Wednesday, March 13, 2013

ማኅበረ ቅዱሳንን የምንወቅሰው በግብሩ እንጂ ማኅበር ሆኖ ስለቆመ አይደለም!




ብዙዎች ስለማኅበረ ቅዱሳን በምንጽፋቸው ጠጣር መልዕክቶች  በጣም ሲያዝኑ እንመለከታለን።  በኢሜል ወቀሳና ከዚያም ሲያልፍ ስድብ የሚልኩልን አሉ። በጽሁፎቻችን ውስጥ ማኅበሩን ነካ ባደረግን ቁጥር የሚያማቸውና ጸያፍ አስተያየቶችን የሚሰጡንም አጋጥሞናል። አንዳንዶች ስለማኅበረ ቅዱሳን የምንጽፋቸውን  እውነትነት አላቸው  ብለው እንደሚቀበሉን ሁሉ ተቃራኒውን አመለካከት እንደተለየ ሃሳብ ቆጥረን በአክብሮት እኛም ስንቀበላቸው ቆይተናል። ወደፊትም እንደዚሁ! የሃሳብ ልዩነት በዱላ ማስገደድ እስካልተቀላቀለበት ድረስ ለበጎ ነው እንላለን።  እኛ የሚታየንና እውነት ነው ብለን የተቀበልነው ነገር ለእነርሱ እንደስህተት ቢቆጠር አያስገርምም። እኛም ያላየንላቸው የእነርሱ እውነት ሊኖር እንደሚችል አስበንላቸው ተቃራኒ ሃሳባቸውን እናከብራለን። በዚሁ መንገድ የሁለት ወገን እሳቤን ተቀብለን ወደተነሳንበት ርዕሰ ጉዳይ እናምራ።
ማኅበረ ቅዱሳን እንዴት ተመሠረተ? ብለን የዓመታቱን መታሰቢያ የልደት ሻማዎችን ለመለኮስ ወይም አስልቺ የሆነውን የልደት ትረካ በመዘብዘብ ጊዜ ለማባከን አንፈልግም። ግብሩን ለመናገር ጥያቄዎችን እንጠይቅና እንመርምር።

፩/ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱ  የእውቀት ገበታ ነው ወይ?

ማኅበረ ቅዱሳንን እንደምናየው በጠለቀ ደረጃ ባይሆንም በተወሰነ መልኩ በቤተ ክህነቱ የአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ ያለፉ ሰዎችን ለመያዝ ሞክሯል። አብዛኛው ግን የቤተ ክርስቲያን ፍቅር ያቃጠላቸው እንደሆኑ የሚናገሩ የሰንበት ት/ቤት አባላትን ያቀፈና ዘግየት ብሎም ከሰንበት ት/ቤትም ሆነ ከፈለገ ሕይወት ት/ቤት ቅርበት ያልነበራቸውን ለመያዝ የሞከረ እንደሆነ ይታወቃል።  ይህንና ይህንን የመሳሰሉ ሰዎችን ይዞ እየተጓዘ እዚህ የደረሰው ማኅበር በነማን ምን ሰራ? ምንስ አበረከተ? የሚለውን  ልክ ስንመለከት ማኅበሩ እንዳዋቀሩት ሰዎች የማንነት ደረጃ አለኝ የሚለውን  የእውቀት ልክ ከነድርጊቶቹ እንመዝናለን እንጂ ዝም ብለን በጥላቻ አንፈርጅም። 

