Tuesday, April 2, 2013

ድኅነት በሂደት ወይስ በቅጽበት? ለሚለው የዳንኤል ክብረት ስብከት የተሰጠ ምላሽ



ደግመን ደጋግመን እንደምንለው አሁንም እንላለን። ማቅና አገልጋይ ወኪሎቹ ጊዜና እድል ስላረገደላቸው ብቻ በጠለቀ እውቀት ውስጥ  ሆነው የሚያስተምሩና የሚሰብኩ ይመስላቸዋል። ከእነዚህ መንጋና ጎጋ ሰባኪዎቹ መካከል አንዱ የተረት አባት የሆነው ዳንኤል ክብረት የተባለው ሰው ነው። ለስሙ፤ ለክብሩና ለዝናው ዘወትር የሚተጋ፤ ነገር ግን የአስተውሎት ደኃው ዳንኤል ክብረት በአንድ ስብከቱ ላይ እንዲህ በሚል ርእስ ስህተቱን ለተከታዮቹ ሲረጭ ተመልክተነዋል።

«መዳን በሂደት ወይም በቅጽበት?

በዚህ ርእስ ላይ ዳንኤል «መዳን» ባመኑበት ሰዓት በቅጽበት የሚሰጥ ሕይወት ሳይሆን በሂደት የሚገኝ ሀብት ነው ይለናል። ስለዚህም ክርስቲያኖች ለመዳን  ከፈለግን ለድኅነት የሚያበቃ ተጋድሎ እየፈጸምን መቆየት የግድ አለብን በማለት ድነት/መዳን/ በቅጽበት የመሰጠቱን ነገር ክዶ ሊያስክድ ያባብላል። እውነት፤ ዳንኤል እንደሚለው መዳን በቅጽበት የሚሰጥ ጸጋ ሳይሆን ክርስቲያኖች ለመዳን ሂደትን መጠበቅ አለባቸው?  የእግዚአብሔርስ ቃል እንደዚያ ያስተምረናል? ሰው ለድኅነት ስንት ዘመን መቆየት አለበት? በስንት እድሜው ላይ ሊያረጋግጥ ይችላል? ድነኻል ብሎስ ማን ይነግረዋል? ዳንኤል ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሆን ማብራሪያ መስጠት አልፈለገም፤ እንዲያው ሾላ በድፍኑ ብሎ ፤ ድኅነት በጥረትና በትግል ሂደት የሚገኝ እንጂ በቅጽበታዊ እምነት የሚሰጥ አይደለም ለማለት አጋዥ ምክንያቶቹን በመፈለግ ሊያሳምነን ይሞክራል። ይህንን የሚሉ ካሉ ተሳስተዋል ወይም መናፍቃን ናቸው ሲልም የራሱን ትክክለኛነት ለራሱ ነገሮ ስሙኝ ይላል።  ከየትኛውም ትምህርት ቤትና መምህር እንደዚህ የሚል ቃል እንዳገኘ አይነገረንም።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን  በ«ቅዳሴ እግዚእ»  ቅዳሴ ወቅት በእርገተ እጣን ሰዓት በኅብስቱና ጽዋዕ ላይ ካህኑ እንዲህ እያለ በማጠን ይጸልያል።
«ሰፍሐ እደዊሁ ለሕማም፤ ሐመ ከመ ሕሙማነ፤ ያድኅን እለ ተወከሉ በላዕሌሁ»  ትርጉም፤  «እጆቹን ለሕማም ዘረጋ፤ በእርሱ የታመኑትን ያድን ዘንድ እንደ ሕሙማን ታመመ» ይለናል።  እንግዲህ ክርስቶስ ሕማምና ስቃይን ተቀብሎ እንዳዳነን ይህ ቃል ያረጋግጣል። ሰባኪው ዳንኤል በክርስቶስ ስቃይ እኛ መዳናችን በጊዜ ሂደት የሚረጋገጥ እንጂ በሞተልን ሰዓት የተቀበልነው አይደለም የሚለው ከየት አምጥቶ ነው?
