Friday, December 27, 2013

በመለኮቱ ቀናተኛ በሆነው በአምላካችን ስፍራ ያልተገለጸውን የመልአክ ስም በመጥቀስ ክብሩን ለሌላ አሳልፎ መስጠት ስህተት ነው!



ስለቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነትና አዳኝነት በዋናነት የሚቀርበው ጥቅስ እንዲሁም አንዳንዶች እንደመከላከያ ምሽግ የሚጠቀሙበት ቃል በመዝሙረ ዳዊት ላይ የተቀመጠው ይህ ቃል ነው።
“የእግዚአብሔር መልአክ በሚፈሩት ሰዎች ዙሪያ ይሰፍራል፥ ያድናቸውማል።” መዝ. 33፡7 ይህ ጥቅስ የእግዚአብሔር ቅዱሳን መላእክት እግዚአብሔርን ለሚፈሩትና ለሚታዘዙ ሰዎች ተልከው እንደሚያግዙና እንደሚራዱ ያስረዳል። ምክንያቱም ቅዱሳን መላእክት ከስራቸው አንዱ ሰዎች ወደጽድቅና ቅድስና የመዳን መንገድ እንዲደርሱ በአምላካቸው ፈቃድ መፈጸም ነው።
 “ሁሉ መዳንን ይወርሱ ዘንድ ስላላቸው ለማገዝ የሚላኩ የሚያገለግሉም መናፍስት አይደሉምን?” ዕብ. 1፡14

  ቅዱሳን መላእክት ለምስጋናና ለተልእኮ የተፋጠኑ በመሆናቸው የጌታቸውን ትእዛዝ ተቀብለው እንደሚራዱና እንደሚያግዙ ቃሉ ስለሚናገር በዘመናት ውስጥ መላእክት በስምም ተገልጸው ይሁን በስም ሳይገለጹ ሰዎችን ሲያገለግሉ ኖረዋል። ከዚህ አንጻር በትንቢተ ዳንኤል ላይ የተጠቀሱትን ሶስቱን ወጣቶች እግዚአብሔር መልአኩ ገብርኤልን ልኮ አናንያ አዛርያ ሚሳኤልን ከእሳቱ ሊያድን እንደሚችል ብናምን ስህተት የለውም። ነገር ግን ሊያድን ይችላል ማለትና ስሙ ያልተገለጸውን ስም ሰጥቶ ሰለስቱ ደቂቅን ገብርኤል አድኗል ማለት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ምክንያቱም ችግሩ የሚነሳው በነብዩ ዳንኤል የትንቢት መጽሐፍ ውስጥ  እንደምናነበው ወጣቶቹ ለጣኦት አንሰግድም በማለታቸው ከተጣሉበት እሳት ውስጥ ያዳናቸው ገብርኤል ነው የሚል ቃል በጭራሽ አለመኖሩ ነው። ከዚያም አልፎ ተርፎ የእሳቱ ወላፈን ቁመት 49 ክንድ እንደሆነም የሚሰበከው ተያያዥ ጉዳይ አለመጠቀሱም በተጨባጭ የሚረጋገጥ እውነት ስለሆነ ነው። 
ስለቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት ያለው የመጽሐፍ ቃል መንገድ እንዲስት ማድረጉ ሳያንስ ሰዎች ይህ ያልተፃፈውን ቃል እውነት አድርገን እንድንቀበል አጋዥና ደጋፊ ይሆኑናል የሚሉትን ለማግኘት በምክንያት ቁፋሮ በመድከም የተጻፈው ቃል ብቻውን ምሉዕ ነው በማለት አርፈው ባለመቀመጥ  ከቃሉ ጋር ያላቸው ግጭት እስከመጨረሻው መሆኑ ያሳዝናል።
  መጽሐፍ ቅዱስ ስለወላፈኑ ቁመት ያለው አንዳች ነገር አለመኖሩና ድርሳነ ገብርኤልም ሆነ ድርሳነ ሚካኤል የተባሉት መጻሕፍት የእሳቱ ቁመት 49 ክንድ ይረዝማል፤ ያዳንኳቸውም እኔ ገብርኤል ነኝ፤ እኔ ሚካኤል ነኝ በማለት እንዲናገሩ የተደረጉት እነዚህ መጻሕፍት ከየት የመጡ ናቸው ?ብለን ብንጠይቃቸው ተገቢ ይመስለናል። ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱሳችንን ስናገላብጥ መላእክቱ እኛ ነን ሲሉ ወይም እግዚአብሔር ለዳንኤል እነሱ ናቸው እያለ ሲናገር አናገኝምና ነው። 

 በዚህ ዘመን በየድርሳናቱ እንደምናነበው የእሳቱ ቁመት 49 ክንድ የሚለውና የተራዳው የመልአክ ስም ገብርኤል (በድርሳነ ገብርኤል)፤ ሚካኤል (በድርሳነ ሚካኤል) በማለት የጻፉት ዳንኤል ረስቶት ነው? ወይስ እግዚአብሔር ለዳንኤል ያልገለጸውን ቃል እነርሱ ጉድለት ስላገኙበት ለማሟላት ልዩ ፈቃድ ተቀብለው ይሆን ? 


    በሌላ መልኩ ከእግዚአብሔር ቃል ጋር ለመጣላት ቃል የገባ የሚመስለው ማኅበረ ቅዱሳን ደግሞ በድርሳነ ገብርኤል እንደተጻፈው ያዳነው ገብርኤል መልአክ ነው ቢልና ድርሳነ ሚካኤል ደግሞ ቅዱስ ሚካኤል ነው ቢል ችግር የለውም፤ ምክንያቱም ገብርኤል ባለበት ሚካኤል አለ፤ ሚካኤል ባለበትም ገብርኤል አለ በማለት የሁለቱን ድርሳናት ግጭት ለማስታረቅ በመሞከር መላእክቶቹ በጋራ ሆነው  የትም ስፍራ ለተልእኮ እንደሚሄዱ በመግለጽ የሌለ ታሪክ እያመጣ ሌላ ችግር ውስጥ ሲገባ መስተዋሉ ነገሩን አስገራሚ ያደርገዋል። 

ምክንያቱም እንደማኅበረ ቅዱሳን አባባል ይሁን ቢባል እንኳን ሰለስቱ ደቂቅ በተጣሉበት እሳት ውስጥ አምስት ሰዎች ሲመላለሱ በታዩ ነበር። ነገር ግን ሶስቱ ወጣቶችና ሌላ አንድ የሰውን ልጅ የሚመስል በድምሩ አራት ሰዎች እሳቱ ውስጥ እንደሚመላለሱ በአደባባይ ከመታየታቸው በስተቀር አምስት ሰዎች እሳቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ እናያለን የሚል ቃል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አናገኝም።  ምናልባት አንዱ መልአክ ገብርኤልም፤ አልፎ አልፎም ሚካኤል እየሆነ ራሱን ይለዋውጣል ካልተባለ በስተቀር በሁለቱ ድርሳናት ላይ ያለው የእኔነት ጥያቄ በማኅበረ ቅዱሳን አሸማጋይነት ፈጽሞ የሚታረቁበት ሁኔታ ከቶ ሊኖር አይችልም። 
ያልታዩ አምስት ሰዎችን እሳቱ ውስጥ እንዳሉ በመቁጠር፤ ስማቸው ያልተገለጸ መላእክቶችንና ሁለቱን ድርሳናት በማኅበረ ቅዱሳን ሽምግልና ከእግዚአብሔር ቃል አንጻር መቼም ላይስማሙ የተጻፉ ናቸው። ምክንያቱም እግዚአብሔር ካልተናገረ በቃ አልተናገረም ነው እንጂ የሰው ቃል የጭማሪ ማሻሻያ አያስፈልገውም። ከተናገረ ደግሞ የተናገረው እውነት: መቼም ቢሆን ለዘለዓለም እውነት ሆኖ ይኖራል።
  መላእክት የእግዚአብሔርን ቃል ፈጻሚዎች ስለሆኑ ይራዱናል፤ ያግዙናል ማለት አንድ ነገር ነው። ይህንን የሚያስረዳ የእግዚአብሔር ቃል ማረጋገጫ ስላለን እንቀበላለን። ይሁን እንጂ ጉድለትና ስህተት በሌለበት በእግዚአብሔር ቃል ላይ ስሜቶቻችን እያስገባን በመተርጎም እግዚአብሔር ያደረገውን ድንቅ ስራ እጹብ እያልን እንዳናመሰግነው ዓይናችንን ወዳልተገለጹ መላእክት እንድንወረውር ማድረግ ደግሞ ሌላ ነገር ስለሆነ በዚህ አንስማማም። ሰውን ወደስህተት መምራት በደል እንደሆነ እንናገራለን። እግዚአብሔር ማን መሆኑን ሳይገልጽ የተወው የስራው ባለቤት እሱን እንድናመሰግነውና ስለድንቅ ስራው እንድናደንቀው እንጂ ማንነቱ ያልተገለጸውን፤ በትርጉም ሽፋን ስም ሰጥተን እኛ በጎደለው እንድንሞላው አይደለም። ክብሩን ላልተገለጸ መልአክ መስጠት ኃጢአት ስለሆነ ስለስቱ ደቂቅን ያዳናቸው እግዚአብሔር ነው በማለት ምስጋናውን ከእቶኑ ያድነናል ብለው እንደመሰከሩት ሶስቱ ወጣቶች ለእግዚአብሔር መልሰን ስላልተገለጸው መልአክ በተናገርነው ደግሞ  ንስሐ ልንገባ ይገባል። ገብርኤልን ጠቅሶ ልኮ ያዳነ ቢሆንም እንኳን አዳነ ተብሎ የሚመሰገነው እግዚአብሔር ነው እንጂ መልአኩ አይደለም፡፡  መልአኩም እኔን አመስግኑኝ አይልም። እንደዚህ አይነት ምስጋና መቀበል የሚፈልገው የወደቀው መልአክ እንጂ ከቅዱሳን መላእክቱ አንዱም አድርጉልኝ ሲሉ አናገኝም።
  ለዮሐንስ በራእዩ የተናገረው እንዲህ ሲል ቅዱሱን መልአክ እናገኛለን። «ልሰግድለትም በእግሩ ፊት ተደፋሁ። እርሱም፦ እንዳታደርገው ተጠንቀቅ፤ ከአንተ ጋር የኢየሱስም ምስክር ካላቸው ከወንድሞችህ ጋር አብሬ ባሪያ ነኝ፤ ለእግዚአብሔር ስገድ፤ የኢየሱስ ምስክር የትንቢት መንፈስ ነውና አለኝ» (ራእይ 19፤10)
 እኛ ገብርኤል ወይም ሚካኤል የሚል የተጻፈ የለም ስንል መጽሐፍ ቅዱስ የነገረን ይበቃናል፤ የሌለ ታሪክ በቃሉ ላይ አንጨምር በማለት እንጂ ቅዱሳን መላእክቱ ከአምላካቸው በሚወጣ ትእዛዝ አይራዱም ወይም አያግዙም ከማለት አንጻር እንዳልሆነ መታወቅ አለበት። ምስጋና ሁሉ፤ ሁሉን ማድረግ ለሚችል ለእግዚአብሔር ብቻ ይሁን እንላለን። ይሁን እንጂ «እናንተን የተቀበለ እኔን ይቀበላል» ማቴ 10፤40 በሚለው ቃል ስር ተጠልለው ለመላእክቱ የምናቀርበው ምስጋና ጌታችንን ማመስገናችን ነው በማለት መከራከር የሚሹ ወገኖች ቢኖሩም ምስጋና ውዳሴውን ለእነሱ አድርጉ: እኔ በተዘዋዋሪ እቀበላለሁ የሚል ቃል የለም። የተላኩትን የምንቀበለው የላካቸውን ስናውቅ ነው።


ከቤተ መንግስት ወደ አንድ ሰው የተላከ ስጦታን የሚቀበል ሰው፤ የተላከውን ሰው ማንነት አረጋግጦና በአክብሮት አስተናግዶ ለተደረገለት ስጦታ ግን ምስጋናና ውዳሴውን ለስጦታው ባለቤት ለቤተ መንግስቱ ክፍል ቢችል በጽሁፍ፤ ካልቻለም በቃል ያቀርባል እንጂ መልእክተኛውን ሰው ስለሰጠኸኝ ስለዚህ ስጦታ አመሰግንሃለሁ፤ ያደረክልኝን ውለታ መቼም አልረሳውም በማለት ለቤተ መንግስቱ ሊቀርብ የሚገባውን ምስጋና መንገድ ላይ በማስቀረት ለመልእክተኛው አያደርግም። ለመልእክተኛው ማድረጌ ለቤተ መንግስት እንዳደረኩ ይቆጠራል ቢል የስጦታውን ባለቤት ስጦታ መዘንጋት ይሆናል።

 ስለሆነም ለቅዱሳን መላእክት የምናከብራቸው አምላካቸውን ስለሚያውቁ፤ ለቃሉም ስለሚታዘዙ፤ ምስጋናና ውዳሴን ዘወትር ስለሚያቀርቡ፤ መልእክት ከዙፋኑ ሲደርሳቸው ለምህረት ይሁን ለመዐት ስለሚወጡ እንጂ እነሱ በተዐዝዞ ለሚያደርጉት ሁሉ ምስጋናና ውዳሴ የተገባቸው ተቀባዮች ስለሆኑ አይደለም።
«አሁንም እኔ ብቻዬን እኔ እንደ ሆንሁ፥ ከእኔም በቀር አምላክ እንደሌለ እዩ፤ እኔ እገድላለሁ፥ አድንማለሁ፤ እኔ እመታለሁ፥ እፈውስማለሁ፤ ከእጄም የሚያድን የለም» ዘዳ 32፤39  ይህንን ቃል አምናለሁ እያሉ መላእክቱን በስልጣናቸው አዳኝ አድርጎ ማስቀመጥ ብቻውን ገዢ ለሆነና ምስጋና የባህርይ ገንዘቡ በሆነው አምላክ ላይ የአምልኮ ምንዝርና መፈፀም ነው። አመንዝራ ቃል ኪዳን ከፈፀመላት ባለቤቱ ውጪ የሚደረግ ስርአተ አልበኝነት እንደሆነው ሁሉ፤ ምስጋናና ውዳሴ ከእግዚአብሔር ውጪ ለማንም እንዳናጋራ በእምነታችን ለአምላክ ቃል ኪዳን መግባታችንን በመዘንጋት እየቆረሱ ለሁሉም በማደል የምንፈጽመው የአምልኮ ስህተት ሁሉ ነው።


ሌላው አሳዛኝ ነገር እግዚአብሔር ከእልፍ አእላፋቱ መላእክቶቹ መካከል የትኛውን መልአክ፤ ለምን አገልግሎት እንደሚልክ ሳናውቅ በእኛ ጥሪ የሚመጣ ይመስል « እንደአናንያ፤ እንደአዛሪያ፤ እንደሚሳኤል፤ አድነን ገብርኤል» በማለት ከበሮ በመደለቅ ገብርኤል ራሱ እንዲመጣ መጥራታችን ነው። መላእክቱ ወደታዘዙበት ስፍራ ከምስጋና ከተማቸው የሚነሱት ከቅዱሱ መንበር ትእዛዝ ሲወጣ ብቻ ነው እንጂ ሰዎች ተሰብስበው በስም ስለጠሯቸው አይደለም።
«ቆርኔሌዎስም እንዲህ አለው፦ በዚች ሰዓት የዛሬ አራት ቀን የዘጠኝ ሰዓት ጸሎት በቤቴ እጸልይ ነበር፤ እነሆም፥ የሚያንጸባርቅ ልብስ የለበሰ ሰው በፊቴ ቆመና።ቆርኔሌዎስ ሆይ፥ በእግዚአብሔር ፊት ጸሎትህ ተሰማ ምጽዋትህም ታሰበ» (የሐዋ 10፤30-31) ላይ የተጻፈው ቃል የሚያስተምረን ሰዎች ፈቃደ እግዚአብሔርን በመፈጸም ስንጸና እኛ የማናውቀው ወይም በስም ያልተገለጸ መልአክ መልእክት ይዞልን በመምጣት ሊያግዘን እንደሚችል እንጂ ሚካኤል ና! ና! ወይም ገብርኤል ቶሎ ድረስ! ስላልን አይደለም። ምክንያቱም የእኛ የጥሪ ምኞትና የአምላክ ሃሳብ አንድ አይደለምና።

