Monday, May 27, 2013

የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ለምን ተሐድሶ ያስፈልጋታል?


ምንጭ፡-http://www.tehadeso.com/
ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔር እና በክርስቶስ ደም የታደሱና የተቀደሱ የምእመናን ጉባኤ ናት፡፡ ይህቺን አማናዊት ቤተ ክርስቲያን ከሐዋርያት ዘመን ጀምሮ ታሪኳን ስናጠና በእግዚአብሔር ሐሳብ ውስጥ የሰው ሐሳብ እየተቀላቀለ እና ጤናማውንና ርቱዕ የሆነውን አስተምህሮ የሚያደፈርሱ ሰብኣዊ፣ አጋንንታዊና ዓለማዊ ሐሳቦች በተለያየ ሁኔታና መንገድ ወደ አማናዊቷ ቤተ ክርስቲያን ዘልቀው እየገቡ እውነተኛ የሆነውን መንፈሳዊ ትምህርትም ሲያደፈርሱ እናያለን፡፡ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ ያሉ ለእውነተኛው የእግዚአብሔር ሐሳብ ቀናዕያን የሆኑ ቅዱሳን የእግዚአብሔርን ሐሳብ በሚያደፈርሱ አስተሳሰቦች እና ግለሶቦች ላይ ጠንከር ያለ ተግሣጽ ሲሰጡና አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ሲወስዱ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እናነባለን፡፡ ምክንያቱም ተሐድሶ አዲስን ነገር አፍልቆ ማምጣትና በነበረ እውነት ላይ መጨመር ሳይሆን ከጌታችንና ከሐዋርያት የተቀበልነውን የሚያድነውን መለኮታዊ መገለጥ (አስተርእዮ) የሚጋርድ ትምህርትና ድርጊት ሲከሠት መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ትምህርት ለመጠበቅ የሚወሰድ የእርምት እርምጃ ስለሆነ ነው፡፡
ቤተ ክርስቲያናችንም ሐዋርያዊት በመሆኗ የተመሠረተችበት የእምነት መሠረት አማናዊ እንደሆነ እሙን ነው፡፡ ነገር ግን በየጊዜው ምንጫቸው የማይታወቅ፣ ከእግዚአብሔር ይልቅ ዲያብሎስንና ሰብእን ከእውነት ይልቅ ሐሰትን የሚያገለግሉ አስተሳሰቦች እና አስተምህሮዎች በመስኮት እውነተኛው የእግዚአብሔር ሐሳብ ወደ ጎን ተትቶ መንፈሳዊ ሕይወታችን ታውኮ በእውነተኛው ትምህርት ላይ ሐሰት ተቀላቅሎበት መንፈሳዊ ቁመናዋ ተበላሽቶ እንመለከታለን፡፡
ይህንን መንፈሳዊ ዝቅጠት የተመለከቱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና መምህራን በየዘመናቱ እርምት እንዲወሰድበት ሲታገሉና ሲያስተምሩ ቢኖሩም ከእግዚአብሔር ያልሆነው ከቅዱሳት መጻሕፍት (ከአሥራው መጽሐፍት) የሚቃረነው አዲስ ትምህርት እንዳይታረም በነገሥታቱ ተደግፎና ታግለውለት ሲቆይና ሌላ ጊዜ ደግሞ ጨዋው ከአባቶቼ የተቀበልኩት ትምህርት ስለሆነ በማለት በእውነተኛ የክርስትና ትምህርት ላይ እንደ እራፊ የተለጠፈውን ባዕድ ትምህርት ለማስጠበቅ ሊቃውንቱንና መምህራኑን አፉን ሞልቶ “መናፍቃን ናችሁ” ብሎ መከራና ስደት እንዲነሣባቸው በማድረጉ በቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ብዙዎች ስለቤተ ክርስቲያንና ስለእግዚአብሔር እውነት በብዙ መከራ ሕይወታቸውን መሥዋዕት አድርገዋል፡፡ ሌሎችም ተሰድደዋል፤ ተደብድበዋል፤ ታስረዋል፤ ተራቁተዋል፡፡
