Monday, November 24, 2025

የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ስለተቀየረ ሰይጣን ውጊያውን አያቆምም!

gg
(ከመሥፍን ግርማ) እኔ ከወንጌላውያን አማኞች ነኝ። አዎ ኦርቶዶክስ ብዙ የአስተምህሮ መፋለስ አለባት። ነገር ግን ይሄንን ቄስ በማጣቷ ምንም አልተጎዳችም። እንዲያውም እየተጎዱ ያሉት ይሄን ሰውዬ የተቀበሉ ወንጌላውያን ናቸው። ሰውየው ወንጌል አልገባውም። ከገባውም እየኖረበት አይደለም። መዋሸትና ማጭበርበር መደበኛ ስራው አድርጓል። ኦርቶዶክስን መሳደብ እውቀት መስሎታል። የትኛውም ቦታ አፉን የሚያሟሸው ኦርቶዶክስን በመሳደብ ነው። ይሄንን ቄስ ተረጋጋ የሚለው ዘመድ እንዴት ይጥፋ? የተቀበሉት ወንጌላውያንም የላንቃህን ቶን ትንሽ ቀነስ አድርግ ማለት ለምን አቃታቸው? በጣም መልፍለፍ አበዛ። ሰውየው ቀራንዮ አካባቢ ሚስቱ አስወልዶ እንደጣላት ስትከሰው ሰምተናል። ያስወለዳቸውን ልጆች ያላሳደገ አሁን ስለ ዘመን አቆጣጠር መለፍለፍ እውቀት መስሎታል። በትክክል ድኖ ከሆነ የዳነ ሰው ሕይወትን ይኑር። ንግግሩ የታረመ ይሁን። ትምሕርቱ ወንጌልን ይግለጥ፣ ሰዎች ወደመዳን እንዲመጡ ይትጋ። ከዚያ ውጪ ስድብ፣ ኃይለ ቃልና ከንቱ ልፍለፋውን ያቁም። አሁን ኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠሯን ወደአይሁድ ዘመን ብትቀይረው እንንእስራኤል ሀብታም ትሆናለች ማለት ነው? ወደአመተ ሂጅራ ብትቀይረው እንደአረቦቹ ነዳጅ በነዳጅ እንሆናለን? ወደፖፕ ጎርጎርዮስ ቀመር ብንቀይረው እንደኢጣሊያ ወይም አውሮፓን ልንሆን ነው ማለት ነው? ከኛ የተሻሉ ሀገሮች ሀብታም የሆኑት በዘመን አቆጣጠራቸው የተነሳ ነው? ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች የጽድቅና የቅድስና ዘመን ተብሎ የተሰጠው የትኛው የዘመን አቆጣጠር ነው? ይሄ ሰውዬ፣ የዚያ የእውቀት ድሃው የትዝታው ሳሙኤል ወንድም ነው። በግሌ ዘመን ቢቀየር፣ ባይቀየር በኔ ላይ የሚያመጣው ልዩነት እንደሌለ አምናለሁ። ነገር ግን ከሰኞ እስከ እሁድ ያሉትን ቀናት በስም መጥራት ብንተወውና ወይም ከዛሬ ጀምሮ 1,2,3,4, ብለን በቁጥር ብንለውጠው ወይም ከመስከረም እስከ ነሀሴ ያሉትን ወራት በእጽዋት ወይም በእንስሳት ስም ብንቀይረው የዘመኑ መለወጥ ኢትዮጵያን ሀብታም አያደርጋትም፣ ህዝቦቿንም ጻድቅ አይሆኑም ብዬ አምናለሁ። መለወጥ ያለበት በኢየሱስ ክርስቶስ አምኖ ወደመዳን መድረስ ያለበት ህዝቡና ቢያምንም፣ ባያምንም ጠንክሮና ተግቶ በመስራቱ ብቻ ነው ከድህነት መውጣት የሚቻለው። ጃፓንና ቻይና ሀብታም የሆኑት ይሄ ደንቆሮ መንፈስ የያዘው ቄስ እንደተናገረው ዘመን ስለቀየሩ ሳይሆን የስራ ባህላቸውን ስለቀየሩ ነው። እነዚህ ደናቁርት ግን የሚለፈልፉት ለኛ መዳንና ባለጸጋ መሆን መፍትሄው የዘመኑ መለወጥ ይሉናል። ይሄ ዲስኩር ተልእኮ ያለው ሲሆን ከኋላ ሆኖ push የሚያደርጋቸው ሃይል መኖሩን ያሳያል። ዘመኑን ወደአይሁድ ወይም ወደፖፕ ጎርጎርዮስ ዘመን ስለቀየርን ሰይጣን አይጠፋም። የአጋንት ውጊያም አይቀርም። መለወጥ ያለበት ይሄንን ቄስ የመሰሉ ደንቆሮ መንፈስ የያዛቸው ሰዎች ናቸው። በዚህ ሰው የሚመገቡ ምዕመናን ምን እንደሚመግባቸው ባይገባንም መጋቢ ነኝ ባዩ ሶፎንያስ ሞላልኝ በዩቱብ አካውንቱ የሚያቀርባቸው አብዛኛዎቹ ሰዎች እብዶች፣ ከበሽታ መፈወስ ያለባቸው ሰዎችን ልክ ጤናማና የተመሰከረላቸው አስተምህሮ ያላቸው አስመስሎ ማቅረብ ከጀመረ ጊዜያት ተቆጥረዋል። ጉዳዩ ስለወንጌል ሳይሆን ከዩቱብና ከሌሎች የሚዲያ ምንጮች የሚቀራርማትን ሽርፍራፊ ሳንቲም ስለመለቃቀም ነው። ለሁሉም ፈውሱን ይላክላቸው!

Saturday, November 22, 2025

የብልጽግና ወንጌል ምንድነው?

ብልፅግና ወንጌል (Dr Dereje Kebede) (2020) ከቤተመቅደስ እስከ ቤተመንግስት! መንግሥታት በቀንደ መለከትና በአዋጅ ሊያግዱት ሲገባ ቸል በማለታቸው በዓመታት መካከል አድጎና ተመንድጎ፣ ብዙሃኑን አራቁቶ፣ ጥቂቶችን ሚሊኒየርነት ማማ ላይ የሰቀለ አስተምሮ ምን እንደሆን የሚገምት ሰው አለ? ታመው የሚማቅቁን ተፈውሳችኋል፣ የደኸዩትን ባለጠጋዎች ናችሁ፣ አንድ ብር ስጡና እግዚአብሔር 10 ብር አድርጎ ይሰጣችኋል የሚለውንስ የተወላገደ ትምህርት ታውቁት ይሆን??? አማኝ የሚታመመውና የሚደኸየው ጠንካራ እምነት ሲያጣ ነው፣ አለበለዚያ ክርስቲያኖች አይደኸዩም አይታመሙም የሚለውን ትምህርትስ ደርሳችሁበት ይሆን? የእግዚአብሔርን በረከት በግል ሥጋዊ ጥቅም፣ በብርና በምድራዊ ቁሳቁስ ብዛት ብቻ የሚገለጥ፣ በካፒታሊስት ዋና መዲናዋ በአሜሪካ ተወልዶ በአፍሪካ ያደገውን “የወንጌል ተጧሪዎች፣ ስራ ጠል ሰዎች” ትምህርትስ ለይታችሁ አውቃችሁት ይሆን??ትክክል ገምታችኋል። የብልፅግና ወንጌል ይሉታል። እኔ ግን “የብልፅግና ወንጀል” እለዋለሁ። ስለብልጽግና ወንጌልና አስተምህሮ በዚህ ጊዜ መፃፍ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት ይህ የወንጀለኞች ዶክትሪን የፕሮቴስታንት ክርዝማቲክ አማኞችን በየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያኖቻቸውን ከማራቆት አልፎ ዛሬ አገራችንን ለመምራት ቤተመንግሥት የተኮፈሱ ጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድንና ጥቂት ጴንጤቆስጤ የሥራ አሥፈፃሚዎቻቸውን፣ ይሄ9ው አደገኛ ዶክትሪን፣ ተብትቦ እንደያዛቸው ግልፅ እየሆነ በመምጣቱ ህዝቡ ሃገራችን የገባችበትን አሌ የማይባል እጥፍ ድርብ ሰቆቃ እንዲረዳ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ነው። ስለመሪዎቻችን በተለይም ስለ ጠ/ሚኒስትሩ እንግዳ የሆነ፣ በአለም ላይ ታይቶ የማይታወቅ የአመራር ክፍተት፣ ፍዘትና፣ ንዝህላልነት ላለፉት ሁለት አመት ከመንፈቅ ፀጉራችንን ስንነጭና ጥርሳችንን ስናፋጭ የቆየን በብዙ ሚሊዮን የምንቆጠር ዜጋዎች፣ መልስ ላጣንበት የአስተዳደር ውድቀታቸው፣ ምክንያት ከሆኑት ነገሮች መካከል አንዱ የሆነውን ይህንን የምናብ እምነት properity Gospel ተንትኖ መረዳትና ማስረዳት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ እናውቃለን። አያችሁ ብልፅግና ወንጌልን የሚያምን ወይም የሚከተል ሰው በሃዘን፣ በድህነት፣ በበሽታ፣ በተፈጥሮአዊ መቅሰፍት ሰፈር መገኘት አይፈልግም። ያ ማለት፣ ምርት በአንበጣ ተወሮ ገበሬ ሲያለቅስ ብልፅግና ወንጌልን የሚከተል ሰው የተፈፀመው ውርጂብኝ እንዳልተፈፀመ፣ ቀና ቀናውን በማሰብና (Positive thinking) በእምነት (strong faith) ድልን በማወጅ አንበጣውም ይጠፋል፣ ምርቱም ይተርፋል ነው የሚለው። ጥቃቱም በህዝቡ አለማመን፣ ወይም ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በደል ፈፅሞ ወይም እምነት ስለጎደለው የተፈጠረ የሰማይ ላይ ቅጣት ነው ብሎ ነው የሚያምነው። ስለዚህም አዘኔታ የለውም፣ ለተጎዳው ህዝብ መራራት አይችልም። ስለዚህ ነው መሪያችን እርጉዝ ሆዷ ተዘንጥሎ ፅንሱ ሜዳ ላይ ሲጣል፣ ዝንብ የሞተ ያህል እንኳን ርህራሄ ያላሳዩት። ለጠ/ሚኒስትሩ ያ ድርጊት አልተፈፀመም ወይም በሰለባዋ እምነት ጉድለትና ኃጢአት የተነሳ የተፈፀመ ስለሆነ ለሳቸው ምንም ማለት አይደለም። በሰለባዋና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ነገር ነው ብለው ስለሚያምኑ ህዝብ ያለቅሳል እሳቸው ያፏጩብናል። ጁዌል ኦስቲን የተባለው በአሜሪካን አገር በጣም የታወቀ የብልፅግና ወንጌል ፓስተር በመጽሐፉ “Become a better you” ላይ ያለው አይነት ነው። “Dwell only on positive, empowering thoughts toward yourself, “You will see God’s blessings and favor in a greater way.” “ሃሳብህን በገንቢ ሃሳቦች ላይ ብቻ አድርግ ያን ጊዜ የእግዚአብሔር በረከትና ሞገስ በህይወትህ በትልቅ መንገድ በሙላትህ ይገለጻል” ብልፅግና ወንጌልን የሚከተሉ መሪዎች፣ የሌሎችን ችግር ማየት አይችሉም (No Empathy) ርኅራኄ የለም። ችግር፣ በሽታና ድህነት ለእምነታቸው ተስማሚ የድል ትርክት ስለማይፈጥር፣ እያለ እንደሌለ መቁጠርና ጭንቅላታቸውን አሸዋ ውስጥ ቀብረው በምድር ላይ ያለውን እውነታ መካድ ይቀላቸዋል። እውነታው ግን አንታመምም ቢሉም ይታመማሉ፣ ሃዘንን ቢክዱም ሃዘን ይደርስባቸዋል፣ የተፈጥሮ አደጋን የለም ቢሉም የተፈጥሮ አደጋ ዙሪያቸውን ሲከሰት ያዩታል። አለበለዚያ ዶ/ር አቢይ እንደሚያደርጉት ሃዘን በሰሜን ሲከሰት ወደ ደቡብ መፈርጠጥ፣ ፅንፈኞች ህዝብን ሲያርዱ ወደ ኢሳያስ አፈወርቂ ግዛት ማቅናት፣ በመተከል ከ 300 በላይ አማራዎችና አብረው የተገኙ አገዎችም በመንግስት በተደገፉ ፅንፈኞች ሲጨፈጨፉ ወደ ደቡብ ሄዶ ስለፓርክ ማውራት፣ ወሎ በአንበጣ ሲመታ እሳቸው በአሩሲ የለማ የእርሻ ማሳን መጎብኘት፣ Go kart እየነዱ፣ ኢላማ ተኩስ እየተለማመዱ መዝናናት፣ በጉራ ፈርዳ አማራዎች ሲታረዱ ስለሃዘኑና ጭፍጨፋው ላለማሰብና ላለመመስከር ዝምታን መምረጥ፣ በጠቅላላ አይንን ጨፍኖ አላየሁም ወይም አልሰማሁም ነበር ማለት ሊኖርባቸው ነው። ሌላስ? በጃልሜዳ ለብዙ አመታት በኦርቶዶክስ ቤተክርስትያናት ተተተክሎ የነበረን መስቀል በአስተዳደሩ ትእዛዝ ከነበረበት ተነቅሎ አልሰማሁም ነበር ብሎ መሸምጠጥ፣ የቡራዩ ማፈናቀልንም አልሰማምሁም ነበር ማለትን ሊጠይቅ ነው። አልያማ ከላይ የዘረዘርኳቸውና ሌሎችም ያልተጠቀሱ በርካታ አሰቃቂ ወንጀሎችና የተፈጥሮ አደጋዎች በምድራችን በተደጋጋሚ አይናችን እያየ መከሰታቸውን የሚክድ ፍጥረት ከብልፅግና ወንጌል አማኞች፣ ሰባኪዎችና ከኦሮሙማ ፖሊቲክስ አመራሮቻችን በቀር ማን ይኖራል? በሃገሪቷ እንብርት ላይ እየተፈፀሙ ያሉትን ጉዶች አላየሁም ነበር፣ አልሰማሁም ነበር በሚል ፌዘኛ መሪ 110 ሚሊዮን ህዝብ ሲመራ እንግዲህ ከዛ በላይ መቅሰፍትስ አለ እንዴ? ጠ/ሚኒስትሩ በዋናነት ኢትዮጵያን የኦሮሞ ምድር ለማድረግ ካላቸው አጀንዳ ጋር የብልፅግና ወንጌል እምነት ፅንሰሃሳብ በአስተዳደር ሥርዓታቸው ገብቶ ታላቁንና የበለፀገውን የኦሮሞ የምናብ ምድር በቅዠትና በሰመመን እያጣጣሙ ወደፊት መሄድን እንጂ ሃዘንን፣ ድህነትን፣ ሞትን፣ የማሰቢያ ጊዜውም ልቦናም የላቸውም። ስለዚህ ለቅሶ ቤት ከመሄድ ሰርግ ላይ ቢገኙ ይመርጣሉ። የጠ/ሚኒስትሩ ፀጥታን አለማስከበርና፣ የጥቃት ሰለባዎችን በጊዜውና በቦታው ተገኝቶ ችግራቸውን አለመጋራት፣ አለማፅናናት፣ አለመካስና ከሚመጡት ጥቃቶች አለመጠበቅ ምክንያት የብልፅግና ወንጌል እምነታቸው ብቻ ነው የሚል ካለ ጭንቅላቱን አሸዋ ውስጥ የቀበረ ሰጎን መሆን አለበት። እንዲያውም ላስረግጥ የምፈልገው ነገር ከብልፅግናውም ቅዠት ይልቅ የኦሮሙማ አጀንዳቸው፣ አማራን፣ አማርኛንና ኦርቶዶክስን የማጥፋት እቅዳቸው እጅግ የከፋና እንደሆነ ነው። አንትያ በትለር (Anthea Butler) የተባሉ የስነመለኮት ፕሮፌሰር ስለፕሮስፔሪቲ ጎስፕል መሪዎች ሲናገሩ “ዶናልድ ትራምፕንና ጆዌል ኦስቲንን ያመሳስሉዋቸዋል። እንደ ፕሮፌሰሯ አባባል ሁለቱም ከአማኞች ትልቅ ቅቡልነት ያላቸው ናቸው፣ በስኬታማነትም ያምናሉ፣ ነገርግ ግን በወንጌል ቃል ላይ የተመሰረቱ ወይም የበሰሉ አይደሉም” ይላሉ። ሁለቱም ማለትም ዶናልድ ትራምፕና ጆዌል ኦስቲን እንደማንኛውም የብልፅግና ወንጌል ተከታይ፣ የአሸናፊነትን እንጂ የውድቀትንና የተሸናፊነትን ወሬ መስማት አይፈልጉም። ፕሮፌሰሯ የበለጠ ግልፅ በሆነ መንገድ ሲያስቀምጡት ታዲያ፣ ትራምፕንና ኦስቲንን የመሰሉ የብልፅግና ወንጌል መሪዎች የጎርፍና የዐውሎ ነፋስ ዜናዎች አይስማሟቸውም፣ ምክንያቱም ከብልፅግና ወንጌል ዶክትሪናቸው ጋር የሚስማማ የድልና የፈንጠዝያ ወሬ ስለማያበስር። በዚያም ላይ የብልፅግና ወንጌል መሪዎች አደጋንና ክፉ ክስተቶችን አደብስብሶና አቃሎ የማቅረብ፣ ሰለባዎች የደረሰባቸውን አደጋና አካላዊ ጉዳት ደግሞ ከግንዛቤ ያለማስገባትና ከጉዳይ ያለመፃፍ ባህሪይ አላቸው ይላሉ። ደግ ደጉን፣ አሸናፊነትን፣ መበልፀግን፣ አዎንታዊ ስነልቦናን (እምነትን) ይዞ ለቅሶና ዋይታ የሌለባትን አሮምያን መገባት። ልብ ብላችሁዋል? የኛም ጠ/ሚኒስትር አንትያ በትለር (Anthea Butler) የገለፀችው የጆዌል ኦስቲንና የዶናልድ ትራምፕን ጠባይና ተግባርን ኮፒ ነው ሲያሳዩን የኖሩት። የማፅናናት ቃል ከአፋቸው እኮ አይወጣም። በወሎው አንበጣ ወረራ ሰአት እሳቸው Go-kart እየነዱ ኢላማ ተኩስ ጨዋታ እየተጫወቱ ልክ እንደነ ኦባማና እንደ ሌሎች የሰለጠኑና ሃብታም አገር መሪዎች ለመሆን፣ ነገረ ዓለሙን ረስተው ይቧርቁ ነበር። በጣም የሚገርም ዓይነት መደንዘዝ ይላሉ ያ ነው እንግዲህ። እነኦባማ ቢጫወቱ ያምርባቸዋል። ኦባማ በኤኮኖሚ የተንኮታኮተች አሜሪካንን ከቡሽ ተረክቦ ሌት ከቀን ሰርቶ ሃገሪቱን ከሪሰሽን (Recession) ያወጣ ጀግና መሪ ነው። ቢጫወትም ያምርበታል። የኛ መሪ የተረከቡትን ሃገር ጥለው አንዴ ዱባይ ሌላ ጊዜ ደግሞ ኤርትራ የሚዞሩ፣ አገር መምራት አይደለም አንድ ሱቅ ማስተዳደር የማያውቁ፣ ለካሜራና ለታይታ የሚንቀሳቀሱ፣ በብሄር ተበጣጥቃ የአንድ ብሔር የበላይነት በፈረቃ የሚለዋወጥባትን አገር ለፅንፈኞች አሳልፈው ሰጥተው አገር ሲታመስ እንዳልሰሙና እንዳላዩ የሚሆኑ መሪ ናቸው። ብልፅግና ወንጌል በቤተክርስቲያን፣ የብልፅግና ወንጌልን አሰራር በቅጡ ለተመለከተ ሰው፣ በውስጡ ያዘለው ትምህርት ህዝብን በባዶ ተስፋና በወሬ፣ ያለውን እምነትና ንብረት የሚያስጥል፣ የመሰሪዎች “ በጨ ጠቆረ” ቁማር እንደሆን በቀላሉ ይረዳል። እንዲያውም የወንጌል አገልግሎት ሳይሆን አይን ያወጣ ዝርፊያ ነው ቢባል ማጋነን እይሆንም። ህዝቡ ያለውን ይሰጣል፣ ወትዋቹ ሰባኪ ግን የብር ፍቅር አስክሮት ጨምሩ በረከቱ በሰጣችሁት መጠን እንዲጨመርላችሁ ይላል። ብልፅግና ሰባኪው መድረክ ላይ ወጥቶ ህዝቡን ሲደልልና ሲሸጥ የጨረታ ገበያ አይነት ልፍለፋ መለፍለፍ አለበት። የምእመናኑን ልብ ለማባባት፣ ዝሩና አስር እጥፍ ታጭዳላችሁ ይላቸዋል። በኢየሱስ ስም የተለበጠ ወንጀል። በእስር ሊያስቀጣ የሚገባ ወንጀል። በካፒታሊዝም ስርአት የተለመደው፣ ግለሰቦችን በብዙሃን ላይ በገንዘብና በስልጣን የመቆለል ልምምድ (Individual achivement) የብልፅግና ወንጌል መሰረቱ ነው። ምን ማለቴ ነው? ብልፅግና ወንጌልን በመስበክ ሃብት ያካበቱ እንደነ ክራፍሎ ዶላር፣ እንደ ቲዲ ጄክ፣ እንደነ ኬኔት ኮፕላንድና እንደነጆይስ ማየር አይነቶች በአባሎቻቸው ላይ ያላቸው ተፅእኖ የአሽከርና የጌታ ያህል ነው። የእነኝህ ብልፅግናውያን አገልግሎትና እንቅስቃሴ ዋና የደም ስር የሆነው አባላቸው ደህይቶ፣ እነሱ ስመጥር ባለፀጋዎች ሆነዋል። በጣም የሚገርመው ነገር ደግሞ የሚንደላቀቁበትን ሃብት የሚሰጣቸውን ህዝባቸውን ራሱን መልሰው ሲንቁትና እንደ ጀሌያቸው ሲቆሩጡት ነው። የብልፅግና ወንጌል አስተማሪዎች ምእመናኑን በእምነት ከጌታ በረከትን እንዲጠብቅ ያስተምሩታል እነሱ ግን “እጅ በእጅ ፍቅር እንዲደረጅ” እንዳለው የሃገሬ ጉራጌ፣ በእምነት ሳይሆን በሚታይና በሚጨበጥ ጥሬ ገንዘብ (cash) ነው የሚደራደሩት። የአባሎቻቸው አስራትና ስጦታ ለሽቶ፣ ለሱፍ፣ ለጫማ፣ ለውድ መኪናዎች፣ ለግል ፕሌኖች፣ ለወርቅ፣ ለብዙ ሚሊዮን ዶላር ቤቶችና ለወፍራም የግል ባንክ አካውንት ነው የሚውለው። ስለብልፅግና ወንጌል ማንበብ የጀመርኩት ከብዙ አመታት በፊት ነበር። ከ 20 አመታት በፊት አሜሪካ በብልፅግና ወንጌል ቴሌቪዢን ሰባኪዎች (Televisionpreachers/Teleevangelists) ቁማርና ወንጀል ታምሳ በነበረበት ጊዜ እኔ እዚሁ አሜሪካ አሁን የምኖርበት ስቴት ነበር የምኖረው። እውቅና የነበራቸው የብልፅግና ወንጌል አስተማሪዎች አንድ በአንድ ወደላይ እንደወጡ እንደ ሉሲፈር ወደታች የተወረወሩባቸውን ወቅቶች በደንብ አስታውሳለሁ። ከፀጋ ከወደቁት የዶክትሪኑ አስተማሪዎች አንዱ የሆነው ጂም ቤከር የምእመናንን ገንዘብ ወደግል አካውንት በማዘዋወር ተከሶ ከሚወዳት ሚስቱ ከታሚ ቤከር (ወደ ጌታ ሄዳለች ከብዙ አመታት በፊት) ተለይቶ በ48 አመታት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ ተፈርዶበት ወደ እስርቤት ሲላክ ቴሌቪዥን ላይ ተጣብቆ የተከታተለው የአሜሪካ ህዝብ ቁጥር ቀላል አልነበረም። በኋላ ግን የጂም ቤከር ቅጣት በጥሩ ጠባይ ተቀንሶለት ከ 8 አመታት በኋላ ተፈታ። ያ ዘመን የብልፅግና ወንጌል ቴሌቪዥን ሰባኪዎች ዙሪያ ገፃቸውን በህዝብ ቁጣ ተከበው የነበረበት ዘመን ነበር። ሌላው ትልቅ የመነጋገሪያ ርእስ የነበረው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ ኦራል ሮበርት በ 1987 በህዝብ ፊት፣ በህዝብ መገናኛ ወጥቶ “እግዚአብሔር በአንድ ወር ውስጥ 8 ሚሊዮን ዶላር ካልሰበሰብክ እገድልሃለሁ ብሎኛልና እባካችሁ ገንዘብ ስጡኝና ከሞት አድኑኝ” ብሎ ተናገረ። መቼም የአሜሪካን ህዝብ የዋህም ሩህሩህም ነውና የተባለውን ገንዘብ በተባለው ጊዘ ሰበሰበለት። የሚገርመው ግን ያም በቂ አይደለም ብሎ ሌላ 8 ሚሊዮን ብር እንዲሰበስቡለት የጠየቀበት ሁኔታ ነበር ያለው። እግዚአብሔር ብር ካላዋጣህ እገድልሃለሁ ብሎኛል ማለቱ በማያምኑ መካከል ሳይቀር መሳለቂያ ነገር ሆኖ ነበር። ከዚያም ወዲህ በተለያዩ ወቅቶች የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች እንደነ ቢሾፕ ላንግ (ነፍስ ይማር)፣ ሮበርት ቲልተን፣ ጆዌል ኦስተን፣ ቲዲ ጄክ፣ በኒሂን፣ ክራፍሎ ዶላር፣ ጆይስ ሜየርና ሌሎችም በርካታ ብልፅግናውያን የአገልግታቸውና የዕለት ዕለት አስረሽ ምቺው ሕይወታቸው ጉዳይ ለትልቅ ምርመራ (Scrutiny) ተዳርጎ ነበር። መቼም ምን አለፋችሁ በወንጌል ታሪክ ውስጥ በጴንጤቆስጤና በሌሎችም ክርዝማቲክ ቤተክርስቲያናት ውስጥ በተለያየ ወቅት ከተነሱት ሃሰተኛ ትምህርቶች ሁሉ አንደ ብልፅግና ወንጌል (prosperity Gospel) አማኙን ህዝብ ከምድር ዳርቻ እስከምድር ዳርቻ የጎዳ ትምህርት የለም። ዛሬም እየተራባ ነው። ብልፅግና ወንጌል የማያሻማ ስርቆት ነው። ስለዚህም ይህ የአጭበርባሪዎች ትምህርት በብዙ መንገድ ቤተክርስቲያናት ብቻ ሳይሆኑ መንግስትም ሊከታተለው የሚገባ ነገር ሆኖ ሳለ፣ በተለያዩ ምክንያቶች ከልካይ ስላላገኘ ከዓመት ወደ ዓመት እየሰፋና እያደገ ነው የሄደው። እውነትን ወዳድ የሆኑ ኢትዮጵያውያን አገልጋዮችም ጭምር ይህንን ትምህርት በሃገራችን ህዝብ መሃከል የሚዘሩ አጭበርባሪ ሰባኪዎችን ሁሉ በአንድነት እንዲያወግዙም ጥሪዬን አቀርባለሁ። ብልፅግና ወንጌል ከየት መጣ እነማን አመጡት? የብልፅግና ወንጌል ፅንሰሃሳብ የተፈጤረው የእምነት ቃል (Word of faith) ከተባለ ትምህርት ነው። የእምነት ቃል በጭሩ አንድ አማኝ ቀና ቀናውን በማሰብና በእምነት ከፈጣሪ እንዲደረግለት የሚፈልገውን ነገር በንግግር/በአንደበቱ በመናዘዝ/በመናገር በአእምሮውም ሳይጠራጠር በመቀበል የልቡን መሻት ሊያገኝ ይችላል ብሎ የሚያስተጋባ ሀተታ ነው። ይህ ዱቄት እንኳን መያዝ የማይችል ወንፊት ትምህርት/እምነት በአጋጣሚ ከሚሊዮን አንድ ካልሆነ በተቀር የማይፈፀም የቅዠት ነፀብራቅ ነው። የእምነት ቃል (word of faith) በ 20 ኛው ክፍለዘመን መጨረሻ በክርስማቲክ ጴንጤቆስጤዎች ጎራ የተፈጠረ ትምህርት ሲሆን ትምህርቱ እግሮች አውጥቶ እንዲሮጥ ያደረጉት ወስላታ የእምነት አስተማሪዎችና መሪዎች አሉት። ከነዚያም ውስጥ ኬኔት ሄገን የተባለው ሰው የትምህርቱ አባት በሚባል ይታወቃል። ነገር ግን ከእሱ በፊት የቃለ እምነትን መሰረት የጣለው ፋይነስ ፓርከርስት ኩዋምቢ (Phineas Parkhurst Quimby (1802-1866) የተባለ ሲሆን ፋይነስ ለኬንዮን፣ ኬንዮን ለኬነት ሄገን እንዳስተላለፉት ነው የሚታወቀው። የእምነት ቃል “የሰው እምነት እግዚአብሔርንም ያዘዋል ነው የሚለው። በዚያም አባባል “”እምነት” ከእግዚአብሔር ውጭ የሚሰራ ራሱን የቻለ ሃይል ያስመስለዋል። እውነታው ግን ሰው እምነትም ኖሮት የጠየቀውን ወይም የፈለገውን ከእግዚአብሔር ላያገኝ ይችላል። ወይም “የፈልጉትን ሰጣቸው ለነፍሳቸው ግን ክሳትን ላከ” (መዝሙር 106: 15) እንደሚል አንዳንዴ የፀለይንበትን አግኝተን ነገር ግን ጥቅሙ ሳይሆን ጉዳቱን እናጭዳለን። የ ”ቃለ እምነት” ወይም “የእምነት ቃል” አስተማሪዎች በቃሉ ላይ ከመመስረት ይልቅ እግዚአብሔር በተለየ መንገድ ለእነሱ የሚገልጠው የተለየ የቃለ እምነት መገለጥ አለ እያሉ ነው ህዝብን የሚያጭበረብሩት። መጽሐፍ ቅዱስን የእነሱን አጀንዳ እንዲደግፍ አድርገው በመተርጎም ያው እንደሚታየው በሕንፃ ላይ ሕንፃ የሚገነቡ ቢሊዮነሮች ሆነው ቁጭ ብለዋል። መጽሐፍ ቅዱስን ቁጭ አድርገው በመገለጥ፣ አየን ወይም ሰማን በሚሉት መሰረት ዬለሽ ቅብጥርጥር ሰውን ይዋሹታል፣ይዘርፉታል፣ ያደኸዩታል፣ ያሞኙታል። የቃለ እምነት (Word of faith) በጨረፍታ 1/ሰዎች ትናንሽ እግዚአብሔሮች ናቸው ምክንያቱም ሲፈጥሩ ሙሉ የእግዚአብሔርን ባህሪይ ተሰጥቶአቸዋል ይላል። ሰው በምድርንና በውስጧ ባሉት ላይ ትንሹ እግዚአብሔር እንዲሆን እንዲያዝና እንዲገዛ፣ እግዚአብሔር ስልጣኑንና ኃይሉን ሰጠው። እግዚአብሔርን የሰማዩን መንግስት ሲመራ ሰው ደግሞ ምድሪቱን ሊገዛ ማለት ነው (Capps, Authority in Three Worlds, pp. 16-17). እውነታው ግን በሰማይም በምድርም አንድ እግዚአብሔር ብቻ ነው ያለው። ሰው መቼም እግዚአብሔር አልነበረም አይሆንምም (ዮሐ 17:3)። ከሱ በፊት ከሱ በኋላም ሌላ እግዚአብሔር አልተፈጠረም አይፈጠርምም (ኢሳያስ 43 : 10). 2/ እምነት በቃል የሚንቀሳቀስ ሃይል ነው። የሚጨበጥ የሚዳሰስ ያህል ነገራትን የሚያንቀሳቅስ፣ እግዚአብሔርን የሚያዝ ገፊ ነው። እውነታው ግን እምነት በእግዚአብሔር ቃልኪዳኖች ላይ መታመን ብቻ ነው። (ዕብራይስጥ 11:1)። እምነት ብቻውን እግዚእብሔርን አያዘውም። እኛ የሰው ልጆች የማናውቃቸው ነገርግን እግዚአብሔር የሚያያቸው፣ የሚያገናዝባቸው ነገሮች ሁሉ ለጠየቅነው ነገር ከእግዚአብሔር ምን አይነት መልስ እንደምናገኝ፣ መቼ እንደምናገኝ ይወስናሉ። እምነት አለኝ ገንዘብ አምጣ የምንለው አምላክ አይደለም የምናመልከው። ብልፅግና ወንጌል ከቃለ እምነት ጋር የተያያዘ ሆኖ ሳለ አንድ ልዩነት ግን አላቸው። ያም ልዩነት የብልፅግና ወንጌል ወሮበላዎች በእምነት ውስጥ ገንዘብን አስተዋወቁ። ለመጀመሪያ ጊዜ “የእምነትን ቅንጣት ዝሩ” ማለት የጀመረው ከላይ የጠቀስነው ኦራል ሮበርት የተባለው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ ነበር። አያችሁ የእምነትን ቅንጣት የምትዘሩት በገንዘብ ነው ማለት ነው። አማኞች ለምን የእምነትን ቅንጣት በእምነት፣ ገንዘብና ወርቅ በሌለበት መዝራት አይችሉም?? ያቺ ለእምነት ቅንጣት የተጠየቀችው ገንዘብ ወደሰባኪዎቹ ኪስ የምትገባ ገንዘብ ናት። ያቺ ገንዘብ ቀላል ገንዘብ አይደለችም። ብዙዎቹን የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች የግል ጄት ባለቤቶች እንዲሆኑ ያደረገች ያቺ የእምነት ቅንጣት (seed of faith)ብር ናት። በአሜሪካን አገር በ”እምነት ቅንጣት” ዝሩ ሳቢያ የናጠጡ የወንጌል ወስላቶች በአሜሪካን አገር በአንድ ወቅት በኮንግረስ ሳይቀር ገቢና ወጪያቸው እንዲመረመር ተደርጎ ነበር። ብልፅግና ወንጌል ከሌሎች ሃሰተኛ ትምህርቶች ሁሉ የከፋ ነው ብዬ ያልኩበት ምክንያት ምንድነው? የብልፅግና ወንጌል 1ኛ/ የእግዚአብሔርን መለዮና ባህርይ ደልዞ የሌለውን ባህሪይ ይሰጠዋል። እግዚአብሔርንና ምድራዊ ሃብትን ያዛምዳቸዋል። እግዚአብሔርና ገንዘብ ምን ያገናኛቸዋል? ገንዘብ ለሰጡት ገንዘብ የሚሰጥ ላልሰጡት ደግሞ የማይሰጥ? ገንዘብ ከሰጡት ጤንነትንና ስኬትን የሚሰጥ፣ ገንዘብ ካልሰጡት ግን ግድ የሌለው? ለመሆኑ ይህ የእግዚአብሔር ባህርይ ነው? አይደለም (ማቴዎስ 19:23-24 ፣ 1 ጢሞቴዎስ 6:10) 2ኛ/ የእምነትን ምንነት፣ በአማኞች ህይወት ውስጥ የሚጫወተውንም ሚና ፍፁም ያጣምመዋል። የእምነት ቅንጣት (ዘር) ና ገንዘብ ምን አገናኘው? እምነት የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። እምነት ሰው ከእግዚአብሔር ጋር የሚዋሃድበት መለኮታዊ ልምምድ ነው። በገንዘብ አይገኝም። በገንዘብ አይሸጥም፣ በገንዘብ አይለወጥም (ኤፌሶን 2:8) 3ኛ/ በድህነት የሚማቅቁንና በበሽታ የተጎሳቀሉ ሰዎችን ኢላማ ያደርጋል። ስለዚህም በአሁኑ ወቅት የብልፅግና ወንጌል ዋና መራቢያ ቦታ አፍሪካ ሆኖአል። በኢትዮጵያም በግልፅ ይህንን የሌብነት ወንጌል እየሰበኩ ህዝቡን የሚሰርቁ ሰባኪዎች አሉ። እነሱን በህብረት ማውገዝ ይገባል። ያላችሁን አሟጣችሁ ከሰጣችሁ ሃብታም ትሆናላችሁ፣ ጤና ትሆናላችሁ ፣ በሚል የቀረቻቸውን ቤሳቤስቲን በመውሰድ በእግዚአብሔርም ላይ ያላቸውን እምነት ይነጥቃቸዋል። 4ኛ/ ብልፅግና ወንጌል የሚያበለፅገው ሰባኪውን ወይም መጋቢውንና የእርሱ ፍርፋሪ ለቃቃሚዎች የሆኑትን አጃቢዎቹን ብቻ ነው። ህዝቡ ግን ያለውን ለመጋቢው ወይም ለሰባኪው ሰጥቶ ላም አለኝ በሰማይ እንዳለ በባዶ ተስፋ አይኑን እንዳፈጠጠ ይቀራል። 5ኛ/ ህዝቡ ያለውን እየሟጠጠ ከሰጠ በኋላ በሰባኪው የተነገረው የሰማይ ብርና ወርቅ ሲዘገይና ሳይከሰት ሲቀር፣ ጮሌው ሰባኪ መልሶ እምነት ስለጎደለህ ነው፣ ኃጢአትህን ስላልተናዘዝክ ነው ከእግዚአብሔር ገንዘብ ወይም ጤንነት ያላገኘኸው ወይም ያላገኘሽው ብሎ ጥፋቱን በተዘረፈው(ችው) ደሃ ይላክካል። ይህም አሰራር ዋሾው የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ (ዘራፊ) የእኔ ጥፋት አይደለም ብሎ እንዲያሳብብ ቀዳዳ ከመስጠቱም በላይ ተዘራፊዎቹ የደረሰባቸውን ጥቃት በራሳችን ጥፋት ነው ብለው እንዲቀበሉና ወደ ህግም እንዳይሄዱ ያግዳቸዋል። የጥቃት ጥቃት። 6ኛ/ እግዚአብሔርን በፎርሙላ ማንቀሳቀስ ይቻላል ይላል። ልክ እንደ ሂሳብ ትምህርት የተደነገጉ የአሰራር ፎርሙላዎችን ለተከተለ ሁልጊዜ ወደተጠበቀው ውጤት እንደሚወስድ ሁሉ የብልፅግና ወንጌል ትምህርትም አንድ ሰው እምነት ካለውና ይሆንልኛል ብሎ እስካመነና በቃሉም እስከተናዘዘ ድረስ ወይም በአእምሮው የጠየቀውን ነገር ሲቀበል ማየት ከቻለ የጠየቀው ነገር ከእግዚአብሔር ይሰጠዋል ይላል። ይህ ደግሞ ፍፁም ውሸት ነው። የእግዚአብሔር ምላሽ አዎንታ ወይም አሉታ የሚሆንበት ምክንያት ሁልጊዜ ለሰዎች አይታወቅም። እግዚአብሔር ሥራው በተለያዩ ወቅቶች የተለያዩ ናቸው። እምነትም ኖሮን፣ በቃላችንና በስነልቦናችንም ተናዘን የጠየቅነው ነገር ላይሰጠን ይችላል። ወይም ገንዘብ ጠይቀን ጤንነት እንቀበል ይሆናል። እግዚአብሔር በፎርሙላ አይሰራም። ማንም አያዘውም። የአገራችንን ምስኪን ህዝብ የሚግጡ የብልፅግናና የቃል እምነት (word of faith) ሰባኪዎች ደሃውን ህዝብ ሃብታም ትሆናለህ፣ ከበሽታህ በእምነት ትፈወሳለህ፣ ድህነት አይነካህም፣ ከእንግዲህ እያሉ በጋጡት ገንዘብ ሚሊየነሮች ሆነዋል። አንዳንዶቹ ከየክልሉ ሌሎቹም ከዚያው ከአዲስ አበባ የተጠራቀሙ የኢየሱስን ስም የሚሸቅጡ ነውረኞችና ዘራፊዎች ከፍተኛ ድጋፍ ከዚህ ከወንበዴ መንግስት ስላገኙ ያለምንም ፍራቻ ወንጀላቸውን እየፈፀሙ ነው። ዶ/ር አቢይ አህመድ የወንጀለኞች ሿሚ ጠ/ሚኒስትር ቤተ መንግሥታቸው ድረስ ከሚጋብዟቸው ውስጥ የቃል እምነቶችና የብልፅግና ወንጌል ሰባኪ አጭበርባሪዎች ይገኙበታል። እንዲያውም እነኚህ ዘራፊዎችና ጤናማ ወንጌል ሰባኪዎች ይቅር ተባብለው አንድ ማኅበር እንዲጠጡ ባዘዙት መሠረት ከጥቂቶች በተቀር ካውንስል መስርተው በአንድ ተቋዳሽ ሆነዋል። ጤነኛዎቹ ተብለው ይከበሩ የነበሩ ሰባኪዎችና መጋቢዎች፣ ሃሰተኛ ነቢያትንና ሐዋርያትን (እነሱው ናቸው ብልፅግናና ቃል እምነትን የሚሰብኩት) አቅፈው ስመው “ድሮም እኮ ልዩነታችን ጥቃቅን ነበር” “ሥራቸውን እንጂ እነሱን አልጠላም” የሚሉ ሰበቦችን እያዥጎደጎዱ በአንድ ላይ “በካውንስሉ” ስም ይሰራሉ። ጤናማ ዘማሪዎችና ሰባኪዎችም በካውንስሉ ስብሰባዎች እየተገኙ ፕሮግራማቸውን ያደምቁላቸዋል። ዛሬ “ሰው ትንሹ እግዚአብሔር ነው” የሚሉ ወሮበላዎች እድሜ ለጠ/ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ከርቸሌ መጋዝ ሲኖርባቸው ምላሳቸውን እያወጡ ያላግጡብናል። ባለዲዛይነር ሱፎች ናቸው። ከየት አመጡት ገንዘቡን አይሰሩ አይነግዱ? ከምስኪን ደሃዎች፣ ከህመምተኞች፣ እምነተ ለጋዎች ኪስ ነው የሰበሰቡት። ይህ ሴይጣናዊ ትምህርት በአሜሪካም ሆነ በአፍሪካ እንደ ሰደድ እሳት የተሰራጨው በኢኮኖሚ በተጎዱት ህብረተሰቦች መካከል ነው። ምክንያቱም ግልፅ ነው። ደሃ ከድህነቱ የሚያላቅቀው ነገር አለ ከተባለ የትም ይሄዳል። ምንም ያድርግ ? ህዝብ ሞኝ ስለሆነ ሳይሆን ቢጨንቀው ነው ብልፅግና ብልፅግና የሚሉትን ሰባኪዎች የሚከተለው። የብልፅግና ወንጌል ሰባኪዎች አፍሪካ ድረስ ዘልቀው ታዋቂ መጋቢዎችን እየተጠቀሙ በቀን ከአንድ ዶላር በታች ከሚያገኘው ህዝብ ሳንቲም ይቃረጣሉ። የዚህ ስህተተኛ ትምህርት አዛማቾች በቀጣዩ ዓለም በእግዚአብሔር ዘንድ የሚጠየቁ ቢሆንም በምድር ደግሞ ብዙ ጥፋት ሳያጠፉ በፍርድቤትና በዳኞች ፊት ሊቀርቡ የሚገባው ነው። እውነትን የሚወድ ሁሉ ደግሞ ሊያወግዛቸው ይገባል። (ዶ/ር ደረጀ ከበደ፣ 2020- 5 years ago)

