Friday, May 18, 2012

ቅዱስ ሲኖዶስ የግለሰቦችን ነጻነት በመጋፋት፤ስም በማጥፋትና ከማውገዝ የወንጀል ድርጊት ሊቆጠብ ይገባል!

አሁን ባለው ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ማንኛውም ሰው የመሰለውን እምነት የመከተል መብቱ የተጠበቀ ነው። ከፕሮቴስታንቱ ጎራ ለመቀላቀል ወይም ካቶሊክ  ለመሆን አለያም  እስላም የማንም ክልከላ አይደርስበትም። የሌላውን መብት እስካልነካ ድረስ በመሰለው ቦታ እምነቱን የማስተማር፤ የመስበክ መብቱን እየተገበረ እንደሚገኝ ይታወቃል። ያንንም ስንል ሁሉ ነገር እንከን አልባ ነው እያልን እንዳልሆነም ሳይዘነጋ ነው። እያልን ያለነው ሁሉም እምነቶች ዋና መሠረታዊ ነጥብ በእያንዳንዳቸው በኩል የሚመለከው  አምላክ ከሌላው የተሻለ፤ ዋስትናን የሚሰጥ፤ ዘላለማዊነትን የሚያጎናጽፍ፤ የሚያጸድቅና የሚኰንን መሆኑን በማስረዳት  ለሌላው በማስተማር ተከታዮችና አባላትን ማፍራት መቻላቸው የማይካድ መሆኑን  ነው። በአብዛኛው  ችግሮች የሚመጡት በእምነት ተቋማት በራሳቸው በኩል ሲሆን ሌላውን አዲስና መጤ፤ የሰይጣን ትራፊ እንደሆነ አድርጎ ጥላሸት በመቀባት በትምህርት ሳይሆን በማስፈራራት አባሎቹን ጠብቆ ለማቆየት ሲሞክርና ማብጠልጠል ላይ ብቻ የመንጠልጠል ችግር እየተስተዋለ  ሲገኝ ነው። እንዲያውም አንዳንዶች የእምነት ተቋሙን ስም እየጠሩና የሰይጣን ቁራጭ አድርጎ በመሳል በጽሁፍ፤ በምስልና በቃል የተደገፈ አስተምህሮ የሚያስተላልፉና የሚያሰራጩ በየትኛውም ወገን ባሉ የእምነት ተቋማት በኩል ልቅ በሚባል ደረጃ ሲፈጽም ይስተዋላል።
 ስለስህተት አስተምህሮ ለመስበክ ከእምነቱ መሰረታዊ አቋም ተነስቶ ከሚሰጥ አንጻራዊ ስብከትና ትምህርት ውጪ የሌለ ነገር በመፍጠር ወይም በውሸት ላይ ተመስርቶ  በቀጥታ የእምነቱን ተቋም ስም በመጥራት ለማጥቃትና ለማንቋሸሽ የሚውል ከሆነ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ወንጀል ሕግም ይሁን በአማኙ ወይም በእምነት ተቋሙ ላይ ለሚደርስ የሞራል ጉዳት በፍትሐ ብሔር ህግ የሚያስጠይቅ ጉዳይ ነው።

 በማስረጃ የተደገፈና እውነት የሆነ ነገር በመዘገብ ማስተማር መብት ቢሆንም ሌላውን በማንኳሰስ፤ በማንቋሸሽ፤ ስምና ክብሩን በማጉደፍ የሚደረጉ አስተምህሮዎች ሁሉ አግባብነት እንደሌላቸው የኢትዮጵያ ህጎች በማያሻማ መልኩ ደንግገዋል። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን በቀጥታ ለማጥቃትና ለማዋረድ የሚደረጉ አስተምህሮዎች አሉ። እንደነዚህ ዓይነቶቹ በማስረጃና በጭብጥ ያልተመሰረቱ  አስተምህሮዎች ፍጹም ተቀባይነት የሌላቸው ናቸው። እንደዚም ሁሉ የፕሮቴስታንቱን ጎራ ወይም ካቶሊኩን በማጥላላትና በማበሻቀጥ የሚደረጉ ስም ማጉደፍ ዘመቻዎችም ከኦርቶዶክሱ ወገን እንዳለም የሚካድ አይደለም። በሁሉም ረድፍ  አንዱ አንዱን ለማጥቃት የተደረጉ ተግባራት ስለመኖራቸው ምንጮችን ጠቅሶ አስረጂ ማቅረብ ከባድ አይደለም። ደግነቱ ኢትዮጵያ ውስጥ መቻቻሉ ስላለ እስካሁን ያንን ያህል በህግ ደረጃ የገፋ መካሰስ አልተስተዋለም ። አንዳንድ ጊዜ ገደብን የሚያልፉ ድርጊቶች የኋላ ኋላ ችግር መፍጠራቸው አይቀሬ ሊሆን ይችላል። እነዚህን ለማረም  ከወዲሁ ያሉትን ችግሮች በጋራ መድረክ ሁሉም ራሱንና የሚመራበትን የእምነት መሰረት ላይ ብቻ በማትኰር ማስተማር እንዲችል መነጋገር ቢኖር ተመራጭ ነበር። ይሁን እንጂ እስካሁን ለዚህ የተዘጋጀ የለም፤ ካለም በቂ በሚባል ደረጃ የተሰራ ነገር አይታየንም። እያንዳንዱ የእምነት ተቋም ራሱን በልክ እያስቀመጠ በጎውን መቻቻል ቢያዳብር የተሻለ ቢሆንም አሁን ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቅዱስ ሲኖዶስ ተከባብሮ መኖር እንዲቻል የሚያግባባ መድረክ ከመፍጠር ይልቅ ማኅበራትንና የግለሰዎችን ስም እየጠራ ለማውገዝና ለማንቋሸሽ ለዚሁ ጉዳይ አጀንዳ ቀርጾ ጉባዔ መቀመጡን ስንመለከት እስካሁን የነበሩትን መቻቻሎች ሁሉ ንዶ ወደ መካሰስና ፍርድ ቤት ወደመጓተት እንዳይወስድ አስጊ ነገር ነው። ከላይ ለመጥቀስ እንደሞከርነው የአስተምህሮ ስህተቶች በየትኛውም ወገን  ግልጽ ሆኖ ቢታይም ወደመካሰስና መወነጃጀል ተግባር እስካሁን ያልተገባው በመቻቻልና በመታገስ ላይ በተመሰረተ ሃይማኖታዊ ሞራል የተነሳ እንደሆነ ግምት ይወሰዳል። ይህ ድርጊት እንዳይቀጥል የሚፈልግ አካል ቢችል በመነጋገርና በመወያየት ስም ማጥፋቶችና ማጥላላቶች እንዳይቀጥሉ ለመግባባት ቅድሚያ ሰጥቶ ቢሞክር ተመራጩ መንገድ ቢሆንም ሲኖዶሱ እንደቀደመው ዘመን አውግዤ እለያለሁ እንጂ እነዚህን ሃይማኖት የለሾችን አልታገስም እያለ መገኘቱ አሳዛኙና አስገራሚው ነገር ነው። ሃይማኖት የለሽነትም መብት መሆኑን የሳተ ይመስለናል። ፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶና ጴንጤን አወግዛለሁ ቢልም ጉዳዩ  ፕሮቴስታንትም፤ ተሐድሶም መሆን መብት መሆኑን አለመቀበል ከመሆን አያልፍም። ማንም የማንንም መብት ሳይነካ በሀገሪቱ ህግ ስር የመሰለውን እምነት ማራመድ የሚችልበት ሥርዓት መኖሩ መረሳት የለበትም።
የቀድሞው ዘመናትን የሲሶ መንግሥት ሥልጣን  ዛሬም ያለ ይመስል እነእገሌን እለያለሁ፤ አዋርዳለሁ፤ አበሻቅጣለሁ፤ የእምነታቸውን መሰረት አወግዛለሁ የሚል ሲኖዶስ ካለ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ  ጉዳዩ በውግዘት የራስን ልዕልና ማረጋገጥ ሳይሆን  ወንጀልን በመፈጸም  የግለሰቦችን ስብዕና መጣስ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
ዛሬ እነ አርዮስ ፤ መቅዶንዮስ፤ አውጣኪ ወይም እነልዮን ከኦርቶዶክሱ ጎራ ቢኖሩ እንኳን ጎራውን ለቀው እንዲወጡ ከሚደረግና የራሳቸውን እምነት በፈለጉበት መድረክ ከሚያራምዱ በስተቀር እንደቀደሙ ዘመናት በእምነት ባለመመሳሰላቸው ወይም በመለየታቸው ብቻ ማውገዝና ማጥላላት፤ ከማኅበራዊ ኑሮና አገልግሎት እንዲነጠሉ የሚያደርግ የአንድ ወገን ዘመቻና ውግዘት ማንም  ሊያደርስባቸው  ከማይችልበት በህግ ከለላ የመጠበቅ ዘመን ላይ ስለተደረሰ የጥንቱን ነገር ዛሬ ማሰብ የዋህነት ይሆናል። ይህንን ማድረግ በወንጀል የሚያስጠይቅበት ሁኔታ ላይ በመደረሱ በድሮ በሬ ለማረስ መሞከር ዘመኑን አለመረዳት ከመሆን አያልፍም።  ቅዱስ ሲኖዶስ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ  ውስጥ አስተምህሮውን፤ ስርዓቱንና ህጉን ለመጠበቅ የማይፈልገውን አማኝ ከእምነት አባልነቱ የመሰረዝ  መብቱ የተጠበቀ ስለመሆኑ ማንም ጥያቄ የለውም። ያንንም ለማድረግም ቢሆን  በሰው፤ በሰነድ፤ በጽሁፍ፤በድምጽና ራሱም ግለሰቡ እምነት ክህደቱን ተጠይቆ ሲረጋገጥና እንደቤተክርስቲያኒቱ ቀኖና በንስሀ ለመመለስ ካልፈለገ  እንጂ ከአባልነቱ ሊሰናበት የሚችለው በዘመቻና አድመኞች በሚያቀነባብሩት መረጃ ከሆነ ተቀባይነቱ ሚዛን አይደፋም። ከዚያ ውጪ ሲኖዶሱ ስልጣን የሰጠውን መብት ለፈለጉገው ጉዳይ ማስፈጸሚያ በማዋል የማቅን የስለላ ውጤት ተንተርሶ እሱን ለማስደሰት ሌላው ኦርቶዶክሳዊነቱን ለመካድ ሳይፈልግ በግድ እናስጥልሃለን በማለት በሰዎች መብትና ሰብአዊ የእምነት ነጻነት ላይ ጣልቃ በመግባት እኔ አውቅልሃለሁ፤ እኔ እወስንልሃለሁ፤ አስምልሃለሁ፤ እገዝትሃለሁ ማለት ተገቢ  ሊሆን አይችልም።  በስጋ ድካም የተሰራ ስህተትና የእምነት ህጸጽ  ካለ ቅድሚያ ማረምና ማስተማር ይገባል። ከዚያ ውጪ ክርስቶስ የሞተለትን የአንድ ሰው ህጸጹን ወይም ድካሙን ለውግዘት መመዝገብ እውቀት አይደለም። አንዳንዶች አውቀውም ይሁን ሳያውቁ የፈጸሙትን ስህተት ረጋ ብሎ በማየት መክሮና ዘክሮ በንስሐ መመለስ እየተቻለ በማቅ ምሪት በደረሰው ወከባና ግፊያ የሚወዷትን ቤተክርስቲያን ጥለው ለመውጣት ከመገደዳቸውም በላይ በደረሰባቸው የሥነ ልቡና ጉዳት ጥላቻና ብቀላን አርግዘው ተመልሰው የሚያጠቁ ሆነው ታይተዋል።  «አንድ ሳር ቢመዘዝ ያፈሳል ወይ ቤት» የሚል ምሳሌ ቦታ ሊሰጠው አይገባም። ይህንን ሁሉ አልፎ ተርፎ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን  የማትቆጠጣረውና የማታስተደዳድረውን፤ መንግሥት በሚያስተዳድረው ሀገርና በየጎዳናው ያለውን፤ ከእምነቷ ክልልና ቅጥር የወጣውን፤ በአባልነት ያልመዘገበችውን ማኅበር ወይም ግለሰብ ወይም ተቋም በስም እየጠራች  አውግዣለሁ፤ ከህዝብ ለይቻለሁ፤ አዋርጃለሁ፤ ከነዚህ ወራዶች ጋር እንዳትተባበሩና እንዳትገናኙ ብትልና በማኅበራዊ ኑሮአቸው ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር በቅዱስ ሲኖዶስ በኩል ብታውጅ ወንጀል እየተፈጸመ መሆኑ መታወቅ አለበት። ቅዱስ ሲኖዶስ በእምነቱ ቅጥርና ክልል ውስጥ ላለው ተከታይ እንጂ ከዚያ ውጪ ያለውን ግለሰብእ እና ማኅበራት ፈቃድ ሰጪና ነሺ፤ አውጋዥና ረጋሚ አይደለም። ሲኖዶስ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የበላይ ጠባቂ እንጂ አሁን ሀገሪቱን የሚመራው ፓርቲ (የኢህአዴግን) ውክልና የተቀበለ እንዳልሆነ እንዴት ይጠፋዋል? አሁን ለማድረግ እየተሞከረ ያለውን ከቅጥሯ ክልል የወጡትን ሁሉ ለመቆጣጠርና በላዩ ላይ ለመወሰን የተፈለገ ይመስላል። ያ ከሆነ ግን የውጤቱን መጥፎነት ለማወቅ ነብይ መሆንን አይጠይቅም።
ቅዱስ ሲኖዶስ የማውገዝ ዘመቻ  ከማካሄዱ በፊት ሊያስብበት የሚገባው፤ ያለው ሰላማዊና ህጋዊ አካሄዶችን ማስቀመጥ እንወዳለን።
               ሰላማዊው የመነጋገር መድረክ
1/  ሲኖዶሱ በኦርቶዶክሱም በኩል  የሌላውን እምነት  ስም ጠቅሶ ማጥላላት፤ መስደብ፤ ማዋረድና ማራከስ በሰነድ፤ በምስልና በጽሁፍ ማስረጃ አስደግፎ  ማቅረብ የሚቻልበት እንደሆነ  አውቆ የኦርቶዶክስን  ስምና ክብር ለማስጠበቅ  ሲባል ብቻ በራሱ ሥልጣን ወዳልሆነ የውግዘት ሽኩቻ በመግባት የህግ ተጠያቂነትን ከማስከተል ይልቅ የሌላውን እምነት በማክበርና ህጋዊ ነጻነቱን ጠብቆ፤ ስም ከማጥፋትና ከማጥላላት ዘመቻ እንዲወጣና  እያንዳንዱ የራሱን እምነት ብቻ እንዲያራምድ ለማስቻል በመነጋገርና በመወያየት የቅን እሳቤ መድረክ እንዲኖር ቢያደርግ ቅድሚያ የተሻለው መንገድ ነው እንላለን።
               ቤተክርስቲያናዊ ስርዓትን በተከተለ አካሄድ