  ከዚህ አንጻር ማኅበሩ ሌላውን የሚመለከትበት ዓይን ራሱን ባዋቀረበት አቅምና ባለው የእውቀት ልክ ሳይሆን ነገሮች እየገጠሙ ስለተጓዙለት ብቻ ራሱን የቤተ ክርስቲያኒቱ የእውቀት ገበታ አድርጎ ማስቀመጡ አስገራሚ ይሆንብናል። በማኅበረ ቅዱሳን ሠፈር ራስን በማሳበጥ የእውቀትና የቤተ ክርስቲያኒቱን ትምህርት አብጠርጥሮ የማወቅ ችግር እንደሌለ ትልቅ ሥዕል አለ። መድረክ ላይ ቆሞ የማስተማር  እድልና  የእውቀት ጥማት ባላቸው ብዙ ምእመናን ጉባዔ ላይ ተገኝቶ የመናገር እድል በመግጠሙ ብቻ ማኅበሩ የእውቀት ርካታ የማካፈል ብቃት እንዳለው አድርጎ ራሱን አግዝፎ  ማየቱን ስናይ ይገርመናል። ብዙዎቹን የማኅበሩ አንጋፋ ተናጋሪዎቹን ትምህርት በአካልና በድምጽ ወምስል መልዕክት ማስተላለፊያ መንገዶች የማየት እድሉ ነበረን። አንዳንዶቹ የእውቀት ሳይሆን የንግግር ችሎታ ያላቸው ናቸው። አንዳንዶቹ የእውቀትም፤ የንግግር ችሎታ የሌላቸው ነገር ግን እድል የከነፈችላቸውና የሰው ወፍ የሚረግፍላቸው  ስለሆኑ ብቻ መምህራን መሆናቸውን ለራሳቸው የነገሩ ናቸው። አንዳንዶቹ እውቀት ያላቸው ቢሆኑም  ነገር ግን እውነቱን በማጣመም ልክፍት የተያዙ ጠማማዎች ሲሆኑ  አረፋ እየደፈቁ ለጉባዔ ሲናገሩ ከማንም በላይ የደረሱበትን እውቀት የሚያስተምሩ ይመስላቸዋል። ሌሎቹም እውቀቱ እያላቸው ለማስተማር የማይፈልጉ  ጥገኞች/Parasitic/ ሆነው ተጎልተዋል። ከምንም ከምኑም  ውስጥ የሌሉ ነገር ግን ክፋትና ሴራ በመጎንጎን የተካኑ የጥፋት መንፈስ ያሰገራቸው ሰዎችንም ተሸክሟል።

 እንግዲህ እነዚህ ሁሉ ባሉበት ማኅበር ውስጥ በተለየ መደብ በቅንነት፤ በየዋህነትና በእምነት የተሰለፉ አያሌዎች ደግሞ የማኅበሩ ቀኝ እጅ ሆነው እያገለገሉ መገኘታቸው እውነት ነው።  አለማወቅ በራሱ ችግር ቢሆንም ቅኖችና የዋሃን ከማኅበሩ ጋር በመቆማቸው የማኅበሩ ድክመት እንደጥንካሬ  በመቆጠሩ ብቻ ቅን ማኅበር ነው ሊሰኝ አይችልም።


 የቱንም የሰው ሰልፍ ቢሸከም ራሱን ለማቆየት ሌላውን እስካልተጫነ ድረስ ለእኛ ጉዳያችን አልነበረም። ችግሩ የሚነሳው በቤተክርስቲያን ውስጥ ራሱን የእውቀት የመጨረሻ ጥግ አድርጎ ማስቀመጡና ሁሉ ሊመገበው የሚገባው የእውቀት ማእድ በእጁ እንዳለ የሚያስብበት መንገድ ነው ተቀባይነት የማይኖረው።
ማኅበረ ቅዱሳን ካሰባሰባቸው ሰዎች ዓይነትና ደረጃ አንጻር ስንመዝነው ከቤተ ክርስቲያኒቱ አስተምህሮና የተግዳሮቶች ልክና መጠን ጋር በፍጹም መቀራረብ የማይችል ስብስብ ነው። ራሱን ያስቀመጠበትን ስፍራ የሚለካው በቤተ ክርስቲያን የአስተዳደር ድክመቶችና የስብከት ደረጃ እያደገ አለመሄዱ፤ ጥቅመኝነት እያየለ በመምጣቱ የተነሳ  ድምጹ የተሰማለት ማኅበር ለመሆን በመብቃቱ እንጂ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱ የእውቀት ገበታ ለመሆን ቀርቶ ራሳቸውን ማዳን የቻሉ ሰዎች ስላሉበት አይደለም። 