ይህንን የዳንኤልን አሳሳች ስብከትና የጥፋት መርዝ ትምህርቱን  በወንጌል ቃል ገላልጠን  ለማሳየት እንፈልጋለን። አንባቢም የዳንኤልን ስብከት ፈልጎ እንዲያዳምጥ እንጋብዛለን ወይም በስተግርጌ ያስቀመጥነውን ሊንክ በመጫን ይህንን ጽሁፍ አንብቦ እንደጨረሰ አዳምጦ እንዲያገናዝብ ለሚዛናዊ ፍርድ አስቀምጥነዋል። ለወደፊቱም እሱንና እሱን መሰል ስሁታን አረፋ እየደፈቁና እየተንዘፈዘፉ በየመድረኩ የሚወራጩ  የሐሳውያንን  የጥፋት መንገዶች ለማሳየት እንመረምራለን። ሕዝቡን ወደጥፋት የሚነዱ የጠላት መልእክተኞች የሆኑበትን ስብከት እንደዚሁ እየመዘዝን ለማሳየት እንሞክራለን።


ወደርእሰ ጉዳያችን ስንገባ የዳንኤል «መዳን በሂደት ወይስ በቅጽበት» በሚለው ክሂዶተ ድኅነት ትምህርቱን ከመመልከታችን በፊት /መዳን ፤ድኅነት/ ማለት የሚለውን ቃል ራሱን እንይ።

የአለቃ ደስታ ኪዳነ ወልድ መዝገበ ቃላት በገጽ 362 ላይ እንዲህ ሲል ይፈታዋል።
መዳን (ድኂን፤ ድኅነት) መፈወስ፤ መትረፍ፤ ማምለጥ  በማለት ሲያስቀምጠው አድራጊውን ሲያመልክት ደግሞ፤  አዳኝ (አድኃኒ) ያዳነ፤ የሚያድን፤ ፈዋሽ እግዜር፤ ሐኪም ባለመድኃኒት  በማለት ይፈታዋል። ለዚህም ትርጉም ደጋፊ የእግዚአብሔርን ቃል ፪ኛ ሳሙ ፳፪፤3 ላይ በመጥቀስ አመልክተዋል። ጥቅሱም እንደዚህ የሚል ነው።
«እግዚአብሔር ጠባቂዬ ነው፥ በእርሱም እታመናለሁ ጋሻዬና የረድኤቴ ቀንድ፥ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ፥ መድኃኒቴ ሆይ፥ ከግፍ ሥራ ታድነኛለህ»
እንደአለቃ ደስታ አፈታት «መዳን» ማለት መፈወስ፤ መትረፍ፤ ማምለጥ ማለት ነው። አድራጊው አዳኝ ይባላል። እሱም አድኃኒ፤ ያዳነ፤ የሚያድን፤ ፈዋሽ፤ እግዜር/ከፊለ ስም ነው/ ሐኪም፤ ባለመድኃኒት ማለት ሲሆን ለአማኝ ደግሞ ማዳን፤ መጠበቅና መታደግ የእግዚአብሔር ኃይል ስለሆነ ጋሻዬ፤ ረድኤቴ፤ መጠጊያዬና መሸሸጊያዬ ይለው ዘንድ የተገባው እሱን ብቻ ነውና ሊቁ በትርጉማቸው ይህንኑ በኃይለ ቃል አረጋግጠዋል። እንግዲህ መዳንና አዳኝ የሚለው ቃል ትርጉም ይህንን መምሰሉን ከተረዳን የወንጌሉ ቃል አንጻር ስለመዳን ምን ይላል? የሚለውን ደግሞ ቀጥለን እንመልከት።
አለቃ ደስታ እንዳሉት ዘላለማዊ መዳን በቅዱስ ወንጌላችን እንደተጻፈው አዳኝና ፈዋሽ፤ መድኃኒትና ታዳጊ ለሆነው ለኢየሱስ ክርስቶስ የተገባ ስም ነው። ሥግው ቃል በመሃከላችን ከመገኘቱ በፊት ራሱን በነብያቱ በኩል ገልጾ ነበር። ይህንንም ትንቢት ኢሳይያስ ነብይ እንዲህ ሲል ጽፎታል።
«እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ማዳኔ ሊመጣ ጽድቄም ሊገለጥ ቀርቦአልና ፍርድን ጠብቁ ጽድቅንም አድርጉ» ኢሳ ፶፮፤፩
እንግዲህ እግዚአብሔር ወልድ ፤ በሞት ጥላና በጭለማ ለሚኖሩ ሕዝቦች ማዳኑን ሊያሳይ እንደሚመጣ  አስቀድሞ እንደተናገረው ሁሉ የቀጠሮው ሰዓት ሲደርስ ሥጋችንን ተዋሕዶ በመካከላችን የተገኘው ሊያድነን እንጂ ለተጨማሪ ማረጋገጫ ጊዜ ጥበቃ አይደለም።  እግዚአብሔርን የማያውቁ አወቁት፤ አሕዛብ ተብለው በመጻተኝነትና በርኩሰት የተጠሉ  ሁሉ  የእግዚአብሔር ሕዝብ የተሰኙት በፈጸመው የማዳን ሥራው ነበር።
እሱም በቃሉ «ላልጠየቁኝ ተገለጥሁ፥ ላልፈለጉኝም ተገኘሁ በስሜም ያልተጠራውን ሕዝብ። እነሆኝ፥ እነሆኝ አልሁ» ኢሳ ፷ ብሏል።
ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንኑ ቃል በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሲገልጠው እንዲህ ብሏል።
«እንግዲህ፤ የተሰናከሉ እስኪወድቁ ድረስ ነውን? እላለሁ። አይደለም፤ ነገር ግን እነርሱን ያስቀናቸው ዘንድ በእነርሱ በደል መዳን ለአሕዛብ ሆነ» ሮሜ ፲፩፤፲፩
