Wednesday, April 24, 2013

ንስሐ ለማን፤ ለምንና እንዴት?


 (ከዚህ በፊት የቀረበ ጽሁፍ ነው)

«ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት» (መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ማቴ ፫፤፩-፪)

«ነስሐ»  ስርወ ቃሉ እብራይስጥ ሲሆን ትርጉሙም አዘነ፤ ተጸጸተ፤ ተመለሰ፤ ክፉ ዐመሉን ተወ፤ መጥፎ ጠባዩን ለወጠ ማለት ነው። የግእዙም ግስ ይህንኑ ቃል እንዳለ ወርሶ ይጠቀምበታል።
«ነስሑ እምፍኖቶሙ እኩይ፤ ወእግዚአብሔርኒ ነስሐ እምዘነበበ» ይላል በዮናስ ፫፤፲ ላይ። ከክፉ መንገዳቸው ተመለሱ፤ እግዚአብሔርም በተናገረው ተጸጸተ»  እንደማለት ነው። ሰብአ ነነዌ ከኃጢአታቸው በንስሐ በተመለሱ ጊዜ እግዚአብሔርም ሊቀጣቸው በነበረው ፍርድ አዘነና ምህረትን ሰጣቸው። የእግዚአብሔር ሀዘን ከምህረቱ ሲሆን የሕዝቡ ሀዘን ደግሞ ከበደሉ ነው።       «ነስሐ» የሚለው ቃል በሁሉም ሥፍራ ማዘንን፤ መመለስን፤ መፀፀትን፤ መተውን ያመለክታል። «እግዚአብሔር ተፀፀተ» ስንል አምላካዊ ምሕረቱን ለመቀበል በማይፈልግ የሰው እልክኛ ልብ ወይም በሌላ መልኩ ምሕረቱን በሚጠይቅ ተነሳሒ ላይ ባለው አባታዊ ፍቅር እንጂ የሚጎድለው ወይም የሚጨመርለት ስላለ ያንን ከማጣትና ከማግኘት ጋር በተያያዘ አይደለም። ሰብአ ነነዌ ከተዘጋጀው ጥፋት ለመመለስ ንስሐ ሲገቡ እግዚአብሔርም በአምላካዊ ምህረቱ አዝኖላቸው ጥፋቱን መልሶላቸዋል። በሌላ ቦታም እንዲህ የሚል አለ።
በዘመነ ኖኅ የሰው ልጅ ዐመጻ በዝቶ የጥፋት ውሃ በታዘዘ ጊዜ «እግዚአብሔርም ሰውን በምድር ላይ በመፍጠሩ ተጸጸተ፥ በልቡም አዘነ» ዘፍ ፮፤፮ ይላል።
«ተጸጸተ» የሚለው ቃል «ነስሐ» የሚለው ቃል ትርጉም ነው። «እግዚአብሔር ተጸጸተ፤ አዘነ» ሲል ቀድሞ ያላወቀው ነገር በመድረሱ ወይም የማያውቀው ነገር እንደተከሰተ በማየቱ የተሰማው ስሜት ሳይሆን የሰው ልጅ ቀድሞ ከገነት ሕጉን አፍርሶ በመውደቁና ዳግመኛም በዚህ ምድር ላይ ኃጢአቱን እያበዛ በመሄዱ የተነሳ ሰው በራሱ በደል የሚመጣበት የፍርድ ቁጣ ስለሚያሳዝነው ብቻ ነው። ፻፳ የንስሐ ዘመንን ለመጠቀም ያልፈለገ ሕዝብ በውሃ ሰጥሞ ሲጠፋ ቢመለከት እግዚአብሔር መጸጸቱ አምላካዊ ባሕሪው ነው። እግዚአብሔር አባት በመሆኑ ሰዎች ይጠፉ ዘንድ ሳይፈልግ ዐመጻቸው ከሚያመጣባቸው ፍርድ የተነሳ ግን ያዝናል፤ ይጸጸታል።

«እንደዚሁ ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱ እንዲጠፋ በሰማያት ያለው አባታችሁ ፈቃድ አይደለም» ማቴ ፲፰፤፲፬ ፈቃዱ ሁሉም እንዲድኑ ቢሆንም ሁሉም ለመዳን ፈቃደኞች ስላይደሉ በሚጠፉ ሰዎች ላይ እግዚአብሔር ያዝናል፤ ይጸጸታል። በሌላ ቦታም እንደዚህ የሚል ተጽፏል።
«የእግዚአብሔርም መልአክ ኢየሩሳሌምን ያጠፋት ዘንድ እጁን በዘረጋ ጊዜ እግዚአብሔር ስለ ክፉው ነገር አዘነ፥ ሕዝቡንም የሚያጠፋውን መልአክ። እንግዲህ በቃህ እጅህን መልስ አለው። የእግዚአብሔርም መልአክ በኢያቡሳዊው በኦርና አውድማ አጠገብ ነበረ» ፪ኛ ሳሙ ፳፬፤፲፮  እግዚአብሔር በሰው ልጆች ሞት ያዝናል፤ ይጸጸታል። ምንም እንኳን ፍርዱ ምን ጊዜም ትክክል ቢሆንም በአርአያውና በምሳሌው የፈጠረው የሰው ልጁ በበደሉ ሲጠፋ ሲያይ ማዘኑ አይቀርም።
ከላይ ስንመለከተው እንደመጣነው «ንስሐ» የሚለው ቃል ማዘንን፤ መጸጸትን፤ መመለስን፤ መተውን፤ ከቀድሞ መንገድ መመለስን ያመለክታል። የሰው ጸጸት ከኃጢአቱ፤ የእግዚአብሔር ጸጸት ከምሕረት የተነሳ ነው።
ንስሐ ለሰው ልጅ ከኃጢአት ጋር የተያያዘ የጸጸትና የመመለስ ተግባር ነው ብለናል። ንስሐ የተነሳሒውን የቀደመ ማንነት የሚመልስ መንፈሳዊ ሳሙና ነው። ንጽሕናን ከልጅነት ደርቦ የሚያሰጥ የሕይወት ክፍል ነው። ይህ ከሆነ ንስሐ ለመግባት ኃጢአት በምን ይታወቃል? ጥቂት እንመልከት።
የሰው ልጅ ኃጢአት መሥራት የጀመረው በጎና ክፉ ምን እንደሆነ ማወቅ ከጀመረበት ሰዓት ነው።
«ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ»  ዘፍ ፫፤፭ 
ሰይጣን የመጀመሪያዎቹን የሰው ልጆች የስብከት ሥራውን ጀመረ።
አዳምና ሔዋን ዓይናቸውና ሃሳባቸው ከደጉ አምላካቸው ጋር ነበር። ስለዚህ አምላካዊ ባሕርይ በውስጣቸው ስለነበር ምንም የሚያሳስባቸውና የሚያስጨንቃቸው ነገር አልነበረም። ይሁን እንጂ ይህንን የሚጋፋ አዲስ ነገር ሲመጣባቸው በተደራቢነት ለማስተናገድ ፈቀዱ። ዓይን በመክፈት ደግና ክፉን የሚያሳውቅ ነገር ለመቀበል ምክር ሰሙ። ለሁለት ጌቶች ለመገዛት ፈቀዱ። ይሁን እንጂ አንዱን ሲወዱ አንዱን ማጣት የግድ ነበር።
«ለሁለት ጌቶች መገዛት የሚቻለው ባርያ ማንም የለም፤ ወይም አንዱን ይጠላልና ሁለተኛውንም ይወዳል፥ ወይም ወደ አንዱ ይጠጋል ሁለተኛውንም ይንቃል። ለእግዚአብሔርና ለገንዘብ መገዛት አትችሉም» ሉቃ ፲፮፤፲፫
ለአዳምና ለሔዋን የነበረው ምርጫ ከእግዚአብሔር የተሰጠ የገነትን ሲሳይ ወይም ሰይጣን ከሚሰጠው ኃጢአት ምን እንደሆነ የማወቅና ዓይናቸው ሲከፈት የበለስ ገንዘብን፤  የራሳቸው ገንዘብ  ማድረግን፤ ከሁለት አንዱ መምረጥ ነበረባቸው። አትንኩ፣ ይህ ሞትን ያመጣባችኋል የተባሉትን ነገር በመቅመስ ሞት ምን እንደሚመስል ለማየት ሁለተኛውን መርጠው ዓይናቸው ቢገለጥ ያገኙት ነገር ራቁት መሆናቸውን ማወቃቸውንና በኃፍረት መሸማቀቅን ነበር። በዚህም የነበራቸውን አጡ፤ ያልነበራቸውን ሀፍረት ተሸከሙ፤ ከብርሃን ይልቅ የቅጠል ልብስንም ለራቁታቸው ለበሱ። በሕይወት ዛፍ ዘላለማዊነትን ከማግኘት ወጥተው ከሞት ጋር ኅብረት አደረጉ።
ጥንተ ጠላታችን አዳምንና ሔዋንን ያሳተው መልካሙንና ክፉውን ለይቶ የሚያስታውቃችሁን ዛፍ ብትበሉ ዓይናችሁ ይከፈታል በማለት ነበር። ይኼ  የጠላት ጥሪ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬም አላቋረጠም።  አጠራሩና ዘዴው እንደየሁኔታው ከመለያየቱ በስተቀር የሰው ልጆችን ይህን ብታደርጉ የዓይናችሁ እርካታ ይሳካል እያለ ይመክራል።
ዓይናችሁን ከፍታችሁ ቆንጆ እየመረጣችሁ ብታመነዝሩ የወሲብ ጥማታችሁን ታረካላችሁ እያለ ከዝሙት በለስ ሰዎች እንዲቀጥፉ ያደፋፍራል። በኃላፊነት በተሰጣቸው የታማኝነት የሥራ ድርሻ ውስጥ «የአባትህ ቤት ሲወረር አብረህ ውረር» በሚል ቅስቀሳ ከዘረፋና ከስርቆት በለስ ሰዎች የድርሻቸውን የኃጢአት ሸክም እንዲወስዱ ዓይናቸውንና ልባቸውን ወደ ገንዘብ ፍቅር እንዲወረውሩ ያደርጋል። ለብዙ ወይንና መጠጥ እንዲጎመጁ ዓይናቸውን ከበለሲቱ ጠርሙስ ላይ እንዲያሳርፉ ይመክራል። ከስካር፤ ከውርደትና ኅሊናን ከመሳት ገሃዳዊ የውድቀት አዘቅት እንዲቋደሱ ይጋብዛል። ከጫት፤ ከሲጋራ፤ ከሀሺሽ በአጠቃላይ ሱስ የሚገኘውን የውድቀት ዓለም እንዲቀላቀሉ ይጎተጉታል፤ ፤ ቀጥፈው እንዲበሉ ጥንተ ምክሩን ያቀብላል። ግደልና እንደአቤል አሸዋ ውስጥ ቅበረው እያለ ክፉውን ምክር አቀብሎ በሰው ደም ተቅበዝባዥ ሆኖ እንዲኖር ይገፋፋል። በጓደኛው፤ በቤተሰቡ፤ በአካባቢው፤ በኑሮው ሁሉ ይህ በተሞክሮ የዳበረ ጠልፎ የመጣል ምክር ለአፈንጋጮች ሁሉ ይቀርባል። ሰዎች ለሚናገሩት እያንዳንዷ ጸያፍና አስነዋሪ ኢ-ክርስቲያናዊ ቃል እንኳን ሰይጣን ይጠነቀቃል። ይህንን በል፤ እንዲህም አዋርደው፤ እንዲህም ስትለው ታጠቃዋለህ፤ ስሜቱን ትጎዳዋለህ እያለ ይመክራል። ስለዚህ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ፈቃድ አሠራር ሲለይ የሰይጣንን የዓይን አምሮትና የልብ ምክርን ፈጻሚ ይሆናል ማለት ነው።
የመጀመሪያው የኃጢአት ጎዳና የተከፈተውና የሰው ልጅም የተጓዘበት ፈቃደኝነት ከብርሃኑ ወጥቶ ወደሚያስጎመጅ የዓይን አምሮት መሄዱ ነው። ዛሬም የሚፈጸመው ኃጢአት ሁሉ በቀድሞው መንገድ የመጓዝ ምርጫ የተነሳ ነው። ከዚህ ራቁት የመሆን ምርጫ ለመመለስ ሰው ንስሐ መግባት አለበት። ንስሐ የኃጢአትን ሸክም ማራገፊያና ከሞት ወደ የሕይወት የሚገቡበት መንገድ ነው። ጌታ ራሱ «ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁም» እንዳለው። ሉቃ ፭፤፴፪ ንስሐ ለኃጢአተኞች መንጻት ከእግዚአብሔር የተሰጠ የምሕረት በር ነው። በዚህ ንስሐ ለመዳን ለሰው ልጆች ምርጫ የተተወ ስለሆነ ማንም አያስገድደውም። መልካምም ቢሰራ ከመልካምነት የሚከፈለውን ዋጋ ያገኛል። በኃጢአት መኖርን ፈቅዶ ቢሞት ደግሞ ከኃጢአት የሚታጨደውን ዋጋ ይቀበላል።
የንስሐን አጭር ትርጉም፤ ለንስሐ የሚጋብዙ የውድቀት አመጣጥንና የንስሐን አስፈላጊነት ለማየት ሞክረናል። ታዲያ «የመዳን ቀን ዛሬ ነው» እንዳለው ቃሉ ኃጢአት ከሚያመጣው ሞት ዛሬውኑ ለመዳን ንስሐ የምንገባው እንዴት ነው? ለማነው? የሚለው አጥርቶ መመልከት ጠቃሚ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ ለዚህ ጥያቄ በቂና የተብራራ መልስ አለው። በቂና አስተማማኝ መልስ የሚገኘው ከመጽሐፍ ቅዱስ እንጂ ከድርጅት ወይም ከሃይማኖት ተቋም አይደለም።

1/ ኃጢአትና ንስሐ በብሉይ ኪዳን፤
ለአዳም በገነት የተሰጠው ሕግ አንዲት ነበረች። ይኼውም ዕጸ በለስን አለመብላት። ይህን ሕግ መጣሱ ኃጢአት ምን እንደሆነ እንዲታወቅ ሆነ። ለእስራኤል ዘሥጋም  የኃጢአትን መኖር ያስታወቀው የብሉይ ኪዳን ሕግ መሰጠት ነው። ሕግ ሳይሰጥ በፊት /ሕገ ልቡና/ ሕዝቡ በሚሰጠው የልቡና ሚዛን እንጂ እነዚህን ማድረግ ኃጢአት ነው የሚል የተቀመጠ ድንጋጌ ባለመኖሩ ኃጢአት አይታወቅም ነበር። ሐዋርያው ጳውሎስም ይህንን ሲገልጸው እንዲህ ብሎታል።
«ሕግ እስከ መጣ ድረስ ኃጢአት በዓለም ነበረና ነገር ግን ሕግ በሌለበት ጊዜ ኃጢአት አይቈጠርም» ሮሜ ፭፤፲፫   ሕግ ሲሰጥ ኃጢአት ታወቀ። ኃጢአትም ባለበት የሕግ ፍርድ አለ።  ሕጉ ይህንን አድርግ፤ ይህንንም አታድርግ ይላል። ስለዚህ የኃጢአትን ማንነት ገላጭ ሕግ ነው። ለእስራኤል ዘሥጋ የተሰጡ  የሥርየት ሕጎች በሁለት መንገዶች ይታያሉ። አንደኛው ማደረግ ያለበትን ሲያሳይ ሁለተኛው መሆን የሚጠበቅበትን ያመላክታሉ።
«ማድረግ» ያለበት የሚለው ኃይል ቃል ይህንንና ይህን አድርግ ይህንንና ይህንን ደግሞ አታድርግ ሲል በዝርዝር ይደነግጋል።  «መሆን» የሚገባው ኃይለ ቃል ደግሞ የሚያመላክተው በሰውዬው ፈቃድ ላይ ያልተመሠረተ ነገር ግን የእስራኤል ዘሥጋ ሙሉ ሰው ለመሆን የሚያበቃ ማንነትን ይገልጻል። ማድረግ ከሚገባው አንዱን ብንጠቅስ ፤
«ማናቸውም ሰው ኃጢአትን ቢሠራ፥ እግዚአብሔርንም ቢበድል፥ ያኖረበትን አደራ ወይም ብድር ወስዶ ባልንጀራውን ቢክድ፥ ወይም ቢቀማ፥ ወይም በባልንጀራው ላይ ግፍ ቢያደርግ፥ ወይም የጠፋውን ነገር ቢያገኝ፥ ያንንም ሸሽጎ በሐሰት ቢምል፥ ሰው ከሚያደርጋቸው ከእነዚህ ነገሮች ሁሉ በአንዲቱ ቢበድል፥ እርሱ ኃጢአትን ሠርቶ በደለኛ ቢሆን፥ በቅሚያ የወሰደውን ወይም በግፍ የተቀበለውን ወይም የተሰጠውን አደራ ወይም ጠፍቶ ያገኘውን፥ ወይም በሐሰት የማለበትን ነገር ይመልስ በሙሉ ይመልስ፥ ከዚያም በላይ አምስተኛውን ክፍል ጨምሮ የበደሉን መሥዋዕት በሚያቀርብበት ቀን ለባለ ገንዘቡ ይስጠው። ስለ በደል መሥዋዕትም ለእግዚአብሔር ከመንጋው ነውር የሌለበትን አውራ በግ እንደ ግምጋሜህ መጠን ስለ በደል መሥዋዕት ወደ ካህኑ ያምጣ። ካህኑም በእግዚአብሔር ፊት ያስተሰርይለታል፥ ስለዚያም ስላደረገው በደል ሁሉ ይቅር ይባላል»
ይህ ማድረግ ስለሚገባው የኃጢአትና የሥርየትን መንገድ የሚያሳይ ሕግ ሲሆን መሆን ስለሚገባው ደግሞ ይህንን እናገኛለን።
«ካህኑም በሥጋው ቁርበት ያለውን ደዌ ያያል ጠጕሩም ተለውጦ ቢነጣ ደዌውም ወደ ሥጋው ቁርበት ቢጠልቅ፥ እርሱ የለምጽ ደዌ ነው ካህኑም አይቶ ርኩስ ነው ይበለው» ዘሌ ፲፫፤፫  ለምጽ ደዌ ነው። ይህንን በሽታ ሰው ወዶና ፈቅዶ የሚያመጣው ሳይሆን በሽታ ቢሆንም ለእስራኤል ዘሥጋ ይህ ደዌ ከማኅበራዊና ኃይማኖታዊ አንድነት በርኩሰት የሚያስገልል ነበር። ሌላ ቦታም «ቍላው የተቀጠቀጠ ብልቱም የተቈረጠ ወደ እግዚአብሔር ጉባኤ አይግባ» ይላል። ይህም በሰውዬው ፍላጎት የሚመጣ ሳይሆን ከአቅሙ በላይ በሆነ ምክንያት ቢከሰት እንኳን ከእግዚአብሔር ጉባዔ የሚያስገልል ኃጢአት ነበር። ሰው ድንኳን ውስጥ እያለ ቢሞት በድንኳኑ ውስጥ የነበሩ ሰዎች ሁሉ እስከ ሰባት ቀን ርኩስ ናቸው። ዘኁል ፲፱፤፲፬ የሚልም አለ።
 ሕዝቡ በአንድ ወገን የጉባዔው አባል ለመሆን የሚያስችለው የተሰጠው የግልና የቡድን ሕግጋት ነበሩት። ካህናቱም በሌላ ረድፍ ለክህነት የሚያበቁ የሕግ ትእዛዛት ነበሩት። ይህንን ይህንን አድርጉ፤ ይህንን ይህንን ደግሞ አታድርጉ ሲል የሚያጠነቅቅ ሕግ ተሰጥቷቸዋል።  ለእስራኤል ዘሥጋ ጉባዔ ብቁ የሚያደርጉ «መሆንን» የሚጠይቁ ሕግጋትም አብረው ተሰጥተዋቸዋል።  እነዚህን ሕግጋት እየተከታተሉ የሚያስፈጽሙትና በተጻፈው መሠረት ሥራ ላይ የማዋል ውክልና የተሰጣቸው ካህናቱ ናቸው። ካህናቱ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ጉባዔ በተሰጣቸው የእግዚአብሔር ሕግ መሠረት ይመሩታል፤ይናዝዙታል። ለበደል ኃጢአት በመስዋዕት ያስታርቃሉ፤ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን የይቅርታ ምሕረት ያድላሉ። በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል፤ ድልድይ ሆነው የማገናኘት አገልግሎትን ይፈጽማሉ። ሕዝቡ የሚጠይቀውን ወደ እግዚአብሔር፤ እግዚአብሔር የሚናገረውን ወደሕዝቡ ያቀርባሉ። አገናኝነታቸው በሃሳብ ሳይሆን በድምጽ ነበር። የእነርሱን ድምጽ እግዚአብሔር ያዳምጣል፤ እነሱም የእግዚአብሔርን ድምጽ በቀጥታ ይሰሙ ነበር። መካከለኛ ማለት ድምጽ የሚሰጥና ድምጽ የሚቀበል አገናኝ ማለት ነውና ይህንን ሲፈጽሙ ኖረዋል። ሙሴን ሕዝቡ እንዲህ ሲል ሲናገረውና ሙሴን የሰማውን ሲመልስላቸው እናያለን።
«አንተ ቅረብ፥ አምላካችን እግዚአብሔር የሚለውን ሁሉ ስማ አምላካችን እግዚአብሔርም ለአንተ የሚናገረውን ሁሉ ለእኛ ንገረን እኛም ሰምተን እናደርገዋለን። በተናገራችሁኝም ጊዜ እግዚአብሔር የእናንተን ቃል ጽምፅ ሰማ እግዚአብሔርም አለኝ፦ ይህ ሕዝብ የተናገሩህን ቃል ድምፅ ሰምቼአለሁ የተናገሩህ ሁሉ መልካም ነገር ነው»     ዘዳ ፭፤፳፯-፳፰
የካህናቱ አገናኝነት የዚህን ያህል ከእግዚአብሔር ጋር የተሳሰረ ነበር። ይሁን እንጂ አገናኝዎቹ ካህናት በሥጋ እረፍት በሞት የሚሸነፉ ናቸው። በኃጢአት በደልም የሚቀሰፉ ነበሩ። የማገናኘት ተልእኮአቸውም ዕለት ዕለት የሚፈጸም አድካሚ ነው። ለኃጢአተኛውም ፍጹም ሥርየትን ማሰጠት አይችሉም ነበር። ምክንያቱም የሚፈሰው የሥርየት ደም የእንስሳ እንጂ ራሳቸው ካህናቱ ለኃጢአተኛው አይሞቱለትም። ይልቁንም በኃጢተኛው ምትክ መስዋዕት ሆኖ በሚቀርበው እንስሳ ላይ እጁን ጭኖ ያቀርበዋል። «እጁንም በኃጢአት መሥዋዕት ራስ ላይ ይጭናል የሚቃጠልም መሥዋዕትን  ያርዳል» ዘሌ ፬፤፳፱

2/ ኃጢአትና ንስሐ በአዲስ ኪዳን

የሚቀርበው መስዋዕትና የበደል ሥርየት ሁል ጊዜ እንዲፈጸም ያደረገው አገልጋዮቹ ካህናት ለህዝቡ ምትክ መስዋዕት ሆነው ለመሞት ብቃት ስለጎደላቸውና ሞት የሚያሸንፋቸው ደካማዎች ስለሆኑ ነበር። ስለዚህ ከእግዚአብሔር ዘንድ ይህንን ድካም የሚተካ፤ ፍጹም ድኅነትን ለሰው ልጆች ማሰጠት የሚችል የንስሐና የሥርየት አዲስ ሥርዓት አስፈልጎታል። ድካም የሞላባት የቀደመችው የክህነት ሕግ ድካም በማያሸንፈው አዲስ ሕግ መሻር አለባት።
«ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል»
            ምክንያቱም፤
«እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው»
             ስለዚህ፤
«ሕጉ ድካም ያላቸውን ሰዎች ሊቀ ካህናት አድርጎ ይሾማልና፤ ከሕግ በኋላ የመጣ የመሐላው ቃል ግን ለዘላለም ፍጹም የሆነውን ልጅ ይሾማል»
የቀደመችውን የክህነት ሕግ በመሻር፤ ሞት የማያሸንፈው፤ በመሐላ የተሾመ የአዲስ ኪዳን ለኃጢአተኞች የቀረበ አስታራቂ መስዋዕት ሊቀ ካህን «ኢየሱስ» ነው፤ ማለት ነው።
           ምክንያቱም፤
ሕጉ ድካም ያለባቸውን ሰዎች ያለመሐላ ይሾማቸዋል። እግዚአብሔር በራሱ ምሎ ያልሾማቸው ሁሉ ድካም የሞላባቸው ስለሆኑ በሞት ይሸነፋሉ። በትንሣዔው ፍጹም የመሆን አምላካዊ ባህይሪው የማይታበል በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት አንተ ዘላለማዊ ነህ ባለው በኢየሱስ ክህነት ግን በስሙ ምሏል።
ያለ መሐላ ካህናት ሆነዋልና፤ እርሱ ግን፦ ጌታ አንተ እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ለዘላለም ካህን ነህ ብሎ ማለ አይጸጸትም ብሎ በተናገረለት ከመሐላ ጋር ካህን ሆኖአልና ያለ መሐላ ካህን እንዳልሆነ መጠን፥እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል»
ይህ የአዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህን በንስሐ ለሚመጡ ኃጢአተኞች ሌላ መስዋዕት እንዲያቀርቡ አይጠይቅም። ፵ ስገድ ወይም ገንዘብ ክፈል አይልም። ምክንያቱም እነዚህ ድርጊቶች በተሻረችው የቀደመችው ሥርዓት ተተግብረው ሰውን ማዳን አልቻሉምና። ካህናቱ ራሳቸው መስዋዕት መሆን የማይችሉና ሟቾች ስለሆኑ እነዚህ አፍአዊ የሥርየት መንገዶች በአዲስ ኪዳን ዘመን የሉም።
                   ምክንያቱም፤
«እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና»
ኢየሱስ ክርስቶስን የአዲስ ኪዳን ሊቀካህን የምንለው ለዚህ ነው። የብሉይ ኪዳኑ ካህናት በሕዝቡና በእግዚአብሔር መካከል የነበሩ መካከለኞች ሞት፤ ኃጢአትና ድካም የሚያሸንፋቸው ስለነበሩ የአዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህን ሞት የማያሸንፈው፤ኃጢአት የማያውቀውና ድካም የሌለበት በመሐላ የተሾመ መካከለኛ ቦታውን ተረክቧል።
ይህንንም ጳውሎስ እንዲህ አለው።
«ስለዚህም የፊተኛው ኪዳን ሲጸና ሕግን የተላለፉትን የሚቤዥ ሞት ስለ ሆነ፥ የተጠሩት የዘላለምን ርስት የተስፋ ቃል እንዲቀበሉ እርሱ የአዲስ ኪዳን መካከለኛ ነው»
በዚህ ዘመን በእግዚአብሔርና በሕዝቡ መካከል የሚገቡ መካከለኞች አሉ? በመሐላ የተሾሙ፤ ሞት የማያሸንፋቸው፤ ድካም የሌለባቸው ካህናት አሉን? በፍጹም የሉም!!!!   ምክንያቱም ኃጢአተኛው ንጹሕ እንዲሆን ሊቀካህኑ ንጹሕ መሆን አለበትና።  ይህንን የሚያሟሉና ሥርየት ማስገኘት የሚችሉ ሊቀካህናት ዛሬ የሉንም። ካህናት መካከለኞች እስከሆኑ ድረስ ይህንን የአስታራቂነት ብቃት ያለው በአዲስ ኪዳን ማንም ሌላ የለም።
                   ምክንያቱም፤
«አሁን ግን በሚሻል ተስፋ ቃል በተመሠረተ በሚሻል ኪዳን ደግሞ መካከለኛ እንደሚሆን በዚያ ልክ እጅግ የሚሻል አገልግሎት አግኝቶአል»
በሰውና በእግዚአብሔር መካከል፤ መካከለኞች እኛ ነን የሚሉ ራሳቸውን ሞት እንደማያሸንፋቸውና ኃጢአት እንደማይጥላቸው የሚመኩ ግብዞች ናቸው። እውነታውን ግን ወንጌል እንዲህ ይለናል።
«አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው» ፩ኛ ጢሞ ፪፤፭
የኦሪቱን የካህናት አገልግሎት መሻር ያስፈለገው ብቁ መሆን የቻለ መካከለኛ ስለሌለ ነውና ብቁ እንደሆናችሁ አስባችሁ በመካከለኝነት ሥፍራ ራሳችሁን ያስቀመጣችሁ እረፉ እንላለን። የንስሐ አባት ኢየሱስ ለኃጢአተኛ ልጆቹ ሞቷል። እነዚህ የዘመኑ የንስሐ አባቶች ነን የሚሉቱ ሥርየት ለማስገኘት ለኃጢአተኛው ሊሞቱ ይችላሉን? እንኳን ለኃጢተኛው ለራሳቸውም ኃጢአት መሞትና ራሳቸውን ማዳን አይችሉም። በቀደመችውስ ሕግ ካህኑ የሕዝቡን መስዋዕት ከማቅረቡ በፊት ለራሱ ሊነጻ ግድ ስለሆነ ቅድሚያ የደም መስዋዕት ያቀርብ ነበር። እነዚህ የዘመኑ ካህናት ነን ባዮች ራሳቸው ሊነጹ ምን ዓይነት የደም መስዋዕት አስቀድመው ያቀርባሉ? ደም ሳይፈስ ሥርየት ስለሌለ በየትኛው ሕግ የታዘዘ የደም መስዋዕት አላቸው? ክርስቶስ ይህንን ሁሉ ድካም ለማስቀረትና ምትክ የሌለው መስዋዕት ለማቅረብ ሲል ሊቀ ካህናችን ሆነና ተሰዋልን። ለክርስቶስ ሰማያዊ ንግሥናው የሚበቃው ሆኖ ሳለ ለእኛ መስዋዕት ሊሆንልን ስለወደደን ብቻ በመካከላችን ሊቀ ካህን ሆኖ ተገኘ። የቀደመችውን ሕግ በሰማያዊ መስዋዕት ተካ። እናም ሌላ ካህን ሊነሳልን አያስፈልግም በማለት ጳውሎስ የተናገረው ትክክል ነበረ።

3/ ካህናት

ኢየሱስ ሊቀ ካህናት/ የካህናት አለቃ/ ነው ካልን በሥሩ አገልጋይ/ ካህናት/ ሊኖሩ የግድ ነው። ካህን በሌለበት ለካህናት አለቃ አይሾምምና። በአዲስ ኪዳን በሊቀ ካህኑ ሥር ያሉት ካህናት፤ የቤተ ክርስቲያን ጉባዔ አባላት ሁሉ ናቸው። ካህን ማለት አገልጋይ ነው። ድሮ ካህን መሆን የሚቻለው ከሌዊ ነገድ በመወለድ ብቻ ነበር። የአዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህን መስዋዕት ደግሞ ከአንድ ነገድ ብቻ የነበረውን የክህነት አገልግሎት ሻረው። «ሕጉ ሲሻር ክህነቱ ደግሞ ሊሻር የግድ ነው» የተባለው ለዚህ ነው። ክህነቱ የተቋቋመው እግዚአብሔር በሰጠው ሕግ ነበር። እግዚአብሔር ያንን ሕግ በአዲስ ሕግ ሲሽረው ክህነቱ ተሽሯል ማለት ነው። ያለእግዚአብሔር ሕግ ክህነት የለም። የአዲስ ኪዳን የክህነት ሕግ ደግሞ በክርስቶስ ተፈጽሟል። ከዚያ ውጪ ከእግዚአብሔር በተሰጠ ሕግ የተመሠረተ ሌላ የክህነት ሕግ በዚህ ዘመን የለም።
ለዚህም ነው በክርስቶስ ያመኑትንና ለሰማያዊ ጥሪ ተካፋይነት የቀረቡትን ሁሉ ወንጌል ወደሌላ ወደማንም እንዳይመለከቱ የሚናገረው።
«ስለዚህ፥ ከሰማያዊው ጥሪ ተካፋዮች የሆናችሁ ቅዱሳን ወንድሞች ሆይ፥ የሃይማኖታችንን ሐዋርያና ሊቀ ካህናት ኢየሱስ ክርስቶስን ተመልከቱ» ዕብ ፫፤፩
«ከኃጢአት በቀር በነገር ሁሉ እንደ እኛ የተፈተነ ነው እንጂ፥ በድካማችን ሊራራልን የማይችል ሊቀ ካህናት የለንም» ዕብ ፬፤፲፭
ክርስቲያኖች ራሳቸውን እንደተቀደሰ መስዋዕት የሚያቀርቡት ራሳቸውን ከኃጢአት በመለየት ነው። ያንን ጊዜ ቅዱሳን ካህናት ይባላሉ።
«እናንተ ደግሞ እንደ ሕያዋን ድንጋዮች ሆናችሁ፥ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእግዚአብሔር ደስ የሚያሰኝ መንፈሳዊ መሥዋዕትን ታቀርቡ ዘንድ ቅዱሳን ካህናት እንድትሆኑ መንፈሳዊ ቤት ለመሆን ተሠሩ» ፩ኛ ጴጥ ፪፤፭
                        ምክንያቱም፤
«እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ» ፩ኛ ጴጥ ፪፤፱
                          ምክንያቱም፤
«መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን» ራእ ፩`፤፮
«መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ» ራእ ፭፤፱-፲
                    ምክንያቱም፤
«በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት ይነግሣሉ» ራእ ፳፤፮
ስለዚህ ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃን በክርስቶስ የተጠሩ፤ ቅዱስ ሕዝብ የተባሉ፤ ለርስቱ የተለዩ፤ የእርሱን በጎነት የሚያውጁ ቅዱሳን ሁሉ ካህናት ይባላሉ። እርሱን ደግሞ ሊቀ ካህናችን ይሉታል።
«ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን» ዕብ ፰፤፩

4/ ሁላችን ካህናት ከሆንን ንስሐ ወደማን እንግባ?

መልሱ አጭር ነው። ከላይ እያየን እንደመጣነው ኃጢአት ለማያውቀው፤ ሞት ለማያሸንፈውና መካከለኛው ሊቀ ካህን ለሆነው ለኢየሱስ ነው። የኦሪቱ የበግ መስዋዕት ሲታረድ ኃጢአተኛው እንደሚድን ካህኑ ኃጢአቱን ይቅር ሲለው ይቅር ይባልለት ነበር። በበጉ ደም ላይ እምነቱን ያሳድራል። በጉ ኃጢአቱን እንደተሸከመ ስለሚያምን መዳኑን አይጠራጠርም። በአዲስ ኪዳን ግን ኃጢአተኛው ያላቀረበው፤ ንጹሕና ኃጢአቱን የተሸከመና ሌላ ካህን ያላስፈለገው ክርስቶስ ኢየሱስ ራሱ በግ ሆኖ መስዋዕት ሆኖ ታርዷል። ለኃጢአቴ ለሥርየት በእሱ አምኜ ወደሊቀ ካህኑ ስመለስ  በይቅርታው እድናለሁ ብሎ ማመን ይጠበቅበታል። እርሱ ብቻ ከአባቱ ጋር ያስታረቀኝና የሚያስታርቀኝ ንጹሕ መካከለኛ ሊቀ ካህኔ ነው ብሎ መቀበል አለበት። ለኃጢአተኛ ይህንን ማድረግ የሚችል መካከለኛው መንገድ ደግሞ ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌላ ማንም የለም።
«ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም» ዮሐ ፲፬፤፮         ዋናው ነገር በስሙ የምናደርገውን ሁሉ እንደሚደረግልን ማመን ይገባል።

«ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ» ዮሐ ፲፬፤፲፬  ይለናል ባለቤቱ ራሱ። በስሙ ስንለምን እኔ አደርገዋለሁ ሲል በምን መልኩ እንድናደርግ ፈልጎ ይሆን? የእግዚአብሔርን መኖር የምንቀበለው በእምነት እንጂ ማረጋገጫ እየጠየቅን አይደለም። ክርስቶስም በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ የሚለውን የምንቀበለው እንደሚደረግልን በማመን ብቻ ነው።  ስለዚህ በስሙ ስንናዘዝ፤ በደላችንን ስንንገር፤ ይቅርታውን እንዲሰጠን ስንጠይቅ ይደረግልናል። «ማናቸውንም ነገር በስሜ ብትለምኑ እኔ አደርገዋለሁ» ካለን ቃሉ የማይታበል መሆኑን አምነን ማድረግ ይገባናል።
በእኛ በኩል ካልሆነ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት አትችሉም የሚሉ ሰዎች ቢኖሩም ማናቸውንም ነገር በእናንተ በኩል እንድናደርግ ስላልተነገረን ዋሾዎች ናችሁ እንላለን። ደጋፊ ቃላትን እየለቃቀማችሁ ለራሳችሁ የሚመች የሥልጣን ወንበር ከምታዘጋጁ በስተቀር በአዲስ ኪዳን እንደኦሪቱ የተቀመጠላችሁ የካህናት ሕግ የላችሁም። አለ ካላችሁ እስኪ አሳዩን!! የኦሪቱ ሕግ ካህን ለመሆን የሚያበቃ ደረጃ፤ አሿሿሙ፤ አለባበሱ፤ የመስዋዕት አቀረራቡ፤ ሥልጣኑ፤ የጉድለቱ ሚዛን እያንዳንዱ ተቀምጦ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን ክርስቶስ ካህን አስፈልጎት ከሆነ ለምን ይህንን የመለያ ሕግ አልሰጠም ነበር?
እውነታው ያልሰጠበት ምክንያት የቀደመውን ሕግ በሌላ አዲስ ምድራዊ ሕግ የመተካት ሳይሆን ራሱ በመፈጸም ሥልጣንን ሁሉ በሰማይም በምድርም ለመጠቅለል ነበር።
«በዘመን ፍጻሜ ይደረግ ዘንድ ያለው አሳቡም በሰማይና በምድር ያለውን ሁሉ በክርስቶስ ለመጠቅለል ነው» ኤፌ ፩፤፲
 የቀድሞዎቹ ሊቃነ ካህናት በቀጥታ ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ያደርጋሉ፤ በቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጥ ድምጹንም ሰምተው የመጣውን መልክዕክት ለሕዝቡ ይነግራሉ። ዛሬስ መልእክት የሚሰሙ ካህናት አሉ? የሉም!! በአዲስ ኪዳን በአብ በመሐላ የተሾመ ከእሱም የተወለደ የባህርይ ልጁ ኢየሱስ ሊቀ ካህን ሆኗልና ድምጹን የሚሰማ እሱ ብቻ ነው። ሁሉን ከተሰጠው ከኢየሱስ ክርስቶስ እንቀበላለን እንጂ ምንም ካልተሰጣቸው ምድራውያን የምናገኘው ነገር የለም። «ሁሉ ከአባቴ ዘንድ ተሰጥቶኛል፤ ከአብ በቀር ወልድን የሚያውቅ የለም፥ ከወልድም በቀር ወልድም ሊገለጥለት ከሚፈቅድ በቀር አብን የሚያውቅ የለም» ማቴ ፲፩፤፳፯
አንዳንዶች ራሳቸውን ለመሞገት ሲፈልጉ እንዲህ የሚለውን ጥቅስ በማቅረብ ሁሉ እንደተሰጣቸው ለመናገር ይፈልጋሉ። ዳሩ ግን በዚህ የመሞገቻ ጥቅሳቸው ውስጥ ምንም የተሰጣቸው ነገር የለም።
«እርሱም ለማንም እንዳይናገር አዘዘው፥ ነገር ግን። ሄደህ ራስህን ለካህን አሳይ፥ ለእነርሱም ምስክር እንዲሆን ስለ መንጻትህ ሙሴ እንዳዘዘ መሥዋዕት አቅርብ አለው» ሉቃ ፭፤፲፬
የዘመኑ ሞጋቾች ካህን አለ ለማለት ከመሐከል «ራስህን ለካህን አሳይ» የምትለውን ቃል በጣም ይወዷታል። ይህም ኃጢአተኛ ለዚህ ዘመን ካህናት ኃጢአቱን እንዲናዘዝ ጌታችን አዟል ለማለት ሲፈልጉ ነው። ይሁን እንጂ ሰዎቹ ልባቸው እንደተመኘው ይህ ቃል አንዳችም ደጋፊነት የለውም። ምክንያቱም ከክርስቶስ ክህነት የጎደለና በእነሱ የሚሞላ ወይም የእነሱ የተሻለ ስለመሆኑ የሚያሳይ ምንም ፍንጭ የለውም።
ከላይ በመግቢያችን ላይ እንደጠቀስነው በዘመነ ብሉይ ሰው ራሱ በሰራው ኃጢአት ብቻ ሳይሆን በተፈጥሮ ምክንያት ጉድለት በመጣበትም ነገር በርኩስነት ይመደብ ነበር። የለምጽ ደዌ ቢወጣበት ርኩስ ነው። ቆራጣ ቢሆንም ርኩስ ነው። ቋቁቻ፤ ቆረቆር ቢወጣበት ከርኩሰት ይጨመራል፤ ሽባ ቢሆንም ኃጢአተኛ ይባላል። ይህ የሕግ መገለል ሕግ በካህናቱ በኩል ይፈጸም ነበር። የአዲስ ኪዳኑ ሊቀ ካህን ግን የሻረው የቀደመውን ክህነት አገልግሎት ብቻ ሳይሆን ሕጉ ያስቀመጠውንም የመገለልን ስርዓት ጭምር ነበር። ክርስቶስ ከለምጻሞች፤ ድውያን፤ እውሮች፤ ጉንድሾችና ልዩ ልዩ ጉድለት ካለባቸው ጋር ይውል ነበር። ይፈውሳቸውና ያጽናናቸው እንደነበር ቅዱስ ወንጌል ይነግረናል። እንዲያውም ካህናቱ ከሚዘልፉበት አንዱ ምክንያት ከኃጢአተኞችና ከርኩሳን ጋር መገናኘቱን በመመልከት ነበር።
«ጻፎችና ፈሪሳውያንም ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው ለደቀ መዛሙርቱ። ከቀራ ጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላና የሚጠጣ ስለ ምንድር ነው? አሉ» ማር ፪፤፲፮
የዘመኑ ምድራዊ ካህናትም በለምጽ በሽታ ከኅብረተሰቡ የተገለለ፤ የተጠላና በርኩሰት ሲቆጠር የኖረውንና ካህናቱ አግልለው ያኖሩትን ሰው ክርስቶስ ቢፈውሰው «ሂድና ለካህን አሳይ» ተብሏል እያሉ ስለካህናት ናዛዚነት እንደተናገረ አድርገው በማሳመን ሊያጭበረብሩን ይፈልጋሉ። ካህናቱ ከርኩሰቱ ማዳን ቢችሉማ ኖሮ ስንት ዘመን አብሯቸው ኖሮ አልነበረምን? እንዲያውም እነሱ የክርስቶስን ከለምጻሞች ጋር መገናኘት አስጥብቀው ሲቃወሙና ሕጋችንን ሻረ በማለት ሲከሱት ኖረዋል። የዘመኑ ቀሳጢዎች ያንን ለምጻም «ለካህን አሳይ» ብሏል ብለው የሚከራከሩት ምን እንዲያደርጉት ነበር? ብለን እንጠይቃቸዋለን።

ሀ/ በኦሪቱ ሕግ ለምጻም ርኩስ ስለነበረ እንደሕጉ በካህናቱ ተባሯል። ስለዚህ አሁን «ራስህን ለካህን አሳይ» ማለቱ ለምጹን ፈውሱት ማለቱ ነበር ? ወይስ ለምጻም በኦሪቱ ካህናት ይወደድ ነበር?
ለ/ ክርስቶስ ለምጻሙን ሲፈውሰው ከለምጹ የቀረ ደዌና ያላለቀ የኃጢአት ይቅርታ ነበረው?
3/በኦሪቱ ሕግ ለምጻም እንደርኩስ ስለሚቆጠር መስዋዕቱ በካህናቱ ተቀባይነት የለውም። ክርስቶስ በፈወሰው ጊዜ ግን ሂድና በሙሴ እንደታዘዘው መስዋዕት አቅርብ ሲለው፤ ብቁና ሙሉ ሰው ስለሆነ አልነበረምን?
4/ ካህናቱ ይህንን የቀድሞ ለምጻም ሲያገሉት እንደቆዩት ሁሉ ከዳነ በኋላ አንቀበልህም ቢሉት ራሳቸው የሙሴን ሕግ ማክበር አለማክበራቸውን ለማጠየቅ «ሂድና ለካህን ራስህን አሳይ» ማለቱ አልነበረምን?
እኮ ምን እንዲያደርጉት ነበር ሂድና ለካህን አሳይ ያለው? በእርግጥ የዘመናችን ጅሎች የመጽሐፉን እውነት አይቀበሉም እንጂ በመቅደሱ ካህናት በኩል ይህ ሰው ክርስቶስ ሳይናገረው በፊትም ያውቁታል። ለምጻምና ኃጢአተኛ ተብሎ ከሕዝቡ ያገለሉት ራሳቸው ነበሩ። ይህንን ለምጻም እንኳን ካህናቱ ይቅርና ሌላ ሰው ከነካው እስከሰባት ቀን ድረስ ርኩስ ይባል ነበር። ስለዚህ «ሂድና ለካህን አሳይ » ብሎታል ባዮች የዘመናችን ቀሳጥያን እነርሱ እንደተመኙት እንዲፈውሱት ወይም ሥርየት እንዲሰጡት አልነበረም።
እሱ መልካም እረኛና የተናቁትን፤ የተጠሉትን የሚፈውስ መሆኑን ለማሳየት ነው። እነሱ የከለከሉትን የመስዋዕት ማቅረብ ንጽህና ስላጎናጸፈው ሂድና ራስህን አሳይ፤ እንደሙሴም የታዘዘውን መስዋዕት አቅርብ አለው። አመንበትም፤ ካድነው እውነታው ይህ ነው።

እነሱማ እንደሕጋቸው አባረውታል። የእነዚህ ቀሳጥያን ሌላው በእውቀት የማንከስ አባዜአቸው ደግሞ ለምጻሙ ሰው እድሜውን ሙሉ በለምጽ ቆይቶ፤ ማንም እንደሙሉ ሰው ሳይቆጥረው የመኖሩ ዘመን እንደሚያበቃ አምኖ፤ በክርስቶስ እግር ላይ ወድቆ በለመነ ጊዜ እምነቱን አይቶ «እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና። እወዳለሁ፥ ንጻ አለው፤ ወዲያውም ለምጹ ለቀቀ» ሉቃ ፭፤፲፫ በማለት ፍጹም የሆነ ፈውስን እንደሰጠው ወንጌል የተናገረውን በመካድ ከክርስቶስ የፈውስ ብቃት የጎደለ እንዳለና ካህናቱ የሚጨምሩለት እንደሚኖር በማሰብ «ሂድና ለካህን አሳይ» ተብሏል የሚሉት የክህደት ማላዘን አስገራሚ ይሆንብናል።  መዳኑን ካልሆነ በስተቀር ለካህናቱ የሚያሳየው ከክርስቶስ ፈውስ የቀረ ምንም ነገር አልነበረም። ካህናቱማ ሁልጊዜ እስከነ ለምጹ ሲያዩት ኖረዋል፤ ከማግለል በስተቀር መፈወስ አልተቻላቸውም። እንኳን ለቀደመችው የክህነት ሕግ እንዲናዘዝ ቀርቶ የቀደመችው የክህነት ሕግ ስለማታድን በመሻር በመስቀል ላይ የአዲስ ኪዳንን ሕግ ያቆመው ለዚህ ነበር።
«ሕጉ ምንም ፍጹም አላደረገምና፥ ስለዚህም የምትደክም የማትጠቅምም ስለሆነች የቀደመች ትእዛዝ ተሽራለች፥ ወደ እግዚአብሔርም የምንቀርብበት የሚሻል ተስፋ ገብቶአል» ዕብ ፯፤፲፰
ማጠቃለያ፤
ንስሐ መጸጸት፤ መመለስ፤ ማዘን፤ የቀደመ ማንነትን መተው ነው ካልን እኛ የሰው ልጆች በኃጢአትና በበደል ውስጥ የኖርበትን ማንነት በማራገፍ ሕይወትም፤ መንገድም እኔ ነኝ ባለው በኢየሱስ ክርስቶስ አዲስ መንገድ ላይ መሄድ ማለት ነው። ይህ የአዲስ ኪዳን እውነትም መንገድም ሌላ ካህን በምትክነት የሌለውና ባለቤቱ ራሱ መካከለኛ ሆኖ ያማለደ፤ ከአባቱ፤ ከራሱና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር ኅብረት ይኖረን ዘንድ በደሙ ያስታረቀን ሊቀ ካህናችን ነው።  ሊቀካህንነቱ ማስታረቅ ነውና ሊቀ ካህናችን እንለዋለን። እናመልከዋለን። እንሰግድለታለን። ለኃጢአታችን ሥርየት ወዶና ፈቅዶ ደሙን ስላፈሰሰልን ሌላ ለኃጢአት ሥርየት የሚሆን ፵ ና ፻፳ ስግደት የለንም። እንደዚህ ስታደርግ ነው ኃጢአትህን የምትደመስሰው የሚለው በክርስቶስ የደም መስዋዕት ላይ እንዳንታመን የሚያደርግ የሰይጣን ወጥመድ ስለሆነ አንቀበለውም።
ይልቅስ መጥምቁ ዮሐንስ እንዳለው በአዳኙ ስም ንስሐ ግቡ። ««ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት» (መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሐ ግቡ ማቴ ፫፤፩-፪)