Sunday, May 26, 2013

የክርስቲያኖች ሰንበት የሚል ሕግ አለ?


 ታሪክ፤
እሁድን እንደመንፈሳዊ የእረፍት ቀን መቁጠር ከመጀመሩ በፊት ቀደምት ሕዝቦች የፀሐይ ቀን አድርገው ያከብሩት ነበር። በእንግሊዝኛው/ Sun- day / የሚለው ቃል ትርጉም የሚያመለክተው ያንን ሲሆን መነሻ ስርወ ቃሉም  የአንግሎ ሳክሶን ቃል ከሆነው / sunnandei/ ከሚለው የመጣ ቃል ነው። ትርጉሙም የፀሀይ ቀን ነው።  እሁድ ወይም /ዮም ርሾን יום ראשון/ ማለት የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን ማለት ነው። ዮም ርሾን እንደአንድ ቁጥር/ 1/  ሆኖም ያገልግላል። የአይሁድ ሰንበት፤ ሰባተኛው ቀን እንደመሆኑ መጠን የእሁድን የመጀመሪያ ቀን መሆንን ከአንድ ተነስተን ብንቆጥር ያረጋግጥልናል። ይህ የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን/ እሁድ/ በጥንት ሮማውያን ዘንድ ከሥራ ሁሉ የእረፍት ቀን ሆኖም አገልግሏል። ቆስጠንጢኖስ ንጉሥ መጋቢት 10/ 313 ዓ/ም ይህንን ቀን የሮማውያን ግዛት እረፍት ቀን ይሆን ዘንድ በአዋጅ አጽድቆታል።  ስለእሁድ የመጀመሪያ ቀን መሆንና በጥንታዊው ስያሜ ዙሪያ ታሪካዊ ዳራውን በአጭሩ ካመላከትን መንፈሳዊ አመጣጡን ደግሞ በጥቂቱ እንመልከት።
1/ ሰባተኛ ቀን፤
ሰንበት የሚለው ቃል ከእብራይስጡ Shabbat (שַׁבָּת) ከሚለው ቃል የመጣ ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙም ከድካም ማረፍ ወይም ሥራን ማቆም (to cease or to desist from exertion) ማለት ነው። ሰንበት እግዚአብሔር በብሉይ ኪዳን ለእስራኤል ከሰጠው አሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ አንዱ ነው።
 ኦሪት ዘጸአት 20:8-11  የሰንበትን ቀን ትቀድሰው ዘንድ አስብ።ስድስት ቀን ሥራ ተግባርህንም ሁሉ አድርግ:: ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር ለአምላክህ ሰንበት ነው አንተ፥ ወንድ ልጅህም፥ ሴት ልጅህም፥ ሎሌህም፥ ገረድህም፥ ከብትህም፥ በደጆችህም ውስጥ ያለ እንግዳ በእርሱ ምንም ሥራ አትሥሩ:: እግዚአብሔር በስድስት ቀን ሰማይንና ምድርን፥ ባሕርንም፥ ያለባቸውንም ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ዐርፎአልና ስለዚህ እግዚአብሔር የሰንበትን ቀን ባርኮታል ቀድሶታልም።
የቃሉ ትርጉምና እንዲሁም መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚናገረው ሰንበት ከድካምና ከሥራ ሰዎችና እንስሳት የሚያርፉበት የእረፍት ቀን ነው። በተለይ ከሰንበት ጋር ተያይዞ የተጠቀሱት ሎሌዎች፣ የቤት ሠራተኞች፣ ባሪያዎችና ከብቶች በዚያን ጊዜ እጅግ አድካሚ ሥራ ይሠሩና ይለፉ የነበሩ ናቸው። ሰለዚህ ሰንበት በመጀመሪያ ደረጃ እግዚአብሔር ከሠራው ሥራ በሰባተኛው ቀን እንዳረፈ ሁሉ ከሥራና ከድካም ማረፍ ጋር የተያያዘ ነው። ለዚህ ነው ሰውን ብቻ ሳይሆን የአምልኮ ፕሮግራም ማድረግ የማይችሉትን ከብቶችንም የሰንበት ትእዛዝ የሚያጠቃልለው።
