በአካፋ የሚዛቀውን ሳይጨምር የ71 ሺህ ብር የወር ደመወዝተኛ ሐዋርያ/ፓስተር/ በኢትዮጵያ? ይቺ ናት ጫወታ!!


በእንግሊዝኛ የአማርኛው ስም «ቸርች» ተብለው ከሚጠሩት ባንዱ የተፈጸመ ድርጊትና እሮሮ ነው።  ምሬት የበዛበት ይህ ሰው «ሐዋርያዬ» በሚለው የዘመኑ ሰው የደረሰበትን ሰቆቃ ሲያሰማ አገኘነውና ራሳቸውን የክርስቶስ ባለሟል አድርገው እውቀት የጎደለውን ሰብስበው እንዴት እንደሚያጃጅሉ ከማሳየቱም በላይ በግራም በቀኝም በክርስቶስ ስም የሚፈጸመውን ዐመጻ ልናካፍላችሁ ወደድን። በወዲህ ሰባኬ ወንጌልና ማኅበር፤ በወዲያ ደግሞ ሐዋርያና ፓስተር ገንዘብ አምላካቸውን ይነግዳሉ።  ከረጅሙ ትርክት ውስጥ ቆንጥረን አቀረብን።
የጽሁፉ ባለቤት ኢዮብ ደምሴ ነው።
ይሄን ጽሑፍ ለምታነቡ ወገኖች ልጠይቅ የምፈልገው ነገር፣
1ኛ. “መልሱኝ” ብዬ ያልጠየቅሁና በብዙ ውትወታና ንግግር ቤተ ክርስቲያን ጥሪ ያደረገችልኝ ሆኖ ሳለ፣
2ኛ. በቤተ ክርስቲያኒቱን ባገለገልኩበት ጊዜ ሁሉ በትጋት በማገልገሌ ውጤታማና ፍሬያማ መሆኔ በራሱ በሐዋርያው እጅ በምስጋና የተጻፈ ያማረ የመሸኛ ደብዳቤ ተሰጥቶኝ እያለ፣
3ኛ. የእረኞች አለቃ የሆነው ጌታ “ጠብቁልኝ” ያለውን መንጋ “ምስጢሩን አያውቅም” በሚል እሳቤ ብቻ፣ በሐሰት ንግግር በማሳሳት ለተሳሳተ ዓላማ እንዲሰለፉ እንዳደረገው ሳይሆን፣ መንጋው እንዳያዝንና እንዳይበተን፣ በመጠንቀቅ ከቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ካቆምኩበት ጊዜ ጀምሮ ራሱን በአደባባይ እስከገለጠበት ጊዜ ድረስ የማውቀውን የሐዋርያውን ችግር በአመራር ክፍሉ ብቻ እንዲያልቅ በምስጢር ይዤ የቆየሁ መሆኔ እየታወቀ፣
4ኛ. እግዚአብሔር ሰፊ የአገልግሎት በር ከፍቶልኝ ከጌታ ምሕረት የተነሳ ተቀባይነትም ባገኘሁበት ጊዜ የተበላሸውንና የፈረሰውን ነገር መልሶ ለመገንባቱ ሥራ ራሴን መስጠቴ ስሕተቱ ምንድን ነው?