የስብስቦቹን ማንነት ለማሳየት እንደተሞከረው ሁሉ አጋጣሚው የፈጠረላቸውን አጋጣሚ ተጠቅመው ያዳበሩትን የንግግርና ሰው ፊት ቆሞ የመናገር ዓይ ነጥላቸውን የመግፈፍ ብቃት ካልሆነ በስተቀር ቤተክርስቲያኒቱ ከ፬ኛው ክ/ዘመን እስከ ፲ኛው፤  ከዚያም ከ፲ኛው እስከ ፲፭ው ክ/ዘመን ድረስ ያለውን ከዚያም እስከ ዕሥራ ምዕት መባቻ ድረስ ያለውን የቤተ ክርስቲያኒቱን እድገቶች፤ ጉድለቶች፤ እንከኖችና ተግዳሮቶች በመተንተን ምን ቀረን? ምንስ ሞላልን? ለማለት ብቃት ያለው አይደለም። በተለይም ወንጌልን ከስሙና ከማነብነቡ በላይ አውቀው የሚኖሩበት፤ ኖረውበትም የሚያውቁት ስለመሆኑ እንዲሁም አምልተው፤ አስፍተው ካስተማሩ አበው መምህራንና  ከቃለ ሐዋርያት ጋር የጠለቀ ቁርኝት እንዳላቸው ምስክር የሚሰጥባቸው አይደሉም። ይልቁንም  ይህ ነገር ጆሮአቸውን ስለሚያሳክካቸው ትውፊትና ባህል ላይ ሙጭጭ ብለው መጣበቅ የሚወዱ መሆናቸውን እናውቃለን።  ተረትና ምሳሌ የሚጥማቸው፤ እንደረበናተ አይሁድ የማይኖሩበት የሙሴ ሕግ የሚያቃጥላቸው፤ ትንኝን የሚያጠሩ ናቸው።  ወንጌልን፤ ከስሜት ቴኦሪ ለይተው ማየት የማይችሉ በመሆናቸው አውቀናል ብለው ባስቀመጡት ከረጢት ውስጥ ሁሉም እንዲገባላቸው የሚፈልጉ ናቸው። የማኅበሩ ሰዎች ከፍተኛው የእውቀት ጣሪያ ላይ ስለደረሱ ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅና በዚያ እውቀታቸው ልክ እንድትራመድ የማድረግ ትልቅ የምኞት ተስፈኞች ስለሆኑ ሌላውን አፈንጋጭና ሴረኛ አድርገው መፈረጅ ይቀናቸዋል። ራሳቸውን እንደፈጥኖ ደራሽና እንደቀድሞ አዋቂ አድርገው ስዕላቸውን አግዝፈው በማስቀመጥ ተመልሰው በማየት ብቁ ነን በማለት የሚኩራሩ ናቸው።  ለቤተ ክርስቲያኒቱ ሁለተናዊ እድገትና  ጥበቃ ሁሉም አባል መሰለፍ ያለበት እንደመሆኑ መጠን  ማኅበረ ቅዱሳንም እንደማኅበር ለዚህ ዓላማ መቆሙ በመልካም ጎኑ ቢታይ ችግር የለውም። 
ጥያቄው የሚነሳው ግን ከቤተ ክርስቲያኒቱ  ምሉዕ ከሆነ የእውቀት ማዕድ ያልዋለበትን ቦታ ራሱን አስቀምጦ ሁሉም በኔ በኩል ይለፍ የሚለው አባዜ ግን አቅሙን የማያውቅ አድርጎታል።

 መናፍቅና ተሀድሶ ብሎ ዘወትር የእርግማን አፉን የሚከፍትበት ጽጌ ስጦታውን በየመድረኩ እያነሳ እድሜውን ሙሉ ሲያላዝን አያፍርም።  ስንት ዓመት ሙሉ የሚያወግዘውን ሰው፤ ማኅበሩ አለኝ ከሚለው የእውቀት ጎተራ ውስጥ እየሰፈረ ጽጌን ለመመለስ የ፴ ደቂቃ መድረክ ቢጠየቅ ግን ሊያገኘው በጭራሽ አይፈልግም። ቤተ ክርስቲያኒቱ ጽጌን አውጥታ ከጣለችና ከረሳች ቆይቷል። ማኅበሩ ግን መባነኑ ሁሉ የሚታየው ጽጌ በሚባል መንፈስ ነው። ወይ ጽጌ ከእውቀት ማጣት የተነሳ ጠፍቷል፤ አለያም ማኅበሩ ከእውቀት ማጣት የተነሳ ጽጌን አጥፍቷል። ከሁለት አንዱ ሊሆን የግድ ነው። ነገር ግን ማኅበሩ እድሜውን ሙሉ ጽጌ፤ጽጌ ሲል መኖሩ የእውቀት ጉደለቱን እንጂ ሙላቱን አያሳይምና ሁሉም በኔ ማረጋገጫ ይለፍ የሚለው አዋቂነቱ መዳኛ የሌለው በሽታ ነው። ጽጌ እያሳመነ አስክዷል እያሉ ከማላዘን ይልቅ መንጋ ሁሉ አባል ያለው ማኅበር ተሰብስቦ የአንዱን የጽጌ ያህል አሳምኖ ሰው መመለስ ለምን አቃተው? የሌለ እውቀት ከየት ይመጣል።