ለእኛ በጭለማና በሞት ጥላ ስር ለነበርነው የእግዚአብሔር ማዳን ተገለጠ፤ ላልፈለግነውም ተገኘ፤ በስሙ ያልተጠራነውንም ሕዝቡ አደረገን። የእስራኤል ዘሥጋ ዐመጽ ለእስራኤል ዘነፍስ መዳን ሆነ። መድኃኒትም ከሰማይ ወረደ። ስሙም በሉቃስ ወንጌል እንደተነገረው «ኢየሱስ« ይባላል። 
«ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና» ሉቃ ፪፤፲፩  ድኅነት ከዚህ መድኃኒት ብቻ ይገኛል። ማዳኑም የተፈጸመው በተሰቀለ ጊዜ ነው። ያኔ ያመኑ ሁሉ ዳኑ። ሐዋርያትም እመኑ፤ ትድናናላችሁ ብለው በስሙ ሰበኩ። ዛሬም ያመኑበት ወዲያው ይድናሉ። ሐዋርያው ጴጥሮስ ከበዓለ ሃምሳ በኋላ በሕያው መድኃኒት ስም ሲያስተምር ቃሉን የሰሙ እንዲህ ሲሉ ጠየቁ። ምን እናድርግ? አሉ። እሱም «ንስሐ ግቡ፤ በኢየሱስ ስም ተጠመቁ፤ የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ ትቀበላላችሁ» አላቸው። ንስሐ በገቡ ቅጽበት ከሞት ወደሕይወት ተሻገሩ ማለት ነው። የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ጸጋ መንፈስ ቅዱስ አደላቸው ማለት ነው። ድኅነት ማለት ይህ ነው። ሐዋርያቱ በሌላ ቦታም «እመን፤ አንተና ቤተሰቦችህ ትድናላችሁ» አላሉምን? የሐዋ ፲፮፤፴፩ ቀስ ብላችሁ ትድናላችሁ አልተባሉም።« እመን ትድናላችሁ!!!  ድኅነት ይህ ነው። ሌላ ዓይነት ድኅነት ካለ ዳንኤልን እንጠይቀዋለን።
እንግዲህ ከላይ እያየን እንደመጣነው መድኃኒት የሚያሻው፤ የታመመ ወይም በሞት ጥላ ስር የወደቀ ክፍል በአንድ ወገን አለ። ከመለኮታዊ ባህርይው ተካፋይ የሆነውንና የእጁን ሥራ፤ ሰውን ልጅ መዳን የሚሻ፤ እንዲሁም ወደቀደመ ክብሩ እንዲመለስ የሚፈልግ የእግዚአብሔር የማዳን ፍቅር በሌላ በኩል አለ። እነዚህ ሁለት ፍላጎቶች ተገናኝተው ደም ፈሶ ይቅርታ መመስረቱን የሚያረጋግጥ የእርቅ ሥርዓት መፈጸም ሊኖርበት የግድ ነው። ይህ የእርቅ፤ የይቅርታ፤ የሰላም፤ የደኅንነትና የዳግም አባትና ልጅነት ኅብረት ውል የተመሠረተው ቀራንዮ በተባለው የራስ ቅል ሥፍራ ነው። ያኔ ሞት ተሻረ፤ በሞት ጥላ ያሉ ህይወትን አገኙ። በጨለማ ለሚሄዱትም ብርሃን ወጣላቸው፤ ሲኦል ተመዘበረች፤ ነፍሳት ተማረኩ፤ የተዘጋው የሰማይ በር ተከፈተ፤ የተባረረው ተመለሰ፤ የልጅነትና የአባት ልማድ እንደቀድሞው ሆነ።     መዳን  ወይም ድኅነት ማለት ይህ ነው።                    
                               ሌላ ታሪክ የለም። የመዳን   ታሪክ ይህ ነው።

በዚህ ድኅነት፤ ሕዝብና አሕዛብ አንድ ሆኑ። የጥል ግድግዳ ፈረሰ፤ ሰው  ያጣው ልጅነት ተመልሶለት የእግዚአብሔር ልጅ ለመባል በቃ። በዚህ የማዳን ሥራ የቀረ፤ የጎደለ፤ የሚጨመር ወይም የሚስተካከልለት አንዳች ነገር የለም።
«እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን» ቆላስ ፩፤፲፫ እንዳለው ሐዋርያው ጳውሎስ።
በዚህ የማዳን ሥራ ሂደት የለም። ጊዜ የለም። የሰው ሥራ የለም። ብቃት ያለው ምትክ ማንም የለም።  የኃጢአትን ሥርየት ሰጥቶ ወደፍቅሩ ልጅ መንግሥት የፈለስነው ቀራንዮ ላይ ደም በፈሰሰ ሰዓት ነው። ሥርየት ምን ጊዜም የደም መፍሰስ ሥርዓት ተከትሎ የሚመጣ ነበርና ይኼው ሲፈጸም ልጆቹ ተባልን። «እንደ ሕጉም ከጥቂቶች በቀር ነገር ሁሉ በደም ይነጻል፥ ደምም ሳይፈስ ስርየት የለም» ዕብ ፱፤ ፳፪ እንደተባለው።

አዳኝ ኢየሱስና መድኃኒት ፈላጊው የሰው ልጅ ቀራንዮ ላይ በደሙ በኩል እርቅ ተፈጽሟል። ይህንን እርቅ የሰው ልጅ የሚቀበለው ወይም አምኖ የሚድንበት እንዴት ነው? 

