Sunday, March 17, 2013

ክርስቶስ በአምላክነቱ ቃል ማዳን ሲችል ለምን ሥጋ መልበስ አስፈለገው?


የብዙ ሃይማኖቶች መምህራን «ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው ነው» በማለት ይመሰክራሉ። ይህም እውነት ነው። ነገር ግን ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር ወልድ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን ሲችል ለምን ሥጋ በመልበስ በሞቱ አዳምንና ልጆቹን ማዳን አስፈለገው? ለሚለው ጥያቄ የጠራ መልስ የላቸውም። ሥጋ መልበስ ማለት አምላካዊ ስልጣኑን በመተው ራሱን ባዶ ማድረግ እንደሆነ ለመቀበል ሲቸገሩ ይስተዋላሉ። ይሁን እንጂ ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ሲል በትክክል ገልጾታል።

«እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ» ፊልጵ ፪፤፮-፯ 

ፍጹም ሰው ሆነ ስንልም መለኮታዊ ማንነቱን ተወ ማለት ሳይሆን አምላካዊ ሥልጣኑን ሸሸገ ማለታችን ነው። ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደእኛ የተፈተነውም ለዚህ ነው። መለኮታዊ ስልጣኑን የመሸሸጉ ምክንያትም ፍጹም ሰው በመሆን ከአብ ጋር ያለውን መለኮታዊ ዕሪናውን  እንደተወ ሳይቆጥር እንደልጅ ለመታዘዝ ነው።  ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን የሆንን ሰዎች ልጅ ሆኖ መታዘዙን ልክ፤ ከአብ  ያነሰ አድርጎ እንደመቁጠር ስለምናስብ እንደነግጣለን። አማለደ፤ አስታረቀ፤ ታዘዘ የሚሉ ቃላትን መስማማት የወልድን ባሕርይ ህጹጽ አድርጎ  የሚያወርድ ነው በማለት ለመቀበል የማይፈልጉ አስተሳሰቦች ሞልተዋል። አምላካዊ ባህርይውን ለመጠበቅ ሲባል ፍጹም ሰው የሆነበትን ምስጢር በመሸርሸር ከማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ የመሆን ማንነቱ ለመሸሽ መሞከር  ምስጢረ ሥጋዌን በሽፍንፍኑ እንደመሻር ይቆጠራል። 

 ማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ መሆኑን አምኖ መቀበል ከሌለ ፍጹም ሰው እንደሆነ ማመን በፍጹም ሊመጣ አይችልም። በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን እየቻለ ሥጋ መልበስ ያስፈለገው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ከኃጢአት ሁሉ ንጹህ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ በመካከል እንዲገባ በማስፈለጉ እንደሆነ አምኖ መቀበል የግድ ነው። ያለበለዚያ ነገረ ድኅነት የሚባል አስተምህሮ አይመጣም።
ቀድሞ ሰውና እግዚአብሔርን ሲያገናኝ የቆየው ሕግ ነበር። ሕጉ የሚያዘውን ሁሉ የሚያስፈጽሙ መካከለኞች ደግሞ ካህናቱ ናቸው። በሕግ ተቀባዮች በሕዝቡና በሕግ ሰጪው በእግዚአብሔር መካከል ያሉት መካከለኛ የሕግ አስፈጻሚዎቹ ራሳቸው ንጹህ መሆን ይጠበቅባቸው ነበር።  ይህንንም የስርየት መስዋዕት በማቅረብ መንጻት ግዴታቸው ነው። ከዚያም የሕዝቡን ሥርየት ሕጉን በመተግባር ያስፈጽማሉ። እንግዲህ ይህ መስዋዕት ዕለት ዕለት የሚደረግ ነው። እንደዚያም ተደርጎ ለሕጉ ፈጻሚዎች  ዘላለማዊ የሆነ ስርየትን ማስገኘት አይችሉም። ይህ መስዋዕት ምድራዊ ነው። ምክንያቱም በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ትዕዛዝን የማፍረስ የጥል ግድግዳ በቀዳማዊው ሰው ጥፋት የተነሳ ተተክሎ ነበርና። 

