አዲስ የወጡ ጽሁፎች
print this page
የቅርብ ጊዜ ጽሁፎች

ቤተ ክርስቲያን ግን እያሽቆለቆለች፤ አስተዳደሯ እየሞተ ነው። እየገደላት ያለው ማነው?


  በቤተ ክርስቲያን ድክመትና የቁልቁሊት ጉዞ ትልቁን ድርሻ የሚወስደው ከውስጥ የሚነሳው ሽኩቻ እንደሆነ ታሪክ ይነግረናል። ከኬልቄዶን ጉባዔ አንስቶ በየዘመናቱ ሂደት በየክፍልፋይ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ሲታይ የቆየው መለያየትና መናቆር መነሻው በመንፈሳዊ ሥልጣን ላይ በሚቀመጡ መሪዎችና ሊቅ ነን በሚሉ ሹመኞች እንደሆነ ብዙ ዋቢ ማቅረብ ይቻላል። ተመሪው ሕዝብም በሚናቆሩ መሪዎች ሁለት ወገን ቆሞ ለአንዱ ወገን አሸናፊነት የቤተክርስቲያኒቱን ግድግዳ እየነቀለ የማፍረሱን ሂደት ማፋጠኑ ሌላው ጉዳት ነው። ሥልጣኑ መንፈሳዊ ሆኖ ሳለ ሽኩቻው ወደሥጋዊ ሕይወት በማድላቱ በመደማመጥ መፍትሄ ለማምጣት ባለመቻሉ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን እየተዳከመች በመሄድ ላይ ትገኛለች። በዚያው አንጻር ያሉባትን ተግዳሮቶችና ጊዜውን የዋጀ ክህሎት ያለው ብቁ አመራር በመፍጠር ስላልተቻለ ችግሩ እንዳለ ሊቆይ ችሏል። በዓለም ላይ ካሉ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ አንዷ የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም አንዷ የችግሩ ሰላባ ቤተ ክርስቲያን መሆኗን መካድ አይቻልም።


   የሩቁን ትተን የራሷን ቤተ ክርስቲያን ላዕላይ መዋቅር ራሷ መምራት ከጀመረችበት ከ1950ቹ አንስቶ ብንመለከት ችግሮች እየገዘፉ እንጂ እንየቀነሱ አለመሄዳቸው አስገራሚ ነው። በተለይም ከአፄው ስርወ መንግሥት መውደቅ ጀምሮ አሁን እስካለው እስከ ዘመነ ኢህአዴግ ድረስ ቤተክርስቲያን በአስተዳደሯ ተዳክማ፤ በተከታዮቿ አሽቆልቁላ መሄዷገሃዳዊ እውነት ነው። ጳጳሳቶቿ ፓትርያርካቸውን ከሰው በላው ደርግ ጋር ወግነው የበሉት ሥልጣን እናገኛለን ብለው ካልሆነ ስለእውነትና ስለቤተ ክርስቲያን ዝም ማለታቸው ሌላ ምን ሊሆን ይችላል? ደርግ ፓትርያርክ ሲሾምላቸው አሜን ብለው መቀበላቸው ሥጋዊ ፍርሃት አሸንፏቸው ካልሆነ በስተቀር ለቤተ ክርስቲያን ልዕልናና ስለክርስቶስ ወንጌል ግድ ብሏቸው ሊሆን አይችልም። እንዲያም ሆኖ ከነፈሰው ጋር የሚነፍሱት ጳጳሳት «ብፁዕ ወቅዱስ» ሲሉ በነበሩት ፓትርያርክ ላይ ሌላ ፓትርያርክ ለመሾም ሰላማዊ ሰልፍ በመውጣት ወደምርጫ የገቡት ለቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ እድገት ተጨንቀው አለመሆኑንም አስረግጦ መናገር ይቻላል።


   በዘመነ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ፕትርክና የተሻለ አስተዳደርና የልማት ምልክቶች የታየበት ጊዜ ቢሆንም ዘመኑን የዋጀ መዋቅራዊ አደረጃጀት ባለመኖሩ የሰውና የሀብት ብክነቱ ግን ወደር ያልተገኘለት ሆኖ አልፏል።  በሌላ መልኩም ከታዩት ስህተቶች ውስጥ ደግሞ ወደመንፈሳዊ ሥልጣን እንዲመጡ የተደረጉት ኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ለለውጥ ሳይሆን ለውድቀት በር የከፈተ መሆኑ ሌላው ጉዳይ ነው። እንኳን ለሊቀ ለሊቀጳሳትነት ይቅርና ለደላላነት የማይመጥኑ ሰዎች በአፈፋ በገፈፋ መሾማቸው በአሳፋሪነቱ ወደር የለውም። ጳጳሳቱ የታወቀና ያልታወቀ የግል ኃጢአታቸው በአደባባይ የተነበበት እንዲሁም በዘረኝነት፤ በጎጠኝነት፤ በአፍቅሮ ንዋይ ፤ በሥልጣን ጥመኝነት፤ በአድመኝነት ራሳቸውን በተግባር ያሳወቁበት ጊዜ መሆኑ ለቤተ ክርስቲያኒቱ ድክመት ትልቁን ድርሻ መውሰዱን መሸፈን ከእውነታው ማፈግፈግ ይሆናል። 


  እነዚሁ ጳጳስ የተባሉት ሰዎች ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር አብ’ረው ለነውራቸው መሸፈኛ ያገኙ መስሏቸው ቤተክርስቲያኒቱን ሲያምሱ መገኘታቸው ለወንጌል አገልግሎት መዳከምና  እረኛ አልቦ የሆኑ ተከታዮቿ ከመቼውም ጊዜ በላይ እንዲኮበልሉ የሆነበትም ዘመን ነበር። አስቀድሞ በተደረገ ፖለቲካዊ ምርጫ ወደፓትርያርክነት የመጡት አባ ማትያስም ከነበረው የተሻለ አስተዳደር ለመፍጠር ይቅርና የነበረውን ለማስቀጠል አለመቻላቸው ሌላው የቀጣይ ውድቀት አንዱ ማሳያ ነው።
የመሻሻል ምልክት የሌለውንና የጅምላ ሹመኞቹን የጳጳሳት ጉባዔ በርዕሰ መንበርነት የሚመሩት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ እንዴት አድርገው ቤተክርስቲያኒቱን ወደአንድ የአመራር ከፍታ ሊያሳድጉ ይችላሉ? በጭራሽ አይችሉም! ምክንያቱም ፓትርያርክ ከመሆናቸው በፊት ያልነበራቸውን ችሎታ ዛሬ ከወዴት ያገኙታል? በብዙ ሚዛን አሁን ካለበት ሁኔታ የተሻለ የነበረውን የአቡነ ጳውሎስን አስተዳደር በምኒልክና አስኳል ጋዜጣ ላይ በመተቸት ይታወቁ የነበሩት አቡነ ማትያስ የሥልጣኑ ሉል እጃቸው ላይ ሲወድቅ ወሬውን በተግባር ከማሳየት ይልቅ ለባለጉዳዮች «ተኝቷል በሉልኝ» በማለት በር ዘግተው መደበቅን ምርጫቸው ማድረጋቸው በሰፊው ይወራል።


  ከዚህ በፊት በዚሁ መካነ ጦማር ላይ የሙስና ታሪኩን በቅጽል ስሙ ያወጣነውና ማኅበረ ካህናቱ «ኑረዲን» የሚሉት(ንቡረእድ) ማንም እንዳይገባ በሩን ዘግቶ ለፓትርያርኩ የብቃት ጉድለት ተጨማሪ ድርሻ የወሰደ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በሩ ቢከፈትስ ፓትርያርኩ መፍትሄ የመስጠት ብቃት አላቸው ወይ? ብለው የሚጠይቁ ብዙዎች ናቸው።  አንድ ሰሞን ትኩስ በሚሆንና ቆይቶ በሚባረድ ስሜት ውስጥ ሆነው ፈታኝ የሆነውን የቤተ ክርስቲያን ችግር መፍታት አይቻልም። ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ትኩስም፤ በራድም በመሆን የለውጥ ሰው መሆን አይችሉም። አንዱን መያዝ የግድ ይላል። በር እየዘጉ መደበቅም ችግሮቹንና ሸክሙን ከሚያበዛ በስተቀር እንከኖችን ሊሰውር የሚችል የምትሃት መንገድ አይደለም። መደበቅን እንደምርጫ ከወሰዱ ደግሞ ሲመተ ፓትርያርኩን ለቤተ ክርስቲያኒቱ ተከታዮች ሰጥተው ወደገዳም መሄድ ይሻላል።


 ሌላው የቤተ ክርስቲያኒቱ የአመራር ጉድለት «ቋሚ» የሚባለው ነገር ቋሚ ያልሆነው ተለዋዋጭ ሲኖዶስ ጉዳይ ነው። ጳጳሳት ስለሚገኙት ብቻ «ቋሚ» ሊባል አይችልም። በየ3 ወሩ በሚደረግ መለዋወጥ «ቋሚ» የሆነ አመራር ሊሰጥ የሚችለው በምን መለኪያ ነው? የሲኖዶስ ውሳኔዎች አፈጻጸም የሚዘገዩት ወይም ለችግሮች አፋጣኝ መፍትሄ ከመስጠት ይልቅ በውዝፍ እየተተወ የሚቀረው 3 ወራት ለሥራ በቂ ጊዜ ባለመሆኑ የተነሳ እንደሆነም መዘንጋት የሌለበት ነጥብ ነው። ቢያንስ ለአንድ ዓመት የሚቆይና ቋሚ ሊያሰኝ የሚችል ሥራ መፈጸም የሚችል የቋሚ ሲኖዶስ ያስፈልጋል። በየ3 ወራት መቀያየር ያስፈለገው ጳጳሳቱ ከአዲስ አበባ ውጪ መቆየቱ ስለሚሰለቻቸው እንደእረፍት ጊዜ የመለዋወጫ መንገድ የወሰዱበት ዘዴ ሊሆን ይችላል እንጂ ሥራ ለመስራት አይደለም። ለዚያውም መሥራት የማይችሉ ሠራተኞች አድርገው አድርገን ከቆጠርናቸው ነው።  ከራሱና ከዘር ጉዳይወጥቶ የቤተ ክርስቲያን ችግር ግድ የሚለው ጳጳስ ከቶውኑ አለን? እነ አባ ማቴዎስ አሁን ባሉበት ሥልጣን እየሰሩ ያለው ሲታይ ለፓትርያርክነት መወዳደራቸው በራሱ ቤተ ክርስቲያኒቱን ራስ ዳሽንን ከሚያክል የተራራ ሸክም ገላገላት የሚያሰኝ ነው። ዛሬ ካሉት ጳጳሳት መካከል ጵጵስና ከመሾማቸው በፊት የጵጵስና የክብር ልብስ በማሰፋት በጉጉት ሲጠባበቁ የቆዩ እንደነበሩ እናውቃለን። አንዳንዶቹም ጳጳስ ሳይሆኑ በፊት የጵጵስናውን ድስት አጥልቀው ፎቶ ተነስተውም ታይተዋል። ዘመቻና ዲናር የሲመት መስፈርት በመሆኑ የተነሳ የተሻለ የአስተዳደር ለውጥ አልታየም፤ ወደፊትም አይታይምም። አንድ ጳጳስ፤ «በኛ ጊዜ ይሄን ያህል ገንዘብ ያስከፍል ነበር» ሲሉ ሰምተን አፍረንባቸዋል።


