Thursday, May 2, 2013

ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአል!





ዕብራውያን     פֶּסַח» ፔሳኽ» ይሉታል። ፋሲካ ማለት ነው።  በወርኀ ኒሳን በዐሥራ ዐምስተኛው ቀን ይከበራል። ሥርዓቱ የሚጀመረው በዐሥራ አራተኛው ቀን ዋዜማ ሲሆን በፋሲካው ሳምንት እርሾ የገባበት ምንም ዓይነት ምግብ መመገብ ክልክል ነው።ዕለቱን ተቦክቶ ወዲያው የሚጋገር እንጂ የኮመጠጠ ወይም የቦካና የዋለ፤ያደረ መመገብ በሕጉ እንደተቀመጠው ከእስራኤል አንድነት ያስወግዳል። ከማንኛውም እርድ ላይ ጥሬ መብላት ወይም ከበሉትም አስተርፎ ማሳደር አይፈቀድም። ለመስዋዕት የሚቀርበው የበግ ወይም የፍየል መስዋዕትም እድሜው ከአንድ ዓመት ያልበለጠ ጤናማና የተመረጠ መሆን ይገባዋል። በዐሥራ ዐራተኛው ቀን ምሽት መስዋዕቱ ይታረዳል።ሥጋውን ደግሞ ሌሊት  ከመራራ ቅጠል ጋር ቀላልቅለው ይበሉታል።  
ደሙን ደግሞ  የበሩን ሁለት መቃንና ጉበኑን ይቀቡታል።  ሁለቱን ቋሚ መቃንና የላይኛውን ጉበን ሲቀቡት ይህንን ቅርጽ ይይዛል።

 
ይህ ቅርጽ የዕብራውያን ስምንተኛውን ፊደል «ኼ» የተባለውን ይወክላል። (እንደአማርኛው በጉሮሮ ሳይሆን በላንቃ የሚነበብ ነው) «ኼ» ማለት በዕብራውያን ትርጉም «ሕይወት» ማለት ነው። ዕብራውያንም በፊደላቸው በ«ኼ» ቅርጽ በሚቀቡት ደም የተነሳ ወደፈርዖናውያን ሠፈር የሚያልፈው ሞት አይነካቸውም። ምክንያቱም ሕይወት የሚል ማኅተም በራቸው ላይ ታትሟልና። ፋሲካ ማለት ይህ ነው። በደሙ ምልክት የተከለሉ በሕይወት ለመቆየት ዋስትና የያዙ ሲሆን ይህንን ማኅተም ያላገኙና ምን እየሆነ እንዳለ የማያውቁ ደግሞ  በሞት የሚወስዱበት  የፍርድ ምልክት ነው። ደሙ የሞትና የሕይወት መለያ ምልክት ሆኖ አገልግሏል።

ይህ ሥርዓት እስራኤላውያንን ከባርነት፤ ከጠላት አገዛዝና ከመገደል የታደገ የዋስትና መንገድ ነበር። እንደዚሁ ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካ ሕዝብና አሕዛብን ከሰይጣን ባርነትና ከዘላለም ሞት የታደገ በመሆኑ ሐዋርያው ጳውሎስ «እንግዲህ ያለ እርሾ እንዳላችሁ አዲሱን ሊጥ ትሆኑ ዘንድ አሮጌውን እርሾ አስወግዱ። ፋሲካችን ክርስቶስ ታርዶአልና» 1ኛ ቆሮ 5፤7 በማለት የሚነግረን።  የእስራኤል ዘሥጋ ፋሲካ መጻጻና የቦካ ይከለክል እንደነበረው ሁሉ የአዲስ ኪዳኑ ፋሲካም እንዲሁ ይከለክላል። በኃጢአትና በዐመጻ የቦካ የውስጣችንን ሆምጣጣ እርሾ ካላስወገድን በስተቀር በፋሲካው የሚገኘውን ሕይወት በፍጹም  አናገኝም።  የቀደመው ፋሲካ እርሾ ያለውን ነገር ከቤቱ ያላጠፋ ከእስራኤል ጉባዔ ተለይቶ ይጥፋ የሚል ሕግ ነበረው።  ምድራዊው ፋሲካ ይህንን ያህል ከከበረ ሰማያዊውማ እንደምን የበለጠ አይከብር? ፋሲካን መናገርና ፋሲካን አውቆ መኖር የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ስለፋሲካ ብዙ ማስተማርና መናገር ይቻል ይሆናል። ስለፋሲካ የመልካም ጊዜ መግለጫና ስጦታም መለዋወጥ ይቻል ይሆናል። ፋሲካ ግን በእነዚህ ሁኔታዎች ውስጥ አይገኝም። ፋሲካ በስግደትና በወይራ ቅጠል በመጠብጠብ የሚገኝም ጸጋ አይደለም።  ፋሲካ የአንድ ወቅት ራስን ማስገዛትና በጽኑ እሳቤና ጭንቅ ማለፍ ውስጥ የሚመጣም አይደለም።

