ባልተዘጋጀችበትና በሚመጣው ለውጥ የሚደርስባት ጉዳት ከባድ ነው።
(ክፍል አምስት)በክፍል አራት ጽሁፋችን በፍላጎት መጠን ማደግ፤ ለስኬት በሚደረገው ሩጫ፤ በኢንዱስትሪው ትንግርታዊ ግስጋሴና ለአእምሮ ልሽቀት የመጋለጥ አደጋ መካከል በሚኖረው ዕለታዊ የኑሮ መስተጋብር የተነሳ የአውሮፓውያን ሃይማኖቶች የማሽቆልቆል፤ የትርፍ ጊዜ ጉዳይ የማድረግ፤ ከዚያም አልፎ ተርፎ በሥራ ብቻ እንጂ በስብከት ልምምድ ምንም ጠብ የሚል ነገር እንደሌለ በመቁጠር ወደ ክሂዶተ እግዚአብሔር የመሄድ ነገር መጠኑ እንደጨመረ እንደሄደና ይህም ክስተት በኢትዮጵያችንም እየታየ መገኘቱን ለማመልከት ሞክረን ነበር። ከዚህም የተነሳ አብያተ ክርስቲያናት በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብዙ መሥራት እንደሚጠበቅባት ነገር ግን ተግዳሮቶችን ለመከላከል የተወሰደ የጅማሮ ፍንጭ አለመኖሩን በማመልከት ለጉዳት የመጋለጣችንን አይቀሬነት በመጠቆም ጥቂት ለማሳየት ሞክረን ነበር። በዚህ ክፍል ደግሞ ቀጣዩን ነጥብ እንመለከታለን።
3/ የኑሮ ምቾት፤ ድሎት የተነሳ በሚከተለው ስግብግብነትና የምኞት ከፍታ በሚያስከትለው የአእምሮ ድንዛዜ የተነሳ የሚመጣው የእምነት ጉድለት፤
በመስከረም ወር ኒውዮርክ ላይ ተደርጎ በነበረው የተመድ
ጉባዔ ላይ ከዓለም የመጨረሻው ደሃ ፕሬዚዳንት እንደሆኑ የሚታወቁት የኡሩጓይ/Uruguay/ ፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ ባደረጉት ታሪካዊ
ንግግር እንዲህ ብለው ነበር።
«ድሃ ማነው? የሚለውን ጥያቄ በኔ አፈታት ሲተረጎም ለመኖር ሲል ብዙ የሚፈልግ አስተሳሰብ ያለው ነው» ሲሉ መናገራቸው
የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር። ለምን? እንዲህ እንዳሉም በሰጡት ማብራሪያ «ብዙ የሚፈልጉ ሰዎች ያንን ለማሟላት የኅሊና እረፍት
የላቸውም፤ ከዚህም የተነሳ በሕይወታቸው ሙሉ እንደሮጡና እንደደከሙ ይኖራሉ፤ በቃኝን አያውቁም። ከእነዚህ የበለጠ የመኖር እርካታ
የሌላቸው ደሃ የትም የለም» በማለት ጉባዔውን አስደምመውት ነበር። የፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ ንግግር በኢትዮጵያውያን ምሳሌ በአጭር
ቃል ሲቀመጥ «ከተራበ ለጠገበ አዝናለሁ» እን,ደማለት መሆኑ ነው። የ78 ዓመቱ ጆሴ ሙጂካ የኡሩጓይ ፕሬዚዳንት ይሁኑ እንጂ የሚተዳደሩት
የገጠር መሬታቸውን በትራክተራቸው እያረሱ የሚተክሉትን ስኳር ድንችና ለውዝ ለገበያ እያቀረቡ መሆናቸው በዓለማችን ላይ ካሉ የሀገር
መሪዎች ልዩ ያደርጋቸዋል። በቅርቡ ለአንድ ቴሌቪዥን በሰጡት የቃለ መጠይቅ ምላሽ ላይ «የኑሮ ምቾትህ በጣም የተደላደለ ከሆነና
ከሌላው ሕዝብ የተለህ እንደሆነ ማሰብ ከጀመርህ፤ በጣም ስግብግብና ስለምትኖርበት ዓለም ማሰብ የማይችል የደነዘዘ አእምሮ ተሸካሚ
ትሆናለህ» በማለት መናገራቸው ብዙዎችን አስገርሟል። ሲወጡና ሲገቡ ቀይ ምንጣፍ የሚረግጡ መሪዎች፤ ተራ ሰው የነበሩና አጋጣሚዎች
ከፍታ ላይ ያስቀመጣቸው ሰዎች በአብዛኛው ስግብግቦች ስለሆኑ ስለወጡበት ማኅበረሰብ ደንታ የላቸውም። ምክንያቱም ሰዎቹ ማሰብ ስለማይፈልጉ
ሳይሆን የሚያስቡበትን አእምሮ የኑሮው ምቾትና የአእምሮ ድንዛዜ እንዳያስቡ ዘግቶ ስለሚይዛቸው ነው» ሲሉ ፕሬዚዳንቱ አክለው ተናግረው
ነበር።
አባባላቸው ሙሉ በሙሉ ተቀባይነት ያለው ነው። ይህ ሁኔታ በአውሮፓውያኑና በአጠቃላይ በምዕራባውያኑ ዘንድ ስር በመስደዱ
የተነሳ የቅንጦት/Luxury/ ኑሯቸው መጠን የለሽ ወደመሆን በመሸጋገሩ የነበረውን አዲስ ነገር አውጥቶ በመጣል ለበለጠ አዲስ ነገር
ራስን በማስገዛት አዲስ ቤት፤ አዲስ መኪና፤ አዲስ የቤት እቃ፤ አዲስ አዲስ ሁሉን አዲስ በማድረግ አባዜ አእምሮአቸው ደንዝዟል።
ስግብግብነትና በቃኝ የማለትን ገደብ የማለፉ አስተሳሰብ የሚጎትተው እንከን ለተራበ ያለማዘንን፤ ለሰዎች ችግር አለመድረስ ብቻ ሳይሆን
ደንታ ቢስ መሆንን፤ ተካፍሎ መብላት የሚለው ብሂል የሰነፎች መፈክር እንደሆነ ማሰብን የመሳሰሉ ችግሮችን ያስከትላል። ምንም እንኳን
የተስተካከለ ኑሮን መኖር ጥፋት ባይሆንም በቃኝን አለማወቅ ግን ትልቅ በደል ነው። በተለይም ደግሞ ክርስቲያኖች ኑሮዬ ይበቃኛል
ማለትን ካልተማሩ እግዚአብሔር እነሱን ለቅንጦት እንደፈጠራቸው ማሰብን መለማመዳቸው አይቀርም።
ይህንን በተመለከተ ሐዋርያው ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ ይለናል። «ይህን ስል ስለ ጉድለት አልልም፤ የምኖርበት ኑሮ
ይበቃኛል ማለትን ተምሬአለሁና። መዋረድንም አውቃለሁ መብዛትንም አውቃለሁ፤ በእያንዳንዱ ነገር በነገርም ሁሉ መጥገብንና መራብንም
መብዛትንና መጉደልን ተምሬአለሁ። ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ። ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለ ተካፈላችሁ መልካም
አደረጋችሁ» ፊልጵ 4፤10-14
የጠገቡና በዚህ ጥጋብ የተነሳ አእምሮአቸው የደነዘዘ፤
የሌሎችን ጥጋብ በማየት ለማግኘት የሚራወጡ፤ ትግላቸው ሁሉ የሥጋን ፍላጎት መሠረት ያደረጉ ሰዎች በሌሎች ችግር የመካፈል ፍላጎት የላቸውም። እምነት እንዳላቸው ቢያስቡም የእምነታቸው ከፊል ምኞታቸውን በማሳካት ላይ የታጠረ
ነው። በአውሮፓ ይህንን መሰሉ ቅንጦትና መጠን የሌለው ምቾት በአእምሮ ላይ በመሰልጠኑ የተነሳ አብያተ ክርስቲያናቱ አማኞችን ከማስተናገድ
ተላቀው ወደመዝናኛና ሆቴልነት፤ የገበያ አዳራሽነትና ጋራዥነት ለመቀየር ተገደዋል። በክርስትና ስም ከሚጠራው ተከታይ ውስጥ ቤተ
ክርስቲያን በመሄድ በዕለተ እሁድ የጸሎት ፕሮግራም ላይ የሚገኘው ተሳታፊ ቁጥር በጣም አሽቆልቁሏል። በእንግሊዝ 1,4% ፤ በፈረንሳይ