  ከዚህ በታች የምንመለከተው ፎቶ ግራፍም የዚያ የሹመት ስካር ውጤት ነው። አባ ገ/ሚካኤል ይባላል። ከዚህ በፊት በቃሲም ሥላሴ ሰባኬ ወንጌል ነበር። ከዚያም ኬንያ ከተላከ በኋላ ፈርጥጦ ከአፈንጋጩ ሲኖዶስ የተቀላቀለ ነው። አሁን ደግሞ ሳይሾም በፊት የሲመት አራራውን እየተወጣው ይገኛል። ነገ ደግሞ ወይም በፈርጣጩ ሲኖዶስ አለያም በዘመቻ መልክ በሀገር ቤቱ ልማት የለሽ ሲኖዶስ ሊሾም ይችል ይሆናል።

 ጳጳስ ከሆኑት መካከልም እንደዚሁ ሲያደርጉ የነበሩ ተሹመው ታይተዋል። ነገ ስላለመሆኑ ማረጋገጫ የለም። የጵጵስናውን ሹመት በተስፋ የሚጠባበቁትም ልብሱ ብል እስኪበላው ድረስ አሰፍተው ጥቅምትና ግንቦትን በህልም ይቋምጣሉ።


ቤተ ክርስቲያን ግን እያሽቆለቆለች፤ አስተዳደሯ እየሞተ ነው። እየገደላት ያለው ማነው?

0 የተሰጡ አስተያየቶች

«ኃጢአት፤ ይቅርታና ተሐድሶ»

አንዳንድ የዋህ የሆኑ ሰዎች የልበ ደንዳኖችን አሳብ ተከትለው ወይም እልከኞቹ የዋሃንን እየነዱ «ቤተ ክርስቲያን አትታደስም» ሲሉ ይደመጣሉ። እነዚህን ሰዎች ስለኃጢአት፤ ንስሐ፤ ይቅርታና ተሐድሶ በማስተማር የሕይወትን መንገድ ማስረዳት ከባድ ነው። ምክንያቱም መነሻቸው እውነትን ላለመቀበል እልክ የገባ መንፈስና የተዘጋ ልብ ስላላቸው እያዳመጡ አይሰሙም። እግዚአብሔርን ከማንም በተሻለ እንደሚያውቁ ይናገራሉ። ነገር ግን እግዚአብሔር ካዘዘው ትዕዛዝ ውስጥ አንዱንም አይሰሩም። ምክንያቱም ሁል ጊዜ ራሳቸውን ከራሳቸው ጋር የሚያስተያዩትና የሚመዝኑስለሆነ እውነትን ወደማወቅ ሊደርሱ አይችሉም። በራሳቸው እውቀት ያለልክ ይመካሉ። ነገር ግን እውነት በማደግ ካልተገለጸ በስተቀር በራሱ በተመካ እውቀት ሊሰፋና ወደሌሎች ሊደርስ ባለመቻሉ ዕለት ዕለት ያሽቆለቁላሉ። እድሜአቸውንና ብዙኅነታቸውን እንደእውነት ምስክር አድርገው ለራሳቸው ያቀርባሉ። ራስን ከራስ ጋር የማስተያየት በሽታ አደገኛ ነው። በዚህ ድርጊት አይሁዳውያን በብዙ ተበድለዋል።አይሁዳውያን የእምነት መሠረቶች እንደነበሩ ግልጽ ነው። ነገር ግን ሕግና መጻሕፍት ይዘው መቆየታቸው በራሱ ወደእውነት አላደረሳቸውም። ምክንያቱም ራሳቸውን ይለኩ የነበረው ከራሳቸው ጋር ነበርና ነው።  በምድረ በዳ ውስጥም የ40 ቀን መንገድ 40 ዓመት ያዞራቸው ያ እልከኛ ልባቸው ነበር። በዚያ ብቻ ሳያበቃ እልከኛ ልባቸው ወደእረፍቱ እንዳይገቡ ከለከላቸው።
«ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ?» ዕብ3፤15-18
ራስን ከራስ ጋር ባለመመዘንና ራስን ከራስ ጋር ባለማስተያየት ችግር ካልተያዙ ዛሬ ያለውን የእግዚአብሔር ድምጽ ለመስማት ካለመፈለግ እልከኝነት ነጻ መሆን ይቻላል። የአባቶች አምላክ መንፈስ ቅዱስ ዛሬም ስለሚናገር «በየት በኩል አልፎ ወደእናንተ ደረሰ?» ከሚል እልከኝነት መውጣት እስካልተቻለ ድረስ ወዳዘጋጀው እረፍት መግባት ከባድ ነው። በአንድ ወቅት ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን እንደተናገረው «እምነት እያደገ፤ ወደሌላው ሰውና ሀገር ሁሉ በሥራው እየጨመረ ካልሄደ በእግዚአብሔር ላይ ያለው መመካትና ምሥጋና ፈተናውን የተወጣ አይደለም ይለናል። ምክንያቱም ራሱን ከራሱ ጋር የሚያስተያይ ራሱን የሚያመሰግን ከመሆኑ የተነሳ ነው። 2ኛ ቆሮ 10፤12-18
እልከኝነትና ደንዳናነት ከኃጢአተኝነት ነጻ ነኝ ከሚል ስሜት የሚመጣ ነው። እልከኝነት የልብን አሳብ ትቶ እውነት የሆነውን ነገር ለመስማት ፈቃደኛ አለመሆን ነው። ደንዳናነት ደግሞ እንደብረት የጠነከረ ግትርነትና ከማንአህሎኝ ድፍንነት የሚነሳ ነው። እልከኛ በኃጢአቱ ከሚመጣ ቅጣት ይማራል። ደንዳና ግን ሳይሰበር ከኃጢአቱ መማር አይችልም ።  የደነደነ ልብ የተሸከመው ፈርዖን በፊቱ የተደረጉትን ተአምራት አይቶ ከመማር ይልቅ ቀይ ባህር ውስጥ ሰጥሞ እስኪቀር መመለስ እንዳልቻለው ማለት ነው። ሁለቱም በደል የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደሆነ በሚነገርለት በእስራኤል ላይ ታይቷል። ወደዚህ ያደረሳቸው ነገር ኃጢአት ነው። በእልከኝነታቸው ተቀጥተውበታል፤ በደንዳናነታቸውም ተሰብረውበታል።  ኃጢአትን መተው ፤ ንስሐ ማድረግን፤ ይቅርታን መጠየቅና በተሐድሶ አዲስ ሰው የመሆን ስጦታን ያለመቀበል ውጤት ምንጊዜም በእልከኝነትና በደንዳናነት ውስጥ ይጥላል። ከዚያም የዘሩትን የኃጢአት ፍሬ በፍርድ ማጨዳቸው ደግሞ አይቀሬ ነው። ለዚህም ነው በዚህ ጽሁፋችን መታደስን ስለሚጸየፉ ሰዎች ጥቂት ማለትን የወደድነው። መታደስን መጥላት ኃጢአትን የመውደድ ውጤት እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፋችንን ዋቢ አድርገን እንገልጣለን።

1/ ኃጢአት

ሥጋ ከለበሰ ከአዳም ልጆች ውስጥ ከክርስቶስ በቀር ከኃጢአት ነጻ መሆን የተቻለው ማንም የለም። ኃጢአት በአንዱ በአዳም በደል ወደሁሉ ደርሷል። ከሰማይ ወረደው ሁለተኛው አዳም የኃጢአትን በደል በመስቀል ላይ ጠርቆ ካስወገደው በኋላ በውርስ ወደሁሉ ይደርስ የነበረው ኃጢአት ተወግዷል። ከእንግዲህ በወል በኃጢአት ቀንበር ሥር መውደቅ ቀርቶልናል።  በክርስቶስ አዲስ ሰው የሆነ ማንም ቢሆን ኃጢአትን እንዳያደርግም ተነግሯል። ነገር ግን ሰው በክርስቶስ አምኖ ከዳነ በኋላ ከሥጋ ድካም የተነሳ ኃጢአትን ቢያደርግ ከኃጢአቱ እንዴት ሊነጻ ይችላል? ኃጢአት በተፈጥሮው ተጠያቂነት አለበት። ኃጢአት የፈጸመ ማንም ቢኖር ዋጋ ሳይከፍል መንጻት አይችልም። በመጽሐፉም ስለኃጢአት ደም ሳይፈስ ስርየት የለም እንደተባለ ለዚህ የምናቀርበው ዋጋ ምንድነው? እኛ ምንም የለንም።ነገር ግን ኃጢአትን አንድ ጊዜ በመስቀሉ ላይ በደሙ የደመሰሰ ክርስቶስ ለእኛ ከኃጢአት የምንድንበት ዋስትናና ጠበቃችን ነው። 1ኛ ዮሐ 2፤1