ይህ በመሆኑና ዛሬም በወንጌል ትምህርት ላይ የተጨመረ አሳሳች ትምህርትን እንደ ዶግማ የሚቆጥሩ የተደራጁ የእውነት ጠላቶች በመኖራቸው ብዙ የማስፈራሪያ ድምፅ ስለሚያሰሙ መምህራኑ አፋቸው ተለጉሞ በመከራ አሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ይህ አደጋ ክፉውን መንፈስ ሊያገለግሉ በቆረጡ ደጋፊዎቹ ታጅቦ ሙሉ በሙሉ የመንፈስ ቅዱስን ሐሳብ የሚዋጋ የዲያብሎስ ጦር ሆኖ ይታያል፡፡ እንዲህ ያለውን አደጋ ገልጦ ማሳየት እና ቤተ ክርስቲያን ወደ አማናዊው የክርስቶስ ሐሳብ እንድትመለስ ማድረግ የማንኛውም ጤናማ አእምሮ ያለው ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ግዴታ ነው፡፡ ከዚህም በመነሣት ለሰው ሳይሆን ለእግዚአብሔር ሐሳብ በመቅናት፣ ሰውን ሳይሆን እግዚአብሔርን በመስማት ቤተ ክርስቲያናችን ለምን ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት አስረጅ የሆኑ ምክንያቶችን እናቀርባለን፡፡
1.    በቤተ ክርስቲያኒቱ እንግዳ ትምህርቶች ስለበዙ
ክርስትናን በተመለከተ ከመሥራቹ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርትና ከእርሱም ቀጥሎ ከእግሩ ሥር ቁጭ ብለው ከተማሩ ሐዋርያት ትምህርት የበለጠና የተሻለ ትምህርት አይገኝም፡፡ እነዚህ ትምህርቶች ለክርስትናችን ቋሚ መሠረት ሆነው የሚታዩና በምንም ሌላ እንግዳ ትምህርት ሊተኩ የማይችሉ ናቸው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እኛም ብንሆን ወይም የሰማይ መልአክ ከሰበክንላችሁ ወንጌል የሚለይ ወንጌልን ቢሰብክላችሁ የተረገመ ይሁን” ብሎ በጻፈልን አምላካዊ ቃል ሙሉ በሙሉ መስማማት ክርስቲያናዊ ግዴታ ነው (ገላ. 1÷8)፡፡ ወደ ፊት በስፋት እና ነጥብ በነጥብ የምንተችበት ቢሆንም በአንዳንድ ገድላት፣ ድርሳናት እና ተአምራት ላይ ተጽፈው የሚገኙ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር በቀጥታ የሚጋጩ እንግዳ ትምህርቶችን ቤተ ክርስቲያኒቱ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ራስዋ ተመልክታ ልታስተካክላቸው ስለሚገባ ወደ እውነተኛውና ከአምላኳ ወደተቀበችው ትምህርት እንድትመለስ ተሐድሶ ያስፈልጋታል፡፡
እንግዳ ትምህርቶቹ መወገድ የሚገባቸው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህች ምድር ወርዶ የሰው ልጆችን ለማዳን በመስቀል ላይ የሠራውን ሥራ ስለሚያቃልሉ እና እነዚህን ትምህርቶች እውነት ናቸው ብለው የተቀበሉት ሰዎች ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ባለመቻላቸው አንዳንዶች እነዚህን እንግዳ ትምህርቶች የኢትዮጵያዊነት መለያ አድርገው ቢወስዱዋቸውም፣ እንደ እውነት ቢከራከሩላቸውም፣ የሰው ልጆችን ከኀጢአት እስር ፈትቶ የዘላለም ርስታቸውን መንግሥተ ሰማያትን እንዲወርሱ ያደረገው የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ደም ነው እንጂ ሌላ ምንም ነገር ስላይደለ ከሲኦል እስር ከዲያብሎስ ቁራኛነት ለመላቀቅ ከቃሉ ውጭ የሆኑ ሐሳቦችን ሽረን ለወንጌሉ እንግዳ የሆኑ ትምህርቶችን ትተን በጠራው የመስቀል መንገድ ላይ በእምነት መጓዝ በዚህ ዘመን ለቤተ ክርስቲያን ወሳኝ ጊዜ ስለሆነ ይህን ውድቀቷን በቃለ እግዚአብሔርና በመንፈስ ቅዱስ ምርመራ ከእንግዳ ትምህርቶች ልትለይ ይገባልና ተሐድሶ ያስፈልጋታል፡፡
