Saturday, April 20, 2024

ጸጋ ምንድነው? (What is grace?)

ጸጋ ምንድነው? (What is grace?) ክፍል ዐራት በባለፉት ክፍሎች የተመለከትነው በኢየሱስ አምነን ለዳንን ሰዎች ሁሉ የጸጋ ኃይል የሚያስፈልገን ለምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ሦስት የኃጢአት በሮችን ለመዝጋት ነው በሚለው ሃሳብ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ስንሰጥ መቆየታችን ይታወሳል። በዚሁ መሠረት ከሦስቱ የኃጢአት በሮች መካከል 1/ሥጋ 2/ ዓለም እንዴት ሊፈትኑን እንደሚችሉና ከሁለቱም የሚመጡ ፈተናዎች እንዴት መዋጋት እንደሚገባን ተመልክተናል። ሥጋ ማለት የተሸከምነውና የራሱ መሻት ያለው በነፍስ ሕያውነት የሚንቀሳቀስ አካላችን ሲሆን ይህም የሚኖረው በዚህች ምድር ላይ እንደመሆኑ መጠን ዓለም ሥጋን በባርነት እንዳትገዛ በሚዛን ለመኖር የሚያስችለን ጸጋ የሚባል ጉልበት እንደሚያስፈልገን አይተናል። ዛሬ ደግሞ ሦስተኛው ክፍል የሆነውንና የክፋት ሁሉ የኃጢአት ሹም ስለሆነው ስለወደቀው መልአክ እንመለከታለን። ይህ ፍጥረት በትዕቢት፣ በተንኮልና በክፋት የተካነ ነው። ረጅም እድሜና ብዙ ልምድ ያለው የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት ነው። የዚህ ዓለም ገዢ የተባለውም ዓለሙን ሁሉ በዐመፃና በኃጢአት ስለያዘው ነው። “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።”1ኛ ዮሐ 5፥19 ይህ ጥንተ ጠላታችን ወደጥልቁ ወርዶ ለዘለዓለም እስኪታሰር ድረስ ለሰው ልጆች ምንም ዓይነት ርኅራኄ የለውም። ራእይ 20:10 የወደቀው መልአክ እብሪትና ትዕቢትን ሞሪስ የተባለ የነገረ መጻሕፍት ተርጓሚ “ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።” ኢሳ 14፥14 ያለውን ቃል ሲተረጉም የወደቀው መልአክ ምኞቱ የመላእክት ሁሉ አለቃ መሆን ብቻ ሳይሆን አምላካዊ ሥፍራንም መፈለጉን ያሳያል ሲል ይፈታዋል። የትኛውም ምኞትና አደገኛ የአምልኮ መሻት ሁሉ ምንጩ የዚህ የወደቀው መልአክ ውጤት ነው። የናቡከደነጾር የዱራ ሜዳ ሐውልት (ዳን3:1) የምናሴ የማመለኪያ አፀድ (2ኛ መዋዕል 33)፣ ዳጎን (መሣ16:23)፣ ቤል (ኤር 50:2) ወዘተ ሁሉም የወደቀው መልአክ ሥራዎች ናቸው። ይህንንም መዝሙረኛው እንዲህ ይላል። “የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።” መዝ 96፥5 ይህ የወደቀው መልአክ ለራሱ ብቻውን ወድቆ አልቀረም፣ የመጀመሪያዎቹንም የሰው ልጆች ጣለ እንጂ። የሚገርመው ነገር ሰዎቹ ሳይጠይቁት ራሱ ሰላማዊ ጠያቂ ሆኖ ነው የቀረበው። ከጠያቂነቱ ባሻገር እንዳይበሉ የተከለከሉት ተክል ስለመኖሩ እያወቀ፣ እንደማያውቅ ፍጥረት ሆኖ ነበር የቀረባቸው። "...ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት።”ዘፍ 3፥1 ስለመከልከላቸው እውቀቱ ከሌለው ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ ባልጠየቀም ነበር። በሚመልሱት መልስ ለማጥመድ ነው። ይህንን በቃል የማጥመድ ተንኮል በኢየሱስ ላይም ሞክሮት ነበር። “በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።”ሉቃ 20፥26 ሔዋን እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ ለጠየቃት የማጥመጃ ቃል የሰጠችው መልስ እንዲህ የሚል ነበር። (ዘፍጥረት 3:2—3) ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፦ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። ሔዋን ሞትን ሞታ ስለማታውቅ ይሄ ጠላት በገዛ ቃሏ ምን እንደሚመስል ሊያሳያት ነው። (ዘፍጥረት 3፣3—4) እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ይህ ጠላት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ይልቅ የሱ ድምፅ የተሻለ ፍቺና ምስጢር እንዳለው እየተናገረ ሰዎቹን ወደቤተ ሙከራ እየወሰዳቸው እንዳለ እናያለን። በሚያምረውና በሚያስጎመጀው የጠላት ቤተ ሙከራ የገቡት እንግዶች አብሯቸው የነበረው ፍሬ የተለየ ውበት እንዳለው ያንጊዜ እንደአዲስ የተገለፀላቸው ይመስል ነበር። “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።” ዘፍ 3፥6 የወደቀው ጠላት አዲሶቹንም ፍጥረቶች ይዞ ወደምድር ተፈጠፈጠ። ይሄንን ሀተታ እዚህ ላይ ማንሳት ያስፈለገው ለመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን ያልተነበበ ታሪክ ለመንገር ሳይሆን ይሄ ረጅም እድሜ፣ ልምድና ሁሉንም ክፋት የያዘ ፍጡር ዛሬም እየሰራ ያለ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። ዛሬም ያማልላል፣ ያስጎመጃል፣ ያስመኛል፣ ያስፈፅማል፣ ያጋድላል፣ ያፋጃል፣ ሁሉንም ክፋት በሰው ልጆች መሀል ያስፈፅማል። ስለዚህ ይሄንን ባለብዙ ልምድ ጠላት ለመዋጋት "ጸጋ" የተባለ መመከቻ የእምነት ጋሻ የግድ ልንታጠቅ ይገባል። ያለበለዚያ የመጫወቻው ሜዳ ከመሆን ልታመልጥ አትችልም። ይህ ጸጋ እንዴት እንደሚሰራ የጳውሎስ ተማሪ የነበረው ቲቶ በመልእክቱ እንዲህ እያለ ይነግረናል። “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” ቲቶ 2፥12-13 ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የዳኑ ሰዎች የክርስቶስን መገለጥ እየጠበቁ፣ ራሳቸውን እየገዙ፣ በጽድቅና በቅድስና እየኖሩ ዘመኑን የሚሻገሩበት ሰማያዊ መሣሪያ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፋቸው መልእክታት በሙሉ የመዝጊያ ቃል አድርጎ ከሚጠቅሳቸው የጸሎት መደምዲያው ክፍል "ጸጋ" ከእናንተ ጋር ይሁን እያለ ይለምን የነበረው አለምክንያት አልነበረም። ሦስቱን የኃጢአት በሮች መዝጋት የሚቻለው ከእግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ ብቻ ነው። ይህ ጸጋ እንዴት እንደሚገለጥና እንደሚሰራ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር በቀጣይ ፅሑፋችን ለማየት እንሞክራለን።