ጥብቅና ሲባል የክርስቶስን አምላክነት አሳንሶ እንደምድራዊ ችሎት ሙግትና ክርክር የሚገባ የሚመስላቸው ሞኞች አሉ። በቅድሚያ ኃጢአት በተፈጥሮው  ተጠያቂነትን ማስከተሉን ማመን የግድ ይለናል። በዚህም የተነሳ በኃጢአቱ ማንም በእግዚአብሔር ዘንድ ሳይጠየቅ የሚቀር የለም።  ደም ሳይፈስ ስርየት ስለሌለ በክርስቶስ አምነን ለተመጠቅን ሁሉ በኃጢአት ምክንያት ለሚመጣ ተጠያቂነት መልስ መስጠት የቻለ የክርስቶስ ደም ብቻ ነው። ሰዎች ኃጢአት ስለሚያመጣው ጥያቄ መልስ መስጠት ስለማንችል ስለእኛ ምትክ ሆኖ በቤዛነቱ ደም ያዳነን በኃጢአት ምክንያት ለሚመጣ ጥያቄ መልሳችን የሆነው ክርስቶስ ጠበቃችን የምንለው ያንን ነው። ኃጢአት ዋጋ እንደማስከፈሉ መጠን ንስሐ ስንገባ ስለፈጸምነው ኃጢአት የምንከፍለው ዋጋ ስለሌለን የክርስቶስ ሞት ስለእኛ ምትክ ወይም ጠበቃ ሆኖ ይቅርታን ያስገኝልናል ማለት ነው። በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረና በኃጢአት የመጣውን ጥል ተከራክሮ በሞቱ ያሸነፈ ጠበቃ በሰማይ አለን የምንለውም ለዚህ ነው።  ወንጌላዊው ዮሐንስም በመልእክቱ የነገረን ያህንኑ ነው። እንዲህ እንዳለ፤
«ልጆቼ ሆይ፥ ኃጢአትን እንዳታደርጉ ይህን እጽፍላችኋለሁ። ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ ከአብ ዘንድ ጠበቃ አለን እርሱም ጻድቅ የሆነ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱም የኃጢአታችን ማስተስሪያ ነው፥ ለኃጢአታችንም ብቻ አይደለም፥ ነገር ግን ለዓለሙ ሁሉ ኃጢአት እንጂ» 1ኛ ዮሐ 2፤1-2
ኃጢአትን የሚያስተሰርየው ክርስቶስ ብቻ ነው። ከሰው ልጅ ይህንን ማድረግ የተቻለውና የሚቻለው ማንም የለም። ኃጢአትን የሚደመስሰው 41 ስግደት ወይም መስቀል መሳለም አይደለም። ስለኃጢአት ንስሐ ለሚገቡ አስተማማኝ ይቅርታን ማስገኘት የተቻለው መስዋዕት ክርስቶስ ብቻ ነው። «ማንም ኃጢአትን ቢያደርግ በአብ ዘንድ ጠበቃ አለን» በማለት ወንጌላዊው የነገረን ያንን የደም ስርየት ነው።

2/ ይቅርታ

 «ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና» 1ኛ ዮሐ3፤8  የኃጢአትም ዋጋው ሞት ነው። (1ኛ ቆሮ 15፤56) ከዚህ ሞት ለመዳን ኃጢአትን ስለመፈጸሙ የተጸጸተና ዳግመኛ ወደንስሐ የቀረበ ማንም ቢኖር የሞት ስርየቱ ያው አንዱ የቀራንዮው መስዋዕት ብቻ ነው። በዚያም ይቅርታን ያገኛል። «ኃጢአታችንን ይቅር በለን» ብለን እንጸልይ ዘንድ ተነግሮናል። ምክንያቱም « በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው» 1ኛ ዮሐ 1፤9
 ሲሞን መሰርይ የተነገረውን ትእዛዝ ከመፈጸም ይልቅ ጉዳዩን ወደሐዋርያው ሲመልስ ከማየታችን ውጪ ሐዋርያው ጴጥሮስም ለሲሞን በትክክል ስለኃጢአት የነገረው ቃል ይህንኑ ነበር። «እንግዲህ ስለዚህ ክፋትህ ንሰሐ ግባ፥ ምናልባትም የልብህን አሳብ ይቅር ይልህ እንደ ሆነ ወደ እግዚአብሔር ለምን» የሐዋ 8፤22
ስርየት የንስሐ ውጤት ነው። በዚህም የይቅርታን ጸጋ ይጎናጸፋል። ስርየታችንም የክርስቶስ ደም ነው። ኃጢአታችንን ስንናዘዝ በክርስቶስ የይቅርታን ሕይወት እናገኛለን።  «አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው» ሮሜ 6፤22 ንስሐ የገባ ሕይወት ከእምነት በሆነ መጸጸትና መመለስ ከእግዚአብሔር ይቅርታን ያገኛል። ንስሐ የጨፈገገ ልብ ነው። ሀዘን የተጎዳኘው። ይቅርታ ተስፋ ነው። ከሀዘን ወደ ሕይወት ፍካት የመመለስ ጎዳና። ተሐድሶ ዋስትና ነው። በገባው ንስሐና በተገኘ ይቅርታ ላይ የሚኖሩት አዲስ የለውጥ መንገድ ነው።

3/ ተሐድሶ

ተሐድሶና አዲስ ነገር መፍጠር የተለያዩ ነገሮች መሆናቸውን መለየት ይገባናል። ተሐድሶ የነበረው ማንነት ሲያረጅ፤ ሲፈርስ ወይም ሲበላሽ ወደቀድሞ ማንነቱ የመመለስ ወይም የማስተካከል አካሄድን ያመለክታል። በበደል ከንጽሕና የመጉደል ማንነት ደግሞ ኃጢአተኝነት ነው። ከኃጢአት የመንጻት ማንነት ደግሞ ወደቀደመው የሕይወት ማንነት መመለስ ማለት ነው። ይህም አሠራር መታደስን፤ መለወጥን፤ መስተካከልን፤ ዳግም መመለስን ያመጣል።
አዲስ መሆን ማለት ግን ያልነበረ አዲስ ግኝት፤ አዲስ ነገርን መጎናጸፍን፤ መፍጠርና መሥራትን ያመለክታል። ብዙ ጠማማዎች መታደስንና አዲስነትን በማምታታት የዋሃንን ለማሳሳት ሲሞክሩ ይስተዋላል። ስለተሐድሶ ምንነት መጽሐፍ ቅዱሳችን በደንብ አድርጎ የተናገረ ቢሆንም ያንን እውነት በጥመት እየተረጎሙ ከእግዚአብሔር ቃል ውጪ ሲያፈነግጡ እናያቸዋለን።  ከላይ በመግቢያችን ላይ ለመጠቆም እንደሞከርነው «ቤተ ክርስቲያን አትታደስም» የሚሉ ወገኖች መታደስን አዲስ ነገር ከመፍጠር ጋር በማያያዝ ቃሉን በማጣመም የመተርጎም ግትርነት የተነሳ ነው። ቤተ ክርስቲያን ወይም ኤክሌሲያ ማለት የክርስቲያን ጉባዔ ማለት ነው። የክርስቲያኖች ጉባዔ ደግሞ በክርስቶስ ያመኑ ሰዎች ማኅበር ማለት ነው። ጉባዔ ክርስቲያን ለግል ጸሎት፤ ለማኅበሩ ለራሱ፤ ለሀገርና ለዓለሙ ኃጢአት ስለይቅርታው ይጸልያሉ። በግል የበደሉ ሰዎች በንስሐ ይታደሳሉ። የጎደለው እንዲመላ፤ የጠመመው እንዲቀና፤ የስህተት መንፈስ እንዲወገድ ምህለላና ልመና ያደርጋሉ። የእግዚአብሔር ፈቃድ ያለበት ተሐድሶቱ እንዲመጣ አበክረው ይጸልያሉ። መታደስን ከሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ጋር የሚያያዙ ካሉ የማትታደስ ህንጻ ቤተ ክርስቲያን በዚህ ምድር የለችም።በአክሱም ያለችው የታቦተ ጽዮን ማደሪያ ቤት እንኳን ስንት ጊዜ ታደሰች? እነሆ አሁንም እየታደሰች ነው። የሳር ክዳን በቆርቆሮ ክዳን ይታደሳል። የጠመመው ግድግዳ፤ የፈረሰው ጣሪያ ይቃናል። ይታደሳል። በክርስትናው ዓለም ሰውም፤ ቤተ ጸሎቱም ይታደሳል። ቤተ ክርስቲያን ማለት ሰውም፤ ቤተ ጸሎቱም ማለት ከሆነ የማይታደሰው ምኑ ነው? እስከሚገባን ድረስ ቤተ ጸሎቱም ቤተ ሰዎቹም ይታደሳሉ። ዘማሪው ዳዊት «ነፍሴ ሆይ» በሚለው ዝማሬው እንዲህ ይላል።
«ኃጢአትሽን ሁሉ ይቅር የሚል፥ ደዌሽንም ሁሉ የሚፈውስ፥
ሕይወትሽን ከጥፋት የሚያድናት፥ በምሕረቱና በቸርነቱ የሚከልልሽ፥
ምኞትሽን ከበረከቱ የሚያጠግባት፥ ጕልማስነትሽን እንደ ንስር ያድሳል» መዝ 103፤1-5

