ከሁሉም በላይ በሆነች ሐዋርያት በሰበሰቧት በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን
በስመ አብ፣ ወወልድ፣ ወመንፈስ ቅዱስ አሀዱ አምላክ፤ አሜን። ላለፉት ሃያ አንድ ዓመታት በሥልጣን ላይ ያለው የኢ ሕ አ ዴ ግ መንግሥት በኃይማኖት ጉዳዮች ውስጥ ጣልቃ በመግባት በመንፈሳውያን አባቶች፤ በካህናትና በምዕመናን መካከል ልዩነት በመፍጠር ፤ ይህንኑ ልዩነት በማስፋትና በማራገብ ለዘመናት የኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ እምነት አገልግሎት ያለአንዳች እንከን እየተካሄደ ባለበት ዘመን በተቀደሰና በተከበረ ዓውደምህረት፤ ላይ ስር የሰደደ ጥላቻ እንዲሰፍንና በኦርቶዶክሳውያን መካከል ሰላም እንዲደፈርስ፤ ብሎም የቡድንና የጐጥ ስሜት እንዲስፋፋ ያላቋረጠ ሴራ ሲሸርብ መቆየቱ ይታውሳል። ይህንን ኃላፊነት የጐደለውን እኩይ ተግባር መላው ሕዝበ ክርስቲያን ተረድቶ በተገቢው ጊዜና ሰዓት አፋጣኝና ሥርነቀል የሆነ ምላሽ ካልሰጠበት፤ የሁለት ሺሕ ዓመታት እድሜ ባለፀጋ የሆነችውን ቤተክርስቲያናችን ሕልውናዋን በፅኑ መሠረት ላይ እንደተጠበቀ ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ ውስብስብ መሰናክሎች እንደሚገጥሙት ከወዲሁ መገመት ይቻላል።
በመሆኑም ጥቂት የችግሩን አስከፊነት በጥልቀት የተረዱት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባላት በቅን ልቦና ተነሳስተው፤ ተግባብተውና ተቀራርበው በመወያየት በተለይም አሁን በአገራችን የታየው የቀኖና ቤተክርስቲያን ጥሰት፤ የኦርቶዶክስ አማኞች አሳፋሪ የመለያየት ፈተና፤ የእምነት ክፍፍል፤ በተለይም የአራተኛው ፓትርያርክ የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳስት ዘኢትዮጵያ በመንግሥት ጫናና ግፊት ያለ በቂ ምክንያት ከመንበረ ከፕትርክናቸው በግፍ እንዲነሱ የተደረገበትን ሁኒታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት እንዲያገኝ ሰፊ ጥረት እያደረጉ በነበሩበት ወቅት፤ አባ ጳውሎስ ከዚህ ዓለም በሞት ስለተለዩ ይህም ወደ አንድነት የማምጣቱን ሂደት መልካም አጋጣሚ በመፈጠሩ፤ የሰላሙ ኮሚቴ የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ በመቀጠል ለሦስተኛ ጊዜ በሀገር ቤትና በውጭ ሀገር ያሉትን የቤተክርስቲያን አባቶች ፊት ለፊት አገናኝቶ እንዲነጋገሩና ለተፈጠረው ችግሮች መፍትሔ እንዲያፈላልጉ የሚይስችል ዕድል አመቻችቶ ነበር።
በዚህ ምክንያት የሁለቱም የሲኖዶስ ተወካይ አባቶች በተፈጠረው አጋጣሚ ተጠቅመው ፍጹም መንፈሳዊ በሆነ መከባበር ከብዙ የልዩነት አመታት በኋላ በዳላስ ርዕሰ አድባራት ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል፤ ስፊ ውይይት አካሂደዋል፤ ለሰላሙ መሳካት በአንድ ላይ ሆነው ሥርዓተ ጸሎትም አድርሰዋል። በዚህ የውይይት ወቅት የታየው ሕብረትና አንድነት መላውን ስላም ፈላጊ ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን እጅግ ያስደሰተና የ 21 ዓመት ልዮነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እልባት ተገኘለት ብሎ ሙሉ እምነት የተጣለበት የሰላም ጉባኤ እጅግ አሳዛኝ በሆነ መልኩ ያለምንም ውጤት ሲበተን ተስፋው ሲጨልም እጅግ መሪር ሃዘን ተሰምቶናል።
