Wednesday, May 8, 2013
አርቲስት ጀማነሽ ሰሎሞን ከፋንታሁን ንጉሤ ጋር ያደረገችው ቃለ መጠይቅ
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአርቲስት ጀማነሽ ሰሎሞን ላይ የማኅበረ ቅዱሳን ብሎጎች፤ የሀገር ቤት ተወካይ መጽሔቶችና ተላላኪዎች የስም ማጥፋት ዘመቻ ከመክፈት በዘለለ ወደኃይል መጠቀም መሸጋገራቸውን ለማወቅ ችለናል። እምነት የግል ነጻነት መሆኑ ያልገባቸው እነዚህ የእስልምና ሰለፊ የግብር ወንድሞች ጀማነሽ ሰሎሞን እንኳን በነብዩ አልያስ ዳግም መምጣት ማመን ቀርቶ ነብያት ሁሉ ተመልሰው መምጣታቸውን በማወጅ የሚቀበላት ካገኘች ለማሳመን መብቷ መሆኑን ባለማወቃቸው ብዙ ብዙ ብለዋል። መካነ ጦማራችን ስለነብዩ ኤልያስ መምጣት ትረካ የማታምንበት ቢሆንም እንኳን የጀማነሽ ሰሎሞን ነብዩ ኤልያስ በመምጣቱ የማመኗን መብት ግን ከመቀበል ባሻገር ይህንን ለመደፍጠጥ የሚፈልጉትን አትደግፍም። ያለንበት የመጨረሻው ዘመን ላይ ስለሆነ ገና ከዚህ የባሰ ልንሰማ ስለምንችል ራስን ጠበቅ አድርጎ እውነቱን በመናገር እንጂ በዚህ መጣ፤ በዚያ ወጣ እያሉ በማጣደፍ ነገሮችን ሁሉ በኃይል ለመፍታት ዘመቻ መክፈት ትክክል አይደለም። ጠማማ ልብና ክፉ ምላስ ቢዘገይ እንጂ መውደቁ እርግጥ ነው። «ጠማማ ልብ ያለው መልካምን አያገኝም፥ ምላሱንም የሚገለብጥ በክፉ ላይ ይወድቃል» ምሳሌ 17፤20 ሌላውን ጠማማ እያሉ ራስን ማጣመም ትክክል አይደለም እንላለን። ነብዩ አልያስ መጥቷል የሚሉትን ለመቃወም የት እንዳለ አሳዩን ማለቱ አይቀልም ነበር? ሐዋርያው እንዳለው «አሁንም እላችኋለሁ። ከእነዚህ ሰዎች ተለዩ ተዉአቸውም፤ ይህ አሳብ ወይም ይህ ሥራ ከሰው እንደ ሆነ ይጠፋልና» የሐዋ 5፤38 ለማንኛውም አርቲስቷ ከእስር ከተፈታች በኋላ ያደረገችውን ቃለ ምልልስ አቅርበንላችኋል።