ስናጠቃልል በንዑስ ርዕሳችን ያነሳነውን ጥያቄ ደግመን እንቋጨው። ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱ የእውቀት ገበታ ነው ወይ? ብለን እንጠይቃለን። በብዙ አስተማሪ ተብዬዎቹ አንደበት የምንሰማቸው ትምህርቶች ጆሮን የሚሞሉ ከመሆን አልፈው በልብ ሰሌዳ ላይ ተጽፈው የሚቀሩ አይደሉም። ስለዚህ ማኅበረ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያኒቱ የእውቀት ገበታ መሆን ይቅርና ተምሮ ለመረዳት ብዙ ዘመን የሚፈጅበት የሰነፍ ተማሪዎች ስብስብና ለማወቅ የእልከኝነት መንፈስ ጠፍንጎ ያሰራቸው ሰዎች የሞሉበት ሥፍራ ነው። 

  አንድ ጥሩ ማስረጃ እንናቅርብ። ወደመቀያየም ሳይደርስ በፊት ቀንደኛ የማኅበሩ አባልና በእውቀት ያይደለ ባለእድለኛ ተናጋሪ ዲ/ን ዳንኤል ክብረት ሳን ጆሴ/ ካልፎርኒያ በሚገኘው ቅ/ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተገኝቶ  ሴቶች በወር አበባ ወቅት ስላላቸው የርኩሰት ጉዳይ በጉንጩ ከሞላው እውቀት ውስጥ ቆንጥሮ የሚያቀርብ መስሎ ለመታየት ሞክሮ ነበር። ሴቶች ቤተ ክርስቲያን መግባት የተከለከሉት ወር አበባቸው እንደርኩሰት ስለሚቆጠር ሳይሆን ባንድ ቤተ መቅደስ ሁለት ደም መፍሰስ ስለሌለበት ነው ሲል ተደምጧል።። ፍትሐ ነገሥት የተባለው የጥንቱ የሕግ መጽሐፍ ይሁን የቤተ ክርስቲያኒቱ ኦሪታዊ አስተምህሮ እንደሚያስረዳው ግን ሴት በወር አበባዋ ወቅት ምንም ዓይነት አስተማማኝ መከላከያ ብትጠቀምም መግባት አትችልም የሚለው ጥንታዊውን ሕግ ተከትሎ ክርስትና ለማስነሳት ወንድ ከሆነ ፵ ቀን፤ሴት ከሆነች ፹ ቀን እንኳን ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከአጸዱም መግባት የምትከለከለው ከርኩሰቷ እስክትነጻ የሚያዘውን የዘሌዋውያን ፲፪፤፪-፮ ሕግ ለመፈጸም እንጂ ሌላ የአዲስ ኪዳን ሕግ ስላለ አልነበረም። የወለደች ሴት እስከ ሰማንያ ቀን  ድረስ የሚፈሳት ደም ስለሌለ ከርኩሰት ጋር ካልተያያዘ በስተቀር የዳንኤል ስለሁለት ደም መቅደስ ውስጥ አይፈስም የሚለው ትረካ ዋጋ የሌለው ፈጠራ ከመሆን ያለፈ አይደለም።   
አንድም የኦሪቱ ጥቅስ መቀመጡ ስህተት ይሆንና የዳንኤል አዲስ ትምህርት ተቀባይነት ይኖረዋል አለበለዚያም ቤተ ክርስቲያን ያስቀመጠችው ስለመንጻትና አጸድ የመግባት የክልከላ ሕጎች መሠረት የማኅበረ ቅዱሳኑ ሊቅ የዳንኤል ተረት ውድቅ ይሆናል።  እንግዲህ እነዚህ ናቸው የማኅበረ ቅዱሳን የእውቀት ጥግ መምህራንና ሌላውን ለመመዘን የቤተ መቅደሱ ሚዛን ነን ብለው  ራሳቸውን አስቀመጡ። ከየት የተገኘ  ትምህርት ነው? ብልን ጊዜና ወቅት አሰልጥኖ ካስቀመጣቸው ዐውደ ምሕረት የተፈበረኩ በመሆናቸው ብቻ የቤተ ክርስቲያኒቱ የእውቀት ሙላት አድርገው ራሳቸው ሰየሙ እንላለን። የእነብርሃኑ አድማስንና የሌሎቹን ዘራፍ ትምህርት ሰምተን ከቤተ ክርስቲያን አስተምህሮና የልብ ምኞታቸው ጋር እያዛመድን ብናስቀምጥ እጅግ የሚዘገንን ነገር እንሰማለን። ምናልባትም ሌላ ጊዜ በማስረጃ አስደግፈን እንመለስበት ይሆናል። 

