Thursday, March 7, 2013

ግብጽ በአንበጣ መንጋ ተመታች!




በዘመነ ፈርዖን ግብጽን ከመቷት መቅሰፍቶች አንዱ የአንበጣ መንጋ ነበር። የአሁኑ የአንበጣ መንጋ በምን መቅሰፍትነት እንደተላከ ባናውቅም መንጋው ግን በግብጽ ምድር በዓባይ ውሃ የበቀለውን ብዙ ጋሻ መሬት አትክልትና ሰብል ጋጥ አድርጎታል። በየከተማው ውስጥ የተረፈረፈውን የአንበጣ መንጋ ሰብስቦ በማቃጠል ቅርናቱ አያድርስ ሆኗል።
 የግብጽ ፖለቲካ እየተናጠና ሥልጣኑ የእስልምናውን ጽንፍ በሚያራምዱ ክፍሎች የመውደቁ ነገር ተጋግሞ ረብሻና ሁከት ባስከተለው መዘዝ ዓመታዊ የቱሪስት ገቢዋ መጠን ከ12 ቢሊዮን ብር ወደ 4 ቢሊዮን ገደማ የመውረዱ ችግር ሳይለቃት ሰሞኑን አዝመራዋን እምሽክ ያደረገ በአንበጣ መንጋ መቷታል።

 ከታሪክ እንደምንማረው ግብጾች ኢትዮጵያን እንደስትራቴጂክ ጠላት ማየታቸው ያልተጠቀምንበት ዓባይ ወንዛችን ያመጣብን መዘዝ እንጂ በድንበር ይሁን በጉርብትና የምንዛመዳቸው ሆነን አይደለም። ለኢትዮጵያ የሚደግሱት ስውር  የሁከትና የብጥብጥ እጃቸው ሳይሰበሰብ ምንም ሳንነካቸው እዳቸውን እየከፈሉ መገኘታቸው ያስገርማል። ምንም እንኳን የማንንም ጥፋትና ውድቀት ባንመኝም፤ ሳንደርስባቸው እየደረሱብን በሚመጣባቸው መርገም እኛ ተጠያቂዎች አይደለንም።  
ይህ ግብጽን እየበላና እየበረረ በማቋረጥ ላይ ያለው የሰማይ ላይ ነፍሳት መንጋ ወደእስራኤልም እንዳይዛመት የእስራኤል መንግሥት በድንበሮቹ ዙሪያ የተባይ ማጥፊያ መርዝ እየረጨ ይገኛል። 

ግብጾችም ሳያስቡት የደረሰባቸውን ውርጅብኝ ለመከላከል እየታገሉ ይገኛሉ። አንዳንድ ሚዲያዎች በዓለም ክርስቲያኖች ዘንድ የሚታወቀው «የጌታ ጾም» የተባለው በደረሰበት ሰዓት ይህ መቅሰፍት በግብጽ ላይ መምጣቱ ለምን ይሆን? ሲሉ ይጠይቃሉ።  በእርግጥ እንደመጽሐፉ ቃል የምጥ ጣር የመጀመሪያ ምልክቶች አንዱ ይሆን? የሁላችንም ጥያቄ ነው።