ማደስ የእግዚአብሔር ሥራ መሆኑን ልንክድ አይገባም።
ሕዝበ እስራኤል ከባቢሎን ምርኮ ይመለስ ዘንድ በተፈቀደለት ጊዜ ነህምያ የቤተ መቅደሱን ቅጥር ለማደስ ከተወሰኑት ጋር ከባቢሎን ወደፈረሰችው ኢየሩሳሌም ወጥቶ ነበር። (ነህምያ 2፤1-20) ነገር ግን  ቅጥሩን የማደስ ሥራ እንቅፋት ገጠመው። ገሚሱ ፈቃድ ከሰጠው ከንጉሡ ጋር ለማጋጨት ሞከረ፤ ገሚሱም ጠላት ሆኖ መታደስ የለበትም በማለት በቀጥታ ጦርነት ገጠመ። የነህምያ የተሐድሶ ሥራ ፈተናው የጠፋውን ቅጥር ወደነበረበት መመለስ ብቻ ሳይሆን ከተቃዋሚዎች ጋር መዋጋትም ነበረው።
«ቅጥሩንም የሚሠሩትና ተሸካሚዎቹ በአንድ እጃቸው ይሠሩ ነበር፥ በአንድ እጃቸውም የጦር መሣሪያቸውን ይይዙ ነበር። አናጢዎቹም ሁሉ እያንዳንዱ ሰይፉን በወገቡ ታጥቆ ይሠራ ነበር ቀንደ መለከትም የሚነፋ በአጠገቤ ነበረ» ነህምያ 4፤17-18
የቤተ መቅደሱ መታደስ ፈተና በዚህ ብቻ ያበቃ አልነበረም። የራሱ ሰዎች ዘመነ ድርቁን ተገን አድርገው የተቸገሩ ሰዎቻቸውን በወለድና በአራጣ ብድር አስጨንቀው ያዟቸው። ንብረቶቻቸውን በወለድ አገድ በመያዝ ባዶ አስቀሯቸው። ለንጉሥ የሚከፈለውን ግብር መክፈል እስኪያቅታቸው ድረስ ግድ አሏቸው። በዚህም የተነሳ የቤተ መቅደሱ መታደስ ፈተና ላይ ወደቀ። ለመታደሱ የእግዚአብሔር እጅ ስለነበረበት በሰዎች ወጥመድ ተስተጓጉሎ የሚቀር አልነበረም።
«በወንድሞቻቸውም በአይሁድ ላይ ትልቅ የሕዝቡና የሚስቶቻቸው ጩኸት ሆነ። አያሌዎቹም። ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ብዙዎች ናቸው በልተንም በሕይወት እንድንኖር እህልን እንሸምት ይሉ ነበር። አያሌዎቹም። ከራብ የተነሣ እህልን እንሸምት ዘንድ እርሻችንና ወይናችንን ቤታችንንም አስይዘናል ይሉ ነበር። ሌሎቹም። ለንጉሡ ግብር እርሻችንንና ወይናችንን አስይዘን ገንዘብ ተበድረናል አሁንም ሥጋችን እንደ ወንድሞቻችን ሥጋ፥ ልጆቻችንም እንደ ልጆቻቸው ናቸው እነሆም ወንዶችና ሴቶች ልጆቻችን ባሪያዎች ይሆኑ ዘንድ ሰጥተናል፥ ከሴቶችም ልጆቻችን ባሪያዎች ሆነው የሚኖሩ አሉ ታላላቆችም እርሻችንና ወይናችንን ይዘዋልና ልናድናቸው አንችልም ይሉ ነበር። እኔም ጩኸታቸውንና ይህን ቃል በሰማሁ ጊዜ እጅግ ተቈጣሁ። በልቤም አሰብሁ፥ ታላላቆቹንና ሹማምቱንም። ሁላችሁ እያንዳንዳችሁ ወለድ ትወስዳላችሁ ብዬ ተጣላኋቸው ትልቅም ጉባኤ ሰበሰብሁባቸው። እኔ ለአሕዛብ የተሸጡትን ወንድሞቻችንን አይሁድን በፈቃዳችን ተቤዠን እናንተስ ወንድሞቻችሁን ትሸጣላችሁን? እነርሱስ ለእኛ የተሸጡ ይሆናሉን? አልኋቸው። እነርሱም ዝም አሉ፥ መልስም አላገኙም።  ደግሞም አልሁ። የምታደርጉት ነገር መልካም አይደለም ጠላቶቻችን አሕዛብ እንዳይሰድቡን አምላካችንን በመፍራት ትሄዱ ዘንድ አይገባችሁምን? እኔም ደግሞ ወንድሞቼም ብላቴኖቼም ገንዘብና እህል ለእነርሱ አበድረናል እባካችሁ፥ ይህን ወለድ እንተውላቸው። እርሻቸውንና ወይናቸውን ወይራቸውንና ቤታቸውንም ከእነርሱም የወሰዳችሁትን ገንዘቡንና እህሉን፥ ወይን ጠጁንና ዘይቱን ከመቶ እጅ አንድ እጅ እባካችሁ ዛሬ መልሱላቸው። እርሱም፦ እንመልስላቸዋለን፥ ከእነርሱም ምንም አንሻም እንደ ተናገርህ እንዲሁ እናደርጋለን አሉ። ካህናቱንም ጠርቼ እንደዚህ ነገር ያደርጉ ዘንድ አማልኋቸው። ደግሞም ልብሴን አራገፍሁና። ይህን ነገር የማያደርገውን ሰው ከቤቱና ከሥራው እንዲሁ እግዚአብሔር ያራግፈው እንዲሁም የተራገፈና ባዶ ይሁን አልሁ። ጉባኤውም ሁሉ። አሜን አሉ፥ እግዚአብሔርንም አመሰገኑ ሕዝቡም እንደዚህ ነገር አደረጉ»  ነህምያ 5፤ 1-13
የመታደሱ ሥራ እንቅፋት ሌላ ሦስተኛ እንቅፋት ገጠመው። የአገሩ ገዢ ሆኖ በነጉሡ የተሾሙት ሰንባላጥና ዐረባዊው ጌሳም ነህምያን ለመግደል ቅድ ነደፉ።  ሰንባላጥም ከቆላውም ስፍራ እንገናኝ ብሎ አምስት ጊዜ መልእክት ጻፈለት። ነህምያ ንጉሥ ሆኖ በኢየሩሳሌም ተቀምጧል እያሉ ከንጉሡ ሊያጣሉህ ነውና ተገናኝተን መፍትሄ እንስጠው በማለት ለጻፈለት ደብዳቤ ነህምያ የሰጠው መልስ መታደሱን ለማስተጓጎል የተፈጠረ የአንተ ድርሰት ነው የሚል ነበር።
«እኔም አንተ ከልብህ ፈጥረኸዋል እንጂ እንደ ተናገርኸው ነገር ምንም የለም ብዬ ላክሁበት።  እነርሱም ሁሉ ሥራው እንዳይፈጸም እጃቸው ይደክማል ብለው ያስፈራሩን ዘንድ ወደዱ አሁንም፥ አምላክ ሆይ፥ እጄን አበርታ» ነህምያ 6፤ 8-9
የመታደስ አገልግሎት ወደቀመ ማንነት የመመለስ ጎዳና በመሆኑ ተቃዋሚው ብዙ ነው። በአሮጌው ሕይወት ወድቀው እንዲቀሩ፤ የቀደመ ክብራቸውና ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጣቸውን ጸጋ እንዳያገኙ የሚያደርግ ተቃውሞ ፈታኝ ቢሆንም እግዚአብሔር ለተሐድሶት ያለው ዓላማ ሰዓቱ ከሆነ ማንም ሊያስቀረው አይችልም። በነህምያ ሕይወትም ያየነው እውነት ይህንኑ ነበር። የመታደሱ ሥራ ለእግዚአብሔር ቃል አገልግሎት እና ክብር እንጂ ለሰውኛ ጥቅም እስካልሆነ ድረስ ተሐድሶቱ እውን መሆኑ አይቀሬ ነው። ብዙ ሴራዎችና እንቅፋቶች ሊገጥሙ ይችላሉ። አሸናፊው ግን የእግዚአብሔር ዓላማ ነው። በእስራኤላውያንም የተሐድሶ ትግል ያየነው ነገር ይህንኑ ነበር። የቅጥሩ ሥራ እንደተፈጸመ የሕጉ መጽሐፍ ከተሸሸገበት ወጥቶ ይነበብ ጀመር። ነህ 7፤1-18 ያን ጊዜም «
ዕዝራም ታላቁን አምላክ እግዚአብሔርን ባረከ ሕዝቡም ሁሉ እጃቸውን እየዘረጉ። አሜን፥ አሜን ብለው መለሱ። ራሳቸውንም አዘነበሉ፥ በግምባራቸውም ተደፍተው ለእግዚአብሔር ሰገዱ» ነህ 7፤6
ከሞዓባውያንና አሞናውያን ጋር የተደባለቁ ሰዎች የእግዚአብሔር ሕዝቦች ሊባሉ እንደማይችሉ ከሕጉ መጽሐፍ ውስጥ ተጽፎ ስለተገኘ እንዲለዩ ተደረገ። ተከድኖ የኖረው የሕጉ መጽሐፍ ሲገለጥ የተሸሸገው ስህተት ይፋ ይወጣ ጀመር። ተሐድሶቱ ሲመጣ እግዚአብሔር ብቻ ይከብራል።
«በዚያም ቀን የሙሴን መጽሐፍ በሕዝቡ ጆሮ አነበቡ አሞናውያንና ሞዓባውያንም ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ ለዘላለም እንዳይገቡ የሚል በዚያ ተገኘ። የእስራኤልን ልጆች በእንጀራና በውኃ ስላልተቀበሉአቸውና ይረግማቸው ዘንድ በለዓምን ስለ ገዙባቸው ነው ነገር ግን አምላካችን እርግማኑን ወደ በረከት መለሰው። ሕጉንም በሰሙ ጊዜ ድብልቁን ሕዝብ ሁሉ ከእስራኤል ለዩ»  ነህ 13፤1-3
ካህኑ ዕዝራም ከቤተ መቅደሱ መታደስ በኋላ በመጽሐፉ እንደተጻፈው ይኖሩ ዘንድ ሕዝቡን ግድ ሲላቸው ነበር። የሕንጻው መታደስ እስራኤላውያንም ለእግዚአብሔር ቃል እንደሚሆን መታደስን ካላመጣ ምንም ስላልነበር ቃሉ በሚያዘው መንገድ እንዲታደሱ አድርጓቸዋል።
«ካህኑም ዕዝራ ተነሥቶ ተላልፋችኋል፤ የእስራኤልን በደል ታበዙ ዘንድ እንግዶችን ሴቶች አግብታችኋል። አሁንም ለአባቶቻችሁ አምላክ ለእግዚአብሔር ተናዘዙ፥ ደስ የሚያሰኘውንም አድርጉ፤ ከምድርም አሕዛብና ከእንግዶች ሴቶች ተለዩ አላቸው» ዕዝ 10፤10-11
እንግዳ ጋብቻን ከልዩ ልዩ አማልክት ጋር የሚፈጽሙና የሚያስፈጽሙ መጻሕፍትና አዋልድ እስካልተወገዱ ድረስ ንጹህ አምልኮተ እግዚአብሔር ሊኖር አይችልም። መዳን በአንዱ በእግዚአብሔር ብቻ እንደሆነ እስካልተነገረ ድረስ የእንግዶች አማልክት ጋብቻ አደገኛ ነው። «ዐሥርቱ ቃላተ ወንጌልን ይሁን ስድስቱ ቃላተ ወንጌልን ከመጠበቅ ይልቅ ተአምሯን ለመስማት ተሸቅዳደሙ» ከሚለው አምልኮተ ጣዖት ጋር ውልን እስካላፈረሱ ድረስ እግዚአብሔርን ማምለክ አይቻልም። «ሥሉስ ቅዱስን የካደ ተአምሯን ሰምቶ ዳነ» ከሚል አጋንንታዊ ትምህርት እስካልተላቀቁ ድረስ እውነተኛ አስተምህሮ በጭራሽ አይታሰብም።  በሰዎች ላይ የመዳን ተስፋ እንድናደርግ በማበረታታት ከራሳችን አልፎ የማናውቃቸውን ሠላሳ እና ዐርባ ትውልድ ዘሮቻችንን እንደሚያስምሩ ቃል ተገባላቸው በተባለ፤ የቂጣ፤የንፍሮ፤ የአፈር፤ የፍርፋሪ፤ የተቅማጥ ወዘተ የተስፋ መንገዶች ሆነው ከእግዚአብሔር ተሰጥተውናል የሚሉ ቢኖሩ በቃለ ኤጲፋኒዮስ የተረገሙ ናቸው።
«ወኢኮነ ተስፋ መድኃኒትነ በሰብእ፤ ወኢክህለ ሰብእ ያድኅነነ እምአዳም እስከ ተፍጻሜተ ዓለም አላ ውእቱ እግዚአብሔር ቃል ዘተሠገወ። ከመ ኢይኩን ተስፋነ በሰብእ ወኢንኩን ርጉማነ ወዳእሙ በእግዚአብሔር ሕያው» ሃይማኖተ አበው ዘኤጲፋንዮስ 59፤9-12
«የድነታችን ተስፋ ፍጡር በሆነ ሰው የተገኘ አይደለም። ከአዳም ጀምሮ እስከፍጻሜ ዓለም ሊያድነን የተቻለው(የሚቻለው) የለም። ርጉማን እንዳንሆን በሕያው እግዚአብሔር እንጂ ፍጡር በሆነው ሰው ላይ ተስፋ እንዳናደርግ።
ማጠቃለያ፤
ተሐድሶ ከውድቀት ለተነሳ፤ ወደእውነት ለመጣ ማንነት፤ ከስህተት ለተመለሰ ሕይወት የሚሰጥ ስያሜ ነው። መታደስ ጥንትም የነበረ፤ ዛሬም ያለ፤ ነገም የሚኖር ከእግዚአብሔር የሆነ ለሰዎች የተሰጠ መንገድ ነው። ኃጢአት በንስሐ ስርየትን ታመጣለች። ስርየት ይቅርታን ታስገኛለች። ይቅር የተባለ ደግሞ የታደሰ፤ የተስተካከለ ማንነትን ይጎናጸፋል። በሕጉ፤ በቃሉ እንደቀድሞው ለመኖር ዳግመኛ ቃል የሚገባበት ተስፋ ነው። በዚህ ተስፋ እስራኤላውያን መቅደሳቸውንም፤ ራሳቸውንም ከስህተት አድሰዋል።  ተሐድሶ የሚያስፈልገው የቀደመውን መንገድ መልሶ ለመከተል ነው። «መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት የሚለውን ጆሮ ያለው ይስማ» በተባለ ጊዜ የተነገረው ቃል ይኸው ነበር። «የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና» ተባለ። ስለዚህም ምን እንዲያደርግ ተነገረው?
«እንግዲህ ከወዴት እንደ ወደቅህ አስብ ንስሐም ግባ የቀደመውንም ሥራህን አድርግ፤ አለዚያ እመጣብሃለሁ ንስሐም ባትገባ መቅረዝህን ከስፍራው እወስዳለሁ» ራእይ 2፤4-5
የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ወደቀደመ ማንነቷ፤ ለእግዚአብሔር ብቻ ወደነበራት ቀናዒነትና ፍቅር እንድትመለስ በዮሐንስ በኩል በእግዚአብሔር የታየላት ራእይ ቢደርሳትም ለመስማት አልፈለገችም። ከጣዖት ጋር መሰሴኗን አልተወችም። እንደኤልዛቤልም እውነቱንና የዋሃኑን መግደል አላቆመችም። የንስሐ እድል ቢሰጣትም ከዝሙትና ግልሙትናዋ አልታቀበችም። ነገር ግን በውስጧ የነበሩ ትያጥሮናውያን የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን ድርጊትና ሰይጣናዊ አስተምህሮ ላልተቀበሉት ተስፋ ተሰጣቸው። እስከመጨረሻውም ጽኑ ተባሉ። የተነገረውን ተቀብላ ተግባራዊ ማድረግ የተሳናት የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን መቅረዟ ተወስዶ ከነአነዋወሯ ከጠፋ እነሆ ሁለት ሺህ ዘመናት ሆነ። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ዛሬ በኤጂያን ባህር ዳርቻ ፍርስራሾቿ የሚጎበኙ የቱርክ ኢስላማዊ ግዛት ከተማ ሆናለች።
የኛይቱ ኤፌሶንም ከትያጥሮን ቤተሰዎቿ የሚነገራትን ተሐድሶ ትቃወማለች። ነገር ግን በቁጥር መሳ ለመሳ እየሆናት ከመጣው ኢስላም ጋር በአንድ ወንበር ቁጭ ብላ ስለሰላም አወራለሁ ትላለች። እንዲያውም ከሕዝቡ ቁጥር 50-60% ኢስላም ነው እያለ የራሱን መንግሥት ናፋቂ ከሆነ ሃይማኖት ጋር ጊዜዋን ከምትገድል ከእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠበቅባትን ፈጽማ የቀድመ ኃይሏን ማደስ አይሻላትም ነበር? ዝሙትና የዝሙት ወሬ፤ ግፍና ቅሚያ፤ በደልና ዐመፃ፤ ስካርና ባዕድ አምልኮዋን ማስወገድ አይሻላትም ነበር? ከንቱ ተስፋና ስሁት ምክንያተ ድኂን ከምትዘራ ይልቅ እውነቱን በአደባባይ ብትመሰክርና የቀደመ የንጉሥ ፍቅሯን ብትመልስ አይሻላትም? ከንቱ ጋብቻቸውን እንዳፈረሱ እስራኤላውያን በሰዎች ላይ የተንጠላጠለ ከንቱ ጋብቻዋንና የጋብቻ መጽሕፍቶቿን ጥላ ልብን በሚያቃጥለው በንጉሡ መጽሐፍ ላይ መጣበቅ አይበጃትም ነበር?
 እምቢ አልሰማም ብትል ግን ንጉሥ በቃሉ ከተናገረው አንዳች አያስቀርም። እነዚያ ተሟጋች ነን ባይ ልጆችሽን ጨምሮ ስሁቱን አስተምህሮዋን እንደእውነት ለተናገሩ ሁሉ ዋጋቸውን ይሰጣቸዋል።  «ልጆችዋን በሞት እገድላቸዋለሁ» ራእይ 2፤23
«መንፈስ ለአብያተ ክርስቲያናት ያለውን ይስማ» ማለቱ ለዛሬዋም ቤተ ክርስቲያንም ጭምር መሆኑን ልናስተውል ይገባናል።

