Friday, May 10, 2013

«ጠንቋዩ ግርማ ወንድሙ በእስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ሲያደርግ ከነበረው የጥንቆላ ሥራው ታገደ»



ግርማ ወንድሙ የተባለው አጥማቂ ነኝ ባይ ግለሰብ ከሚያዚያ 28/2005 ዓ/ም ጀምሮ ከአጥማቂነት ሥራው መታገዱንና ሰው ማንጋጋቱን እንዲያቆም የታዘዘ መሆኑን አያይዞ ባወጣው የእግድ ደብዳቤ ላይ ዝርዝር ምክንያቱን ተጠቅሶ ተጽፎለታል።
እንደሚታወቀው ጠንቅ ዋይ ግርማ ወንድሙ  በመንግሥት ባልተመዘገበና ከአነስተኛና ጥቃቅን የሥራ መስኮች ውስጥ አንዱ ባልሆነው ልዩ የሥራ ፈጠራ ላይ ተሰማርቶ ጥንቆላውን በሱዳንና በሺናሻ ዕጽ እየታገዘ ጤናማውን ሁሉ እያሳበደና እያስጮኸ ሲያጭበረብር መቆየቱ ይታወቃል። ቤተ ክህነት ይህንን ማጭበርበሩን በጸጋ መንፈስ ቅዱስ የሚያደርግ ያህል ቆጥራ ዝምታን በመመምረጧ ልጆቼ ናቸው የምትላቸው ተከታዮቿን ገንዘባቸውን እየመዘበረ፤ አእምሮአቸውን እያቃወሰ፤ የተረጋጋና ሰላማዊ ኑሮ እንዳይኖሩ ብኩን እያደረገ፤ ለሰይጣን ግዛት እያመቻቸ ሲሸኛቸው እስካሁን ዝም ከማለቷ ባሻገር አቡነ እስጢፋኖስን የመሳሰሉ ጳጳሳት ደግሞ ለግርማ ወንድሙ ጥንቆላ እውቅና በመስጠት ይባስ ብለው ሀገረ ስብከታቸው ድረስ ወስደው ሕዝቡን እያሳበደ ገንዘብ እንዲሰበስብላቸው እስከማድረግ መድረሳቸውን አይተን አፍረናል።
ግርማ ወንድሙ የሥራ ፈጠራውን ተደናቂ የሚያደርገው በቤተክርስቲያን ከለላ ስሟን እየጠራና ግቢዋን ተተግኖ መሆኑ እንጂ በግብር ከታምራት ገለታ የሚለይ አይደለም። ከዚያ ባሻገር በስመ አጥማቂና ባህታዊ በቤተ ክርስቲያን ተጠግተው ሕዝብ በማስጮህ ገንዘብ የመሰብሰቢያ ስልት እንጂ ግርማ ወንድሙ መንፈስ ቅዱስ ስላደረበት አይደለም። ቅዱሳን በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሙት ሲያስነሱም ሆነ ድውይ ሲፈውሱ ውሃ ውስጥ በመዝፈቅ ወይም በመቁጠሪያ በመደብደብ ሳይሆን ስመ እግዚአብሔርን በመጥራት ብቻ ነው።
«ጴጥሮስ ግን። ብርና ወርቅ የለኝም፤ ይህን ያለኝን ግን እሰጥሃለሁ፤ በናዝሬቱ በኢየሱስ ክርስቶስ ስም ተነሣና ተመላለስ አለው።በቀኝ እጁም ይዞ አስነሣው፤ በዚያን ጊዜም እግሩና ቍርጭምጭምቱ ጸና» የሐዋ 3፤6-7
መንፈስ ቅዱስ ባደረባቸው አባቶች እንኳን ቃል ተናግረው ይቅርና ጥላቸው ሲያርፍባቸው ሙታን ይነሱ፤ ድውያን ይፈወሱ ነበር። ጠንቅ ዋዩ ግርማ ወንድሙ ግን በእጁ ላይ የሚያንጠለጥላትን መቁጠሪያ ካልያዘ ማዳን ሳይሆን ማሳበድ የማይችል አስማተኛ ነው። የቅርብ ወዳጁ የሆነ አንድ ሰው መረጃ እንዳካፈለን ግርማ ወንድሙ ገንዘብን የአምላኩ ያህል እንደሚወድና እስካሁንም ባግበሰበሰው ብር እንዳልረካ ነገር ግን ወደአሜሪካ መሄድ የሚችልበትን መንገድ ወይም ከሰዎች ጋር እንዲያገናኘው ብዙ ጊዜ እንደጠየቀው የገለጸልን ሲሆን ይህንን ለገንዘብ ያለውን ፍቅር በመመልከት ቀድሞ በሱ ላይ የነበረውን የማጥመቅ ችሎታ እንደተጠራጠረው ተናግሯል። አሜሪካ የመሄዱ ጉዳይ ለጊዜው ባይሳካለትም ሰሞኑን ወደእስራኤል በአበሾች ላይ  እብደት በማስፋፋት ገንዘብ ለመሰብሰብ ማቅናቱ ይነገራል። የግርማን ከሀገር መውጣት ተከትሎ የእስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ በሌለበት የእግድ ደብዳቤ ጽፈውበታል። ቀጣዩ ጉዞው ምናልባትም አሜሪካ ይሆንና የሚበቃውን ዘርፎ የሚመኘውን ያህል ካገኘ አንዷን ቆንጆ አግብቶ ባለትልቅ ኢንቨስትመንት ባለቤት የመሆን ሕልሙን ያሳካል ማለት ነው። የሰው ሃሳብ እንደዚያ ቢሆንም የእግዚአብሔር የተለየ ስለሆነ ግርማ ወንድሙ ሥጋዊ ሩጫህን በጥንቆላ ከምትጨርስ ንስሐ በመግባት ራስህን አድን ምክራችን ነው።
 የእግዱን ደብዳቤ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