Saturday, May 4, 2013

«ደብዳቤ ከመጻፍ መነጋገር፤ ወደሌላው ጣትን ከመጠቆም ቅድሚያ ራስን ማየት፤ ማኅበራትን ተስፋ ከማድረግም በሥራ ማሳየት ይሻል ነበር»


 
ቅዱስ ፓትርያርኩ ለአቡነ አብርሃም ሰሞኑን የንብረት አስረክብ ደብዳቤ መጻፋቸው ይታወሳል። ቅዱስ ፓትርያርኩ ከዚህ ቀደም የተጻፉትንና የተደረጉትን የጽሁፍ ልውውጦች መነሻ በማድረግ ደብዳቤውን ለመጻፍ መቻላቸውን እንጂ በእርሳቸው ደረጃ አቡነ አብርሃም ለምን እስካሁን እንዳላስረከቡ ወይም ለማስረከብም ይሁን ላለማስረከብ ያበቃቸውን ምክንያቶች ምን እንደሆኑ ለማወቅ ያደረጉት ውይይትም ይሁን ንግግር ስለመኖሩ በተጻፈው ደብዳቤ ውስጥ ምንም አልተገለጸም። ደብዳቤውን ለመጻፍ የሚያበቁ አሳማኝ ምክንያቶች መኖራቸው ቢታመንም እንኳን አቡኑን አስጠርቶ በአካል በማወያየት እሺታቸውን ይሁን እምቢታቸውን መረዳቱ የበለጠ ተቀራርቦ የመሥራት ምልክት መሆን በቻለ ነበር። የፓትርያርኩም  አዲስ የሥራ መንፈስ መሆኑን ለመረዳትም እድል እናገኝበት ነበር። ከዚህ አንጻር ፓትርያርኩ ነገሮችን በማርገብ ተወያይቶና አወያይቶ ለችግሮች የቅድሚያ መፍትሄ አምጪ መንገዶችን ለመከተል ገና ብዙ ይቀራቸዋል ብለን እንገምታለን።

እዚህ ላይ ይህንን ጉዳይ ማንሳት ያስፈለገው አቡነ አብርሃም ቅንነቱ፤ ታማኝነቱ፤ አድልዎ የለሽና ሚዛናዊ ኃላፊነት የሚታይባቸው ሰው ናቸውና ለምን ተበደሉ? ብለን ስለእሳቸው ለመከራከር አይደለም። ያንንማ የአገራቸው ልጅ ገመናቸውን ለመሸፈን «አቡነ አብርሃምን ሳውቃቸው» በሚል ርዕስ የሚችለውን ያህል ጥሩ መስሎ የታየውን ጨምሮና ፈጥሮ የጻፈላቸው ይበቃቸዋልና የሌላቸውን ማንነት ከመሬት አንስተን በመለጠፍ ወደመካብ አንወርድም። ዳንኤል ሲያውቃቸው የጻፈላቸውን ያህል እኛም ስናውቃቸው በሚል ርዕስ ብዙ ነገር መጻፍ በተቻለ ነበር። ምክንያቱም ጳውሎስ እንዳለው የአንዳንዶቹ ኃጢአት የተገለጠና የታወቀ ነውና።
«የአንዳንዶች ሰዎች ኃጢአት የተገለጠ ነው ፍርድንም ያመለክታል፥ ሌሎችን ግን ይከተላቸዋል» 1ኛ ጢሞ 5፤24  ለዚህም ይመስላል፤ አቡን ሆነው ብፁዕነትን ከደረቡ በኋላ እንኳን «የአስረክብ፤ አላስረክብም» የሙግት ደብዳቤ እየተከተላቸው  የሚገኘው።
