Friday, April 26, 2013

ማኅበረ ቅዱሳን እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተሐድሶ ያስፈልጋታል የሚሉ ተሐድሶዎች!


ጽሁፍ፤ በተስፋ አዲስ (ይህ ጽሁፍ ከዚህ በፊት የቀረበ ነው)1
ክፍል አንድ
ተሐድሶዎች እነማን ናቸው?

ብዙ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ስሄድ የስብከት ካሴት ሳዳምጥ፤ የተለያዩ ሥነ ጽሑፎችን ሳነብ ፡ተሃድሶዎች ተሐድሶዎች፡ የሚል ጩኸት እሰማለሁ። በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥር የተቋቋመው ማህበረ ቅዱሳን የሚባለው ድርጅት አባላቱም ሆኑ አመራሮቹ ስለተሃድሶዎች በስብከታቸው እና በጽሑፋቸው ሁሉ በቀጥታም ሆነ በተዛዋዋሪ ሳያነሱ አያልፉም።
እኔም ተሐድሶዎችን ለማወቅ ብዙ ጥረት አድርጌአለሁ። ምን ዓይነት አቋም እንዳልቸውና የት እንደሚገኙ፤ አላማቸው ምን እንደሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማሳወቅ ፈለግሁ። እነርሱ ግን ተሃድሶ የሚለውን  ስም አይቀበሉትም።  እኔ ተሃድሶዎች ስል አንባቢ በሚገባው ቋንቋ ለመጠቀም እንዳሰብሁ ይረዳልኝ። ማህበረ ቅዱሳን የሚባለው ማህበርም ከተሐድሶዎች ጋር ያለውን ቅራኔ ለማቅረብ እሞክራለሁ። አንባቢ የራሱን ተቃውሞም ሆነ ድጋፍ እንዲሠጥ አንዳችም ሳልቀንስ እና ሳልጨምር ትክክለኛውን መረጃ ለማቅረብ እሞክራለሁ። መነሻየ ግን ከማህበረ ቅዱሳን እና ከተሐድሶዎች ሥነ ጽሑፎች ነው። የሁለቱንም ቡድን እንቅሥቃሴ በተከታታይ አቀርባለሁ መልካም ንባብ።
ተሀድሶ ማለት ይላሉ ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት የሚሉ ወገኖች ማደስ፣ መጠገን፣ ማጽዳት፣ ማለት ነው ይላሉ።ለምሳሌ ቤት ከተሠራ በኋላ ሳይታደስ ብዙ ከቆየ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ሊፈርስ ይችላል ስለዚህ ከመፍረሱ በፊት የሚደርግለት እንክብካቤ ቤቱን ያጸናዋል። እንደሸረሪት ድር፤ የጢስ ጠቀርሻ ያሉ ነገሮችም ከቤቱ ላይ ሊጠረጉ ይገባል። ማደስ ማለት ማፍረስ አይደለም በቤቱ ውስጥ ያለውን ቆሻሻ፤ ማስወገድ እና በፈረሰው በኩል መጠገን ነው በሌላ አነጋገር መሠረቱን ሳይነኩ እና ሳያናውጡ ጥንታዊነቱን እንደያዘ ቤቱን ማሳመር ማለት ነው።የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ብዙ ዘመን ከመኖሯ የተነሣ ብዙ ስሕተቶች ይገኙባታልና መጽዳት አላባት፤ ባህሉን ከሃይማኖቱ፤ ውሸቱን ከእውነቱ፤ ክፉውን ከደጉ መለየት አለባት የሚል ራእይ ያላቸውና ለዚህ ሌት ተቀን ያለ እረፍት የሚሠሩ ናቸው።
የሚገኙት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው ጳጳሳት፤ ቀሳውስት፤ ዲያቆናት፤ መምህራን፤ የድጓ፤ የቅኔ የቅዳሴ መምህራን የሰንበት ተማሪዎች፤ እንዲሁም ምእመናን ሁሉ ያሉበት የአስተሳሰብ ኃይል ነው። የታወቀ ማህበር ግን የላቸውም። አንዳንዶች ማህበር መሥርተዋል ። ኑራቸው እና ሥራቸው በዚያው በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ሲሆን በተለያየ ቦታ ጽ/ቤት እና በርካታ ማሰልጠኛዎች አሏቸው። በርካታ መነኮሳት እና ሰባኪዎች በነዚህ ቦታዎች ይሰለጥናሉ። ይህን ሁሉ እንቅሥቃሴ የሚያደርጉት ግን ቤተ ክህነቱ ሳይውቅ ነው። ቀሳውስቱ ስልጠናውን