2/ ማኅበረ ቅዱሳን ራሱ የማነው?

ማኅበረ ቅዱሳን ራሱን የቤተ ክርስቲያኒቱ የእውቀት ሙላትና ጥግ አድርጎ በማስቀመጡ የተነሳ ያለው ጉድለትና እክል ለብዙዎች ውድቀትና የድጥ ጉዞ  ምክንያት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሌላው ችግር ራሱ ማኅበረ ቅዱሳን የተባለው ድርጅት የማነው? የሚለው ጥያቄ ግራ ያጋባናል። ሲቋቋም ጀምሮ ማኅበሩን ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገኛል ብላ ያቋቋመችው አይደለም። ራሱ የሕይወት ታሪኩን በሚተነትንበት መድረክ ሁሉ የተቋቋመው በራሱ ትግልና ጥረት እንጂ በቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ ውሳኔ አይደለም። ይህንን ትልቅ ጉድለት ለመሸፈን በእነ የጉድ ሙዳዮች በኩል የቤተ ክርስቲያኒቱን ጥቅም የሚጎዳ፤ ማኅበሩን ደግሞ መንትያው እንደሞተበት የአንበሳ ግልገል የእናቱን ጡት ያለተቀናቃኝ እየጠባ እንዲፋፋ ያደረጉበትን ሕግ አስጸድቀው ማውጣታቸው ካልሆነ በስተቀር ቤተ ክርስቲያን ፈልጋ የተከለችው አይደለም። እሱም ቢሆን የሚለው ቤተ ክርስቲያን ተከለችኝ ሳይሆን የዳቦ ስሜን አቡነ ገብርኤል አወጡልኝ ነው። ከዚህ አንጻር ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ የተቋቋመ፤ ያቋቋሚዎቹ መሳሪያ ነው ማለት ነው። ይህ ግልጽ እውነት መሆኑ እርግጥ ነው።

 በአንድ ወቅት አባ ሠረቀ ብርሃን ወ/ሳሙኤል የቤተ ክርስቲያኒቱ እውቅና አለኝ ካልክ የሂሳብ ምርመራ እናድርግልህ ቢሉት በጉድ ሙዳዮች በኩል አመቻችቶ ራሱ ያዘጋጀውን መተዳደሪያ ደንብ ጠቅሶ ራሴን ደስ ባለኝ የንስሐ አባቴ በኩል አስመርምሬአለሁ ሲል መመጻደቁ አይዘነጋም። የተቋቋመበትን ዓላማ የሚጻረር ስለሆነ ሰርስረውና ፈርፍረው አባ ሠረቀን ከፊት ለፊታቸው ነቅለው ለመጣል ችለዋል። ከፊታቸው ያለውን ስጋት ገለል ማድረግ ከቻሉ በኋላ በአባ ሠረቀ ብርሃን ላይ ሲወርድ የነበረው የተሐድሶ የስድብ አፍ ወደአፎቱ ተመልሷል። አሁን እንዲያውም የአባ ሠረቀ ብርሃን ጉዳይ ተረስቷል። በተፈገለበት ሰዓት የተጠቀሙበት የክስ ፋይል አገልግሎቱ እንዳበቃ ወዲያው ተዘጋ። ምናልባት አባ ሠረቀ ብርሃን አንድ ቀን ወደአስጊ ሥልጣን ማማ ላይ ብቅ ሲሉ ያኔ ደግሞ የተወለወለው የማኅበሩ ሠይፍ ከአፎቱ ሲመዘዝ  እናይ ይሆናል።