ይሁን እንጂ የአቡነ አብርሃምን ድክመትና የታወቀ ስንፍና በሚዛን ላይ እያስቀመጡ ወደንስሐና ወደተሻለ ሚዛናዊነት እንዲታረሙ ከማድረግ ይልቅ ደብዳቤ በመጻፍ መወጠርና ማጨናነቅ ለፍሬአማነት የሚያበቃ  መስሎ አይታየንም። ከሲኖዶስ ጉባዔ በፊት ደብዳቤ መጻፍ ያስፈለገው የውይይትና የንግግር በሮችን አስቀድሞ በመጠርቀም፤ ከደብዳቤ መጻፍ በኋላ ጉዳዩ እንደትዕዛዙ ፍጻሜ ሳያገኝ ከቆየ ለሚመጣው ቀጣይ እርምጃ ራስን የማዘጋጀት ስልት ከመሆን ያለፈ ዓላማ የለውም እንላለን። ስለዚህ ፓትርያርኩ ከማይመቹ ሰዎች ጋርም እንኳን ቢሆን ነገሮችን በትዕግስትና በማስተዋል ለመነጋገር ዝግጁ አይደሉም ወይም የውይይት መንፈስን አስቀድሞ በመተግበር፤ ወደቀጣይ እርምጃ የመጓዝ ስልትን ለመከተል አይፈልጉም ብሎ መደምደም ይቻላል። ምናልባትም አቡነ አብርሃም ቅድመ ፓትርያርክ ምርጫ ላይ ሲኖዶሱን እየበጠበጡ መቆየታቸውና ማንም ሳይጠራቸው ማኅተም የሌለበትን መግለጫ እስከማንበብ ያደረሳቸውን መሰሪ ተግባራቸውን በመመልከትና የአሁኑን ፓትርያርክ የምርጫ ሂደት ለማደናቀፍ የቻሉትን ያህል ስለሰሩ የዚያ ተግባር ብድራት በተዘዋዋሪ መንገድ እየተከፈላቸው እንዳይሆን ያሰጋል።  አባ አብርሃም ከራጉኤል አንስቶ የመምሪያ ኃላፊ ሆነው ለዚያ ሸምቆ ወጊ ማኅበር ለማገልገል ቃልኪዳን እስከተግባቡበት ድረስ ያለውን ነገር እናውቃለን። ቀድሞውንም ቢሆን ስለአቡነ አብርሃም ጵጵስና ነፍሳቸውን ይማርና አቡነ መርሐ ክርስቶስ በሲኖዶስ ጉባዔ መናገራቸውንም ብዙ ሰምተናል።  ይሄ ሁሉ ሆኖ አባ አብርሃም ጥሩ አባት አይደሉም ማለትና ጥሩ አለመሆናቸውን በመመልከት ውሳኔ መስጠት ሌላ ነገር ነው። ይሁን እንጂ ጥሩ ያልሆኑበትን መንገድ ሳይነካኩ በንብረት አስረክብ ሽፋን ሌላ ሂሳብ ለማወራረድ ሚዛናዊ መንገድን መተው ክርስትና አይደለም። ጥሩ ያልሆነውን መንገድ መከተል ከአባ አብርሃም ጥሩ አለመሆን በባሰ የሌሎችን ጥሩ አለመሆን ያሳየናል። የአባ አብርሃምን ጥፋት ቁጭ ብሎ አንድ በአንድ መመርመርና በጥፋታቸው ተከልሎ በሕግ ሽፋን 40 ጅራፍ ለመግረፍ መፈለግ ግን ያሳዝናል። ከጅራፍ ገረፋው በኋላ ዛፍ ላይ ለመስቀል ራስን ማዘጋጀትም እንደ ረበናተ አይሁድ ኢፍትሃዊነት የጎደለው አካሄድ ነው።