2 የተሰጡ አስተያየቶች

የፓስተር ተከስተ ጌትነት የወሲብ ቅሌት በቪኦኤ

የዝሙትና የአፍቅሮ ንዋይ አንበሳ ያልሰበረውን መንፈሳዊ ሰው ማግኘት ከባድ እየሆነ ነው። በመጨረሻው ዘመን ላይ ሰይጣን እንደሚያገሳ አንበሳ እየዞረ ሰዎችን የሚሰብርበት ትልቁ መንጋጋው ትዕቢት፤ ዝሙትና ገንዘብን መውደድ ናቸው።
በየቤተ እምነቶቹ ትላልቅ የሚባሉት ሁሉ መንፈሳዊ አከርካሪያቸው የተሰበረው በነዚህ ወጥመዶች ነው። ጳውሎስም አለ፤ «ስመጣ፥ እንደምወደው ሳትሆኑ አገኛችሁ ይሆናል እኔም እንደምትወዱት ሳልሆን ታገኙኝ ይሆናል ብዬ እፈራለሁና፤ ምናልባት ክርክር ቅንዓትም ቁጣም አድመኝነትም ሐሜትም ማሾክሾክም ኩራትም ሁከትም ይሆናሉ፤
እንደ ገና ስመጣ በእናንተ ዘንድ አምላኬ እንዲያዋርደኝ፥ አስቀድመውም ኃጢአት ከሠሩትና ስላደረጉት ርኵሰትና ዝሙት መዳራትም ንስሐ ካልገቡት ወገን ስለ ብዙዎች ምናልባት አዝናለሁ ብዬ እፈራለሁ»
2ኛ ቆሮ 12፤20-21

0 የተሰጡ አስተያየቶች

ከብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የካይሮ ጉብኝት በከፊል


የኮፕቲክ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ የሆኑት አቡነ ታዋድሮስ ለብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ባደረጉላቸው ጥሪ ይፋዊ ጉብኝት አድርገው መመለሳቸው ይታወሳል። ፓትርያርክ ማትያስ በቆይታቸውም ከግብጽ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው በብዙ ጉዳዮች ላይ የተነጋገሩ ሲሆን የኮፕቲክ ገዳማትንም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል። ከጎበኝታቸው በኋላ በግብጽ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በሆኑትና ምድረ ግብጽን እስኪለቁ ከጎናቸው ባልተለዩት በአቶ ሙሐመድ ድሪር ቱርጁማንነት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል። በከፊል የተወሰደው ይህ ትዕይንተ ምስል የተገኘው ከራዲዮ ምስር 88.7 FM ነው።

0 የተሰጡ አስተያየቶች

የመቁጠሪያዋና የቅባቱ ምስጢር!


0 የተሰጡ አስተያየቶች

«ሳይኖረኝ አኖርከኝ»

አሌክስ ሎዶቅያ፤ ኦስሎ/ ኖርዌይ ( 6/5/ 2007 )

   የሰው አስጨናቂ አገዛዝ ክብደት፣ የመከራ ስጋት፣ የኑሮ ውድነት ጭንቀትና የወዳጅ ክዳት ለሚያስጨንቁን መፍትሔው የሚያኖረንን ማወቅ ነው፡፡ በዘላለም ክንዶቹ ደግፎ፣ አእምሮን ሁሉ በሚያልፍ ሰላሙ አሳርፎ፣ ሳይዘነጋ አስቦ፣ ቸል ሳይል እንደ ዐይኑ ብሌን ጠብቆ፣ ሳይሰስት ሰጥቶ እና ሳይደክም ተሸክሞ የሚያኖረን እግዚአብሔር ነው፡፡ ለሚታየው ኑሮአችን መሰረቱ የማይታየው እምነታችን ነውና በእግዚአብሔር እንመን፤ በእግዚአብሔርም እንተማመን፡፡

