«እኛ ኢትዮጵያውያን ያለነው የት ነው? ተስፋችንስ ምንድነው?»

የሰው ልጅ ሁሉ የአዳምና የሔዋን ዘር ነው። ከዚህ የወጣ የለም።  ሰው ክቡርና በእግዚአብሔር አምሣል የተፈጠረ ስለሆነ እንስሳ አይደለም። ሰው በተፈጥሮው እንስሳ ነው የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም እንኳን ሰው ግን እንስሳ አይደለም። በእርግጥ በተፈጥሮው ሰው ቢሆንም በአስተሳሰቡ ከእንስሳ ያልተሻለ ሰው ይኖራል። እንደባለጤና አእምሮ ሰው፤ ሰውኛ ማንነቱን ገላጭ አስተሳሰብ ሊኖረው የግድ ነው። እንስሳ አስተሳሰብ ማለት በሰው አምሣል ተፈጥሮ እንስሶች የሚሰሩትን የሚሠራ ወይም እንደእንስሳ የሚያስብ ማለት ነው። ዳዊትም በመዝሙሩ ይህን ኃይለ ቃል ሲገልጸው እንዲህ አለ። «ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ»               (መዝ ፵፱፤፲፪)

አዎ ሰው ክቡርነቱን ትቶ በሃሳቡና በግብሩ፤ ነፍስያቸው ምናምንቴ እንደሆኑት እንስሶች መሰለ። ሁሉም ሰው የአንድ ዘር ምንጭ ቢሆንም ቅሉ ለሰይጣን ፈቃድ አድሮ በልዩነትና በክፍፍል መኖርን መርጧል። በክፍፍሉም እርስ በእርሱ ይባላል። ምክንያቱም አእምሮው ወደእንስሳነት አስተሳሰብ በወረደ ማንነት ተመርዟልና ነው። እንስሳት እርስ በእርሳቸው ይጠላላሉ። ነገን የሚጠብቁት አድነው ስለሚበሉት እንስሳ እንጂ በተስፋ ስለሚገነቡት ሕይወት አይደክሙም። ከዚያ ባለፈ እንስሳት ተስፋ የሚያደርጉት ዘላለማዊ ነገር ምንም የላቸውም። የማይሞት ተስፋ የተሰጠው የሰው ልጅ ግን በሚሞት ምድራዊ ተስፋ ላይ ራሱን አጣብቆ ይኖራል።ዳዊትም በመዝሙሩ ላይ ቃሉን በማስረገጥ  ድኩማነ አእምሮው ሰዎችን በእንስሳ ይመስላቸዋል። «አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ» (መዝ ፵፱፤፳)

ጠቢቡስ «ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም» ማለቱ ምን ማለቱ ነበር?  አዎ! ያን ማለቱ በአንጻራዊ ትርጉም አዲስ ነገር ያለው ከፀሐይ በላይ ነው ማለቱ ነበር። ከፀሐይ በላይ አዲስ ነገር እንዳለ እየተናገረን እንደሆነ እንረዳለን።  ስለዚህም ነው ተስፋችን በማይጠፋና ዘላለማዊ በሆነው ከፀሐይ በላይ ባለው ነገር ላይ እንዲሆን አበክሮ በመናገር ከፀሐይ በታች አዲስ ነገር የለም የሚለን። እንዲያውም ከፀሐይ በታች ባለው ነገር ላይ ተስፋ ማድረግ ነፋስን እንደመከተል ነው ይላል። «ከፀሐይ በታች የተሠራውን ሥራ ሁሉ አየሁ እነሆም፥ ሁሉ ከንቱ ነው፥ ነፋስንም እንደ መከተል ነው» (መክ ፩፤፲፬) ነፋስን ማን ሊከተል ይችላል? ነፋስስ መሄጃው ወደየት ነው? መኖሩን እናውቃለን እንጂ ወደየት እንደሚሄድ አንረዳም፤ መቆሚያውም የት እንደሆነ አናውቅም፤ ልንከተለውም ማሰብ ከንቱ ድካም ነው። ከፀሐይ በታች ያለውን ነገር ሁሉ መከተል እንደዚሁ ይለናል። የቀደመው  ነገር አልፏል፤ ያኔ ግን እንደአዲስ ይቆጠር ነበር። ዛሬ ደግሞ ነገ ቀድሞ ይሆናል። ቀድሞም ሆነ ዛሬ የምንላቸው ነገሮች ደግሞ ነገ የሉም። ሁለቱን የሚከተል ተስፋ የለውም።  ቀድሞና፤ ዛሬ የሚባልለት ሁኔታ በሌለው ከፀሐይ በላይ ባለው አዲስ ነገር ላይ ተስፋ ማድረግ ይሻላል። ሐዋርያው እንዲህ ሲል ያስተምረናል። «እርሱም የሰጠን ተስፋ ይህ የዘላለም ሕይወት ነው» (፩ኛ ዮሐ ፪፤፳፭)