ስለዚህ ቅዱስ ፓትርያርኩ ለዐመጸኞችም እንኳን ቢሆን ዐመጻቸው ራሱ ተከትሎ ፍርድ እስኪያመጣባቸው ድረስ አባ አብርሃም ለምን እንዳላስረከቡ በአካል ቢጠይቁ  ፍትህ መስጠት የአባታዊ ትዕግስታቸውን ልክ ያሳያል እንጂ ደብዳቤ የመጻፍ ብቃታቸውን ከሚዛን የሚያወርደው አልነበረም።  ደብዳቤ መጻፉን በፈለጉት ጊዜ ማድረግ የሚችሉት ሆኖ ሳለ እንጂ ዙሪያቸውን በተሰለፉ አማካሪዎች ይሁን አቤቱታ በማቅረብ በሚነዘንዟቸው ሰዎች ግፊት የተነሳ ወይም አጋጣሚዎችን በመጠቀም ልክ የማስገባት ፍላጎታቸውን ለመወጣት  እንደሆነ ለጊዜው ባናውቅም፤ አስቀድሞ ከማናገር ይልቅ ደብዳቤ መወርወሩን መምረጣቸው ለምን? እንድንል ያደርገናል። ከመጻፍ በፊት ማነጋገሩ ለምን አልተፈለገም? ፖለቲከኞች እንኳን የጠረጴዛ ዙሪያ ውይይት በሚሉበት ዘመን  ቶሎ ብሎ ደብዳቤ መጫር የማድረግ አቅምን ለማሳየት ተፈልጎ ይሆን? ወይስ ለቤተ ክርስቲያን ስርዓት ከማንም በተሻለ ከመቆርቆር የተነሳ? ብለን እንጠይቃለን። ጥፋተኞች በቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግ አይዳኙ የሚል ስነሞገት የለንም። ቤተክርስቲያን ግን ሁሉንም ችግሯን በደብዳቤ ልውውጥ ብቻ ትፈታለች ብለንም አናስብም።
ይልቅስ  ዛሬ ተገኝተሃል! የሚል ይመስላል እንጂ ፍትህና ርትዕ እንዲኖር የመፈለግ ስሜት ያዘለ እንዳልሆነ ያህል እንጠረጥራለን።  የአባ አብርሃም አለማስረከብ ጥፋተኝነት ወደ ደብዳቤ ከመግለበጡ በፊት አዲሱ ፓትርያርክ አስቀርበው ቢያነጋግሩ ኖሮ አዲስ የአሠራር መንፈስ መምጣቱን የሚያመላክትና ታውቆ ያደረን ጉዳይ እንኳን እስከመጨረሻው ድረስ በንግግር ለመፍታት የመቻልን ብቃት እንድናይ ያደርገን ነበር። አባ አብርሃምን በጥፋት መጠየቅ ተገቢ እንደሆነ ብናምንም የተያዘው መንገድ ግን ጥፋትን ለማረም ሳይሆን ወንጀለኛነት ለማጋለጥ የተፈለገ ይመስላል።
አባ አብርሃም ለተወረወረው ደብዳቤ ያዋጣቸውም፤ አያዋጣቸው የመልስ ምት እንደሚያቀርቡ ይገመታል። አንዳንዶቹን እንደቅድመ ትንበያ ብንገምት ውይይትና መነጋገር ለችግሮች መፍትሄ ከማድረግ ለራቀው ጉባዔ ቢቀርብ አያስገርምም።  ሲኖዶሱን ወደራሳቸው ሃሳብ የመሳብ አቅም ያለው ምክንያት ሊፈጥሩ ይችላሉ። ውይይቱን የመልስ ምት ጉባዔ እንዲሆን ለማድረግ ማለት ነው። ሌሎቹም ብዙዎቹ ጳጳሳት ከመቀመጫቸው ላይ ቁስል ያለባቸው ስለሆኑ ነግ በኔ የማይሉበት ምክንያት የለም።  እኔ የተጠየኩትን አስረክባለሁ ሲኖዶሱ ግን ለእነዚህ ጥያቄዎቼ ምላሽ ይስጠኝ ቢሉ ምን ይላል?