ፋሲካ በልባችን መቃንና ጉበን ላይ የደሙን ምልክት በመያዝ ዕብራውያን ከሞት እንዳመለጡበት የ «ኼ» ምልክት ማኅተም በመያዝ ብቻ ነው የምንድነው። ያን ጊዜ ብቻ ነው ሞት በራችን ላይ ያለውን የአዲስ ኪዳኑን ፔሳኽ አይቶ የሚያልፈን። ይህንን የደም ማኅተም ለመያዝም ከክፋት፤ ከሀሰት፤ ከግፍና ከዐመጻ እርሾ መለየት የግድ ነው። ከዝሙት፤ ከስርቆት፤ ከጉቦ፤ ከምኞትና ከኃጢአት ሁሉ እርሾ ሳንለይ ውስጣችን የሞላውን መጻጻ ተሸክመን የፋሲካ ሕይወት አይገኝም። ጳውሎስም እንዲህ አለን።

«ስለዚህ በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም» 1ኛ ቆሮ 5፤8

እንግዲህ  ከፋሲካው ተስፋ የምናደርግ ሁላችን እስኪ ራሳችንን እንመርምር። እንደመጽሐፍ ሊያነበን በሚቻለው ከፋሲካችን ክርስቶስ ፊት እስኪ ራሳችንን እናንብበው። በእውነት እነዚህ እርሾዎች በውስጣችን ከሌሉ ከ2000 ዓመት በፊት ለሕይወት የፈሰሰውን ደም ይዘናል ማለት ነው። ያኔም ሞት በኛ ላይ ምንም ሥልጣን እንደሌለው አረጋግጠናል። እስራኤላውያን የበራቸውን ጉበንና መቃን በቀቡ ጊዜ ሞት እንደማይነካቸው እርግጠኞች እንደነበሩ ሁሉ እኛም የበለጠውንና የተሻለውን የሕይወት ደም በእምነት ስለያዝን ለዘላለማዊ ሕይወት እርግጠኞች መሆን እንችላለን። ከዚያ ባሻገር በየዓመቱ በሚመጣ በዓል የሚገኝ የደም ምልክት የለም። በጥብጠባና በስግደትም የሚገኝ የሕይወት ዋስትና የለም። የተደረገልንን ማሰብ አንድ ነገር ሆኖ ሰው ግን ዓይኑን በዚያ በዓል ላይ ተክሎ የዓመቱ ኃጢአት ወይም ሸክም እንደሚወድቅ ማሰብ ስህተት ነው። ዓመቱን ሙሉ ከክፋትና ከግፍ እርሾ በመላቀቅ፤ አንድም ሰከንድ የማይለይ የልባችንን ጉበንና መቃን ላይ ደሙን በእምነት ይዘን መገኘት የግድ ይሆንብናል። ያኔ ነው ፋሲካችን ታርዷል የምንለው። ያኔም ነው ሁልጊዜ በሕይወት መንገድ ላይ እንዳለን የምናውቀው። መንፈሳዊ ሕይወት እንዲኖረን፤ መንፈሳዊ ጉዞ እንዲሰምርልን ዕለት፤ ዕለት መታደስ መታደስ ይገባዋል።

«ስለዚህም አንታክትም፥ ነገር ግን የውጭው ሰውነታችን ቢጠፋ እንኳ የውስጡ ሰውነታችን ዕለት ዕለት ይታደሳል» 2ኛ ቆሮ 4፤16

ፋሲካችን የሆነው ክርስቶስ ኢየሱስ ያደረገልንን ውለታ እያሰብን ውስጣችንን መፈተሽ የግድ ነው። በአምናው እኛነታችንና በዘንድሮው እኛነታችን መካከል የሕይወት ለውጥ ከሌለን ሞት በመጣ ጊዜ ምንም የመዳን ምልክት እንደሌላቸው ፈርዖናውያንን ወደዘላለማዊ ሞት መሄዳችን እውነት ነው። በወይራ በመጠብጠብ 30 እና 40 ለመስገድ ከመሽቀዳደም ይልቅ፤ ከሞት የማምለጫ የፋሲካው ዓርማ ክርስቶስን ከኃጢአት በጸዳ ማንነታችን ውስጥ ዘወትር ይዘነው እንኑር።  የሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እሁድ ነው። ከእሁድ እስከ እሁድ 8 ቀናት አሉት። ዕብራውያን የበራቸውን ጉበንና መቃን የቀቡት ቅርጽ ከዕብራውያን አሌፋት መካከል የ «ኼ» ስምንተኛው ፊደል አምሳል ነው። «ኼ» ደግሞ ትርጉሟ «ሕይወት» ማለት ነው። ይህ የደም ምልክት ነው ሕይወት የሆናቸው። በሳምንቱ የመጀመሪያው ቀን የአዲስ ኪዳኑ ሕይወት በክርስቶስ ትንሣዔ ለዓለሙ ሁሉ ታደለ። ይልቅስ ይህንን ደም በልባችንን ጉበንና መቃን ላይ እንደንጹሕ መስዋዕትለመቀባት እንሽቀዳደም። ያኔም ትንሣዔው የእኛ ሕይወት ይሆናል!!