Saturday, December 28, 2013

የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የደብር ሃላፊዎችና ሠራተኞች አዲሱን መዋቅር ተቃወሙ


(ደጀብርሃን) ሁሉን ዐቀፍ ጥናት ያልተደረገበትና በአናቱ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ላይ የለውጥ ሽፋን ሽብልቅ ሆኖ የገባው ማኅበረ ቅዱሳን ካህናቱንና የቤተ ክርስቲያኑን ላዕላይ አመራር ለሁለት እየሰነጠቀ ይገኛል። አባ ሉቃስን፤ አባ እስጢፋኖስንና ሌሎች የማኅበረ ቅዱሳን አገልጋይ ጳጳሳትን የያዘው ማኅበሩ ከጀርባ ሆኖ በቢሮው አርቅቆ ያመጣውንና በቤተ ክህነት መዋቅር ውስጥ የማንነት አሻራውን ለመትከል ታች ላይ እያለ የሚገኝ ሲሆን ቅዱስ ፓትርያርኩ ጉዳዩ እንዲጠናና ሁሉንም አሳታፊ እንዲሆን የነበራቸውን አቋም በማስለወጥ በጓሮ ያቀረበውን «የያብባል ገና» ፕሮጄክት በመደገፍ ላይ እንደሆኑ ውስጥ አዋቂ ምንጮቻችን መረጃውን አድርሰውናል። ሰሞኑን በፓትርያርኩ ቢሮ የከተመው ማኅበሩና አቀንቃኝ ጳጳሳቱ ለውጡን የሚቃወሙት ወገኖች በጣት እንደማይቆጠሩና ለዚያው ሌቦችና ዘራፊዎች ናቸው በማለት በማጠየም ላይ ተጠምዶ ሰንብቷል። ፓትርያርኩ ከዚህ በፊት የነበራቸው ሃሳብ ሁሉን አሳታፊ፤ አጠቃላይ የለውጥ እቅድ እንዲሆንና የቤተ ክርስቲያኒቱ አመራር የሚያወጣውና የሁሉንም ካህናት ሃሳብ ያካተተ ሊሆን እንደሚገባው የነበራቸውን አቋም ትተው ማኅበሩ እየተሯሯጠለት የሚገኘውን እቅድ እንዲደግፉ ሲወተውት ሰንብቶ ፓትርያርኩን የቀደመ ሃሳባቸውን አስጥሎ የራሱን እቅድ እንዳስጨበጠ መረጃችን አክሎ ገልጿል። ጉዳዩ እስከየት ይሄዳል? የሚለውን ወደፊት የምናየው ሆኖ አሁን ባለው ሁኔታ አለቆችን ለብቻ የነጠለ በሚመስል ስልት እየታከከ፤ የካህናቱን የስራ ዋስትና በመንጠቅ የራሱን አዲስ መዋቅር እየተከለ የሚገኘውን እንቅስቃሴ ማኅበረ ካህናቱ በዝምታ የሚያልፈው ከሆነ አሉታዊ ውጤቱ ለቤተ ክርስቲያኒቱም፤ ለሀገርም የሚተርፍ ይሆናል።
ይህንን በመቃወም የአዲስ አበባ ሀ/ስብከት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች እያቀረቡ ያለውን አቤቱታ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዛሬ እንዲህ ዘግቦታል።
ዲግሪ ያላቸው በየአስተዳደሩ እንዲገቡ መደረጉ አግባብ አይደለምበኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአዲስ አበባ ሃገረ ስብከት፣ ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ እያካሄደ ያለውን አዲስ የመተዳደሪያ ደንብ የማፅደቅ ሂደት እና መዋቅራዊ ለውጥ አጥብቀው እንደሚቃወሙ የሃገረ ስብከቱ የአድባራትና ገዳማት አስተዳዳሪዎችና ሠራተኞች ለቅዱስ ፓትሪያርኩና ለጠቅላይ ሚኒስትር /ቤት አስታወቁ፡፡ ቅሬታ አቅራቢዎቹ ለፅ/ቤቶቹ ባስገቡት ደብዳቤ፤ የሃገረ ስብከቱ አዲስ መተዳደሪያ ደንብ ሁሉም የቤተክርስቲያኒቱ ሊቃውንት ሳይሳተፉበት በጥቂት አመራሮች ብቻ የተቀረፀና በውይይት ያልዳበረ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ መተዳደሪያ ደንቡ ከነባሩ ህገ ቤተ ክርስቲያንና ከቃለ-አዋዲ ደንብ ጋር የሚጋጭና የሚጣረስ ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ደንቡ፤ ነባሩን የቤተክርስቲያኒቱን ሠራተኛ በማፈናቀል በምትኩ ስለቤተ ክርስቲያን ትምህርት ምንም እውቀት የሌላቸውን ግለሠቦች በስመ ድግሪና ዲፕሎማ በመሠግሠግ የቤተክርስቲያኗን ሙሉ አስተዳደራዊ መዋቅር ለመቆጣጠር ያለመ ነውሲሉ ተቃውመዋል፡፡