ፓትርያርኩ ከዋሽንግተን ዲሲው ደብረ ገነት መድኃኔ ዓለም ቤተክርስቲያን ደመወዝ የላቸውም ወይ? ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያንስ ምንም ደመወዝ እንደማይከፍላቸው በደብዳቤ በመግለጽ አስተዳዳሪው መልአከ ገነት ልሳነ ወርቅ ውቡ ይህንን ያረጋግጣሉ? ፓትርያርኩ ለምርጫው ካበቃቸው ምክንያቶች አንዱ የአሜሪካን መንግሥት የጡረታ ክፍያ አለመቀበላቸውን በሰነድ ያረጋግጣሉ?   የአሜሪካንን ዜግነት ስለመመለስ ከአሜሪካ መንግሥት የሚቀርበውን ቅጽ ሞልተው ይህንን ላደረገ ማንኛውም አመልካች የአሜሪካ መንግሥት የሚሰውን ማረጋጫ ማቅረብ ይችላሉ?  አሜሪካዊ ስለመሆንና አለመሆን ከማይመለከተው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንጂ ከአሜሪካ መንግሥት ስለተሰጠ ጽሁፍ እስካሁን አልሰማንም። ፓትርያርኩ ራሳቸው እነዚህን ጉዳዮች ለመመለስ የማይፈልጓቸው ቢሆኑም ነገሮቹ እውነትነት አላቸው። ያገኘናቸው አንዳንድ መረጃዎች እነዚህን ያስረዳሉ። አባ አብርሃምን በሽፍትነት የሚፈርጅ የአስረክብ ደብዳቤ ለማስተካከል ብዙ ክርክር ቢጎትትስ? ሳበው ልቀቀው ከመምጣቱ በፊት የጥያቄ በሮችን አስቀድሞ መዝጋት የተሻለ ይሆን ነበር። ለነገሩ አባ አብርሃምን የሚጠሉ ወይም በምርጫው ሰሞን አድራጎታቸው የተበሳጩ ዛሬ አጋጣሚውን ተጠቅመው የቡድን አሰላለፋቸውን ከአዲሱ ፓትርያርክ ጋር ያደርጉና የፓትርያርኩን የኃይል ሚዛን  ሊያጠናክሩ ቢችሉ አያስገርምም። ቀድሞም ሲሰራበት የቆየ ስልት ነው። አንድ ሰሞን ትተቃቀፋለህ አንድ ሰሞን ደግሞ ጎራህን ለይተህ ትጠዛጠዛለህ። ሲኖዶሱ በዚህ ጉዳይ ብዙ ጊዜውን ፈጅቷል። እንደአባ አብርሃም የማነሽ ባለሣምንት? ወርተራ  የአቡነ ሳሙኤል ይሆን ይሆናል። ሁለቱም ጳጳሳት «ወጣ ወጣና እንደሸንበቆ ተንከባለለ እንደሙቀጫ» ከተባለው ጫፍ መድረሳቸው ራስን ያለመሆን ችግርና ያንን ማኅበር አምኖ የመጠጋት ውጤት ነው። ድሮስ ከማቅ የተጠጋ ምን መቅኖ ይኖረዋል? ለዚህ ደግሞ የከፋፍለህ ምታ ስልት ሊጠብቃቸው ይችላል። አባ ሳሙኤል የኮሌጁን ተቃውሞ ይመራሉ ተብሎ ይታሙ ነበር። እርግና ያደከማቸውን የኮሌጁን የበላይ ኃላፊ ጓዴ ተጠያቂ ለማድረግ የሚጨክን አንጀት አልተገኘም እንጂ የእሳቸው ችግር በግልጥ የታየ ነበር። አባ ሳሙኤል እዚያ የሽማግሌው ቦታ ተገኝተው ቢሆን ኖሮ እጣቸው በአቅም ማነስ ሽፋን ፓትርያርክነትን ለተመኙበት ሙከራቸው ግብር ሊከፍሉ እንደሚችሉ ከግምት በላይ መናገር ይቻላል።  «ምኒልክ ተወልዶ ባያነሳ ጋሻ፤ ግብሩ እንቁላል ነበር ይሄን ጊዜ አበሻ«  ለተባለው ዜማ  ለጊዜው ያገዛቸውና ጋሻ የሆነላቸው እድል ነው። እዚያ ቦታ ተሹሞ ያለመገኘት እድል!  ወደፊት ዕዳ የሚከፍሉበት ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ ማለት ነው።