ከወሰዱ በኋላ በየቤተክርስቲያናቸው ሌሎች ቀሳውስት በመመልመል ያሰልጥናሉ። ከጳጳሳትም ውስጥ ለዚሁ ሥራ የሚውል በግላቸው ከፍተኛ እርዳታ ያደርጋሉ። ተሐድሶዎች ቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ቁልፍ ቦታና ስልጣን አላቸው። በተለይ በአሁኑ ሰዓት በየአብያተ ክርስቲያናቱ  ሚሊዮኖች በብዛት ይገኛሉ። በገጠር አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እና በገዳማት ሁሉ አሉ። ደሞዛቸውን የሚያገኙት ከዚያው ከቤተ ክርስቲያኒቱ ነው። ግን ከሌሎች የእምነት ድርጅቶችም እርዳታ ያገኛሉ ተብለው ይታማሉ። ተሐድሶዎች  እንደቀደምት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አማኞች እንጂ እራሳቸውን ተሃድሶ ብለው አይጠሩም።  ስማቸው በሥራቸው ምክንያት ከሚጠሏቸው ወገኖች የተሰጣቸው ነው። በቤተ ክርስቲያን ባሕላዊ ትምህርት ጥልቅ የሆነ ዕውቀት ያላቸው ስለሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱን ሁለንተና ደካማ ጎንም ሆነ ጠንካራ ጎን ለይተው የሚያውቁ ሊቃውንት ናቸው። የተሃድሶዎች እንቅሥቃሴ ከባድ እንቅሥቃሴ ነው ምክንያቱም እስከሞት ድረስ የቆረጡ ሲሆኑ ታላቅ ራዕይ ያላቸው ናቸው። በማኅበር መደራጀት ሳይሆን  በግል እያንዳንዱ አውቆ መስራት አለበት ስለሚሉ እዚህ ጋ ወይም እዚያ ጋር ናቸው ያሉት አይባልም። በአጭሩ የሌሉበት ቦታ የለም።
የማኅበረ ቅዱሳን ደጋፊ ነን የሚሉ ጳጳሳት ሳይቀሩ የዚህ ተሐድሶ የሚባለውን እንቅስቃሴ በስውር ይደግፋሉ። አሁን ባለው ሁኔታ ተሐድሶ የሚባሉት ክፍሎችን ከቤተክርስቲያኒቱ ማስወገድ በፍጹም አይቻልም። ከላይ እስከታች በተያያዘ ሰንሰለት የሚሰሩ ናቸው።


የተሃድሶ እንቅሥቃሴ በኢትዮጵያ መቼ ተጀመረ?
የተሃድሶ እንቅሥቃሴ በኢትዮጵያ የቆየ ታሪክ አለው። በጣም ጎልቶ የወጣው ግን በአስራ አምስተኛው መቶ[1430] ክፍለ ዘመን ነው። በአሥራ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ደቂቀ እስጢፋኖስ የሚባሉ ኃይለኛ የሃይማኖት ሰዎች ተነሥተው ነበር። እነዚህ ሰዎች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በዘርዓ ያዕቆብ የሚካሄደውን አምልኮ፤ ባዕድ አምልኮ አለበትና ይህን ሁኔታ አንቀበልም ብለው ለማስወገድ የተነሡ ነበሩ።
አባ እስጢፋኖስ የሚባሉት መነኩሴ በምሥራቅ ትግራይ በአጋሜ አውራጃ ስቡሐ በተባለ አውራጃ የተወለዱ ናቸው። አባታቸው በልጅነታቸው ስለሞቱ አጎታቸው አሳድገዋቸዋል። አባ ስጢፋኖስ በግና ፍየል በሚጠብቅበት ወቅት መንፈሳዊ ስሜት አደረበትና ያደገበትን መንደር ለቆ ቤተ ኢየሱስ በተባለች ሥፍራ መንፈሳዊ ትምህርቱን ጀመረ። ቤተ ሰባቸው ደግሞ ወታደር እንጂ ቄስ እንዲሆንላቸው ስለአልፈለጉ ከሄዱበት አመጧቸው። እርሳቸው ግን እንደገና ተመልሰው ለዲቁና የሚያበቃቸውን ትምህርት አጠናቀው በ18 ዓመታቸው ዲቁና ተቀበሉ። አባ ስጢፋኖስ ቤተ ሰባቸው ያወጣላቸው ስም «ሀደገ አንበሳ» ሲሆን መምህራቸው ግን ትጋታቸውን እና ትህትናቸውን አይተው እስጢፋኖስ ብለው ሰየሟቸው።