ለማሳያነት አንድ ነገር እናቅርብ። በዚህ ምድር ላይ ስንኖር በሕይወት ዘመናችን ሕመም  እንደሚያጋጥመን እውነት ነው። የራስ ህመም ቢሰማን ለዚሁ ሕመም ተብሎ የተሠራውን መድኃኒት እንጠቀማለን። ጥርሳችንን ቢያመን ለጥርስ ሕመም ማስታገሻ ወይም መፈወሻ ተብሎ የተመረተውን መድኃኒት በባለሙያ ትእዛዝ መውሰዳችንም አይቀርም። ለሌላም ሕመም እንዲሁ። ለየሕመሞቹ ዓይነት ተብሎ የተሠሩ መድኃኒቶች የሆነ ተለዋጭ ነገር ካላገጣማቸው በቀር እንደመድኃኒት ተቆጥረው ለሥጋ ሕመም ፈውስ ይሰጣሉ። አንዴ ተሠርተው ከወጡ በኋላ ለየበሽታዎቹ ዓይነቶች ከሚውሉ በስተቀር ራሱን የሚታመም ሰው በተገኘ ቁጥር አዲስ ምርት ወደማምረት አይገባም። ፋርማሲ ውስጥ የፈዋሽነት ደረጃቸውን  ይዘው ሕመምተኛውን ይጠባበቃሉ እንጂ  ሕመምተኛ በመጣ ቁጥር አይመረቱም።  በሽተኛ ቢመጣም ባይመጣም መድኃኒቶቹ ተመርተው የሚመጣውን ለመፈወስ ይጠባበቃሉ። ምንም እንኳን ፍጹም የሆነ ማዳንን ባይሰጡም መድኃኒት ተብለው ህመምተኛን ለመፈወስ አንዴ ተመርተው ሁሌ ለሚመጡ ህመምተኞች ይታዘዛሉ።
እንደዚሁ ሁሉ ማዳኑ ሥጋንም ነፍስን፤ ከሞት ጥላና ከጭለማ ሥፍራ ለመታደግ  መድኃኒት የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ የሥርየት ደም አንዴ ቀራንዮ ላይ የቀረበ ስለሆነ መታመሙን አምኖ ለመጣ ሁሉ ነፍሱንም፤ ሥጋውንም ይፈውሳል። ይህ መድኃኒት በበደልና በዐመጽ፤ በኃጢአትና  በውድቀት ውስጥ ላለ ሁሉ የሚያገለግል ዘላለማዊ መድኃኒት ነው። መድኃኒቱ አንዴ ቀርቧል። ለየትኛውም ዓይነት የነፍስና የሥጋ ደዌ ሁሉ የሚታዘዝ አንድ መድኃኒት ነው። ይህ መድኃኒት ፈዋሽነቱ አስተማማኝ ነው። ፈውሱ ሥርየትን፤ ቅድስናንና ልጅነትን ያሰጣል። ይህንን መድኃኒት ለመውሰድ ከታማሚው የሚጠበቀው «ማዳኑ« ፍጹም እንደሆነ ማመን ነው። የቀደመ ማንነቱን ትቶ ከዚህ መድኃኒት ጋር ኅብረት ማድረግ ነው። ምክንያቱም በሽታውን ተናግሮ ይህንን ፈዋሽ መድኃኒት በእምነት የተቀበለ ሁሉ ወደቀደመው ሕመሙ ለመመለስ ፈቃደኛ መሆን የለበትም። ምክንያቱም ይህ መድኃኒት ዘላለማዊ ነው። ይህ መድኃኒት የማይፈውሰው ሕመም የለም። ይህ መድኃኒት ፍቱን መሆኑ የተረጋገጠው የዓለሙን ሁሉ የሕመም ኃጢአት ቀራንዮ ላይ ተሸክሞ በመሞቱ ነው። ማዳኑ ደግሞ እውነት መሆኑ፤ በሞተ በሦስተኛው ቀን ሁሉንም አሸንፎ የኖረው ሞትን ራሱን በማሸነፍ ብቸኛው የሕይወት መድኃኒት ስለሆነ ነው። ስለዚህ ይህ አንዴ ቀራንዮ ላይ ለሕይወታችን የቀረበው የድኅነታችን ዋስትና ነው።  አምነን እንቅረበው ያኔም መዳናችን ፈጥኖ ይከናወናል።