እንግዲህ እውነታው እንዲህ ከሆነ የእኔ መመለስ ለምንድን ነው ሐዋርያውን የሚያስደነግጠው? “ጥሩ ሠርቷል” በማለት የምስጋና ደብዳቤ በገዛ እጁ ፈርሞ ከሰጠኝና በምንም ነገር ያልተከሰስኩኝ ከሆነ፣ በጸጋው የሚጠቅም እውነተኛ አገልጋይና ጠንካራ ሠራተኛ ሲመጣለት ደስ ሊለው ይገባው ነበር፡፡ ሌላው ቢቀር ወደ ቤተ ክርስቲያኒቱ የምመጣው አካሉን ለመጥቀም ጸጋ ወደ ሰጠኝ ወደ እግዚአብሔር ቤት (ቤተ ክርስቲያን) እንጂ ወደ ሐዋርያው የግል መኖሪያ ቤት አይደለም፡፡ ጌታ አገልጋዮችን የሰጠው ለቤተ ክርስቲያን መታነጽ (ኤፌ. 4፥11) እንጂ ቤተ ክርስቲያንን የአንድ ሰው የግል ንብረት እንድትሆንና ማንማ የወደደውን እንዲያደርግባት አይደለም፡፡
ዳግም የተወለደ ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነጻነት የመኖር፣ የመናገርና የማገልገል መብት አለው፡፡ ታዲያ በቤተ ክርስቲያን በር ላይ ቆመን፣ “አንተ ግባ፤ አንተ ደግሞ አትግባ”፣ “የባለራእዩ ወዳጅ ነህ ወይስ ጠላት?” እንድንል ማነው መበት የሰጠን? እንዲያውም ሁለት ያልተግባቡ ሰዎች አብረው የሚቀመጡበትና የሚዳኙበት ቦታ የእግዚአብሔር ቤት ነው፡፡ ጤነኛ ባልሆነ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን የከፈተ ባለ ዕዳ ይቅርና ሐዋርያው ጳውሎስ እንኳ በመሠረታት የቆሮንቶስ ቤተ ክርስቲያን በተሳሳተ መንገድ ተከስሶ በነበረ ጊዜ፣ “በሐዋሪያዊ ሥልጣኔ ሽሬአችኋለሁ” አላለም፤ ለተጠየቀው ጥያቄ በአግባቡ መልስ ሰጠ እንጂ (1ቆሮ. 9፥1)፡፡
ይህ ሁሉ ጉዳይ መንፈሳዊ ሕይወታችን ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ያመለክታል፡፡ ይህ እንዲህ ከሆነ በአመራር ክፍሉ እና በሐዋርያው መካከል የተፈጠረው አለመግባባት መንሥኤው ምን ይሆን ታዲያ? ዋናው ምስጢር ከዚህ በኋላ የምጽፈው ሲሆን፣ ሌላው ሁሉ እንደ ማደናገሪያ ነው፡፡
IV.  በአመራር ክፍሉና በሐዋርያው መካከል አለመግባባትን እያባባሱ የመጡ እውነተኛ ጉዳዮች የሚከተሉት ናቸው፡-
1. ሐዋሪያው ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ብክነት በቤተ ክርስትያኒቱ ላይ እያስከተለ ባለበት ጉዳይ ቦርዱ የማያዳግም የእርምት እርምጃ በመወሰዱ ፣
1.1.  ሐዋሪያው በወር 71,500.00 (ሰባ አንድ ሺህ አምስት መቶ) ብር ደሞዝ ስለሚያገኝ፣
1.2.  በውጭ አገር በሚቆይበት ጊዜ በቀን 250 ዶላር የቀን አበል ይከፈለው የነበረ ሲሆን፣ ይህም በዓመት ከ600 መቶ ሺህ ብር ያላነሰ ይሆናል፡፡
1.3.  በአማካይ 800 መቶ ሺ ብር ከሆነው የቤተ ከርስቲያኒቱ ወርሃዊ ገቢ 10 በመቶ ይወስድ ነበር፤ ይሄም በዓመት ወደ 960 ሺህ ብር ማለት ነው፡፡ ይህ የተፈቀደው እርዳታ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እርሱ እንዲያዝበት ሆኖ ሳለ ሙሉ በሙሉ ለግል ጥቅሙ በማዋሉ በዚህ አቅጣጫ ምሳሌነቱን አጥቷል፤