Friday, August 29, 2025

እንዳንጠፋ ድነታችንን በጸጋው ኃይል አጽንተን እንጠብቃለን!

በጌታችንንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አንዴ ድነናል፣ በዚህ ድነት በመንፈስ እንመላለሳለን፣ ኃጢአትን አንፈፅምም! “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።” — ገላትያ 5፥16 የሀልዎተ እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን መጋቢ ዘነበ ግርማ ድነታችን በሕይወት ዘመናችን በጽድቅና በቅድስና በመመላለስ ካልፈጸምነው ልንጠፋ እንችላለን ብሎ ያስተማረውን ትምህርት የሪል ስቴቱ ባለቤት ነብይ በላይ ሽፈራውና ኢየሱስ ክርስቶስ የሞተው ለተመረጡት ሰዎች ብቻ እንጂ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም ብሎ የሚያስተምረው አማን ሻሎም የተባሉት ነብይ ዘነበን ተቃውመው የሙግት ትምህርት ሲለፈልፉ ሰማሁ። አዘንኩም፣ ገረመኝም። ያዘንኩት እነዚህ ተቃዋሚዎች ከእነሱ በስተቀር የቃል እውቀት ማንም እንደሌለው አስበው መናገራቸው ሲሆን የገረመኝ ለከት የሌለው ባዶነታቸውን በአደባባይ ሲገልጹ አለማፈራቸው ነው። የዘነበን፣ የበላይ፣ የአማን ሻሎም እና የተመሳሳይ ሰዎች አስተምህሮ በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ከመበርበራችን በፊት እንደመግቢያ የመጀመሪያውን ሰው የአዳምን ማንነት እንደማስረጃ እንመልከት። አዳም እንዲኖር የተሰጠው ቦታ የት ነበር ብትባሉ በገነት እንደምትሉ እርግጠኛ ነን። የሰው ልጆች ከዚህ ምድር በሞት ሲለዩ ነፍሳቸው የት ትሄዳለች ብለን ብንጠይቃችሁ መልሳችሁ ምን ሊሆን ይችላል? በገነት ልትሉ እንደምትችሉ ብንገምት የተሳሳትን አይመስለንም። ምክንያቱም ከኢየሱስ ጋር ከተሰቀለው አንዱን ፍርደኛ ኢየሱስ እንደዚህ ሲል ሰምተነዋል። “ኢየሱስም፦ እውነት እልሃለሁ፥ ዛሬ ከእኔ ጋር በገነት ትሆናለህ አለው።” — ሉቃስ 23፥43 በፊትም አዳም የኖረበት፣ በኋላም በኢየሱስ ክርስቶስ ያመንን እኛ የምንኖርበት ቦታ ገነት መሆኑን እንረዳለን። አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እስኪፈጠሩ መኖሪያችን ዔድን ገነት ነው። “ነገር ግን ጽድቅ የሚኖርባትን አዲስ ሰማይና አዲስ ምድር እንደ ተስፋ ቃሉ እንጠብቃለን።” — 2ኛ ጴጥሮስ 3፥13 እሺ! እውነቱ ይህ ከሆነ አዳምን ለዘላለም ይኖር ዘንድ እግዚአብሔር ከሰጠው መልካም ሥፍራ ከሆነው ገነት ያስወጣው ምንድነው? እግዚአብሔር አዳምን በገነት ማኖር ስላልፈለገ ነው እንዴ ከገነት የተባረረው? አይደለም! አዳም ከሚስቱ ጋር የእግዚአብሔርን ቃል በገዛ ምርጫቸው ስላፈረሱ ነው። ባለመታዘዝና የተሰጣቸውን ትዕዛዝ በማፍረሳቸው፣ ከእግዚአብሔር ድምፅ ይልቅ የሰይጣንን ፈቃድ ለመፈፀም ፈቃደኛ ስለሆኑ ነው የተባረሩት። ሁሉን አዋቂ እግዚአብሔር አዳም እንደሚሳሳት አያውቅም ነበር? እግዚአብሔር አስቀድሞ ያውቃል! የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት የሰውን ልጆችን ነጻ ምርጫ አይጋፋም። ማወቅና መረዳት የምንችልበትን ነፍስያ ባህርይውን ያካፈለን ለዚህ ነው። በምርጫህ ወደህ፣ አምነህ ታመልከዋለህ፣ አልፈልግህም ብለኸው ለኃጢአት ብትገዛ ከኃጢአት የሚታጨደውን ደመወዝ በምርጫህ ትቀበላለህ። ስለሆነም አዳም በበደለ ጊዜ ዐመጽና ኃጢአት ከእግዚአብሔር አምላካዊ ባህርይ ጋር በገነት አብሮ መኖር ስለማይችል አዳም ከቅዱሱ ከእግዚአብሔር ፊት ተባረረ። የመጀመሪያው አዳም ሕይወት የተጠናቀቀው በዚህ የእውነት ፍርድ ነው። የመጀመሪያው አዳም ከተጠናቀቀበት ፍርድ ነጻ ለመውጣት ዋጋ ከፍሎ ወደ አዳነው ወደ ሁለተኛው አዳም እንምጣ! ሁለተኛው አዳም የመጀመሪያው አዳምንና ልጆቹን ለማዳን ከኃጢአት የነጻ፣ ለእግዚአብሔር አልታዘዝም ከሚል ዐመጽ የተለየ ንጹህ ነበር። ለዚህም የማዳን ሥራ ራሱ እግዚአብሔር ሰው ሆኖ መጣ። “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥ አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን።” — ዮሐንስ 1፥14 እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ሆኖ ሳለ በቃሉ ብቻ አዳምን ወደገነት መመለስ እየቻለ ለምን ሰው መሆን አስፈለገው? ብለን ስንጠይቅ መልሳችን እግዚአብሔር በጽድቅ ፈራጅ፣ በእውነትም ፍትህ ሰጪ ስለሆነ ነው የሚል ይሆናል። ዳዊት በመዝሙሩ እንዳለው። “እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት ይዳኛቸዋል።” — መዝሙር 9፥8 ለኃጢአት ዋጋ ፍርድ ሳይሰጥ ጽድቅ የለም። ከእግዚአብሔርም ጋር እርቅ አይኖርም። የስርየት መስዋእቱም ደም ነበር። ለዚህ ነበር እግዚአብሔር ራሱ ሰው የሆነውና ስለአዳም ኃጢአት የደም መስዋእት የከፈለው። ፊልጵስዩስ 2፣6-8 "እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።" አዳም ለኃጢአት ሲታዘዝ ተባረረ። ኢየሱስ ለጽድቅ ሲታዘዝ ሕይወት ሆነልን። እስከዚህ ድረስ መግቢያ ይሆነን ዘንድ ስለወደቀው የመጀመሪያው አዳምና የዘላለም ሕይወት ስለሆነው ስለሁለተኛው አዳም፣ ኢየሱስ ቤዛነት ይሄንን ያህል ካልን ስለእነዘነበ ግርማ፣ በላይ ሸፈራውና አማን ሻሎም የክርክር ጉዳይ እንግባ። ነብይ ዘነበ ግርማ ስለድነት በተናገረበት አንቀጽ በኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ በነጻ የተሰጠንን ዋጋ መጠበቅ አለብን፣ ከኃጢአት ካልጠበቅነው የዘላለም ሞት ያገኘናል፣ የተሰጠንን ድነት ልናጣ እንችላለን የሚል ይዘት የነበረው አስተምህሮ አቅርቦ ነበር። በላይ ሽፈራውና አማን ሻሎም የተባሉት ሰዎች ደግሞ በተቃውሞ የሰጡት መልስ የተሰጠንን ድነት እኛ መጠበቅ አይጠበቅብንም። አንዴ ድነናል፣ ይሄንን ድነት የትኛውም ኃጢአት አያጠፋብንም፣ የሚጠፋ ከሆነ ለዘላለም አልዳንም ማለት ነው ሲሉ የሚያግዛቸውን ጥቅስ በማቅረብ እውነቱ በነሱ ዘንድ ብቻ እንዳለ ለማስረዳት ታግለዋል። እዚህ ላይ እኛ ጥያቄ እናንሳ! ከላይ በመግቢያችን ለማብራራት የሞከርነው የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እዚህ ላይ ይነሳል። የመጀመሪያው ሰው፣ አዳም ገነት የገባው ለጊዜው ነበር እንዴ? አይደለም! እግዚአብሔር ሰውኛ ድራማ ስለማይጫወት አዳም የተፈጠረው ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንዲኖር እንጂ አዳም የበለሲቱን ፍሬ እስኪበላ ድረስ ለጊዜያዊ ማቆያነት አልነበረም። አዳም የተፈጠረበትን ዘላለማዊ ሕይወት የተሰጠውንና ከእግዚአብሔር ጋር ከመኖር ይልቅ የጠላቱን ድምፅ ሰምቶ ሞትን በራሱ ላይ ስላመጣ እግዚአብሔር ጻድቅ ሆኖ ሳለ ዐመጸኛ እንዴት ከእርሱ ጋር ኅብረት ሊያደርግ ስለማይችል በፍርድ ቀንበር ስር ወደቀ። ዐመጸኛ ከእግዚአብሔር ፍርድ ሊያመልጥ አይችልም። የመጀመሪያው አዳም እምቢተኛ ሲሆን ሁለተኛው አዳም የመጣው ደግሞ የአባቱን ትዕዛዝ ለመፈጸም ነው። “ፈቃዴን ለማድረግ አይደለም እንጂ የላከኝን ፈቃድ ለማድረግ ከሰማይ ወርጃለሁና።” — ዮሐንስ 6፥38 በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ የዘላለም ሕይወት በማመን ያገኘ ሰው፣ ዐመጸኛ ሆኖ የዲያብሎስን ድምፅ ቢሰማ ሊሆን ይችላል? አትጠራጠር፣ የዘላለም ሞት ይፈረድበታል! ኢየሱስ ሞት ዋጋ ያለው በሁለት መንገድ ነው። አንደኛው ዋጋ ኢየሱስ የተወደደ የእግዚአብሔር መስዋእት ሆኖ ከአዳም ኃጢአት መዳንህን ባመንክበት ቅጽበት ስርየት ሆኖልህ የእግዚአብሔር ልጅ ትሆናለህ። “አባ አባት ብለን የምንጮኽበትን የልጅነት መንፈስ ተቀበላችሁ እንጂ እንደገና ለፍርሃት የባርነትን መንፈስ አልተቀበላችሁምና።” — ሮሜ 8፥15 ልጅ በቅዱሱ በአባቱ ፊት ምን መሆን ይጠበቅበታል? ይሄ ሁለተኛው የኢየሱስ የሞት ዋጋ በእግዚአብሔር ፊት ልጆቹ ሆነን የምንመላለስበት ጉልበታችን ነው። ጸጋ ይባላል። “ነገር ግን እንደ ክርስቶስ ስጦታ መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጠን።” ኤፌሶን 4፥7 ይህ ጸጋ በእምነት የዳንነውና የእግዚአብሔር ልጆች የሆንነው እኛን ምን ያደርግልናል? “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” — ቲቶ 2፥12-13 በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ አምኖ የዳነ ሰው በጽድቅ መኖር ግዴታው ነው። የተሰጠው ድነት በነጻ ነው ማለት ዋጋ አልተከፈለበትም ማለት አይደለም። “በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ የሚያደርግ እንጂ፥ ጌታ ሆይ፥ ጌታ ሆይ፥ የሚለኝ ሁሉ መንግሥተ ሰማያት የሚገባ አይደለም።” — ማቴዎስ 7፥21 አዎ፣ በሥራችን አልዳንም። ይህ ማለት ግን ሥራ የለብንም ማለት አይደለም። በላይ ሽፈራውና አማን ሻሎም ይሄንን ቃል አይወዱትም። በእምነት አገኘነው ያሉትን ድነት ለሥጋ ፈቃዳቸው የሚከለክል ቃል ስለሆነ አይጠቅሱትም። አንዴ የተሰጠን ድነት በእኛ ስራ አይጠበቅም ይላሉ። ባንሰራም ያገኘነው ድነት አይጠፋብንም ብለው ይጮሃሉ። የሚጠፋ ከሆነ ቀድሞውኑ አልተሰጠንም ነበር እያሉ ስጦታቸውን ለፈለጉት የዐመጽ ተግባር እንደማስረጃ እንዲቆጠርላቸው ይታገላሉ። የተሰጠህን ነጻ ውድ ስጦታ ካልጠበከው ስጦታው ቀድሞውኑ አልነበረም ማለት ነው እንዴ? ስጦታው የማይጠፋ ነው። የማይጠፋው የሰማይ ስጦታ ስለሆነ ነው። ነገር ግን የሰው ልጅ አጥፊ ልምምድ ስላለው ሊያጠፋው ይችላል። ምሳሌው የገነቱን አዳም አስብ። “እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” ያዕቆብ 2፥17 ዐመፀኞች ለተሰጣቸው ድነት ሥራ ስለሌላቸው ዐመጽነታቸውን የሚደግፍ ጥቅስ ይደረድራሉ። አዳም በሄዋን፣ ሄዋንም በእባብ እባብም በዐመጽ ምክንታቸው ስር ቢደበቁም ከፍርድ አላመለጡም። የዚህ ዘመን ወንጌላውያን የተባሉት አብዛኛዎቹ መንፈሳዊ መረዳት የላቸውም። ብዙ አንብበው፣ ብዙ የቲዎሎጂ ትምህርት ቢኖራቸውም ብዙ አነበቡ እንጂ ከመንፈሳዊ እውቀት የተለዩ ዝናብ የሌለባቸው ዳመናዎች ናቸው። ዳዊት ፋሲል የሚባልም ግብዝ ሰው በተሳልቆና እውቀት በሚመስል የፌዝ ንግግር የገነት በር ቁልፍ በእጄ ነውና፣ በኔ በኩል ግቡ በሚመስል መልኩ ብዙ ያወራል። አማን ሻሎም የተባለው ሌላኛው ግብዝ ሰው ራሱን ብዙ ባነበበው መጽሐፎች ውስጥ ደብቆ አዋቂ መስሎ ለመታየት ብዙ ጊዜውን ይጨርሳል። ይጋጋጣል። የተከራካሪዎቹን አፍ ዝም ስላሰኘ በእውቀት የበለጣቸው ይመስለዋል። ከነዚህ ደካማ እውቀቶቹ መካከል አንዱ ኢየሱስ የሞተው ለኛ ለጥቂቶች ነው የሚለውን የጆን ካልቪንን Limited Atonement ወይም Particular Redemption መዳን የሆነው ለተወሰኑት ብቻ ወይም የተመረጡ ብቻ ነው የሚል አስተምህሮ አስፋፊ ነው። ይህ ትምህርት የመጨረሻው የክህደት ጫፍ ነው። እግዚአብሔርን ጨካኝ፣ ፈራጅ አድርጎ የሚከስ ነው። እግዚአብሔር ኢየሱስን የላከው የተወሰኑ ሰዎች ብቻ ለማዳን ከሆነ ከመዳን ውጪ ያሉት ሰዎች ለሲኦል ማገዶነት እግዚአብሔር ያዘጋጃቸው ናቸው ማለቱ ነው። እንዳይድኑ ተደርገው የተፈጠሩ ሰዎችን እግዚአብሔር በእሳት እያቃጠለ ለመደሰት ያዘጋጃቸው ናቸው ማለት እግዚአብሔር ፍቅር አይደለም ማለቱ ነው።። እነዚህ ሰዎች ከዘላለም እሳት ውጪ ለመዳን ምርጫም፣ እድልም የሌላቸው ናቸው ማለት ነው። ይህ ትምህርት ደግሞ ይሄንን የእግዚአብሔር ቃል በቀጥታ ይቃወማል። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” — ዮሐንስ 3፥16 እግዚአብሔር አብ አንድያ ልጁን ወደዓለም የላከው የተወሰኑ ሰዎችን ብቻ ለማዳን ብቻ ነው የሚለው አማን ሻሎም Mouthpiece of Satan የሰይጣን አፍ አገልጋይ ነው። በዚህ ቃል ውስጥ ጥቂቶች፣ የተመረጡ፣ የተወሰኑ፣ የተለዩ...የሚል ቃል ይታያችኋል? “ሁሉ በእርሱ በኩል እንዲያምኑ ይህ ስለ ብርሃን ይመሰክር ዘንድ ለምስክር መጣ።” — ዮሐንስ 1፥7 "ሁሉ" ማለት በግሪክኛ πάντες ፓንቴስ ማለት ሁሉ፣ all, everyone እያንዳንዱ ማለት እንጂ የተወሰኑ፣ የተለዩ ማለት አይደለም። በላይ ሽፈራው አግብቶ የፈታ፣ ዳግመኛ ያገባና ሌላም፣ ሌላም የሚወራበት፣ በሪል ስቴት ገንዘብ ብዙዎች ያለቀሱበት፣ አማን ሻሎም በሱስ የተጠመደ፣ ቀለበት አስሮ የከዳ፣ ሌላም፣ ሌላም ሆነው ሳለ በእግዚአብሔር ፊት በጽድቅ መመላለስ ሲያቅታቸውና ለምኞታቸው ልጓም ማስገባት ሲሳናቸው፣ ለኃጢአታቸው አርነት የሚሰጥ ጥቅስ በማቅረብ የስህተት ደጋፊዎቻቸውን ለማሰባሰብ ይሯሯጣሉ። ማጠቃለያ፣ የዳንነው በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በነጻ ነው። በነጻ የተሰጠን ሕይወት ዋጋ ተከፍሎበታል። የከፈለልንን ስለምንወደው ትእዛዛቱን እንጠብቃለን። ትእዛዛቱን የምንጠብቀው ስለምንወደው እንጂ ለመዳን አይደለም። “ብትወዱኝ ትእዛዜን ጠብቁ። እኔም አብን እለምናለሁ ለዘላለምም ከእናንተ ጋር እንዲኖር ሌላ አጽናኝ ይሰጣችኋል፤” — ዮሐንስ 14፥15-16 ያ አጽናኝ ከኃጢአት ይጠብቀናል። ተሳስተን ኃጢአት ብናደርግ ስንኳን የንስሐ እድል አለን። “በኃጢአታችን ብንናዘዝ ኃጢአታችንን ይቅር ሊለን ከዓመፃም ሁሉ ሊያነጻን የታመነና ጻድቅ ነው።” — 1ኛ ዮሐንስ 1፥9 ድነናል፣ ድነታችንን እንጠብቃለን። እንደዴማስ ኢየሱስን ትተን ለዓለም ኃጢአት ባሪያ አንሆንም።