«ኃጢአት አይገዛችሁምና፤ ከጸጋ በታች እንጂ ከሕግ በታች አይደላችሁምና» ሮሜ ፮፤፲፬  ሕግ ባለበት ሞት አለ። ሕግን መፈጸም ቢያቅተን ራሱ ፈጽሞ ከሕግ ሞት ያዳነንን ባመንን ጊዜ ከሕግ ሞት ድነናል ማለት ነው። ድኅነት ይህ ነው። ከሞት የማስጣል፤ የማዳን የመታደግ ተግባር!!  አለቃ ደስታ ምን አሉ?  «መዳን» ማለት መፈወስ፤ መትረፍ፤ ማምለጥ ማለት ነው። እንዳሉት። ያመንን እኛ ድነናል። ከሞት አምልጠናል። ከሞት ተርፈናል። ሕይወት አግኝተናል። በዚህ የክርስትና ጎዳና ላይ ሂደት የሚባል ነገር የለም። ዳንኤል ግን እስካሁን አልዳነም፤ የሚድነው በሂደት ነው። መዳኑን መቼ እንደሚያረጋግጥ የሚያውቀው እሱ ብቻ ነው። ወንጌል ግን ድኅነት ያልሆነለት ሰው ያለው ሞት ውስጥ መሆኑን ይነግረናል። የዳኑ ሰዎች ግን በሕይወት ውስጥ አሉ።
«ጻድቁ ከጽድቁ ቢመለስ፥ ኃጢአትንም በሠራ ጊዜ፥ በዚያም ቢሞት፥ እርሱ ባደረገው በደል ይሞታል። ኃጢአተኛውም ከሠራው ኃጢአት ቢመለስ ፍርድንና ቅን ነገርንም ቢያደርግ ነፍሱን ይጠብቃል» ሕዝ ፲፰-፳፮-፳፯ የሚል ቃል አለና። ስለዚህ ድነትም ሆነ ፍርድ ቅጽበት እንጂ ሂደት አይደለም እንላለን። ኃጢአትን ሲሰራ ወደፍርድ ገብቷል፤ ያኔውኑ ቢሞት ፍርድ ይጠብቀዋል። ኃጢአቱን ተናዞ ፅድቅን ቢፈጽም እሱም ሕይወትን አግኝቷል። በዚህ መኻከል ሌላ የማቆያ መንገድ የለም።

እንግዲህ ታማሚ፤ አዳኝና ድኅነት ምን እንደሚመስል ለማሳየት እንደሞከርነው ሁሉ ይህ «ድኅነት» ላመኑ ሰዎች የሚሆንላቸውና ሕይወታቸውን የሚቀይረው በሂደት ነው ወይስ በቅጽበት? የሚለውን በቀጣይነት እንመልከት።

የሰው ልጅ ምድራዊ መድኃኒት ታማሚውን ለማዳን ጊዜ ሊወስድ ይችላል። ለዚያውም አስተማማኝ አይደለም። ይሁን እንጂ ሰማያዊው መድኃኒት እንደዚያ አይደለም። ያመነ ሰው የሚድነው ባመነበት ቅጽበት እንጂ በሂደት አይደለም። ሰማያዊና አስተማማኝ መድኃኒት/ኢየሱስ/ ወደ ምድር የመጣው ምድራዊ ተላኪ ሰዎች በዚህ ምድር ስላልነበሩ አይደለም። ፍጹም ድኅነት ማሰጠት ስለማይችሉ ብቻ ነበር። ቀደምት ካህናቱ ብዙ የሥርየት ደም አፍስሰዋል። ፍጹም የሆነ ድኅነትን ማስገኘት ባይችል ጊዜያዊ ሥርየትን እንኳን ማስገኘት የሚችለው ለኃጢአተኛው  በጸለዩበት ሰዓት ወዲያኑ እንጂ በሂደት አልነበረም።
«ካህኑም ስለ ሠራው ኃጢአት በእግዚአብሔር ፊት በበደል መሥዋዕት በግ ያስተሰርይለታል የሠራውም ኃጢአት ይቀርለታል» ዘሌ ፲፱፤፳፪
ምድራዊው መስዋእት ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚችል ኃይል ከነበረው ሰማያዊውማ እንደምን የበለጠ አይሆን? አዎ የቀራንዮው መድኃኒት በእሱ ላመኑ ወዲያውኑ የእግዚአብሔርን ልጅነት ማሰጠት ይችላል። ይህም ከመድኃኔ ዓለም ስጦታ እንጂ ከእኛ ብቃት ወይም ሥራ አይደለም።
«እንደ ምሕረቱ መጠን ለአዲስ ልደት በሚሆነው መታጠብና በመንፈስ ቅዱስ በመታደስ አዳነን እንጂ፥ እኛ ስላደረግነው በጽድቅ ስለ ነበረው ሥራ አይደለም» ቲቶ ፫፤፭
