Sunday, March 24, 2013

ዓለም ለእኔ ብቻ በሚሉ ስግብግቦች የተሞላች ነች!


በአንድም ይሁን በሌላ ምክንያት ሁላችንም የዚህ ስግብግብነት ሰለባዎች ነን። ምናልባት ላይታወቀን  ቢችል ወይም በሌላው ላይ ያደረስነው የስግብግበት መገለጫ ጠባይዓት በግልጽ ባለመታየቱ ብቻ ራሳችን ነጻ እንደሆንን እናስብ ይሆናል። ነገር ግን የሰው ልጅ ከሥጋ ድካምና ከፈተናው ጽናት የተነሳ ስግብግብ ነው። ስግብግብነት ማለት ሁሉን ለእኔ በሚል ፍላጎት ዙሪያ ብቻ የሚሽከከረከር  ሳይሆን ስሱዕ /ስስታምነትን/ ፤መጠን የለሽ ጉጉነትን ይጨምራል።  ስስታምነት ለራስ ማድላትና ራስን ማዕከል ባደረገ ስሜት ስር መታጠር በመሆኑ የስግብግብነት አንድ አካል ነው። ጉጉነት ደግሞ እዚያ ጠርዝ ላይ ለመድረስ የሚጠይቀውን መስዋዕት ሁሉ ለመክፈል መሮጥ ነው። ስግብግብነት ከመጠን በላይ መብላት፤ በብዙ ወጪ ለመርካት መሞከር፤ የፍላጎት ጣሪያ መናር እና የአኗኗር ቅንጡነትንም ይጨምራል። «ሁሉ አማረሽን ገበያ አታውጧት» የሚባለው የፍላጎት ስግብግብነት ልክ ማጣት ማሳያ ነው።
ስግብግብነትን ካምብሪጅ ዲክሽነሪ በምሳሌ እንዲህ ይለዋል።
(industrialized countries should reduce their gluttonous (= greater than is needed) consumption of lifesyle)
የበለጸጉ ሀገሮች የስግብግብ ፍጆታ አኗኗራቸውን መቀነስ አለባቸው እንደማለት ነው።  ምክንያቱም የአኗኗራቸው ቅንጡነት ስግብግቦች እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።ለልቅ ኑሮ ጉጉ ናቸው። ጉጉነት /AVID / ያላዩትን ነገር እንዲያዩ ይገፋቸዋል። ጉጉነት ምንጊዜም አንድን እርከን ከመሻገር በኋላ የሚመጣ ፍላጎት ነው።  ምንም የሌለውና በጣም የተራበ ሰው በቅድሚያ የሚታየው ወይም ከፊቱ ድቅን ብሎ የሚመጣበት ጉጉት ምንም ይሁን ምንም ረሃቡን የሚያስታግስበትን የእህል ዘር እንጂ ከትልቅ አዳራሽ ውስጥ ተሰይሞ የበግ አሮስቶ በውስኪ እያወራረደ መርካት አይደለም።  ያ ማለት ግን አይፈልግም ማለት አይደለም። ይህ የቅንጦት እሳቤ ምንም ከማጣት ችጋር ጋር ስለማይቀራረብ ብቻ ነው። የበለጸጉ ሀገሮች ግን በብዙ መልኩ ከችጋር ስለወጡ አመጋገባቸው ሁሉ ጊዜ ሰርግና መልስ ነው። እንደ ችጋር ሀገሮች የበሉት የምግብ ተረፍ ለበኋላ ተብሎ ይቀመጥ ዘንድ በፍጹም አይታሰብም። አዲስ ሞዴል መኪና፤ አዲስ የቤት እቃ፤ አዲስ ሁሉ አዲስ እንዲሆንላቸው ፍላጎታቸው ጣሪያ ነው። ለሌላው አዲስ ለእነሱ አሮጌ ነው። መሪዎቻቸው የእነዚህን ቅንጡ ሰዎች ኑሮ ላለማጓደል ከሌላው ዘርፈው ወይም ቀምተው ያመጡላቸዋል። ዘረፋው በቀጥታ ላይሆን ይችላል። ሚዛናዊ ባልሆነ ንግድ ወይም የምርት ልውውጥ፤ ሽያጭና ጥቅሞቻቸውን በሚያስከብሩ ስምምነቶች ሊሆን ይችላል። በአንዱ ቦታ የመሳሪያ ቅነሳ ወይም ማስተላለፍ እገዳ ፊርማ ቢያኖሩ  በሌላ ቦታ ደግሞ በመርከብ ጭነው ሊሸጡ ይችላሉ። ይህንን ካላደረጉ ሰማይ የደረሰውን ስግብግብ ፍላጎታቸውን መሙላት አይችሉም።