የማይጠፋውን የዘላለም አዲስ ተስፋ በእምነቱ የሚጠባበቅ እንደምናምንቴ ሰው ተስፋ በሌለው በዚህ ዓለም ከንቱ ነገር ላይ ራሱን አያጣብቅም። ሰማያዊ ተስፋ የሌላቸው ሰዎች በዚህ ምድር ላይ መኖራቸውን እንደመጨረሻ ምዕራፍ ቢቆጥሩት አያስገርምም። መዝሙረኛው እንደተናገረው በአሳባቸው የሚጠፉ እንስሳትን መስለዋልና።

በእምነት ተስፋ ውስጥ ያሉ ሰዎች ከፀሐይ በላይ ያለውን አዲስ ነገር ይጠባበቃሉ። ስለሆነም በዚህ ምድር ላይ እስካሉ ሁላቸውም በእምነት አንድ ናቸው። ልዩነትን አይሰብኩም። ጳውሎስም እንዲህ አለ። «በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤ ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና።አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም፥ ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም፥ ወንድም ሴትም የለም፤ ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና። እናንተም የክርስቶስ ከሆናችሁ እንኪያስ የአብርሃም ዘር እንደ ተስፋውም ቃል ወራሾች ናችሁ» (ገላ ፫፤፳፮-፳፱)

ዓለማችን ልዩነትን እንዴት ታያለች?

 የልዩነት ሁሉ ምንጩ ሰይጣን ነው። ሰይጣን አንድነትንና ኅብረትን ይጠላል። ሰይጣን የዚህ ዓለም ገዢ የተባለው ዓለሙም ግዛቱም ሁለቱም የሚጠፉ በመሆናቸው ናቸው። በዚህ ጠፊ ነገር ላይ የሚታመኑቱ ሁሉ አብረው ይጠፋሉ። ምክንያቱም «የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና» (፩ኛ ቆሮ ፯፤፴፩)የተባለው ለዚህ ነው።  በአንድ ዘመን ገናና የነበሩና ዓለሙን ያስገበሩ ዛሬ የሉም። ተስፋቸው ሁሉ በዚህ ምድር ላይ የቆመው እነዚያ ሁሉ ጠፍተዋል። ተስፋ ከዓለሙ ግዛት በላይ ስለሆነ ይህንን ተስፋ ሳያገኙ ለዓለሙ ደክመው አልፈዋል። ሰማያዊ ተስፋም አልተጠበቀላቸውም። ለእግዚአብሔር መንግሥት ከሰራና ለመንግሥቱ አገልግሎት ከተጋ በቀር በሰማይ ያለውን ተስፋ የሚጠብቅ እሱ ማነው?   «…..በእግዚአብሔር ኃይል ለተጠበቃችሁ ለእናንተ በሰማይ ቀርቶላችኋል» (፩ኛ ጴጥ ፫፤፭) የተባለው ከፀሐይ በላይ ባለው አዲስ ነገር ተስፋ ያደረገ አይደለምን? በዚህ ዓለም ተስፋ ያደረጉ ተስፋቸው እዚሁ ያበቃል።

ከዚህ ምድር ባለፈ ሰማያዊውን ተስፋ ሰዎች እንዳይጠብቁ ለማጥፋት ጠላት አበክሮ ይሰራል። ሰይጣን ተስፋ የለውም። የተጠበቀውም ለዘላለም እሳት ነው። «መኖሪያቸውንም የተዉትን እንጂ የራሳቸውን አለቅነት ያልጠበቁትን መላእክት በዘላለም እስራት ከጨለማ በታች እስከ ታላቁ ቀን ፍርድ ድረስ ጠብቆአቸዋል»                ይሁዳ ፩፤፮

ለእርሱ የተጠበቀው ተስፋ የዘላለም እሳት መሆኑን ስለሚያውቅ የጥፋት ተስፋ ከፀሐይ በታች እንዲበረታ አዲስ አድርጎ ያሳያል። የምድሩ አዲስ ሆኖ መታየት የሰማዩን አዲስ ሕይወት ይሰውራል። ይህንን ተልዕኮውንም ለመፈጸም በእንስሳ አስተሳሰብ በተመሰሉ ሰዎች ውስጥ ያሳድራል። ከቅርብ ጊዜ ክስተት አንዱን ብንጠቅስ የ፪ኛውን የዓለም ጦርነት ውጤት እንኳን ብናነሳ የናዚዎች እንስሳዊ ተግባር ለ፶ ሚሊዮኖች ሞትና ለ፻ ሚሊዮኖች ስቃይ ምክንያት እንደሆነ እናውቃለን።  የሰው  ሆድ ዕቃ ለሳሙና ፋብሪካ ጥሬ ዕቃ ሆኖ እንዲቀርብ ከማድረግ ወዲያ ለሰው እንስሳነት ገላጭ ነገር ይኖር ይሆን? ዓለሙም ግዛቱም አላፊ ጠፊ በሆነው በዚህ ዓለም ይህ መደረጉ እውነት ነው። የ፫ኛው የዓለም ጦርነት ቢነሳ ምክንያቶቹ በተመሳሳይ ተስፋ የለሾች እንስሳዊ አስተሳብ በሚያጭሩት ሰዎች ይሆናል። ውጤቱም እጅግ ዘግናኝና አስከፊ መሆኑን መገመት አይከብድም። የሰው እንስሳዊ ጭከና መጠኑን እያለፈ መጥቷል። ዛሬ ሰው ገንዘቡ እንዳይዘረፍ ሳይሆን የሆድ ዕቃው እንዳይሰረቅ ከሚፈራበት ዘመን ላይ ደርሷል። እጅግ አስፈሪ ሁኔታ ውስጥ እንኖራለን። ስስት፤ ግድያ፤ ስቃይና ሰቆቃ እንግዳ ነገር መሆኑ ቀርቷል። ዓለም ጭንቅ ልጇን እያማጠች ትገኛለች። የምትወልደው መቼ ይሆን?

አፍሪቃ አኅጉራችንስ?

በሌላ መልኩም ከክርስትናው ይልቅ ለባዕድ አምልኮ ቅርብ የሆነው የአፍሪቃው ክፍለ አኅጉር ተስፋ የሌለው የጨለማው አኅጉር የመባሉ ነገርም አለምክንያት አይደለም። ቀደም ሲል /back-ward continent/ ይባል ነበር። ኋላቀር ማለት ብቻ አይደለም፤ወደኋላው የሚሄድ ማለትንም ስለሚያመለክት ጥቂት ማሻሻያ ተደርጎለት /developing/ ወይም እያደገ ለማለት ተሞክሯል። እያደገ የሚሄድ ማለትስ ምን ማለት ነው? ለአፍሪቃ አለማደግ የእግዚአብሔር የፍጥረት ስራ ጉድለት ነበረው? በፍጹም! አይደለም።

 ያለማደጉ ምክንያት እንስሳዊ አስተሳሰቡ ነው።  ይህ አኅጉር እንደእንስሳ ከመሸጥ፤ ከመለወጡ በስተቀር በብዙ መልኩ እንስሳዊ ሃሳቡን ዛሬም እርግፍ አድርጎ አልተወም። ተራራን፤ ወንዝን፤ ዛፍን፤ የእጁ ስራዎች ጣዖታትን፤ ሰውን፤ እንስሳትንና ልዩ ልዩ ምስሎችን እንደመጨረሻ የእምነቱ ምዕራፍ አድርጎ ሲያመልክ ኖሯል፤ ዛሬም ይህንኑ አምልኮ አልተወም። ያለማወቁ፤ የድህነቱ፤ የችግሩ፤ የህመሙ፤ የእርስ በእርስ ፍጅቱ መነሻ ተስፋ በሌለው ነገር የመታመኑና ከእንስሳ አስተሳሰብ ያለመውጣቱ ምክንያት እንጂ ከእግዚአብሔር ለአፍሪቃ ብቻ የተሰጠ የተለየ የአርባ ቀን እድል ስላለ አይደለም። አፍሪቃ ዛሬም በዚሁ የእንስሳ አስተሳሰቡ ውስጥ አለ። የዚህ ዓለም ድህነት፤ በሽታና ጦርነት እንደምሳሌ የሚጠቀሰው ይህ አህጉር ዛሬም ከዚህ ተስፋ የለሽ ጥፋት መውጣት አልቻለም። ከምዕራብ እስከምሥራቅ፤ ከሰሜን እስከ ደቡብ ድረስ አፍሪቃ ዛሬም ከጨለማ አስተሳሰብ ጋር ይኖራል። በመንፈሳዊ አሳብ ያልተለወጠና ከጥበብ አሠራር ጋር ያልተገናኘ ይህ አኅጉር ዛሬም በጨለማ ሕይወት ውስጥ ይዳክራል። ከማሊ እስከኮንጎ፤ ከሩዋንዳ እስከዝምባብዌ፤ ከሱዳን እስከቻድ፤ ከኮትዲቯር እስከ ግብጽ ድረስ ይህ ጨለማነት በልዩ ልዩ መልኩ ነግሦ ይታያል። በሩቅ ምስራቅ ያሉ አፍሪቃን መሰል ሕዝቦችም ኑሯቸው ጨለማ መሆኑ በተወራራሽ ልምድና ባህል ውስጥ ስላሉ ነው። ሰይጣን በጨለማ አስተሳሰብ እንዲኖሩና ራሳቸውን የሚለውጡበትን ጥበብ በባእድ አምልኮ ውስጥ ይሰውራል። ሁሉም ነገር በጨለማ አምልኮ ውስጥ እንደሚመነጭ ይስላል። ከዚህ ወጥተው ራሳቸውን ወደመለወጥ ለተራመዱት ደግሞ መልኩን የለወጠ ምድራዊ ተስፋን ከፊታቸው ያስቀምጣል። ሁሉንም ከፀሐይ በታች ባለው ነገር እንዲታመኑ ያደርጋል። እኛ ግን ሀገራችን በሰማይ ነው ጳውሎስ በመልዕክቱ። (ፊልጵ ፫፤፳)

ኢትዮጵያስ የት ናት?

ስለሀገራችን ስናነሳ ብዙውን ነገር ለራሳችን ቆርሰን በጎነቱን እናበዛለን። በጎነቱን ማብዛት ባይከፋም የሌለውን ነገር ለማሳመር መፈለግ  «ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ» እንደሚባለው መሆኑ ነው። ይሁን እንጂ እኛ እንደምንለው ኢትዮጵያ ከሌላው በተለየ መልኩ «ሀገረ እግዚአብሔር» ናት ወይ? ከሌላውስ ዓለም በተናጠል እንደሚወራው «ለእመቤታችን ዐሥራት» ትሁን ተብላ ተሰጥታለች ወይ? ተግባር የለሽ ራስን ከፍ ከፍ የማድረግ ነገር ጸያፍ ነው።

በአንድ ወቅት የያዕቆብ ሰማርያና፤ የይሁዳው ኢየሩሳሌም የእግዚአብሔር የአምልኮ ስፍራ እንደሆኑ አድርገው ለራሳቸው ትልቅ ግምት ሰጥተው ነበር። ከሰማይ ሆኖ ሁሉን የሚያየው እግዚአብሔር ግን ሰዎቹ ለራሳቸው ከሰጡት ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ዓይን የተለየ ሁኔታ ውስጥ ነበር። ሕቅዝኤል ነብይ በራእይ ሸክሙ አንዲት እናት የወለደቻቸውን ሁለት እህትማማቾች ተመልክቷል። ኦሖላና ኦሖሊባ ይባላሉ። ሁለቱ እህትማማቾች ለአቅመ ሔዋን ሲደርሱ በወግ በማእርግ ጋብቻቸውን በሕግ ማጽናት ሲገባቸው በግልሙትና ረከሱ። ገንዘብ ያለው ወደጣሪያቸው ገባ፤ አብሮአቸውም ተዳራ፤ ከሹማምንቱ፤ የከበረ ስፍራ ከተቀመጠ፤ ዝናና ስሙ ከገነነው ጋራ ተወዳጁ። አብረውም አንሾካሾኩ። በድሪያ የተወለዱ ልጆቻቸውም አገልጋይ ሆነው በስካር ተንገዳገዱ፤ የውርደት፤ የቅሚያ፤ የግፍና የዐመጽ ጽዋዎችን ጨለጡ። የብልቃጡን ዘይት በርኩሰት ለኮሱ። ከክፋት ፍም ጭረው፤ በዐመጽ እጃቸው ከዘገኑት እጣን መቅደሱን አጠኑ። መቅደሴን አረከሱ፤ በቤቴ ውስጥም ይህንን አደረጉ። ስለዚህ እግዚአብሔርም ፍዳ እዳቸውን በእዳቸው እመልሳለሁ ሲል በሕዝቅኤል በኩል ተናገረ። እነዚህ ሁለት የተቀደሱ ከተሞች እንደሆኑ ሲያስቡ የነበሩት «ኦሖላ» የያዕቆብዋ ሰማርያ ስትሆን «ኦሖሊባ» ደግሞ ኢየሩሳሌም ነበሩ።  (ሕዝ ፳፫-፩-፵፱) (ሚል ፩፤፩-፲፮) ይህ የሆነው የእግዚአብሔር ከተማ ስትባል በነበረችው በኢየሩሳሌም ነው። ሆኖ መገኘትና እንደሆኑ አድርጎ ማውራት ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው።

ኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያ ድንግል መሬትሽ የሚባል ነገር የለም። መሬትዋ ተቆርሷል፤ ተገምሷል፣ ተከፍሏል። በእንስሳ የተመሰሉ ልጆችዋ በባሕርና በተራራ ላይ መስዋዕት አቅርበዋል። ለሰው አዋቂ ሰግደዋል፤ ገንዘብና ወርቃቸውን ሸጠዋል። ግልሙትናና ምንዝርና በእሳት ደዌ እንዲጠበሱ አድርጓቸዋል። ብዙዎችም ረግፈዋል።  ስደትና ሞት የዘወትር ዜናዎቻችን ናቸው። ረሃብና ድህነት የጆሮ ጉትቻዎቻችን ከሆኑም ቆይተዋል። ሹማምንቱና ነገሥታቱ የመቅደሱ ውስጥ ተዋናይ ሆነዋል። የመቅደሱ አገልጋዮችም የግፍና የዐመጽ፤ የምንዝርናና የቅሚያ ግብራቸውን እንደ ተወደደ መስዋእት ቆጥረውታል። ከክፋት ፍም ጭረው፤ በዐመጽ እጃቸው ከዘገኑት እጣን መቅደሱን አጥነዋል። መቅደሴን አረከሱ፤ በቤቴ ውስጥም ይህንን አደረጉ፤ ዘይታቸው በኃጢአት ግማት ሸቷል፤ ዕጣናቸው በድፍረት ርኩሰት ቅርናት ሆኗል። ታላቂቱ ኦሖላ በቤተ መንግሥቱ፤ ታናሺቱ ኦሖሊባ በቤተ ክህነቱ ቢመሰሉ ግብራቸው  ከእውነት የራቀ አይደለም።  ይህን አገልግሎት ይሆን በሀገረ እግዚአብሔርነት ሽፋን የሚሰብኩን? ይህ የእግዚአብሔር አገልግሎት ከተባለ፤ የእግዚአብሔር ቃል ተለውጧል ማለት ነው።? [በዚህ ጽሁፍ ቤተ ክህነት የሚለው ቃል አንድ የተወሰነ ክፍልን አያመለክትም። ክህነት ማለት አገልጋይ ማለት እንደመሆኑ መጠን የየትኛውንም እምነት አገልጋይ ይወክሏልና በዚያ መልኩ ይተርጎም]

