- ቤተ ክህነትም አካባቢውን በፌዴራል ፖሊስ እያስጠበቀች ነው።
- የምግብ አቅርቦት ከተቋረጠባቸው ሦስተኛ ቀኑ መሆኑ ተሰምቷል።
በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የአስተዳደር ጉድለት፤ የትምህርት ጥራትና የመምህራን ብቃት ጉዳይ ተማሪዎቹን ለዓመታት እያስጨነቀ
የቆየና አቤቱታ ቢያቀርቡበትም መፍትሄ የራቀው ሆኖ መዝለቁ ይታወቃል። ሙስና የተስፋፋበት ሆኖ ቆይቷል። ለተማሪዎች ጥያቄ የሚሰጠው
ምላሽ ኃይል፤ ዛቻና ከትምህርት ገበታ ላይ ማባረር ሆኗል። ብዙ ጊዜ
የተነገረለትን የአስተዳደርና የመብት ጥያቄ ጉዳይ ቤተ ክህነት ጆሮ ዳባ ልበስ ከማለትዋም በላይ መፍትሄ ብላ የያዘችው ጉዳይ ጣቷን
ወደሌላ አካል መቀሰርና በሙስና ለበሰበሱ ሹመኞቿ ጋሻ በመሆን መከላከል ነው። አባ ጢሞቴዎስ የበላይ ጠባቂነቱን ወንበር እንደግል
ርስት ከተረከቡበት ጊዜ አንስቶ ተማሪዎቹ የተለያዩ ጥያቄዎችን ቢያቀርቡም ለተማሪዎቹ አንድም ነገር ጠብ ካለማለቱም በላይ ችግሩ
እንተንከባለለ ቀጥሏል።
ለተማሪዎች ቀለብ የሚወጣውን ወጪ አሸዋና ገለባ የሞላበት ዱቄት ከማቅረብ ጀምሮ ጥራቱ የተጓደለ አቅርቦት
መኖሩን ተማሪዎቹ ይናገራሉ። የመኝታቸው ንጽህና መጓደል፤ ብቃት ያላቸው መምህራን አለመኖር፤ ለጥያቄዎች መልስ የሚሰጡ የአስተዳደር
ሰዎች ማንነት የመሳሰሉትን ጩኸት እያቀረቡ ቢገኙም እስካሁን ለማዳመጥ የፈለገ አካል የለም። በቤተ ክህነት አመራሮች ይታይልን፤ ይመርመርልን
የሚል ድምጽ ከተማሪዎቹ ቢቀርብም የበላይ አካላቱ የተበሳጩ ይመስላሉ፤ የተሰጠውን ከሚመገብ በስተቀር የሚጠይቅ ተማሪ አንፈልግም
በማለት በማስታወቂያ ጋጋታ ተማሪዎቹን እያሸማቀቁ ነው።
ከሐሙስ 5/7/ 2005 ዓ/ም ጀምሮ ቤተ ክህነት የቅጣት እርምጃ በመውሰድ ምግብ ከልክላለች። ተማሪዎቹ ደግሞ ጥያቄያችን ምንም ይሁን ምንም
አዳምጡን፤ ጩኸታችንን ስሙንና ከዚያ በኋላ ፍረዱብን እያሉ እየጮሁ ይገኛሉ። ቤተ ክህነት ለጊዜው ጆሮ መስጠት አልፈለገችም። የአባ ጢሞቴዎስ የቅርብ ወዳጅ መሆናቸው የሚታወቁት አዲሱ ፓትርያርክም እልከኛና
ገታራ በሆኑት በአባ ጢሞቴዎስ ላይ ምንም ዓይነት አስተዳደራዊ ምርምራ
እንዲደረግ ይፈቅዳሉ ተብሎ አይታሰብም። ችግሮቹ ትክክል ይሁኑም የተጋነኑ ቀርቦ ማዳመጥና ተገቢ ነው የሚባለውን ወቅታዊ ምላሽ ለመስጠት
ተማሪዎቹን ለማነጋገር አስፈላጊ መሆኑን አምኖ ከመንቀሳቀስ ይልቅ አዲሱ ፓትርያርክ ከአባ ጢሞቴዎስ ጋር ባላቸው ወዳጅነትና በፕትርክናው ውድድር
ላይ ቀንደኛ ተፎካካሪ ለመሆን ሲንቀሳቀሱና ሳይሳካላቸው የቀሩት አባ ሳሙኤል በግቢው ውስጥ እንደመኖራቸው ጉዳዩን ከእሳቸው ጋር
ለማያያዝ የተፈለገ ይመስላል። ቤተ ክህነት ከተማሪዎቹ ጀርባ ሆነው ዐመጽ የሚቀሰቅሱ ኃይሎች አሉ በማለት ችግሯን ለመደበቅ ጣቷን
ወደሌላ ለመቀሰር የምትፈልግ ትመስላለች። ይሁን እንጂ የቅድስት ሥላሴ ኮሌጅ ተማሪዎች ጥያቄ ለዓመታት ሲንከባለል የቆየና መፍትሄ
ያጣ ጩኸት እንጂ ዛሬ ድንገት የተነሳ ነገር አይደለም።
በእውነቱ የምናውቀው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የግለሰቦች የገቢ ምንጭ ተቋምና የሙስና ማምረቻ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል። ቤተክህነት
የሌላትን ማቅረብ ባትችል እንኳን የሰጠችውን ገንዘብ እንዴት ሥራ ላይ እንደዋለ መከታተል ሲገባት ለጋጠወጦች ጋሻና መከታ መሆኗ
ያሳዝናል። የተበላሹ የአስተዳደር ሰዎች የሚያላግጡበት ተቋም መሆኑም ያሳዝናል። እየዘረፉ የራሳቸውን ቢዝነስ የፈጠሩና ላስጀመሩት
ቤት ማስፈጸሚያ የገቢ ምንጭ ያደረጉት እንዳሉ ሲነገር ቆይቷል። በገንዘብ ነክ ክፍል ትሰራ የነበረች አንዲት ሴት የሚበቃትን ዘርፋና
አስዘርፋ ከ60 ሺህ ብር በላይ ከፍላ ከዓመታት በፊት ወደውጪ ሀገር መኮብለልዋ አይዘነጋም።
ተማሪዎቹ እየጮሁ ያሉት ለቤተ ክርስቲያናቸው ነው። እናታቸው ደግሞ የልጆቿን ጩኸት መስማት ይገባታል።
የምትችለውንና ተገቢውንም መፍትሄ መስጠት ይገባታል። ከዚህ በፊት በዚህ ዓይነቱ ተያያዥ ጉዳይ ላይ ሟቹ ፓትርያርክ ብዙ ሲወቀሱበት
ነበር። ትክክልም ሰሩ ጥፋት፤ እሳቸው ዛሬ የሉም። ያለፈውን መውቀስ
የተሻለ ተግባር ከሌለው ባዶ ጩኸት ይሆናል። አዲሱ ፓትርያርክ ከፊታቸው
ብዙ ሥራ ይጠብቃቸዋል፤ ያልነውም አለምክንያት አይደለም።