0,9%፤ በጀርመን 1,2% ብቻ እንደሚገኙ ክርስቲያን ፖስት በ2011 ዓ/ም ባደረገው ጥናት የችግሩን ጥልቀት ለማሳየት ሞክሯል።
የሥነ ምግባር ልሽቀት፤ ስግብግብነት፤ የግብረ ገብነት ድቀት መነሻው የሰው ልጅ የተፈጠረበትን ምክንያት ካለማወቅና ባወቀው ላይ
ለመኖር ካለመፈለግ የሚመነጭ ውስጣዊና ውጫዊ ግፊት የተነሳ የሚመጣ ነው። ምዕራባዊው ኑሮ አሁን አሁን መሥፈሪያውን የሞላ/ Saturate/
ያደረገ ይመስላል። እድገቱን የጨረሰ የወይን ግንድ እንደገና ተገርዞ
ካልታደሰ በስተቀር ፍሬ ከማፍራት መለየቱና መድረቁ የቀን ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር የማብቃቱ ጉዳይ ሳይታለም የተፈታ ነው።
ኢትዮጵያችንን ስንቃኝ የእድገት መሥፈሪያዋ ሞልቷን ማለት አንችልም። ይሁን እንጂ እንደሀገር ለመቀጠል መስራትና ማደግ
የግድ የማለቱን ያህል ዕለታዊ የኑሮ መስተጋብራችንን የሚሻማ የሥራና የሩጫ ሕይወት ወደመለማመዱ መግባታችን አይቀሬ ነው። ከዚህም
የተነሳ ዘመኑን የዋጀ የሃይማኖት አስተምህሮና የተግባር ተሞክሮ በአማኞቻችን ውስጥ ማሳደግ ካልቻልን ጥያቄን በሚያጭሩ፤ እምነትን
በሚሸረሽሩና ምላሽ በሚጠይቁ ዙሪያ ገባ ጥያቄዎች መወጠራችን አይቀርም። ትውልዱን አስፈራርተው፤ በማያረካ ምክንያት ውስጥ አእምሮን
በመደበቅ ማሳመን አይቻልም። ወደዚህ ምድር የመጣበትን ምክንያትና የመኖር ልኬታን የማይዘነጋ ልቡናን እንዲጨብጥ የሚያስችል መንፈሳዊ
የቃል ወተትን መጋት፤ እንደአዋቂ ማሰብ የሚችልበትን የእምነት ተስፋ እንዲጠባበቅ ካላደረግነው ቤተ ክርስቲያን የታሪክ ትምህርት
ቤት ወደመሆን መቀየሯ አይቀርም። ኑሮዬ ይበቃኛልን ማሰብ የተወ ትውልድ ሌብነትን፤ ዝርፊያን፤ ሙስናን፤ ዝሙትን፤አስገድዶ መድፈርን፤
ግድያንና ልዩ ልዩ ወንጀልን መላመዱ አይቀርም። እውነተኛ እምነት ከዚህ ሁሉ አስከፊ ማንነት ይከላከላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ አሁን ያለንበት መንፈስ በቆየ መልካም ባህልና ከቤተሰብእ በተወረሰ ልምድ ብዙ
የሚያሳስብ የላሸቀ የትውልድ ውድቀት ባይታይም ፍንጮች መኖራቸውን መካድ አይቻልም። ከሁሉም ሃይማኖቶች ዘንድ ጉድለቶቹ የትውልዱን
ድክመት እያመላከቱ ናቸው። ገንዘብንና ጥቅምን መሠረት ያደረጉ አብያተ ክርስቲያናት መስፋፋታቸው፤ በአስነዋሪ ስነ ምግባራቸው የተነሳ
በሰማይም በምድርም ከፍ ያለው የእግዚአብሔር ስም እንዲሰደብ ምክንያት
መሆናቸውን እያየን ነው። ዝሙት፤ ስርቆት፤ ስግብግብነት፤ ዘረኝነት፤ አድልዎ፤ ፍትህ ማጣመም፤ በደልና ብቀላ እየነገሠ ነው። ጥላቻና
ቂም እየተዘራና እያደገ ይገኛል። ዘረፋና ጉቦ የብዙዎችን ዓይን አሳውሯል። «ማሰነ» ከሚለው ግእዛዊ ግስ የተጨለፈችው «ሙስና»
የተሰኘችው ዘመናዊ ቃል የሚዲያ የእርግማን ጸሎት መሆን ከጀመረችም ሰነባብታለች። በዚህ ላይ የአብያተ ክርስቲያናቱ ስፍራ የት ነው?