እግዚአብሔር እንደዚህ ዓይነት አገልጋዮች የሉትም። ኢትዮጵያ «ሀገረ እግዚአብሔር» የሚሉት ይሄንን ከሆነ ተሳስተዋል። ስለሚኖሩባት ኢትዮጵያ አያውቁም፤ ወይም ማወቅ አይፈልጉም። እግዚአብሔር ሀገርን የሰራው ሰው እንዲጠቀምበት በመሆኑ ሰው የሌለበት መሬት ለእግዚአብሔር ምኑም አይደለም። የእመቤታችን የዐሥራት ሀገር የሚሉት ሰውን ነው ወይስ ምድሩን? ሚሊዮኖች እንስሳዊ ሃሳብ ያላቸው ሰዎች ሞልተውባታል። የአብዮት ልጇን ትበላለች ዝማሬ ተዘምሮ ነበር። እንደዝማሬዋም አብዮት የምትባል፤ ሰው በሊታ በአንድ ወቅት በዚህችው ሀገረ እግዚአብሔር በምትባል ሀገር ላይ ሰው ስትበላ ኖራለች። በዚህችው ምድር ላይ ዘላለማዊ ነገር እንደሌለ እያወቅን ዘላለማዊ ክብርን በሙታን መንፈስ እናስቀጥላለን ባዮች ዛሬም ይዘምራሉ።  ዘላላማዊ ክብር ለሰው በዚህ ምድር ላይ አልተሰራም። ሁሉም ያልፋሉ። ሰማይና ምድር እንደማያልፍ ለሚያምኑ ሰዎች አዲስ ነገራቸው ያለው እዚህ ምድር ላይ ብቻ ነው። እንግዲህ ኢትዮጵያ ማለት ይህች ናት። ተፈጥሮን በቁጥጥር ስር ከማዋል ጀምሮ ፤የሙት መንፈስ ሌጋሲ እስከማስቀጠል የሚሄዱ ሰዎች የሚኖሩባት ሀገር ናት። በሌላ መልኩም እምነት የለሾች፤ ያላቸው የሚመስሉ ግን የሚያምኑትን የማያውቁ ወይም አውቀው የማይኖሩበት፤ ወይም ያልኖሩበት ሰዎችም ይርመሰመስቡታል። ታዲያ ዐሥራት ተብለው የተቆጠሩት የትኞቹ ይሆን? ዐሥራትነቱ ለተወሰኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች ወይስ ለኦሖሊባና ለኦሖላም ጭምር?

ነገሩ ለራስ ሲቆርሱ አያሳንሱ ሆኖ ነው እንጂ ኢትዮጵያ ከሌላው የተለየች ሆና አይደለችም። እግዚአብሔር ሰውን በምድር ላይ መፍጠሩ ከፀሐይ በታች በምንኖረው ነገር በጥረት ከምናገኘው በቀር ለእኛ የሚተርፈን አዲስ ነገር ኖሮት አይደለም። ይልቅስ ከፀሐይ በላይ ስላለው አዲስ ሕይወት ተስፋ አድርገን እንኖርበት ዘንድ ይፈልጋል። በዚህ ምድር ሰዎች ዙፋን ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ከማየት በላይ ተስፋ የምናደርገው ነገር አለን። «እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ ሰማይ ሲከፈት የእግዚአብሔርም መላእክት በሰው ልጅ ላይ ሲወጡና ሲወርዱ ታያላችሁ አለው» ዮሐ ፩፤፶፪

ታዲያ ኢትዮጵያ ተስፋዋ ምንድነው? ዘር ወይስ ጎሣ? ፖለቲካ ወይስ ሽኩቻ? ክልል ወይስ ክፍለ ከተማ? ሀገረ እግዚአብሔር መባሏ? ወይስ ኦሖሊባነቷ? እኮ የኢትዮጵያ መጪ ተስፋ ምንድነው?

አንዳንዶች ዐባይ ሲገደብ ተስፋችን ይሞላል ሲሉ ይደመጣል። አንዳንዶች ደግሞ ነዳጅ ቆፍረን ብናወጣ የድህነታችን ፋይል ይዘጋል በማለት ያወራሉ። አንዳንዶች የኒዮ ሊበራሊዝም አስተሳሰብ ሲሞትና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ሲነግሥ ነው ይላሉ። ሌሎች ደግሞ በተቃራኒው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጉድጓድ ካልገባ በስተቀር ምንም ጤንነት የለም ሲሉ መደመጣቸውም እንግዳ ነገር አይደለም።  ሰርቶ መለወጥና ኑሮን ማሻሻል የእግዚአብሔር ሃሳብ ነውና ይህንን ማለቱ ባልከፋ፤ ግን በእውነት ከእንስሳዊ አስተሳሰብ ወጥተናል? እንስሳዊ አስተሳሰብ የአእምሮ መመረዝ ውጤት ነውና ይህ አስፈሪ ነገር በሀገራችን ለዘመናት ቆይቷል። ዛሬም አልተለየንም።

ሃይማኖቶቹ በእነሱ በኩል ብቻ የኢትዮጵያ ተስፋ ከእግዚአብሔር እንደሚላክና ይህንን ለመቀበል ወደእነሱ ሰው ሁሉ እንዲመጣ ይሰብካሉ። በእውነታው ግን የሚታየው ኢትዮጵያ በብዙ የአስተሳሰብ ሽቦ የተወጠረች ሀገር መሆኗ ነው። ፖለቲካው ሽኩቻና መጠላለፍ የሞላበት አስቀያሚ ነው።  ላለፉት አርባ እና አምሳ አመታት ብሶበታል። አሁን አሁንማ ከአንድነትና ከኅብረት ይልቅ ልዩነቱ ሰፍቷል። እንዲያውም መጪው ዘመን ኢትዮጵያ ስለምትባለው ሀገር ቀጣይነት አስፈሪ ሁኔታዎች እየታዩ ነው። የፖለቲካው ዲስኩረኛ ሹማምንት ሀገርን የምናድን እኛ ነን እንደሚሉት ሳይሆን በምድሪቱ ሰዎች ያለው አስተሳሰብ ተስፋ የሚጣልበት አይደለም። ሃይማኖት የሚባለውም ነገር በማክረርና በውሻል ከመተዳደር ባለፈ እዚህ ግባ የሚባል የአስተሳሰብ ለውጥ የለውም።አብዛኛውን ጊዜ ኅሊናዊ ምትሐት /delusion/ ላይ ያተኮረ አምልኮ በሁሉም ዘንድ ይታያል። ዘረኝነቱ፤ ጎጠኝነቱ፤ አድርባይነቱ፤ ጭከናው፤ ግድያው፤ስደቱና እስራቱ የእንስሳዊ አስተሳሰብ ውጤት ነው። ዳዊት ያለው እውነቱን ነበር። «አእምሮ የሌለው ክቡር ሰው እንደሚጠፋ እንስሶች መሰለ» (መዝ ፵፱፤፳) አስተሳሰባችን እስካልተለወጠ ድረስ በጥበብ ግስጋሴ ለማደግም ይሁን ተስፋ የምናደርገው ሰማያዊ ነገር ለማወቅ  አይችልም። ስለዚህ ምን እናድርግ? አዎ ምርጫችን-----

ምርጫችን፤
1/ አንድ እንሁን፤ ኅብረት ይኑረን፤ ከትንሿ እንስሳ ከንብ ጥበብንና ትጋትን እንማር። ኅብረት ባይኖራቸው ያንን የመሰለ ጣፋጭ ነገር መስራት ባልተቻላቸውም ነበር።                                                  

2/ አንድ ዓይነት እምነትና አስተሳሰብ ባይኖረን እንኳን ለራሳችንና ለልጆቻችን የምትስማማ ሀገር እንድትኖረን እናድርግ።                                                                                                                                 

3/ ፖለቲካ ከሚሉት ማጭበርበር እንውጣ፤ ከዚህ ይልቅ እውነት ሆኖ በሚታይ ተግባር ላይ እንሰማራ። ፖለቲካ ተግባር አይደለም፤ ተግባር ግን ውጤትነው።