ከዚያም እናታቸው እርሳቸውን ለመዳር ስታወጣ ስታወርድ ባለችበት ሰዓት የሚከተለውን ቃል ተናግረው ወደ አባ ሳሙኤል ገዳም ሄደው ምንኩስናን ተቀበሉ። አባ ስጢፋኖስ ለእናታቸው የተናገሩት“ አባቴ በልጅነቴ ስለሞተ እግዚአብሔር አባት እና እናት ሆኖ አሳደገኝ ስለዚህ ሰው ሁሉ ወልዶ ላሳደገው ይገዛል እኔም ከልጅነቴ ጀምሮ ወልዶ ላሳደገኝ ለእግዚአብሔር እራሴን ማስገዛት ስለምፈልግ ከዛሬ ጀምሮ እኔን ማየት አትችይም እራስሽን ለእግዚአብሔር አስገዢ በሰላም ኑሪ” የሚል ነበር።[ ከገድለ እስጢፋኖስ]
አባ ስጢፋኖስ ብሉያትን እና ሐዲሳትን ከተማሩ በኋላ ነገሮችን ሁሉ ማስተዋል ጀመሩ መምህሩንም እንዲህ ሲሉ ጠየቁት “ ሃይማኖት መጻሕፍት እንደሚናገሩት ነው? ወይስ እንደ ሰው ልማድ” የሚል ነበር። መምህሩም «ሃይማኖትማ መጻሕፍት እንደሚሉት ነው» ብለው ሲመሉስላቸው «ታዲያ ይህ ሃይማኖት የሚመስል የሰው ልማድ ከየት መጣ» ብለው ሲጠይቁ «ይህማ ከራሱ ከሰው የመጣ ነው» ብለው መለሱላቸው። ከዚህ በኋላ አባ ስጢፋኖስ የእግዚአብሔርን ቃል ከሰው ልማድ እየለዩ ውሸቱን ከእውነቱ እያበጠሩ በማስተማር የራሳቸውን ደቀመዛሙርት ለብቻ ማደራጀት ጀመሩ። ያስተማሯቸው ደቀ መዛሙርት በራሳቸው ወዝ ሠርተው እንዲበሉ እንጂ ከሰው እንዳይቀበሉ ሥራ እያስተማሯቸው አትክልት እና ፍራፍሬ በማልማት ከራሳቸው አልፈው ለሌላው ህዝብ መትረፍ ጀምረው ነበር።
በዚህ ጊዜ የራሳቸው ጓደኞች መነኮሳት ትምህርታቸው ከእኛ የተለየ ነው፤ ልማዳቸውም የኛን የሚቃወም ነው በማለት ይከሷቸው ጀመር።ይህንም ክስ በዘመናቸው ንጉሥ ለነበረው ለዘርዓ ያዕቆብ አቅርበውት ነበር። ዘርዓ ያዕቆብ ከአጼ ዳዊት ቀጥሎ የነገሠ ሲሆን በልጅነቱ ግሸን ላይ ታሥሮ እንደኖረ ይነገርለታል ።ከዚያም ወደ ገዳም ገብቶ ከመነኮሰ በኋላ ምንኩስናውን ትቶ አግብቶ የነገሠ ሰው ነው።
ንጉሡ የተማረ ሰው ስለነበር ድርሰት መድረስ ዋና ሥራው ነበር። ከደረሳቸው ድርሰቶች ውስጥ ተምረ ማርያም  እና መጽሐፈ ብርሃን፤ የታወቁት ናቸው። ማህሌተ ጽጌ እና መጽሐፈ ሰዓታት በርሱ ዘመን በሊቃውንቱ የተደረሱ ድርሰቶች ናቸው። በኢትዮጵያ በ30ው ቀናት ውስጥ በርካታ በዓላት እንዲከበሩ አዋጅ ያወጀው አፄ ዘርዓ ያዕቆብ ነው። የእመቤታችን 33 በዓላት እንደ እሑድ ሰንበት እንዲከበሩ፤ የመስቀል በዓል ብሔራዊ በአል ሆኖ እንዲከበር እና ስለ መስቀል ክብር የሚናገሩ ድርሰቶች እንዲደረሱ ያደረገው ዘርዓ ያዕቆብ ነው።
ለማርያም ስእል እና ለመስቀል[ለመስቀለኛ እንጨት] ስግደት እንዲደረግ አዋጅ ያወጣው ዘርዓ ያዕቆብ ነው። አንድ ቀን ዘርዓ ያዕቆብ ታምረ ማርያምን ጽፎ ከአባ እስጢፋኖስ ገዳም በየሳምንቱ እሁድ እሁድ እንዲነበብ ከሚል ጥብቅ ትእዛዝ ጋር ይልከዋል። አባ እስጢፋኖስም መጽሐፉን በጥንቃቄ ካነበቡት በኋላ ይህ መጽሐፍ ከገዳማችን አይገባም መጸሐፉ ደቀ መዛሙርቴን የሚያሰንፍ ነው። ድንግል ማርያምንም አያከብርም፤ በማርያም ስም የተነገረ ባዕድ ትምህርት ነውና አልቀበለውም ብለው መልሰው ላኩለት።
በዚህ ጊዜ ዘርዓ ያዕቆብ በመጀመሪያ ይሰማው ከነበረው ክስ ጋር የሚመሳሰል ነገር አገኘና እጅግ ተቆጥቶ እስጢፋኖስን አስጠራቸው። ደብረ ብርሃን ላይ ትልቅ ጉባኤ ተደረገ ሊቃውንት ምእመናን እና መነኮሳት ከየገዳሙ ተሰበሰቡ። አባስጢፋኖስ እና ደቀ መዛሙርቱ በአንድ በኩል ተቃዋሚዎች እና አፄ ዘርአ ያዕቆብ በሌላ በኩል ቆመው ክርክር ተደረገ።
አፄ ዘርዓ ያዕቆብ እና ተከታዮቹ የሚሉት፦
ለማርያም እና ለሥዕሏ ስገዱ
ለመስቀል[ለመስቀለኛ እንጨት] ስገዱ
ለእኔም ለንጉሡ ስገዱ
ተአምረ ማርያምን ተቀበሉ ነው
የአባ እስጢፋኖስ እና ደቀመዛሙርቱ የሚሉት፦