2.    የእግዚአብሔር ቃል ተገቢውን ስፍራ ስላጣ
ሌላው ቤተ ክርስቲኒቱ ተሐድሶ እንደሚያስፈልጋት አስረጅ የሆነው እውነት ቅዱስ ወንጌል በኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ተገቢውን ስፍራ ማጣቱ ነው፡፡ መጽሐፍ ቅዱስ ሁሉን መጽሐፍ ይመረምራል፣ ይመዝናል፤ እርሱ ግን  በየትኛውም መጽሐፍ አይመረመርም፤ አይመዘንም፡፡ ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት የተለየ ሐሳብ ያለው ማንኛውም በቤተ ክርስቲያን የምንገለገልበት  መጽሐፍ ሌላ ምንም አይነት አንድምታ ሳያስፈልገው ከስህተት ትምህርት ጎራ ሊካተት ይገባዋል፡፡ ምክንያቱም መጽሐፍ ቅዱስ የሁሉ ዳኛ በሆነው በእግዚአብሔር መንፈስ በመጻፉና የእግዚአብሔርን እውነት በመያዙ ነው፡፡ አሁን  ግን ምንጫቸው የማይታወቅ እና በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረኑ መጻሕፍት ከመጽሐፍ ቅዱስ እኩል መሳ ለመሳ በመቀመጣቸው እና መጽሐፍ ቅዱስን በመገዳደራቸው በእውርነት ልምራችሁ የሚሉንን መጽሐፎች ተገቢውን ስፍራቸውን ማሳወቁ አግባብ ስለሆነ ተሐድሶ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አስፈላጊ ነው፡፡
ሌላው ቀርቶ በስብከተ ወንጌል መርሐ ግብር ወቅት ንጹሑን ወንጌል መስበክ እንደ መናፍቅነት እየተቆጠረ ስለመጣ አገልጋዮች የግድ የእግዚአብሔርን እውነት የሚጋፉ መጻሕፍትን እየጠቀሱ እነርሱም አገልግሎታቸውም የእግዚአብሔርን መንግሥት እውነተኛ ሐሳብ የሚቃረኑ እየሆኑ መጥተዋል፡፡ የእውነተኛ ኦርቶዶክሳዊነት መሠረቱ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እና በሐዋርያት አባቶች የተሰበከውን ቃል በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ማብራራት መሆኑ እየቀረ ድርሳነ ባልቴትን መተረክ እየሆነ ይገኛል፡፡
እንዲህ ያለው አስተሳሰብ በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት ትክክለኛውን ተሐድሶ ካላገኘ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ ሙሉ በሙሉ መመሪያዋ እንዲሆናት ወደ እግዚአብሔር ቃል ካልተመለሰች አሁንም ቢሆን በየዕለቱ እየጨመረ የመጣውን የምእመናን ፍልሰት ማስቆም ይቸግራታል፡፡ ሰውን በስፍራው ለማጽናት የተሻለው እና እግዚአብሔርም የሚደሰትበት ትክክለኛው መንገድ የእውነትን ቃል በእውነት ሳያፍሩ እና ሳይሸሽጉ እንደ ጥንት አባቶቻችን ለሕዝቡ መግለጥ ነው፡፡ ለዚህም ቤተ ክርስቲያን ጤነኛ በሆነ የተሐድሶ ኣስተሳሰብ ልትቃኝ ያስፈልጋታል፡፡
3. የመዳንን እውነት የሚገዳደሩ ትምህርቶችን ማስተናገድ ስለጀመረች
የልጅ ቡኮ ዕለቱን ነው
ቢጋግሩት ነቀፋ ነው
ቢቀምሱትም የከረፋ
ቢጨብጡት ወዮ አበሳ
