Thursday, March 7, 2013

«ጉዞው»


መንፈሳዊ ልቦለድ

የሀገርህን እወቅ ጉዞ ደስ ይለኛል። ባለኝ ትርፍ ጊዜ ወይም ዓመታዊ የሥራ ፈቃድ ያላየኋቸውን ታሪካዊም ይሁን ከባቢያዊ መልክዓ ምድሮች፤ የኅብረተሰብ አኗኗርና ባህል መጎብኘት በጣም ስለሚያስደስተኝ እነሆ ተሰናዳሁ። አዲስ አበባ አምስት ኪሎ ባለችው ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን መግቢያ በር አካባቢ በተለጠፈ አንድ ማስታወቂያ ላይ ባገኘሁት አድራሻ መሠረት በዓመታዊው የመርጦ ለማርያም የንግሥ በዓል ላይ ለመታደም ከተጓዦች ጋር እነሆ ታድሜአለሁ።
 
አውቶቡሱ በተቀጠረለት ቦታና ሰዓት ቆሟል። እኔም ሰዓቱን አክብሬ ከቦታው ተገኝቻለሁ። ተጓዦችም ተሰብስበዋል። ግማሹ ሀገሩን ለቆ የሚሄድ እስኪመስል ድረስ የሚያመላልሰው ጓዝ የት የለሌ ነው። ጧፉ፤ ሻማው፤ጥላው ይጫናል። ግማሹ ለስለት፤ ግማሹም ለሽያጭ ነው። ነጋዴው የሚሸቅጠውን እቃ ይጭናል፤ ያስጭናል። ከየአድባራቱ በተንሸዋረረ ጨረታ የሚገዙ ነጋዴዎች በዓላትን እየቆጠሩ ይሸቅጣሉ። የሥራ ፈጠራ ይሁን በተፈጠረው ሥራ የማትረፍ ክህሎት፤ ገንዘብ ለዋጩና ሻማ ሻጩ ብዙ ነው። ግርግሩ ለብቻው ነው። ዓለማየሁ፤ ዓለሚቱ፤ መንግሥቱ.........ከዚህም፤ ከዚያም የሰዉ ስም ይጠራል።  «ስሟ ስንቅ ነው የእመቤቴ» የሚል መዝሙር በትልቁ የከፈተ አንድ ተጓዥም ሲንቅ ሲጭን አይቻለሁ። ጆሮው ላይ ማዳመጫውን የወተፈና በመዝሙር ምርቃና ውስጥ የሰጠመ ሌላው ተጓዥም ምናልባት መንግሥቱ፤ ሀብታሙ....... እየተባለ ሲጠራ ያልሰማው በምናቡ መንግሥተ ሰማይ የገባ መስሎት ይሆናል። ቢሆንስ? ማን ያውቃል።

የንጋት ብርድ አጥንት ሰርስሮ ስለሚገባ የለብስኩትን ጋቢ እጥፋት ዘርግቼ ወደአንድ ጥግ ቆምኩኝ። ከእጄ የቪዲዮ ካሜራ በስተቀር የያዝኩት ምንም ጓዝ ስለሌለ ራሴን ከዚህ ግርግር የሰወርኩ እድለኛ አድርጌ ቆጠርኩት።  ሲፈጥረኝ ግርግር አልወድም። በሰርግና በበዓላት ድግስ ላይ ሰዎች ሲዋከቡ ሳይ ይገርመኛል። ግርግሩ ካለፈ ወደነበረ ማንነት መመለስ ስላለ ያንን መዘንጋት መስሎ ስለሚሰማኝ ምንም አይመስለኝም።  ትንሹን ነገር አዋክበው የተዋጣለት ግርግር መፍጠር የሚችሉ ሰዎችን ሳይ ይገርመኛል። መርጦ ለማርያም ለዓመታዊ ክብረ በዓል ለመሄድ መንፈሳዊነቱ ማድላት ሲገባው ይሄ ሁሉ ግርግርና አታሞ ይገርማል።


  በእርግጥ መርጦ ለማርያም የሚሄድ ሁሉ መንፈሳዊ አይደለም። ግማሹ ለመነገድ ነው። ገሚሱም ለመጎብኘት ነው፤ እንደእኔ። ግማሹም ስለት ይኖርበታልና ያንን ለማድረስ ነው። ግማሹም በረከት ለማግኘት ወይም ንስሀ ለመግባት ይሆናል። ገሚሱም የሚራገመው ሰው ወይም ከቤተ ክርስቲያኗ አጠድ ላይ የሚቋጥረው እጣን ወይም መርፌ ይኖርበት ይሆናል። ምናልባትም አንዳንዱ የመርጦ ለማርያምን የመቃብር አፈር አምጣ ተብሎም ሊሆን ይችላል።  

ጥጌን እንደያዝኩ ግርግሩን ስመለከት አንድ ነገር ላይ ዓይኔ ተተከለ። እድል ይሁን እርግማን ለጊዜው በውል ባላውቅም ወደመርጦ ለማርያም ለመሄድ ከተሰለፉ ተጓዦች የአንደኛዋን ወጣት ቦርሳ ለመንጠቅ የሚያሰፈስፍ ሰው አየሁ። ተበላሽ! ተበላሽ! አልኩ። በቅርብ ርቀት በአንድ እጇ ቦርሳዋን  አንጠልጥላ ቆማ ነበር። ወደልጅቷ ስሮጥ ከመቅጽበት ቦርሳዋን መንጭቆ ለዓይን ያዝ ባደረገው የንጋት ጭለማ ውስጥ ሽቅብ ሸመጠጠ።
 ልጅቱ የሚሆነውን ለማወቅ ኅሊናዋም የተሰረቀ ያህል ባለችበት ደርቃ ቀረች።  መጮህ ያባት ነው። ዝም! ዝም! በቃ አፍዋን ይዛ ዝም ብላ ቀረች። የተሠረቀች ሳይሆን ይዞ እንዲሄድ የፈቀደችለት ይመስል ነበር። ንጋቱ ዓይንን ያዝ ከማድረጉ ጋር ግርግር ስለነበር እየሆነ ያለውን ያስተዋለ አልነበረም። አንዲት ጓደኛዋ ብቻ «አዜብ» ስትላት ሰምቻለሁ።

 በድምጼ ያጀብኳትን ያህል በማስጣልም ላግዛት በሩጫ ሌባውን ተከተልኩት። ከኋላዬ ሌሎች እንደሚከተሉኝ ገምቻለሁ። የሰው ኮቴ ከኋላዬ ይሰማኛል። ሌባው የሰው ንብረት ይዞ የሚሮጥ ሳይሆን ሊገድሉት ከሚያሳድዱት ነፍሱን ለማዳን የሚሮጥ ያህል ጭራው የሚያዝ አልሆነም። በሰው ገንዘብ ይሄንን ያህል ሩጫ?  ገረመኝ። የኔም ሩጫ በትራክ ውድድር ውስጥ ቢሆን ኖሮ ሚዛን ሳይደፋ አይቀርም። ሳንባዬ ጉሮሮዬ ላይ እስኪወተፍ ድረስ መከተሌን አልተውኩም። ሌባው ማቆራረጫ መንገዶቹን በደንብ እንደሚያውቃቸው በውስጥ ለውስጥ መንገዶች ያለችግር እያሳበረ መሮጡ ያስታውቃል። ከዓይኔ እይታ ከተሰወረ ላገኘው እንደማልችል ስላወቅሁ ሩጫዬ እልክና ቁጭት የተቀላቀለበት ነበር።  አልለቀቅሁትም። እሱም እንደማለቀው የገባው ይመስል አድክሞ በተስፋ መቁረጥ ሊያስቀረኝ የፈለገ ያህል ፍጥነቱን ጨምሯል።
 
እየነጋጋ በመሆኑ አልፎ አልፎ ሰዎች ይንቀሳቀሳሉ። ይሁን እንጂ ያንን ያህል እየሮጠ በአጠገባቸው የሚያልፍን ሰው በምን ምክንያት ነው እንዲህ የምትሮጠው? ብሎ ያስቆመው ወይም የጠየቀ አንድም ሰው አልነበረም። መቼም በዚያ ሰዓትና በዚያ ሥፍራ ኃይሌ /ሥላሴ ልምምድ እያደረገ ነው ብለው እንደማይገምቱ እርግጥ ነው። ሰው በራሱ ላይ ካልደረሰ ወይ አይናገርም ወይም ልቡ ቢጠረጥርም በፍርሃት ቆፈን ተይዟል ማለት ነው።  አይ የዘመኑ ሰው መረዳዳት ተወ ማለት ነው? በመያዝ ቢያግዙን ኖሮ ቢያንስ የበረከቱ ተካፋይ መሆን በቻሉ አለያም ለሕግ ልዕልና ሰዎች ያላቸውን አቋም እየተገበሩ መሆናቸውን ባስመሰከሩ ነበር። ሰው ሁሉ መንፈሳዊነቱም ይሁን ለሕግ መከበር ያለው ስሜት የተሟጠጠ ይመስላል። አወይ ዘመን! ሰው ከሁለቱ አንዱን ወይም ሁለቱንም ካጣ ሰው ከመሆን ደረጃው ወርዷል ማለት ነው። ለማዳ እንስሳ ሆነ ማለት ይሆን? ሌላ ምን ሊባል ይችላል?