በዚህም ተባለ በዚያ አባ አብርሃምን በደብዳቤ ከማፋጠጥ በፊት ማነጋገሩ የበለጠ የተሻለ  ነበር። ግን አልሆነም። አባ አብርሃም በተአዝዞ በስማቸውና በሴትየዋ  ያስመዘገቡትን ቤት ሲያስረክቡ እናያለን አለያም ከላይ ባነሳናቸው ይሁን በሌሎች ጉዳዮች ሲናጩ እንመለከታለን።  እንደሚስተዋለው የሰው እንጂ የአስተዳደር ለውጥ አላየንም። የውይይት መንፈስ አይሸትም። ፓትርያርኩ ራሳቸውን በሥራ ከመግለጽ ይልቅ በሚዲያ ላይ ለማስተዋወቅ መጠመዳቸው ነገ በሚታይ እውነት ላይ ሽፋን ለማኖር ከመፈለግ የተለየ አይደለም። ስለዚህ መነጋገር፤ መግባባት፤ ሕግና መመሪያን ማስፈጸም፤ ከበቀልና ቂም በመውጣት ሥራ ራሱ እንዲናገር ማድረግ ይሻል ነበር። እንግዲህ ነበር እያልን እንነጋገር። የሆነ ነገር አላየንምና!
ከዚሁ ጋር ተያይዞ  የምንመለከታቸው አንዳንድ የቅዱስ ፓትርያርኩ ፍቅር ያንገበገባቸው የሚመስሉ ሚዲያዎችን ነው። ቅዱስ ፓትርያርኩን በምርጫ ሂደቱ ወቅት ሲቃወም የቆየውና የቱሪስት ሆቴል ዝጉብኝ ማኅበር አባላት እንደሚያንቀሳቅሱት የሚነገረው «ሐራ ዘተዋሕዶ» የተባለው ብሎግ የጫወታውን ስልት በመቀየር ከቅዱስ ፓትርያርኩ ዜና በስተቀር ሌላ አያሰየኝ ማለቱ አስገራሚ ነው። ። በእርግጥ የዘመኑ ጫወታ እንደዚህ ነው። በቃ አንዱ ስልት ካላዋጣህ ቶሎ መገልበጥና የጫወታህን ጥበብ ማስተካከል የሚል ጥቅምህን የመከተል ስልት መሆኑ ነው። ባመኑበት እውነት መቆም ለጥቅመኞች አያዋጣቸውማ!
ስለፕሮቴስታንታዊ ተሐድሶ የተለመደ ዜማ ከማላዘን ባለፈ አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ ቃል የመጻፍ አቅም የሌለው የቤተክርስቲያን ወታደር ነኝ የሚለው ይህ ብሎግ እንደወታደር ከማስፈራራትና  ከድንፋታ በስተቀር ለመስበክ ባህርይው እንደማይፈቅድለት አረጋግጧል።  የወታደር መታመኛው ድሮም ጉልበቱ ብቻ ነውና ድንፋታው ገና ይቀጥላል። የሚገርመው ደግሞ ሁሉም አፍቃሬ ማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች አንድም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነትን አስተምረው አለማወቃቸው ነው። ከዜናና ከበሬ ወለደ ዘገባቸው በስተቀር አንድም ቃል አስተምረው እንደማያውቁ ደጋፊዎቻቸው ጭምር ይገልጡታል። እንደገደል ማሚቱ አንዱን ዜና ይቀባበሉታል።