ይህ የጥል ግድግዳ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መፍረስ ነበረበት። በሕዝቡና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በብቃት ለማፍረስ ደግሞ ኃጢአት የማያውቀው ሰው ያስፈልጋል። ክህነቱም ፍጹም ሊሆን ይገባል። ይህንንም ለማሟላት አምላክ ሰው በመሆን ያንን ደካማ ሥጋችን በመልበስ ከውድቀት ማዳን ነበረበት። በዚህም የተነሳ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ በፈቃዱ የአብ የባህርይ ልጅ ሆኖ ሥጋችንን ለመልበስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን አደረ። እንደሰውነቱ ኃጢአት አያውቀውም። እንደካህንነቱ ዘላለማዊ ካህን ነው። እንደአዳኝነቱ ሞት አያሸንፈውም። እንደልጅነቱ የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። እንደስርየት መስዋዕትነቱ አንዴ፤ ግን ለሁል ጊዜ  የሚሆን ነው። ይህም የነበረውን ጥል አፍርሶ በአብ የተወደደ መካከለኛና ለሕዝቡ ኃጢአት ዘላለማዊ ሥርየትን ማስገኘት የሚችል ሊቀ ካህን ሆኗል።


 ማማለድ ወይም ማስታረቅ ማለት ይህ ነው። መካከለኛ ማለትም ይህ ነው። በኃጢአት ምክንያት በተሰደደው ሕዝብና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን ጥል አፍርሶ እንደሰውነቱ ፍጹም ልጅ ሆኖ  ያስታረቀ/ ያማለደ/ የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ ይቅር በላቸው ያለ፤ ስለጩኸቱም ድምጹ የተሰማለት ልጅ ማለት ይህ ነው። ይህንን  ወልድ ሥጋ የመልበሱን አስፈላጊነትና  የነገረ ድኅነት ምስጢር በመተው ወይም ለመቀበል ሳይፈልጉ መዳን የሚባል ነገር ፈጽሞ ሊታሰብ አይቻልም። አምላክነቱን እንደመተው ሳይቆጥር ፍጹም ሰው ሆነ ማለት ለማስታረቅ/ ለማማለድ/ ካልሆነ ሌላ ለምን? በመለኮታዊ ሥልጣኑማ ሰው መሆን ሳያስፈልገው በለይኩን ቃሉ ማዳን ይቻለው አልነበረምን? ሐዋርያው ጳውሎስም በግልጽ የወንጌል ቃል እንዲህ አለን።

«እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው» ዕብ ፭፣፯-፲፩

አዎ ሐዋርያው እንዳለው አምላክ ሰው ሆኖ ማማለዱንና ማስታረቁን ጆሮአቸው ለመስማማት በፈዘዙ ሰዎች መካከል መናገር ጭንቅ ነው። ሊቀ ካህን መሆኑን እያመኑ የሊቀ ካህን ሥራ ምንድነው ተብለው ሲጠየቁ እውነቱን ለመሸሽ በመፈለግና አምላክነቱን ከማንም በላይ መናገር እንደሚችሉ እየተኩራሩ እስከመስቀሉ ድረስ ብቻ ነው ሲሉ ይደመጣሉ። ከዚያ በኋላስ በሥጋው አላረገም? አሁን በአብ ቀኝ የተቀመጠው በሥጋው አይደለም? እንደመልከ ጼዴቅ ሥርዓት ዘላለማዊ ሊቀ ካህን አይደለም? ከመስቀል በኋላ ግሪካዊው መነኩሴ አውጣኪ እንዳለው ሥጋውን አረቀቀ ካልተባለ በስተቀር እግዚአብሔር ወልድ ዛሬም በሥጋው በዙፋኑ አለ። ክህነቱም ዘላለማዊ ነው። የክህነት ሁሉ ጌታ፤ የሥጋም ፈጣሪ የሆነው እግዚአብሔር ወልድ  ከኃጢአት በቀር በሥጋው እኛን ሆኖ፤ ሞታችንን ሞቶ፤ ያረገውና እንደመልከጼዴቅ ዘላለማዊ ካህን ሆኖ በአባቱ ቀኝ የተቀመጠው ለምን ይሆን? ሹመት አንሶት ነው?
አይደለም!! በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የምሥራቹን ለዓለም የተናገረው ሐዋርያው ጳውሎስ ምክንያቱን ሲነግረን እንዲህ ይላል።

«እንግዲህ በሰማያት ያሉትን የሚመስለው ነገር በዚህ ሊነጻ እንጂ በሰማያት ያሉቱ ራሳቸው ከእርሱ ይልቅ በሚበልጥ መስዋዕት ሊነጹ የግድ ነበረ። ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ» ዕብ ፱፤፳፫-፳፬  ይላል። 