   ከኮሌጅ ተመርቄ እንደወጣሁ በሲኦል ፊት የተጣልኩ ያህል እጅግ ከፍቶኝ ነበር፡፡ ተስፋ ያደረኳቸው ሁሉ አነሱብኝ፡፡ የያዝኩት ዲግሪ ሰርተፊኬት የሌላቸው ሰዎች የሚበሉትን እንጀራ እንኳ ሊሰጠኝ አልቻለም፡፡ በቤቴ እንደ እንግዳ በእናቴ ጓዳ እንደ ባእድ በመሆኔ ልቤን ሀዘን ወጋው፡፡ አንድ ወዳጄ ጋር ሻይ ቡና እያልን የወዳጄ ወዳጅ ድንገት ተቀላቀለን፡፡ “ሕይወት ከምርቃት በኋላ እንዴት ነው?” አለኝ “እንዳሰብኩት መኖር አልቻልኩም” አልኩት፡፡ እርሱም የፍቅር መንፈስ በለበሰ ተግሳጽ “ወዳጄ እንደተፈቀደልህ እንጂ እንዳሰብከው አትኖርም” አለኝ፡፡ ይህ ቃል በልቤ ቀረ፡፡ እንዳሰብነው ለመኖር ብዙ ደክመን ይሆናል፤ መኖር የምንችለው ግን የሚያኖረን አምላክ እንደፈቀደልን ነው፡፡
   ተስፋ ካደረኳቸው ሁሉ አይኔን አንስቼ የሁሉ ዐይን ተስፋ ወደሚያደርገው የዘላለም አምላክ አንጋጠጥኩ፡፡ ያላሰብኩት በረከት ከበበኝ፡፡ ከምኞቴ በላይ በሆነ ከፍታ እግዚአብሔር አኖረኝ፡፡ ከወራት በኋላ በእልፍኜ ብቻዬን ሳለሁ የምድረበዳውን ጉዞ ከጀመርኩ በኋላ የሆነውን አሰብኩ ዐይኖቼ በእንባ ተሞሉ አንደበቴም ለምስጋና ተከፈተ “ሳይኖረኝ አኖርከኝ አምላኬ ተመስገንልኝ” አልኩት፡፡ ዲያሪዬም ላይ የሆነውን ሁሉ መዘገብኩት፡፡ እግዚአብሔር የሚኖር የሚያኖር አምላክ ነው፡፡ ምንም ሳይኖረን እግዚአብሔር እንደሚያኖር የእስራኤል ታሪክ ማሳያ ነው፤ ማንም በማይቀመጥበትና በማያልፍበት ምድረበዳ መርቷቸዋልና፡፡
 ዘዳ. 32፡11፣ ኤር. 2፡5፡፡
   የአንዲት እህት የሰላምታ ቃል “ኖሮ ያኖረኛል” በሚል ምስክርነት የተቃኘ እንደሆነ ሰምቼ ራሴን በሚያኖረኝ ውስጥ ስላገኘሁት ልቤ ሀሴት አደረገ፡፡ እግዚአብሔር ኖሮ የሚያኖር አምላክ ነው፡፡ መኖሩ የሚያኖረን ህልውናው ያቆመን ከእንግዲህ አንታወክም፡፡ ሕይወታችን ለምን በስጋት ታጠረ? የሚያኖረን እግዚአብሔር አይሞትም፤ አይሻርም፤ አያረጅም፤ አይደክምም፤ አይሰለችም፡፡ በአስፈሪ ሁኔታዎች ብንከበብም መኖር እንደምንችል የሚገባን እግዚአብሔር እንደሚያኖረን ስናውቅ ነው፡፡ እግዚአብሔር እንደሚያኖራት የገባት ነፍስ የአራዊት መንጋጋ፤ የክፉዎች መንጋ አይነካትም፡፡
ዳዊት “በክንፎችህ ጥላ ደስ ይለኛል፡፡ ነፍሴ በኋላህ ተከታተለች፡፡ እኔንም ቀኝህ ተቀበለችኝ፡፡” አለ መዝ. 62፡9፡፡ እረኛችንን በደስታ እንከተል በሚያስተማምን እረፍት፣ በማይነጠቅ ደስታና አይምሮን ሁሉን በሚያልፍ ሰላም እንኖራለን፤ በለምለም መስክ እንሰማራለን፤ በእረፍት ውሃ በፍቅሩም ጥላ እናድራለን፤ በጥበቃው አጥር እንከበባለን፤ እረኛችን ሆኗልና የሚያሳጣን የለም፡፡ መዝ. 22፡1
ሙሴ ምድረ ርስትን በናባው ተራራ በሩቅ ከተሳለመ በኋላ ስለማይወርሳት አዘነ፡፡ እግዚአብሔር ግን መኖሪያህ እኔ ነኝ አለው፡፡ ሙሴም ለሕዝቡ “ይሹሩን ሆይ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው፡፡ የዘላለም ክንዶች ከአንተ በታች ናቸው፡፡” አለ፡፡ ዘዳ. 33፡26-29፡፡ የዘላለም አምላክ እግዚአብሔር የዘላለም መኖሪያችን ነው፡፡ እኛም የእርሱ መኖሪያ ዐለማት ነን፡፡
ለመኖር ከመሠረታዊ ጥያቄዎች ባሻገር ለዛሬ ጥበቃ ለነገም ተስፋ ያስፈልገናል፡፡ እግዚአብሔር ለዘላለም መግባትና መውጣታችንን ሳያንቀላፋ የሚጠብቅ መልካም እረኛ ነው፡፡ የትውልድ መጠጊያ የሁላችን ተስፋ እርሱ ነው፡፡ ችግረኛና ምስኪኑን ይረዳዋል፡፡ መዝ. 71፡12፤ 120፡1-8፤ 144፡15፡፡
ስለዚህ ልቤ ከዘማሪው ጋር አብሮ ዘመረ “የሚያኖረኝ ጌታ ነው፤ ምን ያስጨንቀኛል፡፡ የሚያስፈልገኝንም ያዘጋጅልኛል፡፡ አይሻግትም አይጎልም ሞሰቤ፤ ከሰማይ ነው ቀን በቀን ቀለቤ” እንደ እኔ ምንም ሳይኖራችሁ የሚኖረው እግዚአብሔር የሚያኖራችሁ፤ ሀብት፣ እውቀትና ስልጣን ያላስመካችሁ ኖሮ የሚያኖረንን ባርኩ፡፡ ከፍ ስንል ከፍ ያደረገንን አምላክ በምስጋና ቃል ከፍ ማድረግን አንርሳ፡፡
// ካነበብኩት//
0 የተሰጡ አስተያየቶች

ይድረስ ለወንድሜ ዳንኤል ክብረት!

( ምንጭ፤ አባ ሰላማ )
 እኔ ስሜ እገሌ እባላለሁ የተወለድሁት በጎጃም ክፍለ ሀገር ነው። እንደ ማነኛውም የቤተ ክርስቲያን ልጅ ገና የሰባት ዓመት ልጅ ሆኜ ነበር ቆሎ ት/ ቤት የገባሁት። በልጅነቴ የሀገሬ ቤተ ክርስቲያን መርጌታ ከሆኑት ከዬኔታ ሞገሴ ፍቅር እያገኘሁ አደግሁ። እናት እና አባቴ ጥሩ አሳዳጊዎች ነበሩ፣ ነገር ግን ባሀገሩ ባህል ትምህርት እንዲገባው በሚለው አስተሳሰብ ለምኜ እየበላሁ እንድማር ተገደድሁ። አባቴ በግ እንድጠብቅለት ነበር የሚፈልገው፣ እናቴም እንዲሁ። የኔታ ግን ቤተ ሰቦቼን እየመከሩ እንድማር አደረጉ። ቀን ፊደል አቡጊዳ፣ መልክተ ዮሐንስ ወንጌለ ዮሐንስ ከዚያም ዳዊት ጾመ ድጓ እየተማርሁ፣ ማታ ደግሞ የዘወትር ጸሎት፣ ውዳሴ ማርያም፣ አንቀጸ ብርሃን፣ መልክአ ማርያም መልክአ ኢየሱስ፣ ት/ኅቡአት፣ ውዳሴ ማርያም ዜማ፣ መስተጋብዕ፣ አርባዕት፣ አርያም፣ ክስተት፣ ሰለስት፣ ስብሐተ ነግሕ። ተማርሁ እነዚህ ሁሉ የቃል ትምህርት ናቸው ሌት ያለ መብራት ስለምንማራቸው በቃል የምንይዛቸው ናቸው።
 ይህ በእንዲህ እንዳለ እነዚህን ትምህርቶች አጠናቅቄ ገና ሳልጨርስ ከብፁእ አቡነ መቃርዮስ የምስራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ዲቁና ተቀበልሁ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ካጠናቀቅሁ በኋላ የኔታ መርቀዉኝ ጉልበት ስሜ ተሰናብቼ ቅኔ ቤት ገባሁ። ቅኔው ወዲያው ነበር የገባኝ። ሦስት ቦታዎች ላይ ከጉባኤ ቃና እስከ መወድስ ያሉትን ሞልቼ አራተኛው ቦታ ላይ አስነጋሪ ሆንሁ። በቅኔ አዋቂነቴ ባካባቢው ሊቃውንት ዘንድ አድናቆትን አትርፌ ነበር። የኔን ቅኔ ለመስማት የማያሰፈስፍ ሊቅ አልነበረም።

 ከቅኔ ቤት እንደተመልስሁ ወደ ዜማ ቤት ገብቼ አስቀድሜ የተማርኳቸውን የቃል ትምህርቶች እንደ ገና አጥንቼ ድጓ የተባለውን ረጅም ትምህርት ተማርሁ። አከታትየም ወደ አቋቋም ቤት ገባሁና መዝሙር፣ ክብረ በዓል፣ ወርኀ- በዓል፣ ጾም ቀለም፣ ለእመ ኮነ፣ አጠናቀቅሁ። ከዚያም ዝማሬ እና መዋስዕት ተምሬ መሪጌታ ሆኜ ተሾምኩ። በዚህ ጊዜ ጎርምሼ ነበር። እናትና አባቴ ሊድሩኝ እንደሆነ ስሰማ መጽሐፍ ሳልማር አልታሰርም ብዬ ወደ ሽዋ ተሻገርሁ። በአታ ገዳም አራት ኪሎ ገብቼ ብሉይ ኪዳንን ተማርሁ፣ ጎን ለጎንም ሐዲስ ኪዳንን አጠናሁ። የትምህርት ጥማቴ እየጨመረ ሲመጣ ወደ ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ ገብቼ በአራት ዓመቱ ሴሚናር ኮርስ መውሰድ ጀምርኩ። በዚያን ጊዜ አንድ የማህበረ ቅዱሳን አባል በጣም ወዳጅ ሆኖ ቀረበኝ፣ እኔም በጣም ወደድሁት፣ በትርፍ ሰዓቴ ውዳሴ ማርያም አንድምታ አስተምረው ጀምርሁ። እርሱ ግን ታቦት እየቀረጸ ይሸጥ እንደነበር ስላወቅሁ በተለይም ያቡነ ጎርጎርዮስ ታቦት ቀርጾ ሳየው ተቆጣሁ፣ በሲኖዶስ ያልተወሰነ ነገር እንዴት ላንድ ግለሰብ ታቦት ትቀርጻለህ? ብዬ ተቃወምሁት። ወጥመድ ውስጥ የገባሁበት ቀን ይህ ቀን!!!
 ይህ ወዳጄ ከኮልፌ እየተነሣ ወደ ማህበረ ቅዱሳን ቢሮ አምስት ኪሎ ሲመላለስ ነገር እንደሚያመጣብኝ አልጠበቅሁም ነበር። ወዲያውም በማላውቀው ሁኔታ መናፍቅ ተብየ ተከሰስሁ፤ አንተም ዳንኤል ክብረት የስማ ጽድቅ ጋዜጣ አዘጋጅ በነበርህበት ጊዜ እኔን ሳታውቀኝ ስሜን ጠቅሰህ በጋዜጣ መናፍቅ ነው ብለህ አወጅህ። ከዚያ ሰዓት ጀምሮ ሕይወቴ አደጋ ላይ ወደቀች፣ በቆሎ ትምህርት ቤት ውሻ ሲያባርረኝ፣ ባለጌ ሲገፋኝ፣ ቁንጫና ትኋን፣ ሲፈራረቅብኝ፣ ረሃብና ጥም ሲያሰቃየኝ ያደግሁ ሰው ነኝ። ተመርቄ እረፍት አገኛለሁ ስል ዕዳ አመጣህብኝ። ስማ ጽድቅን ያነበቡ ሁሉ ምራቅ ይተፉብኝ ጀመር፣ ከጓደኞቼ አብሮኝ የሚቆም ጠፋ፣ ስበላ ብቻየን፣ ስሄድ ብቻየን ሆነ ኑሮዬ፤ በመጨረሻም የቤተ ክህነቱን ባለሥልጣናት አሳምናችሁ ኖሯል ያለምንም ፍርድ ከት/ቤቱ ተባረርሁ። ዳንኤል አስበው እስኪ እንደ ድሮዬ ለምኜ አልበላ? የማፍርበት ዕድሜ ላይ ነው ያለሁት። በቤተ ክርስቲያን ያደግሁ እንደመሆኔ ደሞዝ መቀበል ሲገባኝ ያንተ ጋዜጣ ዋጋዬን አሰጥቶኛል።

