Wedkom Yaferal Read in pdf
የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ዓርብ ሚያዝያ 18/2005 ዓ.ም.
ከጸሎት ክፍሎች አንዱ ስእለት ነው፡፡ ስእለት ለእግዚአብሔር የምንገባው ቃል ነው፣ እግዚአብሔርም የሚጠብቀው ብርቱ ነገር ነው /መክ. 5፡4-5/፡፡ በተሳልንበት ግለት እንድንፈጽመው ይጠበቅብናል፡፡ ስእለት ለእግዚአብሔር አመጣለሁ የምንለው የምስጋና መግለጫ ነው፡፡ አንዳንዶች ገንዘባቸውን፣ ሌሎች ሕይወታቸውን፣ የቀሩት ልጆቻቸውን፣ ውስኖች የሰጣቸውን ለእርሱ ለመስጠት ስእለት ይገባሉ፡፡ ስእለት መሳል ፈቃድ ነው፣ አለመፈጸም ግን ትልቅ ኃጢአት ነው፡፡ ሰው እግዚአብሔርን እንዴት ይዋሸዋል?
ስእለት እግዚአብሔር ስላደረገልን ነገር የምስጋና መግለጫ ይዘን የምንመጣበት ነው፡፡ ስእለት የውለታው ምላሽ ሳይሆን የውለታው መታሰቢያ ነው ብንል ይገልጸዋል፡፡ በብዙ ጭንቀቶች ባለፍኩባቸው ዘመናት ሁሉ ስእለትን ለእግዚአብሔር እሳላለሁ፡፡ እነዚያን የከበዱኝን ወራቶች ሳስብ መከራው ከባድ ሆኖ ነው ወይስ እኔ ደካማ ሆኜ ነው? የሚለውን እስካሁን ልመልሰው አልቻልኩም፡፡ ብዙ የሀዘንና የስብራት ዘመኖችን እግዚአብሔር አሻግሮኛል፡፡ እንደ ፈቃዱም መልስ ሰጥቶኛል፡፡ እንደ ፈቃዱ ከልክሎኛል፣ እንደ ፈቃዱ ባርኮኛል፡፡
“ስለ እኔ የሚሟገት የለም ወይ?” ያልኩባቸው ዓመታት ብዙ ናቸው፡፡ የሚጠሉኝ የሚያደርሱብኝን ፈተና አስብና፡- “ሬሣ መደብደብ ጀግና ያሰኛል ወይ?” ያልኩባቸው ጊዜያት ጥቂት አይደሉም፡፡ የሚቃወሙኝ ግን ሬሣ ነው ብለው አልናቁኝም፡፡ በእኔ ላይ ያለውን የእግዚአብሔርን ዓላማ ከእኔ ይልቅ ተረድተውታል፡፡ የሚጮኹት ከዚህ ዓላማ ሊያዘገዩኝ መሆኑን የተገነዘብኩት ቆይቶ ነው፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ በአንድ ወቅት፡- “እግዚአብሔር በውስጥህ የከበረ ነገር አስቀምጧል፣ ያንን እንዳታወጣው ግን ሰይጣን ዙሪያህን በድምፅ ሞልቶታል፤ የዙሪያውን ድምፅ ተውና በውስጥህ የተቀመጠውን ቶሎ ቶሎ አውጣ” አሉኝ፡፡ በአስቸኳይ አስጠርተውኝ የነገሩኝ ይህ ብቻ ነው፡፡ ይህን መልእክት ከተናገሩ በኋላ፡- “ጨርሻለሁ ሂድ” አሉኝ፡፡ እንቅልፍ ያጡበት መልእክት መሆኑን ሰምቻለሁ፡፡ የገባኝ ቆይቶ ነው፡፡ አዎ ሰው ደካማ ነው፣ ከእኔ ይልቅ ግን ደካማ ያለ አይመስለኝም፡፡ የደካማው ዋስ ሆኖ የተሰቀለውን ጌታዬን አሁንም እማፀናለሁ፡፡
በብዙ ትግል ውስጥ ባልፍም ከትግሎቹ በላይ የሚቆጨኝ ክርስቲያን በቅድስና ክብሩ አለመቆሙ ነው፡፡ ፖለቲከኛው ጥሩ ፖለቲከኛ ሆኖ አያለሁ፣ ወታደር ለሞት ተልኮ ሲሄድ አያለሁ፡፡ ክርስቲያን ግን ለመኖር ተጠርቶ አለመኖሩ ያሳዝነኛል፡፡ በራሴ አዝናለሁ፡፡ በእውነት ፖለቲካው ከልብ የሚሮጥለትን ያገኘውን ያህል እግዚአብሔር ሰው አላገኘም፡፡ ይህ ያመኛል፡፡ ክርስቲያን በዓለም ፊት፣ በዝሙትና በገንዘብ ፊት በጽናት መቆም አለመቻሉ የሀዘኔ ሀዘን ነው፡፡ ይልቁንም ዛሬ ዛሬ በስካራችን፣ በዝሙታችን ክርስቶስን