“ኢንሰግድ ለባዕድ ዘእንበለ ለአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ” ትርጉም ለአብ ለወልድ እና ለምንፈስ ቅዱስ ካልሆነ በቀር ለአራተኛ አካል አንሰግድም።
የሰው እጅ ለሠራው ለስእልም ሆነ ለመስቀለኛ እንጨት ባዕድ አምልኮ ስለሆነ አንሰግድም አሉ። በዚህ ጊዜ አባ እስጢፋኖስ ከባድ ግርፋት ከደረሰባቸው በኋላ ታስረው በነበረበት ቤት አረፉ።ደቀ መዛሙርቱም ለብቻ እምነታቸውን ቢጠየቁ አባታችን ካስተማረን ንቅንቅ አንልም አሉ። እጅግ ከተገረፉ በኋላ እስከ አንገታቸው የሚደርስ ጉድጓድ ተቆፍሮ በዚያ ገብተው ፈረስ እና ከብት በጭንቅላታቸው ላይ ተነዳባቸው። ይህን ታሪክ በተምረ ማርያም  ምዕ፤ 12 ላይ እና በግድለ እስጢፋኖስ ማግኘት ይቻላል። በተለይም ፕሮፌሰር ጌታቸው በሕግ አምላክ በሚል እርስ የደቂቀ ስጢፋኖስን ገድል ስለ ተረጎሙት እርሱን በማንበብ በቂ መረጃ ማግኘት ይቻላል።

ሌሎች ተደብቀው የቀሩት የአባ እስጢፋኖስ ደቀ መዛሙርት ከያሉበት እየተፈለጉ እጅ እና እግራቸውን ተቆረጡ፤ አፍንጫቸውን ተፎነኑ፤ ሴቶች ማህጸናቸውን በእሳት ተጠበሱ። ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያም በፕሮፌሰር ጌታቸው መጽሐፍ ላይ በሰጡት አስተያየት በደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ የተፈጸመውን ግፍ ሂትለር በአይሁድ ላይ ከፈጸመው ግፍ ጋር አመሳስለውታል።
ደቂቀ እስጢፋኖስ ደቅ እና ቆራጣ የሚባል በጣና ደሴት አካባቢ መታሰቢያ አላቸው በትግራይ ደግሞ ጉንዳጉዴ የሚባል ገዳም አላቸው ።ይህ ገዳም በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሥር የሚተዳደር ሲሆን ተምረ ማርያም ግን እስከ አሁን ድረስ አይነበብበትም።
ደቂቀ እስጢፋኖስ በቤተ ክርስቲያኒቱ እስከ አሁን ድረስ እንደ መናፍቅ የሚወገዙ ሲሆን ምሥጢሩን የሚያውቁ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሰዎች ግን እንደ ሰማእታት እና እንደ ቅዱሳን ይቆጥሩአቸዋል።
ይህ የነ አባ እስጢፋኖስ እንቅሥቃሴ በጊዜው በነበረው የፖለቲካ የበላይነት ተዳፍኖ ቢቆይም ውስጥ ውስጡን ግን ሲሄድ እና ቀስ ብሎ ሲጓዝ የኖረ እንቅሥቃሴ ነው። ይህን ውስጣዊ እንቅሥቃሴ በርካታ ሊቃውንት በሥዉር ሲሳተፉበት ኖረዋል። ለምሳሌ ከነዚህ ሊቃውንት ውስጥ ጥቂቶች ከመጻሕፍቶቻቸው መረዳት እንደሚቻለው አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ፤ አለቃ ታዬ፤ አለቃ ብላቴን ጌታ ሕሩይ፤ ፤ አለቃ ገብሩ ደስታ፤ ዘመንፈስ፤ የሚባሉ ሊቃውንት ሲሆኑ በደንብ ወደ አደባባይ ካወጡት እና ከቤተ ክርስቲያን ከተገለሉት የቅርብ ሊቃውንት ውስጥ አለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ እና ጓደኞቻቸው ይገኙባቸዋል። የአለቃ መሠረት ስብሐት ለአብ ጓደኞች አሁንም በሕይወት ስለአሉ ስማቸውን መጽሐፍ አልፈለግሁም። እነርሱም ስማቸው እንዲወጣ አይፈልጉም። ዛሬም በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ በተለያዩ ሥራዎች ተመድበው ይገኛሉ። ከላይ ስማቸውን የጠቅስኋቸው ሰዎች የአባ እስጢፋኖስ ሐሳብ ነበራቸው። ይህን ለማለት ያስቻለኝ አሁን ያሉት ቤተ ክርስቲያን መታደስ አለባት የሚሉት ወገኖች ከሚያራምዱት አላማ ጋር መጻሕፍቶቻቸውን በማስታያየት እና የሕይወት ታሪካቸውን በማገናዘብ ነው።
የተሐድሶዎች ዓላማ ምንድን ነው?