በኋላ ቀር ሀገሮችም ይህ ስግብግብነት አለ። በአኗኗር ዘዬአቸው ከሕብረተሰቡ ወጣ ያሉ ሰዎች እየተፈለፈሉ ነው። ስግብግብ ፍላጎታቸውን ለማሳደግ ይዘርፋሉ፤ይቀማሉ ወይም ይገድላሉ። ስግብግብነታቸው ጣሪያ እየደረሰ ሲሄድ ቤታቸውን በኮንክሪት፤ ዙሪያውን በግንብ፤ አጥሩን በኤሌክትሪክ ሽቦ፤ በዘበኛና በተናካሽ ውሻ ያስጠብቃሉ። ያለምንም ስጋት ለመተኛትና ለመብላት ከዚያም በላይ የመቆጣጠሪያ ካሜራ ይተክላሉ። ልጆቻቸውንም በቅንጡ ትምህርት ቤት፤ በቅንጡ መኪና ያስተምራሉ። የሚያዩት ከእነሱ በላይ ስላሉት ስግብግቦች ስለሆነ እዚያ ለመድረስ ሌት ከቀን ይጥራሉ። ለመድረስም የሚያስችል የትኛውንም እርምጃ ይወስዳሉ። ቤተሰቦቻቸው ስግብግቦች ስለሆኑ የእነሱን ፍላጎት ማሟላት እንደነባራዊ ሁኔታ ስለሚቆጥሩት ስግብግብነታቸውን አይጸየፉትም። ባላቸው ሀብትና ተቋም ውስጥ በሥጋ ትስስር ወይም በቅርብ ዝምድና ወይም በወዳጅነት ደረጃ ካልሆነ በስተቀር ማንም ሌላ ሰው የጥቅም ተካፋይ እንዲሆን ስለማይፈልጉ አይቀጥሩም ወይም አያስቀርቡም። ማንንም አያምኑም። ስሱዕ /Insatiable/ ናቸው።
ስግብግብነት ለንዋይ ብዛት በመጓጓትና በአኗኗር ቅንጦት ብቻ አይገለጽም። በምኞትና በፍላጎት እድገትም እንጂ። ወጣቶች የዚህ ፍላጎት ሰለባዎች እየሆኑ ነው። በማንቼና አርሴ ደጋፊነት የኔ ይበልጣል በሚል ስግብግብነት የሚጣሉ ሞልተዋል። በገንዘባቸው የሚወራረዱ አሉ። በየትኛውም ጥበብ፤ በእጁም ነክቶ ቢሆን በዳኛው እስካልታየ ድረስ የሚደግፉት ቡድን አሸንፎ እንዲወጣ ይፈልጋሉ። ፍጻሜው በህጋዊ አሠራር የመሄዱ ጉዳይ ሳይሆን ተጋጣሚውን እንዲያሸንፍ ከውስጥ የሚቆሰቁስ ስግብግብ ፍላጎት ስላለ አሸንፎ ማየት ለእነርሱ ደስታ ነው። ሁል ጊዜ የኔ አሸናፊነት ይረጋገጥ የሚል የፍላጎት ጣሪያ አለ። በገንዘቡ ከመወራረድ አንስቶ እስከጥልና ክርክር ድረስ የሚወስደው ስግብግብ ፍላጎት ነው። የእኔ ብቻ የሚል! ኳስ ማለት ለእነርሱ ጥበብ ሳይሆን የፍላጎታቸው ግብ መድረስ ብቻ ነው። ስግብግብ አምሮታቸው ሲረካ ያኔ ጥበብ ከግቡ እንደደረሰች ያምናሉ።
በሃይማኖትም ውስጥ እንደዚሁ አለ። የእኔ ሃይማኖት ብቻ ይደግ፤ ይታወቅ፤ ከሁሉም ይብለጥ የሚል ስግብግብ ፍላጎት አለ። ካለእኔ ብቻ ሌላው አይጸድቅም፤ እውነተኛው እኔ ነኝ የሚል ስግብግብነት ሞልቷል። ይህ ስግብግብነት የወለደው ፍላጎት የማይመስለውን በማሸበር ወይም በማስገደድ እንዲከተለው እስከማድረግ ድረስ ይነዳዋል። ለግድያና ለሽብር የሚያደርሰውም ይሄው መረን የለሽ ስግብግብነት ነው። «ሁሉን ለእኔና ከሁሉም እኔ» የሚል ስግብብነት!       ስግብግብነት እንጂ ሌላ ሥራ ስለሌላቸው ሰዎች መልካም ነገራቸውን አይተው ሊከተሏቸው አይችሉም።
«መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማያት ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ እንዲሁ በሰው ፊት ይብራ»   ማቴ ፭፤፲፮ በሚለው ኃይለ ቃል አንጻር መቆም የሚያስችል ማንነት የላቸውም። ስግብግቦች ስለብርሃንነታቸው ቢናገሩም ግብራቸውን ግን የጨለማ ነው።
ገላጭ የሆነ መልካም ሥራ የላቸውም። ነገር ግን የመልካም ሥራ መሠረቶች እነሱ መሆናቸውን ይደሰኩራሉ። ከእነሱ ወዲያ የሌላውን መስማት አይፈልጉም። እነሱ ግን በሌላ እንዲደመጡ ይፈልጋሉ። ድርጊታቸው ሁሉ ከስግብግብ ፍላጎታቸው የመነጨ ክፉ በመሆኑ ይህንን እንደመልካም ሥራ ቆጥረው በዲስኩራቸው ለመሸፈን ይታገላሉ። በየትኛውም ሃይማኖቶች ውስጥ ስግብግብ ፍላጎቶች አሉ። ስግብግብ ምኞቶች ምን ጊዜም የሥጋ ፍላጎቶች ውጤቶች ናቸው። ሥጋዊ የሆነ ሰው በሕይወቱ ሁሉ ሚዛናዊ ኑሮን አያውቅም። ከፍላጎቱ እርካታና ግብ መድረስ አንጻር እንጂ በመንፈሳዊ ሚዛን ነገሮችን መለካት የሚችል ማንነት የለውም።  ስለዚህ በእኔነት ምኞትና በእኔነት የፍላጎት ስኬት ዙሪያ ታጥሮ ሳያውቀው የስግብግብነት መሣሪያ ሆኖ ይገኛል። እስኪ የትኛው ፍላጎታችን፤ ምኞታችንና እርካታችን ባልተፈለገ ጉጉት፤ስስዕትና፤ እርካታ ውስጥ እንደዘፈቀን ራሳችንን እንመርምር። በመንፈሳዊ ሚዛን ላይ ራሳችንን አስቀምጠን እንመዝን።
የቁጣ ልጆች ወይስ የጽድቅ ልጆች?
«በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን» ኤፌ ፪`፤፫