  ምን ላድርግ ብዬ አሰብሁ፣ ሰዎችም አላስጠጋ አሉኝ፣ እሙንቱሰ ይጸልዑኒ በከንቱ እነርሱ ግን በከንቱ ጠሉኝ እንደተባለው ባልተጨበጠ ወሬ ተጠላሁ። ረሐቡም እየጸናብኝ ማደሪያም እየቸገረኝ ሲመጣ ስማአ ጽድቅን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጦችን ማዞር ጀመርሁ። ስሜን ያጠፋችውን ጋዜጣ እየሸጥሁ ምሳዬን መብላት ችዬ ነበር። ማታ ማታ ያልሸጥኋቸውን ጋዜጦች በረንዳ ላይ አንጥፌ እተኛለሁ። ካልተቀደዱ በማግስቱ እሸጣቸዋለሁ። ማን ይረዳኛል? ዳንኤል? በዚያን ጊዜ አንተና ጓደኞችህ አምስት ኪሎ በሚገኘው የማህበረ ቅዱሳን ሆቴል አልጫና ቀይ ወጥ እየቀላቀላችሁ ትበሉ ነበር። እኔ ሳለቅስ እናንተ ትስቁ ነበር። ጌታ በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ይህን ነገር እንዴት ያየው ይሆን?
   ከላይ የተቀስኋቸውን የትምህርት ዓይነቶች ተንከራትቼ ተምሬ የበረንዳ አዳሪ ስሆን እንኳንስ ሊማሯቸው ስማቸውንና ቅደም ተከተላቸውን እንኳ የማያውቁ ሰዎች የቤተ ክርስቲያን ሰው በመምሰል እያሳዳዱን እንጀራ ይበሉብናል። ዳኛው ማን ይሆን? እያልሁ ሳዝን በከንቱ መገፋቴን ያዩ አንድ አስተዋይ ሰው ወደ ሀገረ ስብከቱ አስተዳዳሪ አቀረቡኝ። እኒያ አስተዳዳሪ እኔን ሲያዩ ያነቡትን እንባ አልረሳውም። ዓይኖቼ ወደ ውስጥ ገብተው አንጀቴ ታጥፎ በየወንበሩ ክልትው ስል ያየ እንዴት አያለቅስ? ቤተ ክርስቲያን ሃያ ዓመት ሙሉ አስተምራ ባንድ ጋዜጣ ምክንያት አውጥታ ስትጠለኝ እንዴት አያስለቅስ? ጌታ በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ይህን ነገር እንዴት ያየው ይሆን?
 ወደ ሀገሬ እንዳልገባ ስሜን በቤተ ክርስቲያን እሁድ ቀን ባንድ ቄስ አማካኝነት አቆሽሻችኋል። ቤተ ሰቦቼ ከዚያ ቄስ ጋር ደም ሊቃቡ ይችሉ ነበር። ጊዜ ይፍታው ብለው ዝም አሉ እንጂ። ዳንኤል ብዙ ለመማር ብዙ ለማደግ ያሰብሁትን ሰው የንጀራ ጉዳይ ብቻ እንዲያሳስበኝ አደረግኸኝ። ዋና ጸሎቴ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገብቼ በተማርሁት እያገለገልሁ እንጀራ የምበላበትን መንገድ ብቻ ማግኘት ነበር። እንዴት እንደጎደሃኝ አስበው። አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ስሄድ የሚያስገባኝ ባለመኖሩ አምሳ ሳንቲም ለዘበኛ እየከፈልሁ እገባ ነበር። ስብከተ ወንጌል ክፍሉ ብር ያለኝ መስሎት እጅ እጄን እያየ ለረጅም ጊዜ አሰቃየኝ። በስንት መከራ አንድ ቤተ ክርስቲያን በሦስት መቶ ብር ተመደብሁ። የሥቃዬ ዘመን አበቃ ብየ ስጠበቅ በተመድብሁ ባመቴ ስሜን በጋዜጣ እንደ ገና አወጣኸው። ስማ ጽድቅ ጋዜጣን ማየት አልወድም እንደ ተናዳፊ ዕባብ ያህል ስለምፈራው ነው። ስማ ጽድቅ ጋዜጣ ሲዞር ሳይ እራሴን ያዞረኝ ነበር።
  አንድ ቀን አንድ ጓደኛዬ የማታ ፕሮግራም ጋብዤው መጥቶ አስተምሮ ከጨረሰ በኋላ እስከሚሳፈርበት ፌርማታ ድረስ ልሸኘው ተከተልሁት። ዳንኤል ክብረት አለቀቀህም? አይደል? አለኝ ለመሆኑ ያውቀሃል? ሲል ቀጠለ። ምን ነው ደግሞ ምን አመጣ? አልሁት። ስምህን ስማ ጽድቅ ጋዜጣ ላይ አላየኸውም? እንዴ መናፍቅ ብለው አውጥተዋል እኮ! ሲለኝ? ከቆምሁበት ላይ ተዝለፍልፌ ወደቅሁ። ጓደኛዬም እኔን ተሸክሞ ወደ ቤቴ ተመለሰ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ለሁለት ወር ያህል ታምሜ ተኛሁ። በዚያን ወቅት እውቀቴ እንጂ እምነቴ ደካማ ነበር። የሰንበት ተማሪዎች ስማ ጽድቀን አንብበው ኖሯል ምንም ሳይጠይቁኝ አባረሩኝ፣ ለአንድ ዓመት ያህል ሳስተምራቸው ያደንቁኝ የነበሩት ሁሉ ስማ ጽድቅን ሲያነቡ ይደቀድቁኝ ጀምር። ስማ ጽድቅ ስላነበቡ እንጂ እኔ ምን እንዳልሁ መረጃ አላገኙም። ዳንኤል መናፍቅ ነው ስላለ ብቻ መናፍቅ ነው ተባልሁ። ጌታ በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ይህን ነገር እንዴት ያየው ይሆን?
  ከቤተ ክርስቲያን ወጥቼ የት ልሂድ? ሌላ ቤተ ክርስቲያን አላውቅ? ሁሉንም ትቼ የቀን ሥራ እየሰራሁ ዘመናዊ ትምህርት ልማር አልሁና ወደ አቃቂ ሄጄ ስሚንቶ ማቡካት ጀመርሁ። ከዚያም የማታ እየተማርሁ ባጭር ጊዜ አንደኛ እየወጣሁ ሰበተኛ ክፍልን አጠናቀቅሁ። እግዚአብሔር ግን አልተወኝም፣ ታምሜ እንዳልሞት፣ እንዳልድን ሆንሁ። አይ ያ ጊዜ አንድ ዳቦ የሚሰጠኝ ያጣሁበት ጊዜ እንዴት የሚያስፈራ ነበር? በዚህ ጊዜ አንድ ነገር ገባኝ እግዚአብሔር ስለስሙ መከራ እንደቀበል እንጂ ኑሮ ተመችቶኝ ዓለማዊ እንድሆን እንደማይፈልግ ተረዳሁ። ሆኖም በእምነት የበሰለ ሰው አግኝቶ እስኪረዳኝ ድረስ እምነቴ ጠንካራ አልነበረም። ከዚህ በኋላ እስኪ ዳንኤል የሚተወኝ ከሆነ፣ ሰውም የማያገለኝ ከሆነ ልመንኩስ ብየ መነኮስሁ። እኔ ማግባት እንጂ መመንኮስ አልፈልግም ነበር። ማህበረ ቅዱሳን መነኩሴ ይወድ እንደሆነ ብዬ አደረግሁት? እውነትም መከራው ቀነሰልኝ ጌታ ግን ይህን አካሄዴን አልወደደውምና ደስታ የለኝም። በመሠረቱ እኔ ግፍን ስቀበል ተሐድሶ አልነበርሁም ተሃድሶ የተባልሁበት ነገር ምንድን ነው? ብዬ ሳጠና ግን ተሐድሶ ሆንሁ። ጌታ ያንን ሁሉ ግፍ እንድመለከት ያደረገኝ ለካ ተሃድሶ እንድሆን ነው። እንዲህ ዓይነቱ የግፍ ሥራ እንዲቆም የማይመኝ ማን አለና?
 ወንድሜ ዳንኤል ሆይ!አንተ በክብር በዝና በብልጽግና እየተጨበጨበልህ እየኖርህ ነው። ግን በዚህ ነገር ንስሐ ግብተህ ይሆን? ወይስ ረስተኸው ይሆን? ስንት ያልታበሱ እንባዎች እንዳሉ ታውቅ ይሆን? ሕይወታቸው የተጎሳቆለ፣ የተሰደዱ የተገደሉ፣ አንገት የደፉ፣ የተደበደቡ፣ ከቤተ ሰባቸው የተፈናቀሉ ስንት እንዳሉ ታውቃለህ? አንተ እኔን ከጨዋታው ሜዳ ገፍተህ አስወጥተህ አንተ የቤተ ክርስቲያን ሊቅ ስትባል በየትኛው ህሊናህ ተቀበልኸው? ጌታ በመንግሥቱ በመጣ ጊዜ ይህን ነገር እንዴት ያየው ይሆን?
 አይ አንቺ በርባንን እየፈታሽ ክርስቶስን የምትሰቅዪ የይሁዳ ዓለም?! ጌታ በመጣ ጊዜ የሚያድንሽ የለም።
ስሜን ከመጽሐፌ ላይ ታገኛላችሁ ታሪኬን እየጻፍሁ ነው። አሁን ስሜን ብነግራችሁ ለስማ ጽድቅ እጋለጣለሁ ጥቂት ጊዜ ተውኝ እባካችሁ። ታሪኬን ሳልጽፈው መሞት አልፈልግም።
1 የተሰጡ አስተያየቶች

ግን የምር ምን ዓይነት ትውልድ እያፈራን ነው?