 2/ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የተሳሳተ ካለ ወይም ጥያቄ አለኝ የሚል አካል በቤተክርስቲያኒቱ ውስጥ ቢነሳ ወይም እገሌና እገሌ የቤተክርስቲያኒቱን ዶግማና ቀኖና ጥሰዋል የሚል ከሳሽ ካለ ወይም ስላገኘበት ማስረጃ ለመከራከር የሚቆም ከተገኘ ሊያከራክር የተገባ ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት አከራክሮ ሊቃውንት ጉባዔው በተሰየመበት ዳኝነት ከዶግማዋና ቀኖናዋ የወጣ ቢኖር ከአባልነት ከማሰናበት ውጪ ለአንዱ ወግኖ በስውር ከሳሽ የቀረበውን ክስ ሊቃውንት ጉባዔው ከሳሽና ተከሳሽን ሳያከራክር ዳኝነት ለመስጠትና በሲኖዶሱ ለማስወገዝ መሞከሩ ትክክል አይደለም። በሃይማኖት ጥርጥር የተያዘውን ግለሰብእ እና ይህንን ጥርጥር አውቃለሁ ባይ ከሳሽን ግራና ቀኝ አቁሞ ማከራከር የቀደመ ስርዓት ስለሆነ ይህንን ማስፈጸም የሲኖዶስ ሥልጣን በመሆኑ ይኼው እንዲደረግ አበክረን እናሳስባለን።
          መብትን በህግ የማስከበር መንገድ
3/ በተራ ቁጥር 1 እና 2 ላይ የተመለከተው አማራጭ ምንም እንኳን የተሻለው መንፈሳዊ መንገድ መሆኑ ባይካድም ይህንን ለማድረግ ትእግሥቱ የለኝም የሚል ከሆነና የቤተክርስቲያኒቱ ስምና ክብር አስከብራለሁ  የሚል ከሆነም ሲኖዶስ ያለው ህጋዊ መብት ማውገዝና ማስወገዝ ሳይሆን በቂና ህጋዊ  ማስረጃውን ይዞ በሀገሪቱ ህግና ህግ ብቻ መብቱን ለማስከበር ወደፍርድ ቤት መሄድ ብቻ ነው።
ከእነዚህ ሦስት አማራጮች  ውጪ የበደለኝ ስላለ  የውግዘትና የስም ማጉደፍ፤ ከማኅበራዊ ኑሮው የመነጠል፤ የማዋረድ፤ ማንም ከሚያምንበት እምነትና አቋሙ የተነሳ ክብርና ነጻነቱን ገፍፌ በውግዘት የአዋጅ  በትሬን አሳርፍበታለሁ ብሎ ሲኖዶስ  እርምጃ ቢወስድ አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ  ወንጀል እየፈጸመ መሆኑን ሊያውቅ ይገባል።
ይህ እንግዲህ ከማንም ቅን ኅሊና ካለው ሰው የሚሰወር አካሄድ አይደለም። ከዚህ ውጪ አሁን እንደምንሰማው ሲኖዶስ ማኅበራትን፤ ተቋሟትን፤ ግለሰቦችን፤ ድርጅቶችን ለውግዘት መዝግቦ በራሱ በኩል እርምጃ ሊወስድባቸው መዘጋጀቱን ነው። ማንም ሰው ህግ ጥፋተኛ ብሎ እስካልፈረደበት ድረስ በወንጀለኛነት ወይም በጥፋተኛነት መፈረጅ በራሱ ወንጀል መሆኑን የሚናገረውን የሀገሪቱን ህጎች መጣስ  መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። በውግዘት፤ ከህዝብ በመነጠልና በመለየት፤ ከማኅበራዊ አኗኗሩ ላይ ተጽእኖ ለመፍጠር መሞከር፤ በስራ ሁኔታው ላይ ክብሩን፤ስሙን ዝቅ ማድረግ፤እምነቱንና አቋሙን ማዋረድ ወንጀል ስለሆነ ይህንን በመፈጸም ቅዱስ ሲኖዶስ ቤተክርስቲያኔን በኃይሌ አስከብራለሁ ቢል ታሪካዊና ህጋዊ ስህተት እየፈጸመ መሆኑን ለመጠቆም እንወዳለን።(የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀጽ 607, 608, 613 እና 816 እንዲመለከቱም እንጋብዛለን)።