ስለማን ሊታይ? ስለእኛ!!! በሰው እጅ ባልተሰራች ሰማያዊ መቅደስ በእርሱ ያመንን ሁሉ መግባት ይቻለን ዘንድ አንድ ጊዜ ባፈሰሰው ደሙ እርሱ አስቀድሞ ስለእኛ ገባ። ዘላለማዊ ሊቀካህናችን የምንለው ለዚህ ነው። ፍጹም በሆነ ፍቅሩ የመላእክትን ሳይሆን የእኛን ሥጋ የመልበሱ ምክንያትም  ይህ ነው። እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር በልጁ በኩል በመግለጽ ወደመቅደሱ ለመግባት በሊቀካህናችን በኩል ድፍረት እንዲኖረን ያደረገበት ምስጢር ይህ ነው። ጳውሎስ ይህንን ረቂቅ ምስጢር ሲፈታ እንዲህ ብሎታል። አምላክ ፈጣሪነቱን እንደጌታና ሎሌ፤ እንደ ንጉሥና አሽከር ማድረግ አልፈለገም። ይልቁንም እንደአባትና ልጅ ኅብረት እንዲኖረን እንጂ። በሥጋችን ካልመሰለን በስተቀር ዝምድናችን በምን ይታወቅ ኖሯል? «በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና» ገላ፫፤፳፮

«ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥ በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ድፍረትና መግባት በእርሱ አለን» ኤፌ ፫፤፲-፲፪
ልጆቹ መሆን የቻልነው በሥጋ በተዛመደን በክርስቶስ በኩል ነው። ልጆች ደግሞ እንደመሆናችን የአባታችን የሆነውን ሁሉ እንወርሳለን። ሮሜ ፰-፲፯

ይህንን የወንጌል እውነት መለወጥ ስለነገረ ድኅነት ያለንን አቋም ይለውጣል። በእርግጥ አንዳንዶች መለኮታዊ ማንነቱን የጠበቁ መስሏቸው ሥጋ የመልበሱን ምስጢር ሲያደበሰብሱ እንደሚገኙት ሁሉ ሥጋ በመልበስ ፍጹም ሰው በመሆን  ያደረጋቸውን የባህርይ ልጅነት ተአዝዞት እየተመለከቱ ወልድ አምላክ አይደለም፤ እሩቅ ብዕሲ ነው የሚሉ ክፍሎችም መኖራቸው እርግጥ ነው። 
«አሁን ነፍሴ ታውካለች ምንስ እላለሁ? አባት ሆይ፥ ከዚህ ሰዓት አድነኝ» ዮሐ ፲፪፤፳፯
«ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም» ማቴ ፳፬፤፴፮
«የሰው ልጅም ስለ ሆነ ይፈርድ ዘንድ ሥልጣን ሰጠው» ዮሐ ፭፤፳፯ ……………………………………  ወዘተ ቃላትን እየለቀሙ ወልድ ፍጹም አምላክ የመሆኑንም ምስጢር የሚክዱ ክፍሎች ሞልተዋል። አምላክ አይደለም፤ እሩቅ ብዕሲ ነው ማለትም በሌላ መልኩ ክህደትና የአዳም ልጆች አልዳኑም  ማለት ይሆናል።እሩቅ ብዕሲ ሰውን ማዳን አይችልም። እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት ዘላለማዊ የሆነ ካህን እስኪመጣ ድረስ ካህናት የሆኑ ብዙ ነበሩ፤ ይሁን እንጂ አንዳቸውም ማዳን አልተቻላቸውም, ሁሉም በኃጢአትና በሞት ተሸንፈዋል። ስለዚህ ከእንደዚህ ዓይነቱ ኑፋቄም መጠንቀቅ ይገባል።
እግዚአብሔር ከአዳም ልጆች መካከል ሰው የመፍጠር ችግር የለውም። እግዚአብሔር የሰው ልጅ መውደዱን የሚገልጽበት ታላቁ ፍቅር ሥጋውን በመልበስ ለድካሙና ለኃጢአቱ ሞቶ፤ ትንሣዔን በማብሰር ወደመንግሥቱ የሚያስገባበት ተልዕኮ ለመፈጸም በመካከሉ ተገኝቶ ሥጋ ከመልበስ የበለጠና የተሻለ መንገድ ስለሌለ ብቻ ነው። ይህንንም ረቂቅ የፍቅር ምስጢር ሐዋርያው ለጢሞቴዎስ ልጁ በጻፈው መልዕክቱ ላይ እንዲህ ሲል አስቀምጦታል።

«እግዚአብሔርንም የመምሰል ምሥጢር ያለ ጥርጥር ታላቅ ነው፤ በሥጋ የተገለጠ፥ በመንፈስ የጸደቀ፥ ለመላእክት የታየ፥ በአሕዛብ የተሰበከ፥ በዓለም የታመነ፥ በክብር ያረገ»  ፩ኛ ጢሞ ፫፤፲፮

