source: http://dejeselaam-dejeselaam.blogspot.com
"ማኅበረ ቅዱሳን" አፍኖ እንደወሰዳቸው ይጠረጠራል"
የጅማ ቅዱስ ሚካኤል አስተዳዳሪ አባ ማቴዎስ ታምሩ የገበቡበት አለመታወቁን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡ አባ ማቴዎስ ታምሩ በተለይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከ"ማኅበረ ቅዱሳን" ተከታታይ የሆነ ጥቃት እንደደረሰባቸው ሲታወቅ፣ እርሳቸውም "ማቅ" የአጥቢያ ቤተክርስቲያኑን መዋቅር በመቆናጠጥ ፈላጭ ቆራጭ ለመሆን የሚያደርገውን ሕገ ወጥ አካሄድ በመቃወም ረገድ ብርቱ እንደነበሩ ተመስክሮላቸዋል፡፡
ይሁን እንጂ "ማቅ" አንድ ጊዜ ያተኮረበትን ቦታና ሰው እስኪቆጣጠር ዕረፍት የሌለው በመሆኑ አባ ማቴዎስን ሌት ተቀን መነዝነዝና ስቃይ ማብላትን ሥራዬ ብሎ መያያዙን ታዛቢዎች ገልጸዋል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ አባ ማቴዎስ በራሳቸው ጊዜና ፍላጎት ዕረፍት ለማድረግና ዘመዶቻቸውን ጠይቀው ለመምጣት ወደ ሲዳማ ዞን አርቤጎና ወረዳ መሄዳቸው ታውቋል፡፡
"ማቅ" ማፊያ ድርጅት እንደመሆኑ መጠን ከሞላ ጎደል የሁሉም ካህናት ትውልድ ሥፍራና የአገልግሎት ቦታዎች መረጃ የመያዝ (Privacy የመጣስ) ልምድ አለው፡፡ በተጨማሪም ሊያጠፋ የሚፈልገውን ሰው ገንዘብ ዘርፏል፤ ከሴት ጋር ተኝቷል፣ ልጅ ወልዷል፤ ነዋየ ቅድሳት ዘርፏል፤ ተሃድሶ ነው፤ መናፍቅ ነው፤ እያለ የስም ማጥፋት ዘመቻ እንደሚከፍት ሁሉ በአባ ማቴዎስም ላይ ገንዘብ ዘርፈዋል የሚል ወሬ አሠራጨባቸው፡፡ ይህ ብቻም ሳይሆን ለዕረፍት በሄዱበት ተከታትሎ ሊያጠቃቸው ወኪሎቹን ላከባቸው፡፡ "ከጅማ ገንዘብ ዘርፈው የመጡ ናቸው" በሚል የሐሰት ክስ አርቤጎና ወረዳ ፖሊስ ጣቢያ እንዲታሠሩ አደረገ፡፡ ይሁን እንጂ የወረዳው ፖሊስ ሊያስከስሳቸው የሚያበቃ መረጃ ስላልቀረበባቸው በነፃ አሰናብቷቸዋል፡፡
አባ ማቴዎስም ፖሊስ በነፃ ካወጣቸው በኋላ ከዕረፍት ወደ ጅማ ከመመለሳቸው በፊት "ቦና ቀባለንካ" ወደ ምትባል ከተማ የሄዱ ሲሆን ከዚያች ከተማ ቆይታቸው በኋላ የት እንደገቡ ማወቅ አልተቻለም፡፡ ዘመዶቻቸው ወደ ወረዳ ፖሊስ እና ሲዳማ፣ ጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በመሄድ ቢያመለክቱም ደብዛቸው ሊገኝ አልቻለም፡፡
ነገር ግን ለዝግጅት ክፍላችን "ወፍ እንደነገረው" ፣ መጠሪያ ስሙ "አዲስ ሰው" የተባለ የበንሳ ወረዳ "ማኅበረ ቅዱሳን" ንዑስ ማዕከል አባልና ግብረ አበሮቹ እኝህን አባት እግር ተእግር ተከታትለው በሕግ ያላዋጣቸውን በጉልበት ተጠቅመው (ከሕግ በላይ ሆነው) አፍነው እንደሰወሯቸው ነው፡፡
"ማቅ" የገንዘብ ዝውውሩ ማለትም አሰባሰቡና አወጣጡ፣ አደረጃጀቱና የአባላት ዝርዝሩ በኦፊሴል የማይታወቅ በመሆኑ ራሱን ከሕግ በላይ አድርጎ የቀጠቀጣቸው፣ ያጠፋቸው፣ ያጉላላቸው፣ የበተናቸው በርካቶች ናቸው፡፡ ይህ ኃላፊነቱንና ተጠያቂነቱን ለይቶ የማይንቀሳቀስ ቡድን በወደፊቷ ኢትዮጵያ ውስጥ በማፊያ ባህርዩ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ አንባቢው ያስተውል፡፡
እግዚአብሔር አጽራረ ቤተክርስቲያንን ያስታግስልን!!!
አሜን!!!