ከዚህ በተጨማሪ ሰንበት በእግዚአብሔርና በእስራኤል ሕዝብ መካከል የተደረገ የምልክት ቃል ኪዳን ነው። እንደማናቸውም የብሉይ ኪዳን ሕግ ሰንበትም በማያከብሩት ላይ መርገምና ፍርድ የሚያመጣም ትእዛዝ ነው።
ኦሪት ዘጸአት 31:12-17 እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው። ለእስራኤል ልጆች እንዲህ ብለህ ንገራቸው። እኔ የምቀድሳችሁ እግዚአብሔር እንደ ሆንሁ ታውቁ ዘንድ በእኔና በእናንተ ዘንድ ለልጅ ልጃችሁ ምልክት ነውና ሰንበቶቼን ፈጽሞ ጠብቁ። ስለዚህ ለእናንተ ቅዱስ ነውና ሰንበትን ጠብቁ የሚያረክሰውም ሰው ሁሉ ፈጽሞ ይገደል፥ ሥራንም በእርሱ የሠራ ሰው ሁሉ ከሕዝቡ መካከል ተለይቶ ይጥፋ። ስድስት ቀን ሥራን ሥራ ሰባተኛው ቀን ግን ለእግዚአብሔር የተቀደሰ የዕረፍት ሰንበት ነው በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል። የእስራኤልም ልጆች ለልጅ ልጃቸው ለዘላለም ቃል ኪዳን በሰንበት ያርፉ ዘንድ ሰንበትን ይጠብቁ። እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን በስድስት ቀን ስለ ፈጠረ፥ በሰባተኛውም ቀን ከሥራው ስላረፈና ስለ ተነፈሰ፥ በእኔና በእስራኤል ልጆች ዘንድ የዘላለም ምልክት ነው።
ብዙ ጊዜ ሰንበት ተብሎ በልማድ የሚታወቀው ሥራ የማይሠራበትንና የአምልኮ ፕሮግራሞች የሚካሄዱበትን ቀን ነው። በመጽሐፍ ቅዱስ ግን ሰንበት የሚባለው በእስራኤልና በእግዚአብሔር ብቻ የተገባን ቃል ኪዳን ነው። በዚያ ቀን "የአምልኮ ፕሮግራም የማይካፈል ይሙት" ሳይሆን ትእዛዙ የሚለው "በሰንበት ቀን የሚሠራ ሁሉ ፈጽሞ ይገደል" የሚል ፍርድና ቅጣት ያለው ነው። በብሉይ ኪዳንም ይሁን በአሁኑ ዘመን እስራኤላውያን ሰንበትን የሚጠብቁት ቅዳሜ ነው፡፡
2/ የመጀመሪያው ቀን
ክርስቲያኖች የአይሁድ ሰንበትን ይጠብቁ ዘንድ አልታዘዙም። በእርግጥ እስራኤላዊ ሆነው ወደ ጌታ እምነት የሚመጡ ሰንበትን መጠበቅ ይችላሉ አልተከለከሉም። ነገር ግን ሰንበት ለክርስቲያኖች የተሰጠ ትእዛዝ አይደለም። እስራኤላዊ ባልሆኑ አህዛብ ክርስቲያኖችም ዘንድ በአዲስ ኪዳን ሰንበት ሲጠበቅ ይሁን ሰንበትን እንዲጠብቁ ሲታዘዙ አናነብብም። ይህ ብቻ አይደለም፤ በመጽሐፍ ቅዱስ ክርስቲያኖች ይጠብቁትና ያከብሩት ዘንድ የተሰጠ ምንም ዓይነት ቀን ወይም በዓል የለም። ክርስትና የቀኖችና የበዓላቶች አክብሮ ሳይሆን በመንፈስ ቅዱስ የሆነ ሕይወት ነውና።
ወደ ቆላስይስ ሰዎች 2:16-17 እንግዲህ በመብል ወይም በመጠጥ ወይም ስለ በዓል ወይም ስለ ወር መባቻ ወይም ስለ ሰንበት ማንም አይፍረድባችሁ። እነዚህ ሊመጡ ያሉት ነገሮች ጥላ ናቸውና፥ አካሉ ግን የክርስቶስ ነው።
በአዲስ ኪዳን ክርስቲያኖች በዚያን ዘመን የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን በሆነው እሁድ እሁድ ይሰበሰቡና ጌታን እያመለኩ የጌታን እራት ይካፈሉ እንደነበር ተጽፎአል፦
የሐዋርያት ሥራ 20፥7 ከሳምንቱም በመጀመሪያ ቀን እንጀራ ለመቁረስ ተሰብስበን ሳለን፥ ጳውሎስ በነገው ሊሄድ ስላሰበ ከእነርሱ ጋር ይነጋገር ነበር፥ እስከ መንፈቀ ሌሊትም ነገሩን አስረዘመ።
ይህ የሳምንቱ መጀመሪያ የሆነው እሁድ ቀን ጌታ ኢየሱስ ከሙታን የተነሳበትም ቀን ሰለ ነበር አንዳንዴም የጌታ ቀን ተብሎ ይጠራል፦
የሉቃስ ወንጌል 24:1-5 ነገር ግን ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን ያዘጋጁትን ሽቱ ይዘው ከእነርሱም ጋር አንዳንዶቹ ወደ መቃብሩ እጅግ ማልደው መጡ። ድንጋዩንም ከመቃብሩ ተንከባሎ አገኙት፥ ገብተውም የጌታን የኢየሱስን ሥጋ አላገኙም። እነርሱም በዚህ ሲያመነቱ፥ እነሆ፥ ሁለት ሰዎች የሚያንጸባርቅ ልብስ ለብሰው ወደ እነርሱ ቀረቡ፤ ፈርተውም ፊታቸውን ወደ ምድር አቀርቅረው ሳሉ፥ እንዲህ አሉአቸው። ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ? ተነሥቶአል እንጂ በዚህ የለም።
የዮሐንስ ራእይ 1፥10 በጌታ ቀን በመንፈስ ነበርሁ፥ በኋላዬም የመለከትን ድምፅ የሚመስል ትላቅ ድምፅ ሰማሁ፥
አዲስ ኪዳን የሚሰጠው ፍንጭ ክርስቲያኖች ጌታ ኢየሱስ በተነሳበት ቀን እሁድ እግዚአብሔርን እንደሚያመልኩና የጌታን እራት እየቆረሱ ሕብረት እንደሚያደርጉ ያመለክታል። ይሄንን ሲያደርጉ ግን ሰንበትን እያከበሩ አይደለም፡፡ ሰራተኞቻቸውንና ከብቶቻቸውን ወዘተ ቀኑን ሙሉ ከድካማቸው እያሳረፉና ሰው ቢተላለፈው ፍርድ ያለበትን በሕግ የተደነገገውን ሰንበትን እያከበሩ አይደለም። በአዲስ ኪዳን የቀንና የምግብ እርኩስና ቅዱስ የለም! የምግብና የበዓላት ትእዛዛት ሁሉ በሕግ ውስጥ ካለ የሥርዓት ሸክምና ለጽድቅ የሚደረግ ልፋት ሊያሳርፈንና ወደ እረፍቱ ሊያስገባን የመጣው የክርስቶስ ጥላዎችና ምሳሌዎች ብቻ ናቸው። የክርስቶስ የሆኑትስ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ እነርሱም ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብና እርሱን ለማግኘት ከሚደረግ የሥርዓት ጥረትና ድካም እርሱን አግኝተው አርፈዋል። ወደ እግዚአብሔር ሰንበትም ገብተዋል።
ወደ ዕብራውያን 4:9-10 እንግዲያስ የሰንበት ዕረፍት ለእግዚአብሔር ሕዝብ ቀርቶላቸዋል። ወደ ዕረፍቱ የገባ፥ እግዚአብሔር ከሥራው እንዳረፈ፥ እርሱ ደግሞ ከሥራው አርፎአልና።
ስለዚህ ክርስቲያኖች ምንም እንኳን ታሪካዊ አመጣጡ ለብዙ የታሪክ ተመራማሪዎችም እንኳን ግልጽ ባልሆነ እሁድ እሁድ የመሰብሰብና እግዚአብሔርን የማምለክ ልምድ ቢኖራቸውም፤ ይሄን ግን እንደ ሰንበት መውሰድ ወይም ይባስ ብሎ ሰንበት ከቅዳሜ ወደ እሁድ እንደተቀየረ ማሰብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም። እሁድ የክርስቲያኖች ሰንበት አይደለም። የብሉይ ኪዳኑን ሰንበትን የመጠበቅ ትእዛዝ ለአዲስ ኪዳን አማኞች አልተሰጠም። ማንም ግን ሰንበትን ማክበር ቢፈልግ፤ ሰንበት ሕግ ነውና ሕጉ ደግሞ ያለ መርገም አልመጣምና በሰንበት ምንም አይነት ሥራ ቢሠራ ራሱን ከሕግና ከእርግማን በታች እያደረገ ነው። ኢየሱስ ክርስቶስ ከሕግና ከእርግማን በታች ሳንሆን ከጸጋ በታች ሆነን በነጻነት እንድንኖር ከሕግ እርግማን ሊያመጣን መጣ እንጂ እንደገና ለሥርዓትና ለበዓላት ባርነት አልጠራንም።
