Wednesday, April 10, 2013

«የአዲሱ ፓትርያርክ ዝምታ «የመጀመሪያው መጨረሻ» ወይስ የመጨረሻው መጀመሪያ?»



ዶ/ር ስቴፈን  ኮቬይ የተባለ ምሁር  «ስምንቱ ልምዶች» በተባለ መጽሐፉ ውስጥ እንዲህ እያለ ይጽፋል።  አእምሮው ውስጥ አስቀድሞ ያልተሰራ የቤት ሥራ ደብተርህ ላይ የራይት/ /እርማት አታገኝም። ልጅ በልጅነቱ ስታድግ ምን ትሆናለህ? ብለው ቢጠይቁት የሚናገረው  የመጀመሪያውን መጨረሻ  ርቆ  በመመልከት ነው።  የመጀመሪያውን መጨረሻ ለማሳመር አስቀድሞ  የመጨረሻውን መጀመሪያ  አእምሮው ውስጥ ዛሬ ሂሳቡን ሰርቶ መጨረስ አለበት።  አለበለዚያ ገና በልጅነቱ አርጅቷል ማለት ይሆናል። አእምሮ/ mental/ ሂሳቡን ማስላት ያለበት አሁን ነው።  ከዚያም ገሃዳዊው ዓለም/ Physical world / ከአእምሮው ጋር የሚቀናጅበት ሥፍራ ነው። አእምሮው ያልሰራውን ነገር ገሃዳዊው ዓለም ሰርቶ አይሰጥህም። በእርግጥ ዶ/ር ስቴፈን ትክክል ብሏል። መጽሐፍ ቅዱስም ይህች ዓለም ጥረን ግረን እንድንበላባት ነው የተሰጠችን እንጂ የምቾት ወንበር እንድናሞቅባት እንዳይደለ አስረግጦ ነግሮናል። እንዲያውም እሾህና አሜከላ የሞላባት እንጂ የተመቻቸች አይደለችም ይለናል።
አንድ ሰው ለራሱ ኑሮ አስቦ ለዚያ ስኬት መድረስ መጣር እንዳለበት ከተማመንን አንድ ሰው ከራሱ ኑሮ ባለፈ የብዙዎችን ኃላፊነት ተሸክሞ በሥሩ ያሉ ሚሊዮኖችን በማንቀሳቀስ ስኬትን ለማግኘት ምን ያህል የርእይና የዓላማ ሰው መሆን እንዳለበት ከጥያቄ የሚገባ አይደለም።
ከዚህ አንጻር ብዙዎች የታገሉለትና በስኬት ያጠናቀቁለት  የብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ የፓትርያርክነት ሥራ ሂደት እንዴት ይታያል? ብለን ልንጠይቅ ወደድን። በእርግጥ ቅዱስነታቸው ከተሾሙ ገና ቅርብ ጊዜ ነውና ብዙም ሊባል አይችል ይሆናል። ይሁን እንጂ  ዶ/ር ስቴፈን እንዳለው  የመጀመሪያውን መጨረሻ አይተን ለመገምገም  ብዙም አንቸገርም።  በትንሹ ያልተሰራ የቤት ሥራ ሲከማች እሰራለሁ ወይም ይቆይልኝ የሚል ተማሪ ቢኖር እሱ ትምህርቱን ያቆመው በአእምሮው ውስጥ ከመነሻው እንጂ ትምህርቱ ቤቱ በሚዘጋበት የዓመቱ መጨረሻ ላይ አይደለም። ከዚህም ተነስተን «የአዲሱ ፓትርያርክ ዝምታ «የመጀመሪያው መጨረሻ ወይስ የመጨረሻው መጀመሪያ» ብለን በርዕሳችን ጠይቀናል።
ይህንን ጥያቄ እንድናነሳ ያስገደደን ልክ በተሾሙበት ሰሞን የትምህርትና የአስተዳደር ጉዳይ ጥያቄዎችን ያነሱ የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎች ጩኸት እስካሁን አጥጋቢ ምላሽ ሳያገኝ ችግሩም በዐመጽ ወይም በሰላም ጾሙን ሊፈታ እነሆ እየተንከባለለ እኩለ ጾሙን አልፏል። ከዚህ ቀደም በዚህ ጉዳይ ላይ እንደጻፍነው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ችግር ድንገት የፈነዳ ሳይሆን እያመረቀዘ፤ ነገር ግን ሰሚ ያጣ ሆኖ በመቆየቱ የተነሳ ነው። ችግሮቹን አንድ ላይ ጨፍልቀን ብንመለከታቸው እንኳን ለመፍታት ያንን ያህል የተወሳሰቡና መፍትሄአቸው ከባዶች አልነበሩም። ዳሩ ግን ከባድ ያደረገው ርእይና ገቢራዊ እርምት መውሰድ የሚችሉ ሰዎች ስለታጣ ብቻ ነው። ይህንን ቀላል ነገር ለማስተካከል አዲሱ ፓትርያርክ አስቸኳይ  የማጣራት እርምጃ ተወስዶ ዝርዝሩ እንዲቀርብላቸው በማድረግ በዚያ ላይ የተንተራሰ አጭር መፍትኄ ለማስገኘት ትእዛዝ መስጠት ብቻ በቂያቸው ነበር።  ሳይጀምሩ የጨረሱ ያህል ቀላሉን ነገር አንድ ጊዜ በቪኦኤ መግለጫ ብቅ በማለት፤ አንድ ጊዜ ደግሞ በኮሚቴ ይታያል እያሉ በማንከባለል እነሆ ምንም የተጨበጠ ነገር ሳይታይ ወር አለፈው፤ በዚህ መልኩ ወራትም ይከተሉት ይሆናል። አሁን ደግሞ ተማሪ ማባረር እፎይ የሚያስብል እርምጃ ተደርጎ መወሰዱን እየሰማን ነው።