Tuesday, April 22, 2025

“እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” ቆላስ 1፥13-14

"ለእኔ ኃጢአት ሥርየት ከሞተልኝ ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ቤዛ የለኝም" “እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” — ቆላስይስ 1፥13-14 ቤዛ የሚለውን ቃል አባ ገብርኤል የተባሉ ሊቀጳጳስ ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ብለው ለምን ተናገሩ? የሚል ንትርክ ተነስቶ በኦርቶዶክሶች መንደር ጩኸቱ በርክቷል። ይሄ ቤዛ በእንግሊዝኛው/ransom,redemption,deliverer/ በማለት ሲተረጉመው ግሪኩ ደግሞ (λύτρον)ሉትሮን ማለት የተከፈለ ዋጋ፣ (λύτρωσις) ሉትሮሲስ ነፃ መውጣት፣ ከእስራት፣ ከባርነት ለመፈታት የተሰጠ ክፍያ፣ ነጻነት ማለት ነው። የጌታችን፣ የመድኃኒታችንና የአምላካችን ቤዛነት ከየትኛው ምትክነት፣ ነጻ አውጪነት፣ አዳኝነትና ከሞት ታዳጊነት ጋር ለንጽጽር የሚቀርብ አይደለም። በዘመነ ኦሪት በባርነት የተሸጠ ሰው ለባርነቱ ዋጋ የሚከፍል ከተገኘ ነጻ ሊወጣ ይችላል። ለሰው ነፍስ ቤዛው ሀብቱ ነው። ምሳሌ13፣8 የመሳሰሉ ስለቤዛ የተነገሩ የቤዛ ቃል ንግግሮች በመጽሐፍ ቅዱሳችን ውስጥ ተፅፈው እናገኛለን። እነዚህ ሁሉ የቤዛነት ትርጉሞች ኢየሱስ ክርስቶስ ካደረገልን ቤዛነት ጋር ለክርክርም፣ ለንጽጽርም፣ ለትርጉም አቻነት የሚቀርቡ አይደለም። የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ከዘላለማዊ ድኅነት፣ ከአብ ጋር እርቅ የተደረገበት፣ መርገመ አዳም የተወገደበት፣ የገነት በር የተከፈበት ስለሆነ ከሰማይ በታች የተነገሩ፣ የተጻፉ፣ የተወሩ ስለቤዛ የተተረጎሙ ቃላት፣ ሃሳቦች ለንጽጽር ሊቀርቡ አይችሉም። በእውቀት ለመገራትና ለመመራት እምቢተኛ አእዱገ ገዳም የሆኑ የኦርቶዶክሶች ምእመናን፣ በተረት ተረት ትምህርት ሊቅ የሆኑት ዘበነ ለማ፣ አዋቂ መስሎ ለመታየት ብዙ የሚደክመው ኄኖክ ኃይሌ፣ ክንድ ከስንዘር መስቀል ጨብጠውና አንጠልጥለው ብዙ የሚያጓሩ፣ የተለሰኑ መቃብር መምህራን፣ ቀሳውስትና መነኮሳት ነን ባዮች የጌታችን፣ የመድኃኒታችንና የአምላካችንን ቤዛነትን ከሌሎች ቤዛነት ጋር ለማነጻጸር ወይም ስለቤዛነት የተነገረው ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ አይደለም ለማለት ከሰሜን ዋልታ እስከ አንታርክቲካ ሮጠው ያልቆፈሩት ጥቅስ፣ ያልዘበዘቡት ፅሑፍ፣ ያልተረተሩት ትርጉም፣ በእልህና ብስጭት መንጋጋቸው በመንጋ ያላፋጩት ጥርስ የለም። በየፌስቡኩ፣ ቲክቶኩና በየድረገጾቹ ላይ የታየው ጩኸት ተአምር የሚያስብል ነው። እነዚህ ስብስቦች ከኛ ወዲያ እውቀት ላሳር ነው ብለው የአእምሮአቸውን በር የዘጉት ድሮ ነው። ከእነዚህ ሰዎች ጋር ተነጋግሮ መተማመን ላይ መድረስ አይቻልም። አንዳንዴማ ከእኛ በስተቀር የሚጸድቅ የለም ብለው በድፍረት ሲናገሩ መንግሥተ ሰማያት በር ላይ ቆመው አንተ ተመለስ፣ አንተ ግባ ብለው የማዘዝ ስልጣን ያላቸው ያህል ያስባሉ። መንግሥተ ሰማያት የፍትሐት ድግስ የሚበሉበት የደጀሰላም በር ይመስላቸዋል። ለነገሩ አይሁድ ፈሪሳውያን መምህራንና ጻፎችም እንደዚሁ ያደርጋቸው ነበር። እነዚህን መሰል ሰዎች ጌታ በአንድ ወቅት እንዲህ ሲላቸው እናገኛለን። (ማቴ23፣27-32) እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ በውጭ አምረው የሚታዩ በውስጡ ግን የሙታን አጥንት ርኩሰትም ሁሉ የተሞሉ በኖራ የተለሰኑ መቃብሮችን ስለምትመስሉ፥ ወዮላችሁ። እንዲሁ እናንተ ደግሞ በውጭ ለሰው እንደ ጻድቃን ትታያላችሁ፥ በውስጣችሁ ግን ግብዝነትና ዓመፀኝነት ሞልቶባችኋል። ብሏቸው ነበር። እነዚህኞቹ ወደመንግሥተ ሰማይ ወይ እነሱ አይገቡ፣ ወይ ተከታዮቻቸውን አያስገቡ መንገዱን በተረትና እንቆቅልሽ ስብከት ዘግተውታል። በዚያ ላይ እውቀት አለርጂክ የሆነበት ተከታያቸው ምዕመን በጩኸት ስለሚያጅባቸውና አዋቂ ነን ብለው ስለደመደሙ ከእነሱ የተለየውን ቃል እውነት ቢሆን እንኳን አይቀበሉም። ምእመኖቻቸውም ከመምህራኖቻቸው የባሱ ስለሆኑ ያንኑ የአለቆቻቸውን ትምህርት መልሰው ይጓራሉ። ይጮሃሉ። ማርያም ቤዛ ናት፣ ገብርኤል ቤዛ ነው። ገንዘብ ቤዛ ነው። ወንድምህ ቤዛ ነው፣ ጓደኛህ ቤዛ ነው የሚሉ ቃላትን ለቃቅመው በማምጣት ከኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ጋር ለንጽጽር፣ ለትርጉምና ለማብራሪያ በማቅረብ ይንጫጫሉ። አንዳንዴ ስትመለከታቸው ክርስቲያን የሚለውን መጠሪያ አምኖ ለመቀበል እስኪከብድህ ድረስ አንደበታቸውና ጽሑፋቸው ልቅ ነው። እነዚህ ተጯጯኺዎች በዘመቻ የተነሱት የቤተክርስቲያኒቱ ጳጳስ አባ ገብርኤል የተባሉት ሰው "ተቀዳሚ፣ ተከታይ የሌለው፣ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻውን የዘላለም ቤዛ ነው" ብለው ስላስተማሩና ማርያምም የዘላለም ቤዛችን አይደለችም ስላሉ ነበር። የዚህን ትምህርት ቃል ለማፍረስና ሌሎችም ቤዛ አሉን ለማለት ያልቆፈሩት የሙግት ትርጉምና ጥቅስ የለም። ዘቤ የተረት አባት በአንድ ወቅት "ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም" ብሎ ሲያስተምር ነበር። ማርያም ማዳን ከቻለች የኢየሱስ ሰው ሆኖ መምጣት ሳያስፈልግ በማርያም ይፈጸም አልነበረም ወይ? ተብሎ ሲጠየቅ እነዲያቆን ያረጋል አበጋዝ ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም ማለት ስህተት ነው ብለው ለማረም ቢሞክሩም ዘቤ የተረት አባት ስህተቱን ሳያምን ዛሬም በተመሳሳይ ስህተት ላይ ይገኛል። ዘበነ ለማን ያክል ቤተክርስቲያኒቱን በአስተምህሮ ስህተት የገደለ ማንም የለም። እነኄኖክ ኃይሌ ላይገባቸው የማሉ ያህል የሚከራከሩት ስለቤዛነት የተሰጠው ትርጉም ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን ማርያምን ይጨምራል፣ ሌሎችን ብዙዎችንም በተጨማሪነት ያጠቃልላል ብለው ለመከራከር ሲንደፋደፉ አይተናል። እዚህ ላይ አስረግጠን የሊቀጳጳሱን ትምህርት የተቀበልነውና ስለኢየሱስ ክርስቶስ ብቸኛ አዳኝነትና ቤዛነት ያስተማሩት ትክክል ነው ያልነው ጳጳሱን በተለየ ስለወደድን ሳይሆን ያስተማሩት እውነት ስለሆነ ነው። ለእውቀት አእዱገ ገዳም ለሆኑት ሰዎች የምንነግራቸው ነገር ስለቤዛ የተጻፈና የተነገረ አንድ መቶ ሺህ ጥቅስና ትርጉም ቢኖራችሁ ለንጽጽር የማይቀርብበት የኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ብቸኛው ነው። የወደቀውን የሰው ልጅ ወደቀደመ ክብሩ ለመመለስ፣ ለበደለው ኃጢአት የተሰጠ ሥርየት፣ የተከፈለ የሞት ዋጋ ምትክ የሆነው ቤዛነት የኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። ይሄንን የሚተካ፣ የሚያክል፣ የሚወዳደር፣ የሚቤዥ ሌላ ቤዛ ከሰማይ በታች የለም። ይሄ ቤዛነት ትልቅነቱ ዘላለማዊ፣ መድኃኒትነቱ ሕያው፣ አዳኝነቱ ሞት ያላሸነፈው ነው። ስለቤዛ በትርጉምም፣ በፍቺም በንፅፅርም ከኢየሱስ ቤዛነት ጋር ሊቀርብ የሚችል ሌላ የለም። ስለቤዛ የተነገረ ሌላ ቃል አለ ብለህ ጭንቁር የቃል ክርክር ታቀርብ ይሆናል። ያንን እያነሳህ እንደዚህ ማለት ነው፣ እንደዚያ ማለት ነው እያልክ ውሃ ወቀጣ ክርክር የማንሳት መብት ይኖርሃል። የጻፎችና የፈሪሳውያን ክርክር የወንጌል እውነት ሊቀይረው እንደማይችለው ሁሉ የትኛውም ስለቤዛ የሚሰጥ፣ የተሰጠ ትርጉምና ንጽጽር ጌታችን ካደረግልን ቤዛነት ጋር አይነጻጸርም፣ ለትርጉም ክርክር ሊቀርብ አይችልም። ለነዚህ የተለሰኑ መቃብሮች የምነግራቸው በኔ በኃጢአተኛው ምትክ ቤዛ ሆኖ የሞተ ከኢየሱስ ክርስቶስ በስተቀር ሌላ ቤዛ ማንም የለም ነው የምንላቸው። ቅድስት ማርያም ቤዛ ናት የሚሉ ሰዎችን ታድናለች ወይ? ተብለው ሲጠየቁ አታድንም፣ ግን መድኃኒትን ወልዳልናለች፣ ስለዚህ ቤዛ እንላታለን ይሉናል። በምትክነትና ለኃጢአት ሥርየት እንዳልሞተችልን ከታወቀ በመጽሐፍ እንደተፃፈ "የጌታ እናት" ማለታችን በቂ አይደለም ወይ፣ ባልተፃፈ የቤዛነቷ ትርጉም ላይ ጉንጭ አልፋ ክርክር ለምን ያስፈልጋል? ሲባሉ ጴንጤ፣ ከሀዲ፣ ጸረ ማርያም የሚሉ ስድቦቻቸውን በእውቶማቲክ ይተኩሳሉ። እነዚህ ለእውቀት አእዱገ ገዳም የሆኑ ሊቀ ሊቃውንትና መተርጉመ መጻሕፍት ነን ባዮች በማርያምም፣ በኢየሱስም ሁለት አዳኝ እንዳላቸው ለጎጋ ምዕመኖቻቸው ያለከልካይ እየጮሁ መገኘታቸው ስናይ በነሱ ዘንድ ኢየሱስ ሌላ ብዙ ቤዛ እንዳላቸው እንረዳለን። አሁንም ደግመን እንላለን፣ ለአዳም ልጆች ቤዛ ሆኖ የሞተና ያዳነን ከኢየሱስ ክርስቶስ በቀር ሌላ ቤዛ የለንም። ስለቤዛ ሚሊየን ትርጉም ቢኖርህ እሱን እያመነዠክ መኖርህ የኢየሱስን ብቸኛ ቤዛነት አይቀይረውም። የኢየሱስን ቤዛነት አምናለሁ ያለ ሰው በኢየሱስ ብቸኛ የቤዛነት ሥራ ላይ ሌላ ትርጉምና ንጽጽር ለምን ይዞ ሊመጣ አይችልም። የሚመስለው፣ የሚተካከለው፣ የዘላለም የሆነ ቤዛነት ከኢየሱስ ውጪ አለ? የለም!!! አዎ! እናውቃለን፣ የኢየሱስን ዘላለማዊ የቤዛነቱን ሥራ በፍጡራንና በምድራዊያን የትርጉም ቃላት ሸፍኖ ለማሳነስና ሰው ሁሉ ወደአንድያ ቤዛው ዓይኑን እንዳያነሳ ለመጋረድ ጠላት በስንዴው መካከል የዘራው እንክርዳድ ነው። እኛ ግን በየትኛውም የቤዛ ትርጉም ሳንወጣ፣ ሳንወርድ፣ ሳንደክም "እርሱ ከጨለማ ሥልጣን አዳነን፥ ቤዛነቱንም እርሱንም የኃጢአትን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግሥት አፈለሰን።” እንላለን። ቆላስይስ 1፥13-14 ሊቀጳጳሱ ስለኢየሱስ ብቸኛና ዘላለማዊ ቤዛነት የተናገሩት ትክክል ነው። ከፍጡራን መካከል ሌላ የዘላለም ቤዛ የሆነልን፣ መሆን የሚችልም የለም። ከሰማይ በታች ቤዛ መሆን የሚችል ስለሌለ ነው አብ አንድያ ልጁን የላከልን። ወስብሐት ለእግዚአብሔር!

Saturday, December 21, 2024

ታቦትም ጽላትም ዛሬ የሉም!

ታቦትና ጽላት ዛሬ የሉም! በዚህ ርዕስ ላይ ብዙ ጊዜ ፅፈናል። አብዛኛው ሰው የሚያምነው የነገሩትን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተፃፈውን ባለመሆኑ ዛሬም ስለታቦትና ጽላት ሲከራከር ይውላል። ስለታቦትና ጽላት ምንነትና እንዴትነት ከመናገራችን በፊት አንድ ነገር በመጠየቅ ልጀምር። አንድ ሰው ናይሮቢ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነው ቢላችሁ መልሳችሁ ምን ሊሆን ይችላል? በእርግጠኝነት መልስ ከመስጠታችሁ በፊት ፊቱን በደንብ ታዩታላችሁ፣ ፈገግ ልትሉ ትችላላችሁ፣ ምን እያልክ ነው ብላችሁ መልሳችሁ ልትጠይቁት ትችላላችሁ። ከመቼ ወዲህ? ልትሉትም ትችላላችሁ። ምክንያቱም ናይሮቢ ከኬንያ ዋና ከተማነት ተዛውሮ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ሆኖ የተቆጠረበትና ሊሆን የሚችልበት እድል ስለሌለ ጠያቂያችሁ እያሾፈ ወይም እየቀለደ እንደሆነ መገመታችሁ የሚጠበቅ ነው። አብዛኛው ሕዝብ የሚረዳው እውነት ናይሮቢ የኬንያ ዋና ከተማ እንጂ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አለመሆኑን ነው። አሁን ባለንበት ሁኔታ ይሄ የተረጋገጠ እውነት ነው። እንደዚሁ ሁሉ ከእስራኤል ውጪ ታቦትና ጽላት ነበረኝ ወይም አለኝ የሚል ሁሉ ናይሮቢ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ነው ብሎ የሚናገርን ሰው ይመስላል። ምክንያቱም እነዚህን ነገሮች እየነገራችሁና እንደሆነ እየመሰከረላችሁ መሆኑ ነውና። እኔ እግዚአብሔር በምድር ላይ ከአህዛብ መካከል ከመረጣቸው ከእስራኤል 12ቱ ነገድ አንዱ ነኝ፣ በኮሬብ ተራራ የኪዳኑ ፅላት ሲሰጥ ነበርኩ፣ ከ40 ዓመት በኋላ ርስት ምድርን ዘመዶቼ በኢያሱ እጅ ሲወርሱ ድርሻ መሬት አግኝቻለሁ፣ ኢየሩሳሌም የንጉሡ ከተማ ከተማዬ ነበረች፣ ሥርዓተ ቤተ መቅደሱ ሲፈፀም እስከናቡከደነጾር ውድመትና ዘረፋ ድረስ እዚያው ሳከናውን ነበርኩ። ወገኖቼ ለ70 ዓመት በባርነት ባቢሎን ሲወርዱ ነበርኩ። በሄሮድስ ዘመን ቤተመቅደሱ ተሰርቶ ሥርዓተ ታቦቱ ባይፈፀምም እየሄድኩ እጸልይ ነበር። በአጭር ቃል እኔ ከተመረጡት ከእስራኤል ወገን እንጂ ከአህዛብ አይደለሁም እያላችሁ ነው። ከዚህ ሰው ጋር ስለታቦትና ጽላት አሰራርና ሥርዓት ጋር መነጋገር የምትችሉት በመጀመሪያ በዚህ ጉዳይ ላይ መግባባት ስትችሉ ብቻ ነው። የታቦትና የጽላት ሥርዓት እንኳን የካም ነገድ እንደሆነ በሚነገርለት በአፍሪካ ይቅርና የሴማውያን ድንኳን መገኛ በሆነችው በኢየሩሳሌምም ዛሬ የለም። ባልተመረጥክበት፣ የተለየ ኪዳን ባልተቀበልክበት፣ የመቅደሱ አገልግሎት በሌለበት ሁኔታ ራስህን በራስህ ስትመርጥ ማድረግ የምንችለው ነገር ጤንነትህን በመጠራጠር ወደምታምንበት ፀበል ሂድ እንልሃለን እንጂ ላንተ ታቦትና ጽላት የምንደፋበት ምንም ምክንያት ሊኖረን አይችልም።ምክንያቱም እኛ በመንፈስ ቅዱስ የታተምን ጤነኞች ስለሆንን ለበኣል መሰዊያና ለማመለኪያ አጸድ የምናፈነድድበት ዜሮ ምክንያት የለንም። እነዚህ ሰዎች ተረፈ ምናሴ ናቸው። ምናሴ የተባለ የይሁዳ ንጉሥ እንዲሁ አድርጎ ነበር። "ያዘዝኋቸውንም ሁሉ፥ ባሪያዬም ሙሴ ያዘዛቸውን ሕግ ሁሉ ቢያደርጉ ቢጠብቁም ለአባቶቻቸው ከሰጠኋት ምድር የእስራኤልን እግር እንደ ገና አላቅበዘብዝም ባለው ቤት የሠራውን የማምለኪያ ዐፀድን የተቀረጸውን ምስል አቆመ። ነገር ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት ካጠፋቸው ከአሕዛብ ይልቅ ክፉ ይሠሩ ዘንድ ምናሴ አሳታቸው።" (2ኛ ነገ 21፣8-9) ሊቁ የተረት አባት ዘበነ ለማ በአንድ ወቅት "ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም" ብሎ ያስተምር ነበር። ከወገኖቹ በኩል ወቀሳ ሲበዛበት እንደዚህ ብሎ የማስተማር ጩኸቱን ቢቀንስም በትምህርቱ የተበከሉት ግን ዛሬም ድረስ "ያለማርያም አማላጅነት ዓለም አይድንም" የሚለው ስሁት ትምህርት ስር እንደሰደደ አለ። የተረት ሊቁ ዘቤ ለማ ታቦትና ጽላት የወረስነው ከሙሴ ሥርዓት ነው የሚለው ጩኸቱ ዛሬም እንደቀጠለ ነው። የታቦት ቁመቱ፣ ርዝመቱ፣ ክብደቱ፣ አሸካከሙ፣ አቀማመጡ፣ ጽላቱ ላይ ምን ተጻፈ፣ ማን ጻፈ፣ ወዘተ የሚለው ጥያቄ ለደፋሩ ዘቤ ጉዳዩ አይደለም። የመናገር እድልና ሥፍራ ስላገኘ የስህተት መርዙን መርጨት ለሱ የተሟላ እውቀት ነው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ በግልጽ ቋንቋ የዘበነ ለማን አስተምህሮ የሚቃወም ትምህርት ሲሰጥ ሰምቸዋለሁ። ትምህርቱ የተሟላ ባይሆንም በትክክል ያንፀባረቀው አቋም ግን ይበል የሚያሰኝ ነው። የኦሪቱ ታቦትና ጽላት ዛሬ የለንም ብሏል። ይሄ ናይሮቢ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ አይደለም ብሎ ሀቁን እንደመመስከር ይቆጠራል። ነገር ግን የተጓደለው ነገር ቢኖር በቤተመቅደሱ ውስጥ መስዋእት እንሰዋበታለን በማለት የተናገረው የተሟላ መልስ አይደለም። ሲጀመር እሱ ከኦሪቱ ኪዳን ጋር በተመሳሳይ ስም ጽላት መባል የለበትም። በሌሎች አብያተክርስቲያናት እንደሚደረገው ለምሳሌ በግብጽ ኦርቶዶክስ ጠረጴዛ፣ መሰዊያ ተብሎ ይጠራል። ከዚያ ባለፈ ተሸክመውት መንደር ለመንደር አይወጡም፣ ገብርኤል ጡጦስ፣ ጣንጦስ፣ ኤፈራንጦስ እያሉ ሕዝቡን በጻድቅ ስም አያደነዝዙበትም። በእልልታና በጩኸት አያሰግዱትም፣ ይቀስፍሃል፣ ይሰነጥቅሃል እያሉ አያስፈራሩበትም። አይሸጥም፣ አይለወጥም። የኢትዮጵያው ግን ምናሴ በእግዚአብሔር ቤት ከፈፀመው አምልኮ ጋር ተመሳሳይ ነው። በዚህ ዘመን የተሰረቀው ታቦት በተለይም ብዙ ዘመን የቆየው ከተገኘ ብዙ ዋጋ እንደሚያወጣ ይታወቃል። ስናጠቃልል፣ ኢትዮጵያ እስራኤል አይደለችም፣ ሆናም አታውቅም። ኪዳን አልተሰጣትም፣ ታቦትም ጽላትም የእርሷ አልነበረም። የአህዛብ ሀገር ነበረች። ክርስትና እንዴት እንደገባ ራሷ በምትተርክበት ታሪክ በፍሬምናጦስ በኩል አብርሃና አፅብሃ የመጀመሪያውን ክርስትና መንግሥታዊ ሃይማኖት አድርጋ ተቀበለች። ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በኦፊሴል መናገር ያለባት የኦሪቱ ታቦትና ጽላት የለኝም፣ አሁን ያለው መሰዊያ ወይም መስዋእት ማቅረቢያ ጠረጴዛ እንጂ የተለየ አምልኮ፣ ስግደትና ምስጋና የሚቀርብለት ነገር አይደለም ብላ ማወጅ አለባት። መሰዊያ የቀረበበትን ማክበር እያለች 365 ቀን በሙሉ ሕዝቡን ማሰገድ ትክክል አይደለም። ሕዝቡ መስዋእቱን ከመብላት ይልቅ የመስዋዕቱን መክተፊያ ይዞ በመውጣት ሕዝቡን በእልልታ፣ በዝማሬ፣ በቅኔና በስግደት ማሳሳት ወንጀልም፣ ኃጢአትም፣ ክህደትም ነው። ሕዝቡ የእግዚአብሔር ታቦት ይህ ነው ብሎ ያምናል። ለዚህ ታቦት ሲል ለመግደልም፣ ለመሞትም አይመለስም። እንደእውነቱ ከሆነ የሕዝቡን አእምሮ በዚህ መልኩ ቀፍድዶ በማሰር ወደሞት ከመንዳት የባሰ ከዚህ በላይ ጥፋት የለም። እውነቱ ግን እግዚአብሔር አብ ለኛ የሰጠን መዳኛችን፣ ጽላታችን፣ አምልኮና ስግደታችን በኢየሱስ በኩል እንጂ በቁሳቁስና ሰዎች ባዘጋጇቸው ምናምንቴ ሥርዓቶች በኩል አይደለም። ዓይናችንን ከኢየሱስ ክርስቶስ ላይ ነቅለን ወደሌላ ወደማንም ለመዳን አናማትርም። ሌላ መንገድ በጭራሽ የለምና ነው። የታቦት፣ የጽላት፣ የተክልዬ፣ የአቦዬ፣ የሳምርዬ፣ የክርስቶፎሎስ፣ የአርሳዲ፣ የፈለቀች፣ የዘነበች፣ የአርሴማ፣ የንፍሮ፣ የዳቦ፣ የአፈር፣ የአመድ የሚባል የመዳኛ ዘዴ እና 20 እና 30 ትውልድህን የሚያስምር መንገድም፣ ኪዳንም ከሰማይ በታች ሌላ ስም በጭራሽ የለም። “ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” — ዮሐንስ 14፥6 የተባልነው ይህንን ነው። የምንድነው፣ የዳንነው በዚህ ስም ብቻ ነው።

Tuesday, December 17, 2024

ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ነው!

ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ክርስቶሰ ነው! ከዚህ በላይ የሚታየው ስእል የጣኦት አምላኪዎች እንጂ የሌላ የማንም ስእል አይደለም። በጣኦት አምላኪዎቹ ልብ ሰይጣን ያስቀመጠው ትርጉም እንደምንገምተው ልጅ እግሩ ሰው የኢየሱስ፣ ሽማግሌው ደግሞ የአብ መሆኑ ነው። በእግዚአብሔር መንግስት ሦስት ምስሎች በአኀዝ የሚቀመጡበት ወይም በወጣትና በሽማግሌ የሚመሰልበት መለኮታዊ ማንነት የለም። ከእግዚአብሔር ያልሆነ የሰው ልብ ያመነጨው ስእል ሁሉ ከተመለከ፣ ከተወደሰ እሱ ጣኦት ነው የሚባለው። “እንዳትረክሱ፥ የተቀረጸውን ምስል የማናቸውንም ነገር ምሳሌ፥ በወንድ ወይም በሴት መልክ የተሠራውን፥” (ዘዳግም 4፥16) አብ፣ ወልድ፣ መንፈስ ቅዱስ ምሕረትና ይቅርታ የአዳም ልጆች እንዲያገኙ ለማንም ኪዳን አልሰጡም። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰው ልጆች የምሕረትን ኪዳን ሞታችንን ከሞተልን ከኢየሱስ በቀር ለፍጡራን እንደሰጡ አንድም ቦታ ተጽፎ አናገኝም። “ብቻውን ለሆነ አምላክና መድኃኒታችን ከዘመን ሁሉ በፊት አሁንም እስከ ዘላለምም ድረስ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ክብርና ግርማ ኃይልም ሥልጣንም ይሁን፤ አሜን።” ነው የተባለው። (ይሁዳ 1፥25) እውነቱ ይህ ከሆነ የመዳን ኪዳን ያገኘነው እንዴት ነው? ኪዳነ ምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ፣ የሥርየት ቃል ድምዳሜ ወይም ፍጻሜ ማለት ነው። ምሕረት የማይገባው ጥፋተኛ፣ በምሕረት አድራጊው እቅድ ከእዳ፣ ከበደል፣ ከወንጀል ነጻ አድርጌሃለሁና የነጻነትህን አዋጅ በዚህ ደብዳቤ አረጋግጬልሃለሁ ብሎ የሚሰጠው የአርነት ሰነድ ነው። የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ወደሆነው ዝርዝር ጉዳይ ከመግባታችን በፊት ራሱ "ኪዳን" የሚለው ቃል ምንን ያመለክታል የሚለውን ለመመልከት እንሞክር! ውል በሁለት ተዋዋይ ወገኖች መካከል በቃል ወይም በፅሑፍ የሚደረግ አሳሪ ሕግ ነው። በውሉ ላይ ተዋዋይ ወገኖችን መብትና ጥቅም በማካተት የሚደርሱበት ስምምነት ሲሆን መሠረታዊው የውል አስፈላጊነት ጥቅምንና መብትን ለማስከበር መርህ አድርጎ የሚነሳ ቢሆንም ውል ሁልጊዜ አዋጭ ወይም ዘላቂ ላይሆን ይችላል። ውል በዓለማችን ላይ እየተሠራበት ያለው የተዋዋይ ወገኖች አሳሪ ስምምነት ከመጽሐፍ ቅዱሳዊ ኪዳን በጣም የተለየ ነው። የእግዚአብሔር ኪዳን ወይም (Covenant) በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የሚደረግ የአቻ ስምምነት አይደለም። ኪዳን ማለት በጥሬ ትርጉሙ ውል:ስምምነት ቢሆንም ኪዳኑ በምድር ላይ ሰዎች እንደሚያደርጉት በሁለት እኩል ተዋዋይ ወገኖች መካከል እንደተደረገው አይደለም። በውል ሰጪ(በእግዚአብሔር) እና በውል ተቀባይ (በሰው ልጆች) መካከል የተደረገው ኪዳን እግዚአብሔር መብትና ጥቅሙን ለማስከበር ወይም ከሰው ልጆች የሚያገኘው የተለየ መብት እንዲጠበቅለት የተደረገ ኪዳን ሳይሆን እግዚአብሔር በባህርይው ፍቅር ስለሆነ የጠፋውን የሰው ልጅ ለማዳን፣ በክንዱ ተጠብቆ እንዲኖር ሲል እግዚአብሔር ፍቅሩን የገለፀበት መንገድ ነው። ሌላውን ወገን የሚጠቅም ኪዳን ማድረግ የሚችለው እግዚአብሔር ብቻ ነው። እግዚአብሔር ከሰዎች ጋር የሚገባው ኪዳን አምላክነቱን አስገድዶ ለመጫን ሳይሆን ጌትነቱን ለተቀበሉት ሁሉ ከአምላክነቱ በረከት እንዲትረፈረፍላቸው ከፍቅሩ የተነሣ የሚደረግ ኪዳን ነው። “በጭንቃቸው ሁሉ እርሱ ተጨነቀ፥ የፊቱም መልአክ አዳናቸው፤ በፍቅሩና በርኅራኄውም ተቤዣቸው፥ በቀደመውም ዘመን ሁሉ አንሥቶ ተሸከማቸው።” (ኢሳ 63፥9) እግዚአብሔር አዳምን የፈጠረው ማንንም ሳያማክር ከአምላካዊ ክብሩ ሕያውነት እንዲካፈልና በዘላለማዊ ፍቅሩ እንዲኖር ነው። “ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም። (1ኛ ዮሐ 4፥10) ለአዳም የሚያስፈልገውን ነገር ሁሉ እግዚአብሔር ያሟላለት በአዳም ጥያቄ አልነበረም። እንዲያውም አዳም የተፈጠረው የአምላክን ባሕርይ ተካፋይ እንዲሆን፣ ክብሩ በሱ እንዲታይ በአርአያውና በምሳሌው ነው። እግዚአብሔር ከፈጠረውና ገዢ እንዲሆን በፍጥረቱ ላይ ካሰለጠነው ከአዳም ጋር የገባው ኪዳን ከሰጠሁህ እልፍ አእላፍ ፍጥረት መካከል ይሄን አንዱ ከበላህ ሞትን ትሞታለህና እንዳትበላው የሚል ትእዛዝ ነበር። አዳም ሞትን የሞተው ባልተነገረውና በማያውቀው ነገር ሳይሆን ራሱ ሞትን በመምረጡና የእግዚአብሔርን ድምጽ በመጣሱ የተነሳ ነው። ይህ የመጀመሪያ ኪዳን የፈረሰው ውል ተቀባዩ ውሉን በማፍረሱ ስለሆነ ውሉ የሚያስከትለው ቅጣት በአፍራሹና በልጆቹ ላይ ሞት ተግባራዊ ሆኗል። ከአዳም ውል አፍራሽነት በኋላ እግዚአብሔር ከአዳም ልጆች ጋር የገባው ሌላኛው ኪዳን ከሰው ልጅ ውድቀት በኋላ በኮሬብ ተራራ ነው። ልቅሷችሁንና ጩኸታችሁን ሰምቻለሁ ከባርነት አወጣችኋለሁ፣ ወተትና ማር የምታፈስ ሀገር አወርሳችኋለሁ ብሎ በታላቅ ድንቅና ተአምራት ከግብጽ ከወጡት እስራኤላውያን ጋር ያደረገው ኪዳን ኮሬብ ላይ ተገልጿል። (ዘጸ19፣4—5) ❝በግብፃውያን ያደረግሁትን፥ በንስርም ክንፍ እንደተሸከምኋችሁ፥ ወደ እኔም እንዳመጣኋችሁ አይታችኋል። አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤❞ ብሏል። ይህ ኪዳን ዘላለማዊው ኪዳን እስኪፈጸም ድረስ በምድራዊ ርስት የእግዚአብሔርን ሕዝብ ከሌሎች ለይቶ የሚያቆይበት የኪዳን ሕግ ተሰጥቶ ነበር። እግዚአብሔር ከመረጠው፣ ራሱ ከሚመራው፣ የተሻለ ሀገር አወርስሃለሁ ካለው ከዚህ ሕዝብ ጋር ኪዳን አደረገ። ይህ ኪዳን እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ከአህዛብ የሚለይበት፣ ደግሞም ከእግዚአብሔር ጋር በድምፅና በመልእክት የሚገናኝበት የሕግ ኪዳን ነበር። በአድርግና አታድርግ የተሠጠው የኪዳኑ ስምምነት በተጻፈው የጽሌ ሠሌዳ ላይ እንዲህ የሚል ተፅፎበት እንመለከታለን። 1/ ከኔ በስተቀር ሌሎች አማልክት አታምልክ፣ 2/ የእግዚአብሔርን ስም በከንቱ አትጥራ፣ 3/ የሰንበትን ቀን አክብር፣ 4/ እናትና አባትህን አክብር፣ 5/ አትግደል፣ 6/ አታመንዝር፣ 7/ አትስረቅ፣ 8/ በሀሰት አትመስክር፣ 9/ የባልንጀራህን ገንዘብ አትመኝ፣ 10/ ባልንጀራህን እንደራስህ ውደድ የሚል የኪዳን ሕግ ነበረ። ይህ ኪዳን ይጠበቅ ዘንድ የሚከናወንበት መንገድ የኃጢአት፣ የደኅንነት፣ የሚቃጠል መስዋዕት በማቅረብና ትዕዛዛትን በመጠበቅ ነበር። “እንዲህም ይሆናል፤ ይህችን ፍርድ ሰምተህ ብትጠብቃት ብታደርጋትም፥ አምላክህ እግዚአብሔር ለአባቶችህ የማለውን ቃል ኪዳንና ምሕረት ለአንተ ይጠብቅልሃል፤” ( ዘዳግ 7፥12) ይህ ሕግና ትዕዛዛቱ ምድራዊ ሥርየትን ያስገኝለታል እንጂ አዳም ትቶ ወደወጣበት ገነት መልሶ የሚያስገባ አልነበረም። ይህንን በእግዚአብሔር ቁጣ የተዘጋውን የገነት በር መልሶ በመክፈት አዳምንና ልጆቹን ማስገባት የሚችል ከሰው ልጆች አንድም ሰው ስላልነበረ በሌዊ ወገን በሚሾሙ ካህናት በኩል ደም በመርጨት ጊዜያዊ ሥርየትን እያገኙ እስከአማናዊ የተሻለ ኪዳን ድረስ ለመቆየት ችለዋል። ምክንያቱም ሰው በጥፋት ሥራው የተረገመ በመሆኑና ምድርም በተረገመው ሰው ምክንያት የተረገመች በመሆኗ ከሰው ልጆች መካከል ከእርግማን ነጻ የሆነ ሰው ስላልነበረ ዘላለማዊ ድነት ማስገኘት የሚችል አንድም ጻድቅ አልነበረምና ነው። “አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤” (ዘፍ 3፥1) እግዚአብሔር ሌሎች ንዑሳን ኪዳናት ከወደዳቸው ጋር ኪዳን አድርጓል። ከኖኅ ጋር በቀስተ ደመና (ዘፍ9፣11-12)፣ ከሙሴ ጋር (ዘጸ34፣27)፣ ከአብርሃም ርስቱን ሲሰጠው(ዘፍ15፣28)፣ የቁልፈታቸው ግርዛት እንዲወድቅ (17፣11)፣ ከይስሐቅ (ዘፍ17፣19)፣ ከያዕቆብ (ዘፍ35፣10-15)፣ ከዳዊት ጋር (ኤር33፣17) ኪዳን አድርጓል። ይህ ኪዳን በዘመናቸው እግዚአብሔርን ለታዘዙበትና ለፈፀሙበት ፍቅር የተነገረላቸው የመኖር ኪዳን እንጂ የአዳምን በደል የሚሽር ወይም ለሰው ልጆች የዘላለም ሕይወትን የሚያስገኝ ኪዳን አልነበረም። “የአምላክህን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ብትጠብቅ፥ በመንገዱም ብትሄድ፥ እግዚአብሔር እንደ ማለልህ ለእርሱ የተቀደሰ ሕዝብ አድርጎ ያቆምሃል።” (ዘዳ 28፥9) እግዚአብሔር የምወደው ልጄ... ያለው ከሰማይ ከወረደው በስተቀር ወደሰማይ የወጣ የለም የተባለለት ባለሙሉ ሥልጣን ዘላለማዊ ሊቀካህን፣ በደሙ በሰማያዊቷ መቅደስ የገባ ኢየሱስ ብቻ ነው። ሞትን አሸንፎ በሞት የተሸነፉትን ሁሉ ከምርኮ ነፃ ማውጣት የቻለ ከኢየሱስ በቀር ማንም የለም። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ በኤፌሶን መልዕክቱ እንዲህ ሲል አስረግጦ ይነግረናል። (ኤፌሶን 4፣8-10) ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል። ወደ ምድር ታችኛ ክፍል ደግሞ ወረደ ማለት ካልሆነ፥ ይህ ወጣ ማለትስ ምን ማለት ነው? ይህ የወረደው ሁሉን ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው ደግሞ ያው ነው። ይህ ኪዳን፣ አዲስ ኪዳን፣ የሕይወት ኪዳን ይባላል። አብ በአዳም ልጆች ላይ የነበረውን ቁጣ ያበረደበት፣ የተወደደ መስዋዕት፣ በደሙ በኩል ዘላለማዊ የማዳን ሥርየት የተፈፀመበት ኪዳን ይህ ነው። “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።” ( ዮሐ 6፥47 ) ከዚህ ኪዳን ውጪ እግዚአብሔር ሌላ ኪዳን የለውም። “ጠላቶች ሳለን ከእግዚአብሔር ጋር በልጁ ሞት ከታረቅን፥ ይልቁንም ከታረቅን በኋላ በሕይወቱ እንድናለን፤” (ሮሜ 5፥10) ከዚህ የምሕረትና የይቅርታ ኪዳን ውጪ እግዚአብሔር የተቀበለውና ደስ የተሰኘበት ሌላ ኪዳን የለም ብቻ ሳይሆን ይሄንን ኪዳን ማሟላት የሚችል ከሰው ልጆች መካከል አንድም ሰው አልነበረም። ቢኖርማ ኖሮ ኢየሱስ ሰው ሆኖ መወለድ ባላስፈለገው ነበር። ስለዚህ ለሰው ልጆች የተሰጠ የምሕረት ኪዳን ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌላ ኪዳነ ምሕረት የለም! ይህንን ኪዳን የሚተካ፣ ማዳን የሚችል፣ አብ የወደደው መስዋእትና የምወደው ልጄ ያለው ከኢየሱስ በቀር ማንም ስለሌለ ኪዳነምሕረት በማለት በቅድስት ማርያም በኩል ዘላለማዊ ድነት አገኛለሁ በሚል ተስፋ ወደ ማርያም የሚለምን ሁሉ ከሕይወት ኪዳን የጎደለ፣ እግዚአብሔር የሰጠውን የመዳን ኪዳን ያቃለለ ሰው ነው። ድንግል ማርያም ቅድስትና ብፅእት እንጂ እግዚአብሔር አብ የምሕረቴን ኪዳን በሷ በኩል አድርጌአለሁ ብሎ ኪዳን የሰጠበት ሁኔታ የለም።አንዳንዶች በማርያም ጉዳይ ስለጥንተ አብሶ (የቀደመ በደል) እያነሱ ጉንጭ አልፋ ክርክር ሲያደርጉ ይታያሉ። ይሄ የማይረባ ክርክር ነው። ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ኢየሱስ መምጣት ድረስ ለሰው ልጆች ሁሉ ገነት ተዘግታበት ይኖር ነበር። በገነት የሌለ ሰው ሁሉ በደለኛ ነው። በሕይወት አኗኗሩ ጻድቅና ንፁህ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ከገነት ውጪ ስላለ በደለኛ ነው። በአጭሩ በኪሩብ የምትጠበቀው ገነት የተዘጋበት የሰው ልጅ ሁሉ በደለኛ ነው። እንዲያውም ብፅእት ማርያም ራሷ ነፍሷ ጌታን እንደምታከብር፣ መድኃኒቷም እንደሆነ እንደዚህ በማለት መስክራለች። “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤” (ሉቃስ 1፥47) እግዚአብሔር የብሉይን (አሮጌውን) ኪዳን ከተመረጡት ከእስራኤላውያን ጋር፣ አዲሱን ኪዳን በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ካመኑት ጋር የሕይወትን ኪዳን አድርጓል። ሌላ ከማንም ጋር የማዳን፣ የሕይወት ኪዳን አላደረገም። “ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” (ዮሐ 14፥6) ኪዳነ ምሕረት ኢየሱስ ነው!

Saturday, November 9, 2024

ስለሸኮናው ድፍንና ቅድ ክርክር መነሻው ከኦርቶዶክስ አጠቃላይ የወንጌል እውቀት ችግር የሚመነጭ ነው!

አባ በርናባስ የተባሉ ሊቀጳጳስ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አስተምህሮና በምእመናኖቹም ቅቡል የሆኑና እንደጽዩፍ የሚቆጠሩ የአህያና ተመሳሳይ እንስሳትን ጉዳይ አንስተው በሐዲስ ኪዳን ትምህርት ክልክል እንዳይደሉ ለማብራራት ሞከረዋል። ምሁርና ሊቅ ነኝ ባይ መንጋው የአቡኑን ትምህርት ለመቃወም ከዳር ዳር ለመጮህ አንካሳ ዶሮ አልቀደመውም። ከአፉ ለሚወጣው መራር ቃላት ግድ የሌለው መንጋ ስለአህያ ሥጋ ርኩሰት ለመናገር የቸኮለው የጽድቅ ጉዳይ አንገብግቦት ሳይሆን እንደፈሪሳውያን ሕጋችን ተነካ ከሚል አጉል ተመጻዳቂነት የመነጨ ነው። ሀገሪቱ ካለችበት ወቅታዊ ችግርና ኦርቶዶክስ እንደቤተ ክርስቲያን በውስጧ ሌባና ማጅራት መቺ አመራር፣ በውጪ ደግሞ በሰሜን የትግራይ፣ በመሐል የኦሮሚያ፣ በጎጃም የቅባት ወዘተ ሲኖዶስ እየተባለ ሊበታትናት ጎራ የለየበትን ችግር ከመፍታት ይልቅ የአህያ ሥጋ ይጣፍጣል! ወይስ ይመራል! ብሎ ለመከራከር መራኮቱ የሚያሳየን ቤተ ክርስቲያኒቱ በአዚም፣ በድንዛዜ ውስጥ እንዳለች አመላካች ይመስለኛል። ከዚህ ድንዛዜ የሚያወጣ ያልተጠበቀ መለኮታዊ ኃይል ካልደረሰላት በስተቀር ቤተክርስቲያኒቱ እንደሥጋ ደዌ በሽታ እየፈራረሰች ማለቋን የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ያየ ያስተውላል። የዚህ ታሪክ ጸሐፊ ከ10 ዓመት በፊት ስለቤተ ክርስቲያኒቱ አደጋ በሰፊው ጽፎ ነበር። ይህንን ሊንክ ከፍተው ያንብቡ! 1/ለውጥ አንድ 2/ለውጥ ሁለት 3/ለውጥ ሦስት 4/ለውጥ ዐራት 5/ለውጥ አምሥት ወደተነሳንበት ርዕስ እንመለስ! ለመሆኑ አህያ፣ ፈረስ ወይም አሳማ፣ ሸኮናው ድፍን፣ሸኮናው ቅድ፣ የሚያመሰኳ፣ የማያመሰኳ ይበላል፣ አይበላም ያለው ማነው? ኢትዮጵያ በሲና ተራራ ላይ ኪዳን የተገባላት የኪዳን ሀገር ናት ወይ? ብለን እንጠይቅ። መልሳችን አይደለችም ይሆናል። ኢትዮጵያ ከግብፅ፣ ከሱዳን፣ ከየመን ወይም ከሶሪያ የተለየች የኪዳን ሀገር አልነበረችም፣ አይደለችምም። ሙሴ የሕጉን ኪዳን በሲና ተራራ ላይ ከተቀበለበት አንስቶ በሰሎሞን ቤተመቅደሱ እስከታነፀበት ድረስ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር ለ500 አመታት ያህል በጣኦትና በፀሐይ አምልኮ ስር እንደነበረች ታሪክ ይነግረናል። ታዲያ ባልኖረችበትና በሌለችበት ረጅም የእንቅልፏ ዘመን ውስጥ ልክ የብሉይ ኪዳንን ሕግ ተቀብላ ስትተዳደርበት የነበረች አድርጋ ስለሸኮና ድፍንና ቅድ የኦሪት ሕግ ለማውራት የሚጠይቃት የተለመደ ድፍረቷን እንጂ እውቀቷን አይደለም። ሲጀመር ከእግዚአብሔር ለኢትዮጵያ የተሰጠ የኪዳን ሕግ የለም። ሕግ ሁሉ ለእስራኤል ብቻ ነው። መጽሐፍ ቅዱስ የሚነግረን እውነት ይህንኑ ነው። “ነገር ግን እናንተን፦ ምድራቸውን ትወርሳላችሁ፤ ትወርሱአትም ዘንድ ወተትና ማር የምታፈስሰውን ምድር እሰጣችኋለሁ አልኋችሁ። እኔ ከአሕዛብ የለየኋችሁ አምላካችሁ እግዚአብሔር ነኝ።” — ዘሌዋውያን 20፥24 ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር በዚህ ኪዳን ውስጥ ነበረች? ኧረ በጭራሽ! በተረትና እንቆቅልሽ PHD ሲኖርህ እንደዘቤ ደፋሩ የሌለህን እውቀትና ማስረጃ በ"ተረቴን መልሱ፣ አፌን በዳቦ አብሱ" ዘዴ ይሆንን ጎጋ ምእመን ታስጨበጭባለህ። ከየት እንደተማረው ባይነግረንም ከዘበነ ለማ በስተቀር የኦሪት ሕግ ለኢትዮጵያ መሰጠቱን ታሪክ አያውቀውም። ንጉሡ ዳዊትም በመዝሙር እስራኤልን ለርስቱ የተመረጠ ሕዝብ እንደነበረ እንዲህ እያለ ሲዘምር እናገኘዋለን። ዳዊት የኢትዮጵያ ንጉሥ ሆኖ ያውቃል እንዴ? ዳዊት ለርስቱ እግዚአብሔር የመረጠው ሕዝብ ንጉሥ እንጂ የአህዛብ ንጉሥ አልነበረም። አህዛብ ግን ከእግሩ በታች ተቀጥቅጠው የተገዙ ባሪያዎች ነበሩ። መዝ 47፣3-4 አሕዛብን ከእኛ በታች፥ ወገኖችንም ከእግራችን በታች አስገዛልን። ለርስቱ እኛን መረጠን፥ የወደደውን የያዕቆብን ውበት። ኦርቶዶክስ ወንጌል ገና አልገባትም ስንል በማስረጃ ነው። እሷ ግን 2000 አመቴ ነው ብላ እድሜዋን በመቁጠር የእውቀት ሁሉ ጫፍ እንደደረሰች ልትነግረን ትፈልጋለች። እኛ ደግሞ ድንጋይ ውሃ ውስጥ ለሺህ አመታት ስለኖረ ዋና ይችላል ማለት አይደለም እንላታለን። እድሜ ጥሩ ቢሆንም በራሱ ምሉዕና ባለእውቀት ያደርጋል ማለት አይደለም። የግእዝን ብሂል ስላጠኑ ብቻ የእውቀት ጫፍ የደረሱ የሚመስላቸው የተረት አባቶች ከእውነት እንደተፋቱ ዛሬም አሉ። የዚህ ፅሑፍ አቅራቢ አህያም። አሳማም፣ አንበጣም አይበላም። የማይበላው የተጠቀሱት ፍጥረታት እንደብሉይ ኪዳን ሕግ አትብሉ ስለተባለ ወይም በሐዲስ ኪዳን አስተምህሮ ርኩሳን እንደሆነ እንደተቆጠሩ ስለተማረ ሳይሆን የመብላቱ ባህልና ልምድ ስለሌለው ነው። እኔ አልበላም ማለት የሚበላ ሰው ቢኖር ረክሷል በሚል ኢ-ክርስቲያናዊ አስተምህሮ ከማነወር ነጻ ሰው ስለሆነ ነው። ወንጌል እንደሚነግረን “የሚበላ የማይበላውን አይናቀው የማይበላውም በሚበላው አይፍረድ፥ እግዚአብሔር ተቀብሎታልና።” ሮሜ 14፥3 የኦርቶዶክስ መምህራን ነን ባይ ከእውቀት የተፋቱ የተረት አባቶች በእግዚአብሔር ቃል ላይ የተምታታ መልስ ሲሰጡ ተዉ እንጂ ብሎ የሚከለክላቸው የለም። ተሳስታችኋል ብሎ የሚያርማቸው ስለሌለ እንደፈለጉት እየተረጎሙ ስለ ሸኮና ቅድ፣ ሸኮና ድፍን፣ የሚያመሰኳ፣ የማያመሰኳ እያሉ ያልተሰጣቸውን ሕግ እየጠቀሱ የረከሰና ያልረከሰ ሕዝብ እያሉ ራሳቸውን ከጻድቃን ጎራ፣ የሚበላውን እንደኃጢአተኛ ፈርጀው ፍርድ ሲሰጡ ድንቁርናቸው አይሰቀጥጣቸውም። በሐዲስ ኪዳን ከልማድና ከወግ ካልሆነ በስተቀር የማይበላ ነገር የለም። 1ኛ ጢሞ 4:4-5 እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና። በዘንዶና በፀሐይ ታመልክ የነበረችው የአህዛብ ሀገር ኢትዮጵያ ያልተሰጣትን ሕግ እየጠቀሰች ቅድና ድፍን የምትለው ተረት ተረት ለእስራኤል የተነገረውን ቃል ወደራሷ እየተረጎመች ካልሆነ በስተቀር በዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ውስጥ አህዛብ ማነው? ሕዝብስ? ብለን እንጠይቃታለን። “አሁንም ቃሌን በእውነት ብትሰሙ ኪዳኔንም ብትጠብቁ፥ ምድር ሁሉ የእኔ ናትና ከአሕዛብ ሁሉ የተመረጠ ርስት ትሆኑልኛላችሁ፤” — ዘጸአት 19፥5 ከእስራኤል ውጪ ያለው ሁሉ አህዛብ ይባላል። አህዛብ ደግሞ የኦሪቱ ሕግ የኪዳን ሕዝብ አካል አይደለም። ስለዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በሌላት የኪዳን ሕግ የሚበላና የማይበላ እያለች ስለኮሼር kosher” (כָּשֵׁר) ሕግ መናገር አትችልም። ከተናገረችም ከድንቁርና የተነሳ ነው። ከእስራኤል ውጪ የነበረው አህዛብ ይባላል። የአህዛብ ሀገር ኢትዮጵያ ስለሕግ ማውራት አትችልም። ከሕጉ ውጪ የነበርነውን እኛን አህዛቦችን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሕጉን ትእዛዛት ሁሉ ፈፅሞ በሐዲስ ኪዳን ሕግ እንደአዲስ ወለደን። ሐዋርያው ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ፣ “እነርሱ እስራኤላውያን ናቸውና፥ ልጅነትና ክብር ኪዳንም የሕግም መሰጠት የመቅደስም ሥርዓት የተስፋውም ቃላት ለእነርሱ ናቸውና፤” — ሮሜ 9፥4 ካለ በኋላ ከሕግ መሰጠት ውጪ የነበርነውን እኛ አህዛብን ወደአዲሱ የድነት ሕግ እንዴት እንደገባን እንዲህ እያለ ይነግረናል። "የምሕረቱ ዕቃዎችም ከአይሁድ ብቻ አይደሉም፥ ነገር ግን ከአሕዛብ ደግሞ የጠራን እኛ ነን። እንዲሁ ደግሞ በሆሴዕ፦ ሕዝቤ ያልሆነውን ሕዝቤ ብዬ፥ ያልተወደደችውንም የተወደደችው ብዬ እጠራለሁ፤ እናንተ ሕዝቤ አይደላችሁም በተባለላቸውም ስፍራ በዚያ የሕያው እግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ ይላል። (ሮሜ9፣24-26) ሕግን የተከተሉ እስራኤሎች ሕግን በመከተላቸው በእምነት ከሚገኘው ጽድቅ ጎደሉ። እኛ አህዛብ ደግሞ በሕግ ከነበረው ሥርዓት ውጪ ስለነበርን በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በማመን ከሚገኘው ጽድቅ የእምነት ተካፋይ ሆንን። "እንግዲህ ምን እንላለን? ጽድቅን ያልተከተሉት አሕዛብ ጽድቅን አገኙ፥ እርሱ ግን ከእምነት የሆነ ጽድቅ ነው፤ እስራኤል ግን የጽድቅን ሕግ እየተከተሉ ወደ ሕግ አልደረሱም።" ሮሜ9፣30-31 ማጠቃለያ፣ ስለሕግ አፈጻጸም ዛሬ ማንም የመናገር መብት የለውም። ፊተኛውን አስረጅቶ ዛሬ በአዲስ ኪዳን ሕግ ውስጥ ነን። የቀደመችቱ ሕግ፣ ሕጉን ያፈረሰ ምን ይሁን ትላለች? በድንጋይ ተወግሮ ይገደል! ኦርቶዶክስ የቀድሞውን ሕግ በግድ እየተገብራለሁ ካለች ስንት ሰው ደብድባ ልትገድል ነው? አባ ባርናባስ ያስተማሩት እንደወንጌል ሕግ ስህተት ባይኖርባቸውም እንደኦሪት ሕግ አስፈጻሚዋ ኦርቶዶክስ አንድ ቀን የማደር መብት ሊያገኙ አይገባም ነበር። ሕጉ ይገደሉ ስለሚል። ዘቤ ለማ ምትክ አልባው የተረት አባት phd በተረት holder፣ ሄኖክ ኃይሌ በተረቱ ብዛት ምእመናን በባዶ ሜዳ ያሰከሩት ዲያቆን፣ መምህራነ ኮኑ በበደወሉ፣ ፊደላተ ዘኈለቁ ኵሉ የተባለላቸው ተረት ጠምጣሚ ሁሉ በማይመለከታቸውና በማያውቁት የኦሪት ሕግ በግድ ነው የሚጮሁት እውነቱን ስለሚያውቁ ሳይሆን ድንቁርናቸውን እንደባለእውቀት ትውልዱ ስላጸደቀላቸው ነው። የእግዚአብሔር መንግስት አሳማ በመብላት አትጠፋም፣ ባለመብላትም አትገኝም። “የእግዚአብሔር መንግሥት ጽድቅና ሰላም በመንፈስ ቅዱስም የሆነ ደስታ ናት እንጂ መብልና መጠጥ አይደለችምና።” — ሮሜ 14፥17 እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ በእግዚአብሔር ቃልና በጸሎት የተቀደሰ ነውና። 1ኛ ጢሞ4፣4-5 ስለዚህ በመብላትና ባለመብላት ራሷን ጻድቅ የምታስመስለው ኦርቶዶክስ ከ2000 ዓመት በኋላም ወንጌል ገና አልገባትም። በግሌ አሳማም፣ አህያም አልበላም። አልበላም አልኩ እንጂ የሚበሉት ተኮንነዋል፣ ረክሰዋልም ማለቴ አይደለም። የሚበሉትን አናረክስም፣ የማይበሉትንም ብሉ ብለን አንሰብክም። ወንጌል ስለመብልና መጠጥ አይደለችምና። አባ በርናባስ ያስተማሩት ምንም ስህተት ባይኖርበትም በመንጋ ለሚነዳ ምእመን ይህንን ማስተማር እንደወንጀል ስለሚቆጠር ስለመብልና መጠጡ ትተው መጀመሪያ ስለወንጌል የመዳን ቃል ይስበኩ። ኦርቶዶክሶች ወንጌልን በግእዝም፣በአማርኛም በልዩ ልዩ ቋንቋ ያነቧታል እንጂ አልተረዷትም! የዘሌዋውያን ሕግ እንኳን በኢትዮጵያ በዛሬይቱ እስራኤል የለም። የሌለውን ሕግ እንዴት አድርጋ ነው ኦርቶዶክስ የምትተገብረው? ዘቤ መልስልኝ። ሕጉ ካልተፈጸመ መውገሪያ ድንጋይህን ይዘሃል ወይ? ለነገሩ አንተ ራስህ የቤተክርስቲያኒቱ መርግ ነህ።

Monday, July 8, 2024

ታቦትና ጽላት ዛሬ የሉም!