ወደ ገላትያ ሰዎች 3፦11-13  ከሕግ ሥራ የሆኑት ሁሉ በእርግማን በታች ናቸውና፤ በሕግ መጽሐፍ በተጻፉት ሁሉ ጸንቶ የማይኖር የማያደርግም ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና።ጻድቅ በእምነት ይኖራል ተብሎአልና ማንም በእግዚአብሔር ፊት በሕግ እንዳይጸድቅ ግልጥ ነው። ሕግም ከእምነት አይደለም ነገር ግን፤ የሚያደርገው ይኖርበታል ተብሎአል። በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለ እኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤
3/ ማጠቃለያ፣
የአይሁድ ሰንበት በእግዚአብሔር በራሱ ከፍጥረት ሥራው በማረፍ ለአይሁዳውያን የተሰጠ የተለየ ቀን ነው። በኋለኛው አዲስ ዘመን ደግሞ ዓለሙን ሁሉ በልጁ ደም ካዳነ በኋላ የመጀመሪያውን ቀን ወይም የጌታ ቀን የተባለውን ዕለት በአይሁዳውያን ሰንበት መልኩ በማረፍ፤ እናንተም ዕረፉ በማለት ሕግን አልሰጠም። ስለዚህም የክርስቲያን ሰንበት የሚባል ቀን የለም። ትንሣዔውን፤ ዕርገቱን፤ ቅዱሳን በጌታ ቀን ሲጸልዩ መታየታቸው በራሱ የዕረፍት ቀን የመሆንን ሕግ ሳይሆን የሚያመለክተው መንፈሳዊ ተግባራትን በማድረግ፤ ቃሉን በማሰብና በመጸለይ ብናሳልፍ መልካም እንዲሆንልን የሚያመለክት ነው። ለጸሎት፤ ለቅዳሴ፣ ለጾምና ጸሎት መፋጠን የተለየ ድንጋጌ መሰጠቱን አያመለክትም። ቅጠል በመበጠስ፤ ከአንድ ምዕራፍ በላይ መንገድ በመሄድ ወይም ሥራ በመስራታችን ለቀኑ ከተሰጠ ድንጋጌና የውግዘት እርግማን ለመጠበቅ ተብሎ አይደለም። እንደአይሁድ ሰንበት የሚያከብሩ ሰዎች  አልፈው ተርፈው፤ የእመቤታችንን 33 በዓላተ ቀኖቿን እንደእሁድ ሰንበት ያላከበረ ፈጽሞ የተወገዘ ይሁን በማለት ብዙ ሰንበታት ፈጥረውልን ይገኛሉ። /መቅድመ ተአምር/ ከዚያም  ባለፈ ሰንበተ ክርስቲያን ተብላ በሰዎች የተሰየመችው ይህች ቀን በሰው አምሳል ከመጥራት ተጀምሮ መልሷን እስከመፈለግም ተደርሷል።«ሰዓሊ ለነ ሰንበተ ክርስቲያን ቅድስት፣ለውሉደ ሰብእ መድኃኒት፣ ወእስከ ለዓለም ሰፋኒት» ትርጉም--ለሰው ልጆች መድኃኒትና እስከዘለዓለም ገዢ የሆንሽ፣ ቅድስት የክርስቲያን ሰንበት ሆይ ለምኝልን ማለት ነው። ሰንበት የተባለው ክርስቶስ ራሱ ነው የሚሉ ደካማዎች ቢኖሩም ክርስቶስን « ለምኝልን» ሊሉ ቢመኙ እንዴትና ከማን? በሚል ጥያቄ ማጣደፋችን አይቀርም። ይልቁንም ይህ የክርስቲያን ሰንበት እንዳለ ከሚያስብ አእምሮ የመነጨ ትምህርት ነው። አንዲቱን ቀን በሰው አንደበት እያናገሩ፤ ከሷ ምላሽ መጠበቅ ክርስቲያናዊ ትምህርት አይደለም።
ብዙ አይሁዶች ከይሁዲነት ወደክርስትና ሲመለሱ ቀዳሚት ሰንበትን በነበራቸው ልምድ ዓይነት የክርስቲያን ሰንበት አድርገው ያከብሩ ነበር። የቀዳሚት ሰንበትን የማክበር ባህል በሀገራችን እስካሁን ድረስ በብዙ ቦታዎች አልተቀየረም። ቀዳሚት ሰንበት የአይሁድ በዓል እንጂ የክርስቲያኖች እንዳልሆነ በ363 ዓ/ም የላኦዲቂያ ጉባዔ አንቀጽ 29 ላይ ተደንግጎ ነበር።  የክርስቶስ ሞትና ትንሣዔ የተለየች ቀንን ለመባረክና የእረፍት ቀን ለማድረግ ሳይሆን ክርስቲያኖች ከነበረን የሕግ ሸክም ሊያሳርፈን መሆኑን ልንረዳ ይገባል። እሁድን በጸሎት፤ በምሥጋናና በቅዳሴ ብናከብር ለክርስቲያን የተሰጠ ልዩ ቀንና ሰንበት ስለሆነ አይደለም። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ቀናት ውስጥ ርጉምና ቅዱስ የሚባል የለም።