የቤተክርስቲያኗን የመጨረሻ ውድቀት ለማፋጠን ዓላማ ቀርጾ የሚንቀሳቀሰው ዘረኛው የኢሕአዴግ መንግሥት በመሳሪያነት እየተጠቀመባቸው በሚገኙ ጥቂት አባቶች መሰሪ ተንኮል፤ የፈነጠቀው የሰላም ተስፋ ብዙም ሳይቆይ በድጋሚ እንዲዳፈን ከማድረጉም አልፎ ከቤተክርስቲያኗ ቀኖናዊ ሥርዓት ውጭ በሆነ አካሄድ ስድስተኛ ፓትርያርክ በማስመረጥ የሰላም በሩን ዘግቶ ታሪክ ይቅር የማይለው ከፍተኛ ጥፋት ፈጽሟል።
በዚህ ሕገ ቤተክርስቲያንን በጣሰ አካሄዳቸው አስገራሚው ትርዒት አምስተኛው ፓትርያርክ ዘረኛ ነበሩ፤ ቀኖና ቤተክርስቲያን ጥሰዋል፤ ሙስና አስፋፍተዋል፤ በቅዱስ መንበሩ ላይ ያለአግባብ ተቀምጠዋል በማለት ይከሱና ይወነጅሉ የነበሩ በመጀመሪያዎቹ የሽምግልና ሂደት ውስጥ የጐላ ተሳትፎ ከነበራቸው አንዱ አባ ማትያስ ነበሩ። አባ ማትያስ ለጽድቅና ለእውነት ቁሜአለሁ እያሉ ቤተክርስቲያናችንን ከገባችበት ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊያወጣት የሚችል የመፍትሔ አቅጣጫ መጠቆም ሲገባቸው፤ የተጠሩበትን ዓላማና የሕዝበ ክርስቲያኑን ጩኸት ችላ ብለው ለመንደራቸው ልጆች በማዳላት የኢ ሕ አ ዴ ግ መንግሥት የሰጣቸውን ሹመት በታላቅ ደስታ መቀበላቸው ጐጠኝነት ከተራው ምዕመን አልፎ ለኃይማኖት ቆመናል፤ ለዓለሙም ሙተናል በሚሉ አባቶች ሳይቀር ሠረጾ መግባቱ እጅግ አሳዛኝ ዘመን ላይ መድረሳችን ያመላክታል።
ከዚህ በመነሳት የደብረ መድኃኒት መድኃኔ ዓለም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ካቴድራል፤ ሕጋዊው ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ርዕስ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መሆናቸውን በድጋሚ እያረጋገጥን፤ በኢ ሕ አ ዴ ግ መንግሥት ችሮታ ቀኖና ቤተክርስትያን አፍርሰው የተሾሙትን አባ ማትያስን የማንቀበል መሆኑን በአጽንኦት እያረጋገጥን፤ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ የሚመራው ሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ከጥር 6-8 ቀን 2005 ዓ/ም በካሊፎርንያ-ሎስ አንጀሎስ ከተማ በተካሄደው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልዕተ ጉባዔ ላይ የተላለፉት ውሳኔዎችንና የውግዘት መግለጫ ሙሉ በሙሉ የምንቀበልና ለተግባራዊነቱም ተግተን የምንሰራ መሆናችንን እናረጋግጣለን።
በሻርለት ኖርዝ ካሮላይና የምትገኘው የመካነ ብርሃን ቅድስት ሥላሴና የዳላሱ ርዕሰ አድባራት ደብረ ምህረት ቅዱስ ሚካኤል ካቴድራል እንደወሰዱት ቆራጥ እርምጃ፤ ሌሎችም የገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ካህናትና አስተዳዳሪዎች ከዚህ በፈት ያለ አባት የተጓዙበትን መንገድ ወደኋላ መለስ ብለው በማየት በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ከሚመራ ከሕጋዊው ቅዱስ ሲኖዶስ ጋር በመቀላቀል አሁን ኃይማኖታችንን ካጋጠማት አስከፊ የልዩነት አደጋ በጋራ እንታደጋት ዘንድ የአክብሮት ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።
To donate use this address:
EIN #31-1405449
610 Neil Ave
Columbus, OH 43215
Care of: Melake Selam Sisay Yimer
(614) 280-0626