Saturday, December 7, 2013

መነኩሴው በግብረሰዶም ወንጀል በእስራት ተቀጡ



በአሸናፊ ደምሴ /ሰንደቅ ጋዜጣ፤ ህዳር 25 እትም/

ዐቃቤ ሕግ ለአካለ መጠን ባልደረሰ ታዳጊ ላይ የግብረ ሰዶም ጥቃት ፈፅመዋል ሲል ክስ የመሰረተባቸው የ33 ዓመቱ ተከሳሽ አባ ገብረፃዲቅ ወልደሩፋኤል በቀረበባቸው ማስረጃ ጥፋተኛ ሆነው በመገኘታቸው የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 7ኛ ወንጀል ችሎት ህዳር 19 ቀን 2006 ዓ.ም ውሎ በ4 ዓመት ፅኑ እስራት የቅጣት ውሳኔ ሰጠ።
የፌዴራሉ ዐቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያስረዳው፤ ተከሳሽ ከእርሱ ጋር ተመሳሳይ ፆታ ካለውና ዕድሜው ለአካለ መጠን ባልደረሰው ልጅ ላይ የግብረ ሰዶም ጥቃት ለመፈፀም አስበው ነሐሴ 22 ቀን 2005 ዓ.ም በግምት ከቀኑ 8፡00 ሲሆን፤ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቀበሌ 13/15 አካባቢ ልዩ ቦታው ዳንኤል ሆቴል ውስጥ ዕድሜው 15 ዓመት ከሆነው የግል ተበዳይ ጋር ግንኙነት ለማድረግ በመስማማት በሆቴሉ ሽንት ቤት ውስጥ ተከሳሽ አባ ገብረፃዲቅ ወልደሩፋኤል የግል ተበዳይን ካስገቡት በኋላ የግብረ ሰዶም ግንኙነት ሊፈፅሙ ሲል ሌሎች ግለሰቦች እየተከታተሏቸው መሆኑን ሲያውቁ ሱሪያቸውን አጥልቀው መሸሻቸውን ድርጊቱም በጅምር የተቋረጠ መሆኑን ያትታል። በመሆኑም ዐቃቤ ሕግ ተከሳሹ ለፈፀመው ለአካለ መጠን ባልደረሰ ልጅ ላይ የሚፈፀም የግብረ ሰዶም ጥቃት ለሥነ-ምግባር ተቃራኒ በሆነ ሌላ ድርጊት ሙከራ ወንጀል ክስ መስርቶባቸዋል።  
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍ/ቤት 7ኛ ወንጀል ችሎትም የጉዳዩን ግራና ቀኝ ሲመረምር ከቆየ በኋላ ተከሳሹ የዐቃቤ ሕግን ማስረጃዎች በሚገባ ማስተባበል ባለመቻሉ ጥፋተኛ ነው ሲል ብይን ሰጥቷል። ይህም በመሆኑ ባሳለፍነው ሐሙስ ህዳር 19 ቀን 2006 ዓ.ም በዋው ችሎት ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆነው በተገኙበት ወንጀል በአራት አመት ፅኑ እስራትና ለአራት አመታት በሚዘልቅ የመምረጥ መመረጥ እና ከማንኛውም ህዝባዊ መብቱ እንደታገድ ቅጣት ተጥሎበታል።