ተሐድሶዎች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን መሻሻል አለባት ይላሉ። ራእያቸውም ቤተ ክርስቲያኒቱ በሐዋርያት እምነት ላይ የተመሠረተች በመሆኗ፤ የሐዋርያትን ትምህርት መከተል አለባት። አሁን የሚታዩት የሕዝብ ልማዶች እንደ ሃይማኖት ሆነው የሚታዩት ከዘርዓ ያዕቆብ ዘመን ጀምረው በኃይል እና በፖለቲካ የበላይነት የተጫኑብን እንጂ እውነተኛው እና ጥንታዊው የኦርቶዶክስ እምነት አይደለም ባይ ናቸው። እውነተኛውን ኦርቶዶክሳዊ ትውፊትንም ሆነ እምነትን የሸፈነ ልማድ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አለ። ይህን ቀስ በቀስ ሕዝብን በማስተማር መሰረቱን ሳያፈርሱ ውሸት የሆነውን ሁሉ እናስወግዳለን የሚል ራእይ አላቸው።
ተሐድሶ እንዲደረግ የሚፈልጉትም፦
1ኛ በአምልኮው ላይ 2ኛ በመጻሕፍቱ ላይ 3ኛ በአስተዳደሩ ላይ ተሐድሶ እንዲደረግ ይፈልጋሉ። ለዚህም መጻሕፍቶቻቸውን ማንበብ ይቻላል በርካታ መጻሕፍት አሏቸው። በገድላት፣ በድርሳነ ሚካኤል እና በድርሳነ ገብርኤል በድርሳነ ኡራኤልም ላይ በጠቅላላ በድርሳናቱ እና በገድላቱ ላይ ከፍተኛ የሆነ ትችታቸውን ጽፈዋል ወደ ፊት እናቀርበዋለን።
በአስተዳደር ላይ የሚያነሱት ጥያቄ ከማኅበረ ቅዱሳን ጋር ተመሳሳይ ነው።ልዩነቱ ማኅበረ ቅዱሳን አስተዳደሩ በራሱ ሰዎች እንዲያዝ የሚፈልግ ሲሆን ተሐድሶዎች ግን ለእውነት በቆሙ ሰዎች መያዝ አለበት በሚለው ነው።አስተዳደሩ መንፈሳዊ ካልሆኑ ሰዎች ተላቆ በተማሩ እና ፈሪሃ እግዚአብሔር ባላቸው ሰዎች ይመራ ባይ ናቸው። በአስተዳደሩ የሚፈጸሙ የዘረኝነት እና የሙስና አሠራርን አጥብቀው የሚቃወሙ ሲሆን በየቤተ ክርስቲያኑ በበዓል ቀን መንፈሳዊ ያልሆነ አሠራር እየተስፋፋ ነው። ይህም  የንግድ ሥራ እንጂ የእምነት ሥራ አይደለም በማለት አጥብቀው ይቃወማሉ። ጠንቋዮች በቤተ ክርስቲያኒቱ መታቀፍ የለባቸውም። ጠንቋይ የሆኑ የቤተ ክርስቲያኒቱ አገልጋዮች ባዕድ አምልኮን በማስፋፋት ትልቁን ሚና እየተጫወቱ ስለሚገኙ ይወገዱልን ባይ ናቸው። በዚህ እረገድ ማህበረ ቅዱሳንም ጠንካራ አቋም አለው። የቀረውን የእንቅሥቃሴያቸውን ታሪክ በሚቀጥለው አቀርባለሁ። ከኔ የቀረውን አንባቢ ቢያስተካክለው ደስ ይለኛል።
ክፍል ሁለት
ማህበረ ቅዱሳን

ማህበረ ቅዱሳን በደርግ ዘመን ለውትድርና እንዲሰለጥኑ በተመለመሉ የዩንቨርስቲ ተማሪዎች ብላቴን ላይ የተመሰረተ ማህበር ነው ይላሉ። ማህበሩ በተለያዩ የጻድቃን እና የቅዱሳን ስም በየአካባቢው የጽዋ ማህበር ሆኖ የቆየ ሲሆን ብዙ አባላቱ ዝዋይ ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ዘንድ እየተሰበሰቡ ይማሩ ነበር። ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ በሞቱ በዓመቱ የተለያዩ የጽዋዕ ማህበራት አባላት ሙት ዐመት ለማሰብ ተሰበሰቡ ከተሰበሰቡት አንዱ የስማቸው መታሰቢያ የሚሆን ማህበር እናቋቁም የሚል ሐሳብ ሲያመጣ ሁሉም የማህበራት አባላት በነገሩ ይስማማሉ። ነገር ግን ስም አወጣጡ ላይ አልተስማሙም ነበር። አንዱ ማህበረ ማርያም፤ አንዱ ማህበረ ተክለ ሃይማኖት፤ አንዱ ማህበረ ጊዮርጊስ፤ ሌላው ማህበረ ሚካኤል ወዘተ በማለት ሲከራከሩ፤ ብፁዕ አቡነ ገብርኤል ሁላችሁም በቅዱሳን ስም ነው የተመሰረታችሁት ለምን ሁሉንም ትተን “ማህበረ ቅዱሳን አንለውም” አሉ። ሁሉም ማህበራት በዚህ ተስማምተው ጸሐፊ እና ሊቀ መንበር መርጠው መሥራት ጀመሩ።
