርኤል፤ አቶ ኢያሱ ተብለው እንደነበረው፤ ማንነታቸው እንደገና ተመርምሮ ውሳኔ ሊሰጥባቸው ይገባል።ጨከን ያለ የሥርዓት ማስከበር አካሄድ መውሰድ ካልተቻለ ነገ ፓትርያርክነቱን አስቀድሞ ከዚያም ቤተመንግሥቱን እንደሚረከብ የሚጠራጠር ካለ ምንም የማያውቅ ብቻ ነው። አመኑንም አላመኑም ፓትርያርክ ጳውሎስ፤አንድ ነገር አስረግጠን እንነግርዎታለን። በማኅበረ ቅዱሳንና በደጋፊዎቹ ጳጳሳት ግብዓተ መሬትዎ ሊፈጸም የቀረው ጥቂት ነው። ከሆነለት ፓትርያርክነቱን ለሚታዘዝ የወሎ ጳጳስ ወይም ለሸዋ ሰው ብቻ ሰጥቶ ወደ ቤተመንግሥት ሰተት ብሎ ለመግባት ከጽዋ ማኅበርነት ወደ መምሪያ ተገዳዳሪነት፤ አሁን ደግሞ ወደ ሀገረ ስብከትነት ማደጉ ከምንም በላይ ማሳያ ነው።  ታዲያ ከእንግዲህ የቀረው ምንድነው? ይህ ሁሉ ለጽድቅ ነው እንዳይሉንና እንዳንስቅ። ነጋዴና ሸቃጭ፤  ጻድቅ ማኅበር አራት ኪሎ የለም እንልዎታለን። እያየነው የወጣው ይህ ሀረግ ተክሉን አንቆ ወዳሰበበት መጓዝ ብቻ ነው። እግዚአብሔር ለዚህ ክፉ ማኅበር አሳልፎ ከሰጠን በእውነትም ቤተክርስቲያኒቱ ለፈተናና ለውድቀት ተመርጣለች ማለት ነው።
ሰውዬው «ኵሉ ንምርዓይ ምቅናይ» ያለው ወዶ አይደለም ለካ! ሁሉ ቢገርመን ሁሉን ለማየት መቆየት ብለናል።