4/እምነት አለን የምን ሰዎችም እምነታችንን በተግባር እንግለጽ፤ ከምትሐት መሰልና በእግዚአብሔር ስም የመነገድ ማታለል እንለይ። ሃይማኖት እምነት አይደለም፤ እምነት ደግሞ በእግዚአብሔር አሠራር ላይ ካልተደገፈ አምልኮ ጣዖት ነው። ራሳችንን በእግዚአብሔር እስትንፋስ እንመርምርና እንመለስ።የማይጠፋ ተስፋ በውስጣችን ይኑር። ወንዝና ተራራ ፍጥረቶች እንጂ የተስፋችን ድንበሮች አይደሉም። ዘር ለእህል እንጂ ለሰው አይጠቅምም። ቆጠራው ከአዳማዊና ሔዋናዊ ማንነቱም አይፍቀውም። ወጣቱ ፖለቲካ የሚባለውን ውሸት መጥላት አለበት። ተግባር የሚለውን መለኪያ እንደመስፈርት ቢጠቀም ኖሮ ማንም ወደእርድ እንደሚነዳ እንስሳ ለሥልጣን መደላድል ባልተጠቀመበት ነበር።

አንድ አስረጂ ላንሳ። ዱባይ የምትባል የዐረብ ከተማ አለች። በአንድ ወቅት የዚህችው ከተማና የስቴቱ መሪ ልዑል ለእርሱ በተዘጋጀ በጀርመን ዓለም አቀፍ የሽልማት መርሐ ግብር ላይ እንዲህ ሲል ሰምቼዋለሁ።  «ልዑል በተባልንበት ሥልጣን አንመካም፤ ፖለቲካ በሚሉት ዲስኩርም አናስተዳድርም፤ ሀገራችን የሚያስፈልጋትንና ሕዝባችን የሚጠቀምበትን ነገር በተግባር ሠርተን እናሳያለን። ሀገራችን ስታድግ፤ ሕዝቡ ኑሮው ሲሻሻል ያኔ በተግባር ልዑል መሪ እንባላለን» አለ። በእውነት ድንቅ አባባል ነው። ዱባይ እድገቷ የዚህ አስተሳሰብ ውጤት ነው እንጂ ምትሐት አይደለም። ነዳጅም አይደለም። እንደነዳጅ ብዛትማ ቢሆን የነዳጅ ጉድጓድ ማከማቻ የሆነችው ናይጄሪያ የት በደረሰች ነበር። ልዩነቱ በተግባር በሚገለጽ አስተሳሰብ የተነሳ እንደሆነ ማስተዋል ይቻላል። እኛ ኢትዮጵያውያን ማስመሰልና ማታለል የፖለቲካ ወንበር መጨበጫ ስላደረግነው እድገታችን የኋሊት ሆኗል። አስተሳሰባችን ይለወጥ፤ የፖለቲካ ቁማር ተጫዋቾቻችን የአስተሳሰብ ርእይ ይኑራችሁ። ከእንስሳነት አስተሳሰብ ተለዩ። ብዙዎች መጥተው ሄደዋል፤ የእናንተም ተራ ሲያልቅ ትሄዳላችሁ። ተስፋ የሚያደርገው ነገር ያለው ትውልድ እንዲኖረን ሀገሪቱን አስማሙ። በተስፋ የተሞላ መንፈስ በተግባር የታገዘ መንገድ መድረሻው የፍቅር ከተማ ነው። ጉንጫችሁ ስር ያለውን ውሸትን ተፍታችሁ የእውነትን ጽዋ ጠጡ። ይህንንም በተግባርም አሳዩ! ያለበለዚያ ኢትዮጵያን ከቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ መለየት አይቻልም!
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 1 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
April 21, 2013 at 6:52 AM

በእውነት ድንቅና አስተማሪ ጽሁፍ ነው። በርቱ። ብንስማማና ለችግሮቻችን ብንነጋገር ኖሮ የት በደረስን ነበር።ኃ።ስላሴ የራሳቸውን አላማ , ደርጉም የራሱን ሶሻሊዝም ጫነብን ፤ መከራ ብቻ አግኝተን ጠፋ፤ ኢህአዲግም የራሱን አብዮታዊ ዲሞክራሲ አምጣብን, እሱም በተራው ይሄዳል። ኢትዮፕያ ግን የመሪዎች ላቦራቶሪ ሆና ቀረች። እስካሁን የፈለግነውን አላገኘም። የሰማንም የለም።
እግዚአብሔር ኢትዮፕያን ይባርክ

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger