«በአርባምንጭ የመድኃኔዓለም
ሕንፃ ቤተክርስቲያን ግንባታ ላይ በብፁዕ አቡነ ኤልያስና በምዕመናን መካከል ተፈጥሮ የነበረው ውዝግብ በዕርቅ ተደመደመ»
(
http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com)
በአርባምንጭ ከተማ በመሠራት ላይ የሚገኘው የመድኃኔዓለም ሕንፃ ቤተክርስቲያን ብፁዕ አቡነ ኤልያስ የሰሜን ኦሞ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ ሕዝብን ሳያማክሩ የዲዛይን ለውጥ በማድረጋቸው ምክንያት አለመግባባት ተፈጥሮ ግንባታው መቋረጡን ቀደም ሲል November 16, 2012 ባወጣነው ዘገባ መግለጻችን ይታወሳል፡፡
ለውዝግቡ መነሻ የሆነው የዲዛይን ለውጥ የመነጨው ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" ሲሆን "ማኅበሩ" አባሉ የሆነ አንድ ኢንጂነርን ከአዲስ አበባ ልኮ የሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ዲዛይን ባለ አንድ ጉልላት ክብ ሕንፃ እንዲሆንና ቀደም ሲል በሕዝብ ምርጫና ስምምነት ግንባታው ተጀምሮ የነበረው ባለሦስት ጉልላት ሕንፃ ቤተክርስቲያን እንዲቀር በመወሰኑ ነው፡፡
"ማኅበረ ቅዱሳን"ና አቡነ ኤልያስ ክብ ባለ አንድ ጉልላት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ዲዛይን የመረጡበት ምክንያት ጥንታዊና ትውፊታዊ ነው በሚል ሰበብ ሲሆን፣ ምዕመናን ግን ይህንን ተልካሻ ምክንያት ካለመቀበላቸውም በላይ ብፁዕ አቡነ ኤልያስ ሆን ብለው ከሀገረ ስብከታቸው በጀት በዲዛይንና በግንባታ ሰበብ ለ"ማኅበረ ቅዱሳን" ገንዘብ ለማስተላለፍ የሸረቡት ሤራ ነው ተብሏል፡፡
ለሕንፃ ቤተክርስቲያኑ ግንባታ የገንዘብና የጉልበት አስተዋፅዖ በማድረግ በባለቤትነት ሲንቀሳቀስ የነበረው የአርባምንጭ አካባቢ ሕዝብ እና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የአርባምንጭ ተወላጆች ቀደም ሲል በመረጥነውና በተስማማነው መሠረት ባለ ሦስት ጉልላት ሕንፃ ቤተክርስቲያን ካልተገነባ ምንም ዓይነት ተሳትፎ አናደርግም በማለታቸው ምክንያት በንትርክ ግንባታው ባለበት ቀርቷል፡፡
ይሁን እንጂ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ስልት ያላዋጣቸው አባ ኤልያስ ለምዕመናን ጥያቄ እና ፍላጎት አዎንታዊ ምላሽ ለመስጠት ሁኔታው ያስገደዳቸው ሲሆን፣ ከምዕመናን ጋር ባደረጉት ውይይትም እንዲያውም ዲዛይኑ ተሻሽሎ ባለ አምስት ጉልላት ካቴድራል ሕንፃ እንዲገነባ ከስምምነት መድረሳቸው ታውቋል፡፡
በሁሉም አጥቢያዎች በስፋት እንደሚታወቀው "ማኅበረ ቅዱሳን" የሕንፃ ቤተክርስቲያናትን ዲዛይን በማዘጋጀት ኪሱን እንደሚያደልብ በቅርብ የሚያውቁት ይገልጻሉ፡፡ ከዚህ አንፃር ዕርቅና ስምምነቱ አንድ ነገር ሆኖ፣ በተሻሻለው የባለ አምስት ጉልላት ካቴድራል ዲዛይንና ግንባታ ውስጥ የ"ማኅበረ ቅዱሳን" ተሳትፎ ምን ሊሆን እንደሚችል ለጊዜው የደረሰን መረጃ የለም፡፡
እግዚአብሔር፣ የአርባምንጭ እና አካባቢው ምዕመናን የጀመሩትን የባለ አምስት ጉልላት ታላቅ ካቴድራል ግንባታ ከፍጻሜ ለማድረስ ይርዳቸው!!!
አሜን!!!