ብለን እንጠይቃለን።
አብያተ ክርስቲያናቱ እንኳን ለሌላው ብርሃን ሊሆኑ ቀርተው ራሳቸው በችግሩ ማስነዋል። ስግብግብነት፤ ለድሎትና ምቾት
የመራወጥ አባዜ ተበራክቷል። ገንዘብን ብቻ ማዕከል ያደረገ በእግዚአብሔር ስም የመሸቀጥ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። ዝሙትና ገንዘብ
መለያቸው ሆኗል። ከወንጌላውያኑ ጀምሮ እስከ ኦርቶዶክሳውያኑ ድረስ የዚህ በሽታ ምልክት ስር ሰዷል። የዚህ ዓይነቱ ፈሪሃ እግዚአብሔር የመጥፋቱ ነገር ለኑሮ ስኬት
የሚራወጠውን ህዝብ አእምሮ አይበርዘውም ማለት አይቻልም።
ከዚህም የተነሳ ሃይማኖት ለእግዚአብሔር አምልኮ የምንሰራበት የማንነታችን ቤት እንደሆነ የማሰቡ ነገር ይቀርና ክህዶተ
እግዚአብሔር የሚስፋፋበት፤ አእምሮአችንን ከተስፋ ማጣት የተነሳ ደንዝዞ ሥጋንና ሥጋን ብቻ ማዕከል ያደረገ አስተሳሰብ ተሸካሚዎች
እንዳንሆን ያስፈራል። ይህ የእምነት ጉድለት ደግሞ ከእግዚአብሔር ጥበቃና ከለላ ውጭ ሊያደርገን ይችላል። ሐዋርያው ጳውሎስ «ኑሮዬ ይበቃኛል አለማለት ወደጥፋት ያደርሳል» ማለቱን ማስተዋል ተገቢ ነው።
አውሮፓውያኑንም ሲጀምራቸው እንደዚሁ በትንሽ በትንሹ ነበር። ምቾትና ምኞት የወለደው ስግብግብነት ሩጫቸውን በእጦት ቀውስ እየመታው ይገኛል። በእነሱ የደረሰ በእኛም ይህ እንዳይሆንብን
ከፈለግን መሥራት የሚገባን ዛሬ ነው። የቀነሰብንን የሰው ቁጥር ለማወቅ ስንፈልግ ያለንን እንዳናጣ እኛው ራሳችን ለመቆጠር የሚያበቃ
ማንነትን እንዳለን ቆም ብለን እናስተውል። ምድራዊው ቁጥር የሰማያዊውን መዝገብ ቁጥር አይተካምና።
ከፕሬዚዳንት ጆሴ ሙጂካ አብነታዊ ቃል ጠቅሰን ጽሁፋችንን እናጠቃልል። «እኔ የተወለድኩት ከሕዝቡ ነው። የኖርኩትና ያደኩት ሕዝቡ መሃከል ነው። ያሳደገኝ ሕዝብ ሲሾመኝ ስራልኝ እንጂ የተሻለ ኑሮ ኑርልኝ የሚል ውክልና አልሰጠኝም። የቻልኩትን ሁሉ ሕዝቡና ለምርጫው የፈቀደኝ እግዚአብሔር የሰጠኝን ችሎታ ሁሉ ሰርቼ ይበቃሃል ሲሉኝ ሕዝቡ መሐከል ተመልሼ እኖራለሁ። በሕይወቴ ሙሉ ኑሮዬ ይበቃኛልን ስለተማርኩ ወደሥልጣን ስመጣ ባዶዬን ነበርኩ፤ ስሄድም ባዶዬን ነው፤ ሳልመጣም፤ ከመጣሁም በኋላ ይሁን ስሄድ ድንች ተክዬ በላቤ ወዝ ብቻ ሰርቼ እኖራለሁ»