አባላቱ በብዛት የዩንበርስቲ ተማሪዎች ሲሆኑ በዘመናዊ ሙያ የበለጸጉ ዶክቶሮች፤ ሎዌሮች፤ ኢንጅነሮች፤ የተሰበሰቡበት ማህበር ነው። ከቤተ ክርስቲያን ባለሙያዎችም ጳጳሳት፤ ቀሳውስት፤ መምህራን፤ ዲያቆናት፤ በአባልነት አሉበት።በአባላት ብዛት፤ በአደረጃጀት፤ በኢኮኖሚ አቅም፤ የሚወዳደራቸው የለም።
ማህበሩ በተለያዩ ሀገሮች እና ከተማዎች ታላላቅ የንግድ ማዕከላት አሉት እያንዳዱ አባል አሥራቱን ለማህበረ ቅዱሳን ዋና ማዕከል ይክፍላል፤ የራሱ ሊቃውንት ጉባኤ፤ የልማት ክፍል፤ የትምህርት ክፍል፤ የራሱ ጽሕፈት ቤት፤ በየሀገረ ስብከቱ የራሱ ማዕከል አለው።
የማህበረ ቅዱሳን አባላት በዘመናዊ ትምህርት እንጂ በመንፈሳዊ እውቀት ብዙ የሚመሰገኑ አይደሉም። ነገር ግን ከማንኛውም የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን በብዙ ይሻላሉ። በቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳዊ እውቀት በኩል ከተሃድሶዎች ጋር ሲወዳደሩ የሰማይና እና የምድር ያክል ይራራቃሉ። ነገር ግን ለባህል ፤ ለቅርስ፤ እንዲሁም ለሀገራቸው እና ለአባቶች ወግ ያላቸው ቅናት ከፍተኛ ነው። ማንኛውም የማህበረ ቅዱሳን አባል ሥልጠናውን ከጨረሰ በኋላ ሦስት ዓይነት ከለር ያለው ክር ባንገቱ እንዲያደርግ ይሰጠዋል የማህበረ ቅዱሳን አባል መሆኑ የሚታወቀው በዚህ ነው። ይህን ሁኔታ የተመለከቱ ሰዎች ወደፊት ማህበረ ቅዱሳን የራሱን ቤተ ክርስቲያን መመሥረቱ የማይቀር ነው ይላሉ።
በአምልኮ ወደ ነፍሳት፤ ወደ መላእክት፤ መጸለይን፤ ለቅዱሳን እና ለመላእክት ሥእል መስገድን አጥብቀው ያስተምራሉ፤ ይጽፋሉ። በመጻሕፍተ አዋልድ አንዳድ ስሕተቶች እንዳሉባቸው ቢያምኑም ይህን ማሻሻል ያለበት ሲኖዶስ እንጂ እኛ አይደለንም ይላሉ። ይህን የሚሉት ጥቂት የማህበረ ቅዱሳን መሪዎች እንጂ ሌሎች ተራ አባላቶች ምንም ስሕተት የለባቸውም ብለው የሚያምኑ ናቸው።
የማህበሩ ዓላማ
ቤተ ክርስቲያንን በሙያቸው በነጻ ማገልገል፤ የቤተ ክርስቲያኒቱን ታሪክ በተለያዩ መንገዶች ለምሳሌ በኢግዚብሽን ማስተዋወቅ፤ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ወጣቱ በቤተ ክርስቲያን እንዲታቀፍ ሥልጠና መስጠት የሚል ነው። በመንግሥት ውስጥ ታላቅ ቦታ አላቸው እስከ አምባሳደር የደረሱ የማህበረ ቅዱሳን አባላት አሉ። በሥራቸው ትጉህ ናቸው፤ በገዳማት እና በተለያዩ ያሉ መምህራንን የገንዘብ እርዳታ ለመስጠት ጥረት ያደርጋሉ የአብነት ትምህርት ቤቶችን እንደገና በዘመናዊ መልክ ለማደራጀት ይታገላሉ፤
ሌላም ከዚህ ያለፈ ዓላማ እንዳለው ይታማል።
ማህበሩ የሚታማባቸው ዋና ዋና ነገሮች
የማህበሩ መሪ የነበረው — አንዱ ሰው ናዝሬት ላይ በሰይጣናዊ አሠራር ሰው ሊገድል ሲል በፖሊስ ተይዞ በመታሠሩ በማህበሩ ላይ ጥላ አጥልቶበት ነበር። ይህ ሁኔታ እስከ አሁን ድረስ ማህበሩን ጥያቄ ላይ የጣለው ነገር ነው። የማህበሩ መሪ ማርያም መሥዋዕት አቅርቡልኝ ስላለች አንድ ሰው ታንቆ መሞት አለበት በማለት አንዲትን ሴት አሳምኖ ኖሯል። በገመድ ተንጠልጥላ በመንፈራገጥ ላይ እያለች ፖሊስ ደርሶ ከሞት አትርፏታል።
ይህ ድርጊት በፖሊስ ፕሮግራም በኢትዮጵያ ተሌቭዥን በተከታታይ ሲቀርብ ነበር። ታሪኩ በመጽሐፍም ተጽፎ ይገኛል። በኋላ ግን ማህበሩ እንደምንም ብሎ ስሙን አደሰ። መንፈሳዊ ዝግጅት እያዘጋጀ መንፈሳዊ ጉዞዎችን እያደረገ አባላትን መስብሰብ ጀመረ። ይህን እንቅሥቃሴ በትኩረት የተመለከቱ አቡነ ቴዎፍሎስን ያስገደለው የታላጉ ጉባኤ አባላት ትኩረታቸውን ማህበረ ቅዱሳን አባላት ላይ በማድረግ ስድስት ኪሎ በሚገኘው ምስካየ ሕዙናን መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ግቢ እየነጠሉ በመሰብሰብ አላማቸውን አስቀይረዋቸዋል ይባላል። ማህበሩ የታላቁ ጉባኤ አባላት ከገቡበት ጀምሮ አቡነ ጎርጎርዮስን ለማሰብና ቤተ ክርስቲያንን ለመርዳት የነበረውን አላማውን ትቶታል የሚሉ አሉ።
ከተመሠረተ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለምሳሌ ሃይማኖተ አበውን ለማፍረስ ያደረገው እንቅስቃሴ እና ለአባላቱም የሚሰጠው ስልጠና በዋናነት “የመናፍቃን ምላሽ” የሚል ሆነ። በጽሑፉም ሃይማኖተ አበውን የሚያጥላላ ጽሑፍ እያሠራጨ ቆይቶ በደንብ ከተዘጋጀ እና እውቅና ካገኘ በኋላ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ቡድን በማደራጀት የሃይማኖተ አበውን አባላት እና ተሃድሶ ናቸው ያላቸውን ሁሉ በመደባደብ በማሳደዱ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን በአንድ ጊዜ ብቻ ከ60 ሺህ በላይ አባላቷን አጥታለች እየተባለ ይተቻል።
ሌላው ማህበሩ የሚታማበት ነገር ብዙ የሚያጠራጥር ነው በመጀምሪያ ቤተ ክህነቱን መቆጣጠር ሲሆን ቤተ መንግሥቱንም ማለፍ አይፈልግም ይባላል። የታላቁ ጉባኤ አባላት እንደ የበላይ ጠባቂ ሁነው የማህበሩ አማካሪ ናቸው፤ ማህበሩ አካሄዱን እንዲያሳምር ያደረጉት እኒህ የታላቁ ጉባኤ አባላት ናቸው አንዳዶች የሞቱ ሲሆን የተወሰኑት አሉ።[በጠቅላይ ቤተ ክህነት የሚዘጋጀው ጋዜጣ ዜና ቤተ ክርስቲያን እንደዘገበው]።
ማህበረ ቅዱሳን ምሥጢራዊ የሆነ የሥለላ ቡድን አለው። ይህ የስለላ ቡድን በዋነኛነት የሚሰልለው ተሃድሶ እና ተቃዋሚዎቼ የሚላቸውን ነው ተቃዋሚዎቹን ሁሉ ተሃድሶ ይላቸዋል። ነገር ግን ብዙዎቹ በከንቱ ነው ስማቸው የጠፋው ይባላል። ከዚህ በተረፈ ጳጳሳትን፣ ካህናትን፣ መነኮሳትን፣ ዲያቆናትን ኑሮአቸውን ሕይወታቸውን ይሰልላል ።የእያንዳንዱ ጳጳስና መነኩሴ የሕይወት ታሪክ፤ በቴፕ እና በቪዲዮ የተደገፈ መረጃ ይሰበስባል። ባማህበረ ቅዱሳን ላይ ያመጸ፤ አገልጋይ ቢኖር ይህ መረጃ ይሰጠውና አፉን እንዲይዝ ይደረጋል።
እያንዳዱ የደብር ጸሐፊ እና አስተዳዳሪ ሒሳብ ሹም፣ ቁጥጥር፣ ገንዘብ ያዥ፤ ሰባኪ፤ ወዘተ በሙሉ በማህበረ ቅዱሳን የመረጃ መረብ ውስጥ የገባ ነው። ከማህበረ ቅዱሳን ማምለጥ የማይቻል ነው። ሆኖም ተሃድሶዎችን ግን አልቻሏቸውም ከማህበረ ቅዱሳን አቅም በላይ የሆኑ ቢኖሩ ተሃድሶዎች ብቻ ናቸው። ምክንያቱም ተሃድሶዎች እጅግ በጣም ቁጥብ፤ በሙስና የማይገኙ ከመሆኑም በላይ ሥራቸውንም በዝግታ፤ በምስጢርና በአስተውሎት  ስለሚያካሂዱት ውስጥ ለውስጥ የሚቀጣጠሉ እና የተዳፈኑ እሳቶች ናቸው። አሁን አሁን ማህበረ ቅዱሳን እንደተሃድሶዎች ሆኖ ተሃድሶዎችን እየሰለለ ቢሆንም ተሀድሶዎችም ራሳቸው ደግሞ በማህበረ ቅዱሳን ውስጥ በስፋት ገብተው አንዳንድ ማዕከላትን ተቆጣጥረው ይገኛሉ። በአሁኑ ሰዓት የተሃድሶዎች እና የማህበረ ቅዱሳን ሁኔታ አሳሳቢ ነው፤ ነገሩ እየከረረ መጥቷል። ይህ ሁኔታ በቶሎ በሲኖዶሱ ሊፈታ ይገባል በማለት አስተያየታቸውን የሚሰጡ ብዙዎች ናቸው።
ክፍል ሦስት
በክፍል ሦስት የምናያቸው ደግሞ መሃል ሰፋሪ አገልጋዮችን ነው። እነዚህ መሃል ሰፋሪ አገልጋዮች በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ እውቅና ያላቸው መድረኩን ተቆጣጥረው የሚኖሩ፤ ዋና ዋና የገንዘብ ቦታዎች ላይ የተቀመጡ ጸሐፊዎች ሒሳብ ሹም ገንዘብ ያዥ፤ አስተዳዳሪዎች ናቸው። ማህበረ ቅዱሳንንም ሆነ ተሃድሶዎችን ይቃወማሉ የሚቃወሙትም ከጥቅማቸው የተነሣ እንጂ ለቤተ ክርስቲያን ስለተቆረቆሩ አይደለም።
እነዚህ ክፍሎች ምንም ዓይነት እራይ የላቸውም ማህበረ ቅዱሳን ወይም ተሃድሶ አይደሉም። ነገር ግን ጥቅም ካገኙ የማንኛውም ጥገኛ ሊሆኑ ይችላሉ የሚያስቡት ለሆዳቸው ብቻ ነው አንዳዶች የፖለቲካ [የኢሀዴግ] ጥገኞች ናቸው በዚም ጥገኛ የሆኑት የኢሃዴግ አላማ ግበቷቸው ሳይሆን ጥቅም ስለአገኙ ብቻ ነው። እነዚህ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘውን ጥቅም አግበስብሰው ዘወር ለማለት የሚሠሩ ደሞዝተኛ ናቸው። በቤተ ክርስቲያን የሚደረገውን ማንኛውንም መንፈሳዊ ነገር አያምኑበትም እራሳቸውን እንደ ሠራተኛ ስለሚመለከቱት መንፈሳዊ ነገር ጉዳይ አይሰጣቸውም።
በዝማሬ እና በስብከት ካሴት የሚታወቁ አንዳድ ሰዎችም ከዚህ ጎራ የሚመደቡ ናቸው። ስብከታቸውም ሆነ ዝማሬያቸው የሰውን ስሜት በመኮርኮር ብዙ ገንዘብ ለማግኘት የታሰበ እንጂ በሊቃውንት የተመረመረ እግዚአብሔርን ለማክበር የታሰበ አይደለም። እነዚህ ሰዎች ሕዝብ በብዛት ለሚወደው ጻድቅ፤ ቦታም ሆነ ታሪክ ይዘምራሉ ይህ ገንዘብ የሚያገኙበት ዘዴ ነው። እነዚህ ወገኖች ምንም ዓይነት እራዕይም ሆነ አላማ ፈጽሞ የላቸውም የሕዝቡን ልብ እና አእምሮ ቆልፈው የያዙት ግን እነዚህ ወገኖች ናቸው። በስብከታቸው ነቀፋ እና ስድብን ስለሚያበዙ፤ በተዘዋዋዋሪ ሕዝብ መናገር የሚፈራውን የልቡን ብሶት በአደባባይ ያለምንም ሐፍረት ስለሚናገሩ በቀላሉ እውቅና ያገኙ ናቸው አስተዋይ ሲመዝናቸው ግን እውቀትም ሆነ መንፈሳዊ ሕይወት የላቸውም እግዚአብሔርንም አይፈሩም። በነዚህም ላይ ጽሑፎችን እናቀርባለን! የኢትዮጵያ ሕዝብ ከነዚህ ውዥንብር ፈጣሪዎች ዘወር ብሎ፡ ማህበረ ቅዱሳንን እና ቤተ ክርስቲያን ተሃድሶ ያስፈልጋታል የሚሉ ሰዎችን ማዳመጥ አለበት እነዚህ ወገኖች ባለራእይ ናቸው።
መልካም የውይይት ጊዜ ይሁንልን!!