1.4.  ብቻውንም ሆነ ሰው ጨምሮ በዓመት ውስጥ በመደበኛነት 4 ጊዜ አሜሪካ፣ በተጨማሪም ወደ አውሮፓና ወደ ሌላም ሀገር ልዩ ጉዞ ሲያደርግ ሙሉ ለሙሉ የአውሮፕላን ትኬት ወጪውን የምትሸፍነው ይህችው ቤተ ክርስቲያን ነበረች፤
1.5.  የቤት ኪራይ፣ የመብራት፣ የውሃ፣ የመኪና ሰርቪስ፣ የስልክ ወዘተ የመሳሰሉት ወርሃዊ የግል ወጪዎቹ ከቤተ ክርስቲያኒቱ ካዝና ይሸፈን ነበር፡፡
ይህ ችግር ቤተ ክርስቲያኒቱን የራሷ ንብረት እንዳይኖራት ከማድረጉም ባሻገር በዕለት ተዕለት ሥራዋ ላይ ጫና እየፈጠረ በመምጣቱ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ቦርዱ ከወርሃዊ ደሞዙ በቀር ሌሎቹን አቁሞበታል፡፡ ይህ ከተደረገ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ቤተ ክርስቲያኒቱ የነበራት የገንዘብ እጥረት ተወግዶ የራሷን ቦታ ለመግዛት በድርድር ላይ ትገኛለች፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብም በካዝና እንዲኖራት ሆኗል፡፡ እጅግ አነስተኛ የነበረው የሠራተኞችና የአገልጋዮች ደሞዝም ከነበረበት 2 እና 3 እጥፍ አድጎ ኑሮን ከመለወጥ ባሻገር የሥራና የአገልግሎት ተነሣሽነትን አስገኝቷል፡፡ የናዝሬትና የሻሸመኔ አጥቢያዎችም የራሳቸው የማምለኪያ ቤት እንዲሠሩ ዋናው ቢሮ ከፍተኛ እገዛ ከማድረጉም ባሻገር ብዙዎቹን አጥቢያዎች በገንዘብ ለመደጐም ተችሏል፡፡ 
2. በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም ከሀገር ውጭ የሚሰበሰብ ገንዘብን በተመለከተ
ሐዋርያው በአሜሪካ ለወንጌል ሥራ ገንዘብ የማሰባሰብ ኮንፈረንሶች በዓመት ሁለት ጊዜ የሚያዘጋጅ መሆኑ ይታወቃል፤ በኤልሻዳይ ቲቪ የወንጌል ብርሃን ቤ/ክ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ሲተላለፍም ዕርዳታ ለማድረግ ለሚፈልጉ የሚቀርበው አድራሻ የአዲስ አበባዋ ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን፣ በአሜሪካ ያለው አድራሻ በመሆኑ በዚህ ዝግጅት ላይ ቤተ ክርስቲያን ተጠቃሚ አይደለችም፡፡ ይህን አካሄድ እንዲመረምርና የአሠራር ግልጽነት እንዲኖረው መጠየቁ፣ በአሜሪካ አለች የምትባለዋ የወንጌል ብርሃን ቤተ ክርስቲያንም ምንም ዐይነት ዕውቅና በዋናው ቢሮ እንደሌላት አስረግጦ መነገሩ፣
3. በቤተ ክርስቲያኒቱ ካልታወቀ ቡድን ጋር ያደረገው ኅብረት
በአሁን ወቅት መቀመጫውን በአሜሪካ ባደረገውና በከፍተኛ ደረጃ በመንቀሳቀስ ላይ ባለው  “Charismatic Dominion” ተብሎ ለሚጠራው እንቅስቃሴ ያለ ቤተ ክርስቲያኒቱ ዕውቅና የኢትዮጵያ ተወካይ ሆኖ ከመገኘቱ በተጨማሪ ቤተ ክርስቲያኒቱንም የዚያ ኢመጽሐፍ ቅዱሳዊ እንቅስቃሴ አጋር አድርጐ መገኘቱ በአመራር ክፍሉ መካከል ከፍተኛ ድንጋጤ ፈጥሮአል፡፡ ይህ እንቅስቃሴ ከቤተ ክርስቲያኒቱ መሠረተ እምነት ጋር ካለመጣጣሙም ባሻገር ቤተ ክርስቲያንንም ከመንግሥት ጋር የሚያጋጭ አካሄድ የሚከተል በመሆኑ በዚህ አቅጣጫ በቀረበበት ማስረጃ የምስክርነት ቃሉን በጽሑፍ እንዲሰጥ መጠየቁ፣
4.  የሥነ ምግበር ጉድለት
ሐዋርያው በሥነ ምግባር ጉድለትና በሞራል ችግር ውስጥ እንዳለ የሚያሳዩ መረጃዎች ለአመራር ክፍሉ እየደረሱት በመሆኑ፣ በዚህ አቅጣጫ በቀረበበት ክስ በቂ መልስ እንዲሰጥ መጠየቁና የማጣራት ሥራው ተጠናክሮ የቀጠለ መሆኑ፣
5.  ማበላለጥ
የክርስቶስ ቤተሰብ የሆኑትን ሁሉ ያለ ማበላለጥ እንዲያገለግል መመከሩም አንደኛው የልዩነት ነጥብ ነው፡፡ ሐዋርያው በሚኖረው የማማከርና የጸሎት አገልግሎት ወቅት ተጠቃሚ የሚሆኑት በኑሮ ደረጃቸው ሻል ያሉት ናቸው፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት፣ “ወደ ጉባኤ መምጣት የሚከብዳቸው ሀብታሞችን ለይቼ ለማስተማር ስለምፈልግ በደንበል ሲቲ ሴንተር ለዚህ አገልግሎት ቤት ተከራዩልኝ” ብሎ ጥያቄ በማቅረቡ፣ “ይህ ከአንተ አይጠበቅም፡፡ ይልቁኑ አገልጋዮችን ብታስተምርና አብረሃቸው ጊዜ ብታጠፋ በብዙ ፍሬያማ ያደርግሃል” ተብሎ ሲመከር ሰምቻለሁ፡፡
እነዚህ ከላይ የተዘረዘሩት የሐዋርያው ዳንኤል መኮንንን ከፍተኛ የሕይወት ምስቅልቅሎሽ ከ3ኛው ተራ ቁጥር በስተቀር የቤተ ክርስቲያኒቱ ከፍተኛ አመራር የሆኑ ሁሉ የሚያውቁትና ለረጅም ጊዜ ያማጡበት ነበር፡፡ ችግሮቹ እኔም ከመጣሁ በኋላ እንኳን የቤተ ክርስቲያኒቱን ዕድገት አንቀው በመያዝ ንጹሑን የእግዚአብሔር ሥራ ለመሥራት በማነቆነት ያስቸግረን እንደ ነበር ዐውቃለሁ፡፡
የአመራር ክፍሉ ለዚህ ችግር በቀላሉ መፍትሔ መስጠት የከበደው መንጋው የሐዋርያው ዳንኤልን ትክክለኛ ማንነት ባለመረዳቱ ሲሆን፣ እርሱም ከዚህ ስህተቱ ተጸጸቶ ላለመመለስና የቀናውን የጌታን መንገድ ላለመከተል ወስኖ በድፍረት የቀጠለው በሕዝቡ ዘንድ ያለውን ተቀባይነት ግምት ውስጥ በማስገባቱ ይመስለኛል፡፡ “በሕዝቡ እንዳትወገዙ፤ እኔ መሥራችና ባለ ራዕይ ነኝ፤ የማይገሰስ አይነኬ ሥልጣን አለኝ” ይል ነበር፡፡ ከ90% በላይ አስተምህሮቶቹ ብሉይ ኪዳንን መሠረት በማድረጋቸውና “የተቀባውን መንካት ያስቀስፋል፤ ያስረግማል” የሚል የፍርሃት መንፈስ በማያስተውሉ ምእመናን ላይ ስለ ተነዛ፣ የቅዱሳን አዲስ ኪዳናዊው የልጅነት ሥልጣን ተሸፍኗል፡፡ ስለዚህም ሕዝቡን ማንቃት እጅግ አድካሚ ሆኗል፡፡ እኔ እስከማውቀውና አብሬ እስከ ነበርኩበት ጊዜ ድረስ የድሮ ዝናውን እንደ ማንም ሰው በወሬ ብሰማም ቀርቤ እንዳየሁት የአሁኑን ሐዋርያ በትጋት የአመራሩ ክፍሉ በብዙ ሲበልጠው አይቻለሁ፡፡
የቦርድ አባላቱ ችግሩን ለመፍታት ሐዋርያውን፣ “በጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ እንኳን ቅር ከተሰኘህ የቆዩ መንፈሳዊ አባቶች በጉዳዩ ላይ ይግቡበት፤ መንጋው በዚህ ምክንያት አይረበሽ” ሲሉት ከዚህ ይልቅ በምድራዊ ሕግ ልዳኝ ያለውና ክስ ያቀረበው እርሱ መሆኑ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው፤ ሕጉ ለማን እንደሚፈርድ ባይታወቅም፡፡ ሰው ከጸጋ ሲጐድል በሕግ መዳኘቱ አይቀርም፡፡
ጊዜው እግዚአብሔር ቤቱን ለማጥራት የተነሣበት ይመስለኛል፡፡ ብዙ ጸልየን፣ ክብሩን ተጠምተንና ተሐድሶ እንዲመጣ ብዙ ተናግረን ይሆናል፡፡ ታዲያ በተለይ ስለ ንስሓና ተሐድሶ በብዙ የነገሩንና ያስተማሩን መሪዎቻችን ከስህተታቸው ንሰሓ በመግባት ምሳሌ ቢሆኑን ምናለ?! ያለ ሕይወት ንጽሕና ስለ እግዚአብሔር ክብር፣ ስለ መገለጥ ተራራ፣ ስለ ቅባት ዐይነት፣ ስለ ሐዋርያነት ትልቅነት ከሚነግሩን፣ ክርስቶስን ኖረው ቢያሳዩን የተሻለ ይሆን ነበር፤ ጥሩ ምግብ ቤት ብዙ ማስታወቂያ አያስፈልገውምና፡፡
በሐዋርያው ዳንኤል ላይ በተነሣው ክስና “ንስሓ ግባ” በመባሉ አንዳንድ ወገኖች ተደናግጠው እምነታቸው ጥያቄ ላይ ወድቋል፤ ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለአገልጋይ በጐ ኅሊና አጥተዋል፡፡ አንዳንዶች “እርሱን የነካ፣ የዐይኔን ብሌን የነካ ነው” በሚል የእርሱ ጠላቶች ናቸው ብለው የገመቷቸውን ለመደብደብ እስከ መጋበዝ ደርሰዋል፤ አጸያፊና ከክርስቲያን የማይጠበቅ ስድብን የሚሳደቡም አሉ፡፡ ይህ ጊዜ እንደ መሪ፣ “የሚከተለን ሕዝብ ምን ያህል ጌታን ያውቃል? ምንስ ያህል መንፈሳዊ ነው?” ለሚለው ጥያቄ መልስ ለማግኘት ወርቃማ ጊዜ ይመስለኛል፡፡ “ሸክም አለን፤ ለሕዝቡ ተጠርተናል” የሚሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮችም ትልቁ ሥራቸው ዕርቅና ሰላም የሚመጣበትን በመፈለግና ግራ ቀኙን የማያውቀውን መንጋ በማረጋጋት ሁሉን ጊዜ እስኪገልጠው በጸሎት እንዲቆይ ማድረግ፣ ከዚህ ካለፈም ለእውነት መቆም እንጂ የግለሰብ ቲፎዞ (ሎሌ) መሆን አይደለም፡፡ ነገሩ ሲስተካከልና ሥርዐት ሲይዝ በመንጋውም ሆነ በመሪዎች ፊት እንዳንቀልና ጥሪያችን ጥያቄ ውስጥ እንዳይገባ ሁላችንም መጠንቀቅ ያስፈልገናል፡፡
የትኛውም አገልጋይ ሊደክምና ሊስት እንደሚችል፣ በምንም ዐይነት ቅባት የተቀባ ልዩ መንፈሳዊ የሆነ ቢመስል እንኳ ለጌታ ትእዛዝ መጠንቀቅ እንዳለበት ቅዱሱ ቃል ይናገራል (1ቆሮ. 14፥37)፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልኩ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ” ካለ (1ቆሮ. 9፥27) ታዲያ ጭንቁ ምንድን ነው?
ይልቁኑ አንድ ቁም ነገር ልናገር፤ ቤተ ክርስቲያን የክርስቶስ ናት! መሠረቷም፤ ድምድማቷም እርሱ ራሱ ነው! መመሪያዋም የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ የእኛም እምነት የተመሠረተው በዚሁ ጌታ ላይ ከሆነ ምን ይረብሸናል? ሐዋርያው ዳንኤል መኮንንን የምንወድ ሁሉ እንደ እግዚአብሔር ቃል በንጽሕና እንዲኖር እንርዳው እንጂ የድርጊቱ ተባባሪ አንሁን! በጌታ ቀን ለእያንዳንዱ መልስ እንሰጣለን፡፡ በዚህም ላይ ቤተ ክርስቲያን በመልካም ሥርዐት የማይሄዱትን ቅዱሳን የማረም፣ የመገሠጽና ካልተመለሱም ከኅብረቱ የማስወገድ መብት አላት፡፡ ሐዋርያ ዳንኤል በመድረክ ያደረገውን ንግግርና የተሠራውን ድራማ ስመለከት የተማርኩት ነገር፣ ሰው ያለ እግዚአብሔር ምስኪን መሆኑን ነው፡፡ ለካ ጸጋ ሲጐድለን የምንሠራውን አናውቅም!
ጌታ እግዚአብሔር ሆይ ፍጻሜዬ እንደ ጅማሬዬ ያማረ ይሁንልኝ፡፡ አሜን!
Share this article :

+ የተሰጡ አስተያየቶች + 3 የተሰጡ አስተያየቶች

Anonymous
April 28, 2013 at 9:21 AM

bewnet deje brhan lebetkrstyan lek end freepreess eyagelegelachihu new neger gn gena orthodoxn kemewkesachihu befit bizu neger matnat yitebekbachihoal mn yahl yene policarpes,awgstinos,jhon chrystom,...etc mesthafochn lemanbeb(the one in english not in amharic)tret adrgachihol mn yahls ahun kalu western theologians,eastern not oriental)anetsasrachihual mn yahles tanebalachihu weys good amharic books lay kalut mesthafoch wuch manbeb afelgum

April 29, 2013 at 3:50 PM

በመጀመሪያ ስለምታወሩት ነገር አስቡ፡፡ እናንተ እራሳችሁ የየትኛው ቤ/ክ አባል እንደሆናችሁና የትኛውን ቤ/ክ እንደምታገለግሉ የምታውቁት አይመስልም፡፡ ስትፈልጉ ስለ ኦርቶዶክ ደስ ሲላችሁ ስለ ፕሮቴስታንትና ተሀድሶ ታወራላችሁ፡፡ ህዝቡን ከጥፋት ከመመለሳችሁ በፊት እናንተ ተመለሱ፡፡በመጀመሪያ ስለምታወሩት ነገር አስቡ፡፡ እናንተ እራሳችሁ የየትኛው ቤ/ክ አባል እንደሆናችሁና የትኛውን ቤ/ክ እንደምታገለግሉ የምታውቁት አይመስልም፡፡ ስትፈልጉ ስለ ኦርቶዶክ ደስ ሲላችሁ ስለ ፕሮቴስታንትና ተሀድሶ ታወራላችሁ፡፡ ህዝቡን ከጥፋት ከመመለሳችሁ በፊት እናንተ ተመለሱ፡፡

April 29, 2013 at 3:53 PM

በመጀመሪያ ስለምታወሩት ነገር አስቡ፡፡ እናንተ እራሳችሁ የየትኛው ቤ/ክ አባል እንደሆናችሁና የትኛውን ቤ/ክ እንደምታገለግሉ የምታውቁት አይመስልም፡፡ ስትፈልጉ ስለ ኦርቶዶክ ደስ ሲላችሁ ስለ ፕሮቴስታንትና ተሀድሶ ታወራላችሁ፡፡ ህዝቡን ከጥፋት ከመመለሳችሁ በፊት እናንተ ተመለሱ፡፡

Post a Comment

አስተያየቶች

 
Support : | |
Copyright © 2011. ደጀ ብርሃን dejebirhan - All Rights Reserved

Proudly powered by Blogger