(ደጀ ብርሃን፤ 3/5/2007)
ይህን  ጽሁፍ ለሚያስተውለው አስደንጋጭ የዘመኑ እውነት ነው። በየስርቻው በስመ ጸሎት ቤት የሚደረገውና የሚፈጸም ስንት ጉድ አለ? የተቀደሰ ውሃ፤ የተቀደሰ ጨርቅ፤ የተቀደሰ መጽሐፍ፤ የተቀደሰ ፓስፖርት፤ የተቀደሰ ዘይት ኧረ ስንቱ በስመ «የተቀደሰ» ይቸበቸባል? አንድ ቤተ ክርስቲያን በምእመናን ጉባዔ የማትመራ ከሆነና በአንድ ፓስተር ወይም ቄስ ስም በፈቃድ የተመዘገበች ከሆነች የግል ሱቅ ትባላለች እንጂ ጉባዔ ቤተ ክርስቲያን ልትባል አትችልም። በዘመነ ሐዋርያት በግል የተመዘገበች ጉባዔ ቤተ ክርስቲያን አልነበረችምና ነው። ሩኒ ከሚባል የማንቸስተር ዩናይትድ እግር ኳስ ተጫዋች ደመወዝ ጋር ራሳቸውን እያስተያዩ እነሱ ሰይጣንን በማስወጣታቸው 70 ሺህ ብር ደመወዝ ወይም 80 ሚሊየን ብር በባንክ አካውንታቸው ውስጥ መገኘቱ እንደማያስገርም ሲናገሩ ትንሽ አይሰቀጥጣቸውም። ደመወዝ ማግኘት አንድ ጉዳይ ነው። ሰይጣንን ለምናስወጣ ለእኛ ግን ይህ ትንሽ ገንዘብ ነው ማለት ደግሞ ሌላ ነው። በዚህ ጉዳይ ሌላ ጊዜ እንመለስበታለን። ለዛሬ ግን ከወደ ኬንያ የተገኘውን መረጃ እናካፍላችሁ!

ከዮናስ ሓጎስ ናይሮቢ
#‎አቋራጭ_የለመደ_ትውልድ‬
ልብወለድ…………………………ቢሆን ደስ ባለኝ ነበረ…
አዳራሹ ጢም ብሎ በመሙላቱ መግባት ያልቻሉ በሺህ የሚቆጠሩ «ምዕመናን» በር ላይ ከተመደቡ አስተናጋጆች ጋር ዱላ ቀረሽ ፀብ ላይ ናቸው። አስተናጋጆቹ ግን በተረጋጋ መንፈስ አዳራሹ ውስጥ የሚካሄደው ነገር ሁሉ በአዳራሹ ዙርያ በተተከሉ 80" ቴሌቨዢኖች በቀጥታ እንደሚተላለፍ ሕዝቡን ለማሳመን እየወተወቱ ነው።
ከአዳራሹ በር በስተቀኝ ያለ አንድ ሱቅ የሚመስል መስኮት ጋር በእጃቸው ብር ይዘው የሚያውለበልቡ ሰዎች ወርረዉታል። ፓስተር ኪኛሪ የፀለየበት ነው የተባለ «ቅዱስ» ውኃ እና እንደ መቁጠርያ የመሰለ ነገር እያንዳንዳቸው በ2000 ሽልንግ (400 ብር) እየተሸጡ ነው። ምንም እንኳ ሻጮቹ በብዛት እንዳለና እንደማያልቅ ለማሳመን ቢጥሩም ሕዝቡ እነርሱን መስሚያ ጆሮ ያለው አይመስልም
አዳራሹ ውስጥ ፕሮግራሙ ተጀምሯል። ፓስተር ኪኛሪ «መንፈስ ቅዱስ» በገለጠለት መሰረት ከሕዝቡ መሐል መርጦ ያወጣቸውን ለዕለቱ እንዲድኑ የተመረጡ ሰዎችን በሰልፍ መድረኩ ላይ ደርድሯቸዋል።
አንዱ አስተናጋጅ በእጅ ማስታጠቢያ ጎድጓዳ ሳህን ውኃ ይዞ ወደ መድረኩ ወጣና እጃቸውን ነክረው እንዲታጠቡ ትዕዛዝ ሰጠ። «የተመረጡት» እጃቸውን ሲታጠቡ አጁን ዉኃው ውስጥ በመጨመር እጃቸውን እየፈተገ ማጠብ ጀመረ። ፓስተሩ አሁንም በከፍተኛ ድምፅ ፀሎት እያደረሰ ነው።
በድንገት ማስታጠቢያው ውስጥ ያለው ውኃ እየቀላ እየቀላ ሄደና ደም መሰለ። የምትታጠበዋ ሴትዮ እጇን ከማስታጠቢያው መንጭቃ ለማውጣት ብትሞክርም አስተናጋጁ ጭምቅ አድርጎ በመያዝ አረጋጋት…
«ኃጥያትሽ፣ በሽታሽ፣ መርገምሽና ልክፍትሽ ሁሉ በዚህ ደም አማካይነት ከሰውነትሽ ወጥቷልና ደስ ይበልሽ!» አላት አስተናጋጁ።
ተረጋጋች!
ወድያውኑ በቅፅበት አስተናጋጁ ፈንጠር ብሎ «ፓስተር ፓስተር ና ተመልከት!!» ሲል በከፍተኛ ድምፅ ተጣራ።
ፓስተሩ ማይክራፎኑን ይዞ ወደ አስተናጋጁ ሲጠጋ ካሜራውም ተከተለው
«አየህ ከእጇ የወጣውን!» ሲል ትናንሽ መርፌዎች ከማስታጠቢያው ውስጥ አውጥቶ አሳየው።
«ኃሌሉያ!!!» ሲል ፓስተሩ አዲስ ሳይንሳዊ ግኝት እንዳገኘ ሁሉ ጮኸ። «አስማትና ድግምት ተደርጎብሽ ነበረ። ዛሬ ድነሻል! ፈጣሪ ይባረክ! ዛሬ ከእስራትሽ ነፃ ወጥተሻል!!» ሲል ጮኸ።
ከሰውነቷ መርፌ መውጣቱ የምር ያስደነገጣት ሴት መብረክረክ ስትጀምር አስተናጋጆቹ ደገፏት።
መድረኩ ላይ ያሉት «ዛሬ ለመዳን የተመረጡ ሰዎች በተራ በተራ ከአስማትና ድግምታቸው ተፈትተው ከአዳራሹ ጀርባ ወዳለ ክፍል በተራ ተራ ተወሰዱ።
በመሐል በመሐል በሚደረግ ዕረፍት ላይ የሚተላለፍ ማስታወቂያ አለ።
«ፍቅር ፣ ስራ ፣ ገንዘብ ማጣት አስቸግሮዎታል? ፓስተር ኪኛሪ ሊፀልይሎት ዝግጁ ነው!! አሁኑኑ በሞባይል ገንዘብ መላኪያ 310 ሽልንግ (60 ብር) ወደ ቁጥር ----------- ይላኩና ሁሉን ነገር በእጅዎ ያስገቡ!! ፓስተር ኪኛሪ የፀለየባቸው ውኃ እና መቁጠርያ በመሸጥ ላይ ናቸውና ፈጥነው ይግዙ!!!»
ኃጥያታቸው የተሰረየላቸው ሰዎችም ወደ አዳራሹ ጀርባ ካመሩ በኋላ ኪሳቸውን ሲዳብሱ ይታይ ነበረ።
**************************************************************
ምሽት ላይ የ KTN Investigative journalist JICHO PEVU በተሰኘ ታዋቂ ፕሮግራሙ ስለ ፓስተር ኪኛሪ አቀረበ።
ጋዜጠኛው በዘገባው ፓስተር ኪኛሪ ሕዝቡን እንዴት እንደሚያጭበረብር ወለል አድርጎ አሳየ። አስተናጋጆቹ እጃቸውን ፖታሲየም ተቀብተው በጣቶቻቸው መሐል መርፌ ይዘው በመግባት (ፖታሲየም ውሃ ጋር ሲቀላቀል ቀይ ከለር ይይዛል) ከዛም ባሻገር የእግዚአብሔር ስብከት አሰራጭበታለሁ በሚልበት ሬድዮ ፕሮግራም ላይ የተለያዩ ሐሰተኛ ምስክርነት የሚሰጡ ሰዎችን በገንዘብ እያማለለ እንደሚያቀርብ ተገለፀ። ለማስረጃነት ያህልም አንድ ከዚህ በፊት በፓስተሩ ፀሎት ከኤድስ በሽታ ድኛለሁ ብሎ ሁለት ፖዘቲቭና ኔጋቲቭ የሆነባቸውን የሐኪም ማስረጃ ያቀረበ ግለሰብ መጀመርያውኑም ኤድስ እንዳልያዘውና ፖዘቲቭነቱን የሚያሳየው መረጃ በዘገባው ላይ ቀረበ።
በማግስቱ የኬንያ ጋዜጠኞች ፓስተሩን ኢንተርቪው ለማድረግ ቢሯሯጡም አልተሳካላቸውም። በሁለተኛው ቀን ላይ አንዱ ዕድለኛ ጋዜጠኛ ፓስተሩ ምሳውን ከአንድ ሆቴል በልቶ ሲወጣ አገኘው።
«ፓስተር፤ በ JICHO PEVU ስለቀረበብህ ውንጀላ ምን ትላለህ?»
«ውንጀላ? ኧረ እኔ አልሰማሁም…»
«ከሕዝብ እፀልይላችኋለሁ እያልክ በሚልዮን የሚቆጠር ገንዘብ አካብታሃል ይባላል…»
«ስማኝ ወንድም!!» አለ መኪናው ጋር የደረሰው ፓስተር ለጋዜጠኛው መኪናውን እያሳየው። «እንዲህ ዓይነት መኪና በነፃ ይገኛል እንዴ ታድያ?»
ይሄው ምላሹም በቴሌቪዥን ተላለፈ።
በቀጣዩ እሁድ ፓስተር ኪኛሪ የሚሰብክበት አዳራሽ በብዛቱ ከባለፈው የበለጠ ሕዝብ ተገኘ። አሁንም ድረስ ፓስተሩ የስብከት አገልግሎት እየሰጠ ነው።
እኛም ሐገር ሚሌኒየም አዳራሽን ጢም ብሎ እንዲሞላ ያደረገ በግል ጄት የሚሄድ ፓስተር መጥቶ ሕዝቤን «የተቀደሰ ውኃ» ለመግዛት እርስ በርሱ ሲራገጥ ውሎ ነበር አሉ ባለፈው ሰሞን…
ለነገሩ የአባባ ታምራትን ሽንት ከፍሎ የጠጣ ሕብረተሰብ ለተቀደሰ ውሃ ቢከፍል ምኑ ይገርማል?
አሁን ሰሞን ደግሞ በ350 ብር ገነትን እና ሲዖልን በ preview ለማየት ሕዝቤ እየተጋፋ ነው አሉኝ…
በሕይወቴ ለመጀመሪያ ጊዜ ልጆች ባለመውለዴ ተደስቻለሁ!!
2 የተሰጡ አስተያየቶች

እንኳን ለአምላካችን፤ ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ የልደት በዓል ክብር አደረሳችሁ!

ኢሳይያስ 9፥6 «ሕፃን ተወልዶልናልና፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል»
 ታህሣሥ 29/2007 ዓ/ም
0 የተሰጡ አስተያየቶች
 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger