Sunday, March 3, 2013

ጥቁር ይሁን እንጂ ማንኛውንም ቀለም መቀባት ትችላላችሁ”

 (Addis Admas)
የዱር አራዊት ተሰብስበው ግብረ - ገብነታችንንና ሥነ-ምግባራችንን የሚያርቅ፣ መሠረታችንን የሚያበጅ፣ ደህና ጠባይ ያለው እንስሳ እንምረጥ ይባባላሉ፡፡
አንበሳ፤ የአራዊቱ ሁሉ ንጉሥ ነውና “ምርጫው ይሳካ ዘንድ ጦጣን፣ አህያንና ነብርን ስጡኝና የአመራረጡን ሥነ ስርዓት አስቀድመን እናበጃጀው!” ይላል፡፡ አራዊቱ፤ “መልካም ሀሳብ ነው፡፡ እነዚህን ሶስቱን ወስደህ ምከሩበት፡፡ አስቀድመህ ግን፤ ለምን እነሱን እንደመረጥክ ምክንያቱን አስረዳ” አሉት፡፡
አንበሳም፤
“መልካም፡፡ በአዘጋጅ ኮሚቴነት ሶስቱን ስመርጥ ሶስት ዋና ዋና ምክንያቶች አሉኝ፡፡ እጅግ አስፈላጊ የሆነው የሥራ ሀላፊነት፡-
አንደኛ - ብልሃተኛ መሆን ነው፡፡ ለዚህ ጦጣን መረጥኩ፡፡
ሁለተኛ - ሸክም የሚችል ትከሻ ያስፈልጋል፡፡ እንደምታውቁት ለዚህ ከአህያ የተሻለ መሸከም የሚችል አይገኝም፡፡
ሦስተኛ - ፈጣን መሆን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እንደነብር ጥይት የለም፡፡
ምክንያቴ ይሄ ነው፤ አለ፡፡ ጭብጨባው ቀለጠ፡፡
“ጥሩ፡፡ በሉ ምርጫውን አሳኩት” ተባሉ፡፡
አንበሳ አስመራጮችን ሰብስቦ “እህስ? እንዴት እናድርግ ትላላችሁ?” አለ፡፡
አህያ፤ “ማናቸውንም በሸክም ዙሪያ ያለ ሥራ ለእኔ ይሰጠኝ” አለች፡፡
ነብር፤ “በፈጣንነቴ የትኛውም የጫካው ድንበር ድረስ ሮጬ የተሰጠኝን መልዕክት አደርሳለሁ” አለ፡፡
አያ አንበሶም፤ “እሺ እመት ጦጣስ? ምን እናድርግ ትያለሽ? መቼም መላ የሚጠበቀው ካንቺ ነው?!” አላት፡፡ ጦጣም፤
“መቼም አያ አንበሶ! የአህያም ሥራ ሸክም መሆኑ በሙያዋ ነው፡፡ የነብርም ሩጫ የተፈጥሮ ክህሎቱ ነው፡፡ እጅግ ከባዱ ጥያቄ ግን በእኔና በእርሶ በጌታዬ በአያ አንበሶ ጫንቃ ላይ ነው የወደቀው፡፡”



ይሄኔ ነብሮ፤ “ምን አዲስ ነገር አለ አንቺ የምትጨምሪልን?” አለና ጠየቃት፡፡
አህያም፤ “ነገሩን ከማስተባበርና ምርጫው በሰላም እንዲያልቅ ከማድረግ በስተቀር ምን የምታከናውኑት ተግባር ይኖራል?” ሲል ጦጣን ጠየቃት፡፡
አያ አንበሶም፤ “እስቲ አትቸኩሉ! የጦጣን ብልህነት አጥታችሁት ነው አሁን? የምትለውን በጥሞና እናዳምጣት” አለ፡፡
ጦጢትም፤ “መልካም እኔ ልል የፈለግሁት፤ ምንም ዓይነት ምርጫ ቢካሄድ አንድ ወሳኝ ቁምነገር መኖሩን አንርሳ ነው”
ነብሮ፤ “እኮ ቁምነገሩ ምንድን ነው?”
አህያ፤ “እኮ ቁም ነገሩን ንገሪና?”
ጦጢት “ታገሡኛ! ዓመት አላወራ! ይሄውላችሁ፤ ወሳኙ ቁም ነገር - የሚመረጠው እንስሳ ማንም ይሁን ማ ለአያ አንበሶ አገዛዝ የሚመች መሆን አለበት!”
ነብሮ፤ “እሱማ ጥርጥር የለውም!”
ጦጢት ቀበል አድርጋ፤ “ስለዚህ” አለችና ቀጠለች፤ “ስለዚህ አሁኑኑ ማን መሆን እንዳለበት እንወስን”
ነብሮ፤ “ለምን እኛ እንወስናለን?”
ጦጢት፤
“1ኛ/ ጊዜ እንቆጥባለን
2ኛ/ አራዊቱ ማንን እንምረጥ እያሉ ግራ እንዳይጋቡ እናግዛቸዋለን
3ኛ/ ተመራጩ ብቁ ነኝ ብቁ አደለሁም፤ ተዘጋጅቻለሁ አልተዘጋጀሁም? እያለ ራሱን እንዳያስጨንቅና በፍርሃት ኃላፊነቱን አልቀበልም እንዳይል፤ ከወዲሁ እናመቻቸዋለን” ስትል አስረዳች፡፡
አያ አንበሶም፤
“ድንቅ ነው! እኔ ጦጢት አስመራጭ ትሁን ያልኩት ይሄንን ጭንቅላቷን አመዛዝኜ ነው! በእኔ እምነት መመረጥ ያለበት ዝንጀሮ ነው፡፡ በሰውና በእንስሳ መካከል ያለው እሱ በመሆኑ እሱ ይመረጥ! በቃ ተመካከሩና ማንን እንደምናስመርጥ ንገሩኝ፡፡ እኔ ትንሽ አረፍ ልበል” ብሎ እየተጐማለለ ወደ ማረፊያው ሄደ፡፡
(ሸክማችንን የሚያቀሉ ጦጣ አስመራጮች አይጥፉ)dejebirhan