Tuesday, May 14, 2013

ኢህ አዴግ ምን ይጠብቃል?


ምድራውያን መንግሥታት በተወሰነ ጊዜ ውስጥ  ይመጣሉ፤ ይሄዳሉ፤ እስከምጽአት ቀን ሕዝቦች ግን በሀገራቸው ቋሚ ዘላቂ ትውልዶች ሆነው ይቀጥላሉ። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ውስጥ ከቅርብ ጊዜ በኋላ ሕዝቡን የሚያቃቅር፤ እርስ በእርሱ የሚያፋጅ፤ ጎሳ ዘርና ብሔር የሚለያይ፤ ሃይማኖታዊ ብጥብጥን የሚቀሰቅሱ ሁኔታዎች እየታዩ መሆናቸው ሀገራችንን ወዴት እየወሰዳት ነው ከሚያሰኝበት ደረጃ ላይ ደርሷል። የብሔሮች እኩልነትና የሃይማኖቶች ነጻነት ተከብሮባታል በተባለባት ኢትዮጵያ ውስጥ አሳዛኝ ሂደቶች እየታዩ ነው። በጭፍን ጥላቻ የትግራይን ብሔር የሚጠሉ እንዳሉ አማራውን ሁሉ እንደጨቋኝ የሚመለከቱ ሰዎችም የጥላቻ ዘር እየዘሩ መገኘታቸው ወደፊት ምን ዓይነት ሁኔታ ይፈጠር ይሆን ቢያሰኘን አግባብነት አለው ብለን እናስባለን። በሩዋንዳና በቡሩንዲ፤ በሴራሊዮንና በላይቤሪያ፤ በኮንጎና ኮትዲቯር የተከሰተው ፍጅት አሁን በሀገራችን ውስጥ እየታየ እንዳለው የብሔርና የጎሳ ጥላቻዎች ቀስ በቀስ እያደጉ የፈጠሩት ክስተት እንጂ ድንገት የደረሰ አይደለም። ስለዚህ ማዕከላዊ የኢትዮጵያ መንግሥት ዝም ብሎ የሚያየው እስከመቼ ነው? የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ሆኖ የፌዴራሉ መንግሥት አካል የሆነው ግለሰብ በአማራና በትግራይ፤ በአሮሞና በሌሎች ብሔሮች መካከል የዘር ፍጅት እንዲከሰት ለጎሳ መሪዎች ማብራሪያና መግለጫ መስጠቱን እንዴት በዝምታ ይመለከተዋል? አማሮችንና ኦሮሞዎችን ጥሉ፤ ትግሬዎችን ውደዱ ማለት ምን ማለት ነው? በአንድ ቀን ከስልጣን አስወርዶ በሕግ ቁጥጥር ስር የሚያስውለውን ይህንን ቅስቀሳ መንግሥት ዝም ማለቱ በቅስቀሳው ፈቃደኝነቱን አያሳይም?  ቃላት እየተተረጎመ ጋዜጠኞች ሕዝብን ለዐመጽ በማነሳሳት ወንጀል እስከእድሜ ልክ ሲፈረድባቸው ይህ የክልል ፕሬዚዳንት ሆኖ ዘር ከዘር ሊያፋጅ ትምህርትና ስልጠና ሲሰጥ ዝም የሚባለው ለምንድነው? ኢሳት የተባለው በውጭ ሀገር የሚገኘው ቴሌቪዥን ጣቢያ መረጃዎችን አግኝቶ ባያወጣው ኖሮ ውስጥ ውስጡን ይህ ቅሰቀሳና ዘመቻ  እንደማይኖር ምን ማረጋገጫ ይኖረናል? ኢሳትን ውሸታምና የቅጥረኛ ቴሌቪዥን ጣቢያ እያሉ ከማጣጣል ይልቅ የተባሉትን መረጃዎች አጣርቶ የሕዝቡን የጥያቄ ወይም የጥርጣሬ መንፈስ ማስተካከል አይሻልም? በበኩላችን የሀገራችን የሕዝቦች አንድነትና እኩልነት፤ ሰላምና ነጻነት የተከበረባት ኢትዮጵያ እንድትኖር ካለን ጽኑ ፍላጎት የተነሳ የሶማሌ ክልል ፕሬዚዳንት ኦሮሞና አማራ እርስ በእርስ የሚፋጁ ጠላቶች ናቸው፤ ትግሬዎች ግን ወዳጆች ናቸው ያሉበትን፤ የቅርብ ሠራተኛቸውና የሶማሌ ክልል ተወላጅ የሆነው ወጣት ለኢሳት የተረጎመውን ይህንን ቪዲዮ እንዳለ ለማቅረብ ወደናል። «አሁን ምን ያደርጋል ድስትን ጥዶ ማልቀስ፤ አስቀድሞ ነበር መጥኖ መደቆስ»እንዲሉ መንግሥት የእርምት እርምጃውን አስቀድሞ እንዲወስድ ጥያቄያችንን በዚሁ አጋጣሚ ለማቅረብ እንወዳለን።