ያዘው! ያዘው እያልኩ ስጮህ እንደመያዝ ጭራሽኑ መንገዱን ለቀው ጥጋቸውን ይይዙ ነበር።  እኔስ ምን ገዶኝ ነው የምሮጠው?  ሰው በሌለበት ሀገር ሰው ለመሆን መፈለግ አንድም ራስን ለችግር መጋበዝ ነው ወይም አጉል ተመጻዳቂ መሆን ነው።  ይሁን እንጂ ሩጫዬን አልተውኩም። «የሮጠ እንጂ የቆመ አመለጠ» ሲባል እስካሁን አልሰማሁም። ሩጫዬ የሰው ሰውኛ ለመቀማት ሳይሆን ለማስጣል እስከሆነ ድረስ ቢያኮራኝ እንጂ አያሳፍረኝምና መሮጤን አልተውኩም። ሰውን ግን ታዘብኩት።

 ሌባውም ንጋቱን ተከትሎ ከሚኖረው የሰው እንቅስቃሴ ለመሰወር የፈለገ ይመስል ዋናውን መንገድ ለቆ ቁልቁል ወዳለው የመንደሩ ሸለቆ ተምዘገዘገ። ይሄኔ እይዘዋለሁ የሚለው ተስፋዬ በኖ ሲጠፋ ታወቀኝ።  ቢያንስ በዚያ ሰዋራ ስፍራ ውስጥ ቆሞ ቢጠብቀኝ  ምን ሊመጣ እንደሚችል ማሰቡ ይከብዳል።  ሌባ ቢመቸው ለመስረቅ ቢደርሱበት ለመግደል አይመለስም።  የመንደሩን ውስጥ መንገድ ለቆ ወደሸለቆው መንደርደሩ ለምን ይሆን? ፍርሃት ወረረኝ።  ይሁን እንጂ መከተሌን አልተውኩም።

በዚያ ፍጥነት፤  በዚያ ሰዋራ ስፍራ መከተሉ አዋጭ እንዳልሆነ በማሰብ ላይ ሳለሁ ወደ ሸለቆ በሚያስገባው ቁልቁለት፤ ኬር ኢትዮጵያ ከሰራቸው የውስጥ ለውስጥ መንገዶች የሚወርደው ጎርፍ ከቦረቦረው ጎድጓድ ውስጥ እጥፍጥፍ ብሎ ሌባው ወደቀ። አጠገቡ እንደደረስኩ የደከመው ልቤን በእጄ ደግፌ ቁልቁል ወደጉድጓዱ አየሁት። የማይላወስ አካል ሲያቃስት ድምጹ ይሰማኛል።  ሰው ሰርቶ መብላት የሚችል ማንነት እያለው በራስ ላይ መዘዝ እስከመጋበዝ ድረስ የዚህን ያህል መስዋእት መቀበል ደነቀኝ። አንዱ ወደመርጦ ለማርያም፤ አንዱ ወደመርጦ ለዘረፋ፤ አንዱም ሀገርህን እወቅ! አንዱም እንደዚህ፤ ሌላውም እንደዚያ! አይ የሰው ነገር! ገረመኝ።
  ሌባው ከወደቀበት ጉድጓድ ተነስቶ መሮጥ እንደማይችል ሳረጋግጥ ከኋላ ይከተሉኝ የነበሩ አሳዳጆች ደረሰቡኝ።  በአደራ የሰጠሁት ሰው እንደሌለ እያወቅሁ ካሜራዬስ ብዬ ጠየቅኋቸው።  ጋቢዬንና ቪዲዮ ካሜራዬን ለካስ የተውኩት እዚያው በአስተውሎት ቆሜ ከነበረበት ከአውቶቡሳችን ሥፍራ ነበር።