 የማኅበሩን ገንዘብ እስኪበቃቸው የተጠቀሙበት እንዳለ ይወራል። የተወራውን ደግሞ ውሸት ነው እንዳንል የሚያደርገን የቤተ ክርስቲያኒቱን የሂሳብ ምርመራ እንደጦር የሚፈራበት መንገድ ነው። ምን ያለበት ዝላይ አይችልም እንዲሉ ሆኖ ማኅበሩ ውስጠ ምስጢሩን ከፍቶ የማይሰጠውና የማያስጠናው የተቋቋመው ለቤተ ክርስቲያን ሳይሆን ያቋቋሚዎች የግል መሣሪያ በመሆኑ ምክንያት ነው። በጥቅሉ ማኅበረ ቅዱሳን የማንም ሳይሆን የራሱ የማኅበረ ቅዱሳን ሰዎች ንብረት ነው። ንብረትነቱ ግዘፍ ነስቶ የሚንቀሳቀሰው ግን ክፍቱን ባገኛት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለተጠለለ ነው። ከዚያ ባሻገር የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አካል ሆኖ አያውቅም። መሆንም አይፈልግም። ቤተ ክርስቲያኒቱ የማኅበሩን አጠቃላይ ካፒታልና አቅም ታውቃለች? ማን ቢነግራት! 

3/ የማኅበረ ቅዱሳን ዓላማ ምንድነው?

ማኅበረ ቅዱሳን የእውቀቱ ደረጃና የማንነቱ ነገር በራሱ ተነስቶ ለራሱ የቆመ መሆኑን በሁለት ነጥቦች አይተናል። ሦስተኛውና  የመጨረሻው ነጥባችን ማኅበረ ቅዱሳን የሚጓዘው የት ለመድረስ ነው? የሚለውን ጥያቄ በማንሳት በማኅበሩ ላይ ያለንን ጥንቃቄ የተሞላበትን የምልከታ ጥያቄ ማንሳት ግድ ይሆንብናል።
እናስ የማኅበረ ቅዱሳን ዓላማ ምንድነው? በእውቀት ያልበሰለ፤ የራሳቸውን ስሜትና ማነብነብ እንደእውቀት የሚቆጥሩ፤ መድረኩን በመቆጣጠራቸው ጠበቃ መሆን የቻሉ በሚመስላቸው ሰዎች መሞላቱን ካየን ዘንድ የቤተ ክርስቲያኒቱን የአስተምህሮ ጉድለት ወይም ችግር ለማሟላት ነው ብለን የምንጠብቀው ነገር አይኖርም፤ ያ ማለት ግን የሚመስላቸው የዋሃን የሉም ማለት አይደለም። የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተዳደር ለማረ’ቅ ነው ወይስ ለመተካት? ይህን ግምት በብዙ ትንታኔ ማረጋገጥ ቢቻልም ከምኞትና ገቢር ሩቅ መሆን የተነሳ ፍላጎቱ ቢኖርም ማኅበሩን ብዙም የሚያስጉዝ ስላለሆነ  እንዲህና እንዲያ እያልን አንደክምበትም። ይልቅስ ትኩረት እንድንሰጥ የሚያደርገን አንድ ነገር እናንሳ። 