አዲሱን መዋቅር ያዘጋጁት አካላት ማንነታቸው በግልፅ እንደማይታወቅ በደብዳቤያቸው የጠቀሡት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ የቤተክርስቲያኗ የመጨረሻ ስልጣን ያለውን ቅዱስ ፓትርያርክ ስልጣንን በመገደብ፣ ቤተክርስቲያኗ የእነዚህ አካላት ሠለባ እንዳትሆን ስጋት አለን ብለዋል፡፡ የቤተክርስቲያኒቱን ቃለ አዋዲ ያልጠበቀ ነው ያሉትን አዲሱን መተዳደሪያ ደንብ እንደማይቀበሉትም አስተዳዳሪዎቹ ገልፀዋል፡፡ ለቅሬታው መነሻ የሆነው ደንብ፣ ህግ በማርቀቅና በማዘጋጀት ከፍተኛ ልምድና እውቀት ባላቸው ገለልተኛ ምሁራንና የቤተክርስቲያኗ ሊቀ ሊቃውንት እንዲሰናዳ የጠየቁት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ህጉን አርቅቋል የተባለውን ማንነቱ ማህበር ፓትሪያርኩ እንዲያጣሩ ተጠይቀዋል፡፡አዲሱ ደንብ የካህናት ቅነሣ መርሃ ግብርም እንዳካተተ በግልፅ ተረድተናልያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ድርጊቱ መንግስት ስራ አጥን ለመቀነስ የሚያደርገውን ጥረት የሚፃረር ነውሲሉ ያጣላሉት ሲሆን ብዙ ሊቃውንትን ከስራ በማፈናቀል ለችግር እና ለእንግልት የሚዳረግ በመሆኑ ህጉ መፅደቅ እንደሌለበት አሳስበዋል፡፡ በጉዳዩ ዙሪያ ማብራሪያ የጠየቅናቸው የፓትርያርኩ ልዩ /ቤት ሃላፊ አቶ ታምሩ አበራ የቅሬታ አቅራቢዎቹ ደብዳቤ ወደ /ቤት ሳይገባ በቀጥታ ለፓትርያሪኩ የደረሰ በመሆኑ በጉዳዩ ላይ ምላሽም ሆነ አስተያየት ለመስጠት እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡ ቅሬታ አለን የሚሉ ወገኖች በተናጥል ከሚቀርቡ፣ ለቤተክርስቲያኗ ይጠቅማል የሚሉትን ኮሚቴ መርጠው ሃሣባቸውን በማደራጀት ቢያቀርቡ እንደሚሻል የጠቆሙት ሃላፊው፤ የእነሡ ሃሣብ ተቀባይነት ባያገኝም እንኳ በውይይት ለመተማመን ዝግጁ መሆን እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