ሌላ ምሳሌ እናቅርብ።  በሥጋቸው ከዘር የወለዱን እናትና አባት አሉን።  ለእነዚህ ምድራዊ እናትና አባት ልጆች የተባልነው በሂደት እየተረጋገጠና እንቅስቃሴያችን በሥራ እየተመዘነ አይደለም። በተወለድንበት  ቅጽበት እኛ ልጆቻቸው ሆነናል። ማንም ወላጅ  ልጁን ልጄ የሚለው በሂደት  አይደለም።  
እግዚአብሔር አብም፤ አንድያ ልጁ በሆነው በኢየሱስ ሞት በሕይወት እንኖር ዘንድ የወለደን ወዲያው ልጆቹ እንድንሆን እንጂ ይኼ ብቁ ነው፤ ይሄ አይደለም እያለ ሥራችንን እየመዘነና እየለካ አይደለም። እንደዚያማ ከሆነ እግዚአብሔር ፍቅር ነው የሚባልለት ባህርይው ወዴት አለ ? ጥንተ ጠላታችን ግን ዛሬም እኛ ያመንን ሁላችን ወዲያውኑ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን የድኅነት ጸጋ ማግኘት እንደማንችልና ሂደት እንደሚያስፈልገን በክፋቱ ሊያሞኘን ይፈልጋል። እኛ ግን ከማይታበለው ቃል ማዳን እንደሆነልንና ባመንን ቅጽበት ልጆቹ የመሆንን ብቃት እንደሰጠን  እናምናለን።
«ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው» ዮሐ ፩፤፲፪ እንዳለው።
መዳን በእምነት የሚቀበሉት ጸጋ እንጂ በሂደት የሚያረጋግጡት የፈተና ውጤት አይደለም። ድኅነት በክርስቶስ ሞት  እንዲያው የተሰጠን የእግዚአብሔር ስጦታ እንጂ በሥራ የምናገኘው የብቃታችንን መገለጫ አይደለም። ድኅነት ማግኘቱን ያላመነ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ የመሆንን ስጦታ ለመቀበል ያልፈለገ ነው።
«እርሱንም ሳታዩት ትወዱታላችሁ፤ አሁንም ምንም ባታዩት በእርሱ አምናችሁ፥ የእምነታችሁን ፍፃሜ እርሱም የነፍሳችሁን መዳን እየተቀበላችሁ፥ በማይነገርና ክብር በሞላበት ሐሤት ደስ ይላችኋል» ፩ኛ ጴጥ ፩-፰-፱ የተባልነው ለምንድነው? የነፍሳችንን መዳን ካላመንን እንዴት በኢየሱስ አዳኝነት ማመን ይቻላል? ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳዳነን ባመንን ጊዜ ነፍሳችንም በእሱ ሞት እንደዳነች አምነናል ማለት ነው።
ዳንኤል ክብረት ግን፤ ሳናየው በወደድነውና፤ የተነገረንን አምነን በተቀበልነው፤ የእምነታችን ፍጻሜ የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስ የማዳን ስጦታ  በሂደት የሚረጋገጥ እንጂ በቅጽበት የሚገኝ አይደለም ይለናል።
መዳን ማለት ከኃጢአትና ኃጢአት ከሚያስከትለው ሞት ማምለጥ ማለት ነው። ሰው ኃጢአቱን በተናዘዛትና በመድኃኒቱ ሕያው ድነት ባመነባት ሰዓት ከዚህ ሞት ይድናል። የድኅነት ተቃራኒው ሞት ነው። ሰው ወይ ሞትን ይመርጣል አለያም ወደዘላለማዊ ድኅነት ይመጣል። በነዚህ መካከል ቅጽበት እንጂ ሂደት የለም።  ሰው ለሁለት ጌቶች መገዛት ወይም ከኃጢአት ጌታ ለመላቀቅ ሂደት መጠበቅ የለበትም። አንዱን ይወዳል ወይም ሁለተኛውን ይጠላል እንዳለው ባለቤቱ ራሱ።

ድኅነት ቅጽበት ከሆነ ሰው መዳኑን የሚጠብቀው እንዴት ነው?