ማኅበሩ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ እንደተፈላጊ ምርጥ እቃ ራሱን ሰይሞ ይህንን ሚዛን እያስጠበቁ ሁኔታዎች ከአቅም በላይ ሆነው መጓዝ እስካልከለከሉ ድረስ አብሮ መሄድ የሚለው ሚዛን የሚደፋ ይመስለናል። ይህንንም ከታዋቂ ሰዎች፤ ከምሁራን፤ ከካህናት፤ ከሥራ አስኪያጆችና ከአስተዳዳሪዎች አባላትን ማሰለፍ ከቻለና  ምልምል ጳጳሳትን ካደራጀ ኅልውናውን ማስጠበቅ እንደማይከብደው የሚረ’ዳ ማኅበር ነው።  ይህንን ለማድረግ ካልሆነ በስተቀር የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት የራሱ አባል አድርጎ መመልመል ባላስፈለገም ነበር። የቤተ ክርስቲያኒቱን አባላት ተቀምጠው ካገኘበት የቤተ ክርስቲያኒቱ መድረክ ላይ ለራሱ ዓላማ ከመመልመል ውጪ ማኅበረ ቅዱሳን የየትኛውንም የሌላ ሃይማኖት ሰዎች ሰብኮ በመወለጥ አባል የማድረግ ብቃት የለውም። እንዲያውም የማኅበረ ቅዱሳን ወከባና ስለላ ሰልችቷቸው፤ የቤተክርስቲያንም አቋም እየመሰላቸው የኮበለሉ ብዙ ሺዎች ናቸው።

የማይመቹትን ሰዎች ሲዘምትባቸው አይተናል። የተመቹትን ደግሞ እስከነ ጉዳጉዳቸው ለመሸከም የማይጸየፍ መሰሪ መሆኑንም አስመስክሯል። አባ ፋኑኤልን ሲዘምትባቸውና ለጉድ ሙዳዮች «የወይን አበባዬን» ሲዘፍንላቸው ታዝበናል። ሰሞኑን ደግሞ ዛሩ የተነሳበት ሆኖ ዘፈኑን ወደእርግማን ለመቀየር ፈልጓል። አባ ቀሌምንጦስንም ካስቀመጠበት የእንቧይ ካብ ላይ ለመናድ ዳር ዳር ብሎም ነበር። ያዝ ለቀቅ ማድረግ ጠቃሚ ስልት መሆኑን ያውቅ ይሆናል።  
 ከቤተ ክርስቲያኒቱ ትልቁ የአገልግሎት ማማ ይልቅ ቁልቁል ወርደው የተራ ማኅበር አባላት ከሚሆኑ ጳጳሳት ድሮስ ምን ሊገኝ ነበር? ወትሮም «ውረድ ሲዋረድ» ይባል የለ!
ከዚህ ውጪ  ማኅበረ ቅዱሳን፤ የማኅበሩ ቀንደኛ አባላትና አመራሮች የግል ተቋም እንጂ ቤተ ክርስቲያን የምታዘውና የምትናዝዘው የንስሐ ልጇ አይደለም። ነኝ የሚልበትን አንድም አስረጂ ማቅረብ አይችልም። ነው ብሎ የሚመሰክርለት አንድም የቤተ ክርስቲያን ተቋማዊ አካል የለም።

ማጠቃለያ፤ 

ማኅበረ ቅዱሳን ከተራ ቁጥር አንድ እስከ ሦስት ድረስ ባሉት ጥያቄዎች ዙሪያ ማለትም  የእውቀቱን ልክ በራሱ ሚዛን የሚለካበትን ትምክህት ሳያራግፍ፤ የማን ንብረት መሆኑንና ማን ሊያዘው እንደሚችል በተግባር ሳያረጋግጥ፤ በዚህ አካሄዱም  የት ሊደርስ እንዳሰበና ዱካውም በየት እንደሚያልፍ ሳይገለጽና  እዚያም እንዴት እንደሚደርስ?  መንገዱን ካላሳየ በስተቀር  መሰሪ ድርጅት፤ የቤተ ክርስቲያኒቱም ጠንቅ ነው ማለታችንን አንተውም። የምደግፈውንና የማንደግፈውን እንደወርቅ ባብለጨለጨ ልባሱ ሳይሆን የምንለካበት ሚዛን የቤተ መቅደሱ የንጹሕ ዱቄት መስፈሪያ ቆሮስ ውስጥ አስገብተነው ብቻ ይሆናል። ሌሎች በራሳቸው ሚዛኖች ለክተው ይህንን ሚዛን ተቀበሉት ቢሉን ሚዛናችሁ ልከኛ አይደለም እንላለን።
የንስሐ እድሉን ቢጠቀምና ለእውነት ነገር ዳግመኛ ራሱን ቢሰራ ይበጀው ነበር። ሁላችንም አብረነው በቆምን! ለዚህ የተዘጋጀ ማንነት ስለሌለው እድሉን ለጥፋት እያባከነ በመገኘቱ እናዝናለን።