ደጀሰላም የተባለው ብሎግ ደግሞ አቡነ ጳውሎስ እስኪሞቱ ድረስ ሌሊትና ቀን በወሬ ሲደክም ኖሮ ከሞቱ በኋላ ስራውን የጨረሰ ያህል አሁን እፎይ ያለ ይመስል የሚጽፈውን አቁሟል።  ተልዕኮው የፓትርያርኩን  ሞት እስከ መዘገብ ድረስ ብቻ ነበር?  የብሎጎቹ መንፈስ አባታቸው ማኅበረ ቅዱሳንም የሚፈልገው አባት ወደ መንበረ ፕትርክናው አለመምጣቱን ሲያውቅ ስልቱን እያስተካከለ ቅዱስነታቸው እንደዚህ ብለው፤ እንደዚያ ብለው የሚል ድምጹን ለማሰማት ይጣደፋል። ይህ የማይለወጥ መርህ ነው። እንደኒውተን የኃይል ሕግ ገለጻ ለየትኛውም ድርጊታዊ ኃይል፤ ምላሻዊ የኃይል ድርጊት ስላለው/ action- reaction force/  ከዚህ ዓይነት መላተም ለመጠበቅ አግጣጫን የመቀየር ስልትን ለመከተል መፈለጉ ከማኅበሩ ባህሪያዊ ማንነት ማወቅ ይቻላል። ይሁን እንጂ አፋፍተውና አስብተው ያሳደጉት ጥጃ የሰው ስብስብ ስለሆነ በቀላሉ የሚታረድ ባለመሆኑ አቡነ ጳውሎስ ሊስማሙት ባልቻሉ ጊዜ በቻለው ሁሉ አቅም አጣድፏቸው  ነበር። ይህንን ጥጃ ለማሻሸት የአዲሱ ፓትርያርኩም መጠጋት አንድም ለስልታዊ ጥቅም ፈልገውት ነው፤ አለበለዚያም  ገና ከጅምሩ ፈርተውታል። ይሁን እንጂ ጥጃው የጠነከረና የደረጀ፤ ቀንድም ያበቀለ ስለሆነ እንዲህ አሻሽተው የሚይዙት ስላይደለ ቢፈሩት አያስገርምም። ለአገልግሎት የሚፈልጋቸውን ጳጳሳት ከዚህ ቀደም እየጠራ የሚዲያ ሥራ ሲሰራ እንደቆየባቸው ሁሉ በዚህ ማኅበር ሚዲያ ላይ  ከቃል አቀባያቸው ወይም ከሕዝብ ግንኙነት ክፍላቸው ባለፈ የፓትርያርኩ መቅረብ ምን ሊያተርፉበት ይሆን? ለማኅበሩ እንደሰጡት የቃለ ምልልስ እድል ሌሎች ማኅበራት በየተራ ቢመጡ ኢንተርቪው ይደረጉ ይሆን?
ለማኅበረ ቅዱሳን ግን የፓትርያርኩን ኢንተርቪው ማድረግ ትልቅ ትርፍ አለው። ምንክያቱም፤
 1/ የሚዲያ ተቋሙን በፓትርያርክ ኢንተርቪው ሽፋን በደንብ ያስተዋውቅበታል።                                2/ አዲሱ ፓትርያርክ ቀጣይ ሥራቸውን ከኔ ጋር ተስማምተው ለመሥራት ኢንተርቪው በመስጠት  አሳይተውኛል ይልበታል።                                                                                          3/ በማኅበሩ እንቅስቃሴ ላይ በጎ አመለካከት ለሌላቸው ክፍሎች ሠራተኛና ተቀባይነት ያለው ለማስመሰል ይጠቀምበታል።
ይህ ሁሉ ታሳቢ ሆኖ አዲሱ ፓትርያርክ እንዳይመረጡ የሚቻለውን የሠራና፤ የሚፈልገውን ለማስቀመጥ ሳይቻለው የቀረው ይህንን ማኅበር ፓትርያርኩ የፈለጉት ለምንድነው? ለስልት ወይስ የዚህ ማኅበር ታታሪነትና ሠራተኝነት ታይቷቸው?  እፍ እፍ ያሉበትን ፍቅር በተግባር እስኪያሳየን አንድዬ ከማያልቀው እድሜ አይንፈገን!