ሰው ኃጢአቱንና ዐመጻውን በንስሐ አራግፎ ወደእግዚአብሔር ልጅነት ከተቀላቀለ በኋላ በሕይወቱ ሁሉ መኖር ያለበት እንደአባቱ ፈቃድ ነው እንጂ እንደልቡ ፈቃድ አይደለም። በሉቃስ ፲፭ ላይ እንደተጠቀሰው ከአባቱ ንብረት ላይ ድርሻውን ተካፍሎ ሲዘልበትና ሲጨፍርበት ኖሮ የተመለሰው ልጅ ይከተል የነበረው የአባቱን ፈቃድ ሳይሆን የልቡን ፈቃድ ነበር። የልቡ ፈቃድ መጨረሻው ኪሳራና የልጅነት መብትን ማጣት ማስከተሉን እናያለን። በራሱ ላይ ሲመሰክርም እንደ ልጅ ሳይሆን ከባሪያዎችህ እንደአንዱ ብሆን ሲል ተመኘ። ይህ ሁሉ የአባቱ የሆነው ሁሉ የራሱም ሆኖ ሳለ እሱ የራሱን ድርሻ አሳንሶ ለጥፋት በማዋሉ የመጣ ጥፋት ነው። እንደዚሁ ሁሉ ድኅነት/መዳን/ የተደረገለት ማንም ክርስቲያን የልጅነት ጸጋ በሰጠው በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ የመኖር ኃላፊነት ይጠብቀዋል። አልፈልግም ማለት መብቱ ቢሆንም ውጤቱ መጥፎ ነው።
«የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና» ዕብ ፫፤፲፬
ስለዚህ በእምነት የነገረ ድኅነቱ ተካፋዮች የሆንን እኛ የቤቱ ልጆች ሆነን ክብሩን እንካፈል ዘንድ ባገኘነው ድኅነት ላይ ጸንተን መቆየት የግድ ይሆናል። ትእዛዛቱን የምንጠብቀው አባታችንን ለመውደዳችን ማረጋገጫዎች ስለሆኑ ነው።
«ወዳጆች ሆይ፥ ስለምንካፈለው ስለ መዳናችን ልጽፍላችሁ እጅግ ተግቼ ሳለሁ፥ ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ» ይሁዳ ፩፤፫
አንድ ጊዜ በክርስቶስ ኢየሱስ ለቅዱሳን በተሰጠችው ሃይማኖት እየተጋደልን የምንቆየው በደሙ ስለዳንንና ይህንን ክቡር የድኅነት ስጦታ ለማስጠበቅ እንጂ  ገና ለመዳን አይደለም። ለድኅነትማ ከሆነ የሚያበቃ ምንም ሥራ አልነበረንም።
«ያዳነን በቅዱስም አጠራር የጠራን እግዚአብሔር ነውና፥ ይህም እንደ ራሱ አሳብና ጸጋ መጠን ነው እንጂ እንደ ሥራችን መጠን አይደለም፤ ይህም ጸጋ ከዘላለም ዘመናት በፊት በክርስቶስ ኢየሱስ ተሰጠን» ፪ኛ ጢሞ ፩፤፱
በእምነት የዳነ ሰው ደግሞ እምነቱን በሥራ ይገልጣል። በሥራ ድኅነት የሚገኝ ቢሆን ኖሮ ስንት መልካም ሥራ ያላቸው ሕዝቦች በዓለም ላይ ከእኛ የበለጡ ነበሩ። ዛሬም አሉ። በደሙ መዳናቸውን ስለማያውቁ ሥራቸው ብቻውን ድኅነት አያስገኝላቸውም። እኛ ግን ማዳኑን እንደፈጸመልን፤ ስለእኛ እንደሞተልን የምናምነው ሊቀ ካህን ስላለን የሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች መሆናችንን እንመሰክራለን። ሐዋርያውም በመልእክቱ እንዲህ ሲል ያበረታታናል።
 «ያን መንፈስም፥ በጸጋው ጸድቀን በዘላለም ሕይወት ተስፋ ወራሾች እንድንሆን፥ በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በእኛ ላይ አትርፎ አፈሰሰው» ቲቶ ፫፤፮
 በጉንፋን የተዘ ሰው ጉንፋን እንዳይዘው የሚያደርገው ጥንቃቄ ምንም አይጠቅመውም። ጥንቃቄው ጠቃሚ ይሆን የነበረው በጉንፋን ከመያዙ በፊት ነበር። ከተያዘ በኋላ ግን ከበሽታው የሚፈውሰውን መድኃኒት መፈለግ ይኖርበታል። መድኃኒት አግኝቶ ከዳነ በኋላ ግን ላለመያዝ መጠንቀቅ ይገባዋል። «ታሞ ከመማቀቅ አስቀድሞ መጠንቀቅ» የሚባለውስ ለዚህ አይደለም?
እንደዚሁ ሁሉ በኃጢአት የተያዘ ሰው ቅድሚያ የሚያስፈልገው ከኃጢአት ደዌ መዳን ነው። ከኃጢአቱ ደዌ ከዳነ በኋላ በዚህ በሽታ ዳግመኛ እንዳይለከፍ መጠንቀቅ የሚገባው ከዚህ የሞት በሽታ ራሱን በመጠበቅ ነው። እንዴት መጠበቅ እንደሚገባው ደግሞ ከኃጢአት በሽታ ለዳኑ ሁሉ የተጻፈ የሕይወት መመሪያ ቅዱስ ወንጌል አለ። የኃጢአት በሽታ እንዴት እንደሚተላለፍና እንዴትስ መጠንቀቅ እንዳለብን በሰፊው ተቀምጧል። ያንን ዕለት ዕለት እየመረመረ ራሱን በእግዚአብሔር ቃል የሚያክም  ክርስቲያን ይሆናል።
ከኃጢአት በሽታ ለመዳን ግን ጊዜን የሚጠብቅ ከሆነ እሱ ችግር አለበት። ድኅነት ምን እንደሆነ ገና አልገባውም። ክርስቲያናዊ ምግባርን የሚሰራው ጤናማ እንጂ በሽተኛ አይደለም። ምግባሩ ከበሽታ የመዳኑ ምልክት እንጂ ከበሽታ የመፈወሻ መንገድ ሊሆን አይችልም። የሰው ልጅ ሥራ የኃጢአትን በሽታ የመፈወስ ብቃት የለውምና አደገኛ አስተሳሰብ ነው። ፈውስ በአንዱ በእግዚአብሔር በማመንና ኃጢአትን በመጥላት የሚገኝ የነጻ ስጦታ ጸጋ ነው።  ዮሐንስ ወንጌላዊ የሚለውም ይህንኑ ነው።
«በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል »ዮሐ ፫፤፲፰
«ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ» ዕብ ፫፤፩
ማጠቃለያ፤
ከላይ እያየን እንደመጣነው ሁሉ በጥብቅ ልንመለከተው የሚገባን ነገር «ድኅነት» የሚሰጠው በመድኃኒቱ ላመኑ ሁሉ ወዲያው እንጂ በሂደት አይደለም። ሐዋርያቱም «እመኑ፤ ተጠመቁ ትድናላችሁ» አሉ እንጂ ጠብቁ፤ ማረጋገጫውን ለማግኘት ጊዜ ያስፈልጋል አላሉም። ምድራዊ አባት ልጁን የሚቀበለው በተወለደ ሰዓት እንጂ በሂደት እያረጋገጠ አይደለም። የእኛ ሰማያዊ አባታችንም አባትነቱን አምነን፤ ኃጢአትን በተውን ቅጽበት እንጂ አንተ ቆይ፤ አንተ ግባ እያለ የሚያዳላ አባት አይደለም። ለሕዝብና አሕዛብ የተደረገው ጥሪ ይህ ነው። የመዳናችን መገለጫ ምግባር ግን ሂደት ነው። ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ ተብለናልና።
ከዚያ ውጪ ድኅነት ሂደት ነው የሚለው የዳንኤል ስብከት ኑፋቄና እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በእምነት እንዲቀበሉ የሰጠውን ትልቁን ስጦታ ማስጣል ይሆናል። ድኅነትን ካልተቀበሉ ልጅነት አይሰጥም። ድኅነት ከሌለ የክብሩ ተካፋይነት የለም። እርሱ ደርሶ ባያድነን ኖሮ ሥራችን የመርገም ጨርቅ ነበር።
«ሁላችን እንደ ርኩስ ሰው ሆነናል፥ ጽድቃችንም ሁሉ እንደ መርገም ጨርቅ ነው ሁላችንም እንደ ቅጠል ረግፈናል፥ በደላችንም እንደ ነፋስ ወስዶናል» ኢሳ ፷፬፤፮
--------------------------------------------