ስለሆነም በመግቢያችን ላይ ለማሳየት እንደሞከርነው ፍጹም አምላክ፤ ፍጹም ሰው በማለት የምንናገረውን በነገረ ድኅነት የአስተንትኖ ትምህርት ሳይነጠልና ሳይከለስ የሚያስተምሩት እንጂ በአንድ በኩል እያመኑ በሌላ በኩል እየሻሩ ወይም ሥፍራውን እያስለቀቁና እየካዱ መሆን የለበትም።
በሌላ መልኩም ወልድ የማዳን ሥራውን በመፈጸም ሙስና መቃብርን ሽሮ በአብ ቀኝ ተቀመጠ ሲባል አንዳንዶች የመውጣትና የመውረድ ተግባር እንዳለ አድርገው ሲናገሩ ይደመጣሉ። እውነታው ግን ለመለኮት መውጣትና መውረድ የሚባል ነገር የለውም። ፍጹም ሰው እንደመሆኑ መጠን፤ ፍጹም አምላክ መሆኑን ለማመልከት እንጂ ወልድ ሥጋ በመልበሱ መለኮታዊ ስፍራውን ለቋል ማለት እንዳልሆነ ማስተዋልም ተገቢ ነው። እንደዚሁ ሁሉ ክርስቶስ የማስታረቅ አገልግሎቱን እስከመስቀል ድረስ ብቻ እንጂ ከዚያ በኋላ የለም የሚሉ ሰዎች ፍጹም ሰው ሆኖ በአብ ቀኝ የተቀመጠበትን ምስጢር መካዳቸው ነው። ሰው ሆኖ አርጓል የሚሉ ከሆነ ለምን? ለሚለው ጥያቄ መልስ ሊሰጡ ይገባል። ሊቀ ካህንነቱ ዘላለማዊ ነው ወይ? ሲባሉም አዎንታ መስጠታቸው ብቻ በቂ ባለመሆኑ ምክንያቱን ማብራራት ይጠበቅባቸዋል። በመለኮታዊ ዕሪናው በአብ ቀኝ ቢቀመጥም ፍጹም ሰው የመሆን ማንነቱን እንዳልተወ ማመን ይገባል። 

«እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና» ዕብ ፯፤፳፪-፳፯ ሊያማልድ ዘወትር የሚኖረው እንዴት ሆኖ ነው?

በሥጋው የማረጉ ዋናው ምስጢር ይህ ነው። ሌላ ታሪክ የለውም። ክርስቶስ አንዴ በፈጸመው የማስታረቅ አገልግሎት ዘወትር ወደእርሱ የሚመጡትን ሁሉ አስተማማኝ ድኅነትን ይሰጣቸዋል።  ዛሬ መስዋዕት ሆኖ የሚፈተተው ሥጋና ደም አንድ ጊዜ ቀራንዮ ላይ የተሰዋው እንጂ ክርስቶስ ዕለት ዕለት እየሞተ ነው ማለት እንዳልሆነ ሁሉ ማለት ነው።  ይህን «ማማለድ» የሚለውን ቃል መስማት የሚያቅለሸልሻቸው ሰዎች የክርስቶስን አምላክ መሆን አሳንሶ የሚያሳይ ሆኖ ስለሚሰማቸው ባደረባቸው ቅንዓት ስለተነሳ ዝም ብሎ አርጓል በሉ እንጂ ዛሬም ሊቀ ካህን ነው አትበሉ ይሉናል። እንደምድራዊው ሊቀ ካህን ዘላለማዊው ሊቀ ካህን የዘወትር መስዋእት የሚያቀርብ ሳይሆን አንዴ ባቀረበው የዘላለም እርቅ ወደአብ የሚመጡትን ሁሉ ያድናቸዋል። ምክንያቱም ሐዋርያው በላይኛው ጥቅስ ውስጥ እንደተናገረው «ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ሊያድን ይችላል። ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎታልና» ብሏል። 