ዛሬ ታቦትና ጽላት የሉም! ሐዋርያው ጳውሎስ ለተሰሎንቄ ሰዎች በላከው መልእክቱ "ከሚመጣው ቁጣ ትድኑ ዘንድ ራሳችሁን ከጣዖት ወደእግዚአብሔር ዘወር እንዳላችሁ" እያለ የነበሩበትን ከንቱ አምልኮ አራግፈው በመተው እንዴት እንደተመለሱ ሲያስታውሳቸው እናነባለን። ይህንንም አስረግጦ ሲያስረዳ ልትተዉት የሚገባውን እየነገርን፣ ለእግዚአብሔር መታዘዝን እያስረዳናችሁ እንጂ በማባበል ወይም በማቆላመጥ እንዳልነበረ እናንተው ምስክሮቻችን ናችሁ ይላቸዋል። "እንደምታውቁ፥ እያቈላመጥን ከቶ አልተናገርንም፥ እግዚአብሔርም እንደሚመሰክር እያመካኘን በመጎምጀት አልሠራንም፤ የክርስቶስም ሐዋርያት እንደ መሆናችን ልንከብድባችሁ ስንችል፥ ከእናንተ ቢሆን ወይም ከሌሎች ክብርን ከሰው አልፈለግንም።" (1ኛ ተሰ2:5—6) ይህንን ቃል ዛሬም ያለማቆላመጥ፣ ክብርና ምስጋናን ባለመፈለግ በግልጽ ቋንቋ መናገር ይገባናል። ይኼውም በዚህ ዘመን ከሰማይ በታች ለተለየ ወገን፣ ዘር፣ ትውልድ ወይም በአጠቃላይ የሰው ልጅ ለተባለ የተሰጠ የቀደመችውን የእስራኤላውያን ዓይነት የታቦትና የጽላት ሕግ የለም። አዎ በዚህ ዘመን ትውልድ የሚንበረከክለት፣ የሚሰግድለት፣ ምሥጋናና ውዳሴ የሚቀርብለት፣ እልልታና እምቢልታ የሚነፋለት ታቦትም፣ ጽላትም የለንም! ይልቅስ ዓይናችሁን ሕግን ሁሉ ወደፈጸመው፣ ሕግ ያስከተለው እዳና በደላችንን ቀራንዮ ላይ በሞቱ ጠርቆ ወዳስወገደው ወደ ኢየሱስ ክርስቶስ ተመልከቱ። (ቆላስ2:15) ሕግ ካስከተለው ሞት ሕይወት ወደሰጠን ሕያው ታቦታችን ኢየሱስ ተመልከቱ። ይኼን በግልጽ / baldly/ መናገር እውነትን መግለጥ እንጂ ሃይማኖታዊ ስብከት አይደለም። (2ኛ ቆሮ3:3) ምክንያቱም፣ 1/ ታቦትም፣ ጽላትም የተሰጠው ከአህዛብ ለተለየው ለእስራኤል ከሥጋ ነው። (ዘዳ7:6) 2/ ለታቦትም ሆነ ለጽላት የተሰጠ መለኪያ፣ መስፈሪያና ሕግ ዛሬ ላይ የለም። (ዘጸ 25:10—23) 3/ ሙሴ በሰበረው ላይም ይሁን ዳግመኛ በቀረጸው ጽላት ላይ 10ቱን ትዕዛዛት በጣቱ የጻፈው እግዚአብሔር ራሱ ነው። (ዘጸ31:18) (ዘዳ10:4) በእነዚህ ዋና መመዘኛዎች የተነሳ ዛሬ ላይ ታቦትም፣ ጽላትም የለም ብሎ ደምድሞ መናገር ይቻላል። እኛ አለን ብለው የሚከራከሩን ካሉ መልሳችን እሱ ወደእግዚአብሔር የሚደረግን አምልኮ የሚጋርዱ የማመለኪያ አፀዶች ናቸው እንላቸዋለን። (ዘዳ16:21—22) እስራኤሎችም ወደ እግዚአብሔር የሚደረግን አምልኮ የሚያጋሯቸው የማምለኪያ አፀዶችን እየተከተሉ እግዚአብሔርን ያስቀኑ ነበር። የማምለኪያ ቅርጾች፣ ምስሎች፣ ስዕሎች፣ ስግደት የሚቀርብላቸው የሰዎችና የመላእክት ስሞች በሙሉ ከአህዛብ የተወረሱ ሲሆኑ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚቀርብን ምሥጋናና ውዳሴ በመጋረድ እነሱም እንዲካፈሉ (share) እንዲያደርጉ በሰይጣን የተፈበረኩ ጣዖታት ናቸው። ለጣዖት አምልኮው መሸፈኛ የሚቀርበው ሞገት እግዚአብሔር ያከበራቸው ስለሆኑ ነው የሚል ቢሆንም ስግደት፣ ምሥጋና፣ ውዳሴ፣ እልልታ፣ ሽብሸባ፣ ቅኔና ዝማሬን አካፍላችሁ ብትሰጡልኝ እኔ በነሱ በኩል እንደደረሰኝ እቆጥርላችኋለሁ ያለበት ጊዜ የለም። አንዳንድ መፍቀሬ ጣዖታት ሰዎች በጻድቅ ስም የተቀበለ የጻድቁን ዋጋ ያገኛል እያሉ አምልኮ አፀዳቸውን ለመከላከል ሲጋጋጡ ይታያሉ። ለምሳሌ ሐዋርያው ጳውሎስ የታመነ የእግዚአብሔር ሰው ነበረ ብሎ ማመን ያላየሁትን ጳውሎስ ምስልና ሐውልት ሰርቼ፣ ታቦትና ጽላት ቀርጬ እንድሰግድለት፣ እንድንበረከክለት፣ የዝማሬ፣ የቅኔ ጎርፍ እንዳፈስለት ሊያደርገኝ አይችልም። ምንጩ ያልታወቀው የጳውሎስ ምስል ለክርስቲያን ምኑ ነው? የጳውሎስስ ጽላት መነሻው ከየት ነው? እስራኤሎችን ሲያስቸግር ከነበረው ከማመልከያ አፀድ የሰይጣን መንፈስ የተቀዳ ነው። እግዚአብሔር በእገሌና በእግሊት በኩል የምታቀርቡት ምስጋናና ውዳሴ በተዘዋዋሪ ይደርሰኛልና ቀጥሉበት ሊል የሚችልበት አምላካዊ ባህርይ የለውም። ይልቁንም “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ስሜ ይህ ነው፤ ክብሬን ለሌላ፥ ምስጋናዬንም ለተቀረጹ ምስሎች አልሰጥም። ”ኢሳ 42፥8 ሲለን እናገኘዋለን። እነዚህ በገበያ ላይ የሚሸጡ የጂፕሰም ምስሎች፣ ቅርጾችና የቀለም ስዕሎችን ግማሽ ክርስቲያኖች እየገዙ ስግደት፣ ጸሎትና ማዕጠንት የሚያቀርቡላቸው ከአምልኮ እግዚአብሔር ጋር የሚያገናኛቸው ምንም ነገር የላቸውም። በአምልኮ ሽፋን የከፍታ ወንበር ላይ የተሰቀሉ ጣዖታት ናቸው። በሰማይ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር እንደተዋጉና ዘንዶውም እንዳልቻላቸው የሚናገረውን የዮሐንስ ራእይ 12:7 መነሻ በማድረግ ጣሊያናዊው ሰዓሊ ጉዊዶ ሬኒ (Guido Reni) በ1635 የሳለውን ስዕል ከገበያ ገዝተው ክርስቲያኖች የሚሰግዱለት፣ በየጥንታውያኑ አብያተ ክርስቲያናት በሱቲ፣ በተንቆጠቆጠ ጨርቅና መብራት በከበረ ቦታ ተቀምጦ፣ ስግደት እየተቀበለ፣ በእጣን እየታጠነ ውዳሴ የሚጎርፍለት ጣዖትን ከማምለክ ውጪ ሌላ ምን ስም ሊሰጠው ይችላል? ጉዊዶ ሬኒ የሰዓሊነት እውቀቱ ያመነጨው እንጂ ከዘንዶው ጋር ስንት የወደቁ መላእክት እንደነበሩና ከሚካኤል ጋር ስንት መላእክት እንደተሰለፉ የሚያውቀው አንዳች ነገር የለም። የወደቀው ባለጡንቻ ወጠምሻው ጥቁር ሰው ሰይጣን መሆኑ ነው? ጥቁር የሆነ ነገርን ሁሉ የሰይጣን መለያ አድርጎ የሰጠው ማነው? የብርሃንን መልአክ ለመምሰል ራሱን መለወጥ የሚችልን ፍጥረት ሁልጊዜም ጥቁር እንደሆነ ማሰብ የእውቀት ጉድለት መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እሱም ስዕሉ ወግ ደርሶት በየቤተመቅደሱና ክርስቲያን መሳይ አላዋቂዎች ቤት በክብር ተሰቅሎ እሱም በወደቀበት ስግደትን ይቀበላል። ያ ወደል ወጠምሻ ሰው ወደስዕሉ የሚደረገውን አምልኮ የሚስማማበት ይመስለኛል።
ማጠቃለያ፣ በአዲስ ኪዳን ለእስራኤል ብቻ ተለይቶ የተሰጠው የኪዳኑ ታቦት ዛሬ የለም። "ሥጋና ደሙ የምንፈትትበት ነው" የሚለው ለክህደት የሚቀርብ ምክንያት አምልኮን ከእግዚአብሔር ውጪ ለሌላ በማጋራት ከሚያስከትለው የዘላለም ሞት አያስጥልም። እንደጠረጴዛ እንገለገልበታለን እንጂ እያልክ በፈጠራ ስዕል አሽሞንሙነህ፣ ተሸክመኸው ውጣና ሕዝብን በእልልታና በሆታ፣ እያስጎነበስክ በስግደትና በከንቱ አምልኮ ወደሞት እርድ ንዳው የሚል ፈቃድ የሰጠህ ማነው? ስዕል፣ ምስልና ቅርጽ በየመቅደሱ፣ በየዐውደ በራፉ አስቀምጠህ እያሰገድክበት የገንዘብ መሰብሰቢያ አዚም አድርገህ እንድትጠቀም በልብልህ ላይ ከሰይጣን ውጪ ይሄንን ረቂቅ ተንኮል ያቀበለህ ማንም የለም። ለዚህ ዓይን ያወጣ፣ ከአምልኮ እግዚአብሔር የራቀ ተግባርህ ዋጋ ትከፍልበታለህ። እግዚአብሔር ያጸዳዋል፣ ቆሻሻውን ይጠርገዋል። የኤልዛቤልን ግልሙትና ገፎ እርቃኗን ያስቀረዋል። እግዚአብሔር ከነክርፏቷ የተሸከማት እድሜ ለንስሐ ነበር፣ አሁን ግን ራሱ ወርዶ የገማውን አስወግዶ፣ አዲስ አድርጎ ይሰራዋል!

Monday, June 10, 2024

ካህን ማነው?

ካህን ማነው? ካህን የሚለው ግስ ስርወ ቃሉ ዕብራይስጥ ሲሆን ኮሄን כהן (kohen) ከሚለው ቃል የመጣ ነው። አጭር ትርጉሙ "አገልጋይ" ማለት ሲሆን አቅራቢ፣ ሠራተኛ፣ የሚራዳ ማለትንም ያመለክታል። በቅዱስ መጽሐፋችን የመጀመሪያው ካህን የሳሌም ንጉሥ የነበረው፣ ትውልድና ዘር ያልተቆጠረለት መልከጼዴቅ ነበር። (ዘፍ 14:18) እሱም የኢየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ ነበር። (ዕብ6:20) የመልከጼዴቅ ክህነት በኢየሱስ ክርስቶስ ምሣሌነት የተነገረበት ምክንያት የካህንነት ሹመቱ በነገድ አልተቆጠረም። የኦሪቱ የክህነት ሥልጣን ከሌዊ ነገድ በመወለድ የሚገኝ ቢሆንም ኢየሱስ ግን ሊቀካህን የሆነው ከይሁዳ ነገድ ነው። የኦሪቱ ክህነት ያለመሃላ የሚፀና ቢሆንም የኢየሱስ ክህነት እንደመልከ ጼዴቅ ክህነት በእግዚአብሔር በመሃላ የተረጋገጠ ነው። (ዕብ 7:20—21) የዚህ ክህነት ዋና ምስጢር በአዲስ ኪዳን ከኢየሱስ በስተቀር በመሃላ እንደመልከ ጼዴቅ ለዘላለም ካህን ነህ ተብሎ የሚሾም ሌላ ካህን የለም ማለትን ያመለክታል። የኢየሱስ የካህንነት ምስጢር ራሱ መስዋእት፣ ራሱ መስዋእት አቅራቢ፣ በአብ የተወደደ መስዋእት ሆኖ በደሙ የዘላለም የኃጢአት ማስተሰሪያ መስዋእት ሆኖልን ስለእኛ ጸንቶ መቆሙን ያረጋግጥልናል። “እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና።” (ዕብ 7፥27) የዚህ በመሃላ የተሾመው ሊቀካህን መስዋእት ወደእሱ የሚመጡትን ነፍሳት ሁሉ የሚቤዥ አንዴ የቀረበ፣ ሕያው የሥርየት መስዋእት ነው። “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”(ዕብ 7፥25) ስለመልከጼዴቅ ከብሉይ ኪዳን የምናነበው ቃል ከአብርሃም ጋር ተገናኝቶ ከመባረኩ በስተቀር በፊት የት እንደነበረ፣ በኋላም ወዴት እንደሄደ የተነገረ ምንም ታሪክ የለም። ይህንን ታሪክ ኢየሱስ ራሱን በዘላለማዊ የማዳን የምልጃው ውስጥ መስዋእት ሆኖ ራሱን ሲገልጥ ብቻ ነው ለማየት የቻልነው። (ዕብራውያን ምዕራፍ 7ን ደግመው ያንብቡ) ስለዘላለማዊ ሊቀካህን አገልግሎት ስንናገር ይሄንን ሥርዓት ኢየሱስ በራሱ መስዋእትነት የደመደመው ስለሆነ እኛ ክርስቲያኖች ከእንግዲህ ሌላ ምድራዊ ሊቀካህን ዛሬ የለንም። ምክንያቱም የሊቀካህን አገልግሎት በእግዚአብሔርና በሰው መካከል፣ መካከለኛ አገልጋይ ሆኖ ሥርየትን ማስገኘት ነበር። በኦሪቱ የነበረውን የደም መስዋእት በራሱ ሕያው ሞትና ትንሣኤ ላመኑበት ሁሉ ሥርየትን ስላስገኘ ለክርስቲያን የሚሞትና ቢሞትም ሥርየትን ማሰጠት የሚችል ሰው የለምና ነው። እንኳን ለሌላው የኃጢአት ሥርየት መሆን ይቅርና ራሱን ለማዳን የሚበቃ ማንነት ያለው ሰው በምድር ላይ በጭራሽ የለም። በዚህ ዘላለማዊ ሊቀካህን ሞትና ትንሣኤ ያመንን እኛ በሱ የዘላለም ሕይወትን አግኝተናል። “እውነት እውነት እላችኋለሁ በእኔ የሚያምን የዘላለም ሕይወት አለው።”ዮሐ 6፥47 ሌላኛው የክህነት አገልግሎት ያለመሃላ የተሾሙይ የአሮን ዘሮች ነበሩ። በብሉይ ኪዳን የካህናት ወገን መሆን የሚቻለው ከያዕቆብ ልጆች ሥስተኛ በሆነው ከሌዊ ዘር በመወለድ ብቻ የሚገኝ የአገልግሎት ክብር ነበር።(ዘዳ10:8) ሌዊ ማለት በዕብራይስጥ የተባበረ፣ የተያያዘ፣ የተገናኘ ማለት ነው። ምናልባትም የስሙ ትርጓሜ ከመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ጋር የተያያዘና በእግዚአብሔርና በሰዎች መካከል አገናኝ የሆኑበትን የክህነት አገልግሎት የሚያመለክት ስም ይሆናል። ሌዋውያን የመገናኛው ድንኳን አገልጋዮች ስለሆኑ ከ፲፩ዱ የእስራኤል ነገድ ጋር እንዳይቆጠሩ እግዚአብሔር አዘዘ። (ዘኁ1:48—49) የሌዋውያን አገልግሎት የምስክሩን ድንኳን መጠበቅ (ዘኁ1:51) ሲንቀሳቀሱ መሸከም (ዘኁ1:53) በማረፊያቸው ደግሞ መትከል ሲሆን አሮንና ልጆቹ ደግሞ የመስዋዕቱን ሥርዓት በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ማከነወን ነበር። (ዘጸ28:41) በኋለኛው ታሪክ እንደምናነበው ከሌዋውያኑ ወገን የሆኑት አሳፍና ወንድሞቹ ደግሞ በከበሮ፣ በጸናጽል፣ በመሰንቆ ይዘምሩ ነበር። (1ኛ ዜና 15:16—19) ከክህነት አገልግሎቱ ጋር በተያያዘ ከሌዊ ወገን የሆኑ ካህናት በምስክሩ ድንኳን ውስጥ ልዩ፣ ልዩ የአገልግሎት ድርሻ ነበራቸው። ሕዝበ እስራኤል ሲንቀሳቀስ የመገናኛውን ድንኳን በታዘዘው መሠረት ነቅለው ለሸክም የሚያዘጋጁ፣ የተዘጋጀውን ንዋያተ ቅድሳት ደግሞ የሚሸከሙ፣ በሚያርፉበት ቦታ ደግሞ ከተሸከሙት ተቀብለው በሥርዓቱ ተክለው ለአገልግሎት የሚያዘጋጁ፣ በተተከለው ድንኳን ውስጥ የማስተሰርያ መስዋዕቱን የሚያከናውኑ፣ ተሸክመው ሲሄዱም ሆነ ሲያርፉ በመዝሙርና በመሰንቆ እያሸበሸቡ የሚያገለግሉ መዘምራን ነበሩ። በዚህ የመገናኛው ድንኳን አገልግሎት ውስጥ ከሌዊ ነገድ የተወለዱት ብቻ በአገልግሎት ተከፍለው በእግዚአብሔር የታዘዙትን አገልግሎት ሲፈፅሙ ኖረዋል። የዚህ ክህነት ባለሙሉ መብት ደግሞ በእግዚአብሔር የተመረጡት የእስራኤል ሕዝቦች ሲሆኑ ከእነርሱም መካከል የሌዊ ዘሮች ብቻ ነበሩ። ከሌዊ ዘሮችም ለድንኳኑ አገልግሎት የተለዩት የአሮን ልጆች ብቻ ናቸው። ስለዚህ፣ 1/ በዚህ ዘመን እስራኤላውያን ብቻ ናቸው ለእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች የሚል የአዲስ ኪዳን ትምህርት የለም። ስለዚህ ለተለየ ሕዝብ የተሰጠ የብሉይ ኪዳን የክህነት ሕግ በዚህ ዘመን የለም። አማኞች ሁሉ ካህናት ናቸው። “መጽሐፉን ትወስድ ዘንድ ማኅተሞቹንም ትፈታ ዘንድ ይገባሃል፥ ታርደሃልና፥ በደምህም ለእግዚአብሔር ከነገድ ሁሉ ከቋንቋም ሁሉ ከወገንም ሁሉ ከሕዝብም ሁሉ ሰዎችን ዋጅተህ ለአምላካችን መንግሥትና ካህናት ይሆኑ ዘንድ አደረግሃቸው፥ በምድርም ላይ ይነግሣሉ እያሉ አዲስን ቅኔ ይዘምራሉ።” ራእይ 5፥9-10 2/ ሌዊ በሌለበት ሌዊ፣ መስዋዕትና ሥርየት አቅራቢው ኢየሱስ በሆነበት ራሱን የተለየ ካህን የሚያደርግ ቢኖር እሱ ምድራዊ ሥርዓት ነው። እኛ በኢየሱስ ሊቀካህንነት ያመንን ሁላችን ለርስቱ የተለየን በደሙ የተዋጀን ካህናት ነን። “እናንተ ግን ከጨለማ ወደሚደነቅ ብርሃኑ የጠራችሁን የእርሱን በጎነት እንድትናገሩ የተመረጠ ትውልድ፥ የንጉሥ ካህናት፥ ቅዱስ ሕዝብ፥ ለርስቱ የተለየ ወገን ናችሁ፤” — 1ኛ ጴጥሮስ 2፥9 3/ ሌላ የምድራዊ ሹመት ሊቀካህን ይሁን ካህናት የማያስፈልገን ምክንያት ሁሉም ሰዎች በሞት የሚሸነፉና በኃጢአት የወደቁ ወይም ሊወድቁ የሚችሉ ደካማ ፍጥረቶች ስለሆኑ ነው። ዕብ 7፣22—23 እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው። ሥልጣነ ክህነት የሚባል መለኪያና መስፈሪያ የተዘጋጀለት የአገልግሎት መስፈርት በዚህ ዘመን አለ ቢሉ እሱ ከምድራዊ አስተምህሮ የመነጨ እንጂ ከሰማያዊ አገልግሎት ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። በሰማይም፣ በምድርም ያለን ሊቀካህን አንድ ሲሆን እሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ዕብራውያን 8፣ 1—2 ከተናገርነውም ዋና ነገሩ ይህ ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት አለን፤ እርሱም የመቅደስና የእውነተኛይቱ ድንኳን አገልጋይ ነው፥ እርስዋም በሰው ሳይሆን በጌታ የተተከለች ናት። በሊቀካህናችን በኢየሱስ መስዋዕትነት ያመንንና የኃጢአትን ሥርየት ከአብ የተቀበልን፣ እኛ አማኞች ሁላችን በኢየሱስ የተሾመን ካህናት ነን። “መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ላደረገ፥ ለእርሱ ከዘላለም እስከ ዘላለም ድረስ ክብርና ኃይል ይሁን፤ አሜን።” — ራእይ 1፥6 ማጠቃለያ፣ ካህን ማነው? ለሚለው ጥያቄ የማጠቃለያ መልሳችን በእስራኤል ዘሥጋ ዘመን ከ12ቱ ነገድ ለሌዊ ብቻ የተሰጠ ነበር። በአዲስ ኪዳን ዘመን በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት የዘላለም ሊቀካህናችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሲሆን በእሱ ያመን እኛን በደሙ ተቀድሰን የመንግሥቱ ካህናት፣ የሰማያዊት ኢየሩሳሌም አገልጋዮች ሆነናል። " ነገር ግን ወደ ጽዮን ተራራና ወደ ሕያው እግዚአብሔር ከተማ ደርሳችኋል፥ ወደ ሰማያዊቱም ኢየሩሳሌም፥ በደስታም ወደ ተሰበሰቡት ወደ አእላፋት መላእክት፥ በሰማያትም ወደ ተጻፉ ወደ በኵራት ማኅበር፥ የሁሉም ዳኛ ወደሚሆን ወደ እግዚአብሔር፥ ፍጹማንም ወደ ሆኑት ወደ ጻድቃን መንፈሶች፥ የአዲስም ኪዳን መካከለኛ ወደሚሆን ወደ ኢየሱስ፥ ከአቤልም ደም ይልቅ የሚሻለውን ወደሚናገር ወደ መርጨት ደም ደርሳችኋል" (ዕብ 12:22—24)

Monday, April 29, 2024

ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?)

ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?) (ክፍል አምስት) የመጨረሻ— ጸጋ ማለት በአጭር ቃል ያለዋጋ በነፃ፣ የማይገባህ ግን የተበረከተልህ ስጦታ ማለት ነው። ጸጋ በቅዱሱ ወንጌል ውስጥ በሁለት ዋና ክፍሎች በኩል በእኛ ላይ ተፈጻሚ የሚሆን የሕይወትና የኃይል ስጦታ ነው። አንደኛው፣ ሰጪውን አምኖ በመቀበል የሚገኝ የዘላለም ሕይወት ስጦታ ሲሆን ሁለተኛው የጸጋ ስጦታ አሠራር ደግሞ አምነን በተቀበልነው የዘላለም ሕይወት ውስጥ ለመኖር የዘላለም ሕይወት ሰጪውን ፈቃድና ዓላማ እየፈፀምን፣ እየተለማመድን የምንቆይበትን የኃይል ስጦታ ማለት ነው። የመጀመሪያው ሰው ይኖርበት ዘንድ ከተዘጋጀለት ቦታ የአምላኩን ትዕዛዝ ጥሶ ከተገኘበት ቦታ ከወጣ በኋላ ወደዚያ የመመለሻ እድል አልነበረውም። ይሄንን ወደቀደመ ክብሩ የመመለስን ስጦታ ለአዳምና ለልጆቹ ያቀረበው እግዚአብሔር ራሱ ነው። ይሄ ስጦታ ከሰማይ ባይመጣ ኖሮ የሰው ልጅ ወደሰማይ መመለስ ባልቻለም ነበር። እግዚአብሔር ኮናኔ በጽድቅ፣ ፈታኄ በርትዕ አምላክ ስለሆነ የኃጢአት ዋጋ መከፈል ስለነበረበት አዳም የበደለውን የኃጢአት ዋጋ ለመክፈል ኢየሱስ የኛን ሥጋ ለብሶ፣ ኃጢአት ሳይኖርበት ለመስቀል ሞት የታዘዘ ሆነ። ይህ ለዘላለም እኛን የማዳን ዋጋ ጸጋ ይባላል። “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤” ኤፌሶን 2፥8 እኛ ስለበደላችን ልንከፍለው የሚገባን ዋጋ ቢሆንም ኃጢአተኛ በራሱ ሞት ራሱን ማዳን ስለማይችል ቅዱሱ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ በኛ ምትክ ሞቶልን ከዘላለም ሞት ያዳነበት ምስጢር ነው። ይህ ስጦታ ዋጋ የተከፈለበት ነገር ግን እኛ ያልከፈልንበት፣ የማይገባን ሆኖ ሳለ አምነን እንድንበት ዘንድ በነጻ የተሰጠን ስጦታ ነው። “ሰዎችን ሁሉ የሚያድን የእግዚአብሔር ጸጋ ተገልጦአልና፤” ቲቶ 2፥11 የተገለጠው የማዳን ስጦታችን ኢየሱስ ነው። ያመኑበቱ ሁሉ የዘላለም ሕይወትን እንዲያው ያገኛሉ። እንዲያው ማለት እኛ ሰርተን ያላገኘነው፣ በነጻ የተሰጠን ውድ ዋጋ ማለት ነው። የማዳኑን ጸጋ የትኛውም የኛ ዋጋ አይተካውም። ይህ ጸጋ በመላእክት፣ በጻድቃን፣ በቅዱሳን ወይም በሰማእታት ልመናና ምልጃ የሚገኝ አይደለም። እግዚአብሔር ራሱ በልጁ በኩል በነጻ የሰጠን የዘላለም ሕይወት ነው። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16 ይህ ሁሉ የተደረገልን ከእግዚአብሔር ፍቅር የተነሳ ነው። ለዚህም ነው፣ ወንጌላዊው ዮሐንስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና ያለው። የሚያስወድድ ማንነት የሌለው የሰውን ልጅ በአምላካዊ ፍቅሩ እንዲሁ ወደደው። “ፍቅርም እንደዚህ ነው፤ እግዚአብሔር እርሱ ራሱ እንደ ወደደን ስለ ኃጢአታችንም ማስተስሪያ ይሆን ዘንድ ልጁን እንደ ላከ እንጂ እኛ እግዚአብሔርን እንደ ወደድነው አይደለም።” — 1ኛ ዮሐንስ 4፥10 በጌታችን፣ በመድኃኒታችንና በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ያመነ ሰው ከሞት ወደሕይወት ተሸጋግሯል። አሁን አዲስ እንጂ አሮጌ ማንነት የለውም። ሁለንተናው ተቀድሷል። የእግዚአብሔር ጠላት የነበረው ሰው በኢየሱስ በኩል ልጅ ሆኗል። አባ፣ አባት ብሎ የሚጠራበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብሏል። ከእንግዲህ ይሄ የንጉሡ ልጅ ቀሪ ዘመኑን የሚኖረው እንደንጉሡ ፈቃድና ሃሳብ ነው። ሰው በእምነቱ በኩል የመዳንን ጸጋ በነጻ እንደተቀበለ ሁሉ ከዚህ ምድር በሥጋ በሞት እስኪለይ ድረስ በእምነቱ ጸንቶ ለመኖር የጸጋ ኃይል ዕለት፣ ዕለት ያስፈልገዋል። አንዴ ድኛለሁ፣ ከእንግዲህ ምንም አያስፈልገኝም ሊል አይችልም። " ስለዚህም ምክንያት ትጋትን ሁሉ እያሳያችሁ በእምነታችሁ በጎነትን ጨምሩ፥ በበጎነትም እውቀትን፥ በእውቀትም ራስን መግዛት፥ ራስንም በመግዛት መጽናትን፥ በመጽናትም እግዚአብሔርን መምሰል፥ እግዚአብሔርንም በመምሰል የወንድማማችን መዋደድ፥ በወንድማማችም መዋደድ ፍቅርን ጨምሩ።" (2ኛ ጴጥ1፣5—7) አንዴ የዳነ ሰው እምነቱ በበጎ ማንነት ሊገለፅ የግድ ነው። በጎ ማንነቱ የሚገለፀው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው። የተተከለ ብርቱኳን የሚያፈራው ብርቱኳን ለመሆን ሳይሆን ብርቱኳን ስለሆነ ነው። አንድም ክርስቲያን የዳነው በእምነቱ ሲሆን እምነቱን በመልካም ሥራ የሚገልፀው ለመዳን ሳይሆን ስለዳነ ነው። ለመዳንም ሆነ ከዳነ በኋላ እምነቱን በሥራ ለመግለፅ ጸጋ የተባለ ኃይል የግድ ያስፈልገዋል። በባለፉት ዐራት ክፍሎች ላይ እንደገለፅነው ሦስቱን የኃጢአት በሮች መዝጋት የሚቻለው ጸጋ በተባለ ኃይል ስለሆነ የጸጋውን ኃይል መያዝ ይኖርብናል። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16 ጸጋ፣ ቅዱሱን መጽሐፍ በመመርመር (2ኛ ጢሞ 3:15) በጸሎት (የሐዋ 1፣14) (የሐዋ 6፣4) (ማር 9፣29) ከነውር የፀዳች ሕሊና በመያዝ (የሐዋ 24፣16) በጽድቅ ንቁ በመሆን (1ኛ ቆሮ 15:34) ኃጢአትን ባለማድረግ (1ኛ ዮሐ 3:6) “ከክፉ የጎልማሳነት ምኞት ግን ሽሽ፥ በንጹሕም ልብ ጌታን ከሚጠሩ ጋር ጽድቅን እምነትን ፍቅርን ሰላምን አጥብቀህ ተከተል።” — 2ኛ ጢሞቴዎስ 2፥22 ከላይ እንደተጠቀሰው አንድ አማኝ ካመነ በኋላ ቀሪ ዘመኑን ተጠብቆ እንዲኖር በጸጋው ስጦታ ፊት ዕለት፣ ዕለት መኖር አለበት። ለአንድ አማኝ የሥጋውን መሻት፣ ዓለም የምታቀርብለትን ፈተና እና ከጠላት የተዘጋጀበትን ውጊያ አሸንፎ በእምነቱ ለመዝለቅ ጸጋ የተባለ የመከላከያ ጋሻ የግድ አስፈላጊው ነው። ያለጸጋው ኃይል መሸነፉ አይቀሬ ይሆናል። ብዙዎችም "ዳሩ ግን ባለ ጠጎች ሊሆኑ የሚፈልጉ በጥፋትና በመፍረስ ሰዎችን በሚያሰጥምና በሚያሰንፍ በሚጎዳም በብዙ ምኞትና በፈተና በወጥመድም ይወድቃሉ። ገንዘብን መውደድ የክፋት ሁሉ ሥር ነውና፥ አንዳንዶች ይህን ሲመኙ፥ ከሃይማኖት ተሳስተው በብዙ ሥቃይ ራሳቸውን ወጉ። አንተ ግን፥ የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ ከዚህ ሽሽ፤ ጽድቅንና እግዚአብሔርን መምሰል እምነትንም ፍቅርንም መጽናትንም የዋህነትንም ተከታተል" (1ኛ ጢሞ 6፣ 9—11) ማጠቃለያ፣ የእግዚአብሔር ጸጋ እኛን ለማዳን ተገልጿል። ደግሞም የዳንበትን እምነታችንን እስከመጨረሻው አጽንተን ለመጠበቅ የጸጋው ኃይል ተሰጥቶናል። ጸጋ ታላቅ በረከት ነው። ያለጸጋ ክርስትና የለም። ከጸጋው የጎደለ ሞቷል። (ሮሜ 6፣ 22—23) አሁን ግን ከኃጢአት አርነት ወጥታችሁ ለእግዚአብሔርም ተገዝታችሁ፥ ልትቀደሱ ፍሬ አላችሁ፤ መጨረሻውም የዘላለም ሕይወት ነው። የኃጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ ግን በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የዘላለም ሕይወት ነው።

Saturday, April 20, 2024

ጸጋ ምንድነው? (What is grace?)