« ሰማይ ከምድር ከፍ እንደሚል፥ እንዲሁ መንገዴ ከመንገዳችሁ አሳቤም ከአሳባችሁ ከፍ ያለ ነው» ኢሳ 55፤9 የሚልም ቃል ተጽፎልናል።
 ስለዚህ እኛ አምላካችንን በጸሎትና በምስጋና ዘወትር ከፍ ከፍ  ከማድረግ ውጪ ይህኛው ፈጣን ነው፤ ያንኛው አዳኝ ነው እያልን በመጥራታችን መላእክቱ አያ እገሌ ስማችንን ጠርቷል፤ የእገሌ ደብር ፍሪዳ በስሜ አርዷልና ልሂድ፤ ልውረድ አይሉም።   ከመሰለንም ተሳስተናል።  ዘማሪው በመዝሙሩ  «መላእክቱ ሁሉ፥ አመስግኑት ሠራዊቱ ሁሉ፥ አመስግኑት» እንዳለው፤
«አየሁም፥ በዙፋኑም በእንስሶቹም በሽማግሌዎቹም ዙሪያ የብዙ መላእክትን ድምፅ ሰማሁ፤ ቍጥራቸውም አእላፋት ጊዜ አእላፋትና ሺህ ጊዜ ሺህ ነበር፥በታላቅም ድምፅ። የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ። በሰማይና በምድርም ከምድርም በታች በባሕርም ላይ ያለ ፍጥረት ሁሉ በእነርሱም ውስጥ ያለ ሁሉ። በረከትና ክብር ምስጋናም ኃይልም ከዘላለም እስከ ዘላለም በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠው፥ ለበጉም ይሁን ሲሉ ሰማሁ» ራእይ 5፤11-13

ዘወትር ያመሰግኑታል።
ዝም ብሎ ሲጠራም ይሁን ሳይጠራ የትም የሚዞረውና ዓለምን በማሰስ ጊዜውን የሚፈጀው ሰይጣን ብቻ ነው። «እግዚአብሔርም ሰይጣንን፦ ከወዴት መጣህ? አለው። ሰይጣንም። ምድርን ሁሉ ዞርሁአት፥ በእርስዋም ተመላለስሁ ብሎ ለእግዚአብሔር መለሰ» ኢዮብ 1፤7
ስለዚህ እግዚአብሔር እንዴት እንደሚሰራ፤ በማን በኩል እንደሚሰራ፤ መቼ እንደሚሰራ ስለማናውቅ የመላእክቶችን ስም መጥራት አቁመን የእሱን ስም ብቻ ዘወትር በመጥራት እንጽና። በየትኛው መልአክና እንዴት እንደሚረዳን የሚያውቀው እሱ ብቻ ስለሆነ በተስፋ እንጠብቀው። የሚራዱንን መልእክተኞቹን እናከብራቸዋለን፤ እንወዳቸዋለን፤ በማንኛውም ስራ ግን ምስጋናና ውዳሴውን ለእሱ ብቻ እንሰጣለን።
በመለኮታዊ ሥልጣኑ ቀናተኛ ነውና። «ለሚወድዱኝ፥ ትእዛዜንም ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዚአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝና» ዘጸ20፤6 ያለን እግዚአብሔር ራሱ ነው።