ሌላው አሳዛኙ ነገር «እግዚአብሔር» በሚል ስመ ተጸውኦ የምንናገረውን የሦስትነት፤ አንድ ስሙ እንዳልሆነ በመቁጠርና በተለየ አካሉ መድኃኒት የሆነበትን «ኢየሱስ» የሚለውን ስም መጥራት ልክ ሩቅ ብእሲ አድርጎ እንደመቆጠርና ከእግዚአብሔርነት ባህርይው  እንደማውረድ የሚመለከቱ ሰዎች እያሳዩ ያለው ኑፋቄ ነው። አባት ሲባል ወልድን በማሳነስ እንዳልሆነ ለብዙዎች መረዳቱ እያዳገተ መጥቷል። አያውቁም እንዳይባል ሲናገሩ ይደመጣል፤ አምነዋል እንዳይባሉ ተመልሰው ይክዳሉ። ይህ ሁሉ ችግር መለኮታዊ ዕሪናውን ለመጠበቅ  ቅን ካልሆነ ቅናት የተነሳ ነው።
 እንደዚሁ ሁሉ «ማማለድ» የሚለውን ቃል ከክርስቶስ የማዳን ባህርይ ጋር በተያያዘ ወንጌል ቢያስቀምጠውም አዲስ የወጣው መጽሐፍ ቅዱስ ሰርዞት ለኢትዮጵያ አራተኛ ወይም አምስተኛ የትርጉም ቋንቋ የሆነውን ግእዝን እንደማጣቀሻ ሲጠቀሙም ታይቷል። በህዳግ ላይ በግሪኩ «ማማለድ» ይላል ብለው እንደአጫፋሪ ሲጠቅሱ ማየት አሳዛኝ ነው። ቤተ ክርስቲያን እንደምታስተምረው የአዲስ ኪዳናት መጻሕፍት የመጀመሪያ ትርጉማቸው ጽርዕ መሆኑን ነው። ስለማማለድ የተጻፉት የእብራይስጥ፤ የግሪክና የልሳነ ቅብጥም ይሁን የዐረብኛው የመጽሐፉ ቃላት ተመሳሳይ ትርጉም ሲኖራቸው የግእዙ ትርጉም ግን ከዚህ ውጪ መሆኑ ለምንድነው? የአምላክን መለኮታዊ ሥልጣን ለመጠበቅ ሲባል ምስጢረ ሥጋዌውን ለመደፍጠጥ ሰይጣን የመሸገበት መንገድ ከመሆን አያልፍም። ለማሳያነትም፤ 
1/ ጽርዕ፤
«ὅθεν καὶ σῴζειν εἰς τὸ παντελὲς δύναται τοὺς προσερχομένους διαὐτοῦ τῷ Θεῷ, πάντοτε ζῶν εἰς τὸ ἐντυγχάνειν ὑπὲρ αὐτῶν» ዕብ ፯፤፳፭  በቀይ የተሰመረበት ቃል /ኢንታይኻኔየን/ ማለት «ሊያማልድ» ማለት ነው። ይህም « ἐντυγχάνειν  የሚለው ግሳዊ መስተአምር  -  ἐντυγχάνω  ἐντυγχανω   በሚለው የአገባቡ ልክ (God on behalf of), plead, appeal) መካከለኛ የሆነ፤ አስታራቂ ማለት ነው።
2/ ዕብራይስጥ
«אשר על כן יוכל גם להושיע בכל וכל את הנגשים על ידו לאלהים כי חי הוא תמיד להפגיע בעדם׃»ዕብ ፯፤፳፭ 
በቀይ የተጻፈው ቃል / ሌሐፍጊያ/ ማለት ሲሆን ትርጉሙም  ሁለት የተለያዩ ነገሮችን በመሃከል ሆኖ ማገናኘት፤ማያያዝ  ማለት ነው። ይህም በ፩ኛ ጢሞ ፪፤፭ ያለውን የመካከለኛነት ተግባር በትክክል ገላጭ ሆኖ ይገኛል።
በጥቅሉ ቅዱስ ወንጌል ላይ የተጻፉት መሠረታዊ ትርጉሞች ሐዋርያት በጉስዐተ መንፈስ ቅዱስ የጻፏቸው ቃላት በስርዋጽና በኑፋቄ ቃላት ተተክተው በዕሥራ ምዕቱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከመታተማቸው በስተቀር የቀደሙት ጽሁፋት በትክክል የእግዚአብሔር ወልድን ፍጹም ሰውነትና አምላክነት ያለመጠፋፋት፤ ያለመቀላቀልና ያለመለያየት በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጹን የሚያስተምሩ ናቸው።
ስለዚህም በርዕሳችን እንዳመለከትነው ክርስቶስ በአምላክነቱ ቃል ብቻ ማዳን ሲቻለው ሰው ሆኖ መገለጽ ያስፈለገው በሰውና በአምላክ ያለውን ልዩነት በማፍረስ መካከለኛ ሆኖ ለማገናኘት ነው እንላለን። ከሰው ልጆች መካከል፤ መካከለኛ መሆን የቻለና የሚቻለው ሌላ ማንም የለም።  
ይህንንም ካህኑ በጸሎተ ፈትቶ ላይ « እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ » በማለት የሚያውጀው አምላክ ሰው የሆነበትን ምሥጢር ነው።