በአደባባይ እየገፈፍነው፣ በአደባባይ ምራቅ እየተፋንበት ነው፡፡ ወዳጆቼ በአንድ ክርስቲያንና በአንድ አረማዊ መካከል ልዩነት ከማጣት የበለጠ ምን የሚያሳዝን ነገር አለ? ክርስትናችን የቆመው በአጽሙ እንጂ በሕይወቱ አይደለም፡፡ ብዙ ያስተማርናቸው ብዙ የተለፋባቸው የወደዷት ዓለም እንደ ተጋጠ ቆሮቆንዳ ግጣ ጥላቸዋለች፡፡ ቤተ ክርስቲያን ያደረ ስካር ማስለቀቂያ፣ ጉባዔ ዝሙት ያመጣውን ድብርት ማባረሪያ መሆኑ ያሳዝናል፡፡ ችግሩ ያለው ከእኛ ከአገልጋዮች ነው ብለን ብዙ ዘመን ለማልቀስ ሞክረናል፡፡ ግን የያዝነው ሕዝብም ዋዛ አይደለም፡፡ መቅለስለስ ቅድስና ከተባለ ብዙ ቅዱሳን አሉን፡፡ ያ የሰማዕታት የደም ዋጋ የተከፈለበት፣ ያ ስንት ጀግኖች እየዘመሩ የተሠዉበት ክርስትና እንዲህ መቀለጃ መሆኑ በእውነት ልብ ያለውን ልብ ይነካል፡፡ አዎ የሀዘኔ ሀዘን ኃይል አልባ ክርስትና ውስጥ መሆናችን ነው፡፡
ብዙ ዓይነት ስእለቶችን ለእግዚአብሔር እገባለሁ፡፡ ዛሬ ግን ከቃሌ ፈጥኖ ልመናዬን ስለ ፈጸመልኝ ነገር ልቤ ተደነቀ፡፡ የልመናዬን ልክ ሳይሆን አትርፎ ስላደረገልኝ ነገር ምን ልክፈልህ? አሰኘኝ፡፡ ታላላቅ መሰናክሎች በዙሪያዬ ያሉ መስሎ ይታየኛል፡፡ ታላቅ መዳን በውስጤ ይከናወናል፡፡ ልቤ ተገረመ፡፡ ማንን ላድንቅ መደነቅ በእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ሰይጣን ሲደነቁለት ይጨምርበታል፡፡ እግዚአብሔር ይገሥጽህ ሲሉት አፍሮ ይሸሻል፡፡ በክፉዎች ክፋት መደነቅ ሰይጣንን ማድነቅ፣ ኒሻን መሸለም ነው፡፡ አሳቡን አንስተውም ተብሎ እንደ ተጻፈ አሳቡን መሳት አይገባንም፡፡ እኔ ግን ባለ ማስተዋል ብዙ ጊዜ እጐዳለሁ፡፡ ምስጋናዬን ሊዋጋ በቅርብም በሩቅም ሰዎች ተስፋም ባደረኳቸው ወገኖች በኩል የወጣውን ክፉ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እቃወማለሁ፡፡
እግዚአብሔር እንዲያደርግልኝ የፈለግሁትን ነገር በስእለት አቀረብኩ፡፡ ተጨንቄአለሁ፣ ለእግዚአብሔር ስእለት ተሳልኩ፣ ስእለቴ ምን ይሁን? ብዬ አሰብኩ፡፡ ኤልሳቤጥ ትዝ አለችኝ፡፡ ጌታ ልጅ በሰጣት ጊዜ የእርጉዝ ልብስ ለመግዛት፣ መሐን ናት ተረግማለች ላሏት፡- “እግዚአብሔር የሠራውን እዩ” ለማለት አልቸኰለችም፡፡ እግዚአብሔር እንደ ጐበኛት ስታወቅ ስድስት ወር ራሷን ሰወረች /ሉቃ. 1፡24/፡፡ እኔም የመሰወር፣ ከእግዚአብሔር ጋር ብቻ የመሆን ስእለት ተሳልኩ፡፡
ስእለትን ለመፈጸም የሄድኩበት ስፍራ ከዛፎች ጋር ጉባዔ ከወፎች ጋር ምስጋና የማቀርብበት ነበር፡፡ እግዚአብሔር ይህ ያስፈልግሃል እንዳለኝ ተሰማኝ፡፡ ጸሎቴን አድርሼ የምቀመጥባቸው ስፍራዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ አንድ ቀን የተቀመጥኩት የዛፍ ግንድ ላይ ነው፡፡ እግሬ መሬት ነክቶ ግንዱ ላይ ተቀምጫለሁ፡፡ ተዳፋት ላይ የበቀለው ያ ዛፍ ወድቋል፡፡ ወድቆ ግን አልደረቀም፣ አልረገፈም፡፡ ወድቆ ለምልሟል፣ እያፈራም ነው፡፡ እጅግ ተገረምኩኝ፡፡ ወድቆም ያፈራል!
እግዚአብሔር የጠራን የጽድቅ ዛፎች እንድንሆን ነው /ኢሳ.61፡3 /፡፡ እነዚያን የወደቁ ዛፎች ሳይ ትዝ ያለኝ የዘመናችን ክርስትና ነው፡፡ የተተከልነው ተዳፋት ላይ ነው፡፡ ጐርፍ በቀላሉ የሚሸረሽረው ስፍራ ላይ ነን፡፡ ይህ ተዳፋት በሰው የመታመን ክርስትና ነው፡፡ ዓይናችን ያለው ሰው ላይ ነው፡፡ ኃጢአትን ሌሎቹ ከፈጸሙት እኛም ለመፈጸም ድፍረት ይሰማናል፡፡ አንድ ወጣት ከባድ ስህተት ፈጽሞ ለምን እንዲህ አደረግህ አልኩት፡፡ እርሱ ግን የሰጠኝ መልስ እገሌ እገሌ የሚባሉ አገልጋዮች በአንድ ጊዜ ወደ ብቃት ልትሄድ ነው ወይ? ብለውኝ ነው አለኝ፡፡ ያለው ትክክል መሆኑን አረጋግጫለሁ፡፡ ያ ወጣት ሳገኘው እንዴት ተበላሽቶ እንደነበር ልገለጽ አልችልም፡፡ ወገኖቼ አገልጋዩ በእግዚአብሔር ይመዘናል እንጂ እግዚአብሔር እንዴት በአገልጋዩ ይመዘናል! አዎ ብዙዎች የጠራቸውን ጌታ ሳይሆን የሚያደፋፍራቸውን ሰው እየፈለጉ ነው፡፡
ልቤ አዝኖ፣ ስለ ውድቀታችን እያነባው ሳለ እነዚያ ወድቀው የሚለመልሙ ዛፎች ትዝ አሉኝ፡፡ ወድቀናል ግን እያፈራን ነው፡፡ ዛሬም ድውዮች ይፈወሳሉ፣ ዛሬም በንስሐ ብዙዎች ይመለሳሉ… ፡፡ እግዚአብሔር በውድቀታችንም ካልተወን በትንሣኤያችንማ እንዴት ያከብረን ይሆን!?
ብዙ መልካም አገልጋዮች ባለው ነገር ልባቸው ተስፋ እንደ ቆረጠ አውቃለሁ፡፡ ግድ ሆኖባቸው ያገለግላሉ፣ ይሰብካሉ፡፡ ብዙ ሰዎች ወደ እነርሱ እየመጡ በእውነት ተነክተናል፣ ከዓለም ለመውጣት ወስነናል ሲሏቸው ለማመን ይቸገራሉ፡፡ እግዚአብሔር ስለ ቸርነቱ አልተወንም፡፡
ትዳር በየዘመናቱ ፈተና ቢገጥመውም እንደ ዛሬው ዘመን ግን ብዙ ፈተና የገጠመው አይመስልም፡፡ ወንዶች በጭካኔ፣ ሴቶች መብት በሚል ስም ትዳር የፍቅር ቤት ሳይሆን የእልህ ቤት ሆኗል፡፡ በፍቅር እንጂ በእልህ ቤት አይቆምም፡፡ መብት ፍቅርን አያመጣም፣ ፍቅር ግን መብትን ያመጣል፡፡ ባለትዳሮች አንዱ አንዱን ለመቀበል ፈቃደኛነት ያስፈልጋቸዋል፡፡ የችግሩ ሥር ያለው መነጋገር አለመፍቀድና ልክ ነኝ በሚል ስሜት መወጠር ነው፡፡ ትዳር ግን እንዲህ ቢወድቅም ዛሬም ልጆች ይወለዳሉ፡፡ ትዳር ወድቆ እያፈራ ነው፡፡ ወድቆ ማፍራት ግን ጊዜያዊ እንጂ ዘላቂ ፍሬ አይኖረውም፡፡
አገራችንን ስናይ ከቀደሙት ነገሥታት ጀምሮ እንድታድግ ብዙ ጥረቶች ይደረጋሉ፡፡ መንገዶችና ሕንጻዎች እየተሠሩ ነው፡፡ በተቃራኒው ግን የትውልድ ሞራል ወድቋል፡፡ ትውልድ እንደ ዓይን የጠፋበት ዘመን ቢኖር ይህ የእኛ ዘመን ነው፡፡ አገራችን ወድቃ እያፈራች ነው፡፡ ይህ ፍሬ ግን ትንሣኤ ካላገኘ ቀጣይነት አይኖረውም፡፡
በመጽሐፈ መሳፍንት፡- “… ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር” ይላል (መሳ. 8÷4)፡፡ ደክመንም የምናሳድደው እግዚአብሔር ስላልጣለን ነው፡፡ እርሱ ትንሣኤና ሕይወት ነውና ለውድቀታችን ትንሣኤን፣ ለሞታችን ሕይወትን ይሰጠናል፡፡ ክርስቲያን ሆይ እንደገና በርታ፡፡ አዚም እንቅልፍ አይደለም፣ አዚም በሽታ ነው፡፡ በአዚም ከተያዝንበት ነገር የኢየሱስ ክርስቶስን ስም ጠርተን መንቃት ይገባናል፡፡ እግዚአብሔር ያግዘን!