ተማሪዎቹ ወጪ ጨምሩልን፤ አካዳሚያዊ ነጻነት ይሰጠን፤ ሰላማዊ ሰልፍ ይፈቀድልን፤ በዲሞክራሲያዊ መብታችን እንጩህ አላሉም። በሚሰጠን ወጪ በአግባቡ እንድንመገብ ይደረግልን፤ የአስተዳደር ኃላፊዎቹ ሙሰኞች ስለሆኑ ይነሱልን፤ ብቁ መምህራን ይመደቡልን፤ ንጽህናችን እንዲጠበቅ የተቻለው ይደረግልን የሚሉ ጥያቄዎችን ነበር ያነሱት። እነዚህን ችግሮች አጣርቶ የመፍትሄ እርምጃ ለመውሰድ አንድ ወር ይፈጃል? ግቡ አትግቡ፤ ብሉ አትብሉ፤ የሚልስ ማስታወቂያ እስከመለቅለቅ ያስደርሳል? ፓትርያርኩስ ይህንን ቀላሉን ነገር ማስተካከል ካልቻሉ በጾሙ ሱባዔ ምክንያት አቤቱታ አቅራቢ ሁሉ በያለበት ክትት ብሎ የተቀመጠው፤ ወርኀ ጾሙ ሲያበቃ ከያለበት ሲወጣ እንዴት አድርገው ሊያስተናግዱት ይሆን? ምናልባት በወርኀ ጾሙ ያላዩትን የአቤቱታ ጋጋታ ጾሙ ሲፈታ እንዳይመጣባቸው የጾሙን ጊዜ ያስረዝሙት እንደሆነ እንጃ!
የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎች አቤቱታ ለምላሽ የዘገየው  ከሌሎች ጉዳዮች ጋር አያይዘውት እንደሆነ በባለሥልጣኖቹ ዘንድ እሳቤ አለ። በአንድ በኩል በአባ ጢሞቴዎስና አቡነ ሳሙኤል መካከል የተከሰተው የአስመራጭነትና የተመራጭነት ሽኩቻ እንደተዳፈነ ነው። መፍትሄውም ቅርብ አይመስልም። የተማሪዎቹን ጥያቄ ወደዚያ በመወርወር አባ ጢሞቴዎስ ራሳቸውን ከጥያቄው ለማውጣት የፓትርያርኩን ውለታ መላሽነት በመጠቀም ባሉበት ቦታ እንደሐቀኛ ሰው መቀጠል ይፈልጋሉ። በሌላ መልኩም ማኅበረ ቅዱሳን ከነጀሌዎቹ በተማሪዎቹ ጥያቄ ሽፋን ቅዱስ ፓትርያርኩ የጸረ ተሐድሶ ኑፋቄዎችን የሚቃወሙና ተስፋችን የሆኑ አባት ናቸው በማለት በሆዱ የሌለውን ፍቅር እየሰጠ በትር እንዲያርፍባቸው የተዘጋጁ ሰዎች ላይ ትልቅ ዱላ ይዟል። በአንድ ወገን ደግሞ እንደእናታቸው ጡት የሚጠቡትን ጥቅም እንዳያጡ የሚራወጡ ወሮበሎች የሚከላከልልላቸውን ምክንያት እየያዙ በዚያ ስር መደበቅ ይፈልጋሉ። እንግዲህ ትንሹ የተማሪዎች ጥያቄ የየራሱን ጥቅም ለማስከበር በሚፈልጉ ክፍሎች ምላሽ እንደሰማይ ርቆት ይገኛል። ወደፊትም ጠብ የሚል ነገር የለውም። ሁሉም አመራሮች ሳይጀምሩ የጨረሱ ርእይ አልባዎች ናቸውና መፍትኄው ቅርብ አይደለም። ሳሙና ይገዛልን፤ ንጽሕናው በተጠበቀ ሽንት ቤት እንጠቀም፤ የምግብ ወጪው በአግባቡ ይታይልን፤ መምህራን ይስተካከሉልን  ማለት ይህንን ያህል ዙሪያ ጥምጥም የሚያስኬድ አልነበረም። «አፍህ የት ነው ሲሉት፤ በጆሮዬ አልፎ» እንዳለው ጠማማ ሰው  የቅርቡን ትቶ ነገሩን ማወሳሰብ አግባብ አልነበረም።  ይሁን እንጂ የተወሳሰበውን ለመፍታት አሁንም አልረፈደም እንላለን። በዚህ ላይ የፓትርያርኩ እርምጃ አወሳሰድ ወሳኝነት አለው። በአጭር ጊዜ ጉዳዩን አጣርቶ መፍትኄ መስጠቱ ከባድ አይደለም። ከዚህ በፊትም «ፓትርያርኩ ከፊታቸው ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል» ብለናል። ወሮበላውን፤ ሥልጣን ናፋቂውን፤ አስመሳዩን፤ አለቅላቂውንና የቀሚሱን ጭራ የሚቆላውን ሁሉ መልኩን አይተው ካዳመጡት አንድም እርምጃ ወደፊት መሄድ አይችሉም እንላለን።
የመጨረሻው መጀመሪያ እንዳይሆን መጠንቀቅ ይጠቅማል።