እንደተባለው መንፈስ ቅዱስን ሳያማክሩ ለአሸናፊው የእግዚአብሔር ሐሳብ ብቻ መገዛትን ትተው የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምሮ በማያውቁ እና ለስሜታቸው ባሪያ በሆኑ ሰዎች እየተፈጠሩ ያሉት አዳዲስ አስተምህሮዎች ሀይ ባይ ከልካይ አጥተው የክርስቶስን መስቀል እየወጉ ይገኛሉ፡፡ እኛም እንደ ቤሪያ ምእመናን “ነገሩ እውነት ይሆንን?” በማለት ለመመርመር ከመሞከር ይልቅ “ከኛ ወገን ያለ ሁሉ የሚለው ሁልጊዜ እውነት ነው” በሚል በጨዋ ምእመን አመክንዮ ተይዘን ለስህተት ትምህርቶች ተገዝተን እንገኛለን፡፡ እነዚህ የስህተት ትምህርቶች የመዳንን እውነት ቀስ በቀስ እየሸረሸሩ አሁን ፊት ለፊት መዋጋት ጀምረዋል፡፡ “ያለ ድንግል ማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም” የሚለውና እርሱን የመሰሉ ጥንተ ተፈጥሮዋቸው አጋንንታዊ የሆኑ እና “መዳን በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና” (የሐዋ.ሥራ 4÷12) የሚለውን የመንፈስ ቅዱስ አዋጅ የሚሽሩ እንግዳ ትምህርቶች በመጽሐፍ ደረጃ ታትመው እስከ መሰራጨት ደርሰዋል፡፡
በእግዚአብሔር ቃል የተገለጸውን “መዳን በሌላ በማንም የለም” ተብሎ የተዘጋውን የጽድቅ ማኅተም የሚከፍቱ በመጽሐፍ ቅዱስ ከተገለጸው እውነት ውጭ  ሌላ አማራጭ አለ ብለው የሚያስተምሩ ሁሉ ለሰው መዳን ሳይሆን መጥፋት በአጋዥነት የሚሠሩ ናቸው፡፡ ከዚህ ጋር የተያያዙ እና በዝክር፣ ወንዝ በማቋረጥ፣ ገዳማት በመሳለም፣ በቀብር ቦታ እና በሌሎችም ብዙ መንገዶች ሰው ሊድን ይችላል፡፡ ብለው የሚያስተምሩ ደፋር ብዕር የገለበጣቸው አጋንንታዊ ሐሳቦች ያሉባቸው ገድላት እና ተአምራት በመኖራቸው ሕዝቡ ያዳነውን ጌታ በእውነተኛ ማንነቱ ሳይረዳ በዋል ፈሰስ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
መዳን የህልውና ጉዳይ ስለሆነ በቀላሉ ሊታይ የሚችል አይደለም፡፡ እናቶቻችን እንደሚሉት “እስቲ ይሁና!! ምን ይታወቃል የአንድዬ ሥራ” በማለትም በቀላሉ ሊታለፍ የሚችል ነገርም አይደለም፡፡ የአንድዬ ሥራ የሚታወቅ እና በአደባባይ በመስቀል ላይ የተከናወነ ነው፡፡ አንድዬ ለመዳናችን ከደሙ የተሻለ አማራጭ አልሰጠንም፡፡ በመስቀል ላይ የፈሰሰውን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ለኔ ስለኃጢአቴ የተከፈለ ቤዛነት ነው ብሎ አምኖ መቀበል ለመዳን ዋነኛውም ብቸኛውም አማራጭ ነው፡፡
ነገር ግን ህዝቡ ይህንን እውነት አምኖ እንዳይቀበል የሚከለክሉ ሌላም አማራጭ አለህ ብለው የሚያስተምሩ በክርስቶስ የተሰጠንን መዳን ቀብረው ማሳሳቻ የሚሰብኩ ስለበዙ ቤተክርስቲያናችን ወደ ሐዋርያት ትምህርት እንድትመለስ መታደስ አለባት፡፡ መዳን በክርስቶስና በመስዋዕታዊ ሞቱ በማመን መሆኑን መቀበልና ማስተማር አዲስ ትምህርት የሚመስላቸው አሉ ግን አይደለም፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ እና በተደጋጋሚ የተቀመጠ፣ ሐዋርያት የሰበኩት እስከ ዘመናችን ድረስ እውነተኛውን መንገድ የተከተሉ እንደ እነ ሊቀ ጉባኤ አባ አበራ ያሉ አባቶቻችን መዳን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ የሆነ እና በክርስቶስ በማመን ብቻ የምንቀበለው ነው፡፡ ብለው ያስተማሩት ትምህርት ነው፡፡(ትምህርተ ሀይማኖትና ክርስቲያናዊ ሕይወት )
ስለዚህ በእነዚህ እና በሌሎች ተጨማሪ ምክንያቶች ተሐድሶ ለቤተክርስቲያኒቱ ያስፈልጋታል ብለን እናምናለን፡፡ ለእናት ቤተክርስቲያናችን መታደስም የበኩላችንን አስተዋጽኦ ለማድረግ እናገለግላለን፡፡
ይቀጥላል