ጸጋ ምንድነው? (What is grace?) ክፍል ዐራት በባለፉት ክፍሎች የተመለከትነው በኢየሱስ አምነን ለዳንን ሰዎች ሁሉ የጸጋ ኃይል የሚያስፈልገን ለምንድነው? ለሚለው ጥያቄ ሦስት የኃጢአት በሮችን ለመዝጋት ነው በሚለው ሃሳብ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማብራሪያ ስንሰጥ መቆየታችን ይታወሳል። በዚሁ መሠረት ከሦስቱ የኃጢአት በሮች መካከል 1/ሥጋ 2/ ዓለም እንዴት ሊፈትኑን እንደሚችሉና ከሁለቱም የሚመጡ ፈተናዎች እንዴት መዋጋት እንደሚገባን ተመልክተናል። ሥጋ ማለት የተሸከምነውና የራሱ መሻት ያለው በነፍስ ሕያውነት የሚንቀሳቀስ አካላችን ሲሆን ይህም የሚኖረው በዚህች ምድር ላይ እንደመሆኑ መጠን ዓለም ሥጋን በባርነት እንዳትገዛ በሚዛን ለመኖር የሚያስችለን ጸጋ የሚባል ጉልበት እንደሚያስፈልገን አይተናል። ዛሬ ደግሞ ሦስተኛው ክፍል የሆነውንና የክፋት ሁሉ የኃጢአት ሹም ስለሆነው ስለወደቀው መልአክ እንመለከታለን። ይህ ፍጥረት በትዕቢት፣ በተንኮልና በክፋት የተካነ ነው። ረጅም እድሜና ብዙ ልምድ ያለው የሰው ልጆች ሁሉ ጠላት ነው። የዚህ ዓለም ገዢ የተባለውም ዓለሙን ሁሉ በዐመፃና በኃጢአት ስለያዘው ነው። “ከእግዚአብሔር እንደ ሆንን ዓለምም በሞላው በክፉው እንደ ተያዘ እናውቃለን።”1ኛ ዮሐ 5፥19 ይህ ጥንተ ጠላታችን ወደጥልቁ ወርዶ ለዘለዓለም እስኪታሰር ድረስ ለሰው ልጆች ምንም ዓይነት ርኅራኄ የለውም። ራእይ 20:10 የወደቀው መልአክ እብሪትና ትዕቢትን ሞሪስ የተባለ የነገረ መጻሕፍት ተርጓሚ “ከዳመናዎች ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፥ በልዑልም እመሰላለሁ አልህ።” ኢሳ 14፥14 ያለውን ቃል ሲተረጉም የወደቀው መልአክ ምኞቱ የመላእክት ሁሉ አለቃ መሆን ብቻ ሳይሆን አምላካዊ ሥፍራንም መፈለጉን ያሳያል ሲል ይፈታዋል። የትኛውም ምኞትና አደገኛ የአምልኮ መሻት ሁሉ ምንጩ የዚህ የወደቀው መልአክ ውጤት ነው። የናቡከደነጾር የዱራ ሜዳ ሐውልት (ዳን3:1) የምናሴ የማመለኪያ አፀድ (2ኛ መዋዕል 33)፣ ዳጎን (መሣ16:23)፣ ቤል (ኤር 50:2) ወዘተ ሁሉም የወደቀው መልአክ ሥራዎች ናቸው። ይህንንም መዝሙረኛው እንዲህ ይላል። “የአሕዛብ አማልክት ሁሉ አጋንንት ናቸውና፤ እግዚአብሔር ግን ሰማያትን ሠራ።” መዝ 96፥5 ይህ የወደቀው መልአክ ለራሱ ብቻውን ወድቆ አልቀረም፣ የመጀመሪያዎቹንም የሰው ልጆች ጣለ እንጂ። የሚገርመው ነገር ሰዎቹ ሳይጠይቁት ራሱ ሰላማዊ ጠያቂ ሆኖ ነው የቀረበው። ከጠያቂነቱ ባሻገር እንዳይበሉ የተከለከሉት ተክል ስለመኖሩ እያወቀ፣ እንደማያውቅ ፍጥረት ሆኖ ነበር የቀረባቸው። "...ሴቲቱንም፦ በውኑ እግዚአብሔር ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? አላት።”ዘፍ 3፥1 ስለመከልከላቸው እውቀቱ ከሌለው ከገነት ዛፍ ሁሉ እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ ባልጠየቀም ነበር። በሚመልሱት መልስ ለማጥመድ ነው። ይህንን በቃል የማጥመድ ተንኮል በኢየሱስ ላይም ሞክሮት ነበር። “በሕዝቡም ፊት በቃሉ ሊያጠምዱት አልቻሉም በመልሱም እየተደነቁ ዝም አሉ።”ሉቃ 20፥26 ሔዋን እንዳትበሉ አዝዞአልን? ብሎ ለጠየቃት የማጥመጃ ቃል የሰጠችው መልስ እንዲህ የሚል ነበር። (ዘፍጥረት 3:2—3) ሴቲቱም ለእባቡ አለችው፦ በገነት ካለው ከዛፍ ፍሬ እንበላለን፤ ነገር ግን በገነት መካከል ካለው ከዛፉ ፍሬ፥ እግዚአብሔር አለ፦ እንዳትሞቱ ከእርሱ አትብሉ አትንኩትም። ሔዋን ሞትን ሞታ ስለማታውቅ ይሄ ጠላት በገዛ ቃሏ ምን እንደሚመስል ሊያሳያት ነው። (ዘፍጥረት 3፣3—4) እባብም ለሴቲቱ አላት፦ ሞትን አትሞቱም፤ ከእርስዋ በበላችሁ ቀን ዓይኖቻችሁ እንዲከፈቱ እንደ እግዚአብሔርም መልካምንና ክፉን የምታውቁ እንድትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው እንጂ። ይህ ጠላት ከእግዚአብሔር ትእዛዝ ይልቅ የሱ ድምፅ የተሻለ ፍቺና ምስጢር እንዳለው እየተናገረ ሰዎቹን ወደቤተ ሙከራ እየወሰዳቸው እንዳለ እናያለን። በሚያምረውና በሚያስጎመጀው የጠላት ቤተ ሙከራ የገቡት እንግዶች አብሯቸው የነበረው ፍሬ የተለየ ውበት እንዳለው ያንጊዜ እንደአዲስ የተገለፀላቸው ይመስል ነበር። “ሴቲቱም ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደ ሆነ፥ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፥ ለጥበብም መልካም እንደ ሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ።” ዘፍ 3፥6 የወደቀው ጠላት አዲሶቹንም ፍጥረቶች ይዞ ወደምድር ተፈጠፈጠ። ይሄንን ሀተታ እዚህ ላይ ማንሳት ያስፈለገው ለመጽሐፍ ቅዱስ አንባቢያን ያልተነበበ ታሪክ ለመንገር ሳይሆን ይሄ ረጅም እድሜ፣ ልምድና ሁሉንም ክፋት የያዘ ፍጡር ዛሬም እየሰራ ያለ መሆኑን ለማስገንዘብ ነው። ዛሬም ያማልላል፣ ያስጎመጃል፣ ያስመኛል፣ ያስፈፅማል፣ ያጋድላል፣ ያፋጃል፣ ሁሉንም ክፋት በሰው ልጆች መሀል ያስፈፅማል። ስለዚህ ይሄንን ባለብዙ ልምድ ጠላት ለመዋጋት "ጸጋ" የተባለ መመከቻ የእምነት ጋሻ የግድ ልንታጠቅ ይገባል። ያለበለዚያ የመጫወቻው ሜዳ ከመሆን ልታመልጥ አትችልም። ይህ ጸጋ እንዴት እንደሚሰራ የጳውሎስ ተማሪ የነበረው ቲቶ በመልእክቱ እንዲህ እያለ ይነግረናል። “ይህም ጸጋ፥ ኃጢአተኝነትንና ዓለማዊን ምኞት ክደን፥ የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ክብር መገለጥ እየጠበቅን፥ ራሳችንን በመግዛትና በጽድቅ እግዚአብሔርንም በመምሰል በአሁኑ ዘመን እንድንኖር ያስተምረናል፤” ቲቶ 2፥12-13 ጸጋ በክርስቶስ ኢየሱስ አምነው የዳኑ ሰዎች የክርስቶስን መገለጥ እየጠበቁ፣ ራሳቸውን እየገዙ፣ በጽድቅና በቅድስና እየኖሩ ዘመኑን የሚሻገሩበት ሰማያዊ መሣሪያ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በጻፋቸው መልእክታት በሙሉ የመዝጊያ ቃል አድርጎ ከሚጠቅሳቸው የጸሎት መደምዲያው ክፍል "ጸጋ" ከእናንተ ጋር ይሁን እያለ ይለምን የነበረው አለምክንያት አልነበረም። ሦስቱን የኃጢአት በሮች መዝጋት የሚቻለው ከእግዚአብሔር በሚሰጠን ጸጋ ብቻ ነው። ይህ ጸጋ እንዴት እንደሚገለጥና እንደሚሰራ እግዚአብሔር ቢፈቅድና ብንኖር በቀጣይ ፅሑፋችን ለማየት እንሞክራለን።

Thursday, April 11, 2024

ጸጋ ምንድነው? What is Grace?

ጸጋ ምንድነው? (What is Grace?) (ክፍል ሦስት) በባለፈው ፅሑፋችን ከሦስቱ የኃጢአት በሮች አንዱ የሆነውን የሥጋን ልቅ የሆነውን ፍላጎትና መሻት በመንፈሳዊ ጉልበት በሚዛን ለማስጠበቅ ጸጋ እንዴት እንደሚያስፈልገን ተመልክተናል። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዳለው “ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ።”ገላ 5፥16 ምክንያቱም “ስለ ሥጋ ማሰብ ሞት ነውና፥ ስለ መንፈስ ማሰብ ግን ሕይወትና ሰላም ነው።” ሮሜ 8፥6 በምድር ላይ በሕይወት እስካለን እኛ አማኞች መጠበቅ ከሚገቡን የኃጢአት በሮች የመጀመሪያው የሥጋችንን መሻት መቆጣጠር ነው። ሥጋ ተፈጥሮዋ አራት የማይስማሙ ባህርያትን የተሸከመች ስለሆነ ፍላጎትዋ ገደብ የለውም። መገደብና መወሰን ያለብን አምነንበትና ዘላለማዊ ሕይወትን ባገኘንበት በኢየሱስ ክርስቶስ መንፈስ ነው። መንፈሱ ይመራናል፣ ያስተምረናል፣ ይመክረናል። ነገር ግን ሥጋን ተሸክመን የምንኖረው በዚህ ዓለም ውስጥ ስለሆነ የሥጋን ፈተና ለማሸነፍ የዓለምን ጠባይ ማወቅ ደግሞ ግድ ይለናል። 2/ ዓለም፣ ዓለም ሌላው የኃጢአትና የመከራ በር ናት። ሕይወት ያለው ሥጋችንን ተሸክመን የምንዞረው በዚህ በተረገመች ዓለም ውስጥ ነው። “አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤”ዘፍ 3፥17 ይህች ዓለም በሰው ልጅ የተነሳ የተረገመች ዓለም ከሆነች ለሰው ልጆች ዘላለማዊ መኖሪያ አልተሰራችም ማለት ነው። ስለዚህ ከዘላለማዊ መኖሪያችን የወጣን የዚህች ዓለም መጻተኛና ስደተኛ ሆነናል ማለት ነው። ስደተኛና መጻተኛ ደግሞ ኑሮው ጊዜአዊ ነው። ሐዋርያው ጴጥሮስ ለውድቀት የዳረገን የሥጋችንን ምኞት ሲገልጸው እናንተ የዚህች ዓለም ስደተኛ፣ መጻተኛ ናችሁ ይለናል። “ወዳጆች ሆይ፥ ነፍስን ከሚዋጋ ሥጋዊ ምኞት ትርቁ ዘንድ እንግዶችና መጻተኞች እንደ መሆናችሁ እለምናችኋለሁ፤” 1ኛ ጴጥ 2፥11 ስለዚህ ዓለም ለኛ የስደት ሀገራችን ናት እንጂ የሰማያዊ ዜግነት መኖሪያችን አይደለችም። በዚህ ዓለም ስንኖር እንደስደተኛ እንጂ እንደባለሀገር የፈለግነውን የማድረግ መብቱ የለንም። ስደተኞችና መጻተኞች የመሆናችንን ምስክርነት ስናረጋግጥ እንደዚህ እንላለን። "ሀገራችን በሰማይ ነው።"ፊልጵ 3:20 በስደተኝነት በምንኖርባት በዚህ ዓለም ልክ ለዘለዓለም እንደሚኖር ሰው ከዓለም ጋር ተስማምተን መኖር አንችልም። ዓለም የምታቀርብልንን ግብዣ፣ መሻትና ለዓይን የሚያስጎመዠውን ነገር ሁሉ የማድረግ ፈቃድም የለንም። ምክንያቱም ስደተኛ ወይም እንግዳ በተሰደደበትና በእንግድነት በሚኖርበት ሀገር የፈለገውን መሆን ስለማይችል ነው! አባታችን አብርሃም ከከለዳውያን ዑር ወደተስፋይቱ ምድር ወደከነዓን ውጣ ተብሎ በእግዚአብሔር በታዘዘ ጊዜ ተስፋ የሰጠውን የአምላኩን ትእዛዝ ተቀብሎ ቢወጣም አብርሃም በከነዓን ዘመኑን ሙሉ ይኖር የኖረው እንደእንግዳ በድንኳን ነበር። ምክንያቱም የአብርሃም ተስፋው እግዚአብሔር የሰራትን፣ በተስፋ የሚያልማትን ሰማያዊ ከተማ ስለነበር በእድሜው ሙሉ በከነዓን እንግዳ ሆኖ ኖሯል። ዕብ 11፣ 9—10 "ለእንግዶች እንደሚሆን በተስፋ ቃል በተሰጠው አገር በድንኳን ኖሮ፥ ያን የተስፋ ቃል አብረውት ከሚወርሱ ከይስሐቅና ከያዕቆብ ጋር፥ እንደ መጻተኛ በእምነት ተቀመጠ፤ መሠረት ያላትን፥ እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ ይጠብቅ ነበርና።" ስለሆነም የእኛም የክርስቲያኖች አኗኗር በዚህ ዓለም እንደእንግዳና መጻተኛ እንጂ ተስፋችን በዚህ ዓለም እንደተፈፀመ አድርገን መሆን የለበትም። “ዓለምን ወይም በዓለም ያሉትን አትውደዱ፤ በዓለም ያለው ሁሉ እርሱም የሥጋ ምኞትና የዓይን አምሮት ስለ ገንዘብም መመካት ከዓለም ስለ ሆነ እንጂ ከአባት ስላልሆነ፥ ማንም ዓለምን ቢወድ የአባት ፍቅር በእርሱ ውስጥ የለም።”1ኛ ዮሐ 2፥15-16 የሥልጣንህ ማማ ከደመናው ጣራ ቢደርስ፣ ገንዘብህ እንደተራራ ቢቆለል፣ እውቀትህ በአደባባይ ቢነገር፣ ዝናህ ዓለሙን ሁሉ ቢናኝ ይሄ ሊያስመካህ አይገባም። “የሚገዙም ምንም እንደሌላቸው፥ በዚችም ዓለም የሚጠቀሙ በሙሉ እንደማይጠቀሙባት ይሁኑ፤ የዚች ዓለም መልክ አላፊ ነውና።”1ኛ ቆሮ 7፥31 ወደድክም ጠላህም ዓለም የሰጠችህ የውሸት ስለሆነ የሰጠችህን ሁሉ አንድ ቀን ትቀማሃለች። "ሺህ ዓመት ንገሡ" የተባሉ ሁሉ ጨርሶ እንዳልነገሱ ሆነው ከዚህች ዓለም ፊት ተሰውረዋል። ሰሎሞን እንኳን ከዚህች ዓለም በሆነች ጥበብና ብዕል/ሀብት/ የበለጸገ ሰው ምንም እንደሌለው መሆንን መርጧል። መክብብ 2፣ 10—12 ዓይኖቼንም ከፈለጉት ሁሉ አልከለከልኋቸውም፤ ልቤም በድካሜ ሁሉ ደስ ይለው ነበርና ልቤን ከደስታ ሁሉ አላራቅሁትም፤ ከድካሜም ሁሉ ይህ እድል ፈንታዬ ሆነ። እጄ የሠራቻችን ሥራዬን ሁሉ የደከምሁበትንም ድካሜን ሁሉ ተመለከትሁ፤ እነሆ፥ ሁሉ ከንቱ ነፋስንም እንደ መከተል ነበር፥ ከፀሐይ በታችም ትርፍ አልነበረም። እኔም ጥበብን ዕብደትንና ስንፍናን አይ ዘንድ ተመለከትሁ፤ በፊት ከተደረገው በቀር፥ ከንጉሥ በኋላ የሚመጣው ሰው ምን ያደርጋል? ይላል። የዚህ ዓለም የሆነውን ነገር ሁሉ እየተከተሉ መኖር ንፋስን እንደመከተል ነው። ንፋስን ተከትሎ የጨበጠው እንደሌለ ሁሉ ዓለምን መከተል የከንቱ ከንቱን እንደመከተል ነው። ሰባኪው በእድሜው መጨረሻ ዘመናት የደረሰበት መደምደሚያ እንዲህ የሚል ነበር። አንተንም፣ እኔንም የሚያዋጣን፣ ሰሎሞንን የጠቀመው ምክር እሱ ነው። መክብብ 12፣ 7—8 አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ ፈጣሪህን አስብ። ሰባኪው፦ ከንቱ፥ ከንቱ፤ ሁሉ ከንቱ ነው ይላል። (%ይቀጥላል)

Thursday, March 28, 2024

ጸጋ ምንድነው? What is Grace?

ይህ ፅሑፍ ከባለፈው ፅሑፋችን የቀጠለ ነው። በባለፈው ፅሑፋችን "የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግንብ ሳይሆን ሰው ራሱ ነው፣ በእግዚአብሔር የተቀደሰው" ካልን በኋላ የተቀደሰ ቤተ መቅደስ መሆን የሚቻለው እንዴት ነው? በሚለው ጥያቄ ላይ ተመርኩዘን ዛሬ ደግሞ በዚሁ ዙሪያ የተወሰነውን ሐተታ እናቀርባለን። መልካም ንባብ! በጌታችን፣ በአምላካችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ያመኑ ሁሉ የኃጢአታቸውን ሥርየት አግኝተው የዘላለምን ሕይወት ይወርሱ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጆች ተብለው ይጠራሉ። “በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ እግዚአብሔር አንድያ ልጁን እስኪሰጥ ድረስ ዓለሙን እንዲሁ ወዶአልና።” ዮሐ 3፥16 አብ በአንድያ ልጁ በኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ ልጆቹ እንድንሆንለት በመፈለጉ የተነሳ ከቀዳማዊው የአዳም ኃጢአት፣ ሥርየት ያገኘንበትን ሰማያዊ ስጦታ ልጅነትን ሰጥቶናል። በዚህም የተነሳ የዐመጻ ልጆች እንዳልነበርን ሁሉ (ዕብ 8:12) አባ፣ አባት ብለን የምንጠራበትን የልጅነት መንፈስ (ሮሜ 8:15) ካገኘን በኋላ ልጅነታችንን በመጠበቅ መኖር ያለብን እንዴት ነው? የሚለው ጉዳይ የግድ ሊታወቅ የሚገባው መንፈሳዊ እውቀት ነው። በዚህ ምድር ላይ ለሚኖር ሰው ሁሉ የነፍስ የኃጢአት በሮቹ ሦስት ናቸው። አምነው ባልዳኑ ሰዎች ላይ ሦስቱም የኃጢአት በሮች ክፍት ስለሆኑ በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት እስኪያምኑ ድረስ በዚህ ፅሑፍ ስለጸጋ አስፈላጊነት ልንመክራቸው አንደፍርም። *ሦስቱ የኃጢአት በሮች ምንድናቸው? እንዴትስ ይሰራሉ? ሦስቱ የኃጢአት በሮች የተባሉት፣ 1/ ሥጋ 2/ ዓለም 3/ የወደቀው መልአክ ናቸው። ያመኑና የዳኑ ክርስቲያኖች በሙሉ እነዚህን የኃጢአት በሮች ምንነት ማወቅና ለመዝጋት የሚችሉበት አስፈላጊ ኃይላቸው ጸጋ /grace/ይባላል። የእግዚአብሔር ልጅ መሆን የቻልንበትን ድነት/ድኅነት/ ይሄንን ምድር ለቀን እስክንሄድ ድረስ አስጠብቀን መገኘት የግድ ነው። አንዴ ድኛለሁና ከእንግዲህ የፈለኩትን መሆን እችላለሁ አይባልም። ይሄንንም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ መንፈሳዊ ማሳሰቢያ ይሰጠናል። "እንግዲህ ለምኞቱ እንድትታዘዙ በሚሞት ሥጋችሁ ኃጢአት አይንገሥ፤ ብልቶቻችሁንም የዓመፃ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለኃጢአት አታቅርቡ፥ ነገር ግን ከሙታን ተለይታችሁ በሕይወት እንደምትኖሩ ራሳችሁን ለእግዚአብሔር አቅርቡ፥ ብልቶቻችሁንም የጽድቅ የጦር ዕቃ አድርጋችሁ ለእግዚአብሔር አቅርቡ።" (ሮሜ 6: 12—13) ስለሆነም ከድነት በኋላ አማኝ ሁሉ ራሱን በጽድቅና በቅድስና መጠበቅ አለበት። ይሄን ከባድ የሚመስል ነገር ግን የመንፈሳዊ ብቃት ኃይል የሆነውና ጸጋ የተባለው የታላቅ ምስጢር እውቀት ያስፈልገዋል። ጸጋ የሚገኘው እንዴት ነው? የሚለውን ከማየታችን በፊት ጸጋ የሚከላከላቸውን ሦስቱን የነፍስ የኃጢአት በሮችን ማወቅ አለብን። የኃጢአት በሮቹን ካወቅን በሚሰጠን ጸጋ እንዴት መዝጋት እንደምንችልና አስፈላጊ እንደሆነ በደንብ ይገባናል። 1/ ሥጋ፣ የለበስነው ሥጋ ፈራሽና በስባሽ ነው። በዳግም ትንሣኤ በአዲስ መልክ እስኪለወጥ ድረስ “እኛም ሁላችን በመጋረጃ በማይከደን ፊት የጌታን ክብር እንደ መስተዋት እያብለጨለጭን መንፈስ ከሚሆን ጌታ እንደሚደረግ ያን መልክ እንመስል ዘንድ ከክብር ወደ ክብር እንለወጣለን።”2ኛ ቆሮ 3፥18 "እንለወጣለን" የሚለውን የግሪኩ ቃል"μεταμορφούμεθα" ሜታሞርፌውሜታ ይለዋል።ይህም ከአንድ ከነበረበት ሁኔታ ወዳልነበረበት ሌላ ሁኔታ መለወጥ ማለት ነው። ለምሳሌ ቢራቢሮን ለመወጥ ይመለከቷል! ነፍስ ወደተገኘችበት ወደሰማይ ስትወጣ ሥጋ የምትኖረው በዚህ ምድር ነው። ምክንያቱም ሥጋ የተሠራችው ከዚሁ የምድር አፈር ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር ያበጀውን የምድር አፈር ሕይወት የሰጠው የሕይወትን እስትንፋስ እፍ ባለባት ጊዜ ነው። ሥጋ በራሱ ሕይወት የለውም። የሥጋ ሕይወቱ ነፍስ እስካለበት ድረስ ብቻ ነው። ከደቂቃዎች በፊት አንድ ወንበር ላይ ቁጭ ብላ ስታወራ የነበረች ሥጋ፣ ነፍስ ትቷት ቢወጣ በድን ሆና ትቀራለች። ነፍስ ከመለየቷ በፊትና ከተለየች በኋላ ሥጋ እዚያው ወንበሩ ላይ ቁጭ ብሎ ይገኛል። ልዩነቱ ነፍስ ስለሌለበት ሥጋው ሕይወት የለውም። ነገር ግን ነፍስ እስካለችበት ድረስ ሥጋ ሕይወት ስለሚኖረው የተዋቀረችበት የዐራት ባህርያቷ መሻትና አደገኛ የማይስማሙ ፍላጎቶች አሏት። መሻቷንና ፍላጎቶቿን ማወቅና መቆጣጠር ያለበት ባለቤቷ የሆነው የዳነው ሰው ራሱ ሲሆን ይህም ኃይል የእግዚአብሔር ጸጋ ይባላል። ሰው የነፍስና የሥጋ ውሁድ ሆኖ ድነቱን/መዳኑን/ መጠበቅ የሚችለው በመንፈሱ ነው። በኢየሱስ አምኖ የዳነ ሰው ሥጋውን መቆጣጠር የሚችለው ከእግዚአብሔር ጋር ባለው መንፈስ ሲሆን በየዕለት ግንኝነቱ የሚያግዘውንና የሚረዳው ጸጋ እንዲበዛለት ያደርጋል። “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ።” ዕብ 4፥16 ምክንያቱም ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ እያለ አበክሮ የሚነግረን ራሳችንን ማሸነፍ የምንችልበት ይህ ጸጋ ከውድቀት ይታደገናልና ነው። "ነገር ግን እላለሁ፥ በመንፈስ ተመላለሱ፥ የሥጋንም ምኞት ከቶ አትፈጽሙ። ሥጋ በመንፈስ ላይ መንፈስም በሥጋ ላይ ይመኛልና፥ እነዚህም እርስ በርሳቸው ይቀዋወማሉ፤ ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ አትችሉም።" (ገላ 5:16—17) ሥጋ ከምትበላውና ከምትጠጣው ሙቀት የተነሳ ወሲባዊ ፍላጎቷ ተቀስቅሶ ከትዳር በፊት ይሁን በኋላ ከተመኘኋት ጋር ላመንዝር ትላለች። የነፍስ መንፈሳዊ እውቀት ደግሞ “ከዝሙት ሽሹ። ሰው የሚያደርገው ኃጢአት ሁሉ ከሥጋ ውጭ ነው፤ ዝሙትን የሚሠራ ግን በገዛ ሥጋው ላይ ኃጢአትን ይሠራል።” (1ኛ ቆሮ 6፥18) ብሎ ይቆጣጠራታል። ሥጋ ልስረቅ፣ ልዋሽ፣ ላታልል፣ መሻቴን ሁሉ እንድፈፅም አትከልክሉኝ ትላለች። ጾም፣ ጸሎት አድካሚ ነው። ይሄ ሁሉ ለምኔ ነው? ልቀቁኝ፣ በአምሮቴ ልኑርበት ትላለች። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ "“በሥጋ ያሉትም እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም።” ሮሜ 8፥8 በማለት እቅጩን የነገረን። ለዚህም ነው፣ የሥጋን አምሮትና የመሻት በር ለመዝጋት ጸጋ የተባለው ኃይል የሚያስፈልገን። የእግዚአብሔር የበዛው ደግነቱ፣ በልጁ ሞት የዘላለምን ሕይወት ከሰጠን በኋላ የተፈጠርንበትን የሥጋ ፍላጎት መቆጣጠር የምንችልበትን ጸጋ የተባለውን ኃይልም አብሮ ሰጥቶናል። ወሲብ ለሥጋ የተሰጠ የአምላክ ፈቃድ ነው። ነገር ግን ኃጢአት የሚሆነው አለቦታውና አለጊዜው ስንጠቀመው ነው። ቅድመ ይሁን ድኅረ ጋብቻ ወሲብ ሁሉ ዐመፅ ነው። ምክንያቱም፣ “እንደ ሥጋ ፈቃድ ብትኖሩ ትሞቱ ዘንድ አላችሁና፤ በመንፈስ ግን የሰውነትን ሥራ ብትገድሉ በሕይወት ትኖራላችሁ።”ሮሜ 8፥13 “ዳሩ ግን ማግባት ወደሚገባው ዕድሜ በደረሰ ጊዜ ስለ ድንግልናው ያፈረ ሰው ቢኖር፥ የወደደውን ያድርግ፤ ኃጢአት የለበትም፤ ይጋቡ።”1ኛ ቆሮ 7፥36 መብልና መጠጥ የሥጋ ባሕርያት ናቸው። ነገር ግን የምንበላውንና የምንጠጣውን መለየት፣ ሆዴ ይሙላ፣ ደረቴ ይቅላ ባለማለት ሥጋን ለመጎሰም በጾምና ጸሎት የምንጠመድበትን ኃይል ለማግኘት ጸጋ የተባለ ጉልበት ያስፈልገናል። “መብል ለሆድ ነው፥ ሆድም ለመብል ነው፤ እግዚአብሔር ግን ይህንም ያንም ያጠፋቸዋል። ሥጋ ግን ለጌታ ነው እንጂ ለዝሙት አይደለም፤ ጌታም ለሥጋ ነው፤”1ኛ ቆሮ 6፥13 እዚህ ላይ በኢየሱስ አምነው ያልዳኑ ሰዎች ማለትም ሥጋና ነፍሳቸው ከእግዚአብሔር ባልሆነ መንፈስ ቁጥጥር ሥር የሚገኙ ስለሆነ ከጸጋው ተለይተው ስለወደቁ ሁሉም ኃጢአቶች በነሱ ላይ አቅም ኖሮት የፈለገውን ይሰራል። “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።” (1ኛ ዮሐ 3፥8) (...ይቀጥላል%)

Tuesday, March 12, 2024

እግዚአብሔር ሰው በሠራው ቤተ መቅደስ አይኖርም!

ይህ አባባል እግዚአብሔር ሰው በሠራው መቅደስ ዛሬ ይኖራል ብለው ለሚያምኑ ሰዎች ጆሮን ጭው የሚያደርግ ቃል ነው። ነገር ግን እውነቱ እግዚአብሔር ዛሬ ሰው በሠራው መቅደስ አለመኖሩ ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔር አዝዞት፣ ወርድና ቁመቱን ነግሮት የተሠራ ምድራዊ ቤተመቅደስ ዛሬ የለምና ነው። የቀደመችቱን የእስራኤል ቤተ መቅደስ ወርዱንና ቁመቱን፣ ስፋትና ርዝመቱን፣ ጽላቱንና ታቦቱን፣ ኤፉዱንና አልባሳተ ካህናቱን፣  መጋረጃዎቹንና ቀለማቱን፣ በአጠቃላይ የቤተ መቅደሱን ንዋያተ ቅድሳት የመረጠው እግዚአብሔር ራሱ ነበር እንጂ ምድራውያን ሰዎች አልነበሩም። ያቺ እግዚአብሔር ይገለጽባት የነበረችው ቤተ መቅደስ ዛሬ የለችም። በሙሴ የነበረው የመገናኛው ድንኳን እግዚአብሔር ራሱ ባዘዘው መሠረት የተሠራ ነው። (ዘጸ36:1) በሰሎሞን ዘመን ወደሕንጻ ቤተ መቅደስ ሲቀየር ለዳዊት ከወገቡ የሚወጣው ልጁ እንደሚሰራለት እግዚአብሔር ራሱ ተናግሮ ስለነበር እንጂ ሰሎሞን ከልቡ አንቅቶ የሰራው አልነበረም። (2ኛ ዜና 6:9) ይህ ሰሎሞን ያሠራው ቤተ መቅደስ የፈረሰበትን ታሪክ መጽሐፍ ቅዱሳችን ሲነግረን ሕዝቡ እንደአሳቡ፣ እንደፈቃዱና እንደትእዛዙ ባለመሄዱ የተነሳ የደረሰባቸውን መከራ እንዲህ ይተርክልናል።  “ሴዴቅያስም በነገሠ በዘጠኝኛው ዓመት በአሥረኛው ወር ከወሩም በአሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆርና ሠራዊቱ ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው ከበቡአት፤ በዙሪያዋም ዕርድ ሠሩባት።  (2ኛ ነገሥት ምዕራፍ 25ን  ያንብቡ) ቤተ መቅደሱ በናቡከደነጾር ፈርሶ፣ ንዋያተ ቅድሳቱ ተዘርፎ፣ ሕዝቦ ለባርነት ተግዞ ከተወሰደ በኋላ ኢየሩሳሌም ዳዋ ወርሷት ነበር። “እናንተንም ከአሕዛብ መካከል እበትናችኋለሁ፥ ሰይፍንም አስመዝዝባችኋለሁ፤ ምድራችሁም የተፈታች ትሆናለች፥ ከተሞቻችሁም ባድማ ይሆናሉ።”   ዘሌ 26፥33 ያለው ቃል ተፈጽሟል። ሁለተኛው ቤተ መቅደስ ተመልሶ የተሠራው በታላቁ ሄሮድስ ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሞቱ በተናገረበት አንቀጽ የ2ኛውንም ቤተ መቅደስ መፍረስ ሲተነብይ እንዲህ ብሎ ነበር። “ኢየሱስም መልሶ፦ ይህን ቤተ መቅደስ አፍርሱት፥ በሦስት ቀንም አነሣዋለሁ አላቸው።” ዮሐ 2፥19 አይሁዶችም ሲመልሱለት፣ "ወይቤልዎ ፡ አይሁድ ፡ በአርብዓ ፡ ወስድስቱ ፡ ዓመት ፡ ተሐንጸ ፡ ዝንቱ ፡ ቤተ ፡ መቅደስ ፡ ወአንተሰ ፡ በሠሉስ ፡ መዋዕል ፡ ታነሥኦ?" ይህ ቤተ መቅደስ ለማነጽ 46 ዓመት ፈጀ፣ አንተ በሦስት ቀን መልሰህ ትሰራዋለህን? ብለው ጠይቀውታል። ዋናው መልእክቱ ለሰውነቱ ቤተ መቅደስ ቢሆንም ከሕንጻው ቤተ መቅደስም መፍረስ ትንቢት ነበር። ይህ በሄሮድስ የታነጸው ሁለተኛው ቤተ መቅደስ 46 ዓመት የፈጀ ሲሆን ሰሎሞን ካሰራው ቤተ መቅደስ የተለየ ነበር። ምክንያቱም እግዚአብሔር ያዘዘው ቃል ሥርዓት የሚፈጸምበትና የሚከናወንበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። ታቦቱ የለም። ታቦቱና ጽላቱ በሌለበት የእግዚአብሔር ክብር አይታይም ማለት ነው። የቤተመቅደሱ ሥርዓት የሌለበት፣ ታቦቱና ጽላቱ የማይገኝበት፣ እግዚአብሔርም በሁለቱ ኪሩብ መካከል በሚታየው የክብር ደመና መካከል  ተገልጾ በአሮን የክህነት ማዕረግ ተሹመዋል የተባሉትንና በወቅቱ ሊቀካህናት የነበሩት ሐናንና ቀያፋን የሚያናግርበት ቤተ መቅደስ አልነበረም። የእግዚአብሔር ድምጽ የሚሰሙበት ቤተ መቅደስ ሆኖ ቢሆን ኖሮ ስለኢየሱስ ድምጽ ይመጣላቸው ነበር። ከዚያ ይልቅ በዚህ በሄሮድስ ቤተ መቅደስ አደባባይ የሕዝቡ የኃጢአት ሥርየትና የደኅንነት መስዋዕት ሳይሆን ይቀርብ የነበረው የገንዘብ ለዋጮችና የርግብ ሻጮች ገበታ ነበር። ገንዘብ ለዋጮቹ ለበዓል ከተለያዩ ሀገራት የሚመጡትን ሰዎች ገንዘብ የሚመነዝሩ /money exchangers/ ሲሆኑ ርግብ ሻጮቹ ደግሞ ለበደል ሥርየት የሚሆኑ ርግቦችን ለሚመጡ ለእንግዶች የሚሸጡ የነጋዴዎች አደባባይ ሆኖ ነበር። ይህ ተግባር እግዚአብሔር አዝዞ በተሠራው በሰሎሞን ቤተ መቅደስ አደባባይ ተደርጎ ቢሆን ኖሮ ከሕዝቡ ተለይቶ ይጥፋ የሚለውን ቅጣት ያስከትል ነበር። ኢየሱስም፣ በዚህ ድርጊታቸው በተበሳጭቶ “ቤቴ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ ተጽፎአል፥ እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።” (ማቴ 21፥13) ይህ ቤተ መቅደስ እግዚአብሔር የማይከብርበት፣ ሥርዓተ መቅደሱ የማይፈጸምበት ስለነበረ መፍረስ ነበረበት። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ቤተ መቅደሱ እንደሚፈርስ በተናገረው ቃል መሠረት ባረገ በዐርባኛው ዓመት፣ የሮማው ንጉሥ ጥጦስ በ70 ዓ/ ምህረት ገደማ ካፈረሰው በኋላ ላለፉት 2000 ዓመታት ቤተ መቅደስ የሚባል ታሪክ የለም። ከዚያ በኋላም  እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ስሩልኝ ያለው የተለየ ሕዝብና ሀገርም የለም። የቤተመቅደሱን ስፋትና ቁመት፣ የንዋያተ ቅድሳቱን ዝርዝርና ዓይነት የነገረው አንድም ሕዝብ ስለሌለ እግዚአብሔርን ለመገናኘት የምንሄድበት ቤተ መቅደስ በዓለም ላይ የትም ሀገር የለም። ልባቸው ያፈለቀውን፣ ኅሊናቸው ያሰበውን፣ ያላቸው የገንዘብ አቅም የፈቀደላቸውንና በሕንጻ አሠሪ ኮሚቴ በተፈቀደ ዲዛይን በተሠራ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔርን ይገባበት ዘንድ በወይራና በቅብዐ ሜሮን ግንቡን ረጭተው እግዚአብሔር ሆይ ቀድሰነዋልና ና ግባበት እያሉ ሲጣሩ ውለው ቢያድሩ በዚያ በሰዎች ሃሳብ ሕንጻ ውስጥ እግዚአብሔር የለም። እግዚአብሔር እንደዚያ አድርገው እንዲሰሩለት ያዘዘው ሕዝብና ሀገር ስለሌለ፣ ሰዎች በልባቸው መሻት በሰሩት ቤተ መቅደስ ውስጥ በተሽሞነሞነ ጥሪና ልመና  የሚገባ አምላክ አለ ብለው የሚያስቡ ከሆነ ተሳስተዋል። የሚገባ ካለም ሌላ መንፈስ ይሆን ይሆናል እንጂ የሰማይ አምላክ አይደለም። ሐዋርያት 17፣ 24—25 "ዓለሙንና በእርሱ ያለውን ሁሉ የፈጠረ አምላክ እርሱ የሰማይና የምድር ጌታ ነውና እጅ በሠራው መቅደስ አይኖርም፤ እርሱም ሕይወትንና እስትንፋስን ሁሉንም ለሁሉ ይሰጣልና አንዳች እንደሚጎድለው በሰው እጅ አይገለገልም"። አሁን ቤተ መቅደሱ አንተ ነህ። ይሄን አንተ ቤተ መቅደስ የሆነው ሰውነትህን አቆሽሸህ ስታበቃ ሕንጻውን ቀድሼዋለሁ ብትል ስህተትም፣ ክህደትም ነው። ለዚህም ነው፣ የቆሸሹ፣ ከኃጢአት ያልተመለሱ፣ ለመመለስም ፍላጎት የሌላቸው ዐመጸኞች ቤተ መቅደስ በሚሉት ሕንጻ ውስጥ ተሰግስገው መደበኛ ኑሮአቸውን የሚኖሩት። እግዚአብሔር እኔ ውስጥ የለም፣ እዚያ እኔ በሠራሁት ሕንጻ ውስጥ አምላኬ ስላለ ጥዋትና ማታ እየሄድኩ ኃጢአቴን ይቅር እንዲለኝ እነግረዋለሁ ብትል ሕንጻ ውስጥ ቁጭ ብሎ የአንተን ኃጢአት የሚሰማ የሰማይ አምላክ ስለሌለ መጀመሪያ ራስህን ቀድስ። ኢየሱስ ከኦሪቱ ቤተ መቅደስ አገልግሎት ይልቅ ወደበለጠው የአዲስ ኪዳን አገልግሎት የመጣው አንተን አማኙን ለመቀደስ እንጂ በድንጋይ የተሠራ ቤት ለመቀደስ አይደለም። “ኢየሱስም መለሰ አለውም፦ የሚወደኝ ቢኖር ቃሌን ይጠብቃል፤ አባቴም ይወደዋል ወደ እርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን።”   — ዮሐንስ 14፥23 እኔ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ስለተባለ ቤተ መቅደሱ አንተ ራስህ ነህ። ቃሉን ጠብቅ፣ አብ ይወድሃል። ወልድም ይወድሃል። አንተም መኖሪያው ትሆናለህ። አንተ መኖሪያው ካልሆንክ የእግዚአብሔር መኖሪያ የሆነ ሌላ ሕንጻ የለም። ሕንጻው አንተ ነህ። ይሄንን ሕንጻ የሠራው ኢየሱስ ነው። (በቀጣይ ፅሑፋችን "ሰው የእግዚአብሔር መኖሪያ ሕንጻ መሆን እንዴት ይችላል?") የሚለውን እንመለከታለን።

Saturday, March 2, 2024

የኢየሱስ ክርስቶስ አማላጅነት!

የብዙ ሃይማኖቶች፣ መምህራን «ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፤ ፍጹም አምላክ ነው» በማለት ያምናሉ። ያስተምራሉ። በተቃራኒው ይህን የሚክዱም አሉ። ነገር ግን በመጽሐፍ ቅዱስ የተረጋገጠው እውነት " ኢየሱስ ክርስቶስ ፍጹም ሰው፣ ፍጹም አምላክ የመሆኑ እውነት ነው። ፍጹም ሰው የመሆኑ ምስጢርን እንዲህ ይላል። “የሰው ልጅ የጠፋውን ለማዳን መጥቶአልና።”ማቴ 18፥11 ፍጹም አምላክ የመሆኑ ምስጢርን ደግሞ ራሱ እንዲህ ሲል ይነግረናል። “እኔና አብ አንድ ነን።” ዮሐንስ 10፥30 ሲል እናገኘዋለን። ታዲያ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል የሆነው እግዚአብሔር ወልድ፣ በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን ሲችል ሥጋ በመልበስ በሞቱ አዳምንና ልጆቹን ማዳን ለምን አስፈለገው? ለሚለው ጥያቄ የጠራ መልስ ማግኘት ስንችል ብቻ ነው የምልጃው ትርጉም ሊገባን የሚችለው። ወልድ ሠው በመሆን ራሱን ባዶ ማድረጉ ለምን እንደሆነ ካልገባህ ስለምልጃ የሚነገረው ነገር ሊገባህ አይችልም።። «እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ» ፊልጵ ፪፤፮-፯ እግዚአብሔር "ኰናኔ በርትዕ፣ ፈታኄ በጽድቅ" ነውና ኃጢአት የሚያስከፍለውን ዋጋ ሳያስከፍል አይተውምና ለአዳምና ለልጆቹ በደል የኃጢአት ዋጋ መከፈል ስለነበረበት ነው፣ ከሰማይ ለዚህ ሞት የተገባ ሆኖ ራሱን ባዶ ያደረገው። የፊልጵስዩስ መልእክት የሚነግረን ይሄንን ነው። የመጀመሪያው ሰው ከገነት ከወጣ በኋላ ትውልዱ በሙሉ በሞት ጥላ ሥር ወድቋል። ስቃይ፣መከራ፣ ድካም፣ በላቡ ወዝ ፍሬን የሚበላ፣ ሕመምና ሞት የሚገዛው ፍጥረት ሆኗል። ዘፍጥረት 3፣ 17—18 "አዳምንም አለው፦ የሚስትህን ቃል ሰምተሃልና፥ ከእርሱ እንዳትበላ ካዘዝሁህ ዛፍም በልተሃልና ምድር ከአንተ የተነሣ የተረገመች ትሁን፤ በሕይወት ዘመንህም ሁሉ በድካም ከእርስዋ ትበላለህ፤ እሾህንና አሜከላን ታበቅልብሃለች፤ የምድርንም ቡቃያ ትበላለህ" ስለዚህም ሰውም፣ ምድርም የተረገሙ ፍጥረቶች መሆናቸውን እናነባለን። በዚህም የተነሳ የእግዚአብሔር ቃል በአዳም ጥፋት ስለተጣሰ በእግዚአብሔርና በሰው ልጆች መካከል የጥል ግድግዳ ቆሟል። ሰው ከአምላኩ ዘላለማዊ ኑባሬ ውጪ በሞት የሚሸነፍ ፍጥረት ሆኗል ማለት ነው። የሰውን ልጅ በመቀደስ፣ በማንፃትና ከዘላለም ሞት በማዳን ማን የእግዚአብሔር ልጅ ያድርገው? ከወደቀው የሰው ልጆች መካከል ይህንን ማድረግ የሚችል አንድም ፍጥረት አልነበረም። ሊኖርም አይችልም። ገነት በሰው ልጅ ላይ ከተዘጋበትና በኪሩብ የሚጠበቅ ከነበረ ከፍጡር ገነትን መልሶ መክፈት የሚችል ምን ዓይነት መስዋእት ስለሌለ እግዚአብሔር ራሱ ከሰማይ ወርዶ ሰው ለመሆን የተገደደው ለዚህ ነው። የእግዚአብሔር ወልድ ሰው የመሆን ምስጢር በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በደሙ ለማፍረስ ነው። “ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።” ኤፌሶን 2፥16 ስለኢየሱስ ሰው የመሆን ምስጢርና የምልጃ ሥራው ከመግለጻችን በፊት ስለምልጃና አማላጅነት ጥቂት ሀተታ እናቅርብ። 1/ መማለድና አማላጅነት (Interceds & intercession) ተንበለ በዐሥሩ መራህያን ሲረባ ይተነብል፣ ይተንብል/ዘንድ/፣ ይተንብል/ትእዛዝ/ ይሆናል። አማለደ፣ ለመነ በግእዙ ግስ «ተንበለ» ማለት ሲሆን ትርጉሙም መለመን፣ መጸለይ፣ ማማለድ፣ አማላጅ መሆን፣ ማላጅ፣ አስታራቂ፣ እርቅ ፍቅር ይቅርታ መለመን ማለት ነው። አማላጅ ሲል አንዱ ለሌላው ይቅርታን፣እርቅን ሰላምን ለማስገኘት በአድራጊውና በተቀባዩ መካከል የሚያገናኝ መስመር ማለት ነው። ይህም ተቀባዩ ከአድራጊው ጋር የሚኖረውን ግንኙነት የተስተካከለ እንዲሆን በመካከለኛነት አገኛኝ ድልድል በመሆን ማገልገል የማማለድ አገልግሎት ይሰኛል። ፍጹም ሰው ሆነ ስንልም መለኮታዊ ማንነቱን ተወ ማለት ሳይሆን አምላካዊ ሥልጣኑን ሸሸገ ማለታችን ነው። ከኃጢአት ብቻ በቀር እንደእኛ የተፈተነውም ለዚህ ነው። መለኮታዊ ስልጣኑን የመሸሸጉ ምክንያትም ፍጹም ሰው በመሆን ከአብ ጋር ያለውን መለኮታዊ ዕሪናውን እንደተወ ሳይቆጥር እንደልጅ ለመታዘዝ ነው። ብዙዎች ኦርቶዶክሳውያን የሆኑ ሰዎች ልጅ ሆኖ በመታዘዙን ልክ፤ ምልጃ አቅርቧል ሲባሉ ከአብ ያሳነስን ይመስላቸዋል። አማለደ፤ አስታረቀ፤ ታዘዘ የሚሉ ቃላትን መስማማት የወልድን ባሕርይ ህጹጽ አድርጎ የሚያወርድ ነው በማለት ምልጃውን ለመቀበል የማይፈልጉ አስተሳሰቦች ሞልተዋል። አምላካዊ ባህርይውን ለመጠበቅ ሲባል ፍጹም ሰው የሆነበትን ምስጢር በመሸርሸር ከማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ የመሆን ማንነቱ ለመሸሽ መሞከር ምስጢረ ሥጋዌን በሽፍንፍኑ እንደመሻር ይቆጠራል። ማማለድ፤ ማስታረቅና መካከለኛ መሆኑን አምኖ መቀበል ከሌለ ፍጹም ሰው እንደሆነ ማመን በፍጹም ሊመጣ አይችልም። በመለኮታዊ ሥልጣኑ ማዳን እየቻለ ሥጋ መልበስ ያስፈለገው በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ ማፍረስ የሚችል ከኃጢአት ሁሉ ንጹህ የሆነ የእግዚአብሔር ልጅ በመካከል እንዲገባ በማስፈለጉ እንደሆነ አምኖ መቀበል የግድ ነው። ያለበለዚያ ነገረ ድኅነት የሚባል አስተምህሮ አይመጣም። 2/ የዕብራውያኑን መልእክት መጽሐፍ የጽርዑ ቋንቋ ምን ይለዋል? “ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል።”ዕብ 7፥25 «ὅθεν καὶ σῴζειν εἰς τὸ παντελὲς δύναται τοὺς προσερχομένους δι’ αὐτοῦ τῷ Θεῷ, πάντοτε ζῶν εἰς τὸ ἐντυγχάνειν ὑπὲρ αὐτῶν» ዕብ ፯፤፳፭ በቀይ የተሰመረበት ቃል /ኢንታይኻኔየን/ ማለት «ሊያማልድ» ማለት ነው። ይህም « ἐντυγχάνειν የሚለው ግሳዊ መስተአምር - ἐντυγχάνω ἐντυγχανω በሚለው የአገባቡ ልክ (God on behalf of), plead, appeal) መካከለኛ የሆነ፤ አስታራቂ፣ አማላጅ ማለት ነው። 3/ ዕብራይስጥ «אשר על כן יוכל גם להושיע בכל וכל את הנגשים על ידו לאלהים כי חי הוא תמיד להפגיע בעדם׃»ዕብ ፯፤፳፭ / ሌሐፍጊያ/ ማለት ሲሆን ትርጉሙም ሁለት የተለያዩ ነገሮችን በመሃከል ሆኖ የሚያገናኝ፤ የሚለምን፣ መካከለኛ የሆነ አስታራቂ ማለት ነው። ይህም በ፩ኛ ጢሞ ፪፤፭ ያለውን የመካከለኛነት ተግባር በትክክል ገላጭ ሆኖ ይገኛል። 4/ ኢየሱስ በሰውነቱ አማላጅ፣ በአምላክነቱ ፈራጅ ነው! ኢየሱስ ከትንሣኤው በኋላ በ40ኛው ቀን በሥጋው አርጓል የሚለውን አምነው ሲያበቁ ዛሬም በግርማው ዙፋን በሥጋው በአብ ቀኝ እንደተቀመጠ የማያምኑ ሃይማኖተኞች አሉ። እነዚህ ሰዎች ካረገ በኋላ ሥጋውን አረቀቀው፣ መጠጠው፣ ለወጠው ብለው በአደባባይ የማይናገሩ፣ ነገር ግን በዝምታ ውስጥ የሚክዱ አውጣኪያውያን ናቸው። ኢየሱስ በክብሩ የተቀመጠው ዛሬም በሥጋው ነው። ያለዚያማ በሥጋ አልተዛመደንም ወይም በትንሣኤ ዘጉባዔ እኛ ሰዎችም በሥጋ አንነሳም ብሎ እንደመካድ ነው። ለዚህም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፣ “ክርስቶስ በእጅ ወደ ተሰራች፥ የእውነተኛይቱ ምሳሌ ወደ ምትሆን ቅድስት አልገባምና፥ ነገር ግን በእግዚአብሔር ፊት ስለ እኛ አሁን ይታይ ዘንድ ወደ እርስዋ ወደ ሰማይ ገባ።” ዕብራውያን 9፥24 በጥቅሉ ቅዱስ ወንጌል ላይ የተጻፉት መሠረታዊ ትርጉሞች ሐዋርያት በጉስዐተ መንፈስ ቅዱስ የጻፏቸው ቃላት በስርዋጽና በኑፋቄ ቃላት ተተክተው በዕሥራ ምዕቱ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ከመታተማቸው በስተቀር የቀደሙት ጽሁፋት በትክክል የእግዚአብሔር ወልድን ፍጹም ሰውነትና አምላክነት ያለመጠፋፋት፤ ያለመቀላቀልና ያለመለያየት በፍጹም ተዋሕዶ ሰው ሆኖ መገለጹን የሚያስተምሩ ናቸው። ስለዚህም በርዕሳችን እንዳመለከትነው ክርስቶስ በአምላክነቱ ቃል ብቻ ማዳን ሲቻለው ሰው ሆኖ መገለጽ ያስፈለገው በሰውና በአምላክ ያለውን ልዩነት በማፍረስ መካከለኛ ሆኖ ለማገናኘት ነው እንላለን። ከሰው ልጆች መካከል፤ መካከለኛ መሆን የቻለና የሚቻለው ሌላ ማንም የለም። ይህንንም ካህኑ በጸሎተ ፈትቶ ላይ « እንዘ ባዕል ውእቱ በኩሉ አንደየ ርእሶ » በማለት የሚያውጀው አምላክ ሰው የሆነበትን ምሥጢር ነው። በዚህም የተነሳ ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ በፈቃዱ የአብ የባህርይ ልጅ ሆኖ ሥጋችንን ለመልበስ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በመካከላችን አደረ። እንደሰውነቱ ኃጢአት አያውቀውም። እንደካህንነቱ ዘላለማዊ ካህን ነው። እንደአዳኝነቱ ሞት አያሸንፈውም። እንደልጅነቱ የአባቱን ፈቃድ የሚፈጽም ነው። እንደስርየት መስዋዕትነቱ አንዴ፤ ግን ለሁል ጊዜ የሚሆን ነው። ይህም የነበረውን ጥል አፍርሶ በአብ የተወደደ መካከለኛና ለሕዝቡ ኃጢአት ዘላለማዊ ሥርየትን ማስገኘት የሚችል ሊቀ ካህን ሆኗል። ማማለድ ወይም ማስታረቅ ማለት ይህ ነው። መካከለኛ ማለትም ይህ ነው። በኃጢአት ምክንያት በተሰደደው ሕዝብና በእግዚአብሔር መካከል የነበረውን ጥል አፍርሶ እንደሰውነቱ ፍጹም ልጅ ሆኖ ያስታረቀ/ ያማለደ/ የሚያደርጉትን አያውቁምና አባት ሆይ ይቅር በላቸው ያለ፤ ስለጩኸቱም ድምጹ የተሰማለት ልጅ ማለት ይህ ነው። ይህንን ወልድ ሥጋ የመልበሱን አስፈላጊነትና የነገረ ድኅነት ምስጢር በመተው ወይም ለመቀበል ሳይፈልጉ መዳን የሚባል ነገር ፈጽሞ ሊታሰብ አይቻልም። አምላክነቱን እንደመተው ሳይቆጥር ፍጹም ሰው ሆነ ማለት ለማስታረቅ/ ለማማለድ/ ካልሆነ ሌላ ለምን? በመለኮታዊ ሥልጣኑማ ሰው መሆን ሳያስፈልገው በለይኩን ቃሉ ማዳን ይቻለው አልነበረምን? ሐዋርያው ጳውሎስም በግልጽ የወንጌል ቃል እንዲህ አለን። «እርሱም በስጋው ወራት ከሞት ሊያድነው ወደሚችል ከብርቱ ጩኸትና ከእንባ ጋር ጸሎትንና ምልጃን አቀረበ፥ እግዚአብሔርንም ስለ መፍራቱ ተሰማለት፤ ምንም ልጅ ቢሆን፥ ከተቀበለው መከራ መታዘዝን ተማረ፤ ከተፈጸመም በኋላ በእግዚአብሔር እንደ መልከ ጼዴቅ ሹመት ሊቀ ካህናት ተብሎ ስለ ተጠራ፥ ለሚታዘዙለት ሁሉ የዘላለም መዳን ምክንያት ሆነላቸው። ስለ እርሱም የምንናገረው ብዙ ነገር አለን፥ ጆሮቻችሁም ስለ ፈዘዙ በቃል ልንተረጕመው ጭንቅ ነው» ዕብ ፭፣፯-፲፩ ምልጃው እስከመስቀሉ ድረስ ብቻ ነው የሚሉ ከሀዲዎች አሉ። እንዴ ከሀዲዎች? ከመስቀሉ በኋላ የተፈጠርን ትውልዶች በሙሉ የኢየሱስ ክርስቶስን ሞትና ትንሣኤ ያመንን እኛ ከአብ ጋር የታረቅነው በምንድነው? አንዴ የተደረገ ነገር ግን በአብ ዘንድ የተወደደ ያ የይቅርታና የምሕረት መስዋእት ዛሬም ይማልዳል። እንደኦሪቱ መስዋእት ዕለት፣ ዕለት የማይቀርብ፣ ነገር ግን አንዴ ለሁልጊዜ የተፈፀመ፣ ዕለት፣ ዕለት ለሚመጡ ነፍሳት የኃጢአትን ስርየት የሚሰጥ መስዋዕት ነው። «ብዙ ልዩ ልዩ የእግዚአብሔር ጥበብ አሁን በቤተ ክርስቲያን በኩል በሰማያዊ ስፍራ ውስጥ ላሉት አለቆችና ሥልጣናት ትታወቅ ዘንድ፤ይህም በክርስቶስ ኢየሱስ በጌታችን የፈጸመው የዘላለም አሳብ ነበረ፥ በእርሱም ዘንድ ባለ እምነታችን በኩል በመታመን ድፍረትና መግባት በእርሱ አለን» ኤፌ ፫፤፲-፲፪ ልጆቹ መሆን የቻልነው በሥጋ በተዛመደን በክርስቶስ በኩል ነው። ልጆች ደግሞ እንደመሆናችን የአባታችን የሆነውን ሁሉ እንወርሳለን። ሮሜ ፰-፲፯ «እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል። እነርሱም እንዳይኖሩ ሞት ስለ ከለከላቸው ካህናት የሆኑት ብዙ ናቸው፤ እርሱ ግን ለዘላለም የሚኖር ስለሆነ የማይለወጥ ክህነት አለው፤ ስለ እነርሱም ሊያማልድ ዘወትር በሕይወት ይኖራልና ስለዚህ ደግሞ በእርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው ይችላል። ቅዱስና ያለ ተንኮል ነውርም የሌለበት ከኃጢአተኞችም የተለየ ከሰማያትም ከፍ ከፍ ያለ፥ እንደዚህ ያለ ሊቀ ካህናት ይገባልና፤እርሱም እንደነዚያ ሊቃነ ካህናት አስቀድሞ ስለ ራሱ ኃጢአት በኋላም ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ዕለት ዕለት መሥዋዕትን ሊያቀርብ አያስፈልገውም፤ ራሱን ባቀረበ ጊዜ ይህን አንድ ጊዜ ፈጽሞ አድርጎአልና» ዕብ ፯፤፳፪-፳፯ ራሱ የስርየት መስዋዕት፣ ራሱ ስርየት አቅራቢ ሊቀካህን፣ ራሱ ከአብ አስታራቂ የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። አንዳንዶች ዛሬም ሊቀ ካህን ሆኖ ያማልዳል አትበሉ ይሉናል። እንደምድራዊው ሊቀ ካህን የአገልግሎት ጊዜው በዐረፍተ ዘመን ያበቃለትና የጨረሰ ሳይሆን ዘላለማዊው ሊቀ ካህን ሆኖ የዘወትር መስዋእት የሚያቀርብ ሳይሆን አንዴ ቀራንዮ ላይ ባቀረበው የዘላለም ምልጃ ዛሬም ወደአብ የሚመጡትን ሁሉ ዛሬም ያድናቸዋል ማለት ይህ ነው። እዚህ ላይ እስኪ አንድ ጥያቄ እናንሳ! አንድ ሃይማኖት የለሽ ወይም የአንድ ሃይማኖታዊ ድርጅት ተከታይ የሆነ ሰው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለአዳም ኃጢአት ከሰማይ ወርዶ እንደሞተና ለሚያምኑበት ሁሉ የኃጢአት ስርየት እንደሰጠው፣ ወደሰማይም እንዳረገና በአባቱ ቀኝ ስለእሱ ዛሬም እንደሚታይ፣ ለፍርድና ኩነኔ ዳግም እንደሚመጣ፣ ተምሮ ለሚያምን ሰው ድነት /ድኅነት/ የሚሆንለት እንዴት ነው? መልስ፣ ግለሰቡ ሲያምን ለአዳም ኃጢአት ስርየት በተደረገው ቀራንዮ ላይ አንዴ በፈሰሰውና ዛሬም ሕያው በሆነ ደሙ ከበደሉ በእምነት ይነጻል። ያ ደም ለዘላለም ሕያው ስለሆነ ከአብ ጋር ያስታርቀዋል። አባ፣ አባት የሚልበትን የልጅነት መንፈስ ይቀበላል። ሮሜ 8:15 የቀራንዮ ምልጃው ዛሬም ሕያው ነው። አንድ አማኝ የእግዚአብሔር ልጅ ይሆን ዘንድ ዛሬ ቢያምን በአብ ዘንድ ያለው አስታራቂው መስዋእት ያ የደም ስርየት ብቻ ነው። ይህንን የሚተካ ሌላ ምልጃ የለም። አንዳንዶች ሐዋርያው ጳውሎስ "“እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለ ክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለ ክርስቶስ እንለምናለን።” 2ኛ ቆሮ 5፥20 ያለውን ቃል አንጠልጥለው በአብ ዘንድ ያለን አስታራቂና አማላጅ ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት ናቸው ሲሉ ይደመጣሉ። ይህ ትልቅ ስህተት ነው። የመጀመሪያ መታወቅ ያለበት ነገር አዲስ አማኝ ወደአብ የሚቀርበው በቀራንዮው መስዋእት በኩል ብቻ ነው። ሌላ ተኪ ፍጡር የለም። ሲቀጥል ቅዱሳን ሰዎችና መላእክት በምድር ሳሉ ይማልዱ የነበረው ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ፣ ከኃጢአት ውጡ፣ ንስሐ ግቡ እያሉ እንጂ የኢየሱስን ቦታ ተክተው ከአብ ጋር ማስታረቅ አይችሉም። ዛሬም መምህራኑ፣ ወንጌላውያኑ፣ ሰባኪያኑ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ እያሉ በስብከታቸውና በዝማሬያቸው አዎ ይማልዳሉ /ይለምናሉ/፣ ሰዎች ከኃጢአት፣ ከዐመጻና ከበደል ተመለሱ እያሉ ይለምናሉ፣ ይማልዳሉ። ከዚያ ባለፈ ለኃጢአተኛው ንጹሕ የኃጢአት ስርየት መስዋእት ሆነው በእግዚአብሔር ፊት ይታያሉ ማለት ከሆነ አደገኛ ክህደት ነው። ከአንዱ ከኢየሱስ በስቀተር ንጹሕና የተወደደ የኃጢአተኛ የምልጃ መስዋእት በእግዚአብሔር አብ ፊት ሌላ የለም። “እንዲሁ ኢየሱስ ለሚሻል ኪዳን ዋስ ሆኖአል።” ዕብ 7፥22 እኛ መክፈል ላቃታን የኃጢአት እዳችን አስተማማኝ የአዲስ ኪዳን ዋስ የሆነን ኢየሱስ ብቻ ነው። ሌላ ዋስ፣ ሌላ ጠበቃ፣ ሌላ መታያ፣ ሌላ አስታራቂ፣ ሌላ አማላጅ ከኢየሱስ በቀር በአብ ፊት የተወደደ ምልጃ ከፍጡር አንድም የለም። ክርስቶስ ለፍርድ ዳግም እስኪመጣ ድረስ ለኃጢአተኛ የሚቀርበው የሥርየት መስዋእት ሕያው የሆነውና በቀራንዮ አንዴ ለምልጃ የፈሰሰው የኢየሱስ ደም ነው። ወደአብ የምንቀርብበት ሌላ መንገድ የለም። “ኢየሱስም፦ እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም።” — ዮሐንስ 14፥6 በገብርኤል ይሁን በሩፋኤል፣ በሳዊሮስ ይሁን በገላውዴዎስ፣ በጅሩ አርሴማ ይሁን በክርስቶስ ሳምራ፣ በኪሮስ ይሁን በተክልዬ፣ በአድዋ ይሁን በዲላ፣ በዝቋላ ይሁን በጩቃላ፣ በአባ እንጦንስ ይሁን በእማሆይ ትብለፅ፣ በየትኛውም ሥጋ ለባሽ ፍጥረት በኩል ወደአብ መግባት ፈፅሞ አይቻልም! ምክንያቱ የጥል ግድግዳ የፈረሰውና የእዳ መስዋእት የተከፈለው በእነሱ ሞት በኩል አይደለምና። የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ዛሬም ለሚያምኑበቱ ሕያው ነው። ደሙ የኃጢአት ስርየት፣ በሊቀካህንነቱ ዛሬም አስታራቂ ነው። በአምላክነቱ ለፍርድ ዳግም ይመጣል! “በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ።” — ዮሐንስ 5፥28-29

Wednesday, January 17, 2024

“መዳንም በሌላ በማንም የለም፤ እንድንበት ዘንድ የሚገባን ለሰዎች የተሰጠ ስም ከሰማይ በታች ሌላ የለምና።” ሐዋ 4፥12

አዳም ከአምላኩ ትዕዛዝ በወጣ ጊዜ፣ ከሔዋን ጋር ከገነት ተባሮ አሜከላና እሾህ ወደምታበቅለው ምድር መጣሉን መጽሐፍ ቅዱሳችን ይነግረናል። ዘፍ 3:1—24 ይህ የአዳም በደል ከእሱ በተወለዱ ዘሮቹ በሙሉ በውርስ ሲተላለፍ ኖሯል። ከሰማይ ከወረደው ሁለተኛው አዳም/ ኢየሱስ/ በቀር ያለ ውርስ ኃጢአት የኖረ ማንም አልነበረም። የኢየሱስም ከሰማይ ወርዶ ሰው የመሆን ምስጢሩም የሚነሳው፣ የአዳም ዘር በሙሉ በሞት ፍርድ ሥር ያለ በመሆኑ ከሥጋ ለባሽ አንድም ሰው ዘሩን ነጻ ማድረግ ስለማይችል ነበር። ይህንንም ሐዋርያው ጳውሎስ አስረግጦ ሲያስረዳ ወደ ሮሜ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ እንደዚህ ብሎታል። “ስለዚህ ምክንያት ኃጢአት በአንድ ሰው ወደ ዓለም ገባ በኃጢአትም ሞት፥ እንደዚሁም ሁሉ ኃጢአትን ስላደረጉ ሞት ለሰው ሁሉ ደረሰ፤” ሮሜ 5፥12 ስለዚህም ከሦስቱ አካላት አንዱ አካል "ወልድ" በሥጋ ሰብእ ከድንግል ማርያም ተወልዶ፣ ከኃጢአት ብቻ በቀር አዳማዊ ባህርይን ተዋሕዶ ሰው ሆነ። አዳምንና ልጆቹን ከዘላለም ሞት ማዳን የሚችለው ከኃጢአት ነጻ መሆን የቻለ ብቻ ስለነበር ኢየሱስም የእግዚአብሔር በግ ሆኖ ለኃጢአተኞች ነጻ መውጣት የአብ መስዋእት ሆኖ ቀረበ። “በነገው ዮሐንስ ኢየሱስን ወደ እርሱ ሲመጣ አይቶ እንዲህ አለ፦ እነሆ የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ።”ዮሐ 1፥29 ይህ የዓለምን ኃጢአትን የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ (ካልቪኒስቶች ለዓለሙ ሁሉ አልሞተም ይላሉ) መስቀል ላይ ውሎ የኃጢአት ሥርየት እርሱ መሆኑን አምነው፣ በስሙ ለተጠመቁና እስከመጨረሻው እምነታቸውን አጽንተው ለተጠበቁ በሙሉ እንጂ ለተወሰነ ዘር፣ ነገድ፣ ጎሣ፣ ብሔር ወይም ለተወሰነ ወገን የተፈፀመ ማዳን አልነበረም። ሐዋርያው ጳውሎስ ሞት ወደዓለም በአንዱ አዳም በኩል ለሁሉ እንደደረሰ ሕይወት ደግሞ በአንዱ በኢየሱስ በኩል ለተቀበሉት ሁሉ ሆነ በማለት ያስረዳናል። “በአንዱም በደል ሞት በአንዱ በኩል ከነገሠ፥ ይልቁን የጸጋን ብዛትና የጽድቅን ስጦታ ብዛት የሚቀበሉ በአንዱ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል በሕይወት ይነግሣሉ።” ሮሜ 5፥17 እግዚአብሔር አንድያ ልጁን ወደዓለም የላከውና ለመስቀል ሞት የታዘዘው የአዳም ዘር በሙሉ በእርሱ አምነው እንዲድኑበት እንጂ የተወሰነ ቡድን ወይም በምርጫ ለተለየ ወገን ለይቶ ለማዳን አይደለም። በዚህ ዘመን ጆን ካልቪን የተባለ የ17ኛው ክ/ዘመን የተነሳ የአዲስ ሃይማኖት አስተማሪ ደቀመዛሙርት ነን የሚሉ በዚህ ዘመንም ኢትዮጵያ ውስጥ ሃይማኖታዊ ክሂዶትን አጠናክረው በመቀጠል ኢየሱስ የሞተልን ለእኛ ለተመረጥን፣ አስቀድሞ ለተለየንና ለተጠራን ብቻ እንጂ ለአዳም ልጆች ሁሉ ኃጢአት አይደለም እያሉ በታላቅ ድፍረት ሲናገሩ ይደመጣሉ። ብዙዎችንም እያሳቱ ይገኛሉ። በመጥምቁ ዮሐንስ የተመሰከረልንና "የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ" ዮሐ 1:29 የሚለው ቃል በካልቪኒስቶች አስተምህሮ "ለኛ ለተመረጥነው እንጂ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም" በሚለው መቀየር አለበት እንደማለት ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በአዳም አለመታዘዝ ሞት ለሁሉ እንደደረሰ፣ በአንዱ በኢየሱስ መታዘዝ ሕይወት ለሁሉ እንደበዛ እንዲህ በማለት ይነግረናል። “በአንዱ ሰው አለመታዘዝ ብዙዎች ኃጢአተኞች እንደ ሆኑ፥ እንዲሁ ደግሞ በአንዱ መታዘዝ ብዙዎች ጻድቃን ይሆናሉ።” ሮሜ 5፥19 ከእኛ ከኃጢአተኞቹ የሚጠበቀው እግዚአብሔር በልጁ ሞት እንዳዳነን፣ ሕይወትም እንደሰጠን ማመንና መቀበል ብቻ እንጂ ከእኛ በሆነ ሥራ አይደለም። "ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ ይህም የእግዚአብሔር ስጦታ ነው እንጂ ከእናንተ አይደለም፤ ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም" ኤፌ 2:8—9 ነገር ግን ካልቪኒስቶች ሥራም፣ እምነትም፣ ማወቅም፣ መረዳትም፣ ማመንም ሳይጠበቅብን አስቀድሞ በእግዚአብሔር የተመረጥነውና የተለየነው እኛ ብቻ /predestination/ የተሰጠን ስንድን ለሲኦል የተዘጋጁት ደግሞ ያልተመረጡና አስቀድሞ የተፈረደባቸው ናቸው በማለት አምላካዊ ምህረቱን ለግላቸው በመውሰድ በሌሎች ላይ የፍርድ ቃል በድፍረት ሲናገሩ አይሰቀጥጣቸውም። ይህ አባባላቸው ኢየሱስ የተሰቀለው አስቀድሞ ለተመረጡና ለተወሰኑ ሰዎች እንጂ በእርሱ አምነው ለሚመጡ ለዓለሙ ሁሉ አይደለም ለማለት የሚረዳቸውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ጥቅስ ቦጭቀው ሲጠቀሙ ይህንን ይጠቅሳሉ። “አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፤ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፤ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው።” ሮሜ 8፥30 ይሄንን ቃል ሲያብራሩ እኛ /ካልቪኒስቶቹ/ ራሳቸውን ማለታቸው ነው። አስቀድሞ እንድንድን የተወሰነልን ነን። ከእንግዲህ የትኛውንም ኃጢአት ብንሰራ አንጠፋም። አስቀድሞ በተሰወነልን መሠረት የጠራን አንዴ ልጆቹ አደረገን። አፅደቆም በሰማይ አከበረን ይላሉ። ከዚህ ከእግዚአብሔር ቃል እውነት ፍፁም ተቃራኒ በሆነ ክህደት ውስጥ እንዲዘፈቁ ያደረጋቸው ሰይጣናዊ ትርጉም ሁለት መሰረታዊ ነገርን ከመሳት የመጣ ነው። እሱም፣ 1/ የእግዚአብሔር ሁሉን አዋቂነት ወደሰውኛ እውቀት ማውረድና 2/ የእግዚአብሔርን ምሕረትና የይቅርታ ሚዛን አለመረዳት ናቸው። እግዚአብሔር አምላክ የማያውቀውና የተሰወረበት ምን ምስጢር አለ? እግዚአብሔር ፍጥረትን ከፈጠረበትና ዓለማትን ከሚያሳልፍበት ሁሉን ቻይነቱ፣ የሉዓላዊነት ሥልጣን ውጪ የሆነና መሆን የሚቻለው አንዳችም ፍጥረት የለም። ይህም የእግዚአብሔር የሁሉን አዋቂነቱ /Omniscient/ እና የከሃሌ ኩሉነት /Omnipotent/ በራሱ አምላካዊ ባህርይው የሚገኝ ነው። ከዚህ ተነስተው እነዚህን ጥያቄዎች ብናነሳ የምናገኛቸው ትክክለኛ መልሶች ያሉት በእርሱ ዘንድ ብቻ ናቸው። የሰው ልጅ ከተፈጠረ ጀምሮ ስንት ሰው ተወልዷል፣ በፆታ ስንቱ ወንድ ስንቱስ ሴት ነው? ስንትስ ሰው ሞቷል፣ ስንት ሰውስ በሕይወት አለ? ስንቱ ገነት ገባ? ስንቱስ ሲዖል ወረደ? የሚሉትን ጥያቄዎች ብንጠይቅ ይህንን በትክክል የማወቅ ኃይሉ ያለው በእግዚአብሔር ዘንድ ብቻ ነው። በዚህም እግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂ አምላክ እንለዋለን። “ፍጥረታችንን እርሱ ያውቃልና፤ አቤቱ፥ እኛ አፈር እንደ ሆንን አስብ።” መዝ 103፥14 “የጠለቀውንና የተሠወረውን ይገልጣል፤ በጨለማ ያለውን ያውቃል፥ ብርሃንም ከእርሱ ጋር ነው።”ዳን 2፥22 የእግዚአብሔርን ሁሉን አዋቂነት ካልቪኒስቶቹ ራሳቸውን ከፀደቁት ጎራ ጨምረው እግዚአብሔር ዓለም ሳይፈጠር የፈረደባቸውንና በሰማይ ያፀደቃቸውን ስለሚያውቅ እኛን ከፀደቁት አድርጎ አስቀድሞ ወደፅድቁ ስለጨመረን ኩነኔ የሚባለው ነገር አይመለከተንም እያሉ በአስቀድሞ መወሰን/Predestination/ ውስጥ ራሳቸውን ያስቀምጣሉ። እግዚአብሔር ሁሉንም አዋቂ ነው ማለት ጄምስን ኮንኜዋለሁ፣ ገብረማርያምን ደግሞ አፅድቄዋለሁ ብሎ አስቀድሞ ውሳኔ የሰጠበት ሰው የለም። እንደዚያ አስቀድሞ ከተወሰነ የኢየሱስ ሰው መሆን ለምን አስፈለገ? ለምንስ ተሰቀለ? እምነትስ ምን ሊጠቅመን? እምነትንስ በሥራ መግለፅ ምን ሊጨምር? አስቀድሞ ለፅድቅ የተወሰነ ሰው ስለኃጢአት የሚከፈል ዋጋስ ለምን አስፈለገው?ቢከፈልለትም ሆነ ባይከፈልለት አስቀድሞ የተወሰነለትን ከመቀበል የሚያግደው ነገር ምን አለ?የሚሉ ጥያቄዎችን ብናነሳ መሆን የሚገባቸው ትእይንቶች/ ትርኢቶች/ እንጂ በመሰረታዊ የሰው ልጆች የመዳን መንገድ ላይ ትርጉም የሌላቸው ሆኖ እንዲታዩ የሚያደርግ ነው። ውሳኔው ቀድሞ ስለተሰጠ መዳኑ አይቀርበትም። ቀራንዮ ላይ የተፈፀመው ስቅለት አስቀድሞ የተነገረለትን ለማሳየት የተደረገ ትርኢት ነው ማለት ነው። ይህ የጆን ካልቪን ትምህርት አደገኛና የእግዚአብሔርን ፍፁም የሆነ ፍቅር በመሻር ሰው የሚፈረድበት በራሱ ምርጫ ሳይሆን ለሲዖል እሳት እንደማገዶ እንጨት አስቀድሞ አዘጋጅቶት የነበረውን ሰው ወደእሳት በመወርወር የሚደረግ ድምዳሜ እንጂ በማመኑ ወይም ባለማመኑ የሚደረግ ፍፃሜ አይደለም የሚል ክህደት ነው። ይህም እግዚአብሔር ሰው በምርጫው እንዲወስን ነባቢት፣ ለባዊትና ሕያዊት ነፍስ አልሰጠውም የሚል አምላክን እንደጨካኝ ገዢ የሚስል ሰይጣናዊ ትምህርት ነው። ዮሐንስ በራእዩ የጻፈልን ቃል፣ "ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ። እነሆ፥ በቶሎ እመጣለሁ፥ ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። አልፋና ዖሜጋ፥ ፊተኛውና ኋለኛው፥ መጀመሪያውና መጨረሻው እኔ ነኝ"ራእይ 22:11—13 የሚለው ቃል አስቀድሞ በተወሰነ ነገር ላይ ዝም ብሎ የተጻፈ እንጂ ፅድቅም፣ ርኩሰትም በማድረግ እንደሥራው የሚባል ክፍያ የለም እያሉን ነው ካልቪኒስቶቹ። የጆን ካልቪን ክሂዶተ እምነትና አስቀድሞ የመወሰን /predestination/ ስህተቶች በ5 ነጥቦች የተመደቡ ናቸው። 1/ Total Depravity/ የሰው ልጅ ከውድቀት በኋላ በጭራሽ ጻድቅ መሆን አይችልም የሚል ነው። ይህ የስህተት ትምህርት በአዳም ስህተት የተላለፈው ውድቀት የሰውን ልጅ ከነአካቴው የክፋት ሁሉ ባለቤት ነው ብሎ በሰው ጆሮ የሚያንቃጭል የሰይጣን ውንጀላ ሲሆን ሰው ሁሉ እኔን መስሏል የሚል ሰይጣናዊ ድምፀት ያለበት ክስ ነው። ከውድቀት በኋላ ለአዳም ልጆች ሁሉ የተላለፈውን ሞት የሚያስቀር የጽድቅ ሥራና ወደወጣበት ገነት የሚመልስ ማንነት በሥራው አያገኝም ማለት፣ ሰው በጎነት፣ ደግነት፣ በፈሪሃ እግዚአብሔር መኖር፣ የጽድቅ ሥራ መፈፀም አይችልም ማለት አይደለም። በመጽሐፍ ቅዱሳችን በዚህ ተግባር የተመሰከረላቸው ሰዎች ነበሩ። ለምሳሌ ሄኖክ፣ ኖኅ፣ አብርሃም፣ ሎጥ፣ ሳሙኤል፣ ኤልያስ፣ ኤልሳዕ፣ ዳንኤል፣ ሠለስቱ ደቂቅ ወዘተን መጥቀስ ይቻላል። ከዚህም የተነሳ የካልቪኒስቶች ስሁት ትምህርት በምድር ላይ የጽድቅ ስራን መሥራት በመቻልና በሥራ በመጽደቅ መካከል ያለውን ልዩነት አቅላቅለው እውነትን ደፍጥጠው ይክዳሉ። 2/ Unconditional Election /አስቀድሞ መመረጥ/ እግዚአብሔር በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የሚድኑትን አስቀድሞ መርጧቸዋል። ሲመርጣቸውም ምንም ዓይነት መስፈርትና መለኪያ አላደረገም። በቃ! ጻድቅ እንዲሆኑ ተፈጠሩ የሚል ነው። ኃጢአት፣ ሥርየት፣ እምነት፣ የሚባል ነገር ለፎርማሊቲ እንጂ ከተመረጡበት አያስቀራቸውም፣ አይጨምርላቸውም። የትኛውም ኃጢአት ከምርጫው አያስቀራቸውም የሚል ሲሆን እግዚአብሔር ለሲዖል መርጦ ያስቀራቸው አሉ በማለት ፍፁም ፍቅር የሆነውን የእግዚአብሔር ፍቅር ከሰው ልብ አውጥቶ የሚጥል ሰይጣናዊ ትምህርት ነው። ሲጀመር ሲዖል ለሰይጣንና ለመላእክቱ እንጂ ለሰው ልጅ አልተፈጠረም። ማቴ 25:41 3/ Limited Atonement የኢየሱስ ክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት የተከናወነው ለእኛ አስቀድሞ ለተመረጥነው ብቻ ነው የሚል አስተምህሮ ነው። ለዚህም እንዲረዳቸው ይህንን ጥቅስ ይጠቅሳሉ። “መልካም እረኛ እኔ ነኝ። መልካም እረኛ ነፍሱን ስለ በጎቹ ያኖራል።”ዮሐ 10፥11 ኢየሱስ ነፍሱን የሰጠው ለእኛ ለተመረጥነው በጎቹ ብቻ ነው የሚል ነው። ሲጀመር ካልቪኒስቶች በ/Limited Atonement/ /ለበጎቹ ብቻ/ በሚለው አስተምህሮአቸው ውስጥ ሁለት ነገር ይስታሉ። አንደኛው በማይቀየር ማዳኑ ውስጥ አስቀድሞ በጎቹ ከተመረጡ ኢየሱስ ለምን መሰቀል አስፈለገው? ዝም ብሎ እነሱን እየለየ ወደገነት ማስገባት ተገቢ በሆነ ነበር። ሲቀጥል ካልቪኒስቶች የስህተት ትምህርታቸውን ተርጉመው የኢየሱስ በጎች እኛ ነን ያሉት ራሳቸው እንጂ ካልቪኒስቶች ብቻ የተመረጡ ናቸው የሚል ማረጋገጫ በመጽሐፍም፣ በመላእክትም የተመሰከረ አይደለም። ደግሞ የተነገረን እውነት የተለየ ወንጌል የሰበከ የተረገመ ይሁን የሚል ነው። ገላ 1:8 እኛ ግን እንዲህ ብለን እናምናለን። “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና፤” ገላ 3፥26 በኢየሱስ አዳኝነት ያመነ፣ የተጠመቀና እምነቱን በሥራ የገለፀ አማኝ ሁሉ የእግዚአብሔር ልጅ ሆኗል ብለን እንናገራለን እንጂ ኢየሱስ የዓለም መድኃኒት የተባለበትን ሞትና ትንሣኤውን የካልቪኒስቶች ብቻ መድኃኒት ብለን ስለሁሉ የሞተበትን ምስጢር አንክድም። 4/ Irresistible Grace/ የካልቪኒስቶች ሌላው ስሁት አስተምሮአቸው አስቀድሞ በፀጋው የተጠሩት መቼም እንዳይጠፉ ሆነው የሚል ነው። ለዚህም ደጋፊ እንዲሆናቸው ዮሐንስ በወንጌሉ የጻፈውን የራሳቸው ብቸኛ ማረጋገጫቸው አድርገው ያቀርባሉ። “አብ የሚሰጠኝ ሁሉ ወደ እኔ ይመጣል፥ ወደ እኔም የሚመጣውን ከቶ ወደ ውጭ አላወጣውም” ዮሐ 6፥37 የሚገርመው ነገር በ30 ጠገራ ብር ኢየሱስን የሸጠው ይሁዳ ከተጠሩት ሐዋርያት መካከል አልነበረም ወይ? ሲባሉ ከሐዋርያነት የተደመረው ሽያጩን እስኪፈፅም እንጂ በዘላለማዊ ጥሪ ውስጥ አልነበረም ይላሉ። ለያህዌ ስም አጠራሩ ክብር ይግባውና ካልቪኒስቶች እግዚአብሔር በሰው ሕይወት ላይ ቁማር ይጫወታል፣ ያለምርጫህ ብትጠፋም ላንተ መጥፋት ግድ አይሰጠውም ወደሚል የአምላክን ባህርያዊ ፍቅር ወደማስካድ ይወርዳሉ። እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ስለሆነ የሚጠፉትንና የሚድኑትን ያውቃል ማለት የሚጠፉትና የሚድኑት እግዚአብሔር አስቀድሞ ስለወሰነባቸው ሳይሆን ሰዎች በሚያደርጉት የራሳቸው ውሳኔ የተነሳ መሆኑን አይቀበሉም። አዳም ከገነት ከመባረሩ በፊት ፍጻሜውን እግዚአብሔር ያውቅ ነበር ማለት አትብላ ያለውን እፀ በለስ በግድ እንዲበላ ስለወሰነበት ነበር ብሎ ማቅረብ አደገኛ ክህደት ነው። ይህም የሰው ልጅ በራሱ ማሰብና መወሰን የማይችልና አስቀድሞ በተገጠመለት የውሳኔ ሶፍትዌር የሚንቀሳቀስ ቁስ ነው እንደማለት ነው። የተወሰነብህን ትኖራለህ እንጂ በእውቀትም፣ በእምነትም የምትጨምረውና የምትቀንሰው ነገር የለም ማለት ነው። መጽሐፍ ቅዱሳችን የሚነግረን አንዴ በተሰጠ ምርጫ የለሽ ውሳኔ ሳይሆን የምናምነው አምላክ አውቀን በዚሁ በእምነታችን ፀንተን ስንቆይ እንደሆነ በግልፅ ይነግረናል። “የመጀመሪያ እምነታችንን እስከ መጨረሻው አጽንተን ብንጠብቅ፥ የክርስቶስ ተካፋዮች ሆነናልና፤” ዕብ 3፥14 እስራኤላውያን ከግብጽ ባርነት ከወጡ በኋላ ወተትና ማር ወደምታፈሰው ምድር ሳይገቡ በምድረ በዳ የቀሩት እግዚአብሔር በረሃ በልቷቸው እንዲቀሩ አስቀድሞ በወሰነባቸው ውሳኔ ሳይሆን ድንቅና ተአምራትን አድርጎ ከሰማይ መና፣ ቀን በደመና፣ ሌሊት በብርሃን ዓምድ እየመራቸው በነበረው አምላካቸው ላይ በማመፃቸው ነበር። " ዛሬ ድምጹን ብትሰሙት፥ በማስመረር እንደሆነ ልባችሁን እልከኛ አታድርጉ። ሰምተው ያስመረሩት እነማን ነበሩ? በሙሴ ተመርተው ከግብጽ የወጡ ሁሉ አይደሉምን? አርባ አመትም የተቆጣባቸው እነማን ነበሩ? ሬሳቸው በምድረ በዳ የወደቀ፥ ኃጢአትን ያደረጉት እነርሱ አይደሉምን? ካልታዘዙትም በቀር ወደ እረፍቱ እንዳይገቡ የማለባቸው እነማን ነበሩ? ባለማመናቸውም ጠንቅ ሊገቡ እንዳልተቻላቸው እናያለን" ዕብ3: 15—19 5/ PERSEVERANCE OF THE SAINTS ይህ ማለት አንዴ ከዳንክ ለዘላለም ድነሃል። በየትኛውም ኃጢአት ወይም በዓመጻ የሚጎድልህ ማንነት አይኖርህም ማለት ነው። Once saved, always saved ይሉሃል። በካልቪኒስቶቹ ዘንድ በዕብራውያን 10:36 ላይ የተመለከተው በእምነት ፀንቶ፣ ፈቃዱን እያደረጉ መኖር ነገር እርባና የለውም። “የእግዚአብሔርን ፈቃድ አድርጋችሁ የተሰጣችሁን የተስፋ ቃል እንድታገኙ መጽናት ያስፈልጋችኋልና።” ዕብ 10፥36 አንዴ የዳነ፣ ለዘላለም የማይጠፋ ስለሆነ በካልቪኒስቶች ዘንድ የሐዋርያው ጴጥሮስ ምክር ምንም አያስቀርበትም። “ስለዚህ፥ ወዳጆች ሆይ፥ ይህን እየጠበቃችሁ ያለ ነውርና ያለ ነቀፋ ሆናችሁ በሰላም በእርሱ እንድትገኙ ትጉ፥” 2ኛ ጴጥ 3፥14 የእግዚአብሔር ፈቃድ ብታደርግም፣ባታደርግም አንዴ ድነሃልና አትጠፋም፣ አትጨነቅ። ዮሐንስ በመልእክቱ የፃፈው ካልቪኒስቶችን አይመለከትም። ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው የሚለው ቃል ቢኖርም አንዴ ስለዳንክ ችግር የለውም ይሉሃል። “ኃጢአትን የሚያደርግ ከዲያብሎስ ነው፥ ዲያብሎስ ከመጀመሪያ ኃጢአትን ያደርጋልና።”1ኛ ዮሐ 3፥8 አንዴ ስለዳንክ በኃጢአት የተነሳ ከዲያብሎስ ብትሆንም አትጨነቅ፣ አትጠፋም እያሉ ለድፍረት ኃጢአት ያበረታቱሃል። ኃጢአት መስራት፣ አለመስራትህ የሚቀንስብህ ወይም የሚጨምርልህ ነገር የለም ይሉሃል። “ዓለሙም ምኞቱም ያልፋሉ፤ የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርግ ግን ለዘላለም ይኖራል።”1ኛ ዮሐ 2፥17 ፈቃዱን ብታደርግ ጥሩ ነው። ሳትፈፅመው ብትቀርም ችግር አያስከትልብህም፣ አትጨናነቅ፣ አንተ ለዘላለም የተመረጥህ ነህና። ዮሐንስ በእግዚአብሔር ዘላለማዊ ዓላማ ውስጥ ለመኖር ፈቃዱን መፈፀም ተገቢ ነው ያለው የራሱ ግምት በመሆኑ ካልቪን ያሻሻለውንና አንዴ የዳነ፣ ለዘላለም ዳነ የሚለውን ትምህርት ተከተል ይሉሃል ከሃዲዎቹ! ማጠቃለያ፣ ካልቪኒስቶቹ የሳቱት እውነት፣ የምሥራቹ ቃል የኢየሱስ ክርስቶስ ቃል እንጂ የጆን ካልቪን ትርጉም፣ አባባል፣ አገላለፅ ወይም የአስተምህሮ አቋም አለመሆኑን አለማወቃቸው ነው። ካልቪን በአንድ ወቅት የተለየ የወንጌል አስተምህሮ ተገልጾልኛል ብሎ የራሱን ትርጉም ይዞ የመጣ ሰው እንጂ የምሥራቹ ቃል ምንጭ ስላልሆነ ካልቪኒስት ነኝ ብሎ እሱን መከተል አደገኛ ስህተት ነው። ማንም አማኝ የወንጌልን ትምህርት በብዙ መንገድ፣ ከብዙ ሰዎች ሊሰማ ወይም ሊያገኝ ይችላል። ያ ማለት ግን የወንጌል እውነት እሱ ከሰማበት ቦታ ብቻ ይገኛል ማለት አይደለም። የየትኛውም ትምህርት ማረጋገጫና መመዘኛ መንፈስ ቅዱስና የምሥራቹ ቃል እውነት መሆኑን አለማወቃቸው ነው። ሉተር፣ ካልቪን፣ ዝዊንግሊ፣ ኤራስመስ፣ ኖክ፣ ዊክሊፍ፣ ኸስ፣ ሜላንክቶን ወይም ቲንዳል የእውነት ቃል ምንጭ ወይም የመጨረሻው የእውነት ማረጋገጫ ሊሆኑ እንደማይችሉ አለመረዳታቸው ነው። ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌል ይልቅ ግለሰቦቹ በሰጡት ትንታኔ ላይ በመመስረት ለማመን መሞከራቸው ነው ካልቪኒስት ሆነው ለመኖር የወሰኑት። እኛ ግን የተሰቀለልንና ከሞት ያዳነን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታይና ደቀመዛሙርት እንጂ የአጵሎስ ወይም የጳውሎስ አይደለንም። ከሰማይ በታች እንድንበት ዘንድ የተሰጠን ስም ማነው? ከሰማይ በታች ሊድኑበት ለወደዱና ወደእርሱ ለመጡ በሙሉ የሚያድነው ስም ኢየሱስ ብቻ ነው። ከሰማይ በታች የተሰጠ የካልቪን አስተምህሮ፣ ለካልቪኒስቶች ሊኖር ይችላል። እኛን ክርስቶሳውያንን አይመለከትም። የካልቪን የሚባል አስተምህሮም፣ መምህርም የለንም።